ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት
“በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”—ዮሐንስ 14:6
1. ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ትእዛዝ ሰጠ? የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ትእዛዝ በመታዘዛቸውስ ምን ውጤት ተገኝቷል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን “አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19) ባለፉት አሥር ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ከሦስት ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች አምላክን እንዲያውቁና ፈቃዱን ለማድረግ ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ረድተዋል። እነዚህን ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት በመቻላችን ምንኛ ደስተኞች ነን!—ያዕቆብ 4:8
2. ብዙ አዳዲስ ተጠማቂዎች ቢኖሩም ምን ሁኔታ ይታያል?
2 ይሁን እንጂ በአንዳንድ አገሮች ብዙ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት የተጠመቁ ቢሆንም የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከዚያ ጋር የሚመጣጠን ጭማሪ ሳያሳይ ቀርቷል። እርግጥ በየዓመቱ የሚሞቱትን ወደ 1 በመቶ የሚጠጉ አስፋፊዎች ቁጥር ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ይሁንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው አስፋፊዎች በአንዳንድ ምክንያቶች ወደኋላ ብለዋል። ለምን? በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ሰዎች ወደ ይሖዋ የሚቀርቡት እንዴት እንደሆነና አንዳንዶች የእምነት ጎዳናን ትተው እንዲወጡ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ምን እንደሆኑ እንመረምራለን።
የምንሰብክበት ዓላማ
3. (ሀ) ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የተሰጠው ተልእኮ በራእይ 14:6 ላይ የተገለጸው መልአክ ካለው ተልእኮ ጋር አንድ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመቀስቀስ ውጤታማ ሆኖ የተገኘው ዘዴ የትኛው ነው? ሆኖም ምን ችግር አለ?
3 በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ ‘መንግሥቱ ወንጌል’ የሚናገረውን ‘እውነተኛ እውቀት’ የማሰራጨት ተልእኮ አላቸው። (ዳንኤል 12:4፤ ማቴዎስ 24:14) ተልእኳቸው “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል [ካ]ለው” መልአክ ተልእኮ ጋር አንድ ነው። (ራእይ 14:6) ዓለማዊ ነገሮችን በማሳደድ በተጠመደው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የማወቅ ፍላጎት እንዲያድርባቸውና ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ለመርዳት የሚያስችለው ውጤታማ መንገድ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት የሚገልጸውን ተስፋ መንገር ነው። ይህ ስህተት ባይሆንም ገነት ለመግባት ሲሉ ብቻ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር የሚተባበሩ ሰዎች ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብ መንገድ ላይ በጽናት ለመመላለስ የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ አይኖራቸውም።—ማቴዎስ 7:13, 14
4. ኢየሱስና በሰማያት መካከል የሚበርረው መልአክ በተናገሩት መሠረት የስብከት ሥራችን ዓላማ ምንድን ነው?
4 ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) በሰማይ መካከል እየበረረ “የዘላለም ወንጌል” የሚያውጀው መልአክ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት” በማለት ይናገራል። (ራእይ 14:7) በመሆኑም ምሥራቹን የምንሰብክበት ዋነኛው ዓላማ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት ነው።
በይሖዋ ሥራ ውስጥ ያለን ድርሻ
5. የምንሠራው የራሳችንን ሳይሆን የይሖዋን ሥራ መሆኑን የሚያሳዩት ጳውሎስና ኢየሱስ የተናገሯቸው የትኞቹ ሐሳቦች ናቸው?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ ለመሰል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲጽፍ ስለ ‘ማስታረቅ አገልግሎት’ የተናገረ ሲሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት አምላክ ራሱን ከሰዎች ጋር እንደሚያስታርቅ ተናግሯል። ጳውሎስ ‘አምላክ በእኛ አማካኝነት እንደሚማልድና’ ‘የክርስቶስ ተተኪዎች በመሆን ከአምላክ ጋር ታረቁ ብለን እንደምንለምን’ ተናግሯል። እንዴት ደስ የሚል ሐሳብ ነው! ‘የክርስቶስ ተተኪ አምባሳደሮችም’ ሆንን ምድራዊ ተስፋ ያለን መልእክተኞች የምንሠራው ሥራ የራሳችን ሳይሆን የይሖዋ መሆኑን በፍጹም መዘንጋት የለብንም። (2 ቆሮንቶስ 5:18-20 የ1980 ትርጉም) ሰዎችን ወደ እርሱ በመሳብ ወደ ክርስቶስ የሚመጡትን የሚያስተምረው አምላክ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።”—ዮሐንስ 6:44, 45
6. ይሖዋ ብሔራትን የሚያናውጥ መቅድም እርምጃ የወሰደው እንዴት ነው? ከዚሁ ጎን ለጎን በአምልኮ “ቤቱ” ደህንነት እያገኙ ያሉት እነማን ናቸው?
6 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ ሰዎችን ወደ ራሱ የሚስበውና ‘የእምነትን በር’ የሚከፍትላቸው እንዴት ነው? (ሥራ 14:27 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) አንደኛው ቁልፍ መንገድ ምሥክሮቹ የእሱን የመዳን መልእክትና በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ የሚወስደውን የቅጣት እርምጃ እንዲያውጁ በማድረግ ነው። (ኢሳይያስ 43:12፤ 61:1, 2) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወነው ይህ እወጃ በቅርቡ ለሚወሰደው የፍርድ እርምጃ መቅድም በመሆን ብሔራትን እያናወጠ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በአምላክ ዓይን “ውድ” የሆኑ ሰዎች ከዚህ ሥርዓት እየወጡ በእውነተኛ አምልኮ “ቤቱ” ውስጥ ደህንነትን በማግኘት ላይ ናቸው። በዚህ መንገድ ይሖዋ ሐጌ የመዘገባቸውን “እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፣ በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል” የሚሉትን ትንቢታዊ ቃላት በማስፈጸም ላይ ይገኛል።—ሐጌ 2:6, 7 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፣ ራእይ 7:9, 15
7. ይሖዋ የሰዎችን ልብ የሚከፍተውና ግለሰቦችን ወደ ራሱና ወደ ልጁ የሚስበው እንዴት ነው?
7 ይሖዋ የእነዚህን ‘ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡ’ አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው ሰዎች ልብ በመክፈት ምሥክሮቹ ‘የሚናገሩትን በትኩረት እንዲያዳምጡ’ ያደርጋል። (ሐጌ 2:7 ጁዊሽ ፐብሊኬሽን ሶሳይቲ፤ ሥራ 16:14) ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ አንዳንድ ጊዜ ምሥክሮቹን ለእርዳታ ወደ እርሱ ወደሚጮኹ ቅን ሰዎች ለመምራት በመላእክቱ ይጠቀማል። (ሥራ 8:26-31) ሰዎች አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ስላዘጋጀላቸው ድንቅ ነገሮች በሚማሩበት ወቅት ይሖዋ ያሳያቸው ፍቅር ወደ እርሱ ይስባቸዋል። (1 ዮሐንስ 4:9, 10) አዎን፣ አምላክ ሰዎችን ወደ ራሱና ወደ ልጁ የሚስበው ‘በፍቅራዊ ደግነቱ’ ወይም ‘በታማኝ ፍቅሩ’ አማካኝነት ነው።—ኤርምያስ 31:3፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።
ይሖዋ ወደ እርሱ የሚስበው እነማንን ነው?
8. ይሖዋ ወደ ራሱ የሚስበው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው?
8 ይሖዋ ወደ ራሱና ወደ ልጁ የሚስበው የሚፈልጉትን ነው። (ሥራ 17:27) ይህ ደግሞ በሕዝበ ክርስትናም ሆነ በመላው ዓለም ውስጥ ‘በሚደረገው ርኩሰት ሁሉ የሚያዝኑና የሚተክዙ ሰዎችን’ ይጨምራል። (ሕዝቅኤል 9:4) ‘ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ’ ናቸው። (ማቴዎስ 5:3 NW) በእርግጥም ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩት “የምድር ትሑታን” እነሱ ናቸው።—ሶፎንያስ 2:3
9. ሰዎች ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው’ መሆናቸውን ይሖዋ ሊያውቅ የሚችለው እንዴት ነው? እነዚህንስ ወደ ራሱ የሚስበው እንዴት ነው?
9 ይሖዋ የአንድን ሰው ልብ ማንበብ ይችላል። ንጉሥ ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞን “እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፣ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና . . . ብትፈልገው ታገኘዋለህ” ብሎት ነበር። (1 ዜና መዋዕል 28:9) ይሖዋ የአንድን ግለሰብ የልብ ሁኔታና መንፈስ ወይም ጎላ ብሎ የሚታየውን ዝንባሌውን መሠረት በማድረግ ለኃጢአት ይቅርታ ለተደረጉት መለኮታዊ ዝግጅቶች እንዲሁም ጽድቅ በሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለሚኖረው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ምላሽ ይሰጥ ወይም ትሰጥ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ይችላል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይሖዋ ምሥክሮቹ እንዲሰብኩትና እንዲያስተምሩት በሰጣቸው በቃሉ አማካኝነት ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸውን በሙሉ’ ወደ ራሱና ወደ ልጁ በመሳብ ላይ ሲሆን እነዚህም ‘አማኞች ይሆናሉ።’—ሥራ 13:48 NW
10. ይሖዋ አንዳንዶችን ወደ ራሱ ሲስብ ሌሎችን ግን መተዉ ዕድል አስቀድሞ መወሰኑን የማያሳየው እንዴት ነው?
10 ይሖዋ አንዳንዶችን ወደ ራሱ ሲስብ ሌሎችን ግን መተዉ ዕድል አስቀድሞ እንደ ተወሰነ የሚያሳይ ነውን? በጭራሽ! አምላክ ሰዎችን ወደ ራሱ መሳቡ የተመካው በራሳቸው በሰዎቹ ምኞትና ፍላጎት ላይ ነው። ነፃ ምርጫቸውን ያከብርላቸዋል። ይሖዋ ከዛሬ 3,000 ዓመታት ገደማ በፊት በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን ካቀረበው ምርጫ ጋር የሚመሳሰል ምርጫ በዚህ ዘመን ላሉ የምድር ነዋሪዎችም አቅርቧል:- “ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፣ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ። . . . በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ . . . እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም [“እርሱን ሙጥኝ ትል፣” NW] ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።”—ዘዳግም 30:15-20
11. እስራኤላውያን ሕይወትን እንደመረጡ የሚያሳዩት እንዴት ነበር?
11 እስራኤላውያን ‘ይሖዋን በመውደድ፣ ቃሉን በመስማትና እርሱን ሙጥኝ በማለት’ ሕይወትን መምረጥ እንደነበረባቸው ልብ በል። እነዚህ ቃላት በተነገሩበት ጊዜ እስራኤላውያን ገና የተስፋይቱን ምድር አልወረሱም ነበር። በሞዓብ ምድር ላይ በመስፈር የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ከንዓን ለመግባት በዝግጅት ላይ ነበሩ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስለሚገቡባት ‘ወተትና ማር ስለምታፈስሰው ሰፊና መልካም አገር’ ማሰባቸው የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም የሕልማቸው እውን መሆን የተመካው ግን ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር፣ ቃሉን በመስማታቸውና እሱን ሙጥኝ በማለታቸው ላይ ነበር። (ዘጸአት 3:8) ሙሴ እንዲህ በማለት ይህንን ጉዳይ ግልጽ አድርጎታል:- “ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትፈጽሙና እርሱን ብትወዱት ብትታዘዙለትም፣ ሕግጋቱን ሁሉ ብትጠብቁ ትበለጽጋላችሁ፤ የብዙ ሕዝብ መንግሥትም ትሆናላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔርም በዚያች በምትወርሱአት ምድር ይባርካችኋል።”—ዘዳግም 30:16 የ1980 ትርጉም፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
12. ከእስራኤላውያን ምሳሌ ስለ ስብከትና ስለ ማስተማር ሥራችን ምን ልንማር እንችላለን?
12 ከላይ ያለው ሐሳብ በዚህ የፍጻሜ ዘመን ስለምንሠራው የስብከትና የማስተማር ሥራ የሚያስገነዝበን ነገር ሊኖር አይገባምን? ወደፊት ገነት ስለምትሆነው ምድር እናስባለን፤ በአገልግሎታችንም ላይ ስለዚህ አንስተን እንናገራለን። ሆኖም እኛም ሆንን ደቀ መዛሙርት የምናደርጋቸው ሰዎች አምላክን የምናገለግለው ለግል ጥቅማችን ስንል ብቻ ከሆነ ማናችንም ብንሆን የተስፋውን ፍጻሜ አናይም። እኛም ሆንን የምናስተምራቸው ሰዎች ልክ እንደ እስራኤላውያን ‘ይሖዋን መውደድን፣ ቃሉን መስማትንና እርሱን ሙጥኝ ማለትን’ መማር አለብን። አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ጊዜ ይህን የምናስታውስ ከሆነ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ በማድረጉ ሥራ የእሱ ተባባሪዎች እንሆናለን።
የአምላክ የሥራ ባልደረቦች
13, 14. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ 3:5-9 መሠረት የአምላክ የሥራ ባልደረባ የምንሆነው እንዴት ነው? (ለ) ለሚገኘው ጭማሪ ሁሉ ክብር ሊሰጠው የሚገባው ማን ነው? ለምንስ?
13 ጳውሎስ ከአምላክ ጋር ተባብሮ መሥራትን አንድን እርሻ ከማልማት ጋር አያይዞ ገልጾታል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ። እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፣ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና።”—1 ቆሮንቶስ 3:5-9
14 የአምላክ የሥራ ባልደረቦች እንደመሆናችን መጠን የታመንን በመሆን ‘የመንግሥቱን ቃል’ በሰዎች ልብ ውስጥ በመትከል፣ ፍላጎት ለሚያሳዩት ደግሞ ዝግጅት የተደረገባቸው ተመላልሶ መጠየቆች በማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመምራት ማጠጣት ይኖርብናል። አፈሩ ማለትም ልባቸው ጥሩ ከሆነ ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዘር ፍሬያማ ተክል ሆኖ እንዲበቅል በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል። (ማቴዎስ 13:19, 23) ግለሰቡን ወደ ራሱና ወደ ልጁ ይስበዋል። ስለዚህ በመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ላይ የሚገኝ ማንኛውም እድገት ይሖዋ በሰዎች ልብ ውስጥ የሚሠራው ሥራ ማለትም የእውነት ዘር እንዲበቅል የማድረጉና እንዲህ ያሉትን ሰዎች ወደ ራሱና ወደ ልጁ የመሳቡ ውጤት ነው።
ዘላቂነት ያለው የግንባታ ሥራ
15. ሌሎች እምነታቸውን እንዲያጠነክሩ እንዴት መርዳት እንደምንችል ለማሳየት ጳውሎስ የትኛውን ምሳሌ ተጠቅሟል?
15 ጭማሪ መገኘቱ ቢያስደስተንም ሰዎች ይሖዋን በመውደድ፣ ቃሉን በመስማትና እርሱን ሙጥኝ ብለው ሲቀጥሉ ማየት እንፈልጋለን። አንዳንዶች ሲቀዘቅዙና ወደኋላ ሲሉ ስንመለከት እናዝናለን። ይህን ለማስቀረት ልናደርገው የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን? ጳውሎስ በሌላ ምሳሌ ላይ ሌሎች እምነታቸውን እንዲያጠነክሩ እንዴት መርዳት እንደምንችል ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፣ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፣ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፣ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።”—1 ቆሮንቶስ 3:11-13
16. (ሀ) ጳውሎስ የተጠቀማቸው ሁለቱ ምሳሌዎች ዓላማቸው የሚለያየው እንዴት ነው? (ለ) የግንባታ ሥራችን አጥጋቢ እንዳይሆንና እሳትን እንዳይቋቋም የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?
16 ጳውሎስ ስለ እርሻ በተናገረው ምሳሌ መሠረት እድገት የሚመጣው በጥንቃቄ በመትከል፣ አዘውትሮ በማጠጣትና ከአምላክ በሚገኝ በረከት ነው። ሌላው የሐዋርያው ምሳሌ የግንባታ ሥራቸውን የመጨረሻ ውጤት በተመለከተ ክርስቲያን አገልጋዮች ያለባቸውን ኃላፊነት ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ነው። ጥራት ባላቸው የግንባታ ቁሳቁሶች ተጠቅሞ ጠንካራ መሠረት ላይ ገንብቷልን? ጳውሎስ “እያንዳንዱ . . . እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 3:10) በገነት ውስጥ ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለአንድ ሰው በመንገር ፍላጎቱን ከቀሰቀስን በኋላ መሠረታዊ የሆነውን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት በማስተማር ላይ አተኩረን ሰውየው የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ ማድረግ ያለበትን ነገር ብቻ እናጎላለን? ትምህርታችን ‘በገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ከፈለግህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ ወደ ስብሰባዎች መሄድና በስብከቱ ሥራ መካፈል አለብህ’ የሚል ብቻ ይሆን? እንዲያ ከሆነ የሰውየውን እምነት በጠንካራ መሠረት ላይ እየገነባን አይደለንም፤ የምንገነባውም ነገር የስደት እሳትን ሊቋቋም አይችልም፤ ወይም ጊዜው ቢረዝም አይዘልቅ ይሆናል። ለጥቂት ዓመታት ይሖዋን በማገልገል በገነት ውስጥ በሕይወት መኖር ይቻላል በሚል ተስፋ ብቻ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ ለማድረግ መሞከር ‘በእንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ’ ከመገንባት ጋር የሚመሳሰል ነው።
ለአምላክና ለክርስቶስ ፍቅር እንዲኖራቸው ማድረግ
17, 18. (ሀ) የአንድ ሰው እምነት ጽኑ እንዲሆን ከተፈለገ ምን ነገር የግድ አስፈላጊ ነው? (ለ) ክርስቶስ በልባቸው ውስጥ እንዲያድር ሰዎችን ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
17 እምነት ጽኑ እንዲሆን ከተፈለገ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከይሖዋ አምላክ ጋር በሚኖር የግል ዝምድና ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ፍጹማን ባለመሆናችን ይህን የመሰለውን ሰላማዊ ግንኙነት ከአምላክ ጋር ልንመሠርት የምንችለው በልጁ አማካኝነት ብቻ ነው። (ሮሜ 5:10) ኢየሱስ “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሎ መናገሩን አስታውስ። ሌሎች እምነታቸውን እንዲገነቡ ለመርዳት “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፣ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” ይህ ምንን ይጨምራል?—ዮሐንስ 14:6፤ 1 ቆሮንቶስ 3:11
18 ክርስቶስን መሠረት አድርጎ መገንባት ማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው የኢየሱስን ቤዛነት፣ የጉባኤ ራስነቱን፣ አፍቃሪ ሊቀ ካህንነቱንና በመግዛት ላይ ያለ ንጉሥ መሆኑን በሚገባ በማወቅ ጥልቅ ፍቅር እንዲያዳብርበት በሚረዳው መንገድ ማስተማር ማለት ነው። (ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 20:28፤ ቆላስይስ 1:18-20፤ ዕብራውያን 4:14-16) ኢየሱስ እውን ሆኖ እንዲታያቸው በማድረግ በልባቸው ውስጥ እንዲያድር ማድረግ ማለት ነው። ስለ እነርሱ የምናቀርበው ጸሎት ጳውሎስ በኤፌሶን ስለነበሩ ወንድሞች ካቀረበው ልመና ጋር ሊመሳሰል ይገባል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ . . . ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር . . . የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ።”—ኤፌሶን 3:14-17
19. በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ልብ ውስጥ የክርስቶስን ፍቅር የመገንባታችን ውጤት ምን መሆን አለበት? ሆኖም ምን መማር አለባቸው?
19 ተማሪዎቻችን ክርስቶስን ከልብ እንዲወድዱት በሚያደርግ መንገድ የምንገነባ ከሆነ ይህ ለይሖዋ አምላክ ፍቅር እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። ኢየሱስ ያሳየው ፍቅር፣ ስሜትና ርኅራኄ የይሖዋን ባሕርያት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 11:28-30፤ ማርቆስ 6:30-34፤ ዮሐንስ 15:13, 14፤ ቆላስይስ 1:15፤ ዕብራውያን 1:3) ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን ሲያውቁና ሲያፈቅሩ ይሖዋን ለማወቅና ለመውደድ ይችላሉ።a (1 ዮሐንስ 4:14, 16, 19) ክርስቶስ ለሰዎች ካደረጋቸው ነገሮች በስተጀርባ ያለው ይሖዋ በመሆኑ ልናመሰግነው፣ ልናወድሰውና “የመድኃኒታችን አምላክ” መሆኑን በማሰብ ልናመልከው እንደሚገባ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ማስተማር አለብን።—መዝሙር 68:19, 20፤ ኢሳይያስ 12:2-5፤ ዮሐንስ 3:16፤ 5:19
20. (ሀ) ሰዎች ወደ አምላክና ወደ ልጁ እንዲቀርቡ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምን ይሆናል?
20 የአምላክ የሥራ ባልደረቦች እንደመሆናችን በሰዎች ልብ ውስጥ ፍቅርና እምነት እንዲያድግ በማድረግ ወደ አምላክና ወደ ልጁ እንዲቀርቡ እንርዳቸው። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ለእነሱ እውን ይሆንላቸዋል። (ዮሐንስ 7:28) በክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ለመመሥረት ከመቻላቸውም በላይ አምላክን ሊወድዱትና እርሱን ሙጥኝ ሊሉ ይችላሉ። የይሖዋ አስደናቂ ተስፋዎች እሱ በወሰነው ጊዜ የሚፈጸሙ መሆናቸውን በማመን በፍቅር ተገፋፍተው የሚያቀርቡት አገልግሎት በጊዜ የተገደበ እንዲሆን አይፈቅዱም። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:24-26፤ ዕብራውያን 11:6) ይሁን እንጂ ሌሎች እምነት፣ ተስፋና ፍቅር እንዲያዳብሩ ስንረዳ የራሳችንንም እምነት ጠንከር ያሉ ማዕበሎችን ለመቋቋም የሚችል ጠንካራ መርከብ አድርገን መገንባት አለብን። ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ ኢየሱስና በእሱም አማካኝነት ስለ አባቱ ስለ ይሖዋ የተሻለ እውቀት ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለው መጽሐፍ ግሩም እገዛ ያደርግልናል።
ለክለሳ ያህል
◻ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት እንዲያድርባቸው የምናደርገው እንዴት ነው? ሆኖም ምን አደጋ አለ?
◻ ይሖዋ ወደ ራሱና ወደ ልጁ የሚስበው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው?
◻ የእስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት በምን ላይ የተመካ ነበር? ከዚህስ ምን ልንማር እንችላለን?
◻ ሰዎች ወደ ይሖዋና ወደ ልጁ እንዲሳቡ በመርዳት ረገድ ምን ድርሻ አለን?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በገነት ውስጥ ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለሰዎች ብናካፍልም ዋነኛው ዓላማችን ግን ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት ነው
[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የምናደርጋቸው ተመላልሶ መጠየቆች በደንብ ዝግጀት የተደረገባቸው ከሆኑ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ