የጥናት ርዕስ 23
“ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ”!
“በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።”—ቆላ. 2:8
መዝሙር 96 የአምላክ መጽሐፍ ውድ ሀብት ነው
የትምህርቱ ዓላማa
1. ቆላስይስ 2:4, 8 እንደሚገልጸው ሰይጣን አስተሳሰባችንን ለመማረክ የሚጥረው እንዴት ነው?
ሰይጣን ለይሖዋ ጀርባችንን እንድንሰጥ ይፈልጋል። ይህን ግቡን ለማሳካት ሲል ደግሞ አስተሳሰባችንን ለማዛባት ይኸውም አእምሯችንን በመማረክ እሱን እንድንታዘዘው ለማድረግ ይሞክራል። ሊማርኩን የሚችሉ ነገሮችን በማቅረብ የእሱን አመለካከት እንድንቀበል ሊያግባባን አሊያም ደግሞ ተታልለን እሱን እንድንከተል ሊያደርገን ይጥራል።—ቆላስይስ 2:4, 8ን አንብብ።
2-3. (ሀ) በቆላስይስ 2:8 ላይ ለሚገኘው ማስጠንቀቂያ ትኩረት ልንሰጥ የሚገባው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
2 የሰይጣን ማታለያዎች ያን ያህል ሊያሳስቡን ይገባል? አዎን! ጳውሎስ በቆላስይስ 2:8 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ የጻፈው ለማያምኑ ሰዎች እንዳልሆነ እናስታውስ። ደብዳቤውን የጻፈው በመንፈስ ቅዱስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች ነው። (ቆላ. 1:2, 5) በዚያ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በሰይጣን የመታለል አደጋ ተደቅኖባቸው ነበር፤ እኛም የምንገኘው ከዚያ በባሰ አደገኛ ዘመን ውስጥ ነው። (1 ቆሮ. 10:12) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰይጣን ወደ ምድር የተወረወረ ሲሆን የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ለማሳት ቆርጦ ተነስቷል። (ራእይ 12:9, 12, 17) በተጨማሪም የምንኖረው ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች “በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ” በሚሄዱበት ዘመን ውስጥ ነው።—2 ጢሞ. 3:1, 13
3 ሰይጣን “ከንቱ ማታለያ” በመጠቀም አስተሳሰባችንን ለማዛባት የሚጥረው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን። ከሚጠቀምባቸው “መሠሪ ዘዴዎች” ወይም “ሴራዎች” መካከል ሦስቱን እንመረምራለን። (ኤፌ. 6:11 ግርጌ) በቀጣዩ ርዕስ ላይ ደግሞ የሰይጣን ዘዴዎች በአስተሳሰባችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረው ከሆነ ይህን እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል እናያለን። በመጀመሪያ ግን እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ሰይጣን እንዴት እንዳታለላቸውና ከዚህ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።
በጣዖት አምልኮ ለመካፈል ተፈተኑ
4-6. ዘዳግም 11:10-15 እንደሚገልጸው እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ ከግብርና ጋር በተያያዘ ምን ለውጥ ማድረግ ነበረባቸው?
4 ሰይጣን በዘዴ ተጠቅሞ እስራኤላውያንን በጣዖት አምልኮ እንዲካፈሉ ፈትኗቸዋል። የተጠቀመበት ዘዴ ምንድን ነው? እስራኤላውያንን የፈተናቸው የዕለት እንጀራ የማግኘት ፍላጎታቸውን በመጠቀም ነው። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ እህል የሚያመርቱበትን መንገድ መቀየር አስፈልጓቸው ነበር። በግብፅ እያሉ ከአባይ ወንዝ ላይ ውኃ በመጥለፍ እርሻቸውን በመስኖ ያጠጡ ነበር። በተስፋይቱ ምድር ግን ገበሬዎች እርሻቸውን የሚያለሙት ከትልቅ ወንዝ ውኃ በመጥለፍ ሳይሆን ወቅቱን ጠብቆ የሚጥለውን ዝናብና መሬቱ ላይ የሚያርፈውን ጠል በመጠቀም ነበር። (ዘዳግም 11:10-15ን አንብብ፤ ኢሳ. 18:4, 5) በመሆኑም እስራኤላውያን አዲስ የግብርና ዘዴ መማር ነበረባቸው። ደግሞም ስለ ግብርና እውቀት የነበራቸው አብዛኞቹ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ስለሞቱ ይህ ቀላል አልነበረም።
5 ይሖዋ በተስፋይቱ ምድር ሁኔታዎች እንደሚቀየሩ ለሕዝቡ ነግሯቸዋል። ከዚያም “ልባችሁ እንዳይታለልና ዞር ብላችሁ ሌሎች አማልክትን እንዳታመልኩ እንዲሁም እንዳትሰግዱላቸው ተጠንቀቁ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጣቸው፤ ይህ ሐሳብ ከግብርና ጋር ምንም ግንኙነት ያለው አይመስል ይሆናል። (ዘዳ. 11:16, 17) ይሖዋ አዲስ የግብርና ዘዴ ስለመማር እየተናገረ ባለበት ወቅት የሐሰት አማልክትን ስለማምለክ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ለምንድን ነው?
6 እስራኤላውያን በአካባቢው የተለመዱ የግብርና ዘዴዎችን በዙሪያቸው ካሉት አረማውያን ለመማር እንደሚፈተኑ ይሖዋ ያውቅ ነበር። ደግሞም በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች በግብርና ረገድ ከእስራኤላውያን የበለጠ ተሞክሮ እንደሚኖራቸውና የአምላክ ሕዝብ አንዳንድ ጠቃሚ ዘዴዎችን ከእነሱ ሊማር እንደሚችል የታወቀ ነው፤ ይህ ግን አደጋ ነበረው። ከነዓናውያን ገበሬዎች ከባአል ጋር በተያያዘ የሚያምኑባቸው ነገሮች በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድሩ ነበር። ባአል የሰማይ ባለቤት እንደሆነና ዝናብን እንደሚሰጥ ይታመን ነበር። ይሖዋ፣ ሕዝቡ እንዲህ ባሉ የተሳሳቱ እምነቶች እንዲታለል አልፈለገም። ሆኖም በተደጋጋሚ እንደታየው እስራኤላውያን በባአል አምልኮ ለመካፈል መርጠዋል። (ዘኁ. 25:3, 5፤ መሳ. 2:13፤ 1 ነገ. 18:18) ሰይጣን፣ እስራኤላውያንን ማርኮ ሊወስድ የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ሰይጣን እስራኤላውያንን ማርኮ ለመውሰድ የተጠቀመባቸው ሦስት ዘዴዎች
7. እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ እምነታቸው የተፈተነው እንዴት ነው?
7 ሰይጣን እስራኤላውያንን ያታለለበት የመጀመሪያው ዘዴ ከተፈጥሯዊ ፍላጎታቸው ጋር የተያያዘ ነው፤ ማንኛውም ገበሬ ዝናብ ማግኘት ይፈልጋል። በተስፋይቱ ምድር ደግሞ ከሚያዝያ መጨረሻ እስከ መስከረም ባሉት ወራት ዝናብ አይጥልም ማለት ይቻላል። እስራኤላውያን ለሕይወት የሚያስፈልጋቸውን ምግብና የተትረፈረፈ ምርት ማግኘት እንዲችሉ ከጥቅምት ወር ጀምሮ የሚጥለው ዝናብ ያስፈልጋቸው ነበር። እስራኤላውያን ጥሩ ምርት ለማግኘት በዙሪያቸው ያሉ አረማውያንን ልማዶች መከተል እንደሚኖርባቸው ተሰማቸው፤ ይህ ግን የሰይጣን ማታለያ ነበር። በዙሪያቸው የነበሩት ብሔራት፣ አማልክታቸው ዝናብ እንዲሰጧቸው አንዳንድ የአምልኮ ሥርዓቶችን መፈጸም እንዳለባቸው ያምኑ ነበር። በይሖዋ ላይ እምነት ያጡ አንዳንድ እስራኤላውያንም የድርቁ ወቅት እንዳይራዘም ማድረግ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ይህ እንደሆነ ስለተሰማቸው የሐሰት አምላክ ለሆነው ለባአል በሚቀርቡ የአምልኮ ሥርዓቶች መካፈል ጀመሩ።
8. ሰይጣን የተጠቀመበት ሁለተኛው ዘዴ ምንድን ነው? አብራራ።
8 ሰይጣን እስራኤላውያንን ለመማረክ የተጠቀመበት ሁለተኛው ዘዴ ለብልግና ምኞቶች እንዲሸነፉ ማድረግ ነው። አረማዊ የሆኑት ብሔራት ለአማልክታቸው የሚያቀርቡት አምልኮ አስጸያፊ በሆኑ የብልግና ድርጊቶች መካፈልን የሚጨምር ነበር። አስነዋሪ በሆነው በዚህ የአምልኮ ሥርዓት ሴቶችና ወንዶች የቤተ መቅደስ ዝሙት አዳሪዎች ይካፈሉ ነበር። ግብረ ሰዶማዊነትና ሌሎች የብልግና ድርጊቶች በሕዝቡ ዘንድ የማይወገዙ ከመሆንም አልፈው በስፋት ተቀባይነት አግኝተው ነበር! (ዘዳ. 23:17, 18፤ 1 ነገ. 14:24) አማልክቱ እንደዚህ ያሉ የአምልኮ ሥርዓቶች ሲቀርቡላቸው ምድሪቱን ምርታማ ለማድረግ እንደሚነሳሱ ሕዝቡ ያምን ነበር። በርካታ እስራኤላውያን፣ ብልግና የሚፈጸምባቸው የእነዚህ ብሔራት የአምልኮ ሥርዓቶች ስለማረኳቸው የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀመሩ። ሰይጣን ማርኮ ወስዷቸዋል ሊባል ይችላል።
9. ሆሴዕ 2:16, 17 እንደሚያሳየው ሰይጣን፣ እስራኤላውያን ለይሖዋ ያላቸው አመለካከት እንዲዛባ ያደረገው እንዴት ነው?
9 ሰይጣን የተጠቀመበት ሦስተኛው ዘዴ ደግሞ እስራኤላውያን ስለ ይሖዋ ያላቸው አመለካከት እንዲዛባ ማድረግ ነው። በነቢዩ ኤርምያስ ዘመን የነበሩ ሐሰተኛ ነቢያት፣ ሕዝቡ “በባአል የተነሳ” የይሖዋን ስም እንዲረሳ ለማድረግ እንደሞከሩ ይሖዋ ተናግሯል። (ኤር. 23:27) እስራኤላውያን በይሖዋ ስም መጠቀማቸውን አቁመው ስሙን፣ ባአል (“ባለቤት” ወይም “ጌታ” የሚል ትርጉም አለው) በሚለው ስም የተኩት ይመስላል። በዚህ የተነሳ እስራኤላውያን በይሖዋና በባአል መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ስላልታያቸው የባአልን አምልኮ ከይሖዋ አምልኮ ጋር መቀላቀል ቀላል ሆኖላቸዋል።—ሆሴዕ 2:16, 17ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።
ሰይጣን በዛሬው ጊዜ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች
10. ሰይጣን በዛሬው ጊዜ የትኞቹን ዘዴዎች ይጠቀማል?
10 ሰይጣን በዛሬው ጊዜ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎችም ከጥንቱ ጋር ተመሳሳይ ናቸው። የሰው ልጆችን ተፈጥሯዊ ፍላጎት በመጠቀም፣ የፆታ ብልግና ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ እንዲሁም ስለ ይሖዋ ያላቸውን አመለካከት በማዛባት ሰዎችን ማርኮ ለመውሰድ ይሞክራል። እስቲ በመጀመሪያ ሰይጣን፣ ሰዎች ስለ ይሖዋ ያላቸውን አመለካከት የሚያዛባው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
11. ሰይጣን፣ ሰዎች ስለ ይሖዋ ያላቸው አመለካከት እንዲዛባ ያደረገው እንዴት ነው?
11 ሰይጣን፣ ሰዎች ስለ ይሖዋ ያላቸው አመለካከት እንዲዛባ ያደርጋል። የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች የሐሰት ትምህርቶችን ማስፋፋት ጀመሩ። (ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰ. 2:3) እነዚህ ከሃዲዎች፣ እሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆነው የይሖዋ ማንነት እንዲሰወር አደረጉ። ለምሳሌ፣ ከሚያዘጋጇቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ መለኮታዊውን ስም በማውጣት “ጌታ” እንደሚሉት ባሉ መጠሪያዎች ተኩት። በአምላክ የግል ስም ፋንታ “ጌታ” የሚለውን መጠሪያ መጠቀማቸው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ ሰው፣ በይሖዋና በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተጠቀሱት ሌሎች “ጌቶች” መካከል ያለው ልዩነት እንዲምታታበት ያደርጋል። (1 ቆሮ. 8:5) ለይሖዋም ሆነ ለኢየሱስ “ጌታ” የሚለውን መጠሪያ መጠቀማቸው ደግሞ ይሖዋና ልጁ ያላቸው የተለያየ ማንነትና ቦታ እንዳይታወቅ አድርጓል። (ዮሐ. 17:3) ይህ የፈጠረው ግራ መጋባት፣ ሥላሴ የተባለው በአምላክ ቃል ውስጥ የማይገኝ መሠረተ ትምህርት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዚህም የተነሳ ብዙዎች አምላክን ሚስጥራዊና ሊታወቅ የማይችል አካል እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ይህ እንዴት ያለ አስከፊ ውሸት ነው!—ሥራ 17:27
12. የሐሰት ሃይማኖቶች ምን እንዲስፋፋ አድርገዋል? ይህስ በሮም 1:28-31 ላይ እንደተገለጸው ምን ውጤት አስከትሏል?
12 ሰይጣን፣ ሰዎች ለብልግና ምኞቶች እንዲሸነፉ ለማድረግ ይሞክራል። በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ሰይጣን፣ የፆታ ብልግና ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ በሐሰት አምልኮ ተጠቅሟል። ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል። የሐሰት ሃይማኖቶች፣ የፆታ ብልግናን በቸልታ ማለፋቸው ሳያንስ እንዲህ ያለው ምግባር ተቀባይነት እንዲያገኝም አድርገዋል። በመሆኑም አምላክን እንደሚያገለግሉ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች፣ በግልጽ የተቀመጡትን የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አይከተሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሐሰት ሃይማኖቶች አካሄድ ያስከተለውን ውጤት ገልጿል። (ሮም 1:28-31ን አንብብ።) ‘መደረግ የማይገባው ነገር’ የሚለው አገላለጽ ግብረ ሰዶምን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት የፆታ ብልግና ያካትታል። (ሮም 1:24-27, 32፤ ራእይ 2:20) እኛ ግን ግልጽ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በጥብቅ መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው!
13. ሰይጣን የሚጠቀምበት ሌላ ዘዴ ምንድን ነው?
13 ሰይጣን፣ ተፈጥሯዊ ፍላጎታችንን ተጠቅሞ ሊማርከን ይሞክራል። ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት የሚያስችለንን ትምህርት ለመቅሰም መፈለግ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። (1 ጢሞ. 5:8) ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለውን ትምህርት የምናገኘው ትምህርት ቤት ገብተን በትጋት በማጥናት ነው። ይሁንና ይህን ስናደርግ ጠንቃቆች መሆን አለብን። በብዙ አገሮች የሚሰጠው ትምህርት፣ ጠቃሚ የሆኑ ክህሎቶችን ብቻ ሳይሆን ዓለማዊ ፍልስፍናዎችንም ያካተተ ነው። ተማሪዎች የአምላክን ሕልውና እንዲጠራጠሩ እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲያጡ የሚያደርግ ትምህርት ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም የሕይወትን አመጣጥ በተመለከተ ሁሉም የተማሩ ሰዎች የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ እንደሚቀበሉ ይነገራቸዋል። (ሮም 1:21-23) እንዲህ ያሉት ትምህርቶች ‘የአምላክን ጥበብ’ የሚጻረሩ ናቸው።—1 ቆሮ. 1:19-21፤ 3:18-20
14. ዓለማዊ ፍልስፍና ምንን ያበረታታል?
14 ዓለማዊ ፍልስፍና፣ የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ችላ እንዲባሉ የሚያደርግ አሊያም ከእነዚህ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭ ነው። የአምላክን መንፈስ ፍሬ ከማፍራት ይልቅ ‘የሥጋ ሥራዎችን’ እንድንከተል ያበረታታናል። (ገላ. 5:19-23) ሰዎች ኩሩና ትዕቢተኛ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ ይህም “ራሳቸውን የሚወዱ” ሰዎች እንዲበዙ አድርጓል። (2 ጢሞ. 3:2-4) እነዚህ ባሕርያት፣ ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ከሚጠብቀው የገርነትና የትሕትና መንፈስ ፍጹም ተቃራኒ ናቸው። (2 ሳሙ. 22:28) ዩኒቨርሲቲ ገብተው የተማሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች አእምሯቸው በአምላክ አስተሳሰብ ሳይሆን በሰብዓዊ አስተሳሰብ ተቀርጿል። ይህ አካሄድ የሚያስከትለውን አደጋ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እስቲ እንመልከት።
15-16. አንዲት እህት ካጋጠማት ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?
15 ከ15 ዓመት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፈች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መከታተል ስላለው አደጋ አንብቤያለሁ እንዲሁም ሰምቻለሁ፤ ሆኖም ለእነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት አልሰጠሁም። ምክሩ ለእኔ እንደማይሠራ ተሰምቶኝ ነበር።” ታዲያ ይህች እህት ምን ችግር አጋጠማት? እንዲህ ስትል በግልጽ ተናግራለች፦ “ትምህርቱ ብዙ ጊዜና ጥረት ስለሚጠይቅ እንደ በፊቱ ረዘም ያለ ጊዜ መድቤ ወደ ይሖዋ መጸለይ አልቻልኩም፤ እንዲሁም በጣም ስለሚደክመኝ በአገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ውይይት ማድረግም ሆነ ለስብሰባዎች በሚገባ መዘጋጀት እየከበደኝ መጣ። ደስ የሚለው ግን፣ ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል የማደርገው ጥረት ከይሖዋ ጋር ያለኝን ግንኙነት እያበላሸው እንደሆነ ስገነዘብ ትምህርቱን ለማቆም ወሰንኩ። ያደረግኩትም ይህንኑ ነው።”
16 ይህች እህት ከፍተኛ ትምህርት መከታተሏ በአስተሳሰቧ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? እንዲህ ብላለች፦ “የተከታተልኩት ትምህርት ሌሎችን በተለይም ወንድሞቼንና እህቶቼን እንድነቅፍ፣ ከእነሱ ብዙ እንድጠብቅ እንዲሁም እንድርቃቸው እንዳደረገኝ ሳስበው ያሳፍረኛል። ይህን አስተሳሰብ ለማስወገድ ረጅም ጊዜ ወስዶብኛል። ይህ ሁኔታ፣ ሰማያዊው አባታችን በድርጅቱ በኩል የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ማለት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ አስተምሮኛል። ይሖዋ፣ እኔ ራሴን ከማውቀው በላይ ያውቀኛል። ምክሩን ሰምቼ ቢሆን ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር!”
17. (ሀ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
17 እኛም የሰይጣን ዓለም የሚያስፋፋው “ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ” ማርኮ እንዳይወስደን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በሰይጣን ዘዴዎች እንዳንታለል ሁልጊዜ እንጠንቀቅ። (1 ቆሮ. 3:18፤ 2 ቆሮ. 2:11) ሰይጣን ስለ ይሖዋ ያለንን አመለካከት እንዲያዛባው ፈጽሞ አንፍቀድ። ላቅ ያሉትን የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንከተል። በሰይጣን ተታልለን የይሖዋን ምክር ችላ እንዳንል እንጠንቀቅ። ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳደረገብን ብንገነዘብስ? የአምላክ ቃል እንደ “ምሽግ” ያሉ አስተሳሰቦችንና ልማዶችን እንኳ ለማስወገድ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ የሚቀጥለው ርዕስ ያብራራል።—2 ቆሮ. 10:4, 5
መዝሙር 49 የይሖዋን ልብ ማስደሰት
a ሰይጣን ሰዎችን በማታለል ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። ብዙዎችን ማርኮ በቁጥጥሩ ሥር ያዋላቸው ቢሆንም ነፃነት እንዳላቸው እንዲሰማቸው በማድረግ አታሏቸዋል። ሰይጣን ሰዎችን ለማታለል የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ከከነአናውያን ጋር የተቀራረቡ እስራኤላውያን በባአል አምልኮና በፆታ ብልግና እንዲካፈሉ ግብዣ ሲቀርብላቸው።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ግብረ ሰዶማዊነት ተቀባይነት እንዳለው የሚገልጽ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ማስታወቂያ።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ዩኒቨርሲቲ የገባች ወጣት እህት። ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ ሊያስወግዱ እንደሚችሉ ፕሮፌሰሯ ስትናገር እሷና አብረዋት የሚማሩት ልጆች በተመስጦ እያዳመጡ ነው። በኋላ ላይ ጉባኤ ስትመጣ ፊቷ ላይ የመሰላቸትና የነቃፊነት ስሜት ይነበባል።