የተሟላ መረጃ አለህ?
“እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።”—ምሳሌ 18:13
1, 2. (ሀ) የትኛውን አስፈላጊ ችሎታ ማዳበር አለብን? ለምንስ? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ያገኘነውን መረጃ ገምግመን ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ የመድረስ ችሎታ ማዳበር ያስፈልገናል። (ምሳሌ 3:21-23፤ 8:4, 5) እንዲህ ያለውን ችሎታ ካላዳበርን ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም አስተሳሰባችንን በቀላሉ ሊያዛቡት ይችላሉ። (ኤፌ. 5:6፤ ቆላ. 2:8) ደግሞም ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ መድረስ የምንችለው የተሟላ መረጃ ካለን ብቻ ነው። ምሳሌ 18:13 እንደሚለው “እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።”
2 የተሟላ መረጃ አግኝተን ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ እንቅፋት የሚሆኑብንን አንዳንድ ነገሮች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን። በተጨማሪም ያገኘነውን መረጃ የመገምገም ችሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱንን ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምሳሌዎች እንመለከታለን።
“ቃልን ሁሉ” አትመን
3. በምሳሌ 14:15 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።)
3 በዛሬው ጊዜ ሰዎች በመረጃ ጎርፍ ተጥለቅልቀዋል ሊባል ይችላል። የኢንተርኔት ድረ ገጾች፣ ቴሌቪዥንና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን ስፍር ቁጥር የሌላቸው መረጃዎችን ያቀርባሉ። በተጨማሪም ብዙዎች ከጓደኞቻቸውና ከሚያውቋቸው ሰዎች ኢ-ሜይሎች፣ የጽሑፍ መልእክቶች እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎች በየጊዜው ይደርሷቸዋል። እርግጥ ነው፣ መልእክቶቹን የሚልኩት ሰዎች ይህን የሚያደርጉት መረጃ ለማስተላለፍ አስበው ብቻ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሆን ብለው የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያሰራጩና መረጃዎችን አዛብተው የሚያቀርቡ ሰዎችም አሉ። በመሆኑም የሚደርሱንን መረጃዎች በጥንቃቄ መገምገም ይኖርብናል። ታዲያ ይህን ለማድረግ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ይረዳናል? ምሳሌ 14:15 “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል።
4. ፊልጵስዩስ 4:8, 9 የምናነባቸውን ነገሮች ለመምረጥ የሚረዳን እንዴት ነው? ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (“የተሟላ መረጃ ለማግኘት የሚረዱን አንዳንድ ዝግጅቶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
4 ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ አስተማማኝ የሆነ መረጃ ማግኘት ያስፈልገናል። በመሆኑም የምናነባቸውን ነገሮች በጥንቃቄ መምረጥ አለብን። (ፊልጵስዩስ 4:8, 9ን አንብብ።) ተአማኒ ያልሆኑ የኢንተርኔት የዜና ድረ ገጾችን በመቃኘት ወይም በኢ-ሜይል አሊያም በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት የተላኩልንን ያልተረጋገጡ ዘገባዎች በማንበብ ጊዜያችንን ልናባክን አይገባም። በተለይ ደግሞ የከሃዲዎችን ሐሳብ የሚያስፋፉ ድረ ገጾችን ከመመልከት መቆጠብ ይኖርብናል። የከሃዲዎች ዋነኛ ዓላማ የአምላክን ሕዝቦች እምነት ማዳከምና እውነታውን ማዛባት ነው። አስተማማኝ ያልሆነ መረጃ፣ የተሳሳተ ውሳኔ ወደማድረግ ይመራል። የተሳሳተ መረጃ ምን ያህል መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም።—1 ጢሞ. 6:20, 21
5. እስራኤላውያን ምን መጥፎ ወሬ ሰሙ? ይህስ ምን አስከተለ?
5 የተሳሳተ መረጃን ማመን አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። በሙሴ ዘመን፣ ተስፋይቱን ምድር እንዲቃኙ ከተላኩት አሥራ ሁለት ሰላዮች መካከል አሥሩ መጥፎ ወሬ ይዘው መምጣታቸው ምን ውጤት እንዳስከተለ እንመልከት። (ዘኁ. 13:25-33) እስራኤላውያን እነዚህ ሰላዮች ያመጡትን የተጋነነና አስደንጋጭ የሆነ ዜና ሲሰሙ ወኔ ከዳቸው። (ዘኁ. 14:1-4) ሕዝቡ በፍርሃት የራዱት ለምንድን ነው? እስራኤላውያን ከአሥራ ሁለቱ ሰላዮች መካከል አሥሩ መጥፎ ወሬ ማምጣታቸውን ሲያዩ፣ ወሬው እውነት መሆን አለበት ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። ሕዝቡ፣ እምነት የሚጣልባቸው ኢያሱና ካሌብ ያመጡትን መልካም ዜና ለመስማት አሻፈረን አሉ። (ዘኁ. 14:6-10) እስራኤላውያን እውነታውን ከመስማትና በይሖዋ ከመታመን ይልቅ የተሳሳተውን ዜና ለማመን መረጡ። ይህ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!
6. የይሖዋን ሕዝብ በተመለከተ አስደንጋጭ የሆኑ ወሬዎችን ብንሰማ ልንደናገጥ የማይገባው ለምንድን ነው?
6 በተለይ ደግሞ የይሖዋን ሕዝብ ከሚመለከቱ ዘገባዎች ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ሰይጣን የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከሳሽ መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ። (ራእይ 12:10) ኢየሱስም ቢሆን፣ ተቃዋሚዎች “ክፉውን ሁሉ በውሸት [እንደሚያስወሩብን]” ነግሮናል። (ማቴ. 5:11) በመሆኑም የይሖዋን ሕዝብ በተመለከተ አስደንጋጭ የሆኑ ወሬዎችን ብንሰማ አንደናገጥም።
7. ኢ-ሜይሎችን እና የጽሑፍ መልእክቶችን ከመላካችን በፊት ልናስብባቸው የሚገቡ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
7 ለጓደኞችህና ለምታውቃቸው ሰዎች ኢ-ሜይሎችን እና የጽሑፍ መልእክቶችን መላክ ያስደስትሃል? አዲስ የወጣ ዜና ስታይ ወይም ለየት ያለ ተሞክሮ ስትሰማ ወሬውን ማንም ሳይቀድምህ ለመናገር ትጓጓለህ? ከሆነ እንዲህ ያለውን ወሬ ለሌሎች ከመላክህ በፊት ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘የምልከው መረጃ እውነት ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ? ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃስ አለኝ?’ እርግጠኛ ያልሆንክበትን መረጃ የምትልክ ከሆነ ሳይታወቅህ ለወንድሞችህ የተሳሳተ መረጃ ልታሰራጭ ትችላለህ። መረጃው ትክክል መሆኑን ከተጠራጠርክ አትላከው፤ እንዲያውም አጥፋው!
8. በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ተቃዋሚዎቻችን ምን አድርገዋል? እኛም ሳይታወቀን ከተቃዋሚዎች ጋር ልንተባበር የምንችለው እንዴት ነው?
8 የሚደርሱንን ኢ-ሜይሎች እና የጽሑፍ መልእክቶች ለሌሎች በችኮላ መላክ ሌላም አደጋ አለው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት መስበክ አይችሉም፤ በሌሎች አገሮች ደግሞ ሥራችን ሙሉ በሙሉ ታግዷል። እንደነዚህ ባሉት አገሮች ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች፣ ፍርሃት እንዲያድርብን ወይም ከወንድሞቻችን ጋር በጥርጣሬ ዓይን እንድንተያይ የሚያደርጉ ወሬዎችን ሆን ብለው ይነዛሉ። በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኬ ጂ ቢ ተብለው የሚጠሩት የሚስጥር ፖሊሶች፣ ኃላፊነት ያላቸው በርካታ ወንድሞች የይሖዋን ሕዝብ እንደካዱ የሚገልጽ ወሬ አናፈሱ።a ብዙዎች ይህን የሐሰት ወሬ በማመናቸው ራሳቸውን ከይሖዋ ድርጅት አገለሉ። ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው! ደስ የሚለው ነገር፣ ከጊዜ በኋላ ብዙዎቹ ተመልሰዋል፤ አንዳንዶቹ ግን ሳይመለሱ ቀርተዋል። እነዚህ ሰዎች ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው ጠፍቷል። (1 ጢሞ. 1:19) እንዲህ ያለ አሳዛኝ ነገር እንዳይደርስ መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? አሉታዊ የሆኑ ወይም ያልተረጋገጡ ዘገባዎችን ከማሰራጨት በመቆጠብ ነው። በቀላሉ ላለመሞኘት ወይም ላለመታለል እንጠንቀቅ። የሰማነውን ሁሉ ከማመናችን በፊት የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት እናድርግ።
ያልተሟላ መረጃ
9. ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ እንቅፋት የሚሆንብን ሌላው ነገር ምንድን ነው?
9 ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ እንቅፋት የሚሆንብን ሌላው ነገር ደግሞ በከፊል እውነት በሆነ ወይም ባልተሟላ መረጃ ላይ የተመሠረተ ወሬ ነው። በተወሰነ ደረጃ ብቻ እውነት የሆነ መረጃ በጣም አሳሳች ነው። ታዲያ በከፊል እውነታነት ያላቸው ሆኖም አሳሳች የሆኑ ወሬዎች እንዳያታልሉን ምን ማድረግ እንችላለን?—ኤፌ. 4:14
10. እስራኤላውያን ወንድሞቻቸውን ለመውጋት እንዲነሱ ያደረጋቸው ምን ነበር? ይህን ከማድረግ እንዲቆጠቡ የረዳቸውስ ምንድን ነው?
10 ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምዕራብ የሚኖሩት እስራኤላውያን በኢያሱ ዘመን ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። (ኢያሱ 22:9-34) እነዚህ እስራኤላውያን፣ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩት ወንድሞቻቸው (ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ) በዮርዳኖስ አጠገብ ግዙፍ የሆነ አስደናቂ መሠዊያ መሥራታቸውን ሰሙ። በስተ ምሥራቅ የሚኖሩት እስራኤላውያን መሠዊያ መሥራታቸው እውነት ቢሆንም መረጃው የተሟላ አልነበረም። በስተ ምዕራብ ያሉት እስራኤላውያን ይህን ወሬ ሲሰሙ ወንድሞቻቸው በይሖዋ ላይ እንዳመፁ ስለተሰማቸው በስተ ምሥራቅ ባሉት እስራኤላውያን ላይ ጦርነት አወጁ። (ኢያሱ 22:9-12ን አንብብ።) ደግነቱ፣ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት ጉዳዩን እንዲያጣሩ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎችን ላኩ። ታዲያ እውነታው ምን ሆኖ ተገኘ? ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ መሠዊያውን የሠሩት መሥዋዕት ለማቅረብ ሳይሆን መታሰቢያ ሆኖ እንዲያገለግል ብለው ነበር። የወደፊቱ ትውልድ፣ እነሱም ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸውን እንዳይጠራጠር የሚያደርግ ምሥክር ለማቆም ፈልገው ነበር። ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉት እስራኤላውያን፣ በደረሳቸው ያልተሟላ መረጃ ላይ ተመሥርተው ወንድሞቻቸውን ከማጥቃት ይልቅ ጊዜ ወስደው ጉዳዩን ለማጣራት በመሞከራቸው ተደስተው መሆን አለበት!
11. (ሀ) ሜፊቦስቴ ኢፍትሐዊ ድርጊት የተፈጸመበት እንዴት ነው? (ለ) ዳዊት ምን ቢያደርግ የተሻለ ይሆን ነበር?
11 አንዳንድ ጊዜ፣ ሰዎች ስለ እኛ ያልተሟላ መረጃ በማሰራጨታቸው ምክንያት ኢፍትሐዊ ድርጊት ይፈጸምብን ይሆናል። ሜፊቦስቴ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ንጉሥ ዳዊት፣ ለሜፊቦስቴ ደግነት ያሳየው ሲሆን የአያቱን የሳኦልን መሬት በሙሉ መልሶለት ነበር። (2 ሳሙ. 9:6, 7) ሆኖም ዳዊት በአንድ ወቅት ስለ ሜፊቦስቴ መጥፎ ወሬ ሰማ። ዳዊት ወሬውን ሳያጣራ የሜፊቦስቴ ንብረት በሙሉ እንዲወሰድበት ወሰነ። (2 ሳሙ. 16:1-4) ዳዊት ሜፊቦስቴን ካነጋገረው በኋላ ግን መሳሳቱን ተገነዘበ፤ በዚህ ጊዜ ለሜፊቦስቴ የንብረቱ ግማሽ እንዲመለስለት አደረገ። (2 ሳሙ. 19:24-29) ዳዊት ባልተሟላ መረጃ ላይ ተመሥርቶ በችኮላ ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ረጋ ብሎ እውነታውን ለማወቅ ጥረት ቢያደርግ ኖሮ እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊ ድርጊት አይፈጽምም ነበር።
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ሰዎች ስለ እሱ የተሳሳተ ወሬ ሲያወሩ ምን አድርጓል? (ለ) አንድ ሰው ስለ እኛ የሐሰት ወሬ ቢያዛምት ምን ማድረግ እንችላለን?
12 ሌሎች፣ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ስምህን ቢያጠፉ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስና አጥማቂው ዮሐንስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። (ማቴዎስ 11:18, 19ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ ሰዎች ስለ እሱ የሐሰት ወሬ ሲያናፍሱ ምን አደረገ? ወሬውን ለማስተባበል በመሞከር ጊዜውንና ጉልበቱን አላባከነም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች ተግባሩንና ያስተማረውን ነገር በማየት እውነቱን ራሳቸው እንዲፈርዱ አበረታቷል። ኢየሱስ “ጥበብ ትክክል መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” ብሏል።—ማቴ. 11:19 ግርጌ
13 ከዚህ ግሩም ትምህርት እናገኛለን። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለ እኛ ተገቢ ያልሆነ ወይም ነቀፋ ያዘለ ነገር ይናገሩ ይሆናል። በዚህ ወቅት፣ ነገሩ እንዲስተካከል እንመኝ እንዲሁም የጎደፈውን ስማችንን ለማጽዳት ስንል አንድ እርምጃ ለመውሰድ እንፈልግ ይሆናል። ይሁንና ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ እንችላለን። አንድ ሰው ስለ እኛ የሐሰት ወሬ ቢያሰራጭ ወሬው ውሸት መሆኑን በአኗኗራችን ማሳየት እንችላለን፤ እንዲህ ካደረግን ሌሎች ሰዎች የግለሰቡን ውሸት አያምኑም። በእርግጥም ከኢየሱስ ምሳሌ መመልከት እንደሚቻለው ጥሩ ክርስቲያናዊ ምግባር ካለን ስለ እኛ የሚወሩ ባልተሟላ መረጃ ላይ የተመሠረቱ ወሬዎችና የሐሰት ውንጀላዎች ተአማኒነት እንዳያገኙ ማድረግ እንችላለን።
በራስህ ከልክ በላይ ትተማመናለህ?
14, 15. በገዛ ራሳችን ማስተዋል መመካት ወጥመድ ሊሆንብን የሚችለው እንዴት ነው?
14 ጥሩ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ እንቅፋት የሚሆንብን አንዱ ነገር አስተማማኝ መረጃ ማግኘት አለመቻል እንደሆነ ተመልክተናል። ሌላው ትልቅ እንቅፋት ደግሞ ፍጽምና የሚጎድለን መሆኑ ነው። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ስናገለግል በመቆየታችን ጥሩ የማመዛዘን ችሎታና ማስተዋል አዳብረን ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት የሌሎችን አክብሮት አትርፈን ይሆናል። ይሁንና ይህ ወጥመድ ሊሆንብን ይችላል። እንዴት?
15 በራሳችን ማስተዋል ከልክ በላይ መተማመን ልንጀምር እንችላለን። ስሜታችንና የግል አመለካከታችን በአስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። በመሆኑም ስለ አንድ ጉዳይ የተሟላ መረጃ ባይኖረንም እንኳ ጉዳዩን ጠንቅቀን ማወቅ እንደምንችል ይሰማን ይሆናል። ይህ እንዴት አደገኛ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ በገዛ ራሳችን ማስተዋል እንዳንመካ በግልጽ ያስጠነቅቀናል።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 28:26
16. ምን ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል? ቶም በችኮላ ምን ዓይነት ድምዳሜ ላይ ደረሰ?
16 እስቲ አንድ ምሳሌ ወደ አእምሯችን እናምጣ። ቶም የሚባል ለረጅም ጊዜ በሽማግሌነት ያገለገለ ወንድም፣ አንድ ምሽት ምግብ ቤት ሲገባ ጆን የተባለ ሌላ ሽማግሌ ሚስቱ ካልሆነች ሴት ጋር ተቀምጦ አየ። ቶም ሁለቱ ሰዎች ሲሳሳቁ፣ ሲጨዋወቱና ሲተቃቀፉ ተመለከተ። ሁኔታው በጣም ስለረበሸው እንዲህ ብሎ ማሰብ ጀመረ፦ ‘ጆንና ሚስቱ በዚህ ምክንያት ይፋቱ ይሆን? ልጆቹስ ምን ሊሆኑ ነው?’ ቶም ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ሲፈጠር ተመልክቷል። አንተ በቶም ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር?
17. ቶም በኋላ ላይ ምን ተገነዘበ? ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
17 ቶም፣ ጆንን ከሌላ ሴት ጋር ስላየው ብቻ ጆን ለሚስቱ ያለውን ታማኝነት እንዳጓደለ ተሰምቶታል፤ ሆኖም ቶም የተሟላ መረጃ ነበረው? ቶም በዚያው ምሽት ስልክ ደውሎ ጆንን አናገረው። ቶም፣ ከጆን ጋር ያያት ሴት በሌላ ከተማ የምትኖር የጆን እህት እንደሆነች ሲያውቅ እፎይ ብሎ መሆን አለበት። ጆንና እህቱ ከተገናኙ ብዙ ዓመት ሆኗቸዋል። ምግብ ቤት ውስጥ የተገናኙት፣ የጆን እህት በዚያ ከተማ የምትቆየው ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ስለሆነ ነው። የጆን ባለቤት ደግሞ እዚያ መምጣት አልቻለችም። ቶም የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሶ እንደነበረ ማየት ይቻላል። ጥሩነቱ፣ ቶም የተሰማውን ነገር ለሌሎች አልተናገረም። ታዲያ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የቱንም ያህል ተሞክሮ ቢኖረን አንድ መደምደሚያ ላይ ከመድረሳችን በፊት እውነታውን ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።
18. ከወንድሞቻችን ጋር ያለን የባሕርይ ልዩነት የማመዛዘን ችሎታችንን ሊያዛባው የሚችለው እንዴት ነው?
18 የሚደርሰንን መረጃ በትክክል እንዳንገመግም እንቅፋት የሚሆንብን ሌላም ነገር አለ። በጉባኤ ውስጥ ካለ አንድ ወንድም ጋር ብዙም አንጣጣም ይሆናል። ባሉን ልዩነቶች ላይ የምናተኩር ከሆነ ወንድማችንን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ልንጀምር እንችላለን። በመሆኑም ይህን ወንድም በተመለከተ አንድ መጥፎ ነገር ብንሰማ፣ ምንም ሳናጣራ ወሬውን ለማመን እንፈተን ይሆናል። ነጥቡ ምንድን ነው? ስለ ወንድሞቻችን መጥፎ አመለካከት መያዛችን፣ በእውነታው ላይ ያልተመሠረተ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ሊያደርገን ይችላል። (1 ጢሞ. 6:4, 5) ቅናትና ምቀኝነት በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰዱ ባለመፍቀድ የማመዛዘን ችሎታችን እንዳይዛባ መከላከል እንችላለን። እንግዲያው ለወንድሞቻችን እንዲህ ያለ መጥፎ አመለካከት ከማዳበር ይልቅ እንድንወዳቸውና ከልባችን ይቅር እንድንላቸው የተሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ እናድርግ።—ቆላስይስ 3:12-14ን አንብብ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥበቃ ይሆኑልናል
19, 20. (ሀ) አንድን መረጃ ለመገምገም የሚረዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ምን እንመረምራለን?
19 በዛሬው ጊዜ፣ አስተማማኝ የሆነ መረጃ ማግኘትና መረጃን ገምግሞ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ መድረስ በጣም አስቸጋሪ ነው። ለምን? ምክንያቱም የምናገኘው አብዛኛው መረጃ ያልተረጋገጠ ወይም ያልተሟላ ነው፤ በዚያ ላይ ደግሞ የራሳችን አለፍጽምና አለ። ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ይረዳናል? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ነው። አንዱ መሠረታዊ ሥርዓት፣ አንድ ሰው እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ ቢሰጥ ሞኝነት እንደሚሆንበትና ውርደት እንደሚከናነብ ይገልጻል። (ምሳሌ 18:13) ሌላው መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ ሳናጣራ ቃልን ሁሉ ማመን እንደሌለብን ያሳስበናል። (ምሳሌ 14:15) በተጨማሪም በእውነት ቤት ውስጥ የቱንም ያህል ተሞክሮ ቢኖረን በገዛ ራሳችን ማስተዋል ላለመመካት መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ምሳሌ 3:5, 6) በእርግጥም አስተማማኝ የሆኑ መረጃዎችን በመጠቀም ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ለመድረስና ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ለማድረግ ከጣርን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥበቃ ይሆኑልናል።
20 ይሁንና እውነታውን ማወቅ አስቸጋሪ እንዲሆንብን ሊያደርግ የሚችል ሌላም እንቅፋት አለ። ይህም የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት የመፍረድ ዝንባሌ ነው። በዚህ ረገድ ስህተት ልንሠራ የምንችልባቸውን አንዳንድ አቅጣጫዎች እንዲሁም በዚህ ወጥመድ ላለመውደቅ ምን ሊረዳን እንደሚችል በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።