የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሩት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
ታሪኩ በሁለት ሴቶች መካከል ያለን የጠበቀ ታማኝነት የሚያወሳ እውነተኛ ድራማ ነው። ይሖዋ አምላክን ከፍ አድርጎ መመልከትንና በዝግጅቶቹ መታመንን ያጎላል። መሲሑ ለሚመጣበት የዘር መስመር ይሖዋ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ይጠቁማል። እንዲሁም አንድ ቤተሰብ በደስታም ሆነ በሐዘን ጊዜ ያሳለፈውን ሕይወት ልብ በሚነካ መንገድ ይተርካል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሩት መጽሐፍ ከላይ ያለውን ጨምሮ ብዙ ሊባልለት ይችላል።
የሩት መጽሐፍ “መሳፍንት [በእስራኤል] በሚገዙበት ዘመን” ወደ 11 በሚጠጉ ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙ ታሪኮችን ይሸፍናል። (ሩት 1:1) በዚህ እውነተኛ ድራማ ላይ ከተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት አንዱ በኢያሱ ዘመን የኖረችው የረዓብ ልጅ የሆነው ባለ ርስቱ ቦዔዝ ስለሆነ ታሪኩ የተፈጸመው በመሳፍንት ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። (ኢያሱ 2:1, 2፤ ሩት 2:1፤ ማቴዎስ 1:5) ዘገባው በ1090 ከክርስቶስ ልደት በፊት በነቢዩ ሳሙኤል እንደተጻፈ ይታመናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እስራኤላዊ ባልሆነች ሴት ስም የተሰየመው መጽሐፍ ይህ ብቻ ቢሆንም በውስጡ የያዘው መልእክት ግን “ሕያውና የሚሠራ” ነው።—ዕብራውያን 4:12
“ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ”
ኑኃሚን እና ሩት ቤተ ልሔም ሲደርሱ የሰው ሁሉ ትኩረት በእነርሱ ላይ አረፈ። የከተማው ሴቶች ከሁለቱ በዕድሜ የገፋችውን እየጠቆሙ “ይህች ኑኃሚን ናትን?” እያሉ መጠየቅ ጀመሩ። ኑኃሚን ግን “ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን እጅግ መራራ አድርጎታልና ማራ በሉኝ እንጂ፣ ኑኃሚን ብላችሁ አትጥሩኝ። በሙላት ወጣሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ባዶዬን መለሰኝ” አለቻቸው።—ሩት 1:19-21
በእስራኤል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ኑኃሚን ከቤተሰቧ ጋር ቤተ ልሔምን ለቅቃ ወደ ሞዓብ ምድር ስትሰደድ ባሏና ሁለት ወንዶች ልጆችዋ አብረዋት ስለነበሩ “በሙላት ወጣሁ” ልትል ችላለች። በሞዓብ መኖር ከጀመሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ባሏ አቤሜሌክ ሞተ። ከዚያ ሁለት ወንዶች ልጆቿ ዖርፋና ሩት የተባሉ ሞዓባውያን ሴቶችን አገቡ። አሥር ዓመታት ካለፉ በኋላ ሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ሳይወልዱ በመሞታቸው ሦስቱ ሴቶች ያለ ባል ቀሩ። በዚህ ጊዜ ኑኃሚን ወደ ይሁዳ ለመመለስ ስትነሳ የልጆቿ ሚስቶች የነበሩት መበለቶችም አብረዋት ለመሄድ ወሰኑ። በጉዟቸው ላይ ኑኃሚን ምራቶቿን ወደ ሞዓብ ተመልሰው ከወገኖቻቸው መካከል ባል እንዲፈልጉ ነገረቻቸው። ዖርፋ እሺ ብላ ተመለሰች። ሩት ግን ከኑኃሚን መለየት ስላልፈለገች “ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትኖሪበትም እኖራለሁ። ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል” አለቻት።—ሩት 1:16
ኑኃሚንና ሩት ወደ ቤተ ልሔም የተመለሱት የገብስ አዝመራ የሚሰበሰብበት ወቅት ሲጀምር ነበር። ሩት በአምላክ ሕግ ውስጥ የተደረገውን ዝግጅት በመጠቀም በእርሻ ላይ መቃረም ጀመረች። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ትቃርምበት የነበረው አዝመራ የአቤሜሌክ ዘመድ የሆነ ቦዔዝ የተባለ በዕድሜ የገፋ አይሁዳዊ እርሻ ነበር። ሩት የቦዔዝን ሞገስ በማግኘቷ “የገብሱና የስንዴው አዝመራ ተሰብስቦ እስኪያበቃ ድረስ” በእርሱ እርሻ ላይ መቃረም ቀጠለች።—ሩት 2:23
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:8—ኑኃሚን ለምራቶቿ ወደ አባቶቻችሁ ቤት ተመለሱ በማለት ፋንታ “ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ” ያለቻቸው ለምን ነበር? የዖርፋ አባት በወቅቱ በሕይወት ይኑር አይኑር አልተጠቀሰም። የሩት አባት ግን በሕይወት ነበር። (ሩት 2:11) ሆኖም ኑኃሚን ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ ያለቻቸው በእናታቸው ቤት የሚያገኙትን ፍቅርና እንክብካቤ እንዲያስታውሳቸው ብላ ይሆናል። ይህ በተለይ ከሚወዷት አማታቸው በመለየታቸው የሚሰማቸውን የመረረ ሐዘን ሊያስረሳቸው ይችላል። ከዚህም በላይ የሩትና የዖርፋ እናቶች ከኑኃሚን በተለየ የተመቸና የተደላደለ ኑሮ እንደነበራቸው የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።
1:13, 21—ኑኃሚን ሕይወት መራራና በመከራ የተሞላ እንዲሆንባት ያደረገው ይሖዋ ነበር? አይደለም። ኑኃሚንም እንደዚያ ስትል መከራ አምጥቶብኛል ብላ አምላክን መክሰሷ አልነበረም። ሆኖም ከደረሰባት መከራ አንጻር ይሖዋ ፊቱን እንዳዞረባት ተሰምቷት ነበር። በሁኔታው ክፉኛ የተመረረች ሲሆን ግራ ተጋብታም ነበር። ከዚህም በላይ በጊዜው የማሕፀን ፍሬ የአምላክን በረከት እንደ ማግኘት ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን መካን መሆን ደግሞ እንደ እርግማን ተደርጎ ይታይ ነበር። ሁለት ልጆቿን በሞት ያጣችውና የልጅ ልጅ ለማየት ያልታደለችው ኑኃሚንም ይሖዋ እንዳዋረዳት ተሰምቷት ነበር።
2:12—ሩት ከይሖዋ የተቀበለችው ‘ፍጹም ደመወዝ’ [የ1954 ትርጉም] ምን ነበር? ሩት ወንድ ልጅ ያገኘች ከመሆኑም በላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት በመሆን በታሪክ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው የዘር መስመር ውስጥ የመካተት መብት አግኝታለች።—ሩት 4:13-17፤ ማቴዎስ 1:5, 16
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:8፤ 2:20፦ ኑኃሚን አሳዛኝ መከራ ቢደርስባትም በይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ላይ ያላትን እምነት አላጣችም። እኛም በተለይ ከባድ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት እስከመጨረሻው ይዘን መቀጠል ይኖርብናል።
1:9፦ ቤት ሲባል የቤተሰብ አባላት ምግብ ለመብላትና ለመተኛት ብቻ የሚሰባሰቡበት ቦታ መሆን የለበትም። እረፍትና መጽናኛ የሚገኝበት ሰላማዊ ቦታ መሆን አለበት።
1:14-16፦ ዖርፋ “ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች።” ሩት ግን በትውልድ አገሯ ልታገኝ የምትችለውን የተረጋጋና የተደላደለ ሕይወት ትታ ለይሖዋ ታማኝ ሆና ቀጥላለች። እኛም ለይሖዋ ታማኝ ፍቅር ማዳበራችንና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየታችን ለራስ ወዳድነት ምኞቶች ከመሸነፍና ‘ወደ ኋላ አፈግፍገን ከመጥፋት’ ይጠብቀናል።—ዕብራውያን 10:39
2:2፦ ሩት ትሑት ልብ ስለነበራት መጻተኞችና ምስኪኖች ከአዝመራው እንዲቃርሙ በተደረገው ዝግጅት ለመጠቀም ፈቃደኛ ነበረች። አንድ ችግረኛ ክርስቲያንም የእምነት ባልንጀሮቹ የሚያደርጉለትን ፍቅራዊ ድጋፍ ወይም ከመንግሥት ሊያገኝ የሚችለውን እርዳታ እንዳይቀበል ኩራት ሊያግደው አይገባም።
2:7፦ ሩት ከአዝመራው የመቃረም መብት ቢኖራትም እንደዚያ ከማድረጓ በፊት ፈቃድ ጠይቃለች። (ዘሌዋውያን 19:9, 10) ይህም በተፈጥሮዋ ገር እንደነበረች የሚያሳይ ነው። እኛም ገርነትን ወይም ‘ትሕትናን መፈለግ’ ይኖርብናል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” ይላል።—ሶፎንያስ 2:3፤ መዝሙር 37:11
2:11፦ ሩት ለኑኃሚን ከምራትም በላይ እንደ ቅርብ ጓደኛዋ ነበረች። (ምሳሌ 17:17) ጓደኝነታቸው እንደ ፍቅር፣ ታማኝነት፣ ርኅራሄ፣ ደግነት፣ የራስን ጥቅም መሠዋትና የመሳሰሉት ባሕርያት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ጠንካራ ነበር። ከዚህም በላይ በመንፈሳዊነታቸው ማለትም ይሖዋን ለማምለክና በሕዝቦቹ መካከል ለመሆን ባላቸው ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነበር። እኛም ከእውነተኛ አምላኪዎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት የምንችልባቸው ግሩም አጋጣሚዎች አሉን።
2:15-17፦ ቦዔዝ ሥራዋ እንዲቀልላት ካደረገም በኋላ ሩት ‘እስኪመሽ ደረስ ከአዝመራው ላይ መቃረሟን’ ቀጥላለች። ሩት ታታሪ ሠራተኛ ነበረች። አንድ ክርስቲያን በሥራው ታታሪ ነው የሚል ጥሩ ስም ሊኖረው ይገባል።
2:19-22፦ ኑኃሚንና ሩት ማታ ማታ አስደሳች ጭውውት ያደርጉ የነበረ ሲሆን በዕድሜ የገፋችው ኑኃሚን የወጣቷ ሩት ውሎ ምን ይመስል እንደነበር ለማወቅ ትፈልጋለች። እንዲሁም ሁለቱም ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን አውጥተው በነጻነት ይወያዩ ነበር። አንድ የክርስቲያን ቤተሰብም ተመሳሳይ ልማድ ሊኖረው ይገባል።
2:22, 23፦ የያዕቆብ ልጅ ዲና ካደረገችው በተቃራኒ ሩት ውሎዋ ይሖዋን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር ነበር። በዚህ ረገድም ግሩም ምሳሌ ትሆነናለች!—ዘፍጥረት 34:1, 2፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33
ኑኃሚን ቤቷ ዳግመኛ ‘ሙሉ’ ሆነ
ኑኃሚን በጣም ስላረጀች ልጆች መውለድ አትችልም። በመሆኑም በእርሷ ፋንታ ሩት ሊቤዣት የሚችለውን የባልዋን ዘመድ በማግባት ልጅ እንድትወልድላት ማድረግ ያለባትን ነገረቻት። ሩትም ኑኃሚን እንዳለቻት በማድረግ ቦዔዝን እንዲቤዣት ጠየቀችው። ቦዔዝ ለመቤዠት ፈቃደኛ ቢሆንም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ከእርሱ የቀረበ የሥጋ ዘመድ እንዳለ ነገራት።
ቦዔዝ ጉዳዩን ለማስፈጸም ጊዜ ሳያጠፋ እርምጃ ወሰደ። በቀጣዩ ቀን ማለዳ ላይ የቅርብ ዘመድ የነበረው ሰው በተገኘበት አሥር የቤተ ልሔም ሽማግሌዎችን ሰበሰበና ርስቱን ለመቤዠት ፈቃደኛ መሆን አለመሆኑን ጠየቀው። ሰውየው ፈቃደኛ አለመሆኑን ገለጸ። በመሆኑም ቦዔዝ ርስቱን ገዛ፤ ሩትንም አገባት። ትዳራቸው የንጉሥ ዳዊት ቅድመ አያት የነበረውን ኢዮቤድን አስገኘ። በዚህ ጊዜ የቤተ ልሔም ሴቶች ለኑኃሚን “እግዚአብሔር ይባረክ፤ . . . ልጁ ሕይወትሽን ያድሳታል፤ በእርጅና ዘመንሽም ይጦርሻል፤ የምትወድሽና ከሰባት ወንዶች ልጆች የምትበልጥብሽ ምራትሽ ወልዳዋለችና” አሏት። (ሩት 4:14, 15) ወደ ቤተ ልሔም ‘ባዶዋን’ የተመለሰችው ሴት አሁን ቤቷ ዳግመኛ ‘ሙሉ’ ሆነ!—ሩት 1:21
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
3:11—ሩት “ምግባረ መልካም ሴት” የሚል ስም ያተረፈችው እንዴት ነው? ሩት የሌሎችን አድናቆት ያተረፈችው “በውጫዊ ነገሮች በመሽሞንሞን ይኸውም ሹሩባ በመሠራት” ወይም “በወርቅ በማጌጥና በልብስ” አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ታማኝነቷና ፍቅሯ፣ ትሕትናዋና ገርነቷ እንዲሁም ታታሪነቷና የራሷን ጥቅም ለመሠዋት ዝግጁ መሆኗ “የውስጥ ሰውነት ውበት” እንዲኖራት አድርጓታል። የሩትን ዓይነት መልካም ስም ለማትረፍ የምትፈልግ ማንኛዋም ፈሪሃ አምላክ ያላት ሴት ከላይ የተጠቀሱትን ባሕርያት ለማዳበር ጥረት ማድረግ አለባት።—1 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ ምሳሌ 31:28-31
3:14—ሩትና ቦዔዝ ገና ጎሕ ሳይቀድ የተነሱት ለምን ነበር? እንዲህ ያደረጉት የሥነ ምግባር ብልግና ስለፈጸሙና ሰው እንዲያውቅባቸው ስላልፈለጉ አልነበረም። ሩት ያደረገችው ነገር በጊዜው የሚቤዣትን ሰው የምትፈልግ ማንኛዋም ሴት የምታደርገው የተለመደ ነገር ሳይሆን አይቀርም። እንዲሁም ኑኃሚን የነገረቻትን ነገር ነበር ያደረገችው። ከዚህም በላይ ቦዔዝ የሩትን ድርጊት ተገቢ እንዳልሆነ ነገር አድርጎ እንዳልቆጠረው ከሰጠው ምላሽ መረዳት ይቻላል። (ሩት 3:2-13) ሩትና ቦዔዝ በማለዳ የተነሱት ሰዎች ተመልክተዋቸው መሠረተ ቢስ የሆነ አሉባልታ እንዳይሰራጭ ፈልገው ሊሆን ይችላል።
3:15—ቦዔዝ ለሩት ስድስት መስፈሪያ ገብስ የሰጣት ለምን ሊሆን ይችላል? ይህ ድርጊቱ ከስድስት የሥራ ቀናት በኋላ አንድ የእረፍት ቀን እንደሚኖር ሁሉ ሩትም ከድካሟ የምታርፍበት ወቅት እንደቀረበ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በባልዋ ቤት ‘ዕረፍት’ የምታገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ቆርጦ ነበር። (ሩት 1:9፤ 3:1) ወይም ደግሞ ሩት በጭንቅላትዋ ላይ መሸከም የምትችለው ስድስት መሥፈሪያ ገብስ ብቻ ስለነበረ ይሆናል።
3:16—በጥንቶቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት ኑኃሚን ሩትን “ልጄ ሆይ፣ አንቺ ማን ነሽ?” ብላ የጠየቀቻት ለምን ነበር? የምራቷን ማንነት መለየት ስለተሳናት ነበር? ሩት ወደ ኑኃሚን የተመለሰችው ገና በደንብ ሳይነጋ ሊሆን ስለሚችል ማንነቷን መለየት ተስኗት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኑኃሚን እንዲህ ብላ የጠየቀቻት ሩት የሚቤዣት ሰው አግኝታ ከሆነ ከዚያ ጋር በተያያዘ የሚኖራትን አዲስ ማንነት ለማወቅ ፈልጋም ሊሆን ይችላል።
4:6—አንድ ሰው የቅርብ ዘመዱን በመቤዠት የራሱን ርስት ‘አደጋ ላይ ሊጥል’ የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ለድህነት የተጋለጠው ሰው መሬቱን ሸጦት ከነበረ የሚቤዠው ሰው ቀጣዩ የኢዮቤልዩ በዓል እስከሚከበርበት ጊዜ ድረስ በቀሩት ዓመታት መጠን ተሰልቶ የሚወሰነውን ዋጋ በመክፈል መሬቱን መግዛት ይኖርበታል። (ዘሌዋውያን 25:25-27) ይህም የሀብቱን መጠን ይቀንስበታል። ከዚህም በላይ ሩት ወንድ ልጅ ከወለደች የተገዛውን መሬት የሚወርሰው ርስቱን የተቤዠው ሰው የቅርብ የሥጋ ዘመዶች ሳይሆኑ ይህ ልጅ ነው።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
3:12፤ 4:1-6፦ ቦዔዝ የይሖዋን ዝግጅት በጥንቃቄ ተግባራዊ አድርጓል። እኛስ ቲኦክራሲያዊ ሥርዓቶችን በጥንቃቄ ለመከተል እንጥራለን?—1 ቆሮንቶስ 14:40
3:18፦ ኑኃሚን በቦዔዝ ላይ ሙሉ እምነት ነበራት። እኛስ ታማኝ በሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ ተመሳሳይ እምነት ማሳደር አይኖርብንም? ሩት በመቤዠት ሥርዓት መሠረት ጨርሶ ከማታውቀውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ ካልተጠቀሰ ሰው ጋር ትዳር ለመመሥረት ፈቃደኛ ነበረች። (ሩት 4:1) ለምን? በአምላክ ዝግጅት ላይ ሙሉ እምነት ስለነበራት ነው። እኛስ ተመሳሳይ እምነት አለን? ለምሳሌ ያህል የትዳር ጓደኛ ምርጫን በሚመለከት “በጌታ” ብቻ እንድናገባ የተሰጠንን ምክር እንከተላለን?—1 ቆሮንቶስ 7:39
4:13-16፦ ሩት ሞዓባዊትና ኬሞሽ የተባለው ጣዖት አምላኪ የነበረች ቢሆንም ልዩ መብት አግኝታለች! ይህም “ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት እውነተኝነት ያረጋግጥልናል።—ሮሜ 9:16
አምላክ ‘በወሰነው ጊዜ ከፍ ያደርጋችኋል’
የሩት መጽሐፍ ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳይና ታማኝ አገልጋዮቹን ለመርዳት ጣልቃ የሚገባ አምላክ እንደሆነ ያሳያል። (2 ዜና መዋዕል 16:9) ሩት ባገኘችው በረከት ላይ ስናሰላስል “እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ” ሙሉ እምነት በማሳደር ያለምንም ጥርጣሬ በእርሱ መመካት የሚያስገኘውን በረከት እንመለከታለን።—ዕብራውያን 11:6
ሩት፣ ኑኃሚንና ቦዔዝ በይሖዋ ዝግጅት ላይ ሙሉ እምነት በማሳደራቸው ሁሉ ነገር ተሳክቶላቸዋል። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ “እግዚአብሔር፣ ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮሜ 8:28) እኛም “ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” የሚለውን የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ተግባራዊ እናድርግ።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩት ኑኃሚንን ትታ ለመመለስ ያልፈለገችው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩት “ምግባረ መልካም ሴት” የሚል ስም ያተረፈችው በምን የተነሳ ነው?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሩት ከይሖዋ ያገኘችው ‘ፍጹም ደመወዝ’ ምን ነበር?