የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
ከመጋቢት 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 12-13
“እብሪት ለውርደት ይዳርጋል”
ትዕቢት ውርደትን ያስከትላል
17 እንዲሁ ከላይ ሲታይ ሳኦል ያደረገው ነገር ትክክል ሊመስል ይችላል። ደግሞም የአምላክ ሕዝቦች በነበሩበት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የተነሳ “ተጨንቀው” ይንቀጠቀጡ ነበር። (1 ሳሙኤል 13:6, 7) እርግጥ ነው፣ ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ በራስ ተነሳሽነት አንድ ነገር ማድረጉ ምንም ስህተት የለበትም። ሆኖም ይሖዋ ልብን ማንበብና የተነሳሳንበትን ውስጣዊ ግፊት ማወቅ እንደሚችል አትዘንጋ። (1 ሳሙኤል 16:7) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ባይጠቀስም ሳኦልን በሚመለከት አንድ ያየው ነገር መኖር አለበት። ለምሳሌ ያህል ሳኦል ትዕግሥት ያጣው በውስጡ ባደረበት ትዕቢት እንደሆነ ይሖዋ ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። ምናልባት የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ሳኦል ዕድሜው ከመግፋቱ የተነሳ እያዘገመ እንደሚመጣ አድርጎ የተመለከተውን ነቢይ መጠበቁ አበሳጭቶት ሊሆን ይችላል! ያም ሆነ ይህ የሳሙኤል መዘግየት ነገሮችን በራሱ መንገድ ማከናወንና የተሰጠውን ጥብቅ መመሪያም ችላ ብሎ ማለፍ እንደሚያስችለው ሆኖ ተሰምቶት ይሆናል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሳሙኤል ጎሽ አበጀህ አላለውም። ከዚያ ይልቅ “መንግሥትህ አይጸናም . . . እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና” በማለት በቁጣ ተናግሮታል። (1 ሳሙኤል 13:13, 14) አሁንም ቢሆን ትዕቢት ውርደትን አስከትሏል።
ይሖዋ ታዛዥነትህን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
8 ስለ ንጉሥ ሳኦል የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የታዛዥነትን አስፈላጊነት አጉልቶ ያሳያል። ሳኦል መግዛት በጀመረበት ጊዜ ትሑትና ‘በዓይኑ ፊት ታናሽ’ የሆነ ልኩን የሚያውቅ ንጉሥ ነበር። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ኩራትና የተሳሳተ አመለካከት በውሳኔዎቹ ላይ ተጽዕኖ ያሳድሩ ጀመር። (1 ሳሙኤል 10:21, 22፤ 15:17) በአንድ ወቅት ሳኦል ከፍልስጥኤማውያን ጋር ለመዋጋት እየተዘጋጀ ነበር። በዚህ ጊዜ ሳሙኤል እርሱ መጥቶ ለይሖዋ መሥዋዕት እስኪያቀርብና ተጨማሪ መመሪያ እስኪሰጠው ድረስ እንዲጠብቀው ለንጉሡ ነገረው። ይሁንና ሳሙኤል ይመጣል ተብሎ በታሰበበት ጊዜ ሳይመጣ በመቅረቱ ሕዝቡ መበታተን ጀመረ። ሳኦል ይህን ሲመለከት “የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።” ይህ ይሖዋን የሚያሳዝን ድርጊት ነበር። በመጨረሻ ሳሙኤል ሲመጣ ንጉሡ የሚቃጠል መሥዋዕት ለማቅረብ ‘የተገደደው’ እርሱ በመዘግየቱና የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት በመፈለጉ እንደሆነ በመግለጽ ላለመታዘዙ ሰበብ አቀረበ። ንጉሥ ሳኦል ይህን መሥዋዕት ማቅረብ ሳሙኤልን እንዲጠብቅ የተሰጠውን መመሪያ ከመታዘዝ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ሳሙኤል ግን “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም” አለው። ሳኦል ይሖዋን ባለመታዘዙ ንግሥናውን አጥቷል።—1 ሳሙኤል 10:8፤ 13:5-13
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የይሖዋን ፍቅራዊ አመራር ትከተላለህ?
15 ሕዝቡ፣ የሚሾምላቸው ሰብዓዊ ንጉሥ ከይሖዋ ይልቅ እውንና አስተማማኝ እንደሚሆንላቸው አስበው ይሆን? እንደዚያ አስበው ከሆነ በእርግጥም ከንቱ ነገሮችን እየተከተሉ ነበር! ይህም ሰይጣን የሚያስፋፋቸውን ሌሎች በርካታ ከንቱ ነገሮች ወደ መከተል እንዲያዘነብሉ ያደርጋቸዋል። ሰብዓዊ ነገሥታት ሕዝቡን በቀላሉ ወደ ጣዖት አምልኮ ሊመሯቸው ይችላሉ። ጣዖት አምላኪዎች፣ ከእንጨት ወይም ከድንጋይ የተሠሩ የሚታዩ አማልክት ሁሉን ነገር ከፈጠረው ሆኖም በዓይን ከማይታየው ከይሖዋ አምላክ ይልቅ እውንና አስተማማኝ እንደሆኑ በማሰብ ይሳሳታሉ። ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ጣዖታት “ከንቱ” ናቸው። (1 ቆሮ. 8:4) ማየት፣ መስማት፣ መናገር ወይም ምንም ነገር ማድረግ አይችሉም። ጣዖታትን ማየትና መንካት ይቻል ይሆናል፤ እነሱን ማምለክ ግን ከንቱ የሆነና ወደ ጥፋት የሚመራ እውን ያልሆነ ነገርን እንደ መከተል ይሆንብሃል።—መዝ. 115:4-8
ከመጋቢት 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 14-15
“መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል”
ይሖዋ ታዛዥነትህን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
4 ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን እኛ ያለን ቁሳዊ ሀብት ሁሉ የእርሱ ንብረት ነው። ታዲያ እኛ ልንሰጠው የምንችለው ነገር ይኖራል? አዎን አለ፤ አንድ እጅግ ውድ የሆነ ነገር ልንሰጠው እንችላለን። ይህ ነገር ምንድን ነው? የሚከተለው ምክር መልሱን ይሰጠናል:- “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው፤ ለሚንቁኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችል ዘንድ።” (ምሳሌ 27:11) ለአምላክ ልንሰጠው የምንችለው ነገር ታዛዥነታችንን ነው። ያለንበት ሁኔታና አስተዳደጋችን የተለያየ ቢሆንም ታዛዦች በመሆን ዲያብሎስ ‘ሰዎች ችግር ቢገጥማቸው ለአምላክ ታማኝ አይሆኑም’ በማለት ላነሳው የተንኮል ክስ መልስ መስጠት እንችላለን። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
it-2 521 አን. 2
ታዛዥነት
ታዛዥነትን በምንም ነገር መተካት አይቻልም፤ ካልታዘዝን የአምላክን ሞገስ ማግኘት አንችልም። ሳሙኤል ለንጉሥ ሳኦል እንዲህ ሲል ነግሮታል፦ “ይሖዋን ይበልጥ የሚያስደስተው የትኛው ነው? የሚቃጠሉ መባዎችንና መሥዋዕቶችን ማቅረብ ወይስ የይሖዋን ቃል መታዘዝ? እነሆ፣ መታዘዝ [ሻማ የሚለው ቃል ብዜት] ከመሥዋዕት፣ መስማትም ከአውራ በግ ስብ ይበልጣል።” (1ሳሙ 15:22) አንድ ሰው የማይታዘዝ ከሆነ የይሖዋን ቃል እንደማይቀበል ያሳያል፤ በተጨማሪም በቃሉም ሆነ የቃሉ ምንጭ በሆነው አካል ላይ እምነት እንደሌለውና እንደማይተማመን ያስመሠክራል። ከዚህ አንጻር አለመታዘዝ ከጥንቆላና ከጣዖት አምልኮ ተለይቶ አይታይም። (1ሳሙ 15:23፤ ከሮም 6:16 ጋር አወዳድር።) በተግባር እስካልተደገፈ ድረስ ‘አንድን ነገር ለማድረግ ተስማምቻለሁ’ ማለት ብቻውን ምንም ትርጉም የለውም፤ ከመመሪያው ጋር የሚስማማ እርምጃ አለመውሰድ መመሪያውን በሰጠው አካል ላይ እምነት ማጣትን ወይም ያን አካል አለማክበርን ያመለክታል። (ማቴ 21:28-32) የአምላክን እውነት በመስማትና ያን እውነት በሐሳብ ደረጃ ብቻ በመቀበል ረክተው የሚኖሩ ሆኖም ከዚያ ጋር የሚጣጣም እርምጃ የማይወስዱ ሰዎች የውሸት ምክንያት በማቅረብ ራሳቸውን እያታለሉ ነው፤ ደግሞ ምንም ዓይነት በረከት አያገኙም። (ያዕ 1:22-25) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ከታዘዘው ነገር ጋር የሚመሳሰል ነገር ያደርግ ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ያደረገው በተሳሳተ መንገድ ወይም በተሳሳተ ዓላማ ተነሳስቶ ከሆነ ወደ አምላክ መንግሥት እንደማይገባና በአምላክ ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማያገኝ የአምላክ ልጅ ተናግሯል።—ማቴ 7:15-23
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 493
ርኅራኄ
ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚጻረር መልኩ ርኅራኄ እንድናሳይ ለሚደርስብን ግፊት እጅ መስጠት አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። በንጉሥ ሳኦል ላይ የደረሰው ነገር ይህን ያሳያል። በአማሌቃውያን ላይ መለኮታዊ እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ ደርሶ ነበር፤ አማሌቃውያን ከግብፅ ወጥተው እየተጓዙ በነበሩት ምንም ያልበደሏቸው እስራኤላውያን ላይ ጥቃት የሰነዘሩ የመጀመሪያዎቹ ሕዝቦች ናቸው። ሳኦል ምንም ዓይነት ርኅራኄ እንዳያሳያቸው ታዞ ነበር። ሆኖም በሕዝቡ ተጽዕኖ በመሸነፉ የይሖዋን ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ ሳይፈጽም ቀረ። በመሆኑም ንግሥናው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አጣ። (1ሳሙ 15:2-24) አንድ ሰው የይሖዋ መንገዶች ትክክለኛ እንደሆኑ በሚገባ መገንዘቡና ከምንም ነገር በላይ ለይሖዋ ታማኝ መሆኑ እንደ ሳኦል ያለ ስህተት እንዳይፈጽምና በአምላክ ፊት ሞገስ እንዳያጣ ይረዳዋል።
ከመጋቢት 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 16-17
“ውጊያው የይሖዋ ነው”
“ውጊያው የይሖዋ ነው”
ዳዊት ከአንበሳና ከድብ ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ተሞክሮ በመናገር ሳኦልን ለማሳመን ሞከረ። ታዲያ ዳዊት ጉራ እየነዛ ነበር? በጭራሽ። ዳዊት ከአራዊት ጋር ሲታገል እንዲያሸንፍ የረዳው ማን እንደሆነ በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም “ከአንበሳና ከድብ ጥፍር የታደገኝ ይሖዋ አሁንም ከዚህ ፍልስጤማዊ እጅ ይታደገኛል” በማለት ተናገረ። በመጨረሻም ሳኦል በዳዊት ሐሳብ በመስማማት “እሺ ሂድ፤ ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን” ብሎ አሰናበተው።—1 ሳሙኤል 17:37
እንደ ዳዊት ያለ እምነት እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? ዳዊት እምነቱን የገነባው በምናባዊ ነገር ወይም በምኞት ላይ እንዳልሆነ ልብ በል። ዳዊት በአምላኩ ላይ እምነት ሊኖረው የቻለው እውቀትና ተሞክሮ ስለነበረው ነው። ይሖዋ ለሕዝቡ ከለላ የሚሆንና የገባውን ቃል የሚፈጽም አፍቃሪ አምላክ መሆኑን አውቆ ነበር። እኛም እንዲህ ያለ እምነት እንዲኖረን ከፈለግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጸው አምላክ ትምህርት መቅሰማችንን መቀጠል ይኖርብናል። በተማርነው መሠረት ስንኖር የምናገኛቸው መልካም ውጤቶች ደግሞ እምነታችንን ያጠናክሩታል።—ዕብራውያን 11:1
“ውጊያው የይሖዋ ነው”
ዳዊት ለጎልያድ የሰጠው መልስ እስከ ዛሬ ድረስ ታላቅ የእምነት መግለጫ ሆኖ ይጠቀሳል። ይህ ወጣት ጎልያድን “አንተ ሰይፍ፣ ጭሬና ጦር ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተሳለቅክበት፣ የእስራኤል ተዋጊዎች አምላክ በሆነው በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ስም እመጣብሃለሁ” ብሎ ሲናገረው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ዳዊት የሰው አቅምም ሆነ የጦር መሣሪያ በይሖዋ ዘንድ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ተገንዝቧል። ጎልያድ ይሖዋ አምላክን ስለናቀ መልስ የሚሰጠው ይሖዋ ነበር። ዳዊት እንደተናገረው “ውጊያው የይሖዋ ነው።”—1 ሳሙኤል 17:45-47
ዳዊት የጎልያድን ግዝፈት ወይም የጦር መሣሪያዎች ሳያይ ቀርቶ አይደለም። ሆኖም ዳዊት እነዚህ ነገሮች ወኔውን እንዲሰልቡበት አልፈቀደም። ሳኦልና ሠራዊቱ የፈጸሙትን ስህተት አልደገመም። ራሱን ከጎልያድ ጋር አላነጻጸረም። ከዚህ ይልቅ ጎልያድን የተመለከተው ከይሖዋ አንጻር ነው። ጎልያድ ቁመቱ 2.9 ሜትር በመሆኑ ከሰዎች ጋር ሲወዳደር ተራራ ሊመስል ይችላል፤ ያም ቢሆን ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በእርግጥም ጎልያድ ከይሖዋ ጋር ሲወዳደር እንደማንኛውም ሰው ከአንዲት ትንኝ አይበልጥም፤ በመሆኑም ይሖዋ በቀላሉ ሊጨፈልቀው ይችላል!
“ውጊያው የይሖዋ ነው”
በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች ቃል በቃል በጦርነት አይካፈሉም። ጦርነት የሚደረግበት ዘመን አብቅቷል። (ማቴዎስ 26:52) ያም ሆኖ ዳዊትን በእምነቱ መምሰል ይኖርብናል። እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም ይሖዋ እውን ሆኖ ሊታየን ይገባል፤ እንዲሁም ሊገለገልና አክብሮታዊ ፍርሃት ልናሳየው የሚገባ አምላክ እሱ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ችግሮቻችን በጣም ገዝፈው ይታዩን ይሆናል፤ ያም ቢሆን እነዚህ ችግሮች ገደብ የለሽ ኃይል ባለው በይሖዋ ፊት እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ይሖዋ አምላካችን እንዲሆን ከመረጥንና ዳዊት እንዳደረገው በእሱ ላይ እምነት ካሳደርን ምንም ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ወይም ችግር ሊያስፈራን አይችልም። ከይሖዋ አቅም በላይ የሆነ ምንም ነገር የለም!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 871-872
ሳኦል
ይህ ክንውን ከተፈጸመና ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ከተቀባ በኋላ የይሖዋ መንፈስ ከሳኦል ራቀ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ “ከይሖዋ የመጣ መጥፎ [መንፈስ] ይረብሸው” ጀመር። ይሖዋ መንፈሱን ከሳኦል ላይ በመውሰድ መጥፎ መንፈስ ሳኦልን እንዲቆጣጠረው ፈቅዷል፤ ይህ መንፈስ ሳኦል የአእምሮ ሰላሙን እንዲያጣ አድርጎታል፤ እንዲሁም ስሜቱንና አስተሳሰቡን ወደተሳሳተ አቅጣጫ መርቶታል። ሳኦል ይሖዋን አለመታዘዙ አእምሮውና ልቡ ወደ መጥፎ አቅጣጫ እንዳዘነበለ የሚጠቁም ነበር፤ የአምላክ መንፈስ ሳኦል እንዲህ ያለ ዝንባሌ እንዳያድርበት አልተከላከለለትም ወይም ይህን ዝንባሌ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል አልሰጠውም። ሆኖም ይሖዋ በእሱ መንፈስ ምትክ “መጥፎ መንፈስ” በሳኦል ላይ እንዲያድርበትና እንዲረብሸው ስለፈቀደ ይህ መንፈስ “ከይሖዋ የመጣ መጥፎ መንፈስ” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፤ የሳኦል አገልጋዮችም ይህን መንፈስ ‘ከአምላክ የመጣ መጥፎ መንፈስ’ በማለት የገለጹት በዚህ ምክንያት ነው። ሳኦል ከአገልጋዮቹ አንዱ ባቀረበለት ሐሳብ መሠረት፣ “መጥፎ መንፈስ” ሲረብሸው እንዲያረጋጋው ዳዊትን የቤተ መንግሥቱ ሙዚቀኛ እንዲሆን አስጠራው።—1ሳሙ 16:14-23፤ 17:15
ከመጋቢት 28–ሚያዝያ 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 18-19
“ስኬት ስታገኙ ትሕትናችሁ እንዳይጠፋ ተጠንቀቁ”
በሕይወታችሁ የሚያጋጥሟችሁን ለውጦች ለመቋቋም በአምላክ መንፈስ ታመኑ
4 ይህ እረኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገሩ የታወቀ ሰው ሊሆን ነው። የንጉሡ አገልጋይ እንዲሆንና ሙዚቃ እንዲጫወትለት ተጠራ። የውጊያ ልምድ ያላቸው የእስራኤል ወታደሮች ለመግጠም የፈሩትን ጎልያድ የተባለውን ኃይለኛና ግዙፍ ወታደር ገደለ። ዳዊት የሠራዊቱ አዛዥ ከሆነ በኋላ ፍልስጥኤማውያንን ድል ነሳ። በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት አተረፈ፤ በዘፈንም አሞገሱት። የንጉሥ ሳኦል አገልጋይ የሆነ ሰው ቀደም ሲል ስለ ወጣቱ ዳዊት ‘መልካም አድርጎ በገና መደርደር ይችላል’ ከማለቱም ሌላ “ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” ብሏል።—1 ሳሙኤል 16:18፤ 17:23, 24, 45-51፤ 18:5-7
አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት አስተውሉ
6 አንዳንድ ሰዎች የሚኮሩት መልከ መልካም ወይም ታዋቂ ስለሆኑ አሊያም ጥሩ የሙዚቃ ችሎታ፣ ሥልጣን ወይም ደግሞ አካላዊ ጥንካሬ ስላላቸው ሊሆን ይችላል። ዳዊት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቢኖሩትም በሕይወቱ ሙሉ ትሑት ነበር። ጎልያድን ከገደለ በኋላ ንጉሥ ሳኦል ልጁን ሊድርለት እንደሚፈልግ ሲነግረው ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ለንጉሡ አማች እሆን ዘንድ እኔም ሆንኩ የአባቴ ቤተሰቦች የሆኑት ዘመዶቼ በእስራኤል ውስጥ ከቶ ማን ሆነን ነው?” (1 ሳሙ. 18:18) ዳዊት ምንጊዜም ትሑት እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? እነዚህ ባሕርያት፣ ችሎታዎችና መብቶች የኖሩት አምላክ ‘ወደ ታች በማጎንበስ’ ወይም ራሱን ዝቅ በማድረግ ትኩረት ስለሰጠው መሆኑን መገንዘቡ ነው። (መዝ. 113:5-8) ዳዊት ያሉትን መልካም ነገሮች ሁሉ ያገኘው ከይሖዋ እንደሆነ ያውቅ ነበር።—ከ1 ቆሮንቶስ 4:7 ጋር አወዳድር።
7 እንደ ዳዊት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችም ትሑት ለመሆን ይጥራሉ። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀው አካል ቢሆንም እንኳ ግሩም የሆነውን የትሕትና ባሕርይ ያንጸባርቃል፤ ይህን ማወቃችን በአድናቆት እንድንዋጥ ያደርገናል። (መዝ. 18:35) ይህ ደግሞ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያነሳሳናል። (ቆላ. 3:12) በተጨማሪም ፍቅር ‘ጉራ እንደማይነዛና እንደማይታበይ’ እንገነዘባለን። (1 ቆሮ. 13:4) ትሑት መሆናችን ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ ሊያደርግ ይችላል። ባሎች በሚስቶቻቸው ምግባር የተነሳ ያለቃል ሊማረኩ እንደሚችሉ ሁሉ የአምላክ ሕዝቦች የሚያሳዩት ትሕትናም ሌሎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።—1 ጴጥ. 3:1
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 695-696
ነቢይ
ነቢያት በይሖዋ መንፈስ የተሾሙ ቢሆኑም ሁልጊዜ በመንፈስ ተመርተው ይናገራሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሆነ ጊዜ ላይ የአምላክ መንፈስ ‘በእነሱ ላይ በመምጣት’ የሚናገሩትን መልእክት ያሳውቃቸዋል። (ሕዝ 11:4, 5፤ ሚክ 3:8) ይህ መንፈስ በውስጣቸው ተነሳሽነት በመፍጠር እንዲናገሩ ይገፋፋቸዋል። (1ሳሙ 10:10፤ ኤር 20:9፤ አሞጽ 3:8) ነቢያት ከተለመደው ወጣ ያሉ ነገሮችን የሚያደርጉ ሲሆን አኳኋናቸውና የሚያንጸባርቁት የተጋነነ ስሜት ለተመልካቾች እንግዳ እንደሚሆን አያጠራጥርም። አንዳንዶች ‘እንደ ነቢይ አደረጋቸው’ የተባለበት አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል። (1ሳሙ 10:6-11፤ 19:20-24፤ ኤር 29:24-32፤ ከሥራ 2:4, 12-17፤ 6:15፤ 7:55 ጋር አወዳድር።) ሥራቸው ላይ ሙሉ በሙሉ አተኩረው ሲሠሩ እንዲሁም ተልእኳቸውን በቅንዓትና በድፍረት ሲወጡ የሚያሳዩት ባሕርይ በሌሎች ዘንድ እንደ እንግዳ ነገር ሊታይ አልፎ ተርፎም አእምሯቸውን እንደሳቱ ሊያስቆጥራቸው ይችላል። ኢዩ በተቀባበት ጊዜ የሠራዊት አለቆቹ ኢዩን ሊቀባው ስለመጣው ነቢይ እንዲህ ተሰምቷቸው ነበር። ነቢይ መሆኑን ካወቁ በኋላ ግን መልእክቱን በቁም ነገር ተቀብለውታል። (2ነገ 9:1-13፤ ከሥራ 26:24, 25 ጋር አወዳድር።) ሳኦል ዳዊትን እያሳደደ በነበረበት ጊዜ ልብሱን በማውለቅ እንዲሁም “ቀኑንና ሌሊቱን ሙሉ ራቁቱን ሆኖ” በመጋደም ‘እንደ ነቢይ አድርጎት’ ነበር፤ ይሖዋ፣ ሳኦል እንዲህ እንዲሆን ባደረገበት ጊዜ ዳዊት ማምለጥ እንደቻለ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (1ሳሙ 19:18–20:1) ይህ ሲባል ግን ነቢያት ብዙ ጊዜ ራቁታቸውን ይሆኑ ነበር ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ልብስ ይለብሱ እንደነበር ይጠቁማሉ። ስለ ሳኦል ራቁት መሆን ከሚገልጸው ዘገባ ውጭ ባሉት ሁለት ዘገባዎች ላይ ነቢያቱ ራቁታቸውን የሆኑት በዓላማ ነበር፤ ይኸውም የሚናገሩትን ትንቢት አንድ ገጽታ ለማሳየት ነው። (ኢሳ 20:2-4፤ ሚክ 1:8-11) ሳኦል ራቁቱን የሆነበት ምክንያት በግልጽ አልተጠቀሰም፤ ምናልባት ንጉሣዊ ልብሱ የተገፈፈበት እንዲሁም ከይሖዋ ሥልጣንና ኃይል አንጻር እዚህ ግባ የማይባል ተራ ሰው መሆኑን ለማሳየት ወይም በሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ከሚያዝያ 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 20-22
“ጥሩ ጓደኛ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?”
መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ወዳጅነታችሁን አጠናክሩ
18 በዛሬው ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ አደጋዎች የተነሳ ችግር ደርሶባቸዋል። እንዲህ ያሉ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት አንዳንዶቻችን እነዚህን ወንድሞቻችንን ቤታችን ማሳረፍ እንችል ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉ ይሆናል። ሁላችንም ልናደርገው የምንችለው ሌላ ነገር ደግሞ ይሖዋ፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዲረዳቸው መጠየቅ ነው። በሌላ በኩል አንድ ወንድማችን ወይም አንዲት እህታችን ተስፋ እንደቆረጡ አስተውለን ይሆናል፤ ይሁንና ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ይገባን ይሆናል። ሆኖም ሁላችንም እርዳታ ማበርከት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ችግር ከገጠመው ወንድማችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንችላለን። ወንድማችን ሲናገር አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ማዳመጥ እንችላለን። የምንወደውን የሚያጽናና ጥቅስ ልንነግረውም እንችላለን። (ኢሳ. 50:4) ዋናው ነገር ወዳጆቻችን የእኛ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ከጎናቸው መሆናችን ነው።—ምሳሌ 17:17ን አንብብ።
በይሖዋ መንገድ ሂድ
7 አምላክ እምነት የሚጣልብን ወዳጅ እንድንሆን ይጠብቅብናል። (ምሳሌ 17:17) የንጉሥ ሳኦል ልጅ የሆነው ዮናታን የዳዊት ወዳጅ ነበር። ዮናታን፣ ዳዊት ጎልያድን መግደሉን ሲሰማ ምን እንደተሰማው መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቈራኘች፤ እንደራሱም አድርጎ ወደደው” ይላል። (1 ሳሙ. 18:1, 3) ሌላው ቀርቶ ዮናታን፣ ሳኦል ዳዊትን ሊገድለው እንደሚፈልግ ባወቀ ጊዜ ሁኔታውን በመንገር አስጠንቅቆታል። ዳዊት ከሸሸ በኋላ ዮናታን ከዳዊት ጋር በመገናኘት ቃል ኪዳን አድርጓል። ዮናታን ለሳኦል ስለ ዳዊት መናገሩ ሕይወቱን ሊያሳጣው የነበረ ቢሆንም ሁለቱ ጓደኛሞች በድጋሚ ተገናኝተው ወዳጅነታቸውን አድሰዋል። (1 ሳሙ. 20:24-41) ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት ወቅትም ዮናታን ዳዊትን ‘በአምላክ ስም’ አበረታቶታል።—1 ሳሙ. 23:16-18
ፍቅር በጠፋበት ዓለም ውስጥ ወዳጅነትን ጠብቆ መኖር
11 ታማኝ ሁን። ሰለሞን “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 17:17) ሰለሞን ይህን ሐሳብ ሲጽፍ አባቱ ዳዊት ከዮናታን ጋር የነበረውን ወዳጅነት በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። (1 ሳሙ. 18:1) ንጉሥ ሳኦል ልጁ ዮናታን የእስራኤልን ዙፋን እንዲወርስ ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለዚህ መብት የመረጠው ዳዊትን እንደሆነ ዮናታን ተገንዝቦ ነበር። ዮናታን እንደ ሳኦል በዳዊት አልቀናም። ዳዊት ክብር በማግኘቱ አልተበሳጨም ወይም ሳኦል ስለ ዳዊት የነገረውን የሐሰት ወሬ አላመነም። (1 ሳሙ. 20:24-34) እኛስ እንደ ዮናታን ነን? ወዳጆቻችን በጉባኤ ውስጥ መብት ሲያገኙ እንደሰታለን? መከራ ሲያጋጥማቸው እናጽናናቸዋለን እንዲሁም እንደግፋቸዋለን? ስለ ወዳጃችን መጥፎ ነገር ብንሰማ ነገሩን ሳናጣራ የሰማነውን እናምናለን? ወይስ እንደ ዮናታን በታማኝነት ከወዳጃችን ጎን እንቆማለን?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
21:12, 13፦ ይሖዋ በሕይወት ውስጥ የሚያጋ ጥሙንን ችግሮች ለመወጣት፣ በማሰብ ችሎታችንና ባለን ተሰጥኦ እንድንጠቀም ይጠብቅብናል። ማስተዋል፣ እውቀትና ልባምነትን ወይም የማሰብ ችሎታን ማግኘት እንድንችል በመንፈሱ ያስጻፈውን ቃሉን ሰጥቶናል። (ምሳሌ 1:4) ከዚህም በላይ ከክርስቲያን ሽማግሌዎች እርዳታ ማግኘት እንችላለን።
ከሚያዝያ 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 23-24
“ይሖዋን በትዕግሥት ጠብቁ”
በሕይወታችሁ የሚያጋጥሟችሁን ለውጦች ለመቋቋም በአምላክ መንፈስ ታመኑ
8 ዳዊት በሳኦል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ፈቃደኛ አልሆነም። እምነትና ትዕግሥት በማሳየት ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ለመተው መርጧል። ንጉሡ ከዋሻው ወጥቶ ከሄደ በኋላ ዳዊት ተጣርቶ እንዲህ አለው፦ “እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ። ክፉ ስላደረግህብኝ እግዚአብሔር ይበቀልህ እንጂ፣ እጄስ በአንተ ላይ አትሆንም።” (1 ሳሙኤል 24:12) ምንም እንኳ ሳኦል ጥፋተኛ መሆኑን ዳዊት ቢያውቅም በገዛ እጁ አልተበቀለውም እንዲሁም የስድብ ቃል አልሰነዘረበትም ወይም ከኋላው ክፉ ቃል አልተናገረም። በሌሎች በርካታ አጋጣሚዎችም ዳዊት በገዛ እጁ የበቀል እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቧል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለጉዳዩ መፍትሄ እንዲያመጣ በእርሱ ተማምኗል።—1 ሳሙኤል 25:32-34፤ 26:10, 11
ያለህበት ሁኔታ ሕይወትህን እንዲቆጣጠር አትፍቀድ
ከዮሴፍና ከዳዊት ተሞክሮ የምናገኘው ሦስተኛው ትምህርት ደግሞ ያለንበትን ሁኔታ ለመለወጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ መንገድ ከመጠቀም ይልቅ ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ምንም የማይጐድላችሁ ፍጹማንና ምሉአን እንድትሆኑ ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:4) ትዕግሥት ‘ሥራውን እንዲፈጽም’ ከፈለግን ከችግሩ ቶሎ ለመገላገል ስንል ቅዱስ ጽሑፋዊ ወዳልሆኑ መንገዶች ዞር ከማለት ይልቅ እስከመጨረሻው መጽናት ይኖርብናል። በዚህ መንገድ እምነታችን የሚፈተንና የሚጣራ ከመሆኑም በላይ ጥንካሬው ይታያል። ዮሴፍና ዳዊት እንዲህ ያለ ትዕግሥት አሳይተዋል። ይሖዋን ሊያሳዝን በሚችል መንገድ ለችግሩ የራሳቸውን መፍትሔ ለማምጣት አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ ያጋጠማቸውን ሁኔታ ለመቀበል ጥረት አድርገዋል። ይሖዋን በትዕግሥት የጠበቁ ሲሆን እንዲህ በማድረጋቸውም በእጅጉ ተባርከዋል! ይሖዋ ዮሴፍንም ሆነ ዳዊትን ሕዝቦቹን ነጻ ለማውጣትና ለመምራት ተጠቅሞባቸዋል።—ዘፍጥረት 41:39-41፤ 45:5፤ 2 ሳሙኤል 5:4, 5
እኛም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መፍትሔዎችን እንድንሞክር የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ እስከ አሁን ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ባለማግኘትህ አዝነሃል? ከሆነ ይሖዋ ‘በጌታ ብቻ’ እንድታገባ የሰጠውን ትእዛዝ እንድትጥስ ከሚያደርግ ከማንኛውም ፈታኝ ሁኔታ ራቅ። (1 ቆሮንቶስ 7:39) በትዳርህ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች አጋጥመውሃል? ተለያይቶ መኖርንና ፍቺን በሚያበረታታው በዚህ ዓለም መንፈስ ተጽእኖ ከምትሸነፍ ይልቅ ችግሩን ከትዳር ጓደኛህ ጋር ለመፍታት ጥረት አድርግ። (ሚልክያስ 2:16፤ ኤፌሶን 5:21-33) በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ቤተሰብህን ማስተዳደር አስቸጋሪ ሆኖብሃል? ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ ገንዘብ ለማግኘት አጠያያቂ ወይም ሕገ ወጥ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ከመሳተፍ መቆጠብንም ይጨምራል። (መዝሙር 37:25፤ ዕብራውያን 13:18) አዎን፣ ሁላችንም ያለንበትን ሁኔታ ለበጎ ለመጠቀም መትጋትና የይሖዋን በረከት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ይሖዋን በትዕግሥት በመጠባበቅ ትክክለኛውን መፍትሔ ማግኘት ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።—ሚክያስ 7:7
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ማንኛውም ነገር ሽልማቱን እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ
11 ልባችን በፍቅርና በደግነት እንዲሞላ ካደረግን በሌሎች ላይ ቶሎ ቅናት አያድርብንም። የአምላክ ቃል “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም” ይላል። (1 ቆሮ. 13:4) ቅናት በልባችን ውስጥ ሥር እንዳይሰድ ለመከላከል የአምላክ ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን ይጠቅመናል፤ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የአንድ አካል ክፍሎች እንደሆንን ይኸውም ሁላችንም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እንደሆንን ማስታወስ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን “አንድ የአካል ክፍል ክብር ቢያገኝ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይደሰታሉ” ከሚለው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ ራሳችንን በሌሎች ቦታ እንድናስቀምጥ ይረዳናል። (1 ቆሮ. 12:16-18, 26) እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለን ሌሎች ባገኙት በረከት ከመቅናት ይልቅ አብረናቸው እንደሰታለን። የንጉሥ ሳኦል ልጅ የሆነውን የዮናታንን ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት ንጉሥ ሆኖ በመቀባቱ ዮናታን ቅናት አላደረበትም። እንዲያውም ዳዊትን አበረታቶታል። (1 ሳሙ. 23:16-18) እኛስ እንደ ዮናታን ደግና አፍቃሪ መሆን እንችላለን?
ከሚያዝያ 25–ግንቦት 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ሳሙኤል 25-26
“በስሜታዊነት እርምጃ ትወስዳላችሁ?”
አስተዋይነት የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዳለች
10 ታታሪ የነበሩት የዳዊት ወታደሮች ከእረኞቹ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስላል? የዳዊት ወታደሮች በፈለጉት ጊዜ ከናባል መንጋ በጎችን መዝረፍ ይችሉ ነበር፤ እነሱ ግን እንዲህ አላደረጉም። እንዲያውም እንደ አጥር በመሆን የናባ ልን መንጎችና እረኞች ከጥቃት ጠብቀዋቸዋል። (1 ሳሙኤል 25:15, 16ን አንብብ።) በጎችም ሆኑ እረኞች ለአደጋ የተጋለጡ ነበሩ። በአካባቢው አውሬዎች በብዛት ይገኙ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ቦታው ለእስራኤል ደቡባዊ ድንበር ቅርብ በመሆኑ ከባዕድ አገር የሚመጡ ወንበዴዎችና ዘራፊዎች ብዙ ጊዜ ጥቃት ይሰነዝሩ ነበር።
11 ዳዊት በዚያ ምድረ በዳ እነዚያን ሁሉ ሰዎች መመገብ ከባድ ሥራ እንደሚሆንበት ምንም ጥያቄ የለውም። በመሆኑም ዳዊት አንድ ቀን ናባል ምግብ እንዲሰጠው ለመጠየቅ አሥር መልእክተኞችን ላከ። ዳዊት ይህን ጥያቄ ያቀረበው ጥሩ ጊዜ መርጦ ነበር። ወቅቱ በጎች የሚሸለቱበት ሲሆን በዚህ የደስታ ጊዜ ደግሞ ድግስ መደገስና ለሌሎች ልግስና ማሳየት የተለመደ ነበር። በተጨማሪም ዳዊት ጥያቄውን ያቀረበው በትሕትና እና በአክብሮት ነበር። እንዲያውም ራሱን ያስተዋወቀው ‘ልጅህ ዳዊት’ በማለት ሲሆን ምናልባትም ይህን ያለው በዕድሜ ለሚበልጠው ለናባል አክብሮት እንዳለው ለማሳየት ሊሆን ይችላል። ታዲያ ናባል፣ ዳዊት ላቀረበለት ጥያቄ ምን ምላሽ ሰጠ?—1 ሳሙ. 25:5-8
12 ናባል የዳዊትን መልእክት ሲሰማ በጣም ተቆጣ! በመግቢያው ላይ የጠቀስነው ወጣት በወቅቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ለአቢግያ ሲነግራት፣ ናባል በመልእክተኞቹ ላይ ‘የስድብ ናዳ እንዳወረደባቸው’ ገልጾ ነበር። ስስታም የሆነው ናባል እንጀራውን፣ ውኃውንና ያረደውን ፍሪዳ ለማንም እንደማይሰጥ በቁጣ ገለጸ። ዳዊትን እንደማይረባ ሰው በመቁጠር ያፌዘበት ከመሆኑም ሌላ ከጌታው እንደኮበለለ አገልጋይ አድርጎ ተመልክቶታል። ናባል የነበረው አመለካከት ዳዊትን ይጠላው ከነበረው ከሳኦል የተለየ አልነበረም ማለት ይቻላል። ሁለቱም ቢሆኑ ይሖዋ ለዳዊት ያለው ዓይነት አመለካከት አልነበራቸውም። አምላክ፣ ዳዊትን ይወደው የነበረ ከመሆኑም ሌላ እንደ አንድ ዓመፀኛ ባሪያ ሳይሆን የእስራኤል የወደፊት ንጉሥ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተው ነበር።—1 ሳሙ. 25:10, 11, 14
አስተዋይነት የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዳለች
18 አቢግያ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን ራሷ በመውሰድ ዳዊት ይቅርታ እንዲያደርግላት ጠየቀችው። አቢግያ ባሏ ልክ እንደ ስሙ የማይረባ ሰው መሆኑን አምና መቀበሏን የገለጸች ሲሆን ምናልባትም ይህን ያደረገችው ዳዊት እንዲህ ያለውን ሰው መቅጣቱ ክብሩን ዝቅ እንደሚያደርገው ለመጠቆም ብላ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ዳዊት የሚዋጋው ‘የይሖዋን ጦርነት’ እንደሆነ በመግለጽ የይሖዋ ወኪል መሆኑን እንደምታምን አሳይታለች። አምላክ፣ ዳዊትን ‘በእስራኤል ላይ እንደሚያነግሠው’ መናገሯም ይሖዋ ዳዊትንም ሆነ ንግሥናውን በተመለከተ የገባውን ቃል እንደምታውቅ የሚጠቁም ነው። በተጨማሪም ዳዊት በደም ዕዳ ሊያስጠይቀው ወይም በኋላ ላይ ‘ለሐዘን’ ሊዳርገው ማለትም የሕሊና ጸጸት ሊያስከትልበት የሚችል ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳይወስድ ለምናዋለች። (1 ሳሙኤል 25:24-31ን አንብብ።) በእርግጥም አቢግያ የተናገረችው ሐሳብ ደግነት የተንጸባረቀበትና ልብ የሚነካ ነበር!
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
አስተዋይነት የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዳለች
16 አቢግያ እንዲህ ማድረጓ የባሏን የራስነት ሥልጣን እንደማታከብር የሚያሳይ ነው? በፍጹም። ናባል፣ ይሖዋ በቀባው ሰው ላይ ክፉ ድርጊት የፈጸመ ሲሆን ይህም ምንም ያላጠፉ በርካታ የናባል ቤተሰብ አባላት እንዲገደሉ ሊያደርግ እንደሚችል መዘንጋት የለብንም። አቢግያ እርምጃ ሳትወስድ ብትቀር ኖሮ ከባሏ ጋር ተባባሪ እንደሆነች አያስቆጥራትም ነበር? በዚህ ጊዜ ለአምላክ የምታሳየው ተገዢነት ለባሏ ከምታሳየው ተገዢነት መቅደም ነበረበት።