የአንባብያን ጥያቄዎች
• በኢሳይያስ 14:12 ላይ የሚገኘው “አጥቢያ ኮከብ” የሚለው መግለጫ የሚያመለክተው ማንን ነው?
ኢሳይያስ 14:12 “አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፣ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ!” ይላል። አንዳንዶች ይህ አጥቢያ ኮከብ የሚለው መግለጫ ሰይጣንን እንደሚያመለክት አድርገው ያስባሉ።
እዚህ ላይ የተጠቀሰው አጥቢያ ኮከብ ማን ነው? “አጥቢያ ኮከብ” የሚለው መግለጫ እስራኤላውያን በባቢሎን ንጉሥ ላይ እንዲናገሩት ኢሳይያስ በትንቢት ባዘዛቸው ምሳሌ ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም በባቢሎናውያን ሥርወ መንግሥት ላይ በተነገረው ምሳሌያዊ መግለጫ ውስጥ የሚገኝ አባባል ነው። እንዲሁም ‘ወደ ሲኦል ትወርዳለህ’ የሚለው ሐረግ “አጥቢያ ኮከብ” የሚለው መግለጫ ለሰው እንጂ ለመንፈሳዊ ፍጥረት እንዳልተሰጠ ያመለክታል። ሲኦል ሰይጣን ዲያብሎስ የሚኖርበት ቦታ ሳይሆን የሰው ልጅ የጋራ መቃብር ነው። በተጨማሪም አጥቢያ ኮከቡ ወደዚህ ቦታ ሲወርድ የሚመለከቱት ሰዎች ‘በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፣ . . . ሰው ይህ ነውን?’ ብለው ይጠይቃሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አጥቢያ ኮከብ የሚለው መግለጫ የሚያመለክተው ሰውን እንጂ መንፈሳዊ ፍጡርን አይደለም።—ኢሳይያስ 14:4, 15, 16, 17
ለባቢሎናውያኑ ሥርወ መንግሥት ይሄን የመሰለ የተጋነነ መግለጫ የተሰጠው ለምንድን ነው? አጥቢያ ኮከብ የሚለው መግለጫ ለባቢሎን ንጉሥ የሚሰጠው ከውድቀቱ በኋላ እንደሆነና ይህም በፌዝ መልክ የተነገረ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። (ኢሳይያስ 14:3) የባቢሎን ነገሥታት በማን አለብኝነት ተነሳስተው ራሳቸውን በዙሪያቸው ካሉት በላይ ከፍ ከፍ አድርገው ነበር። ሥርወ መንግሥቱ ያሳየው እብሪት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ “ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፣ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፣ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ . . . በልዑልም እመሰላለሁ” እያለ ጉራውን እንደነዛ ተደርጎ ተገልጿል።—ኢሳይያስ 14:13, 14
‘የእግዚአብሔር ከዋክብት’ በዳዊት የንግሥና መስመር የሚመጡት ነገሥታት ናቸው። (ዘኍልቍ 24:17) ከዳዊት ዘመን ጀምሮ እነዚህ “ከዋክብት” መቀመጫቸውን በጽዮን ተራራ አድርገው ይገዙ ነበር። ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደሱን ከሠራ በኋላ ግን ጽዮን የሚለው ስም መላውን ከተማ ማመልከት ጀመረ። በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት እያንዳንዱ እስራኤላዊ ወንድ በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ጽዮን የመውጣት ግዴታ ነበረበት። በዚህ ምክንያት ይህ ሥፍራ “መሰብሰቢያ ተራራ” ተባለ። ናቡከደነፆር የይሁዳን ነገሥታት ድል ለማድረግና ከዚያ ተራራ ላይ ለማፈናቀል ሲነሳ ራሱን ከእነዚህ “ከዋክብት” በላይ የማድረግ ፍላጎቱን እያሳወቀ ነበር። በእነዚህ ነገሥታት ላይ ለተገኘው ድል ምስጋናውን ለይሖዋ ከመስጠት ይልቅ በትዕቢት ራሱን በይሖዋ ቦታ አስቀመጠ። ስለዚህ የባቢሎናውያኑ ሥርወ መንግስት “አጥቢያ ኮከብ” እየተባለ በፌዝ የተጠራው ከውድቀቱ በኋላ ነው።
እርግጥ ነው፣ የባቢሎን ገዢዎች ያሳዩት ትዕቢት “የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነውን የሰይጣን ዲያብሎስን ዝንባሌ የሚያንጸባርቅ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እርሱም ለሥልጣን የሚቋምጥ ሲሆን ራሱን ከይሖዋ አምላክ በላይ ለማድረግ ይጓጓል። ሆኖም አጥቢያ ኮከብ ለሰይጣን የተሰጠው ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም አይደለም።
• አንደኛ ዜና መዋዕል 2:13-15 ዳዊት የእሰይ ሰባተኛ ልጅ እንደሆነ ሲናገር 1 ሳሙኤል 16:10, 11 ደግሞ ስምንተኛ ልጅ እንደሆነ አድርጎ የሚናገረው ለምንድን ነው?
የጥንቱ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል ከእውነተኛው አምልኮ ዞር ባለበት ወቅት ይሖዋ አምላክ ከእሴይ ልጆች መሃል አንደኛውን ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው ነቢዩ ሳሙኤልን ላከው። ሳሙኤል ራሱ በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው የዚህ ታሪክ ዘገባ ዳዊት የእሴይ ስምንተኛ ልጅ እንደሆነ ያመለክታል። (1 ሳሙኤል 16:10-13) ሆኖም 600 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ካህኑ ዕዝራ የጻፈው ዘገባ “እሴይም የበኩር ልጁን ኤልያብን፣ ሁለተኛውንም አሚናዳብን፣ ሦስተኛውንም ሣማን፣ አራተኛውንም ናትናኤልን፣ አምስተኛውንም ራዳይን፣ ስድስተኛውንም አሳምን፣ ሰባተኛውንም ዳዊትን ወለደ” ይላል። (1 ዜና መዋዕል 2:13-15) አንደኛው የዳዊት ወንድም በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተተውና ዕዝራ ስሙን ሳይጠቅስ ያለፈው ለምንድን ነው?
ቅዱሳን ጽሑፎች እሴይ ‘ስምንት ልጆች እንደነበሩት’ ይናገራሉ። (1 ሳሙኤል 17:12) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው አንደኛው ልጁ አድጎ ትዳር ለመያዝና ልጆች ለመውለድ አልበቃም። ዘር ባለመተካቱ ምክንያት የነገድ ውርሻ አይኖረውም፤ እንዲሁም የእሴይን የትውልድ መስመር በሚናገረው የዘር ግንድ ውስጥ አልተጠቀሰም።
አሁን እስቲ ስለ ዕዝራ ዘመን እናስብ። የዜና መዋዕል መጽሐፍ የተጻፈበትን መቼት መለስ ብለን ለማየት እንሞክር። አይሁዳውያን በባቢሎን ያሳለፉት የግዞት ዓመታት ካበቃ 77 የሚያህሉ ዓመታት ያለፉ ሲሆን አሁን የሚኖሩት ምድራቸው ላይ ነው። ዕዝራ መሳፍንትንና የአምላክን ሕግ የሚያስተምሩ ሰዎችን እንዲሾምና የይሖዋን ቤት እንዲያድስ ከፋርስ ንጉሥ ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። የነገዶቹን ውርሻ በትክክል ለማረጋገጥና በክህንነቱ የሚያገለግሉት መብቱ ያላቸው ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ለመከታተል ትክክለኛ የዘር ሐረግ መገኘት አስፈላጊ ነበር። ስለዚህ ዕዝራ የይሁዳንና የዳዊትን የዘር መሥመር የያዘ ትክክለኛና አስተማማኝ ዝርዝር ጨምሮ የሕዝቡን የተሟላ ታሪክ የያዘ ዘገባ አዘጋጀ። በዚህ ዘገባ ውስጥ ልጅ ሳይወልድ የሞተውን የእሴይን ልጅ ስም መጥቀሱ አስፈላጊ አልነበረም። በመሆኑም ዕዝራ ስሙን አስቀረው።