ምዕራፍ ስድስት
ለአምላክ የልቧን አውጥታ ነገረችው
1, 2. (ሀ) ሐና ለጉዞ እየተዘጋጀች በነበረበት ወቅት ደስተኛ ያልነበረችው ለምንድን ነው? (ለ) ከሐና ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
ሐና ለጉዞ በሚደረጉት መሰናዶዎች ራሷን በማስጠመድ ችግሯን ለመርሳት እየሞከረች ነው። በመሠረቱ ወቅቱ የደስታ ጊዜ ሊሆን ይገባ ነበር፤ ባሏ ሕልቃና በሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን አምልኮ ለማቅረብ በየዓመቱ መላ ቤተሰቡን ይዞ ወደዚያ የመሄድ ልማድ ነበረው። ይሖዋ እንዲህ ያሉት ወቅቶች ሕዝቡ የሚደሰትባቸው እንዲሆኑ ይፈልግ ነበር። (ዘዳግም 16:15ን አንብብ።) ሐናም ከልጅነቷ ጀምሮ በእነዚህ በዓላት ላይ መገኘት ያስደስታት እንደነበር ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቀድሞው ደስታዋ ጠፍቷል።
2 ሐና የሚወዳት ባል በማግኘቷ ተባርካለች። ይሁን እንጂ ሕልቃና ሌላም ሚስት ነበረችው። ፍናና የምትባለው ይህች ሴት ሐናን በሕይወቷ እንድትመረር ለማድረግ ቆርጣ የተነሳች ትመስላለች። ፍናና በየዓመቱ በሚከበሩት በእነዚህ በዓላት ወቅትም እንኳ ሳይቀር ሐናን የምታበሳጭበትን መንገድ ትፈልግ ነበር። ለመሆኑ ይህን የምታደርገው እንዴት ነበር? ሐናስ በይሖዋ ላይ ያላት እምነት ከአቅሟ በላይ የሆነባትን ከባድ ችግር እንድትቋቋም የረዳት እንዴት ነው? አንተም ደስታህን የሚያሳጣ ችግር አጋጥሞህ ከሆነ የሐናን ታሪክ ማንበብህ እንደሚያበረታታህ ጥርጥር የለውም።
‘ልብሽ ለምን ያዝናል?’
3, 4. ሐና ምን ሁለት ከባድ ችግሮች አጋጥመዋት ነበር? እነዚህን ችግሮች ይበልጥ ያከበደባትስ ምንድን ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ ሐና በሕይወቷ ውስጥ ሁለት ከባድ ችግሮች እንደነበሩባት ይገልጻል። የመጀመሪያውን ችግር ለማስተካከል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ማድረግ የምትችለው ነገር አለ፤ ሁለተኛው ችግር ግን ፈጽሞ ከቁጥጥሯ ውጭ ነበር። በመጀመሪያ፣ ባሏ ሌላ ሚስት የነበረችው ሲሆን እሷም ሐናን ትጠላት ነበር። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሐና መሃን ነበረች። መሃንነት፣ ልጅ ወልዳ መሳም ለምትመኝ ለማንኛዋም ሚስት ከባድ ፈተና ነው፤ ሐና በኖረችበት ዘመን ከነበረው ባሕል አንጻር ደግሞ መሃንነት ለከፍተኛ ሐዘን ይዳርግ ነበር። ማንኛውም ቤተሰብ የዘር ሐረጉ እንዳይቋረጥ ስለሚፈልግ ልጅ ለመውለድ ይጓጓ ነበር። በመሆኑም መሃንነት የሚያዋርድና የሚያሳፍር ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።
4 ፍናና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ባትሆንባት ኖሮ ሐና ችግሯን በቻለችው ነበር። ከአንድ በላይ ማግባት ምንጊዜም ቢሆን በትዳር ውስጥ ችግር እንደሚያስከትል የታወቀ ነው። እንዲህ በመሰለው ትዳር ውስጥ ቅናት፣ ግጭትና ስሜት የሚያቆስል ነገር አይጠፋም። ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት አምላክ በኤደን ገነት ውስጥ ካቋቋመው አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ብቻ መጣመር እንዳለበት ከሚገልጸው የጋብቻ መሥፈርት ጋር ፈጽሞ አይጣጣምም። (ዘፍ. 2:24) መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት ያለውን መጥፎ ገጽታ የሚያሳዩ ዘገባዎችን ይዟል፤ በሕልቃና ቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረው ሁኔታም ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው።
5. ፍናና ሐናን አበሳዋን ታሳያት የነበረው ለምንድን ነው? ይህን ታደርግስ የነበረው እንዴት ነው?
5 ሕልቃና ሐናን አብልጦ ይወዳት ነበር። የአይሁዳውያን አፈ ታሪክ እንደሚገልጸው ከሆነ ሕልቃና መጀመሪያ ያገባው ሐናን ሲሆን ፍናናን ያገባው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ነው። ያም ሆነ ይህ በሐና በጣም የምትቀናው ፍናና ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ጣውንቷን አበሳዋን ታሳያት ነበር። ፍናና ሐናን የምትበልጥበት ትልቁ ነገር ልጅ መውለድ መቻሏ ነው። ፍናና እያከታተለች ትወልድ የነበረ ሲሆን የልጆቿ ቁጥር በጨመረ መጠን ይበልጥ ተፈላጊ እንደሆነች ይሰማት ነበር። ለሐና ልታዝንላትና መጽናኛ ልትሆናት ሲገባ ቁስሏን በመነካካት ታበሳጫት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ፍናና ሐናን “ታስቈጣት፣ ታበሳጫትም ነበር” በማለት ይገልጻል። (1 ሳሙ. 1:6) ፍናና ይህን ታደርግ የነበረው ሆን ብላ ነው። ሐናን ማሠቃየት ትፈልግ ነበር፤ ይህም ደግሞ ተሳክቶላታል።
6, 7. (ሀ) ሕልቃና ሐናን ሊያጽናናት ቢሞክርም እሷ ግን የተፈጠረውን ነገር ግልጥልጥ አድርጋ ከመናገር የተቆጠበችው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ሐና መሃን መሆኗ ይሖዋ እንዳልተደሰተባት የሚያሳይ ነው? አብራራ። (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
6 ፍናና ሐናን ለማበሳጨት በጣም ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ያገኘችው በየዓመቱ ለአምልኮ ወደ ሴሎ የሚሄዱበትን ጊዜ ይመስላል። ሕልቃና ለፍናና ‘ወንዶችና ሴቶች ልጆች ሁሉ’ ለይሖዋ ከቀረበው መሥዋዕት ላይ ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር። በጣም ለሚወዳት ለሐና ግን የተለየ ድርሻ ይሰጣታል። በዚህ ጊዜ ቅናት ያደረባት ፍናና ሐናን እንደምትበልጣት ለማሳየት ትጥር እንዲሁም የሐናን መሃንነት እያነሳች በነገር ትወጋት ነበር፤ በዚህም ምክንያት ይህች ምስኪን ሴት ታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ትበሳጭ ነበር። ሕልቃና የሚወዳት ሚስቱ ሐና እንዳዘነችና መብላት እንዳቃታት አስተውሎ መሆን አለበት፤ በመሆኑም እንዲህ በማለት ሊያጽናናት ሞከረ፦ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?”—1 ሳሙ. 1:4-8
7 ሕልቃና፣ ሐና ያዘነችው መሃን በመሆኗ ምክንያት መሆኑን ማስተዋሉ የሚያስመሰግነው ነው። ሐና፣ ሕልቃና እሷን እንደሚወዳት በመግለጽ የተናገረውን ደግነት የተሞላበት ሐሳብ ከፍ አድርጋ እንደተመለከተችው ምንም ጥርጥር የለውም።a ይሁን እንጂ ሕልቃና ፍናና እየፈጸመችው ስላለው የክፋት ድርጊት የጠቀሰው ነገር የለም፤ ሐናም ብትሆን ስለ ሁኔታው ትንገረው አትንገረው መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። ምናልባት ሐና፣ የፍናናን ክፋት ማጋለጧ ያለችበትን ሁኔታ እንደሚያባብሰው ተገንዝባ ይሆናል። ሕልቃና ሁኔታውን ለመለወጥ ምን ማድረግ ይችላል? ደግሞስ ሐና ስለ ሁኔታው መናገሯ ፍናና በእሷ ላይ የምትፈጽመው የክፋት ድርጊት እንዲብስ እንዲሁም የዚህች ክፉ ሴት ልጆችና አገልጋዮች ጭምር ተባብረው እንዲነሱባት ከማድረግ ውጭ ምን የሚፈይደው ነገር ይኖራል? ሐና በገዛ ቤቷ ውስጥ ይበልጥ ባይተዋርነት እንዲሰማት ከማድረግ በቀር የሚያስገኘው ጥቅም አይኖርም።
ሐና በቤት ውስጥ ግፍ ይፈጸምባት በነበረበት ወቅት መጽናኛ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ብላለች
8. ተንኮል የተሞላበት ወይም ኢፍትሐዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጸምብህ ይሖዋ የፍትሕ አምላክ መሆኑን ማስታወስህ የሚያጽናናህ እንዴት ነው?
8 ሕልቃና የፍናና ክፋት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይወቅም አይወቅ፣ ይሖዋ ሁሉንም ነገር ተመልክቶት ነበር። ሁሉም ነገር በቃሉ ውስጥ በዝርዝር ሰፍሯል፤ ይህም በትንሹም ቢሆን የቅናትና የጥላቻ ስሜት ለሚያንጸባርቅ ለማንኛውም ሰው ከባድ ማስጠንቀቂያ ይዟል። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሐና ንጹሕና ሰላማዊ የሆነ ሰው የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ ነገሮችን እንደሚያስተካክል ማወቁ ሊያጽናናው ይችላል። (ዘዳግም 32:4ን አንብብ።) ሐናም ይህን ሳታውቅ አትቀርም፤ ምክንያቱም እርዳታ ለማግኘት ፊቷን ያዞረችው ወደ ይሖዋ ነበር።
“ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም”
9. ሐና ጣውንቷ ምን እንደምታደርግ እያወቀችም ወደ ሴሎ ለመጓዝ ፈቃደኛ መሆኗ ምን ያስተምረናል?
9 ገና በማለዳው ቤተሰቡ ሽር ጉድ እያለ ነው። መላው ቤተሰብ፣ ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ ለጉዞው እየተዘጋጁ ነው። ይህ ትልቅ ቤተሰብ ሴሎ ለመድረስ አቀበት ቁልቁለት የሚበዛውን የኤፍሬምን ምድር አቋርጦ ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ነበረበት።b ጉዞው በእግር አንድ ወይም ሁለት ቀን ይፈጃል። ሐና፣ በዚህ ወቅት ጣውንቷ ምን እንደምታደርግ አሳምራ ታውቃለች። ይሁንና አብራ ከመጓዝ ይልቅ ቤት ብትቀር እንደሚሻል አልተሰማትም። በዚህ መንገድ በዛሬው ጊዜ ላሉት የአምላክ አገልጋዮች ግሩም ምሳሌ ትታለች። ሌሎች የሚፈጽሙት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ለአምላክ የምናቀርበውን አምልኮ እንዲነካብን መፍቀድ ፈጽሞ ጥበብ አይደለም። እንዲህ ማድረጋችን ያለንበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም በሚያስችሉን ዝግጅቶች እንዳንጠቀም እንቅፋት ይሆንብናል።
10, 11. (ሀ) ሐና ወዲያውኑ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ የሄደችው ለምንድን ነው? (ለ) ሐና በጸሎት አማካኝነት በሰማይ ላለው አባቷ የልቧን ያፈሰሰችው እንዴት ነው?
10 ቤተሰቡ አቀበታማ በሆኑት ጠመዝማዛ መንገዶች ላይ ሙሉ ቀን ሲጓዝ ከዋለ በኋላ ወደ ሴሎ ተቃረበ። እዚያም በሌሎች ከፍ ያሉ ኮረብታዎች በተከበበ አንድ ኮረብታ ላይ አረፍ አለ። ወደ ሴሎ እየተጠጉ ሲሄዱ ሐና ለይሖዋ በጸሎት ምን እንደምትነግረው ብዙ ሳታስብበት አልቀረችም። እዚያ እንደደረሱም ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ ምግብ በላ። ከዚያም ሐና ወዲያውኑ ከቤተሰቡ ተነጥላ ወደ ይሖዋ የማደሪያ ድንኳን አመራች። ሊቀ ካህናቱ ዔሊ በቤተ መቅደሱ መቃን አጠገብ ተቀምጦ ነበር። ይሁን እንጂ ሐና ትኩረት ያደረገችው ለአምላኳ በምታቀርበው ጸሎት ላይ ነበር። በአምላክ የማደሪያ ድንኳን ሆና የምታቀርበው ጸሎት ተሰሚነት እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነበረች። ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ ማንም ሙሉ በሙሉ ሊረዳላት ባይችልም እንኳ በሰማይ ያለው አባቷ እንደሚረዳላት የታወቀ ነው። በልቧ ውስጥ አምቃ የያዘችው ምሬት ፈንቅሏት ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ጀመረች።
11 ሐና ተንሰቅስቃ እያለቀሰች በልቧ ወደ ይሖዋ ስትጸልይ ሰውነቷ ይንዘፈዘፍ ነበር። በውስጧ ያለውን ብሶት ለይሖዋ በምትገልጽበት ጊዜ ከንፈሮቿ ይንቀጠቀጡ ነበር። በሰማይ ላለው አባቷ የልቧን በማፍሰስ ረጅም ጸሎት አቀረበች። ይሁንና አምላክ በጣም የጓጓችለትን ነገር ይኸውም ልጅ የመውለድ ፍላጎቷን እንዲያሟላላት በመጠየቅ ብቻ አልተወሰነችም። ሐና ከአምላክ በረከት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ ለአምላክ ለመስጠትም ትጓጓ ነበር። ስለዚህ ወንድ ልጅ ከወለደች ልጁ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ይሖዋን እንዲያገለግል እንደምትሰጠው ተሳለች።—1 ሳሙ. 1:9-11
12. ሐና ከተወችው ምሳሌ ማየት እንደሚቻለው ጸሎትን በተመለከተ ምን ነገር ማስታወስ ይገባናል?
12 በዚህ መንገድ ሐና ጸሎትን በተመለከተ ለአምላክ አገልጋዮች ሁሉ ምሳሌ መሆን ችላለች። አንድ ልጅ አፍቃሪ ለሆነው አባቱ እንደሚያደርገው ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦችም የሚያሳስባቸውን ነገር ሁሉ ያላንዳች ገደብ ግልጥልጥ አድርገው ለእሱ በመንገር ልባቸውን በፊቱ እንዲያፈሱ ይሖዋ በደግነት ጋብዟቸዋል። (መዝሙር 62:8ን እና 1 ተሰሎንቄ 5:17ን አንብብ።) ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ለይሖዋ የሚቀርብ ጸሎትን በተመለከተ የሚከተለውን አጽናኝ ሐሳብ በመንፈስ መሪነት ጽፏል፦ “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥ. 5:7
13, 14. (ሀ) ዔሊ፣ ሐናን በተመለከተ ቸኩሎ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ የደረሰው እንዴት ነው? (ለ) ሐና ለዔሊ መልስ የሰጠችበት መንገድ ግሩም የእምነት ምሳሌ ተደርጎ ሊታይ የሚችለው እንዴት ነው?
13 ሰዎች የይሖዋን ያህል የሌሎችን ስሜት እንደማይረዱ የታወቀ ነው። ሐና እያለቀሰች በምትጸልይበት ጊዜ አንድ ድምፅ አስደነገጣት። ሐናን ያናገራት ስትጸልይ ይመለከታት የነበረው ሊቀ ካህናቱ ዔሊ ነበር። እሱም “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” አላት። ዔሊ፣ ሐና ከንፈሯ ሲንቀጠቀጥና ተንሰቅስቃ ስታለቅስ የተመለከተ ከመሆኑም ሌላ ስሜቷ እንደተረበሸም አስተውሎ ነበር። ሆኖም ምን እንዳጋጠማት ከመጠየቅ ይልቅ ቸኩሎ ሰክራለች የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰ።—1 ሳሙ. 1:12-14
14 ሐና እንደዚያ ባዘነችበት ወቅት የተከበረ ቦታ ከነበረው ሰው እንዲህ ያለ መሠረተ ቢስ ውንጀላ ሲሰነዘርባት ስሜቷ ምን ያህል ተጎድቶ ይሆን! ያም ሆኖ ሐና በዚህ ወቅትም ለሌሎች ግሩም የእምነት ምሳሌ ትታለች። የአንድ ሰው አለፍጽምና ይሖዋን ከማምለክ ወደኋላ እንድትል እንዲያደርጋት አልፈቀደችም። ለዔሊ በአክብሮት መልስ የሰጠችው ሲሆን ስላለችበት ሁኔታም አስረዳችው። እሱም በድርጊቱ እንደተጸጸተ በሚያሳይ የለሰለሰ አንደበት ሳይሆን አይቀርም “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሺውን ይስጥሽ” አላት።—1 ሳሙ. 1:15-17
15, 16. (ሀ) ሐና የልቧን አውጥታ ለይሖዋ መንገሯና በማደሪያ ድንኳኑ አምልኮዋን ማቅረቧ ምን ውጤት አስገኘላት? (ለ) እኛም አፍራሽ ከሆኑ ስሜቶች ጋር በምንታገልበት ጊዜ ሐና የተወችውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
15 ሐና ለይሖዋ የልቧን አውጥታ መናገሯና በማደሪያ ድንኳኑ ለእሱ አምልኮ ማቅረቧ ምን ውጤት አስገኘ? ዘገባው “መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም” ይላል። (1 ሳሙ. 1:18) ሐና ጭንቀቷ ቀሎላት ነበር። እንደ ከባድ ሸክም ሆኖ ስሜቷን የደቆሳትን ነገር ከእሷ ይልቅ ኃያል በሆነው ሰማያዊ አባቷ ጫንቃ ላይ የጣለችው ያህል ነበር። (መዝሙር 55:22ን አንብብ።) ለይሖዋ ከአቅሙ በላይ የሚሆንበት ችግር ሊኖር ይችላል? በጭራሽ! ያኔም ሆነ አሁን ወይም ደግሞ ወደፊት ሊኖር አይችልም!
16 እኛም አንድ ነገር ሲያስጨንቀን፣ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ሲሰማን ወይም በሐዘን ስንዋጥ የሐናን ምሳሌ በመከተል መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጸሎት ሰሚ’ በማለት ለሚጠራው አምላክ የልባችንን አውጥተን መንገራችን መልካም ነው። (መዝ. 65:2) በእምነት እንዲህ ካደረግን እኛም ሐዘናችን ተወግዶ ‘ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ በሆነው የአምላክ ሰላም’ እንደተተካ ሊሰማን ይችላል።—ፊልጵ. 4:6, 7
“እንደ አምላካችን ያለ ዐለት የለም”
17, 18. (ሀ) ሕልቃና፣ ሐና የተሳለችውን ስእለት እንደሚደግፍ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ፍናና በሐና ላይ ምን መፈጸም እንደማትችል ተገነዘበች?
17 በማግስቱ ጠዋት ሐና ከሕልቃና ጋር ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ተመልሳ ሄደች። ሐና ስእለት እንደተሳለችና ይሖዋን ምን እንደለመነችው ለሕልቃና ሳትነግረው አልቀረችም፤ ምክንያቱም የሙሴ ሕግ አንድ ባል ሚስቱ እሱ ሳያውቅ የተሳለችውን ስእለት ሊሽረው እንደሚችል ይገልጻል። (ዘኍ. 30:10-15) ይሁን እንጂ ያ ታማኝ ሰው ስዕለቷን አልተቃወመም። ከዚህ ይልቅ እሱና ሐና ወደ ቤታቸው ከማቅናታቸው በፊት በማደሪያ ድንኳኑ አብረው አምልኳቸውን አቀረቡ።
18 ፍናና እንደ ቀድሞው ሐናን ማበሳጨት እንደማትችል የተገነዘበችው መቼ ይሆን? ዘገባው ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጸው ነገር ባይኖርም ስለ ሐና ሲናገር “ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም” ማለቱ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይበልጥ ደስተኛ እንደሆነች ያመለክታል። ያም ሆነ ይህ ፍናና፣ የክፋት ድርጊቷ ምንም ውጤት እንዳላስገኘ ወዲያው ተገነዘበች። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ በኋላ ስሟን አይጠቅስም።
19. ሐና ምን በረከት አገኘች? ይህን በረከት ያገኘችው ከየት እንደሆነ እንዳልዘነጋች ያሳየችውስ እንዴት ነው?
19 ወራት እያለፉ ሲሄዱ ሐና የአእምሮ ሰላም ከማግኘት ባለፈ ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆን የሚያደርግ ነገር ተከሰተ። ጸንሳ ነበር! ሐና በጣም ብትደሰትም ይህን በረከት ያገኘችው ከየት እንደሆነ ለአፍታ እንኳ አልዘነጋችም። ልጁ ሲወለድ ሳሙኤል ብላ ስም ያወጣችለት ሲሆን ትርጉሙ “የአምላክ ስም” ማለት ነው፤ ይህም ሐና ታደርግ እንደነበረው መለኮታዊውን ስም መጥራትን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። በዚያ ዓመት ሕልቃና ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሴሎ ሲሄድ ሐና አብራቸው አልሄደችም። ልጁ ጡት እስኪጥል ድረስ ለሦስት ዓመት ከቤት አልወጣችም። ከዚያ በኋላ ግን ከምትወደው ልጇ የምትለይበት ቀን እየደረሰ ስለሚመጣ ራሷን ማዘጋጀት ነበረባት።
20. ሐናና ሕልቃና ለይሖዋ የገቡትን ቃል የፈጸሙት እንዴት ነው?
20 ሐና ከልጇ መለየት ከብዷት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እርግጥ ነው፣ ሐና ሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉት አንዳንድ ሴቶች ለሳሙኤል ጥሩ እንክብካቤ ሊያደርጉለት እንደሚችሉ ታውቅ ነበር። ያም ሆኖ ሳሙኤል ገና ትንሽ ልጅ ነበር፤ ደግሞስ ከልጇ መነጠል የምትፈልግ የትኛዋ እናት ናት? የሆነ ሆኖ ሐናና ሕልቃና ልጁን ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ያመጡት ደስ ብሏቸው እንጂ እያዘኑ አልነበረም። እነሱም በቅድሚያ በአምላክ ቤት መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚያም ሐና ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የገባችውን ስእለት ለዔሊ ካስታወሱት በኋላ ሳሙኤልን አስረከቡት።
21. ሐና ወደ ይሖዋ ያቀረበችው ጸሎት እምነቷ ምን ያህል ጥልቅ እንደነበር የሚያሳየው እንዴት ነው? (በተጨማሪም “ሁለት ድንቅ ጸሎቶች” የሚል ርዕስ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
21 ሐና ከዚያ በኋላ ያቀረበችው ጸሎት አምላክ በመንፈስ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ እንዲካተት ፈቅዷል። በ1 ሳሙኤል 2:1-10 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሐናን ጸሎት ስታነብ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር እምነቷ ምን ያህል ጠንካራ እንደነበር እንድትገነዘብ ያስችልሃል። ሐና፣ ይሖዋ ኃይሉን ድንቅ በሆነ መንገድ እንደሚጠቀምበት ማለትም ትዕቢተኞችን ለማዋረድ፣ የተጨቆኑትን ለመባረክ እንዲሁም ሕይወትን ለማጥፋትም ሆነ ለማዳን እንደሚያውለው በመግለጽ አወድሳዋለች። በሰማይ ያለውን አባቷን አቻ ስለማይገኝለት ቅድስናው፣ ስለ ፍትሑና ስለ ታማኝነቱ አመስግናዋለች። ሐና “እንደ አምላካችን ያለ ዐለት የለም” ብላ ለመናገር የቻለችበት በቂ ምክንያት አላት። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበትና የማይለዋወጥ አምላክ ከመሆኑም ሌላ ለእርዳታ ወደ እሱ ፊታቸውን ለሚያዞሩ የተጨቆኑና በግፍ የተደቆሱ ሰዎች መጠጊያ ነው።
22, 23. (ሀ) ሳሙኤል የወላጆቹን ፍቅራዊ እንክብካቤ አግኝቶ እንዳደገ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ሐና ከይሖዋ ምን ተጨማሪ በረከት አግኝታለች?
22 ትንሹ ሳሙኤል በይሖዋ ላይ እንደዚህ ያለ እምነት ያላት እናት ስላለችው በእርግጥም ታድሏል። እርግጥ ነው፣ እያደገ ሲሄድ እናቱን መናፈቁ ባይቀርም እንደተረሳ ሆኖ ተሰምቶት ግን አያውቅም። ሐና በየዓመቱ ወደ ሴሎ ስትመጣ በማደሪያ ድንኳኑ ሲያገለግል የሚለብሰው ትንሽ መደረቢያ ታመጣለት ነበር። ሐና በገዛ እጇ እየሠራች የምታመጣለት ልብስ ልጇን ምን ያህል እንደምትወደውና እንደምታስብለት የሚያሳይ ማስረጃ ነበር። (1 ሳሙኤል 2:19ን አንብብ።) ያመጣችለትን አዲስ መደረቢያ ለልጇ ስታለብሰው፣ በእጇ ስታስተካክልለት እንዲሁም በፍቅር ዓይን እየተመለከተች ደግነት በሚንጸባረቅባቸውና በሚያበረታቱ ቃላት ስታነጋግረው በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን። ሳሙኤል እንዲህ ያለች እናት ስላለችው ተባርኳል፤ እሱም ካደገ በኋላ ለወላጆቹም ሆነ ለመላው እስራኤል በረከት ሆኗል።
23 ሐናም ብትሆን አልተረሳችም። ይሖዋ ሐናን ስለባረካት ለሕልቃና ሌሎች አምስት ልጆች ወለደችለት። (1 ሳሙ. 2:21) ይሁንና ሐና ያገኘችው ከሁሉ የላቀው በረከት በእሷና አባቷ በሆነው በይሖዋ መካከል ያለው ዝምድና ሳይሆን አይቀርም፤ ይህ ወዳጅነት ዓመታት እያለፉ በሄዱ ቁጥር እየተጠናከረ ሄዷል። አንተም ሐና እምነት በማሳየት ረገድ የተወችውን ምሳሌ በመከተል እንዲህ ዓይነት በረከት እንድታገኝ ምኞታችን ነው።
a ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘የሐናን ማሕፀን እንደዘጋ’ ቢናገርም አምላክ በዚህች ትሑትና ታማኝ ሴት እንዳልተደሰተባት የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። (1 ሳሙ. 1:5) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምላክ አንዳንድ ነገሮች እንዲከሰቱ ስለፈቀደ ብቻ እሱ እንደፈጸማቸው ተደርጎ የተገለጸባቸው ቦታዎች አሉ።
b ይህ ርቀት የተሰላው የሕልቃና የትውልድ ከተማ የሆነችው ራማ በኢየሱስ ዘመን አርማትያስ በመባል ትታወቅ የነበረችው ከተማ ሳትሆን እንደማትቀር ታስቦ ነው።