የሐሳብ ግንኙነት ሲባል መነጋገር ማለት ብቻ አይደለም
ውብ የሆነን መልክዓ ምድር በመቃኘት ላይ ያሉ ቱሪስቶችን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ሁሉም የሚያዩት አንድ ሥፍራን ቢሆንም እያንዳንዱ ሰው የሚመለከተው በተለያየ መንገድ ነው። ለምን? ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው የተለያየ የትኩረት አቅጣጫ አለው። ፍጹም አንድ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሁለት ሰዎች ሊኖሩ አይችሉም። ከዚህም በላይ ሁሉም ሰው በዕይታው አንድ ገጽታ ላይ አያተኩርም። እያንዳንዱ ሰው ይበልጥ ስሜቱን የሚመስጠው የተለያየ ገጽታ ይኖራል።
በጋብቻ ውስጥም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ሁለት የትዳር ጓደኛሞች አስተሳሰባቸው የቱንም ያህል የሚገጥም ቢሆን ፍጹም አንድ ዓይነት የሆነ አመለካከት ሊኖራቸው አይችልም። ባልና ሚስት በተፈጥሮ ባላቸው አስተሳሰብ፣ በልጅነታቸው ባሳለፉት ተሞክሮ፣ ቤተሰብ ባሳደረባቸው ተጽዕኖና በመሳሰሉት ነገሮች የተነሳ የተለያዩ ናቸው። የሚፈጠሩት የሐሳብ ልዩነቶች መራራ ለሆነ ጠብ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “የሚያገቡ ሰዎች መከራና ኀዘን አለባቸው” በማለት ሳይሸሽግ ገልጿል። — 1 ቆሮንቶስ 7:28 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል
የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ እነዚህን ልዩነቶች በማቻቻል እንደ አንድ ሥጋ ሆኖ ለመኖር የሚደረገውን ጥረት ይጨምራል። ይህ ለመነጋገር ጊዜ መመደብን ይጠይቃል። (ገጽ 7 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) ነገር ግን በዚህ ብቻ አያበቃም።
ጥልቅ ማስተዋልን ማሳየት
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ:- “የጥበበኛ ሰው ልብ አፉ ጥልቅ ማስተዋልን እንዲያሳይ ከንፈሮቹም የማግባባት ችሎታ እንዲኖራቸው ያደርጋል” ሲል ይገልጻል። (ምሳሌ 16:23 አዓት) ‘ጥልቅ ማስተዋልን እንዲያሳይ ያደርጋል’ ተብሎ የተተረጐመው የዕብራይስጥ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ አርቆ ማሰብ፣ ነገሮችን በአዕምሮ በጥንቃቄ መመዘን ማለት ነው። ስለዚህ ውጤታማ የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ቁም ነገሩ ያለው አፍ ላይ ሳይሆን ልብ ላይ ነው። ጥሩ ግንኙነት የሚያደርግ ሰው ሲባል ተናጋሪ መሆን ማለት ብቻ አይደለም። ራሱን በሌሎች ሰዎች ቦታ አድርጎ የሚያዳምጥ መሆን አለበት። (ያዕቆብ 1:19) የትዳር ጓደኛው ላይ ላዩን ከምታሳየው ጠባይ በስተጀርባ ያሉትን ስሜቶችና ችግሮች መረዳት አለበት። — ምሳሌ 20:5
እንዴት? አንዳንድ ጊዜ በግጭቱ ወቅት ያሉትን ሁኔታዎች በማጤን ይህን መፈጸም ይቻላል። ባለቤትህ ከባድ የሆነ የስሜት ወይም የአካል ውጥረት አለባትን? የትዳር ጓደኛህ የምታሳየውን ጠባይ ሕመም አባብሶባት ይሆን? “ለትክክለኛው ወቅት ትክክለኛው ቃል ምንኛ ያስደስታል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 15:23 ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ) ስለዚህ ሁኔታዎቹን ማመዛዘኑ ተገቢ በሆነ መንገድ ምላሽ እንድትሰጥ ይረዳሃል። — ምሳሌ 25:11
ብዙውን ጊዜ ግን የአንድ ግጭት መንስዔ የሚሆኑት በወቅቱ ካሉት ሁኔታዎች ውጪ ያሉ ነገሮች ናቸው።
ፊት የነበሩትን ሁኔታዎች መረዳት
በልጅነታችን ያጋጠሙን ነገሮች በጉልምስና ዕድሜ የሚኖረንን አስተሳሰብ በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። የትዳር ጓደኛሞች ከተለያዩ ቤተሰቦች የመጡ በመሆናቸው የሐሳብ ግጭቶች መከሰታቸው የማይቀር ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ የሚገኝ አንድ ክንውን ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል። ዳዊት የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ የጋለ ስሜቱን በሕዝብ ፊት ገልጿል። ይሁን እንጂ ሚስቱ ሜልኮልስ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፣ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች፤ በልብዋም ናቀችው።” — 2 ሳሙኤል 6:14–16
ሜልኮል የኃጢአተኛው አባቷን የሳኦልን እምነት የለሽ ዝንባሌ አሳይታለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች የሆኑት ሲ ኤፍ ካይልና ኤፍ ዴሊተሽ በቁጥር 16 ላይ ሜልኮል የዳዊት ሚስት ከመባል ይልቅ “የሳኦል ልጅ” ተብላ የተጠቀሰችው በዚህ ምክንያት ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ያም ሆነ ይህ ዳዊትና ሜልኮል በኋላ ያደረጉት ክርክር በዚህ አስደሳች ወቅት አንድ ዓይነት አመለካከት እንዳልነበራቸው በግልጽ ያሳያል። — 2 ሳሙኤል 6:20–23
ይህ ምሳሌ በአስተዳደግ ምክንያት የመጡ ስውር ግፊቶች ባልና ሚስት ሁኔታዎችን ከተለያየ አቅጣጫ እንዲመለከቱ ሊያደርግ እንደሚችል ያሳያል። ሌላው ቀርቶ ሁለቱም በአንድነት ይሖዋን የሚያገለግሉ ቢሆንም እንኳ ይህ ሁኔታ ይታያል። ለምሳሌ ልጅ በነበረችበት ጊዜ አጥጋቢ የሆነ የስሜት ድጋፍ ያላገኘች አንዲት ሚስት የባልዋ ተቀባይነትና አይዞሽ ባይነት እንደሚያስፈልጋት ከመጠን በላይ ልታሳይ ትችላለች። ይህ ባልዋን ግራ ያጋባው ይሆናል። “እንደማፈቅራት መቶ ጊዜ ልነግራት እችላለሁ፤ ይህም ሆኖ በቂ አይሆንም!” ሲል በመገረም ሊናገር ይችላል።
በዚህ ጊዜ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ‘እያንዳንዱ ራሱን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም መመልከትን’ ይጠይቃል። (ፊልጵስዩስ 2:4) አንድ ባል የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ሚስቱን ከራሱ አመለካከት አንጻር ሳይሆን እርሷ ካሳለፈችው ሕይወት አንጻር መመልከት አለበት። እርግጥ አንዲት ሚስትም ለባልዋ ይህንኑ ነገር ለማድረግ መነሳሳት ይኖርባታል። — 1 ቆሮንቶስ 10:24
ባለፈው ሕይወቷ በደል ተፈጽሞባት ቢሆን
በጊዜያችን በሚያሳዝን ሁኔታ እያደገ የመጣው አስገድዶ የማስነወር ወይም ሴትን አለአግባብ የመድፈር ድርጊት የተፈጸመባት የትዳር ጓደኛ ያለችው ሰው በዚህ ጊዜ አሳቢነት ማሳየቱ አንገብጋቢ ነው። ለምሳሌ አንድ ሚስት በጾታ ግንኙነት ወቅት የአሁኑን ሁኔታ ካለፈው ለይታ ማየት ሊሳናት ይችላል። ባሏን ግፍ ከፈጸመባት ሰው፣ የአሁኑን የጾታ ግንኙነት በፊት ከተፈጸመባት መነወር ለይታ ማየት ትቸገር ይሆናል። በተለይ ደግሞ ባልየው ይህን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ከሚስቱ አመለካከት አንጻር የማያጤነው ከሆነ ትዕግሥት አስጨራሽ ሊሆንበት ይችላል። — 1 ጴጥሮስ 3:8
አንዴ የሆነውን መለወጥ ወይም ያስከተለውን መዘዝ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባትችልም የተጨነቀችውን የትዳር ጓደኛህን ለማጽናናት ማድረግ የምትችለው ብዙ ነገር አለ። (ምሳሌ 20:5) እንዴት? “እናንተም ባሎች አብረዋችሁ የሚኖሩትን የሚስቶቻችሁን ሁኔታ ለመረዳት መጣር ይገባችኋል” ሲል ጴጥሮስ ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:7 ፊሊፕስ ) ባለቤትህ ያሳለፈችውን ሕይወት መረዳት የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። በእርሷ ቦታ ሆነህ ችግሮችን በርኅራኄ ካልተመለከትክ የምትናገረው ነገር መና ሆኖ ይቀራል።
ኢየሱስ ምንም እንኳ ሕመማቸው በራሱ ላይ ባይደርስበትም ታመው የነበሩ ብዙ ሰዎች ባየ ጊዜ “አዘነላቸው”። (ማቴዎስ 14:14) በተመሳሳይ አንተም በግለሰብ ደረጃ እንደ ሚስትህ ቸል አልተባልክ ወይም አግባብ ያልሆነ ነገር አልደረሰብህ ይሆናል፤ ሆኖም ያለባትን ጭንቀት አቃልለህ ከማየት ይልቅ ችግሯን ተረዳላት፤ ድጋፍህንም አትንፈጋት። (ምሳሌ 18:13) ጳውሎስ “እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል” ሲል ጽፏል። — ሮሜ 15:1
በቅሬታ ወጥመድ መያዝ
ትዳር በዋጋ ሊተመን እንደማይችል ዕቃ ነው። ትዳሩ በምንዝር ሲደፈርስ ይህ ነው ተብሎ ሊገመት የማይችል ጉዳት ይደርሳል። (ምሳሌ 6:32) እውነት ነው፣ ተበዳዩ ወገን ይቅር ለማለት ከወሰነ ስብርባሪዎቹን በዕርቅ መልሶ መገጣጠም ይቻላል። ሆኖም ስንጥቆቹ እንዳሉ ይቆያሉ። ጭቅጭቅ በሚፈጠርበት ጊዜ ስንጥቆቹን የማየትና ያለፈውን ነገር እንደማጥቂያ መሣሪያ የመጠቀም ዝንባሌ ሊኖር ይችላል።
አንድ የትዳር ጓደኛ እምነት በማጉደሉ ቅሬታ ማሳየት የተለመደ ነው። ሆኖም ለትዳር ጓደኛችሁ ይቅርታ ካደረጋችሁ ይቅርታ በማድረግ የፈጸማችሁት መልካም ሥራ ንዴታችሁ ሥር ሰዶ እንዲያበላሽባችሁ አትፍቀዱለት። ቅሬታው ውስጥ ውስጡን እየከነከናቸውም ይሁን ያለአንዳች ርኅራኄ በሚፈነዳበት ጊዜ ሁለቱንም የትዳር ጓደኛሞች ይጎዳል። ለምን? አንዲት ዶክተር እንዲህ በማለት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል:- “በትዳር ጓደኛሽ ቅር ተሰኝተሽ ከሆነ ቅር የተሰኘሽበት ምክንያት ስለምትጨነቂለት ነው። ስለዚህ ከእርሱ በመራቅ ወይም ለመበቀል በመሞከር የምትጎጂው የትዳር ጓደኛሽን ብቻ ሳይሆን ራስሽንም ነው። የተሟላ እንዲሆን ትመኚው የነበረውን ግንኙነት ጭራሽ እንዲቋረጥ ታደርጊዋለሽ።”
አዎ፣ ቁጣህ ካልበረደ በትዳርህ ውስጥ የተነሣውን አለመግባባት ልታስቀር አትችልም። ስለዚህ ስሜትህ ባልተጋጋለበት ወቅት የተሰማህን ነገር ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተወያይ። ለምን ቅር እንደተሰኘህ፣ የመንፈስ መረጋጋት ለማግኘት ምን እንደሚያስፈልግህና ግንኙነቱን እንደተጠበቀ ለማቆየት ምን እንደምታደርግ ግለጽ። በክርክሩ አሸናፊ ለመሆን ያለፈውን ነገር እንደ ማጥቂያ መሣሪያ አድርገህ አትጠቀምበት።
ኃይለኛ ሱስ የሐሳብ ግንኙነትን ያቆስላል
የትዳር ጓደኛ አልኮል ወይም ዕፆች አለአግባብ በሚጠቀምበት ጊዜ አንድ ትዳር ከባድ መረበሽ ይገጥመዋል። ከሱስ ነፃ የሆነው የትዳር ጓደኛ ያለበት ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው የአቢጋኤል ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ባልዋ ናባል “እጅግ ሰክሮ” በነበረበት ጊዜ አቢጋኤል የስንፍና ጠባዩ ያስከተለውን መዘዝ ለመለወጥ ብርቱ ጥረት አድርጋለች። (1 ሳሙኤል 25:18–31, 36) ብዙውን ጊዜ አንደኛው የትዳር ጓደኛ በሱስ የተጠቃ ሌላኛው ደግሞ የሱሰኛውን ጠባይ ለመለወጥ ጥረት የሚያደርግበት ትዳር ከናባልና ከአቢጋኤል ቤተሰብ ጋር ይመሳሰላል።a
ሱሰኛ የሆነ ሰው መሻሻል ማድረግ ሲጀምር ትልቅ እፎይታ እንደሚሆን መረዳት አያዳግትም። ይሁን እንጂ ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ያፈራረሳትን አንድ ትንሽ ከተማ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ቤቶች ተደርምሰዋል፣ ዛፎች ተገንድሰዋል፣ የስልክ ገመዶች መሬት ላይ ወድቀዋል። አውሎ ነፋሱ ሲያቆም ታላቅ ደስታ ይሆናል። ሆኖም ከባድ የጥገና ሥራ ያስፈልጋል። የትዳር ጓደኛም የነበረበትን ሱስ አቁሞ አዲስ ሕይወት ሲጀምር ሁኔታው ልክ እንደዚሁ ነው። ፈርሶ የነበረው ግንኙነት እንደገና መገንባት አለበት። መተማመንና ንጹሕ አቋም እንደገና መመሥረት አለባቸው። የሐሳብ ግንኙነት የሚደረግበት መስመር እንደገና መዘርጋት ያስፈልገዋል። ከሱስ ለመላቀቅ ቀስ በቀስ የሚደረገው ይህ የመልሶ ግንባታ ሥራ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች እንዲኮተኩቱት የሚፈልግባቸው “የአዲሱ ሰው” አንዱ ክፍል ነው። ይህ አዲሱ ሰውነት “አእምሮን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል” መጨመር አለበት። — ኤፌሶን 4:22–24 አዓት
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሌዮናርድና ኢሌን ዕፅ መውሰድ እንዲያቆሙ አስቻላቸው፤ ሆኖም አእምሮን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል የሚገባውን ያህል አልሠራም ነበር።b ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ሱሶች ብቅ አሉ። “የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ለማዋልና ትዳራችን አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ለ20 ዓመታት ሞክረን ነበር፤ ሆኖም የማይጨበጥ ሆኖብን ነበር” በማለት ኢሌን ትናገራለች። ያሉብን ሱሶች በጣም ሥር ሰደው ነበር። በጥናትም ሆነ በጸሎት ማሸነፍ ተስኖን ነበር።”
ሌዮናርድና ኢሌን የሱሳቸውን መንስዔ ለመረዳት ምክር ለማግኘት ጣሩ። በልጅነት መነወርን፣ የአልኮል ሱሰኝነትንና ሴቶችን ማክበርን አስመልክቶ “በታማኝና ልባም ባሪያ” የወጣው ወቅታዊ ትምህርት ብዙ ረዳቸው።c (ማቴዎስ 24:45–47) “የደረሰውን ጉዳት ለመጠገንና የቀድሞውን ግንኙነታችንን ለመመለስ እርዳታ አግኝተናል” በማለት ኢሌን ተናግራለች።
ችግሮችን መፍታት
ርብቃ በልጅዋ በዔሳው ሚስቶች የተነሣ ልትሸከመው የማትችል ጭንቀት ተሰምቷት ነበር። ሌላው ልጅዋ ያዕቆብ የዔሳውን ምሳሌ ይከተላል ብላ በመስጋት ርብቃ የተሰማትን ብስጭት ለባሏ ለይስሐቅ እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “ከኬጢ ሴቶች የተነሳ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?” — ዘፍጥረት 27:46
ርብቃ የተሰማትን ስሜት ጠበቅ አድርጋ ብትናገርም ይስሐቅን አልዘለፈችውም። “አንተ ያመጣኸው ጣጣ ነው!” ወይም “እንዳመጣኸው አንተው ተወጣው!” አላለችውም። ከዚህ ይልቅ ርብቃ ችግሩ ምን ያህል እንደነካት ለመግለጽ “እኔ” የሚለውን ተውላጠ ስም ተጠቅማለች። ይህ አቀራረብ ይስሐቅ የራሱን ክብር ለመጠበቅ ከመሞከር ይልቅ ራሱን በእርሷ ቦታ አድርጎ ሁኔታውን እንዲመለከት አደረገው። እንደተዘለፈ ሆኖ ስላልተሰማው ይስሐቅ ለርብቃ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ፈጣን ነበር። — ዘፍጥረት 28:1, 2
ባሎችና ሚስቶች ከርብቃ ምሳሌ ሊማሩ ይችላሉ። አንድ ግጭት ሲነሣ አንዳችሁ በሌላው ላይ ሳይሆን ሁለታችሁም ችግሩ ላይ ተረባረቡ። እናንተም እንደ ርብቃ አንድ ችግር ከራሳችሁ አንጻር እንዴት እንደነካችሁ በመግለጽ ብሶታችሁን ተናገሩ። “ታበሳጨኛለህ!” ወይም “ችግሬ አይገባህም!” ከማለት ይልቅ “ተበሳጭቻለሁ፤ ምክንያቱም . . .” ወይም “የተረዳኸኝ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም . . .” ማለቱ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል።
የጋብቻው መዝለቅ አይበቃም
የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አዳምና ሔዋን ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወልደው ትዳራቸው ለብዙ መቶ ዘመናት ዘልቋል። (ዘፍጥረት 5:3–5) ሆኖም ይህ ሲባል ትዳራቸው ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ ነው ማለት አይደለም። ገና ከጅምሩ በራስ የመመራት መንፈስና ለፈጣሪ የጽድቅ ሕግጋት ያሳዩት ቸልተኝነት የነበራቸውን የአንድ ሥጋ ትስስር አበላሸባቸው።
በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ ትዳር ረዘም ላለ ጊዜ ሊዘልቅ ይችላል፤ ሆኖም የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ነገሮች ይጎድሉት ይሆናል። በጣም ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችንና ተገቢ ያልሆኑ ባሕሪዎችን ነቅሎ መጣል ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል። (ከ2 ቆሮንቶስ 10:4, 5 ጋር አወዳድር።) ይህ ያለማቋረጥ ትምህርት በመቅሰም የሚከናወን ሂደት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ጥረት ዋጋ አለው። ይሖዋ አምላክ ጋብቻን የፈጠረው እርሱ እንደመሆኑ መጠን ለጋብቻ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። (ሚልክያስ 2: 14–16፤ ዕብራውያን 13:4) ስለዚህ እኛ የበኩላችንን ካደረግን ጥረታችንን እንደሚያይልንና በጋብቻ ውስጥ የሚፈጠረውን ማንኛውንም የሐሳብ ግንኙነት መስመር ብልሽት ለመጠገን የሚያስፈልገውን ጥበብና ጥንካሬ እንደሚሰጠን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። — ከመዝሙር 25:4, 5፤ 119:34 ጋር አወዳድር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአልኮል ሱሰኛ ያለባቸውን ቤተሰቦች እንዴት መርዳት እንደሚቻል በግንቦት 22, 1992 ንቁ! እትም ከገጽ 3–7 ላይ ተብራ ርቷል።
b ስሞቹ ተለውጠዋል።
c የጥቅምት 8, 1991፣ የግንቦት 22, 1992 እና የሐምሌ 8, 1992 የንቁ! መጽሔት እትሞችን ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ቆሻሻ መድፋት የበለጠውን ጊዜ ወስዷል”
በትዳራቸው ውስጥ ችግሮች የነበሩባቸው አንድ ባልና ሚስት በየሳምንቱ ቆሻሻ ለመድፋት የሚያጠፉትን ጊዜ በግምት እንዲያሰሉ ተጠይቀው ነበር። የሰጡት መልስ በሳምንት 35 ደቂቃ ወይም በቀን 5 ደቂቃ የሚል ነበር። ከዚያም አንድ ላይ ሆነው የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ምን ያህል ጊዜ እንደሚያሳልፉ ተጠየቁ። ባልየው ደነገጠ። “ቆሻሻ መድፋት የበለጠውን ጊዜ ወስዷል!” ሲል ገለጸ። አክሎም:- “ትዳርን ጠብቆ ለማቆየት አምስት ደቂቃ ይበቃል ብለን አስበን ከነበረ ራሳችንን አታልለናል። እውነትም ትዳርን ለማጠናከር የሚያስችል በቂ ጊዜ አይደለም” ብሏል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መሠረታዊ የሆኑ መመሪያዎችን አውጡ
◻ በአንድ ጊዜ ስለ አንድ ጉዳይ ብቻ መወያየት (1 ቆሮንቶስ 14:33,40)
◻ ስሜታችሁን ግለጹ እንጂ አትካሰሱ (ዘፍጥረት 27:46)
◻ አለመማታት (ኤፌሶን 5:28, 29)
◻ አለመሰዳደብ (ምሳሌ 26:20)
◻ ግባችሁ ለዕርቅ እንጂ ለማሸነፍ አይሁን (ዘፍጥረት 13:8, 9)
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ግጭት ሲነሣ አንዳችሁ በሌላው ላይ ሳይሆን ሁለታችሁም ችግሩ ላይ ተረባረቡ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስሜታችሁን ግለጹ እንጂ አትካሰሱ