ትዕቢት እና ትሕትናን በተመለከተ የተሰጠ ትምህርት
በንጉሥ ዳዊት ሕይወት ውስጥ የተከሰተ አንድ ገጠመኝ በእውነተኛ ትሕትና እና በትዕቢት መካከል ያለውን ልዩነት አጉልቶ ያሳያል። ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል በማድረግ ዋና ከተማው ካደረጋት በኋላ የተከናወነ ክስተት ነው። ዳዊት፣ ይሖዋን እውነተኛው የእስራኤል ንጉሥ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተው ስለነበር የይሖዋን መገኘት የሚያመለክተውን የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ከተማው ለማምጣት ዝግጅት አደረገ። ይህ ክንውን ዳዊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ስለነበር የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት በመከተል ደስታውን በይፋ ገለጸ። የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ንጉሣቸው “ሲያሸበሽብ” እንዲሁም ‘በሙሉ ኀይሉ በእግዚአብሔር ፊት ሲጨፍር’ ተመለከቱት።—1 ዜና መዋዕል 15:15, 16, 29፤ 2 ሳሙኤል 6:11-16
ሆኖም የዳዊት ሚስት ሜልኮል በዚህ አስደሳች ሥነ ሥርዓት አልተካፈለችም። ሁኔታውን በመስኮት ሆና ትመለከት ነበር፤ ዳዊት ይሖዋን የሚያወድስበትን መንገድ ከማድነቅ ይልቅ “በልቧ ናቀችው።” (2 ሳሙኤል 6:16) ሜልኮል እንዲህ የተሰማት ለምን ነበር? ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው፣ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል ልጅና አሁን ደግሞ የሁለተኛው የእስራኤል ንጉሥ ሚስት በመሆኗ ራሷን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጋ ሳትመለከት አልቀረችም። ንጉሥ የሆነው ባሏ እንደ ተራ ሰው ራሱን ዝቅ ማድረግና ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሆኖ መጨፈር እንደሌለበት ተሰምቷት ሊሆን ይችላል። ዳዊት ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ልትቀበለው ስትወጣ ይህ የትዕቢት ባሕርይዋ በግልጽ ታይቷል። በአሽሙር አነጋገር “ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ አንድ ተራ ሰው ራቍቱን መታየቱ ክብሩ ሆኖ ነው!” አለችው።—2 ሳሙኤል 6:20
ታዲያ ዳዊት ለዚህ ትችት መልስ የሰጠው እንዴት ነበር? አባቷ ሳኦል በይሖዋ ፊት ተቀባይነት እንዳጣና በሳኦል ምትክ እሱ መመረጡን በመንገር ሜልኮልን ገሠጻት። ዳዊት በመቀጠልም “ራሴን በፊቱ ዝቅ አደርጋለሁ፤ ከዚህም የባሰ የተናቅሁ እሆናለሁ፤ ነገር ግን በጠቀስሻቸው ገረዶች ፊት እከብራለሁ” አላት።—2 ሳሙኤል 6:21, 22
አዎን፣ ዳዊት ይሖዋን በትሕትና ለማገልገል ቆርጦ ነበር። ይህ የትሕትና ባሕርይው፣ ይሖዋ ዳዊትን “እንደ ልቤ የሆነ” ብሎ የጠራው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። (የሐዋርያት ሥራ 13:22፤ 1 ሳሙኤል 13:14) እንዲያውም ዳዊት የይሖዋ አምላክን ግሩም የትሕትና ምሳሌ ኮርጇል። ዳዊት ለሜልኮል “ራሴን በፊቱ ዝቅ አደርጋለሁ” ብሎ በመለሰላት ጊዜ የተጠቀመበት አገላለጽ አምላክ የሰው ልጆችን የሚያይበትን መንገድ ለመግለጽ ከተሠራበት የዕብራይስጥ ግስ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ አምላክ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉም በላይ ታላቅ የሆነ አካል ቢሆንም መዝሙር 113:6, 7 እንዲህ በማለት ይገልጸዋል:- “በሰማይና በምድር ያሉትንስ ለማየት፣ ራሱን ወደ ታች ዝቅ የሚያደርግ ማን ነው? ድኻውን ከትቢያ ያነሣል፤ ችግረኛውን ከዐመድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።”
ይሖዋ ትሑት በመሆኑ የእብሪተኛ ሰዎችን “ትዕቢተኛ ዐይን” መጥላቱ ምንም አያስደንቅም። (ምሳሌ 6:16, 17) ሜልኮል ይህንን መጥፎ ባሕርይ በማንጸባረቋና አምላክ ለሾመው ንጉሥ ንቀት በማሳየቷ ለዳዊት ልጅ የመውለድ መብት ተነፍጋለች። እንደውም እስክትሞት ድረስ ልጅ አልወለደችም። ይህ ለእኛ ምንኛ ጠቃሚ ትምህርት ይዞልናል! የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ የሚከተሉትን ቃላት መከተል አለባቸው:- “ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣ ‘እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።’”—1 ጴጥሮስ 5:5