አረጋውያን ክርስቲያኖች—ይሖዋ ታማኝነታችሁን ከፍ አድርጎ ይመለከታል
በመላው ዓለም ያሉ ሽማግሌዎች የአምላክን ሕዝቦች የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። እነዚህን ወንድሞች በማግኘታችን ምንኛ ተባርከናል! ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአረጋውያን ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘ አንድ ማስተካከያ ተደርጓል። በዕድሜ የገፉ ሽማግሌዎች ከበድ ያሉ ኃላፊነቶቻቸውን በዕድሜ ከእነሱ ለሚያንሱ ሽማግሌዎች እንዲያስረክቡ ተጠይቀዋል። ይህ ማስተካከያ ምን ነገሮችን ያካትታል?
በአዲሱ ዝግጅት መሠረት የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና በተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች አስተማሪ የሆኑ ወንድሞች 70 ዓመት ሲሞላቸው በዚህ ዘርፍ ማገልገላቸውን ያቆማሉ። በተጨማሪም የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አስተባባሪ ወይም በጉባኤያቸው ውስጥ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ የሆኑ አሊያም እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ኃላፊነቶች ያሏቸው ሽማግሌዎች 80 ዓመት ሲሆናቸው ይህን ኃላፊነታቸውን በዕድሜ ከእነሱ ለሚያንሱ ሽማግሌዎች ያስረክባሉ። እነዚህ ውድ አረጋውያን ሽማግሌዎች ለዚህ ማስተካከያ ምን ምላሽ ሰጥተዋል? ለይሖዋና ለድርጅቱ ታማኝ እንደሆኑ አሳይተዋል!
“በውሳኔው ሙሉ ለሙሉ ተስማምቻለሁ” በማለት በቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አስተባባሪነት ለ49 ዓመታት ያገለገሉት ወንድም ኬን ተናግረዋል። “እንዲያውም እንዲህ ያለ ለውጥ እንደሚደረግ የሰማሁ ዕለት ጠዋት ላይ፣ ከእኔ በዕድሜ የሚያንስ ወንድም አስተባባሪ ቢሆን የተሻለ እንደሆነ በመግለጽ ወደ ይሖዋ ጸልዬ ነበር።” በመላው ዓለም የሚገኙ ታማኝ አረጋውያን ሽማግሌዎችም እንደ ኬን ተሰምቷቸዋል። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውን ማገልገል ስለሚያስደስታቸው መጀመሪያ ላይ ለውጡ አሳዝኗቸው ነበር።
የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ወንድም ኤስፐራንዲዩ እንዲህ ብለዋል፦ “በእርግጥ ለውጡ በመጠኑ አሳዝኖኝ ነበር። ይሁን እንጂ እያሽቆለቆለ የሄደውን ጤንነቴን ለመንከባከብ ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት እንደሚያስፈልገኝ ተገንዝቤያለሁ።” ወንድም ኤስፐራንዲዩ ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን የቀጠሉ ሲሆን አሁንም ለጉባኤው በረከት ናቸው።
ለረጅም ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ሌላ የአገልግሎት ምድብ የተሰጣቸው ክርስቲያኖችስ ምን ተሰምቷቸዋል? ለ38 ዓመታት ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆነው ያገለገሉት ወንድም አለን “ውሳኔውን ስሰማ ክው አልኩ” በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ያም ሆኖ በዕድሜ የሚያንሱ ወንድሞች ሥራውን እንዲረከቡ ማሠልጠን ያለውን ጠቀሜታ የተገነዘቡ ሲሆን በታማኝነት ማገልገላቸውንም ቀጥለዋል።
በተጓዥ የበላይ ተመልካችነትና በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤት አስተማሪነት በድምሩ ለ40 ዓመታት ያገለገሉት ወንድም ራስል መጀመሪያ ላይ አዝነው እንደነበር ይናገራሉ። “እኔና ባለቤቴ የአገልግሎት መብታችንን በጣም እንወደው የነበረ ሲሆን በዚሁ ምድብ ለመቀጠል የሚያስችል አቅም እንዳለንም ይሰማን ነበር” ብለዋል። ወንድም ራስልና ባለቤታቸው ያገኙትን ሥልጠናና ተሞክሮ በጉባኤያቸው ውስጥ እየተጠቀሙበት ነው፤ ይህም አብረዋቸው ለሚያገለግሉ አስፋፊዎች ደስታ አምጥቷል።
አንተ በግልህ ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት ወንድሞች ባይሰማህም እንኳ በ2 ሳሙኤል ላይ የሚገኝን አንድ ዘገባ መመርመርህ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማቸውን ወንድሞች ስሜት ለመረዳት ያስችልሃል።
ልኩን የሚያውቅና እውነታውን የተቀበለ ሰው
የንጉሥ ዳዊት ልጅ አቢሴሎም ባመፀበት ወቅት የተከናወነውን ነገር እስቲ መለስ ብለን እንመልከት። ዳዊት ከኢየሩሳሌም ሸሽቶ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ወደ ማሃናይም ሄደ። ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች በዚያ በቆዩበት ወቅት አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን ማግኘት አስፈልጓቸው ነበር። ታሪኩን ታስታውሰዋለህ?
በአካባቢው የነበሩ ሦስት ሰዎች ለመኝታ የሚሆኑ ነገሮችን እንዲሁም ቀለብና አስፈላጊ ዕቃዎችን ይዘውላቸው መጡ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ቤርዜሊ ነበር። (2 ሳሙ. 17:27-29) የአቢሴሎም ሴራ ከከሸፈ በኋላ ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ተነሳ፤ ቤርዜሊም ንጉሡን እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ሸኘው። በዚህ ጊዜ ዳዊት ቤርዜሊን አብሮት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ ጠየቀው። ንጉሡ ለቤርዜሊ ቀለብ እንደሚሰፍርለት ቃል ገባለት፤ እርግጥ ቤርዜሊ “እጅግ ባለጸጋ” ስለነበር ከዳዊት ቀለብ መቀበል አያስፈልገውም። (2 ሳሙ. 19:31-33) የሆነ ሆኖ በንጉሣዊው ቤተ መንግሥት መኖርና መሥራት ለቤርዜሊ ታላቅ ክብር ነበር! ዳዊት ቤርዜሊን አብሮት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ የጠየቀው፣ ይህ አረጋዊ ሰው በዓመታት ያካበተው ተሞክሮ ስላለው ጥሩ አማካሪ እንደሚሆነው አስቦ ሊሆን ይችላል።
ቤርዜሊ ግን ልኩን የሚያውቅና እውነታውን የሚቀበል ሰው ነበር። በመሆኑም 80 ዓመቱ እንደሆነ ከተናገረ በኋላ “ታዲያ መልካምና መጥፎውን መለየት እችላለሁ?” አለ። ቤርዜሊ ምን ማለቱ ነበር? ቤርዜሊ ባሳለፋቸው በርካታ ዓመታት ብዙ ጥበብ አካብቶ መሆን አለበት። ደግሞም ከጊዜ በኋላ በንጉሥ ሮብዓም ዘመን የኖሩ “ሽማግሌዎች” እንዳደረጉት እሱም በዚህ ዕድሜውም ቢሆን ጥሩ ምክር መስጠት ይችል ነበር። (1 ነገ. 12:6, 7፤ መዝ. 92:12-14፤ ምሳሌ 16:31) ስለዚህ ቤርዜሊ መልካምና መጥፎውን መለየት እንደማይችል ሲገልጽ በዕድሜ መግፋቱ ስላስከተለበት የአቅም ገደብ መናገሩ ሊሆን ይችላል። እርጅና ምግብ የማጣጣምና የመስማት ችሎታውን እንደቀነሰበት ገልጿል። (መክ. 12:4, 5) ይህም በመሆኑ ቤርዜሊ፣ ወጣቱን ኪምሃምን ወደ ኢየሩሳሌም ይዞት እንዲሄድ ዳዊትን ጠየቀው፤ ኪምሃም የቤርዜሊ ልጅ ሳይሆን አይቀርም።—2 ሳሙ. 19:35-40
ለመጪው ጊዜ እቅድ ማውጣት
በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው በዕድሜ ከገፉ የበላይ ተመልካቾች ጋር በተያያዘ የተደረገ ማስተካከያ የቤርዜሊ ዓይነት አመለካከት እንዳለን ያሳያል። እርግጥ ከቤርዜሊ በተለየ መልኩ በዘመናችን እንዲህ ያለ ለውጥ ሲደረግ ከግምት የሚገባው የአንድ ግለሰብ ሁኔታና ችሎታ ብቻ አይደለም። በመላው ዓለም ለሚገኙ ታማኝ ሽማግሌዎች የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ማሰብ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
እነዚህ ትሑት አረጋውያን፣ ለረጅም ጊዜ ሲወጧቸው የነበሩትን ኃላፊነቶች ወጣት ወንድሞች ተረክበው ማከናወናቸው፣ የይሖዋ ድርጅት ወደፊት የሚኖረውን እድገት ለማስተናገድ ዝግጁ እንዲሆን እንደሚረዳ ይገነዘባሉ። ቤርዜሊ ልጁን አሠልጥኖት መሆን አለበት፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ጢሞቴዎስን አሠልጥኖታል። በዘመናችንም አብዛኛውን ጊዜ፣ የአረጋውያኑን ወንድሞች ኃላፊነት የሚረከቡትን ወጣት ወንድሞች ያሠለጠኗቸው በዕድሜ የገፉት ሽማግሌዎች ናቸው። (1 ቆሮ. 4:17፤ ፊልጵ. 2:20-22) ኃላፊነቱን የሚረከቡት ወንድሞችም ቢሆኑ “የክርስቶስን አካል [ለመገንባት]” አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ‘የሰዎች ስጦታ’ እንደሆኑ በተግባር አሳይተዋል።—ኤፌ. 4:8-12፤ ከዘኁልቁ 11:16, 17, 29 ጋር አወዳድር።
አስተዋጽኦ ማበርከት የሚቻልባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች
በመላው ዓለም ባሉት የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙና አንዳንድ ኃላፊነቶቻቸውን ለሌሎች ያስረከቡ ወንድሞች፣ በይሖዋ ሥራ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችሉ አዳዲስ አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል።
ለ19 ዓመታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለገሉት ወንድም ማርኮ “በአሁኑ ወቅት፣ በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ እህቶችን አማኝ ያልሆኑ ባሎች መርዳት ችያለሁ” በማለት ተናግረዋል።
ለ28 ዓመታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለገሉት ወንድም ዠራልዱም “የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ለመርዳትና ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት አዲስ ግብ አውጥተናል” ብለዋል። ወንድም ዠራልዱና ባለቤታቸው በአሁኑ ወቅት 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እየመሩ ሲሆን በርካታ የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችንም በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲጀምሩ ረድተዋል።
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ወንድም አላን ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “አሁን በስብከቱ ሥራ የተለያዩ ዘርፎች ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ችለናል። በአደባባይ ምሥክርነት እንካፈላለን፤ እንዲሁም በንግድ አካባቢዎች መስበክና ለጎረቤቶቻችን መመሥከር ችለናል፤ እንዲያውም ከጎረቤቶቻችን መካከል ሁለቱ በስብሰባዎቻችን ላይ ተገኝተዋል።”
አዲስ የአገልግሎት ምድብ የተሰጣቸው ብቃት ያላቸው ታማኝ ወንድሞች እርዳታ ማበርከት የሚችሉበት ሌላም መንገድ አለ። በጉባኤ ውስጥ ላሉ በዕድሜ ከእናንተ የሚያንሱ ወንድሞች ተሞክሯችሁን በማካፈል የይሖዋን ሥራ መደገፍ ትችላላችሁ። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ወንድም ራስል እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋ ብቃት ያላቸውን ግሩም የሆኑ ወጣት ወንድሞች እያሠለጠናቸውና እየተጠቀመባቸው ነው። እነዚህ ወንድሞች በትጋት የሚያከናውኑት የማስተማርና የእረኝነት ሥራ የወንድማማች ማኅበሩን እየጠቀመ ነው!”—“ወጣት ወንዶች ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙበት እርዷቸው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ይሖዋ ታማኝነታችሁን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
በቅርቡ የአገልግሎት ምድብ ለውጥ ያጋጠማችሁ አረጋውያን ወንድሞች፣ አዎንታዊ ሆናችሁ እንድትቀጥሉ እናበረታታችኋለን። እስካሁን በሙሉ ልብ ባከናወናችሁት አገልግሎት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች መርዳት ችላችኋል፤ ወደፊትም እንዲሁ ማድረግ ትችላላችሁ። ወንድሞቻችሁ ይወዷችኋል፤ ወደፊትም ለእናንተ ያላቸው ፍቅር አይቀንስም።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የይሖዋን ልብ በእጅጉ ማስደሰት ችላችኋል። “አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር [አይረሳም]።” (ዕብ. 6:10) በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ጥቅስ፣ ይሖዋ እንደማይረሳ ቃል የገባልን ቀደም ሲል ያከናወንነውን ሥራ ብቻ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። በይሖዋ ዘንድ ውድ ስለሆናችሁ ቀደም ሲል ያከናወናችሁትን ሥራም ሆነ እሱን ለማስደሰት በቀጣይነት የምታደርጉትን ጥረት ፈጽሞ አይረሳውም!
አንተ በግልህ ከላይ የተገለጸው ዓይነት የኃላፊነት ለውጥ ባያጋጥምህም እንኳ ጉዳዩ ሊመለከትህ ይችላል። በምን መንገድ?
የኃላፊነት ለውጥ ካጋጠማቸው ታማኝ አረጋውያን ወንድሞች ጋር የምትሠራ ከሆነ እነዚህ ጎልማሳ ክርስቲያኖች ካካበቱት የዓመታት ተሞክሮ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። ምክር እንዲሰጡህና ሐሳባቸውን እንዲያካፍሉህ ጠይቃቸው። እንዲሁም ባካበቱት ተሞክሮ ተጠቅመው አሁን ያላቸውን ኃላፊነት እንዴት በታማኝነት እንደሚወጡ ልብ ብለህ ተመልከት።
አዲስ ምድብ የተሰጣችሁ አረጋውያን ወንድሞችም ሆናችሁ እንዲህ ካሉት ወንድሞች ጋር የማገልገል አጋጣሚ ያላችሁ ወንድሞችና እህቶች፣ ይሖዋ ለረጅም ጊዜ ሲያገለግሉት የኖሩና አሁንም እሱን ማገልገላቸውን የሚቀጥሉ ክርስቲያኖችን ታማኝነት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አትርሱ።