2 ወደ ማን?
ሰዎች ወደተለያዩ አማልክት ቢጸልዩም ጸሎታቸው የሚደርሰው ለአንድ አምላክ ነው ሊባል ይችላል? በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች እንዲህ ይሰማቸዋል። ሃይማኖትን የመቀላቀል እንቅስቃሴዎችን የሚደግፉና ሃይማኖቶች ልዩነት ቢኖራቸውም ሁሉም እኩል ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ይማርካቸዋል። ይሁንና እንዲህ ብሎ ማሰብ ትክክል ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ በርካታ ሰዎች የሚጸልዩት ወደ ትክክለኛው አካል እንዳልሆነ ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ሰዎች ጸሎታቸውን ለተቀረጹ ምስሎች ማቅረባቸው የተለመደ ነገር ነበር። ያም ሆኖ አምላክ ይህን ተግባር በተደጋጋሚ ጊዜ አውግዞታል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 115:4-6 ስለ ጣዖታት ሲናገር “ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም” ይላል። ነጥቡ ግልጽ ነው፦ አንድ ሰው ፈጽሞ ወደማይሰማው አምላክ ለምን ይጸልያል?
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይህን ነጥብ ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። እውነተኛ ነቢይ የነበረው ኤልያስ፣ የበኣል ነቢያትን ተገዳድሯቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ኤልያስ መጀመሪያ እነሱ ወደ አምላካቸው እንዲጸልዩ በኋላም እሱ ወደ አምላኩ እንደሚጸልይ ነገራቸው። ከዚያም እውነተኛው አምላክ ለሚቀርብለት ጸሎት መልስ እንደሚሰጥ፣ ሐሰተኛው አምላክ ግን መልስ መስጠት እንደማይችል ገለጸ። የበኣል ነቢያት የቀረበላቸውን ግድድር ተቀብለው ወደ በኣል ከታላቅ ጩኸት ጋር ረጅምና ብርቱ ጸሎት ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ ሳያገኙ ቀሩ! ዘገባው “ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም” ይላል። (1 ነገሥት 18:29) ኤልያስ ሲጸልይስ ምን ተከሰተ?
ኤልያስ ከጸለየ በኋላ አምላኩ አፋጣኝ መልስ ሰጠው፤ የኤልያስ አምላክ ከሰማይ የላከው እሳት የቀረበውን መሥዋዕት በላ። ይህን ልዩነት ያመጣው ምን ነበር? በ1 ነገሥት 18:36, 37a ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የኤልያስ ጸሎት አስፈላጊ የሆነ አንድ ፍንጭ ይሰጠናል። የኤልያስ ጸሎት፣ መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ ወደ 30 የሚጠጉ ቃላትን ብቻ የያዘ በጣም አጭር ጸሎት ነው። ሆኖም ኤልያስ በእነዚያ ጥቂት ቃላት ውስጥ አምላክን ይሖዋ በሚለው የግል ስሙ ሦስት ጊዜ ጠርቶታል።
ስሙ “ባለቤት” ወይም “አለቃ” የሚል ትርጉም ያለው በኣል የተባለው አምላክ የከነዓናውያን አምላክ ሲሆን በአካባቢው የሚመለኩ ሌሎች በርካታ አማልክት በዚህ አምላክ ስም ይሰየሙ ነበር። ይሖዋ የሚለው ስም ግን በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ ልዩ ስም ነው። ይህ አምላክ ለሕዝቦቹ “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ። ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም” ብሏቸው ነበር።—ኢሳይያስ 42:8
ታዲያ ኤልያስም ሆነ የበኣል ነቢያት ያቀረቡት ጸሎት የደረሰው ወደ አንድ አምላክ ነበር? የበኣል አምላኪዎች በሚያደርጉት የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ላይ ዝሙት የሚፈጸም አልፎ ተርፎም የሰው መሥዋዕት የሚቀርብ መሆኑ ይህ አምልኮ ሰዎችን የሚያዋርድ እንደነበር ያሳያል። በተቃራኒው ግን ይሖዋ ሕዝቡን ማለትም እስራኤላውያንን እንደነዚህ ካሉ የሚያዋርዱ ድርጊቶች ነፃ እንዲወጡ በማድረግ አክብሯቸዋል። እስቲ አስበው፦ በጣም ለምታከብረው አንድ ጓደኛህ ደብዳቤ ጽፈህ ከላክ በኋላ ደብዳቤው ጓደኛህ የሚያደርገውን ሁሉ ለሚቃረን መጥፎ ሰው ይደርሳል ብለህ ትጠብቃለህ? እንዲህ ይሆናል ብለህ እንደማትጠብቅ የታወቀ ነው!
ኤልያስ ለበኣል ነቢያት ያቀረበላቸው ግድድር ሁሉም ጸሎት የሚደርሰው ወደ አንድ አምላክ እንዳልሆነ አረጋግጧል
ወደ ይሖዋ የምትጸልይ ከሆነ የሰው ዘር አባት ወደሆነው ፈጣሪ እየጸለይክ ነው ማለት ነው።b ነቢዩ ኢሳይያስ በጸሎቱ ላይ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 63:16) ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው” ባላቸው ጊዜ እየተናገረ የነበረው ኢሳይያስ “አባታችን” ብሎ ስለጠራው አምላክ ነው። (ዮሐንስ 20:17) በመሆኑም ይሖዋ የኢየሱስ አባት ነው። ኢየሱስ የጸለየው ወደ ይሖዋ ሲሆን ተከታዮቹንም ቢሆን እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ወደዚህ አምላክ ነው።—ማቴዎስ 6:9
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኢየሱስ፣ ወደ ማርያም፣ ወደ ቅዱሳን ወይም ወደ መላእክት እንድንጸልይ ያስተምራል? በጭራሽ! የሚያስተምረን ወደ ይሖዋ ብቻ እንድንጸልይ ነው። ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ ሁለት ነጥቦችን እንመልከት። አንደኛ፣ ጸሎት የአምልኮ አንዱ ክፍል ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ አምልኮ የሚገባው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ይናገራል። (ዘፀአት 20:5) ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጸሎት ሰሚ’ የሚለውን ማዕረግ የሚጠቀመው ለይሖዋ ብቻ ነው። (መዝሙር 65:2) ይሖዋ ለሌሎች ብዙ ኃላፊነቶችን ቢሰጥም ጸሎትን የመስማት ኃላፊነትን ግን ለማንም አሳልፎ አልሰጠም። ይሖዋ አምላክ ጸሎቶቻችንን ራሱ እንደሚሰማ ቃል ገብቶልናል።
ስለዚህ ጸሎቶችህ በአምላክ እንዲሰሙልህ ከፈለግህ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ማስታወስ ይኖርብሃል። (የሐዋርያት ሥራ 2:21) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁሉንም ጸሎቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይሰማል ማለት ነው? ወይስ ይሖዋ ጸሎቶቻችንን እንዲሰማልን ከፈለግን ማወቅ የሚኖርብን ሌላ ነገር ይኖር ይሆን?
a አዲስ ዓለም ትርጉም ይህን ጥቅስ እንደሚከተለው በማለት ያስቀምጠዋል፦ “ነቢዩ ኤልያስ የእህል መባው በሚቀርብበት ጊዜ ወደ መሠዊያው ቀርቦ እንዲህ አለ፦ ‘የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደሆንክ፣ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔና እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረግኩት በአንተ ቃል መሆኑ ዛሬ ይታወቅ። ይሖዋ ሆይ፣ መልስልኝ፤ ይህ ሕዝብ አንተ ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደሆንክና ልባቸው እንዲለወጥ ያደረግከው አንተ ራስህ እንደሆንክ ያውቅ ዘንድ መልስልኝ።’”
b አንዳንድ ሃይማኖታዊ ወጎች የአምላክን የግል ስም መጥራት ስህተት ነው ብለው ያስተምራሉ። ይሁን እንጂ ይህ ስም መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው የመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች 7,000 ጊዜ ያህል ይገኝ የነበረ ሲሆን በአብዛኛው ይህ ስም የሚገኘው የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ባቀረቧቸው ጸሎቶችና በዘመሯቸው መዝሙራት ውስጥ ነው።