በእምነታቸው ምሰሏቸው
ኤልያስ ግፍ በበዛበት ዘመን ጸንቶ ኖሯል
ኤልያስ የዮርዳኖስን ሸለቆ ተከትሎ እየተጓዘ ነበር። ርቆ ከሚገኘው ከኮሬብ ተራራ ተነስቶ ወደ ሰሜን ሲጓዝ ሳምንታት አስቆጥሯል። በመጨረሻም ወደ ትውልድ አገሩ እስራኤል ሲደርስ በአገሩ አንዳንድ ለውጦች እንዳሉ ተመለከተ። ምድሪቱ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ድርቅ ካስከተለው ጉዳት እያገገመች ነው። ቀላል የሆነው የመጸው ዝናብ መጣል የጀመረ ሲሆን ገበሬዎቹም እርሻቸውን እያረሱ ነው። ነቢዩ፣ አካባቢው እንደገና እየለመለመ እንደሆነ ሲያይ ልቡ ቢረጋጋም ይበልጥ ያሳሰበው የሕዝቡ ነገር ነው። ሕዝቡ አሁንም በመንፈሳዊ ድርቅ ተጠቅተዋል። የበዓል አምልኮ እንደተስፋፋ በመሆኑ ኤልያስ በዚህ ረገድ ብዙ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል።a
ኤልያስ፣ አቤል ምሖላ ወደተባለችው ከተማ ሲቃረብ ሰፊ የእርሻ መሬት ሲታረስ ተመለከተ። አሥራ ሁለት ገበሬዎች፣ ሃያ አራት በሬዎችን በጥንድ በጥንድ ጠምደው እያረሱ ነው፤ ገበሬዎቹ በመደዳ ሆነው በማረስ እርጥቡን አፈር እየሰነጠቁ ትልም ያወጡ ነበር። ኤልያስ የሚፈልገው በመጨረሻው መደዳ ባሉት ጥማድ በሬዎች የሚያርሰውን ሰው ነው። ይህ ሰው፣ ይሖዋ ለኤልያስ ተተኪ አድርጎ የመረጠው ኤልሳዕ ነው። ኤልያስ፣ አምላክን በታማኝነት የሚያገለግለው እሱ ብቻ እንደሆነ በማሰብ ብቸኝነት ተሰምቶት ስለነበረ ይህን ሰው ለማየት ጓጉቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።—1 ነገሥት 18:22፤ 19:14-19
ኤልያስ የተወሰኑ ኃላፊነቶቹን አሳልፎ እንደሚሰጥ፣ መብቶቹን እንደሚያካፍል ወይም አንድ ቀን በሌላ ሰው እንደሚተካ በማሰብ ከኤልሳዕ ጋር ለመገናኘት አመንትቶ ይሆን? ይህን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ወደ አእምሮው አልመጣም ብለን መደምደምም አንችልም። ምክንያቱም እሱም “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ነበር።” (ያዕቆብ 5:17) ያም ሆነ ይህ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “ኤልያስም ወደ እርሱ [ኤልሳዕ] ወጥቶ መጐናጸፊያውን በላዩ ጣለበት” በማለት ይነግረናል። (1 ነገሥት 19:19) የኤልያስ መጐናጸፊያ፣ ከበግ ወይም ከፍየል ቆዳ የተሠራ ሳይሆን አይቀርም፤ እንደ ካባ የሚደረብና ከይሖዋ ዘንድ ልዩ ሹመት እንደተሰጠው የሚያመለክት ነበር። ከዚህ አንጻር ኤልያስ መጐናጸፊያውን በኤልሳዕ ትከሻ ላይ መጣሉ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ኤልያስ፣ ኤልሳዕን ተተኪው አድርጎ እንዲሾመው ይሖዋ የሰጠውን ትእዛዝ በፈቃደኝነት ፈጽሟል። ኤልያስ በአምላኩ ላይ እምነት ነበረው እንዲሁም ታዝዞታል።
ወጣቱ ሰውም በበኩሉ አረጋዊውን ነቢይ ለመርዳት ጓጉቶ ነበር። ኤልሳዕ፣ ኤልያስን የሚተካው ወዲያውኑ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ለስድስት ዓመታት ያህል ከአረጋዊው ነቢይ ጋር አብሮ በመሆን በትሕትና ይረዳዋል፤ ከጊዜ በኋላ “ቀድሞ የኤልያስን እጅ ያስታጥብ የነበረው” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ነገሥት 3:11) ኤልያስ፣ ብቃት ያለውና የሚረዳው እንዲህ ያለ አገልጋይ ማግኘቱ ምንኛ አጽናንቶት ይሆን! ሁለቱ ሰዎች የቅርብ ወዳጆች የሆኑ ይመስላል። እርስ በርስ መበረታታታቸው፣ በምድሪቱ ተስፋፍቶ የነበረውን ግፍ ተቋቁመው ለመኖር ሳይረዳቸው አልቀረም። ደግሞም የንጉሡ የአክዓብ ክፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ነበር።
አንተስ ግፍ ተፈጽሞብህ ያውቃል? በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ አብዛኞቻችን የፍትሕ መዛባት ይደርስብናል። አምላክን የሚወድ ጓደኛ ማግኘትህ የደረሰብህን ግፍ በጽናት እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም ኤልያስ ካሳየው እምነት ብዙ ነገር መማር ትችላለህ።
‘ተነሣና አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ’
ኤልያስና ኤልሳዕ የሕዝቡን መንፈሳዊ ሁኔታ ለማሻሻል ጠንክረው ሠርተዋል። በማኅበር ሆነው አንድ ላይ የሚማሩ ሌሎች ነቢያትን በማሠልጠኑ ሥራ ግንባር ቀደም ሚና ሳይኖራቸው አይቀርም። ከጊዜ በኋላ ግን ይሖዋ “ተነሣና . . . የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ” በማለት ለኤልያስ አዲስ የሥራ ምድብ ሰጠው። (1 ነገሥት 21:18) አክዓብ ምን አድርጎ ይሆን?
ንጉሡ፣ ከሃዲ በመሆን ከእሱ በፊት ከነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ የከፋ ድርጊት ፈጽሟል። ኤልዛቤልን ያገባ ሲሆን በአገሪቱ ላይ የበኣል አምልኮ እንዲስፋፋ አድርጓል፤ እንዲሁም ንጉሡ ራሱ በኣልን ያመልክ ነበር። (1 ነገሥት 16:31-33) የበኣል አምልኮ፣ የመራባት አምልኮ ማቅረብንና ለአምልኮ ሲባል የሚፈጸም ዝሙት አዳሪነትን አልፎ ተርፎም ልጆችን መሥዋዕት ማድረግን ይጨምር ነበር። በተጨማሪም አክዓብ፣ ይሖዋ ክፉውን የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድን እንዲገድል በቅርቡ የሰጠውን መመሪያ ሳይታዘዝ ቀርቷል። አክዓብ ይህን ትእዛዝ ያላከበረው ገንዘብ እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ ሳይሆን አይቀርም። (1 ነገሥት ምዕራፍ 20ን ተመልከት) አሁን ደግሞ የአክዓብና የኤልዛቤል ስግብግብነት፣ ገንዘብ ወዳድነትና ዓመፅ የከፋ ደረጃ ላይ ደረሰ።
አክዓብ፣ ሰማርያ ውስጥ በጣም ሰፊ ቤተ መንግሥት አለው! በተጨማሪም 37 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኢይዝራኤል ሌላ ቤተ መንግሥት አለው። ከዚህ ቤተ መንግሥት አጠገብ ደግሞ አንድ የወይን ተክል ቦታ ይገኛል። አክዓብ፣ ናቡቴ የተባለ ግለሰብ ንብረት የሆነውን ይህን መሬት ለመውሰድ ቋመጠ። ናቡቴን አስጠርቶ ‘የወይን ተክል ቦታህን ልውሰድና ገንዘብ ወይም ተለዋጭ የወይን ተክል ቦታ ልስጥህ’ አለው። ናቡቴ ግን አክዓብን “የአባቶቼን ርስት ለአንተ መስጠት በይሖዋ ፊት ተገቢ ስላልሆነ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው” በማለት መለሰለት። (1 ነገሥት 21:3 NW) ናቡቴ እንዲህ ያለ ምላሽ የሰጠው ግትር ስለሆነ ወይም የሚያጋጥመውን አደጋ ከቁብ ስላልቆጠረው ነው? ብዙዎች እንደዚያ ተሰምቷቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ናቡቴ ይሖዋ ያወጣውን ሕግ እየታዘዘ ነበር፤ ሕጉ እስራኤላውያን ከቤተሰባቸው ያገኙትን ርስት ለዘለቄታው እንዳይሸጡ ይከለክላል። (ዘሌዋውያን 25:23-28) ይህንን የአምላክ ሕግ መጣስ ለናቡቴ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። አክዓብን መቃወም አደገኛ እንደሆነ እያወቀ ይህንን ማድረጉ ደፋርና የእምነት ሰው እንደነበረ ያሳያል።
አክዓብ ግን ስለ ይሖዋ ሕግ ለአፍታ እንኳ እንዳላሰበ ግልጽ ነው። የፈለገውን ስላላገኘ “ተበሳጭቶና ተቈጥቶ” ወደ ቤቱ ሄደ። ዘገባው በመቀጠል “አኵርፎም በዐልጋው ላይ ተኛ፤ ምግብም መብላት ተወ” ይላል። (1 ነገሥት 21:4) ኤልዛቤል ባሏ እንደ ሕፃን ልጅ አኩርፎ መቀመጡን ስታይ የፈለገውን ማግኘት እንዲችል ወዲያውኑ አንድ እቅድ ነደፈች፤ በእቅዱ አፈጻጸም መሠረት፣ ምንም ጥፋት የሌለበት የአንድ ቤተሰብ ደም ይፈስሳል።
ኤልዛቤል ስለጠነሰሰችው ሴራ ስናነብ ‘ምን ያህል ክፉ ናት’ ብለን መደነቃችን አይቀርም። ንግሥት ኤልዛቤል፣ ከባድ ክስ የቀረበበት አንድ ሰው በአምላክ ሕግ መሠረት ጥፋተኛ ለመባል የግድ ሁለት ሰዎች ሊመሠክሩበት እንደሚገባ ታውቃለች። (ዘዳግም 19:15) ስለዚህ በናቡቴ ላይ በሐሰት ለመመሥከር ፈቃደኛ የሆኑ ሁለት ሰዎች እንዲፈልጉ የሚያዝ በአክዓብ ስም የተጻፈ ደብዳቤ በኢይዝራኤል ላሉ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰዎች ላከች፤ ምሥክሮቹ ‘አምላክን ሲሳደብ ሰምተነዋል’ ብለው የሚመሠክሩ ሲሆን ይህ ደግሞ በሞት የሚያስቀጣ ጥፋት ነበር። የሚያሳዝነው እቅዷ ሰመረላት። ሁለት “ምናምንቴ ሰዎች” (የ1954 ትርጉም) በናቡቴ ላይ በሐሰት መሠከሩበትና በድንጋይ ተወግሮ ተገደለ። ይህም እንዳይበቃ ደግሞ የናቡቴ ወንዶች ልጆችም ተገደሉ!b (1 ነገሥት 21:5-14፤ ዘሌዋውያን 24:16፤ 2 ነገሥት 9:26) አክዓብ የራስነት ሥልጣኑን ሚስቱ እንዳሻት እንድትጠቀምበት አሳልፎ የሰጣት ሲሆን እሷም እነዚያን ንጹሕ ሰዎች አጥፍታለች።
ኤልያስ፣ ንጉሡና ንግሥቲቱ ያደረጉትን ነገር ይሖዋ ሲነግረው ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ገምት። ንጹሕ ሰዎች በክፉዎች ግፍ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ማሰብ በጣም ተስፋ ያስቆርጣል። (መዝሙር 73:3-5, 12, 13) በዛሬው ጊዜም ግፍ ሲፈጸም ማየት የተለመደ ነው፤ የአምላክ ወኪል እንደሆኑ የሚናገሩ ኃይል ያላቸው ሰዎች ሳይቀር አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለ ድርጊት ይፈጽማሉ። ይሁንና ይህ ዘገባ ሊያጽናናን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ይህ ታሪክ ከይሖዋ የተሰወረ ምንም ነገር እንደሌለ ያረጋግጥልናል። አምላክ ሁሉንም ነገር ይመለከታል። (ዕብራውያን 4:13) ታዲያ የሚያያቸውን የክፋት ድርጊቶች አስመልክቶ ምን እርምጃ ይወስዳል?
“ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን?”
ይሖዋ ኤልያስን ወደ አክዓብ ላከው። አክዓብ ‘የሚገኘው በናቡቴ የወይን ተክል ቦታ ነው’ ብሎ በግልጽ ነገረው። (1 ነገሥት 21:18) አክዓብ፣ የወይን ተክል ቦታውን መውሰድ እንደሚችል ኤልዛቤል ስትነግረው አዲሱን ቦታውን ለማየት ሄደ። ይሖዋ እያየው እንደሆነ ጨርሶ አላሰበም። አክዓብ በወይን ተክል ቦታው እየተዘዋወረ በዚህ ቦታ ላይ ምን ዓይነት አስደናቂ የአትክልት ሥፍራ እንደሚሠራ ሲያልም በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ይሁን እንጂ በድንገት ኤልያስ ብቅ አለ! በፈገግታ የተሞላው የአክዓብ ፊት በአንድ ጊዜ ከሰመና በቁጣና በጥላቻ ተሞልቶ “ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን?” በማለት ተናገረ።—1 ነገሥት 21:20
አክዓብ ከተናገራቸው ቃላት የእሱን ሞኝነት የሚያሳዩ ሁለት ሐሳቦችን እናገኛለን። አንደኛ፣ ኤልያስን “አገኘኸኝ” ማለቱ ስለ ይሖዋ ምንም እንዳላሰበ የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም ቀድሞውንም ቢሆን ይሖዋ “አግኝቶታል።” አክዓብ፣ አምላክ የሰጠውን የመምረጥ ነፃነት በአግባቡ እንዳልተጠቀመበትና የኤልዛቤል ክፉ እቅድ ባስገኘው ውጤት መደሰቱን ይሖዋ ተመልክቷል። በተጨማሪም አምላክ፣ በአክዓብ ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ የያዘው ለቁሳዊ ነገሮች ያለው ፍቅር እንጂ ምሕረት፣ ፍትሕ ወይም ርኅራኄ እንዳልሆነ ተመልክቷል። ሁለተኛ፣ አክዓብ ኤልያስን “ጠላቴ ሆይ” ብሎታል። አክዓብ ይህን ሲል፣ የይሖዋ አምላክ ወዳጅ ለሆነውና ወደ ጥፋት ከሚወስደው መንገድ እንዲመለስ ሊረዳው ለሚችለው ሰው ጥላቻ እንዳለው አሳይቷል።
አክዓብ ከፈጸመው የሞኝነት ድርጊት እኛም ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ይሖዋ አምላክ ሁሉንም ነገር እንደሚያይ ምንጊዜም ማስታወስ አለብን። ይሖዋ አፍቃሪ አባት እንደመሆኑ ከትክክለኛው መንገድ ስንወጣ ሲያይ ወደ ትክክለኛው ጎዳና እንድንመለስ ሊረዳን ይፈልጋል። ብዙውን ጊዜ እኛን ለመርዳት ወዳጆቹን ማለትም እንደ ኤልያስ ያሉ ታማኝ ሰዎችን በመላክ ቃሉን እንዲነግሩን ያደርጋል። የአምላክን ወዳጆች እንደ ጠላት መመልከት ምንኛ ስህተት ነው!—መዝሙር 141:5
ኤልያስ ለአክዓብ “አዎን አግኝቼሃለሁ” የሚል መልስ ሲሰጠው ይታይህ። አክዓብ ሌባና ነፍሰ ገዳይ እንዲሁም በይሖዋ ላይ ያመፀ ሰው መሆኑን ኤልያስ ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ ያለ ክፉ ሰው ፊት መቆም ምን ያህል ድፍረት እንደጠየቀበት አስብ! ቀጥሎ ኤልያስ ይሖዋ በአክዓብ ላይ ያስተላለፈውን ፍርድ ተናገረ። ይሖዋ ሁሉንም ነገር ተመልክቷል፤ የአክዓብ ቤተሰብ ክፋት በሕዝቡ መካከል እንደ ወረርሽኝ እየተሠራጨ መሆኑንም አይቷል። በመሆኑም ኤልያስ፣ አምላክ የአክዓብን ቤት ‘ፈጽሞ ለማጥፋት’ ማለትም ሥርወ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ መወሰኑን ነገረው። ኤልዛቤልም የእጇን ታገኛለች።—1 ነገሥት 21:20-26
ኤልያስ፣ ሰዎች ክፋትና ኢፍትሐዊ ድርጊት ፈጽመው ከቅጣት ያመልጣሉ የሚል አስተሳሰብ አልነበረውም። በዛሬው ጊዜ ክፉዎች ምንም እንደማይደርስባቸው እንድናስብ የሚያደርጉን ሁኔታዎች አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ይህ ዘገባ ግን ይሖዋ አምላክ ምን እየተፈጸመ እንዳለ ከመመልከትም አልፎ እሱ በወሰነው ጊዜ ፍትሕን እንደሚያሰፍን ያረጋግጥልናል። ሁሉንም ዓይነት የፍትሕ መጓደል ለዘለቄታው የሚያስወግድበት ጊዜ እንደቀረበ የአምላክ ቃል ማረጋገጫ ይሰጠናል! (መዝሙር 37:10, 11) ይሁን እንጂ ‘የአምላክ ፍርድ ቅጣት ብቻ ነው? ምሕረትንስ ይጨምር ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።
“አክዓብ ራሱን በፊቴ እንዴት እንዳዋረደ አየህን?”
አክዓብ መለኮታዊው ፍርድ ሲነገረው የሰጠው ምላሽ ኤልያስን ሳያስገርመው አልቀረም። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “አክዓብም ይህን ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶ፤ ጾመ፤ በማቅ ላይ ተኛ በሐዘን ኵርምት ብሎም ይሄድ ነበር።” (1 ነገሥት 21:27) አክዓብ ንስሐ ገብቶ አካሄዱን አስተካክሏል ማለት ነው?
ቢያንስ ቢያንስ በትክክለኛው አቅጣጫ ለመሄድ አንዳንድ ለውጦች አድርጓል ብለን መናገር እንችላለን። አክዓብ ራሱን አዋርዷል፤ ኩራተኛና ግትር ለሆነ ሰው ይህን ማድረግ ከባድ እንደሚሆንበት ግልጽ ነው። ይሁንና አክዓብ ከልቡ ንስሐ ገብቶ ነበር? እስቲ ከአክዓብ በኋላ ከነገሠውና የባሰ ክፋት ከፈጸመው ከንጉሥ ምናሴ ሁኔታ ጋር እያነጻጸርን እንየው። ምናሴ፣ ይሖዋ ሲቀጣው ራሱን አዋርዶ አምላክ እንዲረዳው ጸልዮአል። በዚህ ብቻ ግን አላበቃም። ያቆማቸውን የጣዖት ምስሎች በማጥፋት የቀድሞ አካሄዱን ቀይሮ ይሖዋን ለማገልገል ጥረት አድርጓል፤ አልፎ ተርፎም ሕዝቡ ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ ያበረታታ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 33:1-17) አክዓብስ እንዲህ ያለ ነገር ያደረገ ይመስልሃል? በጭራሽ።
ይሖዋ፣ አክዓብ ማዘኑን ለማሳየት ያደረገውን ነገር ተመልክቷል? ለኤልያስ እንዲህ ብሎታል፦ “አክዓብ ራሱን በፊቴ እንዴት እንዳዋረደ አየህን? ራሱን ስላዋረደ ይህን መከራ በዘመኑ አላመጣበትም፤ ነገር ግን ይህን በቤቱ ላይ የማመጣው በልጁ ዘመን ነው።” (1 ነገሥት 21:29) ታዲያ ይሖዋ አክዓብን ይቅር ብሎታል ማለት ነው? አይደለም፤ እንዲህ ያለውን መለኮታዊ ምሕረት የሚያስገኘው እውነተኛ ንስሐ ብቻ ነው። (ሕዝቅኤል 33:14-16) ይሁን እንጂ አክዓብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን መጸጸቱን በማሳየቱ ይሖዋም የተወሰነ ምሕረት አሳይቶታል። አክዓብ መላው ቤተሰቡ ሲያልቅ በማየት ከሚደርስበት ሰቀቀን ይተርፋል።
ያም ቢሆን ይሖዋ በዚህ ሰው ላይ ያስተላለፈው ፍርድ አልተለወጠም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ አክዓብን አሳስቶ የሕይወቱ ማብቂያ ወደ ሆነው ጦርነት እንዲዘምት ማድረግ ስለሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ ዘዴ ከመላእክቱ ጋር ተነጋግሯል። ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ በአክዓብ ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ፍጻሜውን አገኘ። አክዓብ በጦርነቱ ላይ ቆሰለ፤ በሠረገላው ላይ ሆኖ ደሙ ሲፈስስ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ሞተ። ዘገባው የንጉሡ ሠረገላ ሲታጠብ አንዳንድ ውሾች የንጉሡን ደም ይልሱ እንደነበረ ይናገራል። ይሖዋ በኤልያስ በኩል ለአክዓብ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ በዚህ መንገድ በግልጽ ተፈጸመ፦ “ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ውሾች እንዲሁ ይልሱታል!”—1 ነገሥት 21:19፤ 22:19-22, 34-38
ይሖዋ ናቡቴ ያሳየውን እምነትና ድፍረት አልረሳውም፤ በአክዓብ ላይ የደረሰው ነገር ኤልያስንና ኤልሳዕን ጨምሮ ታማኝ ለነበሩ ሌሎች የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ይህን አረጋግጦላቸዋል። ይዋል ይደር እንጂ የፍትሕ አምላክ ክፉዎችን ሳይቀጣ አይቀርም፤ ወይም ደግሞ ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል መሠረት እስካለ ድረስ ምሕረት ከማሳየት ወደኋላ አይልም። (ዘኍልቍ 14:18) በዚያ ክፉ ንጉሥ አገዛዝ ሥር ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በጽናት ላገለገለው ለኤልያስም ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ትምህርት ነው! አንተስ ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብህ ያውቃል? አምላክ ነገሮችን የሚያስተካክልበትን ጊዜ ለማየት ትጓጓለህ? ከሆነ የኤልያስ ዓይነት እምነት ሊኖርህ ይገባል። ኤልያስ ታማኝ አጋሩ ከሆነው ከኤልሳዕ ጋር የአምላክን መልእክት ማወጁን ቀጥሏል፤ እንዲሁም ግፍ በበዛበት ዘመን ጸንቶ ኖሯል!
a ይሖዋ፣ ዝናብና ለምድሪቱ ልምላሜ ያመጣል ተብሎ የሚመለከው በዓል ምንም ማድረግ እንደማይችል ለማሳየት ለሦስት ዓመት ተኩል በምድሪቱ ላይ ድርቅ እንዲኖር አድርጎ ነበር። (1 ነገሥት ምዕራፍ 18) በጥር 1 እና በሚያዝያ 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የወጡትን “በእምነታቸው ምሰሏቸው” የሚሉ ርዕሶች ተመልከት።
b ኤልዛቤል የናቡቴን ልጆች ለማስገደል እንድትነሳሳ ያደረጋት የወይን እርሻውን እነሱ እንዳይወርሱ የነበራት ፍራቻ ሊሆን ይችላል። አምላክ እንዲህ ያሉ የጭቆና ድርጊቶችን የፈቀደበትን ምክንያት ለማወቅ በዚህ እትም ውስጥ የሚገኘውን “አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።