አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .
አምላክ አንድ የተወሰነ መኖሪያ አለው?
በርካታ ሃይማኖቶች አምላክን የሚገልጹት በተመሳሳይ ጊዜ ሁሉም ቦታ የሚገኝ እንደሆነ አድርገው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ አምላክ “በሁሉም ቦታዎችና ነገሮች ውስጥ የሚገኝ” እንደሆነ ይገልጻል። በተመሳሳይም የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን መሥራች የሆኑት ጆን ዌስሊ “በሁሉም ቦታ የሚገኝ አምላክ” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የስብከት ጽሑፋቸው ላይ “በተፈጠሩ ነገሮችም ሆነ ከዚያ ውጪ ባሉ ነገሮች ውስጥ አምላክ የሌለበት አንድም ቦታ የለም” በማለት ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? አምላክ በሰማይና በምድር ላይ ባሉ ሁሉም ቦታዎች ላይ ሌላው ቀርቶ በሰው ልጆች ውስጥም ሳይቀር በተመሳሳይ ጊዜ ይገኛል?
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አንድ የተወሰነ መኖሪያ እንዳለውና ይህም መኖሪያ ሰማይ እንደሆነ ይናገራል። ለምሳሌ ንጉሥ ሰለሞን “አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ” በማለት ወደ አምላክ ጸሎት እንዳቀረበ ይገልጻል። (1 ነገሥት 8:43) ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ባስተማረበት ጊዜ ጸሎታቸውን ‘በሰማያት ለሚኖረው አባታችን’ እንዲያቀርቡ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ “በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ በቀጥታ ወደ ሰማይ ገብቷል” በማለት ይገልጻል።—ዕብራውያን 9:24
እነዚህ ጥቅሶች ይሖዋ አምላክ የሚኖረው በሰማይ እንጂ በሁሉም ቦታ እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያሉ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ጥቅሶች ላይ የተጠቀሰው “ሰማይ” በምድር ዙሪያ ያለውን ከባቢ አየር ወይም ከምድር በላይ ያለውን ሕዋ የሚያመለክት አይደለም። ግዑዙ ሰማይ የአጽናፈ ዓለሙን ፈጣሪ መያዝ አይችልም። (1 ነገሥት 8:27) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ መንፈስ” እንደሆነ ይነግረናል። (ዮሐንስ 4:24) እሱ የሚኖረው በመንፈሳዊው ሰማይ ማለትም ከግዑዙ አጽናፈ ዓለም ውጪ ባለ ስፍራ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:44
ይሁንና አምላክ በሁሉም ስፍራ የሚገኝ እንደሆነ የሚያስመስሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ለምሳሌ በመዝሙር 139:7-10 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ዳዊት አምላክን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤ መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ። በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበር፣ እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣ በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች።” ይህ ሐሳብ በእርግጥ አምላክ በጥቅሱ ውስጥ በተገለጹት ቦታዎች ሁሉ እንደሚገኝ የሚጠቁም ነው?
ዳዊት መጀመሪያ ላይ ያቀረበው ጥያቄ “ከመንፈስህa ወዴት እሄዳለሁ?” የሚል መሆኑን ልብ በል። አምላክ ቃል በቃል ወደ አንድ ቦታ መሄድ ወይም እዚያ ቦታ መገኘት ሳያስፈልገው በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ማንኛውንም ነገር ማየትና ወደየትኛውም ቦታ ኃይሉን በመላክ የሚፈልገውን ነገር ማከናወን ይችላል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በቅርቡ የሳይንስ ሊቃውንት ከምድር በሚሊዮን የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በማርስ ላይ ያለውን አፈር መመርመር ችለዋል። ይህን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው? በአካል ወደዚያ በመሄድ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ማርስ የተላኩ ሰው አልባ መንኮራኩሮች ወደ ምድር ያስተላለፏቸውን ፎቶግራፎችና መረጃዎች በጥንቃቄ በማጥናት ነው።
በተመሳሳይም ይሖዋ አምላክ በዚህ አጽናፈ ዓለም ውስጥ በየትኛውም ቦታ ላይ የሚከናወነውን ነገር ለማየት የግድ ሁሉም ቦታ መገኘት አያስፈልገውም። የአምላክ ቃል “ከእሱ እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም” ይላል። (ዕብራውያን 4:13) አዎ፣ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ማለትም በሥራ ላይ ያለው ኃይሉ የትም ቦታ መገኘት ይችላል፤ ይህ ደግሞ አምላክ አንድ ቋሚ ቦታ ላይ ይኸውም ‘ቅዱስ ማደሪያው’ በሆነው በሰማይ ሆኖ ሁሉም ነገር ግልጽ ሆኖ እንዲታየው እንዲሁም ዓላማውን እንዲፈጽም ያስችለዋል።—ዘዳግም 26:15
a እዚህ ላይ “መንፈስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አምላክ ዓላማውን ለመፈጸም የሚጠቀምበትን በሥራ ላይ ያለውን ኃይሉን ያመለክታል።