ከሞት በኋላ ሕይወት —መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ።”—ዘፍጥረት 3:19
1, 2. (ሀ) የወዲያኛውን ሕይወት በተመለከተ የሚነገሩ ምን የተለያዩ ሐሳቦች አሉ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ የሚያስተምረውን ለማወቅ ምንን መመርመር ያስፈልገናል?
“የዘላለማዊ ሥቃይ ጽንሰ ሐሳብ አምላክ ለፍጥረታት ፍቅር አለው ከሚለው እምነት ጋር ይጋጫል። . . . ነፍስ ማስተካከያ ማድረግ የምትችልበት ዕድል እንኳ ሳታገኝ ለጥቂት ዓመታት በሠራቻቸው ስህተቶች የተነሳ ለዘላለም ትቀጣለች ብሎ ማመን የምክንያታዊነትን መሠረታዊ ሥርዓት እንደ መጣስ ይቆጠራል” ሲል ኒኪላናንዳ የተባለው የሂንዱ ፈላስፋ ተናግሯል።
2 እንደ ሂንዱው ፈላስፋ ኒኪላናንዳ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ስለ ዘላለማዊ ሥቃይ የሚገልጸው ትምህርት አእምሯቸውን ይረብሻቸዋል። ልክ እንደዚሁም ሌሎች ሰዎች የኒርቫና ግብ ላይ መድረስና ከተፈጥሮ ጋር አንድ መሆንን የመሳሰሉ ጽንሰ ሐሳቦችን መረዳት ያዳግታቸዋል። እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚናገሩ የእምነት ክፍሎች እንኳ ስለ ነፍስ ምንነትና ስንሞት ምን እንደምንሆን የሚሰጡት አስተያየት የተለያየ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ ምን ብሎ ያስተምራል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” ተብለው የተተረጎሙትን የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ፍቺዎች መመርመር ይኖርብናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ ምን ይላል?
3. (ሀ) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የትኛው ነው? መሠረታዊ ትርጉሙስ ምንድን ነው? (ለ) ዘፍጥረት 2:7 “ነፍስ” የሚለው ቃል ሰውየውን በጠቅላላ ሊያመለክት እንደሚችል የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
3 “ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ነፈሽ ሲሆን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 754 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። ነፈሽ ማለት ምን ማለት ነው? ዘ ዲክሽነሪ ኦቭ ባይብል ኤንድ ሪሊጅን እንደሚለው ከሆነ ቃሉ “ብዙውን ጊዜ መላውን ሕያው አካልና ግለሰቡን በጠቅላላ ያመለክታል።” መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 2:7 (የ1879 እትም) ላይ ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማማ መግለጫ ይሰጣል:- “እግዚአብሔርም አምላክ ሰውን ፈጠረ መሬት ከምድር ባፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ።” የመጀመሪያው ሰው ነፍስ “ሆነ” እንደተባለ ልብ በል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አዳም ነፍስ ያለው አልሆነም፤ ዶክተር የሆነ ሰው ዶክተር ነው እንደሚባል ሁሉ አዳምም ራሱ ነፍስ ነበር። ስለዚህ እዚህ ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል ሰውየውን በጠቅላላ ያመለክታል።
4. በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የትኛው ነው? የዚህስ ቃል መሠረታዊ ትርጉም ምንድን ነው?
4 “ነፍስ” (ፕስኺ) እየተባለ የተተረጎመው ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከመቶ ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። ነፈሽ እንደሚለው ቃል ሁሉ ይሄኛውም ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ሰውየውን በጠቅላላ ነው። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ዐረፍተ ነገሮች ተመልከት:- “ነፍሴ ታውካለች።” (ዮሐንስ 12:27) “በነፍስ ሁሉ ላይ ፍርሃት ወደቀ።” (ሥራ 2:43 NW) “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ።” (ሮሜ 13:1) “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው።” (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት።” (1 ጴጥሮስ 3:20) ልክ እንደ ነፈሽ ሁሉ ፕስኺ የሚለው ቃልም በግልጽ የሚያመለክተው በጠቅላላ ሰውየውን ነው። ኒጀል ተርነር የተባሉት ምሁር እንዳሉት ከሆነ ይህ ቃል “ሰውየውን ራሱን፣ አምላክ ሩአህ [መንፈስ] እፍ ያለበትን ሥጋዊ አካል ያመለክታል። . . . ቃሉ በይበልጥ የሚያመለክተው ሰውየውን በጠቅላላ ነው።”
5. እንስሳት ነፍሳት ናቸውን? አስረዳ።
5 “ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን እንስሳትንም የሚያመለክት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 1:20 (NW) ስለ ባሕር ፍጥረታት ሲገልጽ አምላክ “ውኃውም ብዛት ባላቸው ሕያው ነፍሳት ይሞላ” ሲል እንዳዘዘ ይናገራል። ከዚያም አምላክ በቀጣዩ የፍጥረት ቀን ላይ እንዲህ አለ:- “ምድሪቱ ሕያው ነፍስ ታውጣ በየዘመድዋ። እንስሳን ተንቀሳቃሽንም የምድርንም አራዊት ኢየዘመዱ።”—ዘፍጥረት 1:24 የ1879 እትም፤ ከዘኁልቁ 31:28 የ1879 እትም ጋር አወዳድር።
6. መጽሐፍ ቅዱስ “ነፍስ” የሚለውን ቃል ስለሚጠቀምበት መንገድ ምን ሊባል ይቻላል?
6 ስለዚህ “ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተሠራበት መሠረት ሰውን ወይም እንስሳን ወይም ደግሞ ሰውየውም ሆነ እንስሳው ያላቸውን ሕይወት ያመለክታል። (ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) መጽሐፍ ቅዱስ ለነፍስ የሚሰጠው ፍቺ ግልጽ፣ ተለዋዋጭ ያልሆነና የሰው ልጆች ከፈጠሯቸው ውስብስብ የሆኑ ፍልስፍናዎችና አጉል እምነቶች የጠራ ነው። ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ አንድ መልስ የሚያሻው አንገብጋቢ ጥያቄ አለ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ አባባል መሠረት በሞት ጊዜ ነፍስ ምን ትሆናለች?
ሙታን አንዳች አያውቁም
7, 8. (ሀ) ቅዱሳን ጽሑፎች ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ምን ይላሉ? (ለ) ነፍስ ልትሞት እንደምትችል የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ስጥ።
7 ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ በመክብብ 9:5, 10 ላይ በሚከተለው መንገድ በግልጽ ሰፍሮ እናገኘዋለን:- “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም . . . በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።” ስለዚህ ሞት ከሕልውና ውጪ መሆን ማለት ነው። መዝሙራዊው ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ “ወደ ዐፈር ይመለሳሉ፤ በዚያኑ ቀን ዕቅዳቸው ሁሉ ያከትማል” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 146:4 የ1980 ትርጉም) ሙታን ምንም አያውቁም፤ ምንም ማድረግም አይችሉም።
8 አምላክ በአዳም ላይ በፈረደ ጊዜ “አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” ሲል ገልጿል። (ዘፍጥረት 3:19) አምላክ ከምድር አፈር ሠርቶ ሕይወት ሳይሰጠው በፊት አዳም ከሕልውና ውጪ ነበር። ሲሞት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ ተመልሷል። ቅጣቱ ሞት እንጂ ወደ ሌላ ዓለም መዛወር አልነበረም። ታዲያ አዳም ሲሞት ነፍሱ ምን ሆነች? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ ራሱን ሰውየውን ለማመልከት ስለተሠራበት አዳም ሞተ ስንል አዳም የተባለው ነፍስ ሞተ ማለታችን ነው። ይህ አባባል ነፍስ አትሞትም ብሎ ለሚያምን ሰው እንግዳ ሊሆንበት ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” ሲል ይገልጻል። (ሕዝቅኤል 18:4) ዘሌዋውያን 21:1 (NW) ስለ “ሞተ ነፍስ” (“አስከሬን” ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ይናገራል። ናዝራውያን ወደ “ማንኛውም የሞተ ነፍስ (NW)” (“ሬሳ” የ1954 እትም) አጠገብ እንዳይደርሱ ታዝዘው ነበር።—ዘኁልቁ 6:6
9. መጽሐፍ ቅዱስ የራሄል ‘ነፍስ በምትወጣበት ጊዜ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?
9 ይሁን እንጂ ሁለተኛ ልጅዋን ስትወልድ በአሳዛኝ ሁኔታ ስለሞተችው ራሄል የሚናገረውን የዘፍጥረት 35:18 ዘገባ በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? እዚያ ላይ “እርስዋም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው” የሚል ቃል እናነባለን። ይህ ምንባብ ራሄል በምትሞትበት ጊዜ ከእሷ የወጣ ሕያው ነገር እንደነበራት ያመለክታልን? በፍጹም፣ አያመለክትም። “ነፍስ” የሚለው ቃል አንድ ሰው ያለውን ሕይወትም ሊያመለክት እንደሚችል አስታውስ። ስለዚህ በዚህ ረገድ የራሄል “ነፍስ” በአጭሩ የሚያመለክተው “ሕይወቷን” ነው። ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች “ነፍሷ በምትወጣበት ጊዜ” የሚለውን ሐረግ “ሕይወቷ ሲያከትም” (ኖክስ)፣ “የመጨረሻዋን እስትንፋስ ስትተነፍስ” (ጀሩሳሌም ባይብል) እና “ሕይወቷ በተለያት ጊዜ” (ባይብል ኢን ቤዚክ ኢንግሊሽ) እያሉ የተረጎሙት ለዚህ ነው። ራሄል ስትሞት ከእሷ ተለይቶ የሄደ ሕያው የሆነ አንድ ምስጢራዊ ነገር እንዳለ የሚጠቁም ምንም ፍንጭ የለም።
10. ከሞት የተነሣው የመበለቲቱ ልጅ ነፍስ ‘ወደ እርሱ የተመለሰችው’ በምን መንገድ ነው?
10 ይህ ሁኔታ በ1 ነገሥት ምዕራፍ 17 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው የአንዲት መበለት ልጅ ትንሣኤ ጋር ተመሳሳይ ነው። በቁጥር 22 ላይ እንደተገለጸው ኤልያስ በልጁ ላይ ተኝቶ ሲጸልይ “እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናው ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፣ እርሱም ዳነ።” እዚህም ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል “ሕይወትን” ያመለክታል። በመሆኑም ኒው አሜሪካን ስታንዳርድ ባይብል “የልጁ ሕይወት ወደ እርሱ ተመለሰችና እንደገና ሕያው ሆነ” ይላል። አዎን፣ ልጁ መልሶ ያገኘው ሕይወት እንጂ ረቂቅ የሆነች ነገር አይደለም። ይህም ኤልያስ “እነሆ፣ ልጅሽ [ልጁን በጠቅላላ ያመለክታል] በሕይወት ይኖራል” ብሎ ለልጁ እናት ከተናገረው ቃል ጋር ይስማማል።—1 ነገሥት 17:23
ስለ መንፈስ ምን ለማለት ይቻላል?
11. “መንፈስ” የሚለው ቃል አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከሥጋው ተለይቶ ሕያው ሆኖ የሚቀጥልን ክፍል ሊያመለክት የማይችለው ለምንድን ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሲሞት “መንፈሱ ትወጣለች ወደ መሬትም ይመለሳል” ይላል። (መዝሙር 146:4 የ1879 እትም) ይህ ማለት መንፈሱ ቃል በቃል ከሥጋው ተለይቶ ሰውየው ከሞተም በኋላ ሕያው ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነውን? ይህ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም መዝሙራዊው ቀጥሎ “በዚያ ቀን አሳቡ ሁሉ ይጠፋል [NW]” (“አስተሳሰቡ ሁሉ ያከትማል፣” ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ይላል። ታዲያ መንፈስ ምንድን ነው? አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ከሰውየው ‘የሚወጣውስ’ እንዴት ነው?
12. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ምን ያመለክታሉ?
12 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት ቃሎች (የዕብራይስጡ ሩአህ፤ የግሪኩ ፕኒውማ) መሠረታዊ ትርጉማቸው “እስትንፋስ” ማለት ነው። በመሆኑም በአር ኤ ኖክስ የተዘጋጀው ትርጉም “መንፈሱ ትወጣለች” ከማለት ይልቅ “እስትንፋሱ ከሥጋው ትለያለች” የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። (መዝሙር 145:4) ሆኖም “መንፈስ” የሚለው ቃል ከመተንፈስም የበለጠን ነገር ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል ዘፍጥረት 7:22 በዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ ወቅት በሰውና በእንስሳት ሕይወት ላይ ስለደረሰው ጥፋት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት ነፍስ [“ኃይል፣” NW፤ ወይም መንፈስ፤ በዕብራይስጥ ሩአህ] እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ።” ስለዚህ “መንፈስ” በሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፣ በሰውም ሆነ በእንስሳት ውስጥ የሚሠራውንና በመተንፈስ ተጠብቆ የሚቆየውን የሕይወት ኃይል ያመለክት ይሆናል።
13. አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ መንፈሱ ወደ አምላክ የሚመለሰው እንዴት ነው?
13 ታዲያ መክብብ 12:7 (የ1879 እትም) አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ “መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል” ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህ ማለት መንፈሱ ቃል በቃል ጠፈርን አቋርጦ ወደ አምላክ ይሄዳል ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም። መንፈስ የሕይወት ኃይል በመሆኑ መንፈሱ “ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል” ሲባል የሰውየው የወደፊት ሕይወት ተስፋ ሙሉ በሙሉ የተመካው በአምላክ ላይ መሆኑን ያመለክታል። አንድን ሰው መንፈሱን ወይም የሕይወት ኃይሉን በመመለስ ዳግመኛ ሕያው ሊያደርገው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። (መዝሙር 104:30) ይሁን እንጂ አምላክ እንደዚያ የማድረግ ዓላማ አለውን?
“ይነሣል”
14. ኢየሱስ ወንድማቸውን በሞት በማጣታቸው ምክንያት ያዘኑትን የአልዓዛር እህቶች ለማሳረፍና ለማጽናናት ሲል ምን ብሎ ተናገረ? ምንስ አደረገ?
14 ከኢየሩሳሌም 3 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ ቢታንያ ተብላ በምትጠራ አነስተኛ ከተማ ውስጥ የሚኖሩት ማርታና ማርያም ወንድማቸው አልዓዛር ያለ ጊዜው በሞት በመቀጨቱ መሪር ሐዘን ላይ ወድቀዋል። ኢየሱስ አልዓዛርንና እህቶቹን ይወዳቸው ስለነበረ የሐዘናቸው ተካፋይ ሆኗል። እነዚህን እህትማማቾች እንዴት ሊያጽናናቸው ይችላል? ውስብስብ የሆነ ታሪክ ሳይሆን እውነት የሆነውን ነገር በመንገር ነበር። ኢየሱስ ቀላል በሆነ አነጋገር “ወንድምሽ ይነሣል” አላት። ከዚያም ኢየሱስ ወደ መቃብሩ ሄደና ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረውን ሰው ዳግመኛ ወደ ሕይወት በመመለስ አልዓዛርን ከሞት አስነሳው!—ዮሐንስ 11:18-23, 38-44
15. ኢየሱስ ለተናገረውና ላደረገው ነገር ማርታ የሰጠችው ምላሽ ምን ነበር?
15 አልዓዛር “ይነሣል” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ማርታ ተገርማ ነበርን? የተገረመች አይመስልም፤ ምክንያቱም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” ብላ መልሳለች። ቀድሞውንም በትንሣኤ ተስፋ ታምን ነበር። ከዚያም ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” አላት። (ዮሐንስ 11:23-25) አልዓዛርን ዳግመኛ ሕያው በማድረግ የተፈጸመው ተአምር የማርታን እምነት ያጠናከረው ከመሆኑም በላይ ሌሎች እምነት እንዲያድርባቸው አድርጓል። (ዮሐንስ 11:45) ይሁን እንጂ “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ ምንድን ነው?
16. “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?
16 “ትንሣኤ” የሚለው ቃል አናስታሲስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “ዳግመኛ መቆም” ማለት ነው። ግሪክኛውን የተረጎሙት የዕብራይስጥ ተርጓሚዎች አናስታሲስ የሚለውን ቃል “የሙታን ወደ ሕይወት መመለስ” (በዕብራይስጥ ቴኪያት ሐሜቲም) በማለት ተርጉመውታል።a ስለዚህ ትንሣኤ በሞት ምክንያት በድን የነበረው ግለሰብ ሕይወት እንዲዘራና ከመሞቱ በፊት የነበረው ሁኔታ እንዲመለስለት ማድረግን ይጨምራል።
17. (ሀ) የግለሰቦች ትንሣኤ ለይሖዋ አምላክና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ችግር የማይፈጥረው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉትን በተመለከተ ምን ተስፋ ሰጥቷል?
17 ይሖዋ አምላክ ወሰን የሌለው ጥበብና ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ ያለው በመሆኑ አንድን ሰው በቀላሉ ሊያስነሳው ይችላል። ሙታን በሕይወት በነበሩበት ዘመን የነበራቸውን አኗኗር፣ ባሕርያቸውን፣ የግል ታሪካቸውንና ማንነታቸውን በተመለከተ ያለውን እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ ማስታወስ ለእሱ ቀላል ነገር ነው። (ኢዮብ 12:13፤ ከኢሳይያስ 40:26 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ በአልዓዛር ሁኔታ ላይ እንደታየው ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታንን ለማስነሳት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው አለው። (ከሉቃስ 7:11-17 እና 8:40-56 ጋር አወዳድር።) እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቶስ “በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር፣” NW] ያሉት ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ . . . ይወጣሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:28, 29) አዎን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሖዋ በአእምሮው የያዛቸው ሁሉ እንደሚነሱ ተስፋ ሰጥቷል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ነፍስ ሟች ከመሆኗም በላይ ለሞት መፍትሔው ትንሣኤ ነው። ሆኖም በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወት ኖረው አልፈዋል። ከእነዚህ መካከል አምላክ በአእምሮው የያዛቸውና ትንሣኤያቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት የትኞቹ ናቸው?
18. ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው?
18 የይሖዋ አገልጋዮች ሆነው የጽድቅ ጎዳና የተከተሉ ሁሉ ይነሣሉ። ሆኖም በሚልዮን የሚቆጠሩት ሌሎች ሰዎች ከአምላክ የጽድቅ መስፈርቶች ጋር ይስማሙ እንደሆነና እንዳልሆነ ማሳየት የሚችሉበት አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ናቸው። አንድም ይሖዋ ያወጣቸውን ብቃቶች አያውቁም፤ አለዚያም ደግሞ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ በቂ ጊዜ አላገኙም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን እንደሚነሱ’ ስለሚናገር እነዚህም ሰዎች ቢሆን በአምላክ አእምሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፤ በመሆኑም ይነሣሉ።—ሥራ 24:15
19. (ሀ) ሐዋርያው ዮሐንስ ትንሣኤን በተመለከተ ምን ራእይ ተመልክቷል? (ለ) ‘በእሳት ባሕር ውስጥ የተጣለው’ ምንድን ነው? የዚህ መግለጫ ትርጉምስ ምንድን ነው?
19 ሐዋርያው ዮሐንስ ከሞት የተነሱ ሰዎች በአምላክ ዙፋን ፊት ቆመው የሚያሳይ አስደሳች ራእይ ተመልክቷል። ይህን ራእይ በመግለጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፣ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።” (ራእይ 20:12-14) ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው! በአምላክ አእምሮ ውስጥ ያሉት ሙታን ሁሉ የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ከሆነው ከሔድስ ወይም ከሲኦል ይወጣሉ። (መዝሙር 16:10፤ ሥራ 2:31) ከዚያም “ሞትና ሲኦል” ሙሉ በሙሉ መጥፋትን ወደሚያመለክተው ወደ “እሳት ባሕር” ይጣላሉ። የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ከናካቴው ይጠፋል።
በዓይነቱ ልዩ የሆነ ተስፋ!
20. በአሁኑ ጊዜ በሞት ያንቀላፉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትንሣኤ የሚያገኙት በምን ዓይነት አካባቢ ይሆናል?
20 በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት የሚነሱት ሰው አልባ በሆነች ምድር ላይ አይደለም። (ኢሳይያስ 45:18) ከሞት ሲነሱ አካባቢው ሁሉ ውበት ተላብሶ ያገኙታል፤ በተጨማሪም ለእነሱ የተዘጋጀ መኖሪያ፣ ልብስና የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል። (መዝሙር 67:6፤ 72:16፤ ኢሳይያስ 65:21, 22) እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያዘጋጀው ማን ነው? ምድራዊው ትንሣኤ ከመጀመሩ በፊት በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች መኖር እንዳለባቸው ግልጽ ነው። ግን እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?
21, 22. ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት’ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምን ተስፋ ይጠብቃቸዋል?
21 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ በዚህ ሥርዓት የ“መጨረሻ ቀን” ውስጥ እንዳለን ያሳያል።b (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሖዋ አምላክ በሰው ልጆች ጉዳዮች ጣልቃ ገብቶ ክፋትን ከምድር ገጽ የሚያጠፋበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። (መዝሙር 37:10, 11፤ ምሳሌ 2:21, 22) አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ ሰዎች በዚያን ጊዜ ምን ይሆናሉ?
22 ይሖዋ ጻድቃንን ከክፉዎች ጋር አንድ ላይ አያጠፋም። (መዝሙር 145:20) ፈጽሞ እንዲህ አድርጎ አያውቅም፤ ወደፊትም ምድርን ከክፋት በሚያጸዳበት ጊዜ እንዲህ አያደርግም። (ከዘፍጥረት 18:22, 23, 26 ጋር አወዳድር።) እንዲያውም የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ማንም ሊቆጥራቸው ያልቻለ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ [የተውጣጡ] እጅግ ብዙ ሰዎች” “ከታላቁ መከራ” እንደመጡ ይናገራል። (ራእይ 7:9-14) አዎን፣ እጅግ ብዙ ሰዎች ይህ ክፉ ዓለም ከሚጠፋበት ከታላቁ መከራ ተርፈው አምላክ ወደሚያመጣው አዲስ ዓለም ይገባሉ። በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች አምላክ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ለማላቀቅ በሚያዘጋጀው ግሩም ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠቀም ይችላሉ። (ራእይ 22:1, 2) በመሆኑም “እጅግ ብዙ ሰዎች” ሞትን መቅመስ አያስፈልጋቸውም። እንዴት ያለ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ተስፋ ነው!
ሞት የሌለበት ሕይወት
23, 24. ገነት በሆነች ምድር ላይ ሞት የሌለበት ሕይወት አግኝተህ ለመኖር ምን ማድረግ አለብህ?
23 በዚህ አስደናቂ ተስፋ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለንን? እንዴታ! ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ሰዎች ሞትን ሳይቀምሱ የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ አመልክቷል። ኢየሱስ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት ከማስነሳቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ማርታን “ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” ብሏት ነበር።—ዮሐንስ 11:26
24 ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህን? በሞት የተለዩህን የምትወዳቸውን ሰዎች ዳግመኛ ለማግኘት ትጓጓለህን? ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ብሏል። (1 ዮሐንስ 2:17) የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ የምትማርበትና ከፈቃዱም ጋር ተስማምተህ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ የምታደርግበት ጊዜ አሁን ነው። እንዲህ ካደረግህ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ካሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ትንሣኤ” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ባይገኝም እንኳ የትንሣኤ ተስፋ በኢዮብ 14:13፣ በዳንኤል 12:13 እና በሆሴዕ 13:14 ላይ ቁልጭ ብሎ ተገልጿል።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 98-107 ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
◻ በመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች “ነፍስ”ን ለማመልከት የገቡት ቃላት መሠረታዊ ትርጉም ምንድን ነው?
◻ በሞት ጊዜ ነፍስ ምን ትሆናለች?
◻ በመጽሐፍ ቅዱስ አባባል መሠረት ለሞት መፍትሔው ምንድን ነው?
◻ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ታማኝ ሰዎች በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምን ተስፋ ይጠብቃቸዋል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ነፍስ”—የፍጡራንን ሕይወት ለማመልከት ሲሠራበት
አንዳንድ ጊዜ “ነፍስ” የሚለው ቃል አንድ ሰው ወይም አንድ እንስሳ ያለውን ሕይወት ሊያመለክት ይችላል። ይህ አነጋገር ነፍስ የሚባለው ሰውየው ወይም እንስሳው ራሱ ነው የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ፍቺ አይለውጠውም። በምሳሌ ለማስረዳት:- አንድ ሰው በሕይወት አለ ስንል ሰውየው ሕያው ነው ማለታችን ነው። ሕይወት አለው ልንልም እንችላለን። በተመሳሳይ መንገድ በሕይወት ያለ ሰው ነፍስ ነው። ይሁንና ሰውየው ሕያው ሆኖ እያለ “ነፍስ” እንዳለው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ለምሳሌ ያህል አምላክ ሙሴን “ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋል” ብሎት ነበር። የሙሴ ጠላቶች ሕይወቱን ለማጥፋት ይፈልጉ እንደነበር ግልጽ ነው። (ዘጸአት 4:19፤ ከኢያሱ 9:24፤ ምሳሌ 12:10 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ “የሰው ልጅ . . . ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ [መጣ]” ብሎ በተናገረ ጊዜ ቃሉን ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 20:28፤ ከ10:28 ጋር አወዳድር።) በሁሉም ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል ትርጉም “የአንድ ፍጡር ሕይወት” ነው።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሁሉም ነፍሳት ናቸው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሃሚንግበርድ:- የዩናይትድ ስቴትስ የዓሣና የዱር አራዊት ጥበቃ አገልግሎት፣ ዋሺንግተን ዲ ሲ/ዲን ቢጊንስ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ለሞት መፍትሔው ትንሣኤ መሆኑን አሳይቷል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም።”—ዮሐንስ 11:26