የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 12—2 ነገሥት
ጸሐፊው:- ኤርምያስ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም እና ግብፅ
ተጽፎ ያለቀው:- 580 ከዘአበ
የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ920 ከዘአበ ገደማ-580 ከዘአበ
የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍም ሁከት ስለ ነገሠበት የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥታት የግዛት ታሪክ መዘገቡን ይቀጥላል። ኤልሳዕ የኤልያስን መጎናጸፊያ ያነሳ ሲሆን የኤልያስን መንፈስ እጥፍ በማግኘት ስለተባረከ ኤልያስ ካከናወናቸው 8 ተአምራት ይበልጥ 16 ተአምራትን አከናውኗል። ኢዩ ብቻ ለአጭር ጊዜ ለይሖዋ መቅናቱን ያሳየባት ከሃዲዋ እስራኤል እንደምትጠፋ የሚገልጽ ትንቢት መናገሩን ቀጥሏል። ሰሜናዊው መንግሥት የኋላ ኋላ በ740 ከዘአበ በአሦራውያን ተጠራርጎ እስኪጠፋ ድረስ ሌሎች ብዙ ነገሥታትም በክፋት ድርጊት ተዘፍቀው ነበር። በደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ለጊዜውም ቢሆን ክህደትን ጠራርገው ያጠፉ እንደ ኢዮሣፍጥ፣ ኢዮአስ፣ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ያሉ ግሩም ነገሥታት የነበሩ ቢሆንም በመጨረሻ በ607 ከዘአበ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲሁም የይሁዳን ምድር በማጥፋት የይሖዋን የቅጣት ፍርድ አስፈጽሟል። ይሖዋ ያስነገራቸው ትንቢቶች በዚህ መንገድ ፍጻሜያቸውን ከማግኘታቸውም ሌላ የቃሉ እውነተኝነት ተረጋግጧል!
2 ሁለተኛ ነገሥት መጀመሪያ ላይ ከአንደኛ ነገሥት ጋር አንድ ጥቅል ስለነበር መጽሐፉን ኤርምያስ ስለ መጻፉም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለ መሆኑና ስለ ትክክለኝነቱ የተጠቀሱት ማስረጃዎች ሁሉ ለሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍም ይሠራሉ። ተጽፎ የተጠናቀቀው በ580 ከዘአበ ሲሆን ከእስራኤሉ ንጉሥ ከአካዝያስ የግዛት ዘመን ጀምሮ እስከ 920 ከዘአበ ድረስ ያለውን ጊዜ በመሸፈን ዮአኪን በግዞት በተወሰደበት 37ኛ ዓመት ማለትም በ580 ከዘአበ ያበቃል።—1:1፤ 25:27
3 የሁለተኛ ነገሥትን ዘገባ የሚደግፉት የአርኪኦሎጂ ግኝቶች የመጽሐፉን እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል በሞዓብና በእስራኤል መካከል ስለተደረገው ውጊያ ሞዓባዊው ንጉሥ ያስጻፈውን መግለጫ የያዘው የታወቀው የሞዓባውያን ጽላት አንዱ ነው። (3:4, 5) እንዲሁም በለንደን ብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ ለሕዝብ የሚታየው አሦራዊው ስልምናሶር ሳልሳዊ ያሠራውና የእስራኤሉን ንጉሥ ኢዩን በስም የሚጠቅሰው የጥቁር ድንጋይ ሐውልትም አለ። ምናሔምን፣ አካዝንና ፋቁሔን ጨምሮ አንዳንድ የእስራኤልንና የይሁዳን ነገሥታት የሚጠቅሱት የአሦራውያኑ ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ሳልሳዊ (ፑል) ያስቀረጻቸው ፊደላትም አሉ።—15:19, 20፤ 16:5-8
4 ይሖዋ በገዛ ሕዝቡ ላይ ስላስፈጸመው የቅጣት ፍርድ መጽሐፉ በፍጹም ሐቀኝነት የሚያቀርበው ዘገባ ለትክክለኛነቱ የማያሻማ ማስረጃ ነው። በመጀመሪያ የእስራኤል ቀጥሎም የይሁዳ መንግሥት በየተራ የቅጣት በትር መቅመሳቸው በዘዳግም 28:15–29:28 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው የይሖዋ ትንቢታዊ የፍርድ ቃል ያለውን ኃይል እንድናስታውስ ያደርገናል። እነዚህ መንግሥታት በጠፉ ጊዜ “በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መርገም ሁሉ ያወርድባት ዘንድ የእግዚአብሔር ቁጣ በዚህች ምድር ነደደ።” (ዘዳ. 29:27፤ 2 ነገ. 17:18፤ 25:1, 9-11) በሁለተኛ ነገሥት ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ሌሎች ክንውኖችም በሌሎች ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተብራርተዋል። በሉቃስ 4:24-27 ላይ ኢየሱስ በገዛ ትውልድ ስፍራው ተቀባይነት ያላገኘው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት ስለ ኤልያስና በሰራፕታ ስለነበረችው መበለት ከጠቀሰ በኋላ ስለ ኤልሳዕና ንዕማን ተናግሯል። በመሆኑም የአንደኛም ሆነ የሁለተኛ ነገሥት መጻሕፍት የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆናቸው ተረጋግጧል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
33 የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ የእስራኤልንና የይሁዳን መንግሥታት ለጥፋት ስለዳረጋቸው አካሄድ በሰፊው የሚተርክ ቢሆንም ለይሖዋና ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ያላቸውን ፍቅር በማሳየታቸው በረከቱን ስላገኙ ግለሰቦች የሚገልጹ ብዙ ምሳሌዎችን ይዟል። ሱነማዊቷ ሴት ከእርሷ በፊት በሰራፕታ እንደነበረችው መበለት ሁሉ ለአምላክ ነቢይ ባሳየችው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ምክንያት ብዙ በረከት አግኝታለች። (4:8-17, 32-37) ኤልሳዕ አንድ መቶ ሰዎችን በ20 ቁራሽ በመገበ ጊዜ ይሖዋ መቼም ቢሆን እጁ አጭር እንዳይደለ የታየ ሲሆን ኢየሱስም ከጊዜ በኋላ ተመሳሳይ ተአምር አከናውኗል። (2 ነገ. 4:42-44፤ ማቴ. 14:16-21፤ ማር. 8:1-9) ኢዮናዳብ የበኣል አምላኪዎች ሲጠፉ ያይ ዘንድ በኢዩ ሠረገላ ላይ እንዲሳፈር መጋበዙ እንዴት በረከት እንደሆነለት አስተውል። ግብዣ የቀረበለት ለምንድን ነው? በቅንዓት ይገሰግስ የነበረውን ኢዩን ሰላም ለማለት በመውጣት አዎንታዊ እርምጃ በመውሰዱ ነው። (2 ነገ. 10:15, 16) በመጨረሻም ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ባሳዩት ትሕትና እንዲሁም ለይሖዋ ስምና ሕግ በነበራቸው አክብሮት የተዉትን ግሩም ምሳሌ እናገኛለን። (19:14-19፤ 22:11-13) እነዚህ ልንኮርጃቸው የሚገቡ ድንቅ ምሳሌዎች ናቸው።
34 ይሖዋ የተሾሙ አገልጋዮቹን የሚያቃልሉትን አይታገስም። ዱርዬ ብላቴኖች ኤልሳዕን የይሖዋ ነቢይ በመሆኑ ምክንያት ባፌዙበት ጊዜ በቅጽበት ተበቅሎለታል። (2:23, 24) ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ ለንጹሐን ደም ያለው ግምት ከፍ ያለ ነው። የአክዓብ ቤት ከባድ ፍርድ የተፈረደበት በበኣል አምልኮ በመካፈሉ ብቻ ሳይሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባፈሰሰው ደም ነው። በመሆኑም ኢዩ የተቀባው “የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ሁሉ ደም ከኤልዛቤል እጅ” ለመበቀል ነበር። በኢዮራም ላይ የፍርድ እርምጃ በተወሰደበት ጊዜ ኢዩ ‘ስለ ናቡቴና ልጆቹ ደም የሚወሰድ እርምጃ’ ስለመሆኑ ይሖዋ የተናገረውን ቃል አስታውሷል። (9:7, 26) በተመሳሳይም የኋላ ኋላ ይሁዳን ለጥፋት የዳረጋት ምናሴ ያፈሰሰው ደም ነበር። ምናሴ የሐሰት አምልኮ በመከተል የፈጸመው ኃጢአት እንዳይበቃ ‘ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር በደም ሞልቷት’ ነበር። ምንም እንኳን ምናሴ ንስሐ ገብቶ ከመጥፎ ጎዳናው ቢመለስም የደም ዕዳው እንዳለ ነበር። (2 ዜና 33:12, 13) ጥሩ ንጉሥ የነበረው የኢዮስያስ አገዛዝና ጣዖት አምልኮን ጠራርጎ ለማጥፋት የወሰደው እርምጃ እንኳን በምናሴ የግዛት ዘመን የፈሰሰው ደም ያስከተለውን ማኅበረሰባዊ ተጠያቂነት ሊሽረው አልቻለም። ከዓመታት በኋላ ይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ሲልክ ‘ምናሴ ኢየሩሳሌምን በንጹሕ ደም ስለ ሞላ ይራራላቸው ዘንድ እንዳልወደደ’ ተናግሯል። (2 ነገ. 21:16፤ 24:4) በተመሳሳይም ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበረችው ኢየሩሳሌም ካህናት “በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ” ይመጣባቸው ዘንድ የነቢያትን ደም ያፈሰሱት ሰዎች ልጆች በመሆናቸው ከተማዋ መጥፋት እንደሚኖርባት ተናግሯል። (ማቴ. 23:29-36) አምላክ የፈሰሰውን የንጹሐን ደም በተለይም ደግሞ ‘ስለ እግዚአብሔር ቃል የታረዱትን’ ሰዎች ደም እንደሚበቀል ዓለምን አስጠንቅቋል።—ራእይ 6:9, 10
35 ይሖዋ ትንቢታዊ ፍርዱን ወደ ፍጻሜው የሚያመጣበት ፍጹም አስተማማኝ የሆነ መንገድ በሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ተንጸባርቋል። ሦስት ታላላቅ ነቢያት ማለትም ኤልያስ፣ ኤልሳዕና ኢሳይያስ ተጠቅሰውልናል። እያንዳንዳቸው የተናገሯቸውም ትንቢቶች አስገራሚ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ተጠቅሷል። (2 ነገ. 9:36, 37፤ 10:10, 17፤ 3:14, 18, 24፤ 13:18, 19, 25፤ 19:20, 32-36፤ 20:16, 17፤ 24:13) በተጨማሪም ኢየሱስ በተራራ ላይ በተአምራዊ መንገድ በተለወጠ ጊዜ ኤልያስ ከሙሴና ከታላቁ ነቢይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብሮ መታየቱ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። (ማቴ. 17:1-5) ጴጥሮስ የዚህን ክንውን ታላቅነት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፣ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።”—2 ጴጥ. 1:19
36 በሁለተኛ ነገሥት ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ክንውኖች ይሖዋ የሐሰት ሃይማኖትን በሚከተሉና ሆን ብለው የንጹሐንን ደም በሚያፈስሱ ሰዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ ጥፋት እንደሆነ በግልጽ ያስረዳሉ። ይሁንና ይሖዋ ‘ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን’ ሲል ለሕዝቡ ሞገሱንና ምሕረቱን አልነፈጋቸውም። (2 ነገ. 13:23) “ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት” ሲል በሕይወት አቆይቷቸዋል። (8:19) በዚህ ዘመንም ወደ እርሱ ለሚመለሱት ሰዎች ተመሳሳይ ምሕረት ያሳያል። የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባዎችና የተስፋ ቃሎች መመርመራችን “የዳዊት ልጅ” ኢየሱስ ክርስቶስ ማለትም ተስፋ የተሰጠበት ዘር የሚያስተዳድረውንና ከደም መፋሰስና ከክፋት ሁሉ ነፃ የሆነውን መንግሥት ይበልጥ በትምክህት እንድንጠባበቅ ያደርገናል!—ማቴ. 1:1፤ ኢሳ. 2:4፤ መዝ. 145:20