በእምነታቸው ምሰሏቸው | ኤልያስ
እስከ መጨረሻው ጸንቷል
ኤልያስ፣ ንጉሥ አክዓብ መሞቱን ሰማ። አረጋዊው ነቢይ በሐሳብ ተውጦ ፂሙን ሲያፍተለትል በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ፤ ኤልያስ ላለፉት በርካታ አሥርተ ዓመታት ከዚህ ክፉ ንጉሥ ጋር በተያያዘ ስላጋጠሙት ነገሮች መለስ ብሎ እያሰበ ነው። በእርግጥም ይህ ነቢይ ብዙ ችግሮች አሳልፏል! አክዓብና ንግሥት ኤልዛቤል ነቢዩን አስፈራርተውታል እንዲሁም አሳድደውታል፤ ኤልያስ ሕይወቱን እንኳ ሊያጣ የተቃረበበት ጊዜ ነበር። ኤልዛቤል በርካታ የይሖዋ ነቢያትን ስታስገድል ንጉሡ በዝምታ ከመመልከት ውጪ አንዳች ያደረገው ነገር የለም። እነዚህ ባልና ሚስት በጣም ስግብግብ ከመሆናቸው የተነሳ ጻድቅ በሆነው በናቡቴ ላይ ሴራ በመጠንሰስ ይህን ንጹሕ ሰው እስከ ልጆቹ አስገድለውታል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ፣ አክዓብም ሆነ የእሱ ሥርወ መንግሥት በሙሉ እንደሚፈረድበት የሚገልጽ መልእክት በኤልያስ በኩል ልኮበት ነበር። አምላክ የተናገረው ቃል አሁን ፍጻሜውን እያገኘ ነው። አክዓብ ልክ ይሖዋ በተናገረው መንገድ ሞተ።—1 ነገሥት 18:4፤ 21:1-26፤ 22:37, 38፤ 2 ነገሥት 9:26
ኤልያስ ግን አሁንም ቢሆን ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚጠብቁት አልጠፋውም። አክዓብ ቢሞትም ሚስቱ ኤልዛቤል በሕይወት አለች፤ በመሆኑም በቤተሰቧም ሆነ በመላው ብሔር ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ማሳደሯን ቀጥላለች። ኤልያስ ከዚህ በኋላም ብዙ ችግሮች ያጋጥሙታል፤ በተጨማሪም ወዳጁ ለሆነውና ወደፊት እሱን ተክቶ ለሚያገለግለው ለኤልሳዕ ማስተማር ያለበት ገና ብዙ ነገር አለ። እስቲ ለኤልያስ የተሰጡትን ሦስት የመጨረሻ ተልእኮዎች እንመልከት። የኤልያስ እምነት፣ ፈተናዎችን በጽናት እንዲቋቋም የረዳው እንዴት እንደሆነ መመልከታችን እኛም በምንኖርበት አስቸጋሪ ዘመን ውስጥ እምነታችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ለመገንዘብ ይረዳናል።
በአካዝያስ ላይ የፍርድ መልእክት ማስተላለፍ
የአክዓብና የኤልዛቤል ልጅ የሆነው አካዝያስ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል። አካዝያስ ከወላጆቹ ስህተት ከመማር ይልቅ እነሱ የሄዱበትን የክፋት መንገድ ተከተለ። (1 ነገሥት 22:52) ልክ እንደ ወላጆቹ እሱም የባአል አምላኪ ነው። የባአል አምልኮ፣ ሰዎች ወራዳ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ሃይማኖት ነው፤ አምላኪዎቹ በቤተ መቅደስ ውስጥ ዝሙት ይፈጽሙ ይባስ ብሎም ልጆቻቸውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። አካዝያስ አካሄዱን ለመቀየርና ሕዝቡ ከክህደት ጎዳናቸው ተመልሰው ይሖዋን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ለመርዳት እንዲነሳሳ ሊያደርገው የሚችል ነገር ይኖር ይሆን?
ትዕቢተኛ የሆነው ይህ ወጣት ንጉሥ ከባድ አደጋ አጋጠመው። በቤቱ ሰገነት ላይ ካለው ክፍል በርብራቡ ሾልኮ በመውደቁ ጉዳት ደረሰበት። የሚገርመው ነገር አካዝያስ ሕይወቱ አደጋ ላይ በወደቀበት በዚህ ሰዓት እንኳ ወደ ይሖዋ አልተመለሰም። ከዚህ ይልቅ ከደረሰበት ጉዳት ይድን እንደሆነ ለማወቅ ሲል የኤቅሮንን አምላክ ባአልዜቡብን እንዲጠይቁለት መልእክተኞች ላከ፤ ኤቅሮን የእስራኤላውያን ጠላት የሆነችው የፍልስጤም ከተማ ናት። የአካዝያስ ድርጊት ይሖዋን በጣም አስቆጣው። የይሖዋ መልአክ ለኤልያስ ተገለጠለትና የአካዝያስን መልእክተኞች መንገድ ላይ እንዲያገኛቸው ነገረው። ኤልያስም የአካዝያስ መልእክተኞች ለንጉሣቸው አስደንጋጭ መልእክት ይዘው እንዲመለሱ አደረገ። አካዝያስ፣ በእስራኤል አምላክ የሌለ ይመስል ወደ ፍልስጤማውያን አምላክ መልእክተኞች መላኩ ከባድ ኃጢአት ነበር። በመሆኑም ይሖዋ አካዝያስን “ከተኛህበት አልጋ ላይ አትነሳም” አለው።—2 ነገሥት 1:2-4
አካዝያስ ግን ንስሐ ከመግባት ይልቅ “እናንተን ለማግኘት የመጣውና ይህን የነገራችሁ ሰው ምን ይመስላል?” ብሎ መልእክተኞቹን ጠየቃቸው። እነሱም የነቢዩን አለባበስ ነገሩት፤ አካዝያስ ይህን ሲሰማ የነቢዩን ማንነት ወዲያውኑ ስላወቀ “ይሄማ ቲሽባዊው ኤልያስ ነው” አለ። (2 ነገሥት 1:7, 8) የኤልያስ ሕይወት ቀላልና አምላክን በማገልገል ላይ ያተኮረ ከመሆኑ የተነሳ ተራ በሆነው አለባበሱ ብቻ መለየት መቻሉ ትኩረት የሚስብ ነው። የኤልያስ ሕይወት፣ በስግብግብነታቸው ከሚታወቁት ከአካዝያስና ከወላጆቹ ምንኛ የተለየ ነበር! ኤልያስ የተወው ምሳሌ የኢየሱስን ምክር በተግባር እንድናውል ያነሳሳናል፤ ኢየሱስ አኗኗራችንን ቀላል እንድናደርግ ይኸውም ዓይናችን ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ እንዲያተኩር መክሮናል።—ማቴዎስ 6:22-24
አካዝያስ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ቆርጦ ስለተነሳ ኤልያስን እንዲያስሩት አንድ ሃምሳ አለቃና በሥሩ ያሉትን 50 ሰዎች ላከ። ሰዎቹ ኤልያስን “ተራራው አናት ላይ ተቀምጦ” አገኙት፤a ሃምሳ አለቃውም “ንጉሡ ‘ና ውረድ’ ብሎሃል” የሚል ቀጭን ትእዛዝ ለኤልያስ አስተላለፈ። ይህን ሲል ኤልያስ ከተራራው ወርዶ ወደሚገደልበት ቦታ አብሯቸው እንዲሄድ ማዘዙ ሊሆን ይችላል። እስቲ አስበው! እነዚያ ወታደሮች ኤልያስ “የእውነተኛው አምላክ ሰው” እንደሆነ ቢያውቁም ሊያስፈራሩት ሞከሩ። እነዚህ ሰዎች ምንኛ ተሳስተዋል! ኤልያስ፣ ሃምሳ አለቃውን “እኔ የአምላክ ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ከአንተ ጋር ያሉትን 50 ሰዎች ይብላ” አለው። ይሖዋም እርምጃ ወሰደ! “እሳት ከሰማይ ወርዶ [ሃምሳ አለቃውንና] 50ዎቹን ሰዎች በላ።” (2 ነገሥት 1:9, 10) የእነዚህ ወታደሮች አሟሟት፣ ይሖዋ የእሱን አገልጋዮች የሚያቃልሉ ወይም የሚንቁ ሰዎችን በቸልታ እንደማያልፍ የሚያሳይ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ነው።—1 ዜና መዋዕል 16:21, 22
አካዝያስ ሌላ ሃምሳ አለቃ በሥሩ ካሉት 50 ሰዎች ጋር እንደገና ወደ ኤልያስ ላከ። ይሄኛው ሃምሳ አለቃ ደግሞ ከመጀመሪያው የባሰ ነበር። በእሳት የተቃጠሉትን 51 ሰዎች አመድ በተራራው ግርጌ ላይ አይቶ ሊሆን ቢችልም እነሱ ካጋጠማቸው ነገር አንዳች ትምህርት አልወሰደም። በዚያ ላይ ደግሞ ከእሱ በፊት እንደመጣው ትዕቢተኛ ሃምሳ አለቃ ኤልያስን “ና ውረድ” ብሎ በማዘዝ ብቻ አላቆመም፤ ከዚህ ይልቅ ነቢዩን “ና ፈጥነህ ውረድ” አለው። እንዴት ያለ ሞኝ ሰው ነው! ልክ እንደ መጀመሪያዎቹ ሰዎች ሁሉ ይህን ሃምሳ አለቃና ወታደሮቹንም እሳት ወርዶ በላቸው። ከሁሉ የባሰው ሞኝ ግን ንጉሡ ራሱ ነበር። ምንም ያልተፈጠረ ይመስል ለሦስተኛ ጊዜ ወታደሮችን ወደ ኤልያስ ላከ። ጥሩነቱ ይሄኛው ሃምሳ አለቃ ብልህ ሰው ነው። በትሕትና ወደ ኤልያስ በመቅረብ እሱም ሆነ ወታደሮቹ እንዳይሞቱ ለመነው። የእውነተኛው አምላክ ሰው የሆነው ኤልያስም የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ለዚህ ሰው ምሕረት አሳየው። የይሖዋ መልአክ ኤልያስን ከወታደሮቹ ጋር እንዲሄድ ነገረው። ኤልያስም የተሰጠውን መመሪያ ተከትሎ ወደ ክፉው ንጉሥ በመሄድ የይሖዋን የፍርድ መልእክት በድጋሚ አሳወቀው። ልክ አምላክ እንደተናገረው አካዝያስ ሞተ። አካዝያስ ንጉሥ ሆኖ የገዛው ለሁለት ዓመት ብቻ ነው።—2 ነገሥት 1:11-17
ኤልያስ በዙሪያው ያሉ ሰዎች ግትርና ዓመፀኛ ቢሆኑም እሱ በጽናት ይሖዋን ማገልገሉን እንዲቀጥል የረዳው ምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን ለእኛም ጠቃሚ ነው። አንድ የምትወደው ሰው የሰጠኸውን መልካም ምክር አልሰማ ብሎ መጥፎ የሆነ አካሄድ መከተሉን በመቀጠሉ ስሜትህ ተጎድቶ ያውቃል? እንዲህ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው? ወታደሮቹ ኤልያስን ያገኙት “ተራራው አናት ላይ” መሆኑ የሚሰጠን ትምህርት ይኖር ይሆን? ኤልያስ ወደ ተራራው የወጣው ለምን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ ሆኖም እንደ እሱ ላለ የጸሎት ሰው እንዲህ ያለው ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ ወደ አምላኩ ይበልጥ ለመቅረብ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት ጥርጥር የለውም። (ያዕቆብ 5:16-18) እኛም በተመሳሳይ ብቻችንን ሆነን አምላክን የምናነጋግርበት ቋሚ ጊዜ መመደብ ይኖርብናል፤ በዚህ ጊዜ አምላክን በስሙ እየጠራን ችግራችንን እና ጭንቀታችንን ሁሉ አውጥተን ልናካፍለው እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን በዙሪያችን ያሉት ሰዎች ሞኝነት የተንጸባረቀበትና ጎጂ የሆነ አካሄድ ቢከተሉም እንኳ እኛ በጽናት እንድንቀጥል ይረዳናል።
ኃላፊነቱን ማስተላለፍ
ኤልያስ የተሰጠውን ኃላፊነት ለኤልሳዕ የሚያስተላልፍበት ጊዜ ደረሰ። ምን እንዳደረገ እስቲ እንመልከት። ኤልያስና ኤልሳዕ ከጊልጋል ተነስተው ጉዞ ጀመሩ፤ በዚህ ጊዜ ኤልያስ 11 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቤቴል ሊሄድ እንደሆነ በመግለጽ ኤልሳዕን እዚያው እንዲቆይ ጠየቀው። ኤልሳዕ ግን “ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ እምላለሁ፣ ከአንተ አልለይም” የሚል መልስ ሰጠው። ሁለቱ ሰዎች ቤቴል ሲደርሱ ደግሞ ኤልያስ 22 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ኢያሪኮ ብቻውን እንደሚሄድ ለኤልሳዕ ነገረው። ኤልሳዕ ግን አሁንም እንደቀድሞው ዓይነት ምላሽ ሰጠው። ኢያሪኮ ከደረሱ በኋላም ኤልያስ 8 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሊሄድ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ኤልሳዕ እንዲቀር ለሦስተኛ ጊዜ ጠየቀው። በዚህ ጊዜም ኤልሳዕ ከኤልያስ ለመለየት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገለጸ።—2 ነገሥት 2:1-6
ኤልሳዕ ግሩም ባሕርይ የሆነውን ታማኝ ፍቅርን አሳይቷል። ታማኝ ፍቅር ሲባል ከሚወዱት አካል ጋር መጣበቅንና እሱን የሙጥኝ ማለትን ያመለክታል፤ ሩት ለናኦሚ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ነበራት። (ሩት 1:15, 16) በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይህን ባሕርይ ማዳበር ያስፈልጋቸዋል። አንተስ እንደ ኤልሳዕ ይህን ባሕርይ የማዳበርን አስፈላጊነት ተገንዝበሃል?
ኤልያስ ወጣቱ ጓደኛው ባሳየው ታማኝ ፍቅር ምንኛ ተበረታቶ ይሆን! ኤልሳዕም ቢሆን እንዲህ ያለ ፍቅር በማሳየቱ ኤልያስ የፈጸመውን የመጨረሻ ተአምር የመመልከት መብት አግኝቷል። ሁለቱ ሰዎች ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ደረሱ፤ ይህ ወንዝ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ጥልቀት ያለው ከመሆኑም ሌላ የሚፈስሰው በፍጥነት ነው። በወንዙ ዳርቻ ላይ ቆመው እያለ ኤልያስ የነቢይ ልብሱን አውልቆ ውኃውን መታው፤ ውኃውም ግራና ቀኝ ተከፈለ! ይህ ተአምር ሲፈጸም ከኤልሳዕ ሌላ “ከነቢያት ልጆች መካከል 50ዎቹ” ተመልክተዋል፤ እነዚህ ሰዎች በእስራኤል ውስጥ ንጹሑን አምልኮ በማራመድ ረገድ አመራር ለመስጠት የሚያስችል ሥልጠና እያገኙ ካሉት ሰዎች መካከል ሳይሆኑ አይቀሩም። (2 ነገሥት 2:7, 8) ይህን ሥልጠና የሚመራው ኤልያስ መሆን አለበት። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ኤልያስ፣ በአገሪቱ የቀረው ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ እሱ ብቻ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ግን የይሖዋ አገልጋዮች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ሲሄድ ተመልክቷል፤ በእርግጥም ይህ ነቢይ ጽናት በማሳየቱ ይሖዋ ክሶታል።—1 ነገሥት 19:10
ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት እንዳደርግልህ የምትፈልገውን ጠይቀኝ” አለው። ኤልያስ ከኤልሳዕ የሚለይበት ጊዜ እንደደረሰ ተገንዝቧል። ኤልያስ፣ ወጣቱ ጓደኛው የተለያዩ መብቶችና ኃላፊነቶች እንደሚያገኝ ቢያውቅም አልቀናበትም። ከዚህ ይልቅ በሚችለው መንገድ ሁሉ ኤልሳዕን ለመርዳት ጓጉቷል። ኤልሳዕ የጠየቀው አንድ ነገር ብቻ ነበር፦ “እባክህ፣ መንፈስህ በእጥፍ ይሰጠኝ” አለው።” (2 ነገሥት 2:9) ኤልሳዕ ይህን ሲል አምላክ ለኤልያስ የሰጠውን መንፈስ ቅዱስ ለእሱ እጥፍ አድርጎ እንዲሰጠው መጠየቁ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የበኩር ልጅ የሚያገኘው ዓይነት ውርሻ እንዲሰጠው መለመኑ ነው፤ በሙሴ ሕግ መሠረት የበኩር ልጅ የቤተሰቡ ራስ የመሆን ኃላፊነት ስለሚቀበል አባቱ ውርስ ሲያከፋፍል ከሁሉ የበለጠውን ድርሻ ማለትም ሁለት እጥፍ ይሰጠው ነበር። (ዘዳግም 21:17) ኤልሳዕም የኤልያስ መንፈሳዊ ወራሽ ከመሆኑ አንጻር፣ የሚሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት የኤልያስን የድፍረት መንፈስ ማግኘት እንደሚያስፈልገው ተረድቶ ነበር።
ኤልያስ ይህን ጥያቄ ይሖዋ ራሱ እንዲመልስ በመተው ትሕትና አሳይቷል። ይሖዋ፣ አረጋዊው ነቢይ ሲወሰድ ኤልሳዕ እንዲያይ ከፈቀደለት ኤልሳዕ የጠየቀውን ነገር ይፈጽምለታል ማለት ነው። የረጅም ጊዜ ወዳጆች የሆኑት እነዚህ ሁለት ሰዎች “እየተጨዋወቱ በመሄድ ላይ ሳሉ” አንድ አስደናቂ ነገር ተከናወነ!—2 ነገሥት 2:10, 11
በኤልያስና በኤልሳዕ መካከል የነበረው ወዳጅነት ሁለቱም ሰዎች በአስቸጋሪ ጊዜያት እንዲጸኑ ረድቷቸዋል
እንግዳ የሆነ ብርሃን በሰማይ ላይ የታየ ሲሆን ብርሃኑ ወደ ሁለቱ ሰዎች እየቀረበ መጣ። ከዚያም አውሎ ነፋስ ሲነሳ የሚያሰማው ዓይነት ኃይለኛ ድምፅ በድንገት ተሰማ፤ እንዲሁም አንድ ደማቅ ነገር እየበረረ ወደ ሁለቱ ሰዎች በመቅረብ ለያያቸው። ኤልያስና ኤልሳዕ ይህን ሲያዩ በድንጋጤ ተውጠው መሆን አለበት። በእሳት የተሠራ ይመስል ደማቅ ብርሃን ያለው ሠረገላ ተመለከቱ። ኤልያስ የሚሄድበት ጊዜ እንደደረሰ ገባው። ታዲያ ሠረገላው ላይ ተሳፍሮ ይሆን? ዘገባው የሚገልጸው ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ፣ አውሎ ነፋሱ ኤልያስን ከመሬት ከፍ ከፍ እያደረገ ወደ ላይ ይዞት ወጣ!
ኤልሳዕ ሁኔታውን በአግራሞት እየተከታተለ ነው። ይህን አስደናቂ ክንውን ማየት ስለቻለ፣ የኤልያስን የድፍረት መንፈስ “በእጥፍ” ለማግኘት ያቀረበውን ጥያቄ ይሖዋ እንደሚመልስለት እርግጠኛ ሆነ። በዚህ ወቅት ግን ኤልሳዕ እጅግ ስላዘነ ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ የሚችል አይመስልም። በጣም የሚወደው አረጋዊው ወዳጁ ወዴት እንደሚሄድ የሚያውቀው ነገር የለም፤ ኤልያስን ዳግመኛ እንደማያገኘው ተሰምቶት መሆን አለበት። ኤልሳዕ “አባቴ፣ አባቴ፣ እነሆ የእስራኤል ሠረገላና ፈረሰኞቹ!” በማለት ጮኸ። የሚወደው አሠልጣኙ እየራቀ ሄዶ ከዓይኑ ተሰወረ፤ ኤልሳዕም በሐዘን ተውጦ ልብሱን ለሁለት ቀደደው።—2 ነገሥት 2:12
ኤልያስ ወደ ሰማይ ከፍ እያለ ሲሄድ የጓደኛውን የሐዘን ጩኸት ሰምቶ ይሆን? ምናልባትም እሱ ራሱ አልቅሶ ይሆን? ኤልያስ ምን እንደተሰማው ባናውቅም እንደ ኤልሳዕ ያለ ጓደኛ የነበረው መሆኑ ያጋጠሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት እንደረዳው ተገንዝቦ መሆን አለበት። እኛም ኤልያስ ከተወው ምሳሌ በመማር፣ አምላክን ከሚወዱና የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ከሚጥሩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረታችን ጠቃሚ ነው!
የመጨረሻው ተልእኮ
ኤልያስ የተወሰደው ወዴት ነው? አንዳንድ ሃይማኖቶች ኤልያስ ወደ ሰማይ ሄዶ ከአምላክ ጋር መኖር እንደጀመረ ያስተምራሉ። ይህ ግን ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ከበርካታ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እሱ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ወደ ሰማይ የወጣ ሰው እንደሌለ ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13) በመሆኑም ኤልያስ “በአውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ወደ ሰማይ ወጣ” የሚለውን ዘገባ ስናነብ ‘ወደ የትኛው ሰማይ?’ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው። (2 ነገሥት 2:11) መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማይ” የሚለውን ቃል ይሖዋ የሚኖርበትን ቦታ ለማመልከት ብቻ ሳይሆን ደመና ያለበትንና አእዋፍ የሚበሩበትን በዓይናችን የምናየውን ሰማይ ለመግለጽም ይጠቀምበታል። (መዝሙር 147:8) ኤልያስ የወጣው በዓይን ወደሚታየው ሰማይ ነው። ከዚያስ?
ይሖዋ ይህን ተወዳጅ ነቢይ ወደ አዲስ ምድብ ወሰደው፤ ኤልያስ የእስራኤል መንግሥት አጎራባች በሆነችው በይሁዳ ማገልገል ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚያሳየው ከሰባት ዓመታት ገደማ በኋላም ኤልያስ በዚህ ምድቡ ላይ ማገልገሉን ቀጥሏል። በወቅቱ ይሁዳን የሚገዛው ደግሞ ክፉው ንጉሥ ኢዮራም ነበር። ኢዮራም የአክዓብንና የኤልዛቤልን ልጅ አግብቶ ስለነበር የእነዚህ ባልና ሚስት መጥፎ ተጽዕኖ በግዛቱ ውስጥ ይታይ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ፣ የፍርድ መልእክት የያዘ ደብዳቤ ለኢዮራም እንዲጽፍለት ኤልያስን አዘዘው። ልክ ይሖዋ እንደተናገረው ኢዮራም አሰቃቂ በሆነ መንገድ ሞተ። ከዚያ የባሰው ደግሞ “ሲሞት ማንም አላዘነለትም።”—2 ዜና መዋዕል 21:12-20
በዚህ ክፉ ሰውና በኤልያስ መካከል ያለው ልዩነት ምንኛ ሰፊ ነው! ኤልያስ መቼ ወይም እንዴት እንደሞተ አናውቅም። ይሁን እንጂ ማንም እንዳላዘነለት እንደ ኢዮራም ዓይነት አሟሟት እንዳልሞተ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኤልሳዕ ጓደኛውን በማጣቱ በጣም አዝኖ መሆን አለበት። ሌሎቹ ታማኝ ነቢያትም እንዲሁ ሳይሰማቸው አልቀረም። ኤልያስ ከሞተ ከ1,000 ዓመታት ገደማ በኋላም ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አሳይቷል፤ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ራእይ ላይ ይሖዋ ይህ ተወዳጅ ነቢይ እንዲታይ አድርጓል። (ማቴዎስ 17:1-9) አንተስ የኤልያስን ምሳሌ መከተልና ልክ እንደ እሱ ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል እምነት ማዳበር ትፈልጋለህ? ከሆነ አምላክን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት፣ በሕይወትህ ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ለመስጠት እንዲሁም አዘውትረህ ከልብህ ለመጸለይ ጥረት አድርግ። አንተም አፍቃሪ የሆነው አባታችን ይሖዋ የሚወድህ ዓይነት ሰው እንድትሆን ምኞታችን ነው!
a አንዳንድ ምሁራን፣ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ተራራ የቀርሜሎስ ተራራ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ኤልያስ ከአምላክ ባገኘው ኃይል ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የባአልን ነቢያት በዚህ ተራራ ላይ ድል አድርጎ ነበር። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኤልያስ በዚህ ወቅት የትኛው ተራራ ላይ እንደነበረ አይናገርም።