ዕድሜ።
አንድ ሰው የኖረበትን ጊዜ ያመለክታል፤ አብዛኛውን ጊዜ በዓመታት፣ በወራትና በቀናት ተቆጥሮ ይገለጻል። በዕብራይስጥ የአንድን ግለሰብ ዕድሜ ለመግለጽ ግለሰቡ የ . . . ዓመት “ልጅ” ነው ይባል ነበር። በመሆኑም ዮሴፍ “በ110 ዓመቱ ሞተ” የሚለው ሐሳብ ቃል በቃል ቢተረጎም ‘የመቶ አሥር ዓመት ልጅ ሳለ ሞተ’ ይባል ነበር። (ዘፍ 50:26) ዕድሜ ጉልምስናንም ሊያመለክት ይችላል። ሴህቭ ወይም ሴህቫህ (ዕድሜ፣ እርጅና) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ‘መሸበት’ የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ሲሆን ‘ሽበት’ ተብሎም ተተርጉሟል። (1ሳሙ 12:2፣ ምሳሌ 20:29) ከእርጅና ጋር ተዛማጅነት ያላቸው በርካታ የዕብራይስጥ ቃላት “ጢም” የሚል ትርጉም ካለው ዛቃን የተባለ ስም የተወሰዱ ናቸው። (ዘሌ 19:27) ሄሊኪያ የተሰኘው የግሪክኛ ቃል በዋነኛነት የሚያመለክተው የአንድን ግለሰብ ‘የሕይወት ዘመን’ ወይም “ዕድሜ” ነው፤ ያም ቢሆን ቃሉ የግለሰቡን ‘አካላዊ እድገት’ ወይም ‘ቁመት’ ጭምር ሊያመለክት ይችላል። (ማቴ 6:27፣ ዮሐ 9:21፣ ሉቃስ 2:52፣ 19:3) በተጨማሪም በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ጀራስ (‘እርጅና’፣ ሉቃስ 1:36)፣ ፕሬስባይቴስ (“አረጋዊ”፣ ፊልሞና 9) እና ፕሬስባይቲስ (“አረጋውያን ሴቶች”፣ ቲቶ 2:3) የሚሉት ቃላት ይገኛሉ። እነዚህ የኋለኞቹ ሁለት ቃላት “በዕድሜ ትልቅ የሆነ ሰው፣ ሽማግሌ” የሚል ትርጉም ካለው ፕሬስባይቴሮስ ከሚለው ቃል ጋር ይዛመዳሉ።
በሕጉ ሥር ወንዶች በ20 ዓመት ዕድሜያቸው ለወታደራዊ አገልግሎት ብቁ ይሆኑ ነበር። (ዘኁ 1:3) ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረውና ኢየሱስ ዓይኑን ያበራለት ሰው ዕድሜው ቢያንስ 20 ዓመት የነበረ ይመስላል፤ ምክንያቱም ወላጆቹ፣ ጥያቄ ላቀረቡላቸው ሰዎች “እሱን ጠይቁት፤ ሙሉ ሰው ነው። ስለ ራሱ መናገር ያለበት እሱ ነው” ብለው መልስ ሰጥተዋል። (ዮሐ 9:21, 23) ሣራ 90 ዓመት ሆኗት ስለነበረ ልጅ መውለጃ ‘ዕድሜዋ እንዳለፈ’ ተገልጿል።—ዕብ 11:11
ሌዋውያን በቤተ መቅደስ ለሚከናወነው አገልግሎት ብቁ የሚሆኑበትና የግዳጅ አገልግሎታቸው የሚያበቃበት ዕድሜ ተወስኖ ነበር። ሌዋውያን አገልግሎታቸውን የሚጀምሩበት ዕድሜ በዘኁልቁ 4:3, 30, 31 ላይ 30 ዓመት፣ በዘኁልቁ 8:24-26 ላይ ደግሞ 25 ዓመት እንደሆነ ስለተገለጸ ሁለቱ ጥቅሶች እንደሚጋጩ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ጥቅሶቹ ላይ የተገለጹት ሁለት የተለያዩ የአገልግሎት ምድቦች ይመስላሉ። በመሆኑም አንዳንድ የረቢዎች ምንጮች ይህን ሐሳብ ይሰጣሉ፦ አንድ ሌዋዊ በ25 ዓመት ዕድሜው በማደሪያው ድንኳን አገልግሎቱን ቢጀምርም የሚያከናውነው ቀለል ያሉ ሥራዎችን ነው፤ ዕድሜው 30 ዓመት ሲሞላ ግን ከበድ ወዳሉት ሥራዎች ይገባል። በዘኁልቁ 4:3, 47 ላይ ሌዋውያኑ ‘ሸክም እንደሚሸከሙና አገልግሎት እንደሚሰጡ’ ይገልጻል፤ የዕድሜው ወሰን 25 ዓመት እንደሆነ በሚናገረው በዘኁልቁ 8:24 ላይ ግን ይህ ሐሳብ አይገኝም፤ የረቢዎቹ ምንጮች ማስረጃ አድርገው የሚጠቅሱት ይህንን ነው። ሌሎች አክለው በሰጡት ሐሳብ ላይ ደግሞ ከ30 ዓመት በላይ ያሉ ሌዋውያን የማደሪያ ድንኳኑንና ዕቃዎቹን ከማጓጓዝ ጋር የተገናኘ ሥራ ይሠሩ እንደነበረና ከ25 እስከ 30 ዓመት ባለው ዕድሜ የነበሩት ደግሞ የማደሪያው ድንኳን በሚተከልበትና ሰፈሩ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ያገለግሉ እንደነበር ይናገራሉ። ከበድ ያሉ ሥራዎች ይመደቡ የነበሩት በ30 ዓመት ዕድሜ ብቻ ነበር ወደሚለው አመለካከት የሚያደላ ማብራሪያ የሚሰጡት ሰዎች በዚህ ዕድሜ ከፍ ያለ አካላዊ ጥንካሬ፣ አእምሯዊ ብስለትና የሰከነ የማመዛዘን ችሎታ ላይ ይደረሳል የሚል ምክንያት ያቀርባሉ። የግሪክኛው ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም በዘኁልቁ 4:3 ላይም ሆነ በዘኁልቁ 8:24 ላይ ያሰፈረው ዕድሜ 25 ዓመት ነው። ከጊዜ በኋላ በዳዊት ዘመን በማደሪያው ድንኳን ማገልገል የሚቻልበት ዕድሜ ወደ 20 ዓመት ወርዷል፤ የማደሪያው ድንኳን በቤተ መቅደሱ ከተተካ በኋላም ይኸው ሥርዓት ቀጥሏል።—1ዜና 23:24-32፤ ከዕዝራ 3:8 ጋርም አወዳድር።
ሌዋውያን ከግዳጅ አገልግሎት ጡረታ የሚወጡት በ50 ዓመት ዕድሜያቸው ነበር። በዘኁልቁ 8:25, 26 ላይ የተገለጸው ሐሳብ እንደሚያመለክተው እዚህ ዕድሜ ላይ የደረሱ ሌዋውያን፣ በመደበኛ ምድባቸው ላይ የሚገኙትን የሥራ ባልደረቦቻቸውን ማገዝ ይችሉ የነበረ ቢሆንም እነሱ ራሳቸው በቀጥታ የሥራ ምድብ አይሰጣቸውም ወይም የሥራ ምድብ እንዲቀበሉ አይገደዱም። ሌዋውያን በዚያ ዕድሜ ጡረታ የሚወጡት አቅማቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ብቻ ሳይሆን የሌዋውያን አገልግሎት የሚሰጡት ሰዎች ቁጥር እንዳይበዛ ለማድረግ ጭምር እንደነበረ ሐሳብ ቀርቧል። ሊቀ ካህናቱ አቅሙ ከፈቀደ እስከ ዕለተ ሞቱ በዚህ ቅዱስ ኃላፊነት ላይ ያገለግል ስለነበረ ለሌዋውያን የተሰጠው የዕድሜ ገደብ ከአሮን የዘር ሐረግ የሚመጡትን ሊቀ ካህናት አይመለከትም። (ዘኁ 35:25) የእስራኤል የመጀመሪያ ሊቀ ካህናት የነበረው አሮን ለአገልግሎቱ የተመረጠው ዕድሜው ከ80 ዓመት አልፎ ሲሆን 40 ለሚያህሉ ዓመታት አገልግሏል።—ዘፀ 7:7፤ ዘኁ 33:39
የግሪክኛው “አዮን።” “ዕድሜ” የሚል ትርጉም ያለው አዮን የተባለው የግሪክኛ ቃል መነሻና መድረሻው በውል የታወቀም ሆነ አልሆነ፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ አንድን የተወሰነ ዘመን ሊያመለክትም ይችላል። አዮን (ብዙ ቁጥር፣ አዮኔስ) የሚለው የግሪክኛ ቃል በአንዳንድ ትርጉሞች ላይ ዕድሜ የተባለበት ጊዜ አለ። የግሪክኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጆች ይህ ቃል “በውል የሚታወቅና ምልክት የተደረገበት የጊዜ ርዝማኔ፣ ዘመን፣ ዕድሜ” እንዲሁም “የሕይወት ዘመን፣ ሕይወት” ወይም “ዕድሜ፣ ትውልድ” ማለት እንደሆነ ይገልጻሉ። አንድ ዘመን ወይም ዕድሜ መጀመሪያና መጨረሻ ሊኖረው ወይም ለዘላለም ሊቀጥል ይችላል፤ በመሆኑም አዮን መጀመሪያ ቢኖረውም መጨረሻ ግን የሌለውን ጊዜም ሊያመለክት ይችላል። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ በማርቆስ 3:29 ላይ እንደተናገረው አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን ከተሳደበ “ለዘላለም [ዕድሜ ልክ፣ እስከወዲያኛው] የሚጠየቅበት ኃጢአት ይሆንበታል”፤ በሌላ አባባል ወደፊት መቼም ቢሆን ሊሰረዝ የማይችል ኃጢአት ይሆንበታል። ኢየሱስ ፍሬ አልባ ሆና ያገኛትን ዛፍ “ከእንግዲህ ወዲህ ፍሬ አይገኝብሽ” ሲላት የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “ዕድሜ ልክ” የሚል ነው። (ማቴ 21:19) ስለ ኢየሱስ መወለድ የተናገረው መልአክ “በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም [ቃል በቃል፣ በዕድሜ ሁሉ] ንጉሥ ሆኖ ይገዛል” ብሏል።—ሉቃስ 1:33
ይሁን እንጂ አዮን ጊዜውን ራሱን ብቻ ሳይሆን ያ ጊዜ፣ ዘመን ወይም ዕድሜ ተለይቶ የሚታወቅባቸውን ገጽታዎች ወይም ነባራዊ ሁኔታ ሊያመለክት ይችላል።። አር ሲ ትሬንች ሲኖኒምስ ኦፍ ዘ ኒው ቴስታመንት (London, 1961, ገጽ 203) ላይ እንደገለጹት ቃሉ “ጊዜን ከማመልከት ባለፈ በዚያ ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ የሚኖረውን ሁኔታ ሁሉ ያመለክታል፤ . . . እንዲሁም ከግብረ ገብ አንጻር በአንድ የተወሰነ ጊዜ ላይ ዓለም የሚታወቅበትን አካሄድና አዝማሚያ የሚገልጽ ቃል ነው።”