ኪሩብ
1. (ኪሩብ)። ኪሩቦች (ኪሩቤል) ለየት ያለ ተግባር የሚያከናውኑ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው መላእክት ሲሆኑ ማዕረጋቸው ከሱራፌል የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ90 ጊዜ በላይ የተጠቀሱ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሱት ዘፍጥረት 3:24 ላይ ነው፤ አምላክ አዳምና ሔዋንን ከኤደን ካባረረ በኋላ ‘ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ’ በስተ ምሥራቅ ባለው መግቢያ ላይ ኪሩቦችና የነበልባል ሰይፍ አስቀመጠ። በቦታው የተመደቡት ኪሩቦች ሁለት ይሁኑ ከሁለት በላይ የተገለጸ ነገር የለም።
በምድረ በዳ በተተከለው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ቁሳቁሶች ላይ የኪሩቦች ምስል ይገኝ ነበር። በታቦቱ መክደኛ ጫፍና ጫፍ ላይ ከተጠፈጠፈ ወርቅ የተሠሩ ሁለት ኪሩቦች ነበሩ። እነሱም እርስ በርሳቸው ትይዩ የነበሩ ሲሆን አምልኮ እያቀረቡ በሚመስል ሁኔታ ወደ መክደኛው አጎንብሰው ነበር። እያንዳንዳቸው ታቦቱን የሚጠብቁ በሚመስል ሁኔታ ወደ ላይ በተዘረጉ ሁለት ክንፎቻቸው መክደኛውን ከልለውታል። (ዘፀ 25:10-21፤ 37:7-9) በተጨማሪም በውስጥ በኩል በሚታየው የማደሪያ ድንኳኑ ጨርቅ ላይና ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ በሚለየው መጋረጃ ላይ የኪሩቦች ምስል ተጠልፈዋል።—ዘፀ 26:1, 31፤ 36:8, 35
አንዳንዶች እንደሚሉት፣ እነዚህ ኪሩቦች በአካባቢው የነበሩ አረማውያን ብሔራት ያመልኳቸው ከነበሩት ክንፍ ያላቸው አስፈሪና አስቀያሚ ምስሎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የተሠሩ አይደሉም። ሁሉም የአይሁዳውያን ጥንታዊ ወጎች እንደሚመሠክሩት (እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚገልጸው ነገር የለም) እነዚህ ኪሩቦች በሰው ቅርጽ የተሠሩ ነበሩ። የሚያስደንቅ ውበት ያላቸውን መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚወክሉ ድንቅ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሲሆኑ ሙሴ ከይሖዋ በተቀበለው ዝርዝር “ንድፍ መሠረት” የተሠሩ ናቸው። (ዘፀ 25:9) ሐዋርያው ጳውሎስ “የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱ ክብራማ ኪሩቦች” ሲል ገልጿቸዋል። (ዕብ 9:5) እነዚህ ኪሩቦች ከይሖዋ መገኘት ጋር ተያይዘው ተገልጸዋል፦ “እኔም በዚያ እገለጥልሃለሁ፤ ከመክደኛውም በላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ። በምሥክሩ ታቦት ላይ በሚገኙት በሁለቱ ኪሩቦች መካከል ሆኜ [አነጋግርሃለሁ]።” (ዘፀ 25:22፤ ዘኁ 7:89) እንዲሁም ይሖዋ “ከኪሩቤል በላይ [ወይም በኪሩቤል መካከል] የተቀመጠው” ተብሎ ተገልጿል። (1ሳሙ 4:4፤ 2ሳሙ 6:2፤ 2ነገ 19:15፤ 1ዜና 13:6፤ መዝ 80:1፤ 99:1፤ ኢሳ 37:16) በምሳሌያዊ አባባል ኪሩቦች፣ ይሖዋ ራሱ የሚነዳውን ‘ሠረገላ ምስል’ እንደሚወክሉ ተገልጿል (1ዜና 28:18)፤ የኪሩቦቹ ክንፎች ከለላ ሆነው ያገለግላሉ፤ እንዲሁም በፍጥነት እንዲጓዝ ያስችሉታል። በመሆኑም ዳዊት፣ ይሖዋ እሱን ለመርዳት በምን ዓይነት ፍጥነት እንደመጣ ሲገልጽ “በኪሩብ ላይ ተቀምጦ እየበረረ መጣ። በመንፈስ ክንፎችም ላይ ሆኖ ይታይ ነበር” በማለት ዘምሯል።—2ሳሙ 22:11፤ መዝ 18:10
ዕፁብ ድንቅ የሆነውን የሰለሞን ቤተ መቅደስ ለመገንባት ባገለገለው ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ የግንባታ ንድፍ መሠረት በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ሁለት ግዙፍ ኪሩቦች ተቀርጸው ነበር። እነዚህ ኪሩቦች ከጥድ እንጨት ተሠርተው በወርቅ የተለበጡ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ቁመታቸው 4.5 ሜትር ነበር። ሁለቱም ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረው በክፍሉ መሃል አካባቢ ቆመዋል። በመካከላቸው አሥር ክንድ ርቀት ቢኖርም ወደ ክፍሉ መሃል የተዘረጉት የሁለቱ ኪሩቦች ክንፎች እርስ በርስ ይነካኩ ነበር፤ ክንፎቻቸውም ከሥራቸው ያለውን የቃል ኪዳን ታቦትና መሎጊያዎቹን ከልለዋቸው ነበር። በጫፍና በጫፍ በኩል ደግሞ የአንደኛው ኪሩብ ክንፍ የሰሜኑን ግድግዳ፣ የሌላኛው ኪሩብ ክንፍ ደግሞ የደቡቡን ግድግዳ ይነኩ ነበር። በመሆኑም የኪሩቦቹ ክንፎች 20 ክንድ የሆነውን የክፍሉን ወርድ ከጫፍ እስከ ጫፍ ይነኩ ነበር። (“ቤተ መቅደስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) በተጨማሪም የቤተ መቅደሱ ግድግዳዎችና በሮች በወርቅ በተለበጡ የኪሩቦች ምስል አጊጠው ነበር። በተመሳሳይም ከመዳብ የተሠሩት የውኃ ጋሪዎች ጎናቸው ላይ የኪሩቦች ምስል ተቀርጾባቸዋል። (1ነገ 6:23-35፤ 7:29-36፤ 8:6, 7፤ 1ዜና 28:18፤ 2ዜና 3:7, 10-14፤ 5:7, 8) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ ግድግዳዎችና በሮችም በኪሩቦች ምስል ያጌጡ ነበሩ።—ሕዝ 41:17-20, 23-25
ከዚህም ሌላ ሕዝቅኤል፣ ምሳሌያዊ የሆኑ ለየት ያሉ ኪሩቦችን በርከት ባሉ ራእዮች ላይ ማየቱን ጠቅሷል። “ሕያዋን ፍጥረታት” (ሕዝ 1:5-28) እያለ ሲገልጻቸው ከቆየ በኋላ “ኪሩቦቹ” ሲል ለይቶ ጠቅሷቸዋል። (ሕዝ 9:3፤ 10:1-22፤ 11:22) በእነዚህ ገላጭ ራእዮች ላይ የታዩት ኪሩቦች ክብራማ ከሆነው ከይሖዋ ጋር በቅርብ ተያይዘው የተጠቀሱ ከመሆኑም ሌላ እሱን ያለማቋረጥ እንደሚያገለግሉት ተገልጿል።
ሕዝቅኤል ትንቢት አዘል በሆነው መጽሐፉ ላይ “ስለ ጢሮስ ንጉሥ ሙሾ አውርድ” ተብሎ ተነግሮት ነበር፤ ሕዝቅኤል፣ ንጉሡ በአንድ ወቅት “በአምላክ የአትክልት ስፍራ በኤደን” የነበረ ክብር የተጎናጸፈ የሚጋርድ ኪሩብ እንደነበር ገልጿል፤ ይሁንና ውበቱ ተገፎ በምድር ላይ እንዳለ ዐመድ ሆኗል። “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ . . . ‘የተቀባህ፣ የምትጋርድ ኪሩብ አድርጌ ሾምኩህ። በአምላክ ቅዱስ ተራራ ላይ ነበርክ፤ በእሳታማ ድንጋዮችም መካከል ትመላለስ ነበር። ከተፈጠርክበት ቀን አንስቶ ዓመፅ እስከተገኘብህ ጊዜ ድረስ በመንገድህ ሁሉ ምንም እንከን አልነበረብህም። . . . የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ [“ጠባቂ ኪሩብ ሆይ፣” አመት]፣ እንደ ርኩስ ቆጥሬ ከአምላክ ተራራ እጥልሃለሁ።’”—ሕዝ 28:11-19
2. (ከሩብ ተብሎም ይነበባል)። በ537 ዓ.ዓ. ከግዞት ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱ አንዳንድ አይሁዳውያን ይኖሩባት የነበረች የባቢሎን ከተማ ናት፤ እነዚህ ሰዎች ከየትኛው የዘር ሐረግ እንደመጡ በውል መለየት ስላልቻሉ እስራኤላዊ መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ አልተቻለም።—ዕዝራ 2:59፤ ነህ 7:61