የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሁለተኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው ሁለተኛ ዜና መዋዕል ዘገባውን የሚጀምረው ሰሎሞን በእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ እንዳለ በመናገር ነው። የሚደመድመው ደግሞ ፋርሳዊው ንጉሥ ቂሮስ በባቢሎን ላሉት አይሁዳውያን ግዞተኞች በተናገራቸው በሚከተሉት ቃላት ነው:- “[እግዚአብሔር] በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ በመካከላችሁ የሚገኝ ማናቸውም ሰው፣ እግዚአብሔር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም ወደዚያው [ወደ ኢየሩሳሌም] ይውጣ።” (2 ዜና መዋዕል 36:23) ካህኑ ዕዝራ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ460 ጽፎ ያጠናቀቀው ይህ መጽሐፍ ከ1037 እስከ 537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን የ500 ዓመት ታሪክ ይሸፍናል።
የቂሮስ አዋጅ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና በዚያም የይሖዋን አምልኮ እንደገና እንዲያቋቁሙ ያስችላቸዋል። ይሁን እንጂ በባቢሎን ምርኮ ያሳለፏቸው ረጅም ዓመታት ያስከተሉባቸው መጥፎ ተጽዕኖዎች ነበሩ። ከግዞት የሚመለሱት እስራኤላውያን ስለ ብሔራቸው ያላቸው እውቀት ውስን ነበር። በመሆኑም ሁለተኛ ዜና መዋዕል በዳዊት የንግሥና መሥመር ያለፉት ነገሥታት ስለሠሯቸው ነገሮች ግልጽ ዘገባ ይዞላቸዋል። ታሪኩ የእኛንም ትኩረት ይስባል፤ ምክንያቱም እውነተኛውን አምላክ መታዘዝ የሚያስገኛቸውን በረከቶችና አለመታዘዝ የሚያስከትላቸውን መዘዞች ጎላ አድርጎ ይገልጻል።
አንድ ንጉሥ ለይሖዋ ቤት ገነባ
ይሖዋ ለንጉሥ ሰሎሞን ሀብትንና ክብርን ጨምሮ አጥብቆ የጠየቀውን ጥበብና እውቀትም ሰጥቶታል። ንጉሡ ኢየሩሳሌም ውስጥ ለይሖዋ ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ገነባ፤ በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ‘በልቡ ደስ አለው፤ ሐሤትም አደረገ።’ (2 ዜና መዋዕል 7:10) ሰሎሞን “በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የበለጠ” ሆነ።—2 ዜና መዋዕል 9:22
ሰሎሞን ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በእስራኤል ላይ ከነገሠ በኋላ ‘እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፤ ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።’ (2 ዜና መዋዕል 9:31) ዕዝራ፣ ሰሎሞን ከእውነተኛው አምልኮ ወደኋላ ማለቱን አልጻፈም። ንጉሥ ሰሎሞን ከሠራቸው ስህተቶች መካከል በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩት ከግብጽ ብዙ ፈረሶች ማስመጣቱና የፈርዖንን ልጅ ማግባቱ ብቻ ናቸው። ዕዝራ ያተኮረው በመልካም ጎኑ ላይ ብቻ ነበር።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
2:14—እዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው የእጅ ባለሙያ ነገድ በ1 ነገሥት 7:14 ላይ ከተጠቀሰው የሚለየው ለምንድን ነው? የዚህ ባለሙያ እናት የንፍታሌም ነገድ ሰው አግብታ ስለነበር አንደኛ ነገሥት “ከንፍታሌም ነገድ ስትሆን፣ እርሷም መበለት ነበረች” በማለት ሊናገር ችሏል። ይሁን እንጂ እርሷ ራሷ ከዳን ነገድ ነበረች። ባሏ ከሞተ በኋላ ደግሞ የጢሮስ ሰው አገባች፤ ባለሙያውንም የወለደችው ከዚህኛው ባሏ ነው።
2:18፤ 8:10—በእነዚህ ጥቅሶች ላይ እንደ ተቆጣጣሪ እንዲሁም እንደ ሹም ሆነው ያገለገሉት የኃላፊዎች ቁጥር 3,600 ሲደመር 250 ሆኖ ሳለ በ1 ነገሥት 5:16 እና 9:23 ላይ 3,300 ሲደመር 550 ሆኖ ተጠቅሷል። ቁጥሮቹ የተለያዩት ለምንድን ነው? ልዩነቱን ያመጣው ተቆጣጣሪዎቹ የተከፈሉበት መንገድ ሳይሆን አይቀርም። ሁለተኛ ዜና መዋዕል 3,600 እስራኤላውያን ያልሆኑና 250 እስራኤላዊ ኃላፊዎች ብሎ ሲከፍላቸው፣ አንደኛ ነገሥት ደግሞ 3,300 ኃላፊዎችና 550 የበላይ ተቆጣጣሪዎች ብሎ ስለከፈላቸው ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ በኃላፊነት ያገለገሉት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 3,850 ነው።
4:2-4—የበርሜሉን መቀመጫ ለመገንባት የኮርማዎችን ቅርጽ መጠቀም ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው? በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ኮርማ ወይም በሬ ጥንካሬን ያመለክታል። (ሕዝቅኤል 1:10፤ ራእይ 4:6, 7) አሥራ ሁለቱ የብረት ኮርማዎች 30 ቶን የሚያህል ትልቅ “በርሜል” ስለሚሸከሙ የኮርማዎች ቅርጽ መመረጡ ተስማሚ ነው። የኮርማዎች ቅርጽ ለዚህ ዓላማ መመረጡ ምሥሎችን ለአምልኮ መጠቀምን ከሚከለክለው የአሥርቱ ትእዛዛት ሁለተኛ ሕግ ጋር በምንም መንገድ አይጋጭም።—ዘፀአት 20:4, 5
4:5—በርሜሉ በአጠቃላይ መያዝ የሚችለው የውኃ መጠን ምን ያህል ነበር? በርሜሉ ከአፍ እስከ ገደፉ ከተሞላ ሦስት ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ወይም 66,000 ሊትር ውኃ ያህል መያዝ ይችላል። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ይይዝ የነበረው ከአጠቃላይ ችሎታው ሁለት ሦስተኛውን ያህል ብቻ ሳይሆን አይቀርም። አንደኛ ነገሥት 7:26 (የ1954 ትርጉም) እንደሚለው “[ገንዳው] ሁለት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ [44,000 ሊትር] ይይዝ ነበር።”
5:4, 5, 10—ከመገናኛው ድንኳን ወጥቶ ወደ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ የገባው ዕቃ የትኛው ነው? ከመገናኛው ድንኳን ወደ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ ተወስዶ ጥቅም ላይ የዋለው ዕቃ ታቦቱ ብቻ ነው። ቤተ መቅደሱ ከተገነባ በኋላ መገናኛው ድንኳን ከገባዖን ወደ ኢየሩሳሌም ከተወሰደ በኋላ እዚያው ሳይቀመጥ አልቀረም።—2 ዜና መዋዕል 1:3, 4
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:11, 12፦ ይሖዋ፣ ንጉሥ ሰሎሞን ከልቡ የሚፈልገው ጥበብና እውቀት ማግኘት መሆኑን ካቀረበው ጥያቄ ተረድቷል። እኛም ወደ አምላክ የምናቀርበው ጸሎት በእርግጥ በልባችን ውስጥ ያለው ነገር ምን እንደሆነ ይገልጣል። የጸሎታችንን ይዘት መመርመራችን የጥበብ መንገድ ነው።
6:4፦ ለይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና ቸርነት ያለን ልባዊ አድናቆት ይሖዋን እንድንባርከው ማለትም በፍቅርና በአመስጋኝነት መንፈስ እንድናወድሰው ሊያነሳሳን ይገባል።
6:18-21፦ አምላክን ሊይዝ የሚችል አንድም ሕንጻ ባይኖርም እንኳ ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አምልኮ እንደ ማዕከል ሆኖ አገልግሎ ነበር። ዛሬም በየአካባቢው የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾች ለእውነተኛው አምልኮ ማዕከል ሆነው ያገለግላሉ።
6:19, 22, 32፦ ይሖዋ ንጉሥ፣ ተራ እስራኤላዊ፣ መጻተኛ ሳይል ሰዎች ከልብ የሚያቀርቡትን ጸሎት ሁሉ ይሰማል።a—መዝሙር 65:2
በዳዊት የትውልድ መሥመር የተነሱ ነገሥታት
አንድ የነበረው የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፈለ። አንደኛው በስተ ሰሜን የሚገኘው የአሥሩ ነገድ መንግሥት ሲሆን ሌላው ደግሞ በስተ ደቡብ የሚገኘው የይሁዳንና የብንያምን ነገዶች ያቀፈው መንግሥት ነው። በመላው እስራኤል የነበሩት ካህናትና ሌዋውያን ብሔረተኝነት ሳያጠቃቸው ለመንግሥቱ ቃል ኪዳን ታማኝ በመሆን ከሰሎሞን ልጅ ከሮብዓም ጎን ተሰልፈዋል። ቤተ መቅደሱ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ ከ30 ዓመት በኋላ በውስጡ የነበሩት በጣም ውድ ዕቃዎች ተዘረፉ።
ከሮብዓም በኋላ በተከታታይ ከተነሱት 19 ነገሥታት መካከል አምስቱ ታማኞች ነበሩ፤ ሦስቱ ጥሩ ጅምር የነበራቸው ቢሆንም የኋላ ኋላ ታማኝነታቸውን አጉድፈዋል፤ አንደኛው ደግሞ ከተከተለው የተሳሳተ መንገድ ተመልሷል። ቀሪዎቹ ገዢዎች በይሖዋ ዓይን ክፉ የሆነውን አድርገዋል።b በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በይሖዋ ላይ የታመኑት የአምስቱ ነገሥታት ታሪክ ሰፋ ያለ ሽፋን ተሰጥቶታል። ሕዝቅያስ የቤተ መቅደሱ አገልግሎት ሕይወት እንዲዘራ ስለማድረጉ እንዲሁም ኢዮስያስ ትልቅ የፋሲካ በዓል ስለማዘጋጀቱ የሚናገሩት ታሪኮች፣ የይሖዋን አምልኮ በኢየሩሳሌም እንደገና ማቋቋም ለሚፈልጉ አይሁዳውያን ትልቅ ማበረታቻ እንደሆኗቸው የታወቀ ነው።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
13:5—“በጨው ኪዳን” የሚለው አገላለጽ ምን ማለት ነው? ጨው አንድ ነገር እንዳይበላሽ ጠብቆ የማቆየት ችሎታ ስላለው የቋሚነትና ያለመለወጥ ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል። ስለዚህ ‘የጨው ኪዳን’ የሚለው ሐሳብ ጽኑ የሆነ ስምምነትን ያመለክታል።
14:2-5፤ 15:17—ንጉሥ አሳ “ማምለኪያ ኰረብታዎችን” በሙሉ አስወግዷል? ሁሉንም ያስወገደ አይመስልም። አሳ ያስወገዳቸው የማምለኪያ ኮረብታዎች እስራኤላውያን ይሖዋን ለማምለክ የተጠቀሙባቸውን ሳይሆን ከሐሰት አምልኮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ብቻ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በአሳ የግዛት ዘመን መጨረሻዎቹ ዓመታት ላይ ሌሎች የማምለኪያ ኮረብታዎች እንደገና ተሠርተው ሊሆን ይችላል። እነዚህን ደግሞ ልጁ ኢዮሣፍጥ አስወግዷቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ በኢዮሣፍጥ የንግሥና ዘመንም እንኳ የማምለኪያ ኮረብታዎቹ ሙሉ በሙሉ አልጠፉም።—2 ዜና መዋዕል 17:5, 6፤ 20:31-33
15:9፤ 34:6—የእስራኤል መንግሥት በተከፈለበት ወቅት የስምዖን ነገድ ከየትኛው ወገን ነበር? የስምዖን ልጆች ነገድ ርስት የተሰጠው በይሁዳ ርስት መካከል ስለነበር ከመልክዓ ምድር አንጻር የስምዖን ነገድ በይሁዳና በብንያም መንግሥት ሥር ይጠቃለል ነበር። (ኢያሱ 19:1) ይሁን እንጂ ይህ ነገድ በአምልኮም ሆነ በፖለቲካ የወገነው ከሰሜኑ መንግሥት ጋር ነበር። (1 ነገሥት 11:30–33፤ 12:20-24) በዚህም ምክንያት ስምዖን አሥር ነገድ ካቀፈው መንግሥት ጋር ተቆጥሯል።
35:3—ኢዮስያስ ቅዱስ ታቦቱን ወደ ቤተ መቅደሱ ያመጣው ከየት ነው? ታቦቱን፣ ቀደም ሲል ከነበሩት ክፉ ነገሥታት መካከል አንዱ አስወጥቶት ይሁን አሊያም ደግሞ ለቤተ መቅደሱ ከፍተኛ እድሳት በተደረገበት ወቅት ኢዮስያስ ለታቦቱ ደኅንነት ሲል ሌላ ቦታ አስቀምጦት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ከሰሎሞን ዘመን በኋላ ስለ ታቦቱ የተጠቀሰው ኢዮስያስ ወደ ቤተ መቅደስ እንደወሰደው በሚናገረው ዘገባ ላይ ብቻ ነው።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
13:13-18፤ 14:11, 12፤ 32:9-23፦ ከእነዚህ ጥቅሶች በይሖዋ መመካት ያለውን ጥቅም በተመለከተ ግሩም ትምህርት እናገኛለን!
16:1-5, 7፤ 18:1-3, 28-32፤ 21:4-6፤ 22:10-12፤ 28:16-22፦ ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር መዋዋል አሳዛኝ ውጤት ይኖረዋል። ከዓለም ጋር አላስፈላጊ ግንኙነት ከመፍጠር መቆጠባችን የጥበብ እርምጃ ነው።—ዮሐንስ 17:14, 16፤ ያዕቆብ 4:4
16:7-12፤ 26:16-21፤ 32:25, 26፦ እብሪተኝነት ንጉሥ አሳ በሕይወት ዘመኑ መጨረሻ ላይ መጥፎ ሰው እንዲሆን አድርጎታል። ዖዝያንን ለውድቀት የዳረገውም የእብሪት መንፈስ ነው። ሕዝቅያስ ለባቢሎናውያን መልእክተኞች ንብረቱ ያለበትን ግምጃ ቤት በማሳየት ጥበብ የጎደለው ድርጊት ፈጽሟል፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው በኩራት መንፈስ ይሆናል። (ኢሳይያስ 39:1-7) መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕቢት ጥፋትን፣ የዕብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 16:18
16:9፦ ይሖዋ በሙሉ ልብ በእርሱ የሚታመኑትን የሚረዳ ሲሆን ኃይሉን ተጠቅሞ እነርሱን ለማበርታት ምንጊዜም ዝግጁ ነው።
18:12, 13, 23, 24, 27፦ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ስንናገር ልክ እንደ ሚካያ ብርቱና ደፋር ልንሆን ይገባል።
19:1-3፦ ይሖዋ አሳዝነነውም እንኳ መልካም ጎናችንን ይመለከታል።
20:1-28፦ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠን በትሕትና እስከጠየቅነው ድረስ ጸሎታችንን እንደሚሰማ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ምሳሌ 15:29
20:17፦ ‘የይሖዋን ማዳን እንድናይ’ የአምላክን መንግሥት በንቃት በመደገፍ ‘ቦታ ቦታችንን መያዝ’ ይኖርብናል። የሚደርሱብንን ችግሮች በራሳችን ለመወጣት ከመጣር ይልቅ በይሖዋ በመታመን ‘ጸንተን መቆም’ ይገባናል።
24:17-19፤ 25:14፦ የጣዖት አምልኮ ለኢዮአስም ሆነ ለልጁ ለአሜስያስ ወጥመድ ሆኖባቸዋል። በዛሬው ጊዜም የጣዖት አምልኮ እንደ መጎምጀትና ብሔራዊ ስሜት ባሉ ስውር በሆኑ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል።—ቈላስይስ 3:5፤ ራእይ 13:4
32:6, 7፦ እኛም ‘የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ለብሰን’ በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ብርቱና ጠንካሮች ልንሆን ይገባናል።—ኤፌሶን 6:11-18
33:2-9, 12, 13, 15, 16፦ አንድ ሰው እውነተኛ ንስሐ እንዳሳየ የሚታወቀው በተሳሳተ ጎዳና መጓዙን አቁሞ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ሲጥር ነው። አንድ ሰው የንጉሥ ምናሴን ያህል ኃጢአት ቢሠራ እንኳ ከልቡ ንስሐ እስከገባ ድረስ የይሖዋን ምሕረት ሊያገኝ ይችላል።
34:1-3፦ በልጅነት ዕድሜያችን ያጋጠመን ማንኛውም መጥፎ ሁኔታ አምላክን አውቀን እርሱን ከማገልገል ወደኋላ እንድንል አያደርገንም። ኢዮስያስ ምሳሌ የሚሆን ነገር ያገኘው በልጅነት ዕድሜው አያቱ ምናሴ ንስሐ በገባበት ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል። በኢዮስያስ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደረበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ውሎ አድሮ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ይህ በእኛም ላይ ሊሠራ ይችላል።
36:15-17፦ ይሖዋ ርኅሩኅና ትዕግሥተኛ ነው። ይሁን እንጂ ርኅራኄውም ሆነ ትዕግሥቱ ገደብ አለው። ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ መትረፍ የሚፈልጉ ሰዎች ለመንግሥቱ የስብከት ሥራ በጎ ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል።
36:17, 22, 23፦ ይሖዋ የተናገረው ቃል ሳይፈጸም አይቀርም።—1 ነገሥት 9:7, 8፤ ኤርምያስ 25:9-11
አንድ መጽሐፍ እርምጃ እንዲወስድ አነሳሳው
ሁለተኛ ዜና መዋዕል 34:33 እንዲህ ይላል:- “ኢዮስያስም አስጸያፊ ጣዖታትን ሁሉ ከመላው የእስራኤል ግዛት አስወገደ፤ በእስራኤል የነበሩትም ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ።” ኢዮስያስ እንዲህ እንዲያደርግ የገፋፋው ምንድን ነው? ጸሐፊው ሳፋን አዲስ የተገኘውን የይሖዋን የሕግ መጽሐፍ ለኢዮስያስ አምጥቶ አነበበለት። ኢዮስያስ የተነበበለት ነገር ልቡን ስለነካው በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ንጹሑን አምልኮ በቅንዓት አስፋፍቷል።
የአምላክን ቃል ማንበባችንና ባነበብነውም ነገር ላይ ማሰላሰላችን በጥልቅ ሊነካን ይችላል። በዳዊት የትውልድ መሥመር በተነሱት ነገሥታት ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን ይሖዋን መታመኛቸው ያደረጉትን ምሳሌ እንድንከተል እንዲሁም በእርሱ ላይ ያልታመኑት ያሳዩትን ምግባር እንድናስወግድ አይገፋፋንም? ሁለተኛ ዜና መዋዕል ለእውነተኛው አምላክ በሙሉ ልብ እንድናድር እንዲሁም ታማኝ እንድንሆንለት ያነሳሳናል። በእርግጥም የመጽሐፉ መልእክት ሕያውና የሚሠራ ነው።—ዕብራውያን 4:12
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ከቤተ መቅደሱ ምርቃት ጋር በተያያዙ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ሰሎሞን በዚያን ጊዜ ካቀረበው ጸሎት ልናገኛቸው የምንችላቸውን ትምህርቶች በተመለከተ የሐምሌ 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 28-31ን ተመልከት።
b በቅደም ተከተል የሰፈረውን የይሁዳን ነገሥታት ዝርዝር በነሐሴ 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 12 ላይ መመልከት ትችላለህ።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የበርሜሉን መቀመጫ ለመሥራት የኮርማዎችን ቅርጽ መጠቀሙ ተስማሚ የሆነበትን ምክንያት ታውቃለህ?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮስያስ በልጅነቱ በቂ እርዳታ ባያገኝም እንኳ ሲያድግ ለይሖዋ ታማኝ ሆኗል