የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የዕዝራ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የዕዝራ መጽሐፍ የሚጀምረው የሁለተኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ ካቆመበት በመነሳት ነው። ጸሐፊው ካህኑ ዕዝራ ሲሆን ዘገባውን የጀመረው ከባቢሎን ምርኮ የተረፉት አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ አዋጅ እንዳስነገረ በመግለጽ ነው። ታሪኩ የሚደመደመው ዕዝራ በምድሪቱ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር በመቀራረብ ራሳቸውን ያረከሱት አይሁዳውያን መንጻት የሚያስችላቸውን እርምጃ እንደወሰደ በመግለጽ ነው። መጽሐፉ በአጠቃላይ ከ537 እስከ 467 ከክርስቶስ ልደት በፊት ያሉትን ሰባ ዓመታት ይሸፍናል።
ዕዝራ መጽሐፉን የጻፈበት ግልጽ ዓላማ ነበረው፤ ይህም ይሖዋ ሕዝቦቹን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ በማውጣትና በኢየሩሳሌም ንጹሕ አምልኮ ተመልሶ እንዲቋቋም በማድረግ የገባውን ቃል እንዴት እንደፈጸመ ማሳየት ነው። ዕዝራ ያተኮረው ከዚህ ዓላማ ጋር በተያያዙ ክስተቶች ላይ ብቻ ነበር። የዕዝራ መጽሐፍ የአምላክ ሕዝቦች የሚደርስባቸውን ተቃውሞና የራሳቸውን አለፍጽምና ተቋቁመው ቤተ መቅደሱን እንዴት ዳግም እንደገነቡ እንዲሁም የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ተመልሶ የተቋቋመው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ታሪክ ይዟል። እኛም የምንኖረው በተሐድሶ ዘመን ውስጥ ስለሆነ ይህ ዘገባ ከፍተኛ ትምህርት ይዞልናል። ብዙዎች ወደ ይሖዋ “ተራራ” እየጎረፉ ከመሆናቸውም በተጨማሪ መላዋ ምድር “የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ” ወደ መሞላት እየደረሰች ነው።—ኢሳይያስ 2:2, 3፤ ዕንባቆም 2:14
ቤተ መቅደሱ በድጋሚ ተገነባ
ለቂሮስ የነፃነት አዋጅ ምላሽ በመስጠት ወደ 50, 000 የሚደርሱ አይሁዳውያን ምርኮኞች በገዢው በዘሩባቤል ወይም በሰሳብሳር መሪነት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከዚያም ተመላሾቹ ወዲያውኑ መሠዊያውን በቀድሞው ቦታ ላይ በመሥራት ለይሖዋ መሥዋዕት ማቅረብ ጀመሩ።
በቀጣዩ ዓመት እስራኤላውያን የይሖዋን ቤተ መቅደስ መሠረት ጣሉ። ይሁን እንጂ ጠላቶቻቸው የመልሶ ግንባታው ሥራ እንዳይካሄድ እንቅፋት መፍጠር የጀመሩ ሲሆን በመጨረሻም ሥራውን ለማስቆም የሚያስችል የንጉሥ ትእዛዝ በማግኘት ተሳካላቸው። ነቢዩ ሐጌና ዘካርያስ እገዳው እያለም ቢሆን የቤተ መቅደሱን ግንባታ እንዲቀጥሉ ሕዝቡን ያነሳሱ ነበር። ጠላቶቻቸው ቂሮስ ያወጣውን የማይለወጥ የፋርስ አዋጅ መቃወማቸው የሚያስከትልባቸውን ነገር በመፍራት ተቃውሟቸውን አቆሙ። የመንግሥት ግምጃ ቤቱ ሲፈተሽ ቂሮስ “በኢየሩሳሌም ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ” የሰጠው ትእዛዝ ተገኘ። (ዕዝራ 6:3) በመጨረሻም ሥራው ያለችግር ቀጥሎ ተጠናቀቀ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
1:3-6—ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑት እስራኤላውያን እምነት ያንሳቸው ነበር? ምናልባት አንዳንዶች ወደ ኢየሩሳሌም ያልተመለሱት ቁሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮራቸው ወይም ለእውነተኛው አምልኮ አድናቆት በማጣታቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሁሉም የቀሩት በእነዚህ ምክንያቶች ነው ማለት አይቻልም። በመጀመሪያ ደረጃ 1, 600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ወደ ኢየሩሳሌም የሚደረገው ጉዞ አራት ወይም አምስት ወራት ይፈጃል። ከዚህም ሌላ ለ70 ዓመታት ባድማ ሆና በቆየች ምድር ላይ አዲስ ኑሮ መጀመርም ሆነ በዳግም ግንባታው መሳተፍ አካላዊ ጥንካሬ ይጠይቃል። ስለዚህ እንደ በሽታ፣ የዕድሜ መግፋትና የቤተሰብ ኃላፊነት የመሳሰሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች አንዳንዶቹን ባሉበት እንዲቀሩ እንደሚያደርጓቸው የተረጋገጠ ነው።
2:43—ናታኒሞች እነማን ነበሩ? በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ እስራኤላዊ ያልሆኑ ባሪያዎች ወይም አገልጋዮች ነበሩ። ከእነርሱ መካከል በኢያሱ ዘመን የነበሩት የገባዖናውያን ዝርያዎች እንዲሁም ‘ዳዊትና ሹማምንቱ ሌዋውያኑን እንዲረዱ’ የሰጧቸው አገልጋዮች ይገኙበታል።—ዕዝራ 8:20
2:55—የሰሎሞን አገልጋዮች ዘሮች የተባሉት እነማን ናቸው? እነዚህ በይሖዋ አገልግሎት ልዩ መብት የተሰጣቸው እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች ነበሩ። በቤተ መቅደስ ውስጥ በጸሐፊነት ወይም ጽሑፎችን በመገልበጥ ተግባር አሊያም በአስተዳደር ሥራ ተሰማርተው ሊሆን ይችላል።
2:61-63—ከስደት የተመለሱት አይሁዳውያን፣ ከይሖዋ መልስ ለማግኘት የሚያገለግለው ኡሪምና ቱሚም ነበራቸው? የካህናት ዘር ስለመሆናቸው የይገባኛል ጥያቄ ቢያነሱም የዘር ሐረጋቸውን ማረጋገጥ ያልቻሉ አይሁዳውያን በኡሪምና በቱሚም አማካኝነት ባለ መብት መሆናቸው እንዲታወቅ ተወሰነ። ዕዝራ ይህንን የጠቀሰው እንደ አንድ አማራጭ አድርጎ ነበር። ቅዱስ ጽሑፉ በዚያ ወቅት ወይም ከዚያ በኋላ ኡሪምና ቱሚም ሥራ ላይ ስለመዋላቸው የሚጠቅሰው ነገር የለም። በአይሁዳውያን አፈ ታሪክ መሠረት ኡሪምና ቱሚም ቤተ መቅደሱ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በወደመበት ወቅት ጠፍተዋል።
3:12—የቀድሞውን የይሖዋን “ቤተ መቅደስ ያዩ በዕድሜ የሸመገሉ ብዙ ካህናት” ያለቀሱት ለምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች ሰሎሞን የሠራው ቤተ መቅደስ ዕጹብ ድንቅ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከፊታቸው የሚያዩትን የአዲሱን ቤተ መቅደስ መሠረት ከዚያኛው ጋር ሲያወዳድሩት ‘በፊታቸው ምንም እንዳይደለ የሚቆጠር’ ሆነባቸው። (ሐጌ 2:2, 3) አሁን እየተደረገ ያለው ጥረት ወደ ቀድሞ ውበቱ እንዲመለስ ያስችለው ይሆን? በመሆኑም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ስለተሰማቸው አለቀሱ።
3:8-10፤ 4:23, 24፤ 6:15, 16—ቤተ መቅደሱን ዳግም ለመገንባት ምን ያህል ዓመት ፈጅቷል? የቤተ መቅደሱ መሠረት የተጣለው እዚያ “በደረሱ በሁለተኛው ዓመት” ማለትም በ536 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። የግንባታው ሥራ በንጉሥ አርጤክስስ የግዛት ዘመን ይኸውም በ522 ከክርስቶስ ልደት በፊት አቆመ። እገዳው እስከ ዳርዮስ ሁለተኛ ዓመት የግዛት ዘመን ማለትም እስከ 520 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ ቀጠለ። በስድስተኛው የዳርዮስ የንግሥና ዓመት ወይም በ515 ከክርስቶስ ልደት በፊት የቤተ መቅደሱ ግንባታ ተጠናቀቀ። (“ከ537 እስከ 467 ከክ.ል.በፊት የነበሩ የፋርስ ነገሥታት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ስለዚህ የቤተ መቅደሱ ግንባታ 20 ዓመታት ገደማ ፈጅቷል ማለት ነው።
4:8 እስከ 6:18—ዕዝራ ይህን ክፍል የጻፈው በአረማይክ ቋንቋ ነው። ግን ለምን? ይህ ክፍል በአብዛኛው የያዘው የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ለነገሥታት የጻፏቸውንና ነገሥታቱ የላኳቸውን የመልስ ደብዳቤዎች ነው። ዕዝራ ደብዳቤዎቹን የገለበጠው በወቅቱ ንግድ ይካሄድበትና የመንግሥት ቋንቋ ሆኖ ያገለግል በነበረው በአረማይክ ተጽፎ ከሚገኘው መዝገብ ላይ ነበር። በዚህ ጥንታዊ ሴማዊ ቋንቋ የተጻፉ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ዕዝራ 7:12-26፣ ኤርምያስ 10:11 እና ዳንኤል 2:4ለ እስከ 7:28 ናቸው።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:2፦ ኢሳይያስ ከ200 ዓመታት በፊት የተነበየው ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ። (ኢሳይያስ 44:28) በይሖዋ ቃል ውስጥ ያሉ ትንቢቶች በሙሉ ሳይፈጸሙ አይቀሩም።
1:3-6፦ ጥንት በባቢሎን እንደቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ወይም ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት አካባቢ ሄደው ማገልገል አይችሉም። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተሳተፉ ላሉት ድጋፍና ማበረታቻ ይሰጣሉ። ከዚህም በላይ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበኩና ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ በፈቃደኝነት የገንዘብ መዋጮ ያደርጋሉ።
3:1-6፦ በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛው ወር (ቲሽሪ የሚባለው ይህ ወር ከመስከረም/ጥቅምት ጋር አንድ ነው) ከምርኮ የተመለሱት ታማኞች ለመጀመሪያ ጊዜ መሥዋዕት አቀረቡ። ንጉሥ ናቡከደነፆር በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ወር (አብ የሚባለው ይህ ወር ከሐምሌ/ነሐሴ ጋር አንድ ነው) ወደ ኢየሩሳሌም የገባ ሲሆን ከሁለት ወራት በኋላ ከተማይቱ ሙሉ በሙሉ ባድማ ሆነች። (2 ነገሥት 25:8-17, 22-26) በትንቢት እንደተነገረው ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና የቆየችበት 70 ዓመት ጊዜውን ጠብቆ በትክክል ተፈጸመ። (ኤርምያስ 25:11፤ 29:10) ይሖዋ በትንቢት ያስነገረው ቃል ምንጊዜም ይፈጸማል።
4:1-3፦ ከምርኮ የተመለሱት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከጣዖት አምላኪዎች የቀረበላቸውን ግብዣ ባለመቀበል ሃይማኖታዊ አንድነት ከመመሥረት ተቆጥበዋል። (ዘፀአት 20:5፤ 34:12) በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አምላኪዎችም በማንኛውም ዓይነት ሃይማኖትን የመቀላቀል እንቅስቃሴ አይካፈሉም።
5:1-7፤ 6:1-12፦ ይሖዋ ሕዝቦቹ እንዲሳካላቸው ሲል ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ማድረግ ይችላል።
6:14, 22፦ በይሖዋ ሥራ በቅንዓት መካፈል በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ከማስገኘቱም በተጨማሪ በረከት ያስገኛል።
6:21፦ በአይሁዳውያን የትውልድ አገር ይኖሩ የነበሩ ሳምራውያንና ከተመላሾቹ መካከል በአረማውያን የጣዖት አምልኮ ተሸንፈው የነበሩት አይሁዶች የይሖዋ ሥራ እያደገ መሄዱን ሲመለከቱ በሕይወታቸው ላይ ለውጥ አድርገዋል። ታዲያ እኛስ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክን ጨምሮ አምላክ በሰጠን ሥራ በቅንዓት መሳተፍ አይገባንም?
ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ
በድጋሚ የተገነባው ቤተ መቅደስ ከተመረቀ ሃምሳ ዓመታት አልፈዋል። ጊዜው 468 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ዕዝራ በባቢሎን ቀርተው የነበሩ የአምላክ ሕዝቦችንና ሕዝቡ ያዋጣውን ገንዘብ ይዞ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። እዚያ ሲደርስ ምን ዓይነት ሁኔታ ገጠመው?
መሪዎቹ ለዕዝራ እንዲህ በማለት ነገሩት:- ‘ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ የእስራኤል ሕዝብ ከጎረቤቶቻቸው ርኵሰት ራሳቸውን አልለዩም።’ በተጨማሪም ‘በዚህ በደል ዋነኛ የሆኑት መሪዎቹና ሹማምቱ ናቸው።’ (ዕዝራ 9:1, 2) ዕዝራ ይህን ሲሰማ በጣም ደነገጠ። ሕዝቡም “በርትተህም፤ አድርገው” በማለት አበረታቱት። (ዕዝራ 10:4) ዕዝራም የማስተካከያ እርምጃዎችን ወሰደ፤ ሕዝቡም ተባበረው።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
7:1, 7, 11—በእነዚህ ቁጥሮች ላይ የተጠቀሰው አርጤክስስ የግንባታው ሥራ እንዲቆም ትእዛዝ አስተላልፎ የነበረው ንጉሥ ነው? አይደለም። አርጤክስስ የሚለው ቃል ስም ወይም ማዕረግ ሲሆን ለሁለት የፋርስ ነገሥታት ተሰጥቷል። የመጀመሪያው ባርዲያ ወይም ጋውማታ የሚባለው ሲሆን ይህም በ522 ከክርስቶስ ልደት በፊት የቤተ መቅደሱ ሥራ እንዲቆም ያዘዘው ነው። ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣበት ወቅት የነበረው አርጤክስስ ግን ሎንጊማነስ በመባል የሚታወቀው ነው።
7:28 እስከ 8:20—በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ ብዙ አይሁዳውያን ከዕዝራ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ያልፈለጉት ለምንድን ነው? የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ 60 ዓመታት ያለፉ ቢሆንም በኢየሩሳሌም ውስጥ በቂ ነዋሪዎች አልነበሩም። ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ማለት ምቹ ባልሆነና በአደገኛ ሁኔታ ሥር አዲስ ኑሮ መመሥረት ማለት ነው። በወቅቱ በኢየሩሳሌም የነበረው በቁሳዊ የማደግ ሁኔታ በባቢሎን የተደላደለ ኑሮ ለነበራቸው አይሁዳውያን የሚስብ አልነበረም። አደገኛ የሆነው ጉዞም ሳይጠቀስ አይታለፍም። ተመላሾቹ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት፣ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዲሁም ጉዞውን ለማድረግ ድፍረት ሊኖራቸው ይገባ ነበር። ዕዝራም ቢሆን የበረታው የይሖዋ እጅ በእርሱ ላይ ስለነበረች ነው። ዕዝራ በሰጣቸው ማበረታቻ 1, 500 ቤተሰቦች፤ ምናልባትም ቁጥራቸው 6, 000 የሚደርሱ ሰዎች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ዕዝራ ባደረገው ተጨማሪ ቅስቀሳ ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ 38 ሌዋውያን እና 220 ናታኒሞች ሊገኙ ችለዋል።
9:1, 2—በምድሪቱ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር መጋባት ምን አደጋ ነበረው? ተመልሶ የተቋቋመው ይህ ብሔር መሲሑ እስኪመጣ ድረስ የእውነተኛው አምልኮ ባለአደራ ነበር። በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር በጋብቻ መጣመር በእውነተኛው አምልኮ ላይ ከባድ ስጋት ይፈጥራል። አንዳንድ አይሁዳውያን ጣዖት አምላኪ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጋብቻ መስርተው ስለነበር መላው ብሔር ቀስ በቀስ በአረማውያን ብሔራት የመዋጥ አደጋ ተደቅኖበት ነበር። በዚህ ዓይነት እውነተኛ አምልኮ ከምድር ገጽ ሊጠፋ ይችላል። እንዲህ ቢሆን ኖሮ ደግሞ መሲሑ ለእነማን መምጣት ያስፈልገው ነበር? ዕዝራ በድርጊታቸው ቢደነግጥ ምንም አያስገርምም!
10:3, 44—ሚስቶቻቸውን ከነልጆቻቸው ያሰናበቷቸው ለምንድን ነው? ልጆቻቸው እዚያው ቢቀሩ ኖሮ የተባረሩት ሚስቶች ልጆቻቸውን ብለው የመመለሳቸው አጋጣሚ ሰፊ ይሆን ነበር። በተጨማሪም፣ ትንንሽ ልጆች በአብዛኛው የእናታቸው እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
7:10፦ ዕዝራ የአምላክ ቃል ትጉ ተማሪና ውጤታማ አስተማሪ በመሆን ረገድ ምሳሌ ትቶልናል። የይሖዋን ሕግ ለመመርመር ልቡን በጸሎት አዘጋጅቶ ነበር። ዕዝራ ቃሉን ሲያጠና ይሖዋ ለሚናገረው ነገር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ነበር። ዕዝራ የተማረውን በተግባር ከማዋሉም በተጨማሪ ሌሎችን ለማስተማር ትጋት የተሞላበት ጥረት አድርጓል።
7:13፦ ይሖዋ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ አገልጋዮች ይፈልጋል።
7:27, 28፤ 8:21-23፦ ዕዝራ ለጉዞው ያነሳሳቸው ይሖዋ መሆኑን ገልጿል፣ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርገውን ረጅምና አደገኛ ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት አቅርቧል እንዲሁም አምላክ እንዲከበር ሲል የራሱን ደኅንነት መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል። በመሆኑም ለእኛ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል።
9:2፦ ጋብቻ “በጌታ መሆን አለበት” የሚለውን ጠንካራ ምክር አክብደን መመልከት ይኖርብናል።—1 ቆሮንቶስ 7:39
9:14, 15፦ ክፉ ባልንጀርነት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያሳጣል።
10:2-12, 44፦ ከሌሎች ብሔራት ሚስት ያገቡ ሰዎች በትሕትና ንስሐ የገቡ ከመሆኑም ሌላ የተሳሳተ መንገዳቸውን አስተካክለዋል። እነርሱ ያሳዩት ዝንባሌና የወሰዱት እርምጃ ምሳሌ ይሆነናል።
ይሖዋ ቃሉን ይጠብቃል
የዕዝራ መጽሐፍ ምንኛ ይጠቅመናል! ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ ሕዝቦቹን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ በማውጣትና ንጹሕ አምልኮ በኢየሩሳሌም ተመልሶ እንዲቋቋም በማድረግ የገባውን ቃል ፈጽሟል። ታዲያ ይህ በይሖዋና በሰጠው ተስፋ ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር አያደርግም?
የዕዝራ መጽሐፍ የያዛቸውን ምሳሌ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች ተመልከት። ዕዝራና በኢየሩሳሌም ተመልሶ ለተቋቋመው ንጹሕ አምልኮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ከስደት የተመለሱት ሰዎች በአርዓያነት የሚታይ ለአምላክ የማደር ባሕርይ አሳይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ይህ መጽሐፍ አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው መጻተኞች ያሳዩትን እምነትና ንስሐ የገቡት ኃጢአተኞች የነበራቸውን የትሕትና ባሕርይ ያጎላል። በእርግጥም ዕዝራ በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ የጻፈው ይህ መጽሐፍ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ” ስለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ ነው።—ዕብራውያን 4:12
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
ከ537 እስከ 467 ከክ.ል.በፊት የነበሩ የፋርስ ነገሥታት
ታላቁ ቂሮስ (ዕዝራ 1:1) በ530 ከክ.ል.በፊት ሞተ
ጠረክሲስ ወይም አሕሻዊሮስ (ዕዝራ 4:6) 530-522 ከክ.ል.በፊት
አርጤክስስ ማለትም ባርዲያ ወይም ጋውማታ የሚባለው (ዕዝራ 4:7) 522 ከክ.ል.በፊት (ሰባት ወር ከገዛ በኋላ ተገደለ)
ቀዳማዊ ዳርዮስ (ዕዝራ 4:24) 522-486 ከክ.ል.በፊት
ዜርሰስ ወይም አሕሻዊሮስa 486-475 ከክ.ል.በፊት (በቀዳማዊ ዳርዮስ የንግሥና ዘመን ከ496-486 ከክ.ል.በፊት እንደራሴ ሆኖ የገዛ)
አርጤክስስ ሎንጊማነስ (ዕዝራ 7:1) 475-424 ከክ.ል.በፊት
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዜርሰስ በዕዝራ መጽሐፍ ውስጥ አልተጠቀሰም። ከዚህ ይልቅ በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ ጠረክሲስ [“አሕሻዊሮስ፣” NW ] በሚባለው ስሙ ተጠቅሶ ይገኛል።
[ሥዕል]
አሕሻዊሮስ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቂሮስ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቂሮስ ሲሊንደር ምርኮኞቹ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያዘውን አዋጅ ይዟል
[ምንጭ]
ሲሊንደር:- Photograph taken by courtesy of the British Museum
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዕዝራ ውጤታማ አስተማሪ እንዲሆን ያስቻለው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?