የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የአስቴር መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
ዕቅዱ ፈጽሞ የሚከሽፍ አይመስልም። አይሁዳውያንን ጠራርጎ ለማጥፋት ታልሟል። ከሕንድ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ ባለው ግዛት ውስጥ የሚኖሩ አይሁዳውያን በሙሉ አስቀደሞ በተወሰነው ቀን ይደመሰሳሉ። የሴራው ጠንሳሽ ዓላማ ይህ ነበር። ይሁንና ይህ ሰው አንድ ትልቅ ነጥብ ዘንግቷል። በሰማይ የሚኖረው አምላክ የመረጣቸውን ሕዝቦቹን ከማንኛውም ዓይነት አስጊ ሁኔታ ሊታደጋቸው አንደሚችል አልተገነዘበም። ይህ የማዳን እርምጃ በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።
መርዶክዮስ በተባለ በዕድሜ የገፋ አይሁዳዊ የተጻፈው የአስቴር መጽሐፍ፣ በፋርሱ ንጉሥ በአሀሱሩስ ወይም ቀዳማዊ ጠረክሲስ ዘመን የተከናወነውን የ18 ዓመታት ታሪክ ያወሳል። ይህ አስደናቂ ትረካ ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ በሰፊ ግዛት ውስጥ ተበታትነው የነበረ ቢሆንም እንኳ ጠላቶቻቸው ከጠነሰሱት ሴራ እንዴት እንዳዳናቸው ይገልጻል። በዛሬው ጊዜ በ235 አገሮችና ደሴቶች ውስጥ እየኖሩ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት የይሖዋ ሕዝቦች ይህን ማወቃቸው እምነታቸውን ይበልጥ ያጠናክርላቸዋል። በተጨማሪም በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት፣ ልንኮርጃቸው አሊያም ልናስወግዳቸው የሚገቡንን ባሕርያት ለይተን እንድናውቅ የሚረዱ ምሳሌዎች ይዘውልናል። በእርግጥም “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።”—ዕብራውያን 4:12
ንግሥቲቷ ጣልቃ መግባት ነበረባት
ንጉሥ ጠረክሲስ በግዛት ዘመኑ ሦስተኛ ዓመት (493 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ታላቅ ንጉሣዊ ግብዣ አደረገ። በዚህ ወቅት በቁንጅናዋ የምትታወቀው ንግሥት አስጢን ባለመታዘዟ ምክንያት የንጉሡን ሞገስና እቴጌነቷን አጣች። በእርሷም ፋንታ ደናግል ከሆኑ የአገሬው ቆነጃጅት መካከል የተመረጠች ሀደሳ የተባለች አይሁዳዊት ተተካች። ንግሥቲቱም አጎቷ መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኗን እንዳትናገር የሰጣትን መመሪያ በመከተል አስቴር በሚለው የፋርስ ስሟ ትጠራ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ሐማ የተባለ አንድ ትዕቢተኛ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ተሾመ። ሐማ፣ መርዶክዮስ ‘ተንበርክኮ እጅ ሊነሳው’ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት እጅግ ስለተበሳጨ በፋርስ ግዛት የሚገኙትን ሁሉንም አይሁዳውያን ለማጥፋት ሴራ ጠነሰሰ። (አስቴር 3:2) ሐማ፣ ንጉሥ ጠረክሲስን በማግባባት በሐሳቡ እንዲስማማና አይሁዳውያንን ለመፍጀት አዋጅ እንዲያወጣ አደረገው። መርዶክዮስ ‘ማቅ ለበሰ፤ በራሱ ላይም አመድ ነሰነሰ።’ (አስቴር 4:1) አስቴር በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት አለባት። ስለሆነም ንጉሡንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለእነርሱ ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ እንዲገኙ ጠራቻቸው። ደስ ብሏቸው በግብዣው ላይ በተገኙ ጊዜ አስቴር በቀጣዩ ቀን በምታዘጋጀው ሌላ ግብዣ ላይ እንዲገኙ ተማጸነቻቸው። ሐማ በሁኔታው በጣም ተደሰተ። ይሁንና መርዶክዮስ ክብር እንዳልሰጠው ሲመለከት እጅግ ተናደደ። ሐማ በሚቀጥለው ቀን ወደ ግብዣው ከመሄዱ በፊት መርዶክዮስን ለመግደል አቀደ።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:3-5—ግብዣው የተደረገው ለ180 ቀናት ነበር? ጥቅሱ፣ ንጉሡ ለ180 ቀናት ያህል የመንግሥቱን ሀብትና የግርማውን ክብር ለባለ ሥልጣናቱ እንዳሳያቸው እንጂ ግብዣው ይህን ያህል ጊዜ መቆየቱን አይናገርም። በእነዚህ ቀናት ንጉሡ መኳንንቶቹ የመንግሥቱን ክብር እንዲያዩለትና ያቀደውን ሁሉ ለማሳካትም አቅሙ እንዳለው እንዲገነዘቡ ለማድረግ ሞክሮ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ በቁጥር 3 እና 5 ላይ የተገለጸው ግብዣ የሚያመለክተው በ180ዎቹ ቀናት መገባደጃ ላይ የተደረገውን የ7 ቀን ድግስ ሊሆን ይችላል።
1:8 የ1954 ትርጉም—‘መጠጡ እንደ ወጉ ያልነበረው’ በምን መልኩ ነው? ፋርሳውያን እንደዚህ ባሉ ግብዣዎቻቸው ላይ አንዳቸው ሌላውን የተወሰነ መጠን ያለው መጠጥ እንዲጠጡ የመገፋፋት ወግ ወይም ልማድ ነበራቸው። ይሁንና በዚህ ግብዣ ላይ ንጉሥ ጠረክሲስ ከዚህ ወግ በተቃራኒ እንደ ፍላጎታቸው እንዲጠጡ ፈቀደላቸው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳለው “ጥቂትም ይሁን ብዙ የፈለጉትን ያህል መጠጣት ይችሉ ነበር።”
1:10-12—ንግሥት አስጢን ንጉሡ ዘንድ ለመሄድ አሻፈረኝ ያለችው ለምን ነበር? አንዳንድ ምሑራን ንግሥቲቱ ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያልነበረችው በሰከሩት የንጉሡ እንግዶች ፊት በመቅረብ ራሷን ማዋረድ ስላልፈለገች ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ። አሊያም ደግሞ ማራኪ ውጪያዊ ውበት ያላት ይህቺ ንግሥት የታዛዥነት ባሕርይ ይጎድላት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ለምን እንዲህ እንዳደረገች በግልጽ ባይነግረንም በጊዜው የነበሩት ጠቢባን ለባል አለመታዘዝ በቸልታ የሚታለፍ ጉዳይ እንዳልሆነና የአስጢን መጥፎ ምሳሌነት በፋርስ ግዛት በሚኖሩ በሌሎች ሚስቶችም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተሰምቷቸው ነበር።
2:14-17—አስቴር ከንጉሡ ጋር የጾታ ብልግና ፈጽማ ነበር? መልሱ አልፈጸመችም ነው። ዘገባው ወደ ንጉሡ የተወሰዱት ሌሎቹ ሴቶች ሲነጋ “የቁባቶች ኀላፊ” በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ ጥበቃ ሥር ወደሚገኝ ሌላ ቤት ይወሰዱ እንደነበር ይገልጻል። ስለሆነም ከንጉሡ ጋር ያደሩ ሴቶች ቁባቶቹ ይሆናሉ። ይሁንና አስቴር ወደ ንጉሡ ከተወሰደች በኋላ ወደ ቁባቶቹ ቤት አልተወሰደችም። በጠረክሲስ ፊት በቀረበች ጊዜ “ንጉሡ ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹ ደናግልም ሁሉ ይልቅ በእርሱ ዘንድ ሞገስንና መወደድን አገኘች።” (አስቴር 2:17) አስቴር በጠረክሲስ ዘንድ “ሞገስንና መወደድን” ያተረፈችው እንዴት ነው? የሌሎች ሰዎችን ሞገስ ልታገኝ በቻለችበት መንገድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልጃገረዲቱም [ሄጌን] ደስ አሰኘችው፤ በእርሱም ዘንድ መወደድን አተረፈች” ይላል። (አስቴር 2:8, 9) ሄጌ አስቴርን ሊወድዳት የቻለው ባየው ነገር ማለትም በመልኳና በመልካም ባሕርያቷ መሆኑ ግልጽ ነው። በእርግጥም አስቴር ‘በሚያዩዋት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አግኝታ’ ነበር። (አስቴር 2:15) በተመሳሳይም ንጉሡ አስቴር ላይ ባየው ነገር በመማረኩ ምክንያት ሊወድዳት ችሏል።
3:2፤ 5:9—መርዶክዮስ ለሐማ ለመስገድ ፈቃደኛ ያልነበረው ለምንድን ነው? እስራኤላውያን ለአንድ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን አክብሮታቸውን ለማሳየት ቢሰግዱ ስህተት አልነበረም። ሆኖም የሐማን ሁኔታ በተመለከተ ሁኔታው ከዚህ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። ሐማ አጋጋዊ ስለነበር አማሌቃዊ ሳይሆን አይቀርም፤ ይሖዋ ደግሞ አማሌቃውያንን ከምድር ገጽ እንዲጠፉ ወስኖባቸዋል። (ዘዳግም 25:19) ለመርዶክዮስ፣ ለሐማ መስገድ ማለት ለይሖዋ ታማኝ የመሆንና ያለመሆን ጥያቄ ነበር። ስለሆነም አይሁዳዊ መሆኑን በመናገር እንደማይሰግድ በግልጽ አሳይቷል።—አስቴር 3:3, 4
ምን ትምህርት እናገኛለን?
2:10, 20፤ 4:12-16:- አስቴር በመንፈሳዊ የጎለመሰ የይሖዋ አምላኪ የሰጣትን መመሪያና ምክር ተቀብላለች። እኛም ‘ለመሪዎቻችን ብንታዘዝና ብንገዛ’ እንጠቀማለን።—ዕብራውያን 13:17
2:11፤ 4:5:- ‘ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችንን የሚጠቅመውን ብቻ መመልከት’ አይኖርብንም።—ፊልጵስዩስ 2:4
2:15:- አስቴር ከሄጌ ካገኘችው ሌላ ተጨማሪ ጌጣጌጦችን ወይም ምርጥ አልባሳት እንዲሰጣት ባለመጠየቅ ልከኛና ራሷን የምትገዛ መሆኗን አሳይታለች። አስቴር የንጉሡን ሞገስ ያገኘችው “ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት” ስለነበራት ነው።—1 ጴጥሮስ 3:4
2:21-23:- አስቴርና መርዶክዮስ ‘በሥልጣን ላሉት ሹማምንት በመገዛት’ ረገድ ግሩም ምሳሌ ናቸው።—ሮሜ 13:1
3:4:- ልክ እንደ አስቴር በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ማንነታችንን አለመግለጹ ጥበብ የተንጸባረቀበት ተገቢ እርምጃ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ አቋማችንን ማሳወቅ ሲኖርብን፣ ለአብነት ያህል የይሖዋን ሉዓላዊነትና ታማኝነታችንን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲገጥሙን የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለማሳወቅ መፍራት አይኖርብንም።
4:3:- የተለያዩ ፈተናዎች ሲደርሱብን ብርታትና ጥበብ እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል።
4:6-8:- መርዶክዮስ የሐማን ሴራ ለማክሸፍ በሕጋዊ መንገድ ተጠቅሟል።—ፊልጵስዩስ 1:7 NW
4:14:- መርዶክዮስ በይሖዋ በመታመን ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው።
4:16:- አስቴር በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር ሞት ሊያስከትልባት ይችል የነበረውን ሁኔታ በታማኝነትና በድፍረት ተጋፍጣለች። ይህ በራሳችን ሳይሆን በይሖዋ የመታመንን አስፈላጊነት ያስተምረናል።
5:6-8:- አስቴር የጠረክሲስን ሞገስ ለማግኘት ስትል ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀችው ድግስ ላይ እንዲገኝ ጋብዛዋለች። ያሰበችውን ለማሳካት ብልሃት ተጠቅማለች፤ እኛም እንደ እርሷ ብልሆች መሆን ይኖርብናል።—ምሳሌ 14:15
ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ ሆነ
ጉዳዩ ገሃድ ሲወጣ ሁኔታው ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነ። ሐማ ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው እንጨት ላይ ተሰቀለ፤ ሊሰቀል የታሰበው ሰው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ! አይሁድን ለማጥፋት የተወጠነው ዕቅድስ ከምን ደረሶ ይሆን? በዚህ ረገድም ቢሆን አስገራሚ ለውጥ ተከስቷል።
ታማኝ የሆነችው አስቴር አሁንም ስሞታዋን አቀረበች። ሕይወቷን አደጋ ላይ በመጣል የሐማን ዕቅድ የሚያከሽፍ ብልሃት ይፈልግ ዘንድ ንጉሡን ቀርባ ተማጸነች። ጠረክሲስ ምን መደረግ እንዳለበት ያውቅ ነበር። በመሆኑም አይሁዳውያን የሚደመሰሱበት ቀን ሲደርስ ሊጎዷቸው የሚፈልጉት ሰዎች ራሳቸው ተገደሉ። መርዶክዮስ ይህን ታላቅ የመዳን ቀን ለማስታወስ በየዓመቱ የፋሪም በዓል እንዲከበር አወጀ። መርዶክዮስ ከንጉሥ ጠረክሲስ ቀጥሎ ያለውን ማዕረግ ከመያዙም በተጨማሪ ‘ለወገኖቹ መልካም ያደርግና ለአይሁድም ሁሉ ደኅንነት ይቆም’ ነበር።—አስቴር 10:3
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
7:4 የግርጌ ማስታወሻ—አይሁዳውያን በመደምሰሳቸው ‘ንጉሡ የሚያጣው’ እንዴት ነው? አስቴር፣ አይሁዳውያን በባርነት ሊሸጡ ይችሉ እንደነበር በብልሃት በመግለጽ መጥፋታቸው ንጉሡን እንደሚጎዳው ተናግራለች። ሐማ ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማስገባት ቃል የገባው 10,000 መክሊት ብር አይሁዳውያንን በባርነት ለመሸጥ አቅዶ ቢሆን ኖሮ ሊገኝ ከሚችለው ትርፍ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። ሐማ ያቀደው ተሳክቶለት ቢሆን ኖሮ ንጉሡ ንግሥቲቱንም ያጣ ነበር።
7:8—የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች የሐማን ፊት የሸፈኑት ለምን ነበር? የሐማን መዋረድ ወይም የሚጠብቀውን ፍርድ ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳለው ከሆነ “አንዳንድ ጊዜ የጥንት ሰዎች የሞት ፍርድ የሚፈጸምባቸውን ሰዎች ራስ ይሸፍኑ ነበር።”
8:17—‘ከሌሎች አገር ዜጎች ብዙ ሕዝብ አይሁድ የሆኑት’ በምን መንገድ ነበር? ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በርካታ ፋርሳውያን፣ የአዋጁ መለወጥ አይሁዳውያን የአምላክን ሞገስ እንዳገኙ የሚያረጋግጥ እንደሆነ አድርገው ስለተመለከቱት ወደ ይሁዲነት ተቀይረው ነበር። እዚህ ላይ የሰፈረው መሠረታዊ ሥርዓት በዘካርያስ መጽሐፍ ውሰጥ የሚገኘው ትንቢት ሲፈጸምም ይሠራል። ትንቢቱ እንደሚከተለው ይላል:- “በእነዚያም ቀናት ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ’ ይሉታል።”—ዘካርያስ 8:23
9:10, 15, 16—አዋጁ ምርኮ መውሰድን ቢፈቅድላቸውም እንኳ አይሁዳውያን ይህን ማድረግ ያልፈለጉት ለምን ነበር? ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ዓላማቸው ራሳቸውን መከላከል እንጂ መበልጸግ እንዳልሆነ በማያሻማ ሁኔታ አሳይተዋል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
6:6-10:- “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች።”—ምሳሌ 16:18
7:3, 4:- ስደት የሚያስከትልብን ቢሆንም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን በድፍረት እንናገራለን?
8:3-6:- ከጠላቶቻችን ከለላ ለማግኘት ስንል ወደ መንግሥት ባለ ሥልጣናትም ሆነ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንችላለን፤ እንዲህ ማድረግም ይኖርብናል።
8:5:- አስቴር ሕዝቧን ለማጥፋት በወጣው አዋጅ ላይ ንጉሡ የነበረውን ድርሻ ባለመጥቀስ ብልህ መሆኗን አሳይታለች። እኛም በተመሳሳይ ለባለ ሥልጣናት በምንመሰክርበት ጊዜ ዘዴኛ መሆን ይገባናል።
9:22:- በመካከላችን ያሉትን ድሆች ልንረሳቸው አይገባም።—ገላትያ 2:10
ይሖዋ “ርዳታና ትድግና” ይሰጣል
መርዶክዮስ፣ አስቴር ንግሥት ለመሆን የበቃችው ይሖዋ ዓላማው ስለነበረ መሆኑን በተዘዋዋሪ ተናግሯል። አይሁዳውያን አስፈሪ ሁኔታ በገጠማቸው ጊዜ እርዳታ ለማግኘት ከመጸለያቸውም በላይ ጾመዋል። ንግሥቲቱ ሳትጠራ በንጉሡ ፊት የቀረበች ቢሆንም ይህን ባደረገችበት ጊዜ ሁሉ ንጉሡ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሏታል። በጣም ወሳኝ በሆነችው በዚያች ምሽት ንጉሡ እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። በእርግጥም የአስቴር መጽሐፍ፣ ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመጥቀም ሲል ሁኔታዎችን እንዴት እንዳስተካከላቸው ያሳያል።
የአስቴር መጽሐፍ የያዘው አስደናቂ ዘገባ በተለይ ‘በፍጻሜው ዘመን’ ለምንኖረው ለእኛ ማበረታቻ ይሰጠናል። (ዳንኤል 12:4) “በኋለኛው ዘመን” ወይም በመጨረሻዎቹ ቀናት መደምደሚያ ላይ የማጎጉ ጎግ የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ የይሖዋን ሕዝቦች ባለ በሌለ ኃይሉ ለማጥቃት ይነሳል። ዓላማውም እውነተኛ አምላኪዎችን ጠራርጎ ማጥፋት ነው። ይሁንና በአስቴር ዘመን እንደሆነው ሁሉ ይሖዋ ለሚያመልኩት ሰዎች “ርዳታና ትድግና” ይሰጣቸዋል።—ሕዝቅኤል 38:16-23፤ አስቴር 4:14
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስቴርና መርዶክዮስ በጠረክሲስ ፊት በቀረቡ ጊዜ