መልካም ቃል ያለው ኃይል
“ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።”—ምሳሌ 12:25
ክርስቲያኖች ምንም መከራ የማይደርስባቸው አይደሉም። በዚህ ‘በሚያስጨንቅ ዘመን ውስጥ’ ስለሚኖሩ አልፎ አልፎ መከራ ያጋጥማቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1
በጣም አስጨናቂ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ታማኝ ከሆነ ወዳጅ መልካም ቃል መስማት ምንኛ በረከት ነው! መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ለመከራ ጊዜ እንደሚወለድ ወንድም ነው” ይላል። (ምሳሌ 17:17 አዓት) ታማኙ ሰው ኢዮብ እንዲህ ዓይነት ወዳጅ በመሆን የታወቀ ነበር። ኤልፋዝ እንኳ “ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፣ አንተም የሚብረከረከውን ጉልበት ታጸና ነበር” ሲል ስለ ኢዮብ ተናግሯል።—ኢዮብ 4:4
ይሁን እንጂ ኢዮብ ራሱ ማበረታቻ ባስፈለገው ጊዜ ኤልፋዝና ጓደኞቹ መልካም ቃል በመናገር አላበረታቱትም። ኢዮብ አንዳንድ የተሰወሩ ጥፋቶችን ሠርቶ ይሆናል በማለት ለደረሰበት መከራ ጥፋተኛው እሱ እንደሆነ ተናገሩ። (ኢዮብ 4:8) ዘ ኢንተርፕሬተርስ ባይብል እንዲህ በማለት አስተያየቱን ይሰጣል፦ “ኢዮብ ያስፈልገው የነበረው ነገር በርኅራኄ የተሞላ ልብ ነበር። ከሌሎች ያገኘው ግን ሙሉ በሙሉ ‘እውነት’ ተደርገው የቀረቡ አሰልቺ ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ሐሳቦችን ነበር።” ኢዮብ የኤልፋዝንና የጓደኞቹን ንግግር ሰምቶ በጣም በመበሳጨቱ እንደሚከተለው ለማለት ተገዷል፦ “ነፍሴን የምትነዘንዙ፣ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?”—ኢዮብ 19:2
አሳቢነትና ደግነት በጎደላቸው አነጋገሮቻችን የተነሣ አብሮን አምላክን የሚያገለግለውን ሰው ማሳዘን በፍጹም አይገባንም። (ከዘዳግም 24:15 ጋር አወዳድር።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የምትናገረው ነገር ሕይወትን ሊያድን ወይም ሊያጠፋ ይችላል፤ ስለዚህ የንግግርህን ውጤት መቀበል ይኖርብሃል” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 18:21 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን
የምንናገረው ቃል ምን ያህል ኃይል እንዳለው በመገንዘብ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ መከተል አለብን። ጳውሎስ በመቄዶንያ በነበረበት ጊዜ ‘በዚያ የነበሩትን በብዙ ቃል ያበረታታቸው ነበር።’—ሥራ 20:2