የእጁ ሥራዎች የሆኑት እንስሳት ይሖዋን ያወድሳሉ
የይሖዋ ፍጥረታት የሆኑት እንስሳት የአምላክን ታላቅነት ይመሠክራሉ። አምላክ የሰው ዘሮችን እንደሚንከባከባቸው ሁሉ ለእንስሳትም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያሟላላቸዋል። (መዝሙር 145:16) እንስሳትንም ሆነ እኛን የፈጠረውን አምላክ መተቸት እንዴት ያለ ታላቅ ስሕተት ነው! ኢዮብ የተባለው ሰው ቅን የነበረ ቢሆንም “ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ ስላደረገ” ትምህርት ሊሰጠው ይገባ ነበር።—ኢዮብ 32:2፤ 33:8-12፤ 34:5
አምላክ ከእንስሳት መካከል አንዳንድ ምሳሌዎች በመጥቀስ፣ የሰው ልጆች የእርሱን መንገዶች ትክክለኛነት በተመለከተ ጥያቄ ማንሳታቸው ያለ ቦታቸው መግባት እንደሚሆንባቸው ኢዮብን አስገንዝቦታል። ይሖዋ ለአገልጋዩ ለኢዮብ የተናገራቸውን ቃላት ስንመለከት ይህ ሐቅ ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል!
ሰብዓዊ እርዳታ አያስፈልጋቸውም
ኢዮብ የእንስሳትን ሕይወት አስመልክቶ አምላክ ላቀረበለት ጥያቄዎች መልስ መስጠት አልቻለም። (ኢዮብ 38:39-41) ይሖዋ ለአንበሳም ሆነ ለቁራ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ለማቅረብ የሰዎች እርዳታ እንደማያሻው ግልጽ ነው። ቁራዎች ምግብ ፍለጋ ወዲያና ወዲህ የሚበሩ ቢሆንም የሚመግባቸው ግን አምላክ ነው።—ሉቃስ 12:24
አምላክ ስለ ዱር አራዊት ሲጠይቀውም ኢዮብ መልስ አልነበረውም። (ኢዮብ 39:1-8) ለበረሃ ፍየሎችም ሆነ ለዋልያ ጥበቃ ማድረግ የሚችል ሰው የለም። ሌላው ቀርቶ የበረሃ ፍየሎችን በቅርበት መመልከት እንኳ በጣም አስቸጋሪ ነው! (መዝሙር 104:18) ዋልያ፣ አምላክ በተፈጥሮዋ የሰጣትን መመሪያ በመከተል ልትወልድ ስትል ከሌሎች ተለይታ ራሷን በጫካ ውስጥ ትሸሽጋለች። እናቶቹ ግልገሎቻቸውን በሚገባ የሚንከባከቧቸው ቢሆንም ‘ሲጠነክሩ’ ግን “ተለይተው ይሄዳሉ፤ ወደ እነርሱም አይመለሱም።” ከዚያ በኋላ ራሳቸውን ችለው መኖር ይጀምራሉ።
የሜዳ አህያ በነጻነት የሚፈነጭ ሲሆን ምድረ በዳው ደግሞ የበረሃ አህያ መኖሪያ ነው። ኢዮብ የበረሃ አህያን ለጭነት ሊጠቀምበት አይችልም። ይህ እንስሳ “ሐመልማሉንም ሁሉ ለማግኘት” በየተራራው ይሰማራል። በከተማ ውስጥ በቀላሉ ምግብ ለማግኘት ሲል በበረሃ ያለውን ነጻነት ማጣት አይፈልግም። የበረሃ አህያ የሚኖርበትን አካባቢ የሰው ልጅ ከያዘበት ቦታውን ለቅቆ የሚሸሽ በመሆኑ “የነጂውንም ጩኸት አይሰማም” ተብሎለታል።
ቀጥሎ ደግሞ አምላክ ስለ ጐሽ አነሳ። (ኢዮብ 39:9-12) እንግሊዛዊው አርኪኦሎጂስት ኦስተን ሌያርድ እንዲህ ብለዋል:- “በተደጋጋሚ ጊዜያት በቅርጻ ቅርጾች ላይ ከሚታየው ምስሉ መገንዘብ እንደሚቻለው [ጐሽ] በአስፈሪነቱና በግርማ ሞገሱ ከአንበሳ ብዙም የማይተናነስ ለአደን የሚፈለግ እንስሳ ነው። ብዙውን ጊዜ ንጉሡ ከዚህ እንስሳ ጋር ሲታገል ይታያል፤ ጦረኞችም ቢሆኑ በፈረስና በእግራቸው ያሳድዱት ነበር።” (ነነቬ ኤንድ ኢትስ ሪሜይንስ፣ 1849, ጥራዝ 2 ገጽ 326) ያም ቢሆን ግን ብልህ የሆነ ማንኛውም ሰው የማይገራውን ጐሽ ለመያዝ አይሞክርም።—መዝሙር 22:21 NW
አእዋፍ ይሖዋን ያወድሳሉ
ቀጥሎም አምላክ ኢዮብን ስለ አእዋፍ ጠየቀው። (ኢዮብ 39:13-18) ሽመላ ጠንካራ በሆኑት ክንፎቿ ከፍ ብላ ትበራለች። (ኤርምያስ 8:7) በሌላ በኩል ሰጎን ክንፎቿን ብታራግብም መብረር ግን አትችልም። ከሽመላ በተቃራኒ ሰጎን እንቁላሎቿን የምታስቀምጠው ዛፍ ላይ በተሠራ ጎጆ ውስጥ አይደለም። (መዝሙር 104:17) አሸዋውን ጭራ ጉድጓድ ካበጀች በኋላ እንቁላሎቿን እዚያ ትጥላለች። ያም ቢሆን ግን አትረሳቸውም። እንቁላሎቹ ተስማሚ ሙቀት በሚያገኙበት አሸዋ ውስጥ ተቀብረው እያሉ ወንዱም ሆነ ሴቷ ሰጎን ይጠብቋቸዋል።
ሰጎን ጠላት አደጋ ሊጥል እንደሆነ ተመልክታ ስትሮጥ ላያት ‘እግዚአብሔር ጥበብን የነሳት’ ትመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ አን ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ባይብል አኒማልስ እንደሚለው “ይህ የጠላትን ትኩረት ለመስረቅ የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው:- [ሰጎኖች] አደጋ ሊያደርስ የሚችልን የማንኛውንም ሰው ወይም እንስሳ ትኩረት ለመሳብ እነርሱን እንዲያያቸው በማድረግና ክንፎቻቸውን በማራገብ የመጣውን ጠላት ከእንቁላሎቹ ያርቁታል።”
ሰጎን “በፈረስና በጋላቢው ትሥቃለች” የተባለው ለምንድን ነው? ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “ሰጎን መብረር ባትችልም በምድር ላይ በፍጥነት በመሮጥ የታወቀች ናት። ረጃጅም ቅልጥሞቿን 4.6 ሜትር ያህል በመዘርጋት በሰዓት እስከ 64 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት መጓዝ ትችላለች።”
አምላክ ለፈረስ ጉልበት ሰጥቶታል
አምላክ ኢዮብን ስለ ፈረስም ጠይቆታል። (ኢዮብ 39:19-25) በጥንት ዘመናት ጦረኞች የሚዋጉት በፈረስ እየጋለቡ ነበር፤ ከዚህም በላይ ፈረሶች ነጂውንና ምናልባትም ሁለት ወታደሮችን የጫኑ ሠረገላዎችን ለመጎተት ያገለግሉ ነበር። የጦርነት ፈረስ ትዕግሥት በማጣት እያሽካካ መሬቱን በሰኮናው ይጭራል። ሰይፍ አይቶ አይፈራም፤ ወደኋላም አያፈገፍግም። ለጦርነት የተዘጋጀው ፈረስ የመለከት ድምፅ ሲሰማ ‘እሰይ’ የሚል ያህል ይቅበጠበጣል። “መሬቱን እየጐደፈረ” ወደፊት ይሸመጥጣል። ያም ሆኖ ፈረሱ ለጋላቢው ታዛዥ ነው።
የአርኪኦሎጂ ተመራማሪ የሆኑት ሌያርድ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል መግለጫ ሰጥተዋል:- “እንደ በግ ገራገር የሆነችውና ከልጓም በስተቀር ሌላ መሪ የማያስፈልጋት የአረብ ባዝራ፣ ለጦርነት የሚነፋውን መለከት ስትሰማና ጋላቢዋ ጦሩን ሲሰብቅ ስትመለከት ዓይኖቿ እሳት የሚተፉ ይመስላሉ፤ ፍም የሚመስሉት የአፍንጫዋ ቀዳዳዎችም በሰፊው የሚከፈቱ ሲሆን አንገቷን እንደ ደጋን ትቀስረዋለች። ጭራዋንና ጋማዋን ስለምታቆመው ነፋሱ ያርገበግበዋል።”—ዲስከቨሪስ አመንግ ዘ ሩዊንስ ኦቭ ነነቬ ኤንድ ባቢሎን፣ 1853, ገጽ 330
ጭልፊትንና ንስርን ተመልከት
ይሖዋ ትኩረቱን ወደ ሌሎች ወፎች መለሰ። (ኢዮብ 39:26-30) ጭልፊት ‘ሲበር ክንፎቹን ወደ ደቡብ ይዘረጋል።’ ዘ ጊነስ ቡክ ኦቭ ሪከርድስ ፔሪግሪን የሚባለው ጭልፊት በፍጥነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ወፍ እንደሆነ ገልጿል፤ አክሎም ይህ ወፍ “ድንበሩን ለማስከበር ከከፍታ ቦታ ላይ ወደ ታች ሲምዘገዘግ ወይም በአየር ላይ የሚበርን ነገር ሞጭልፎ ለመብላት ሲፈልግ በከፍተኛ ፍጥነት በመብረር ሪከርድ እንደያዘ” ዘግቧል። ይህ የጭልፊት ዝርያ በሰዓት 349 ኪሎ ሜትር እየበረረ በ45 ዲግሪ ቁልቁል እንደሚወረወር ተመዝግቧል!
ንስሮች በሰዓት ከ130 ኪሎ ሜትር በሚበልጥ ፍጥነት ይበርራሉ። ኢዮብ በፍጥነት የሚያልፈውን የሰው ልጅ የሕይወት ዘመን ምግብ ፍለጋ በፍጥነት ከሚበር ንስር ጋር አወዳድሮታል። (ኢዮብ 9:25, 26) አምላክ፣ ድካም የሚባል ነገር የማያውቅ በሚመስለው በንስር ክንፍ ላይ የተቀመጥን ያህል ለመጽናት የሚያስችለን ብርታት እንደሚሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳይያስ 40:31) ንስር በሚበርበት ወቅት ሞቃት አየር ወደ ላይ የሚወጣባቸውን ቴርማል በመባል የሚጠሩ መስመሮች በመከተል ከፍ እያለ ይሄዳል። ንስሩ ሞቃቱ አየር ወደ ላይ በሚነሳበት አካባቢ ሲያንዣብብ አየሩ እየገፋ ያወጣዋል። በዚህ መንገድ የተወሰነ ከፍታ ላይ ሲደርስ ቀጥሎ ወዳለው ቴርማል በመሻገር ብዙም ጉልበት ሳያባክን በአየር ላይ ለረጅም ሰዓታት እያንዣበበ መቆየት ይችላል።
ንስር ‘ጎጆውን በከፍታ ላይ የሚሠራ’ በመሆኑ ጫጩቶቹ አደጋ ሊደርስባቸው አይችልም። ይሖዋ ንስርን ሲፈጥር በደመ ነፍስ ይህን የማድረግ ችሎታ ሰጥቶታል። ከዚህም በላይ አምላክ በሰጠው የማየት ችሎታ በመጠቀም “ከሩቅ አጥርቶ ያያል።” ንስር እይታውን ወዲያው የማስተካከል ችሎታ ስላለው ከርቀት ያየውን እንስሳ ወይም በድን ለመውሰድ ከከፍታ ቦታ ላይ ወደ ታች ተምዘግዝጎ ሲወርድ የሚፈልገው ነገር ከእይታው አይጠፋበትም። ንስር የሞቱ እንስሳትንም ሊመገብ ስለሚችል “በድን ካለበት አይታጣም።” ይህ ወፍ ትናንሽ እንስሳትን ካደነ በኋላ ለጫጩቶቹ ይወስድላቸዋል።
ይሖዋ ለኢዮብ ተግሣጽ ሰጠው
አምላክ ስለ እንስሳት ተጨማሪ ጥያቄዎች ከማንሳቱ በፊት ለኢዮብ ተግሣጽ ሰጠው። ታዲያ ኢዮብ ተግሣጹን እንዴት ተቀበለው? ራሱን ዝቅ በማድረግ የተሰጠውን ተጨማሪ ምክር በፈቃደኝነት ተቀብሏል።—ኢዮብ 40:1-14
ከእነዚህ ጥቅሶች እንደተመለከትነው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የኢዮብ ታሪክ ውስጥ የምናገኘው በጣም አስፈላጊ ትምህርት አለ:- ማንኛውም ሰው ቢሆን በአምላክ ላይ ስሕተት አግኝቻለሁ ብሎ ለመከራከር የሚያስችለው ምንም ዓይነት መሠረት የለውም። የምንናገረውም ሆነ የምናደርገው ነገር በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን የሚያስደስት መሆን አለበት። ከዚህም በላይ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው የይሖዋ ስም መቀደስና ሉዓላዊነቱ ከነቀፋ ነጻ መሆኑ ነው።
ብሄሞት አምላክን ያወድሳል
አምላክ ትኩረቱን እንደገና ወደ እንስሳት ዓለም በመመለስ ኢዮብን ስለ ብሄሞት (ጉማሬ እንደሆነ ይታሰባል) ጠየቀው። (ኢዮብ 40:15-24) እድገቱን የጨረሰ ጉማሬ ከ4 እስከ 5 ሜትር ርዝመትና 3, 600 ኪሎ ግራም ክብደት ሊኖረው ይችላል። ብሄሞት “ብርታቱ ወገቡ ውስጥ” ማለትም በኋለኛው የሰውነቱ ክፍል ባሉት ጡንቻዎች ውስጥ እንደሆነ ተገልጿል። አጫጭር እግሮች ያሉት ይህ እንስሳ በወንዝ ውስጥ ሲጓዝ ሰውነቱን በድንጋይ ላይ ስለሚጎትተው በሆዱ አካባቢ ያለው ቆዳ ወፍራም መሆኑ በጣም ይጠቅመዋል። የሰው ልጅ ግዙፍ ሰውነት፣ ሰፊ አፍና ኃይለኛ መንጋጋ ካለው ከብሄሞት ጋር መጋጠም እንደማይችል ግልጽ ነው።
ብሄሞት “ሣር” ለመብላት ከወንዝ ውስጥ ይወጣል። የሚያስገርመው ነገር ጉማሬ ሆዱን ለመሙላት አንድን ተራራ የሸፈነው ሣር እንኳ የሚበቃው አይመስልም! በየቀኑ ከ90-180 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቅጠላ ቅጠል ይመገባል። አንድ ጊዜ ሆዱን ከሞላ በኋላም በአኻያ ዛፎች ሥር አሊያም በውኃ ላይ በሚያድጉ ዕፅዋት ጥላ ተሸፍኖ ያሸልባል። የሚኖርበት ወንዝ ቢሞላ ጉማሬ ጭንቅላቱን ከውኃው በላይ አድርጎ ከማዕበሉ ጋር እየተጋፋ መዋኘት ይችላል። ኢዮብ አንዳች የሚያህል አፍና አስፈሪ ጥርሶች ካሉት ጉማሬ ጋር ቢገናኝ አፍንጫውን በመንጠቆ ለመብሳት ድፍረቱም አይኖረውም።
ሌዋታን አምላክን ያስከብራል
ቀጥሎ ደግሞ ኢዮብ ስለ ሌዋታን ተነገረው። (ኢዮብ 41:1-34) ሌዋታን ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል “የተጎነጎነ ቆዳ ያለው እንስሳ” ማለት ሲሆን ይህም አዞ እንደሆነ ይገመታል። ኢዮብ ሌዋታንን አስሮ ለልጆች መጫወቻ ሊያደርገው ይችላል? የማይታሰብ ነገር ነው! ከዚህ እንስሳ ጋር የተገናኙ ሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት የገጠማቸው ሁኔታ አዞ አደገኛ መሆኑን ያረጋግጣል። በእርግጥም አንድ ሰው ሌዋታንን ለመግራት ቢፈልግ ከፍተኛ ግብግብ የሚጠይቅበት በመሆኑ ዳግመኛ አይሞክረውም!
ሌዋታን ጎህ ሲቀድ ጭንቅላቱን ከውኃው ውስጥ ብቅ በሚያደርግበት ጊዜ ዓይኖቹ እንደ “ማለዳ ጮራ” ያበራሉ። ጀርባው ላይ ያሉት ቅርፊቶች ግጥግጥ ያሉ ናቸው፤ ቆዳው ላይ የተለጠፉትን አጥንት መሰል ሽፋኖች ሰይፍና ጦር ቀርቶ ጥይት እንኳ አይበሳቸውም። በሆዱ ሥር ያለው ሸካራ ሽፋን “እንደ መውቂያ መሣሪያ” በጭቃ ላይ ምልክት ይተዋል። በሚቆጣበት ጊዜ ደግሞ ውኃውን እንደሚፈላ ዘይት ያንተከትከዋል። ሌዋታን ግዙፍና በማይበሳ መከላከያ የተሸፈነ ሰውነት ያለው ከመሆኑም በላይ አስፈሪ መንጋጋውና ኃይለኛ ጅራቱ እንደ ጦር መሣሪያ ስለሚያገለግሉት ፍርሃት የሚባል ነገር አያውቅም።
ኢዮብ አመለካከቱን አስተካከለ
ኢዮብ “ያልገባኝን ነገር፣ የማላውቀውንና ላስተውለው የማልችለውን ጕዳይ ተናገርሁ” በማለት ጥፋቱን አምኗል። (ኢዮብ 42:1-3) አምላክ የሰጠውን እርማት የተቀበለ ከመሆኑም በላይ አመለካከቱን በማስተካከል ንስሐ ገብቷል። ወዳጆቹ እርማት ሲሰጣቸው እርሱ ግን የተትረፈረፈ በረከት አገኘ።—ኢዮብ 42:4-17
የኢዮብን ተሞክሮ ማስታወሱ ጥበብ ነው። አምላክ ለኢዮብ ያቀረበለትን ጥያቄዎች ሁሉ መመለስ እንደማንችል ግልጽ ነው። ሆኖም ይሖዋን ለሚያወድሱት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ድንቅ ፍጥረታቱ አድናቆት ልናሳይ እንችላለን፤ እንዲህ ማድረግም ይኖርብናል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የበረሃ ፍየል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቁራ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንስት አንበሳ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሜዳ አህያ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰጎን ከእንቁላሎቿ ርቃ ብትሄድም አትተዋቸውም
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰጎን እንቁላሎች
[በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፔሪግሪን የሚባለው ጭልፊት
[ምንጭ]
ጭልፊት:- © Joe McDonald/Visuals Unlimited
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአረብ ባዝራ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጎልደን ንስር
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብሄሞት ጉማሬን እንደሚያመለክት ይታሰባል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሌዋታን የተባለው አዞ እንደሆነ ይገመታል