የሰው ልጅ ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚያደርገው ጥረት
“ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፣ መከራም ይሞላዋል። እንደ አበባ ይወጣል፣ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ይሸሻል፣ እርሱም አይጸናም።”—ኢዮብ 14:1, 2
ምንም እንኳ 3,500 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት የተጻፈ ቢሆንም ስለ ሕይወት አጭርነት በሚገልጸው በዚህ ሐሳብ ዛሬ አብዛኛው ሰው ይስማማል። ሰዎች ሕይወትን ገና በወጉ አጣጥመው ሳይጨርሱ የሚያረጁበትና የሚሞቱበት ምክንያት ፈጽሞ ሊዋጥላቸው አልቻለም። በዚህም የተነሳ ሕይወት ያራዝማሉ የሚባሉ እጅግ በርካታ የሆኑ ዘዴዎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሲሞከሩ ቆይተዋል።
በኢዮብ ዘመን የነበሩ ግብፃውያን የእንስሳ ቆለጥ በመብላት ወደ ወጣትነት ለመመለስ ያደረጉት ሙከራ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። የመካከለኛው ዘመን ኬሚስትሪ ዋና ዓላማ ሕይወት ሊያራዝም የሚችል ንጥረ ነገር ማግኘት ነበር። የመካከለኛው ዘመን ኬሚስቶች ሰው ሠራሽ የሆነ ወርቅ ያለመሞትን ባሕርይ ያላብሳል እንዲሁም በወርቅ ሳህን መብላት ዕድሜን ያራዝማል ብለው ያምኑ ነበር። ጥንታዊ ቻይናውያን ታኦይስቶች እንደ ማሰላሰል፣ የአተነፋፈስ ልምምድ ማድረግና ጥሩ የአመጋገብ ሥርዓትን የመሰሉ ዘዴዎችን መጠቀም የሰውነትን ኬሚካላዊ ሂደት ለመለወጥና ዘላለማዊነትን ለማግኘት ያስችላል የሚል እምነት ነበራቸው።
ስፔናዊው አሳሽ ጁዋን ፖንክ ደ ሊዮን የወጣትነትን ምንጭ ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት እንደነበረው ይነገርለታል። አንድ የ18ኛው መቶ ዘመን ሐኪም ሄርሚፐስ ሪዳይቪቨስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በጸደይ ወቅት ወጣት ልጃገረዶች በጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጡ ከተደረገ በኋላ ትንፋሻቸው በጠርሙሶች ቢሰበሰብ ለሕይወት ማራዘሚያነት ሊያገለግል እንደሚችል ሐሳብ ሰጥተው ነበር። ያም ሆነ ይህ ከእነዚህ ዘዴዎች ውስጥ አንዱም የተሳካ ውጤት አላስገኘም።
ሙሴ የኢዮብን አነጋገር ከመዘገበ 3,500 የሚያክሉ ዓመታት ያለፉ ሲሆን ዛሬ የሰው ልጅ ጨረቃ ላይ ወጥቷል፣ መኪናዎችንና ኮምፒዩተሮችን ፈልስፏል እንዲሁም ስለ አቶምና ስለ ሴል ምርምር ማድረግ ችሏል። ይህ ሁሉ ቴክኖሎጂያዊ እድገት ቢደረግም “ሕይወታችን አጭርና በመከራ የተሞላ” ነው። እርግጥ ነው በበለጸጉ አገሮች ሰዎች የሚኖሩበት የዕድሜ ርዝመት ካለፈው መቶ ዘመን በአስደናቂ ሁኔታ ከፍ ብሏል። ሆኖም ይህ በአብዛኛው በጤና እንክብካቤ መስክ ጥሩ መሻሻል መደረጉ፣ ንጽሕናን በመጠበቅ ረገድ ውጤታማ የሆኑ እርምጃዎች መወሰዳቸውና ጥሩ ያመጋገብ ልማድ መዳበሩ ያስገኘው ውጤት ነው። ለምሳሌ ያህል በስዊድን ከ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ እስከ 1990 መጀመሪያ ድረስ በነበሩት ዓመታት የወንዶች የዕድሜ ርዝመት በአማካይ ከ40 ወደ 75 ዓመት ከፍ ያለ ሲሆን የሴቶች ደግሞ ከ44 ወደ 80 ዓመት ከፍ ብሏል። ታዲያ ይህ ሲባል የሰው ልጅ ረጅም ዕድሜ ለመኖር ያለው ጉጉት ተሟልቶለታል ማለት ነውን?
በፍጹም፣ ምንም እንኳ በአንዳንድ አገሮች በርካታ ሰዎች ረጅም ዕድሜ መኖር የቻሉ ቢሆንም ሙሴ ከረጅም ዓመታት በፊት የጻፋቸው የሚከተሉት ቃላት ዛሬም ይሠራሉ:- “ዕድሜአችን ሰባ ዓመት ነው፤ ቢበዛም ሰማንያ ዓመት ነው፤ . . . ዕድሜአችን በቶሎ ያልቃል፤ እኛም እናልፋለን።” (መዝሙር 90:10 የ1980 ትርጉም) በዚህ ረገድ በቅርቡ ለውጥ እናይ ይሆን? በእርግጥ የሰው ልጅ ረጅም ዕድሜ መኖር ይችል ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህና እነዚህን ለመሰሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።