በሰይጣን ፕሮፓጋንዳ አትሸነፍ
‘ፈጽሞ አትታለሉ። አምላካችሁ አይረዳችሁም። ከእኔ ጋር ሰላም ብትመሠርቱ ይሻላችኋል፤ አለበለዚያ ዋጋችሁን ታገኛላችሁ!’ የአሦር ንጉሥ የሰናክሬም የጦር አዛዥ ለኢየሩሳሌም ሕዝብ የተናገረው መልእክት ፍሬ ነገር ይህ ነበር። የንጉሡ ሠራዊት የይሁዳን ምድር ወርሮ ነበር። የንጉሡ መልእክተኛ የተናገራቸው ቃላት የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ወኔ ለማኮላሸት እና በፍርሃት ተሸንፈው እጃቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ የታለሙ ናቸው።—2 ነገ. 18:28-35
አሦራውያን ጨካኝና ርኅራኄ የሌላቸው በመሆናቸው የታወቁ ነበሩ። በምርኮኞቻቸው ላይ ስለፈጸሙት አሠቃቂ ድርጊት የሚገልጽ ዘግናኝ ወሬ በማናፈስ ጠላቶቻቸው በፍርሃት እንዲርዱ ያደርጉ ነበር። ፊሊፕ ቴይለር የተባሉት የታሪክ ምሑር እንደገለጹት አሦራውያን “ሽብርና ፕሮፓጋንዳ የመንዛት ፖሊሲ ይከተሉ የነበረ ሲሆን ይህን የሚያደርጉት በማረኩት ሕዝብ ላይ ፍርሃት በመልቀቅ በቁጥጥራቸው ሥር እንዳለ እንዲቆይ ለማድረግ እንዲሁም ስጋት ለሚፈጥሩባቸው ብሔራት ስለፈጸሟቸው የጭካኔ ድርጊቶች ወሬ በማዛመት ሕዝቡን ለማስበርገግና የሕዝቡን ሥነ ልቦና ለመስለብ ነበር።” ፕሮፓጋንዳ ኃይለኛ መሣሪያ ነው። ዓላማው “ሥነ ልቦናዊ ጥቃት መሰንዘር” እንደሆነ ቴይለር ገልጸዋል።
እውነተኛ ክርስቲያኖች “ትግል” አለባቸው፤ የሚታገሉት ግን “ከደምና ከሥጋ ጋር ሳይሆን . . . ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች” ይኸውም በአምላክ ላይ ካመፁ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር ነው። (ኤፌ. 6:12) ከእነዚህም መካከል ዋነኛው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። እሱም እንደ አሦራውያን ሽብርና ፕሮፓጋንዳ የመንዛት ፖሊሲ ይከተላል።
ሰይጣን እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ ንጹሕ አቋሙን እንዲያላላ ማድረግ እንደሚችል ተናግሯል። ጥንታዊ የቤተሰብ ራስ በሆነው በኢዮብ ዘመን ዲያብሎስ፣ ይሖዋ አምላክን “ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” ብሎት ነበር። በሌላ አባባል ሰው፣ ጫናው ከበዛበት ይዋል ይደር እንጂ ለአምላክ ያለውን ታማኝነት ማላላቱ እንደማይቀር መናገሩ ነበር። (ኢዮብ 2:4) ታዲያ ሰይጣን ትክክል ነው? ማንኛችንም ብንሆን መጽናት የምንችለው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ብቻ ነው? ፈተናው ከተወሰነ ደረጃ ሲያልፍ በሕይወት ለመቆየት ስንል የምናምንባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንጥሳለን ማለት ነው? ሰይጣን እንዲህ ብለን እንድናስብ ይፈልጋል። በመሆኑም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ቀስ በቀስ በልባችን ውስጥ እንዲዘራ ለማድረግ መርዛማ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ይጠቀማል። ይህንን ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዳንዶቹን እስቲ እንመርምር፤ ዲያብሎስን እንዴት ልንቋቋመው እንደምንችልም እንመልከት።
“መሠረታቸው ከዐፈር” ነው
ሰይጣን፣ ሰዎች ለአምላክ ታማኝነታቸውን ጠብቀው መቀጠል የማይችሉ ደካማ ፍጥረታት እንደሆኑ ኢዮብን ሊያጽናኑት ከመጡት ወዳጆቹ አንዱ በሆነው በኤልፋዝ አማካኝነት ገልጿል። ኤልፋዝ፣ ሰዎችን “በጭቃ ቤት የሚኖሩ” ብሎ የጠራቸው ሲሆን ኢዮብን እንዲህ ብሎታል፦ “መሠረታቸው ከዐፈር [ነው]፣ ከብልም ይልቅ በቀላሉ [ይጨፈለቃሉ] . . . በንጋትና በምሽት መካከል ይደቃሉ፤ ሳይታሰብም ለዘላለም ይጠፋሉ።”—ኢዮብ 4:19, 20
በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሌላ ጥቅስ ላይ በቀላሉ ከሚሰበር ‘የሸክላ ዕቃ’ ጋር ተመሳስለናል። (2 ቆሮ. 4:7) በወረስነው ኃጢአትና አለፍጽምና የተነሳ ደካሞች ነን። (ሮም 5:12) በራሳችን ኃይል የሰይጣንን ጥቃት ልንቋቋም አንችልም። ሆኖም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ያለ እርዳታ አልተተውንም። ድክመት ቢኖርብንም በአምላክ ዓይን ብርቅ ወይም ውድ ነን። (ኢሳ. 43:4) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለሚጠይቁት ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣል። (ሉቃስ 11:13) መንፈሱ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ የሚሰጠን ሲሆን ይህም ሰይጣን የሚያመጣብንን ማንኛውንም ዓይነት መከራ ለመቋቋም ያስችለናል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ፊልጵ. 4:13) ‘በእምነት ጸንተን በመቆም’ ዲያብሎስን ከተቃወምነው አምላክ ጽኑና ጠንካሮች እንድንሆን ያደርገናል። (1 ጴጥ. 5:8-10) ስለዚህ ሰይጣን ዲያብሎስን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለንም።
ሰው ‘ክፋትን ይጠጣል’
ኤልፋዝ “ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ፣ ከሴት የተወለደ ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ አነሳ። ከዚያም መልሱን ሲሰጥ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፤ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ እንኳ አይታመንም፤ ሰማያትም በእርሱ ፊት ንጹሓን አይደሉም። ታዲያ፣ ክፋትን እንደ ውሃ [በሚጠጣ] አስጸያፊና ርኵስ ሰውማ እንዴት ይታመን!” (ኢዮብ 15:14-16) ኤልፋዝ፣ በይሖዋ ፊት ማንም ሰው ጻድቅ እንዳልሆነ መናገሩ ነበር። ዲያብሎስም አፍራሽ አስተሳሰብን ይጠቀማል። ቀደም ሲል ስለሠራናቸው ስህተቶች እንድንጨነቅ፣ ከሚገባው በላይ ራሳችንን እንድንኮንን እንዲሁም ይቅርታ ማግኘት እንደማንችል አድርገን እንድናስብ ይፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀውን ነገር አጋንነን እንድንመለከት እንዲሁም ርኅራኄው፣ ይቅር ባይነቱና የሚያደርግልን ድጋፍ ስህተታችንን ለመሸፈን በቂ እንዳልሆነ እንዲሰማን ይፈልጋል።
እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኖናል።’ ፍጽምና ከጎደላቸው የሰው ልጆች መካከል ፍጹም የሆኑትን የይሖዋን መሥፈርቶች ማሟላት የሚችል አንድም ሰው የለም። (ሮም 3:23፤ 7:21-23) ይህ ሲባል ግን በይሖዋ ፊት ምንም ዋጋ የለንም ማለት አይደለም። ኃጢአተኛ መሆናችን በፈጠረው ሁኔታ ተጠቅሞ እኛን ለማሳሳት የሚሞክረው “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ” መሆኑን ይሖዋ ያውቃል። (ራእይ 12:9, 10) አምላክ “ትቢያ መሆናችንን” ከግምት ስለሚያስገባ “ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም።”—መዝ. 103:8, 9, 14
የምንከተለውን መጥፎ አካሄድ በመተው ከልብ ተጸጽተን ንስሐ በመግባት ወደ ይሖዋ ከቀረብን አምላክ “ይቅርታው ብዙ ነው።” (ኢሳ. 55:7፤ መዝ. 51:17) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኃጢአታችን “እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል” ይላል። (ኢሳ. 1:18) እንግዲያው የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ጥረት ከማድረግ ወደኋላ ላለማለት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
ኃጢአተኞች እያለን በአምላክ ፊት ጻድቅ መሆን በራሳችን ልናገኘው የምንችለው ነገር አይደለም። አዳምና ሔዋን እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እኛም ጭምር ፍጹም ሕይወትንና ለዘላለም የመኖር ተስፋን እንድናጣ አድርገውናል። (ሮም 6:23) ይሁንና ይሖዋ ለሰው ዘር ታላቅ ፍቅር ስላለው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደምናምን በተግባር ካሳየን ኃጢአታችንን ይቅር የሚልበት ዝግጅት አድርጓል። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 3:16) ይህ እንዴት ያለ የአምላክ “ጸጋ” ግሩም መግለጫ ነው! (ቲቶ 2:11) ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት እንችላለን! ታዲያ ሰይጣን ከዚህ በተቃራኒ እንድናስብ እንዲያደርገን ለምን እንፈቅዳለን?
“ዐጥንቱንና ሥጋውን ዳስ”
ሰይጣን፣ ኢዮብ ጤንነቱን ካጣ ታማኝነቱን እንደሚያጎድል ተናግሮ ነበር። ዲያብሎስ “ዐጥንቱንና ሥጋውን ዳስ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል” በማለት ይሖዋን ተገዳደረው። (ኢዮብ 2:5) የአምላክ ጠላት፣ ባለብን የጤና እክል የተነሳ ዋጋ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን ሊያደርገን ቢችል በጣም እንደሚደሰት ምንም ጥርጥር የለውም።
ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደ ቀድሞው እሱን ማገልገል በሚያቅተን ጊዜ አይተወንም። አንድ የቅርብ ጓደኛችን ጥቃት ስለተሰነዘረበት ጉዳት ደረሰበት እንበል። በዚህ ጊዜ ጓደኛችን ቀድሞ ያደርግልን የነበረውን ነገር ሊያደርግ አለመቻሉ ለእሱ ያለን አመለካከት ዝቅ እንዲል ያደርጋል? በጭራሽ! ለእሱ ያለን ፍቅር እንደማይቀንስና እሱን መንከባከባችንን እንደምንቀጥል ግልጽ ነው፤ በተለይ ደግሞ ጓደኛችን ጉዳት ያጋጠመው ለእኛ አንድ ነገር ለማድረግ ሲሞክር ከሆነ ለእሱ ያለን አመለካከት አይለወጥም። ታዲያ ከይሖዋስ ከዚህ ያነሰ ነገር መጠበቅ ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” ይላል።—ዕብ. 6:10
ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ “አንዲት ድሃ መበለት” ይናገራሉ፤ ይህች ሴት ለበርካታ ዓመታት እውነተኛውን አምልኮ ስትደግፍ ቆይታ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ፣ ይህች መበለት በቤተ መቅደሱ መባ መሰብሰቢያ ውስጥ “በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” ስትከት ሲመለከት እሷም ሆነች ያደረገችው መዋጮ ብዙም ዋጋ እንደሌላቸው ተሰምቶት ነበር? ከዚህ በተቃራኒ ይህች መበለት እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ በማድረጓ አሞግሷታል።—ሉቃስ 21:1-4
እኛም ንጹሕ አቋማችንን ከጠበቅን በእርጅና ወይም በሕመም ምክንያት አቅማችን ምንም ያህል ቢዳከምም ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት ፈጽሞ እንደማይበላሽ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ በተለያዩ ችግሮች የተነሳ እሱን ለማገልገል አቅም ያነሳቸውን ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ አይተዋቸውም።—መዝ. 71:9, 17, 18
“የመዳንን ራስ ቁር” አጥልቅ
ከሰይጣን ፕሮፓጋንዳ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከጌታና ከታላቅ ብርታቱ ኃይል ማግኘታችሁን ቀጥሉ። የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ።” የዚህ መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ አንዱ ክፍል ‘የመዳን ራስ ቁር’ ነው። (ኤፌ. 6:10, 11, 17) የሰይጣንን ፕሮፓጋንዳ መቋቋም እንድንችል ይህንን የራስ ቁር ማጥለቅ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ፈጽሞ ከራሳችን ላይ ልናወልቀው አይገባም። የአንድ ወታደር የራስ ቁር በጭንቅላቱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት ይከላከልለታል። በተመሳሳይም ‘የመዳን ተስፋችን’ ይኸውም አምላክ አስደናቂ የሆነ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ በገባው ቃል ላይ ያለን የመተማመን ስሜት አእምሯችን በሰይጣን ውሸት እንዳይበከል ይከላከልልናል። (1 ተሰ. 5:8) ትጋት የተሞላበት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ ይህ ተስፋችን ምንጊዜም ብሩሕ ሆኖ እንዲታየንና ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ ይኖርብናል።
ኢዮብ፣ ሰይጣን የሰነዘረበትን ጭካኔና ጥላቻ የተሞላበት ጥቃት በጽናት ተቋቁሟል። ኢዮብ በትንሣኤ ተስፋ ላይ የነበረው እምነት በጣም ጠንካራ ስለነበር የሞት ፍርሃት እንኳ ተስፋ እንዲቆርጥ አላደረገውም። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋን እንዲህ ብሎታል፦ “ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ።” (ኢዮብ 14:15) ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ የተነሳ ቢሞት እንኳ አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ ፍቅር ስላለው ከሞት እንደሚያስነሳቸው እርግጠኛ ነበር።
እኛም በእውነተኛው አምላክ ላይ እንዲህ ዓይነት የመተማመን ስሜት ይኑረን። ሰይጣንና ወኪሎቹ የሚያደርሱብንን ማንኛውንም ነገር ይሖዋ ሊያስተካክለው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ የተናገረውን የሚከተለውን ማረጋገጫ አስታውስ፦ “አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮ. 10:13
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በታማኝነት የምታቀርበውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የመዳንን ራስ ቁር” አጥልቅ፤ እንዲሁም ከራስህ ላይ አታውልቀው