በደስታ የተሞላችሁ ሁኑ
“በደቀመዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።”—ሥራ 13:52
1. (ሀ) ደስታ ምን ዓይነት ፍሬ ነው?(ለ) አምላክ ለየትኛው የደስታ ዝግጅት መከበር ይገባዋል?
ደስታ! ይህ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ጳውሎስ ከጻፈው የመንፈስ ፍሬዎች ዝርዝር ሁለተኛ ሲሆን የአንደኝነት ደረጃ የተሰጠው ለፍቅር ብቻ ነው። (ገላትያ 5:22-25) ግን ይህን ደስታ ያስገኘው ምንድን ነው? ከ1,900 ዓመታት በፊት አንድ የአምላክ መልአክ ለትሁታን እረኞች ያስታወቀው ምሥራች ነው። “እነሆ፣ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና”አላቸው። ከዚያም የመላእክት ሠራዊት ተገለጡና የምሥራች ከተናገረው መልአክ ጋር ሆነው አምላክን እያወደሱ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።”—ሉቃስ 2:10-14
2, 3. (ሀ) አምላክ የበኩር ልጁን የሰው ልጆች አዳኝ እንዲሆን መላክ ተገቢ ሆኖ ያገኘው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ የአምላክን ዓላማ ያገለገለው በምን ሌሎች መንገዶች ነው?
2 ይሖዋ ለሰዎች ያለው በጎ ፈቃድ በጌታ ክርስቶስ አማካኝነት በሰጠው ደህንነት ተገልጦአል። የአምላክ የበኩር ልጅ የእውነተኛ ጥበብ መግለጫ ሲሆን በፍጥረት ጊዜ ስለ አባቱ የሚከተለውን እንደተናገረ ተገልጾአል። “በዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ። ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ። በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ። ደስታየም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበር።”—ምሳሌ 8:30, 31
3 ስለዚህ ይሖዋ ይህን ያህል በሰው ልጆች ይደሰት የነበረውን ልጁን የሰው ልጆች አዳኝ እንዲሆን መላኩ የተገባ ነበር። ታዲያ ይህን ማድረጉ ለአምላክ ክብር የሚያስገኘው እንዴት ነው? ምድርን ጻድቅና ሰላም ወዳድ በሆኑ ሰዎች ለመሙላት ያለውን ታላቅ ዓላማ ለመፈጸም የሚያስችለውን መንገድ ይከፍታል። (ዘፍጥረት 1:28) ከዚህም በላይ ይህ ኢየሱስ የተባለው ልጁ በምድር ላይ በሚኖርበት ጊዜ ፍጹም ሰው ምንም ዓይነት ከባድ ፈተና ቢደርስበት ለይሖዋ ልዕልና ሊገዛ እንደሚችል ያረጋግጣል። ይህም የአባቱ አገዛዝ ትክክል መሆኑን ያስመሰክራል። (ዕብራውያን 4:15፤ 5:8, 9) በተጨማሪም የኢየሱስ የታማኝነትና የንጹሕ አቋም ጠባቂነት አካሄድ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ምሳሌ የሚሆን አኗኗር አስገኝቷል።—1 ጴጥሮስ 2:21
4. የኢየሱስ ጽናት እንዴት ያለ ከፍተኛ ደስታ አስገኘ? ይህስ እንዴት ሊያበረታታን ይገባል?
4 ስለዚህ ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ በዚህ መንገድ በመፈጸም ከመጠን ያለፈ ደስታ አግኝቷል። በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 12:1, 2 ላይ እንደገለጸው ከዚያ የበለጠ ደስታን ይጠብቅ ነበር፦ “የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ (በመከራ እንጨት አዓት) ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” ይህ ደስታ ምንድን ነው? ኢየሱስ የአባቱን ስም በመቀደስና የሰው ልጆችን ከሞት በመቤዠት የሚያገኘው ብቻ ሳይሆን ንጉሥና ሊቀ ካህናት ሆኖ ለታዛዥ የሰው ልጆች በገነቲቱ ምድር ላይ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት በመስጠት የሚያገኘው ደስታ ጭምር ነው።—ማቴዎስ 6:9፤ 20:28፤ ዕብራውያን 7:23-26
5. የኢየሱስ ወንድሞች እነማን ናቸው? የሚካፈሉትስ እንዴት ባለ ልዩ ደስታ ነው?
5 አዎ፣ የአምላክ ልጅ የሰው ልጆችን በማገልገል ሁልጊዜ ታላቅ ደስታ አግኝቶአል። በተጨማሪም “ወንድሞቼ” ብሎ የሚጠራቸውንና ከሞቱ በኋላ ሰማያዊ ትንሣኤ የሚያገኙትን ፍጹም አቋም ጠባቂ የሰው ልጆች በመምረጥ ሥራ ከአባቱ ጋር በማገልገሉ ተደስቶአል። እነዚህም ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ልዩ ወደ ሆነ ደስታ ይገባሉ። ‘ደስተኛና ቅዱስ’ ተብለዋል። “የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ። ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።”—ዕብራውያን 2:11፤ ራእይ 14:1, 4፤ 20:6
6. (ሀ) ንጉሡ ለሌሎች በጎች ምን የሚያስደስት ግብዣ ያቀርብላቸዋል? (ለ) ከእነዚህ በጎቹ መካከል ብዙዎቹ ምን ዓይነት አስደሳች መብት አግኝተዋል?
6 ከዚህም በላይ ንጉሡ የሞገሱ ምሳሌ ወደሆነው ወደ ቀኙ ለይቶ የሚያቆመው “የሌሎች በጎች” እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚከተለውን ግብዣ ይቀበላል፦ “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ፣ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።” (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:34) እንዴት ያለ ደስ የሚያሰኝ መብት ነው! ከእነዚህ የመንግሥቱን ምድራዊ ግዛት ከሚወርሱት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ አሁንም እንኳ ከቅቡዓን ጋር ጎን ለጎን በመሰለፍ የኃላፊነት ቦታዎችን በመቀበል ላይ ናቸው። ይህም ይሖዋ በተነበየው መሠረት የተፈጸመ ነው። “መጻተኞችም ቆመው በጎቻቸውን ያሰማራሉ፣ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላቸዋል። እናንተ ግን (የይሖዋ) ካህናት ትባላላችሁ። ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል።” እነዚህ ሁሉ ከአምላክ ነቢይ ጋር ሆነው “የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፣ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና [በይሖዋ አዓት] እጅግ ደስ ይለኛል” ይላሉ።—ኢሳይያስ 61:5, 6, 10
7. ይህ ከ1914 ወዲህ ያለው ቀን በጣም ልዩ የሆነው ለምንድንነው?
7 አሁን የምንኖረው በጣም ልዩ በሆነ ዘመን ነው። ከ1914 ጀምሮ ክርስቶስ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖአል። የሚገዛበት ቀን ሆኖአል። ይህም ቀን በመዝሙር 118:24, 25 ላይ ተገልጾአል፦ “[ይሖዋ (አዓት)] የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፣ በእርስዋም ደስ ይበለን። አቤቱ፣ እባክህ፣ አሁን አድን፤ አቤቱ፣ እባክህ፣ አሁን አቅና።” ይህ ቀን ይሖዋ በባቢሎናዊው ሃይማኖት ላይ ጥፋት ሲያመጣና የክርስቶስ ሙሽራ ክፍል አባሎች የሆኑትን 144,000 ወንድማማቾች ከሰማያዊ ንጉሣቸው ጋር ሲተባበሩ ይደመደማል። የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ በዚህ ነገር ‘ደስ ይላቸዋል፣ ሐሴትም ያደርጋሉ።’ መሲሐዊ ንጉሣቸው ታማኝ የሆነውን ሕዝብ አድኖ እርሱ ወደሚገዛበት አዲስና ጻድቅ ወደሆነ ዓለም ለማስገባት ብሎ በአርማጌዶን ላይ ሲዋጋ ደስ ይላቸዋል። (ራእይ 19:1-7, 11-16) ታዲያ ሕዝቦቹ ይህን አስደሳች ተስፋ በሚያውጁበት ጊዜ ይሖዋ የተሳካ ውጤት ይሰጣቸዋልን? ቀጥሎ የቀረበው ሪፖርት ይህን ይገልጽልናል።
ዓለም አቀፍ መስፋፋት
8. (ሀ) በዚህ መጽሔት በገጽ 18 - 21 ባለው ሠንጠረዥ ላይ የመንፈስ ቅዱስ ደስታ የተንጸባረቀው እንዴት ነው? (ለ) ግንባር ቀደም የሆኑ አንዳንድ የሪፖርቱ ክፍሎች ምንድን ናቸው?
8 በዘመናችን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች “በመንፈስ ቅዱስ በተስፋ” ተሞልተዋል። (ሮሜ 15:13) ይህንንም በዚህ መጽሔት በገጽ 18 እስከ 21 ላይ በሚገኘው የ1990 የመንግሥት አገልግሎት የዓለም አቀፍ ሠንጠረዥ መረዳት ይቻላል። በመስኩ ሥራ የተሰማሩ 4,017,213 ትጉህ አስፋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር በመገኘቱ በጣም ተደስተናል። ባለፉት አሥር ዓመታት የበጎቹ መሰብሰብ ሥራ በ22 አገሮች ተስፋፍቶ 77 በመቶ ጭማሪ አግኝተናል ማለት ነው። የተጠመቁት ሰዎች ቁጥር ከአሥራ አምስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ 301,518 ደርሷል። በብዙ ትላልቅ ስብሰባዎች በተለይም በምሥራቅ አውሮፓ የይሖዋ ምሥክሮች በተገኙባቸው ስብሰባዎች በጣም ከፍተኛ የሆነ የተጠማቂዎች ቁጥር ተገኝቷል። ከእነዚህም መካከል ብዙ ወጣቶች ስለነበሩ ሃይማኖት ከአሮጌው ትውልድ ጋር ይሞታል የሚለውን ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ ውሸት አድርገውታል።
9. (ሀ) ልጆችን በሕፃንነት ማሠልጠን ምን አስደሳች ውጤት በማስገኘት ላይ ነው? (ለ) ይህንንስ የሚያሳይ የትኛው በአካባቢያችሁ የሚገኝ ወይም ሌላ ተሞክሮ አለ?
9 ብዙ ወጣቶች “ጻድቃን ሆይ፣ [በይሖዋ(አዓት)] ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፣ ልባችሁም የቀና ሁላችሁ እልል በሉ” የሚለውን የመዝሙር 32:11 ጥሪ በመቀበል ላይ ናቸው። ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ከታናሽነታቸው ጀምረው እንዲያሰለጥኑ የተሰጣቸውን ምክር የሠሩበት ይመስላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ለሕፃናት በተዘጋጁት መጻሕፍትና ካሴቶች በጥሩ ሁኔታ ተጠቅመዋል። እነዚህ ወጣት ልጆች ገና ትምህርት ቤት ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣሉ። ለምሳሌ አንዲት የስምንት ዓመት ጃፓናዊት ልጅ እንዲህ ብላለች፦ “ከበጋው የእረፍት ጊዜ በኋላ ወደ አስተማሪዬ ሄድኩና ‘በእረፍቱ ጊዜ የአባትሽን መቃብር ጎብኝተሽ ነበርን?’ ብዬ ጠየቅኋት። ‘አዎ፣ አባቴ በጣም ደግ ሰው ስለነበር ሁልጊዜ በየዓመቱ ወደ አባቴ መቃብር እሄዳለሁ’ ብላ መለሰችልኝ። ‘መጽሐፍ ቅዱስን ብታጠኚና የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ብትከተይ ግን የምትወጂውን አባትሽን በምድራዊት ገነት ውስጥ ልታይው ትችያለሽ’ አልኳት። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፌ ሰጠኋት። አሁን አስተማሪያችን በየሣምንቱ በምሳ ሰዓት ከዚህ መጽሐፍ አንድ ምዕራፍ ለክፍሉ ልጆች በሙሉ ታነባለች።”
10. የወጣቶች ጥያቄ የተባለው መጽሐፍ ምን ጥሩ ውጤት አስገኝቷል? አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ።
10 ከፍ ያሉ ወጣት ልጆችም ወጣቶች የሚጠይቁአቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ የሆኑ መልሶች በተባለው መጽሐፍ በግል ጥናታቸውም ሆነ ለሌሎች ወጣቶች በመመስከር በጥሩ ሁኔታ ተጠቅመዋል። ወላጆችም ጭምር ይህን መጽሐፍ ይወዱታል። በስዊዘርላንድ የምትኖር እህት ረዳት አቅኚ ሆነችና የልጅዋን የትምህርት ቤት ጓደኞች ወላጆች ለመጠየቅ ወሰነች። በዚህ መንገድ ከብዙ ወላጆች ጋር የምትወያይበት አጋጣሚ አገኘች። 20 መጻሕፍትና (በአብዛኛው የወጣቶች ጥያቄ የተባለውን መጽሐፍ) 27 መጽሔቶች አበረከተችላቸው። በትሪንዳድ የምትኖር ተማሪ ለትምህርት ቤት መምህርዋ ይህን መጽሐፍ ካበረከተች በኋላ እናትዋ በዚሁ አጋጣሚ ተጠቅማ 36 መምህራን ባሉበት በዚህ ትምህርት ቤት 25 መጻሕፍት አበረከተች። በሚቀጥለው ወር ደግሞ በግል በምታውቃቸው ወላጆች ላይ ልዩ ትኩረት አደረገችና 92 መጻሕፍት ለማበርከትና አዳዲስ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለመጀመር ቻለች። በኮሪያ አንድ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር በወጣቶች ጥያቄ መጽሐፍ እየተጠቀመ “ማርኬን እንዴት ለማሻሻል እችላለሁ?” እና “ከአስተማሪዎቼ ጋር እንዴት ልግባባ እችላለሁ?” እንደሚሉት ባሉ አርዕስት ላይ አጭር ንግግር ካደረገ በኋላ መጽሐፉን አበረከተ። ተማሪዎቹ 39 የሚያክሉ መጻሕፍት ከወሰዱ በኋላ አንዳንድ ወላጆች ማጉረምረም ጀመሩ። ይሁን እንጂ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር መጽሐፉን ከመረመረ በኋላ ‘በጣም ግሩም መጽሐፍ ነው’ ብሎ እርሱም ለሴት ልጁ አንድ መጽሐፍ አዘዘ።
ከሁሉም የበለጠው ትምህርት
11, 12. የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ጽሑፎች በጣም ጥሩ ትምህርት የሚገኝባቸው መሆኑን የሚገልጹ አንዳንድ ማስረጃዎች ጥቀስ።
11 የመጽሔቶቻችን ትምህርት ሰጪነት በብዙ ሰዎች ተደንቋል። ለምሳሌ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ትምህርት ቤት የሐምሌ 22, 1990 ንቁ! መጽሔት (የክራክ ሱሰኝነትን ማጋለጥ የሚለውን) በክፍል ለመጠቀም አስቦ 1,200 ቅጂዎችን አዘዘ። ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች በትምህርት ቤት የሚያሳዩት ምሳሌያዊ ምግባር ጥሩ ውጤት በማስገኘት ላይ ነው። በታይላንድ አገር በጣም ጫጫታ በሚበዛበት ክፍል ውስጥ አስተማሪዋ የ11 ዓመት ዕድሜ ያለውን ራካን ጠርታ ከተማሪዎቹ ፊት አቆመችና ስለጠባዩ ካመሰገነችው በኋላ “ሁላችሁም እንደርሱ ብትሆኑ ምን አለበት? እርሱ ትምህርቱን በትጋት ከመከታተሉም በላይ ጥሩ ጠባይ አለው” አለችና ቀጥላ “ሁላችሁም ጠባያችሁን እንድታሻሽሉ ከተፈለገ እንደራካ የይሖዋ ምሥክሮች መሆን ይኖርባችሁ ይሆናል” አለቻቸው።—ከምሳሌ 1:8፤ 23:22, 23 ጋር አወዳድር።
12 በዶመኒካን ሪፑብሊክ የምትኖር አንዲት ወጣት እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ገና አራት ዓመት ሲሆነኝ ማንበብና መጻፍ ከተማርኩበት የሃይማኖት ትምህርት ቤት ልመረቅ ተዘጋጅቼ ነበር። ለድንግልዋም አስተማሪዬ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚለውን መጽሐፍ የሚከተለውን መልእክት ተጽፎበት ሥጦታ እንዲሆናት ሰጠኋት። ‘ማንበብና መጻፍ ስላስተማርሽኝ በጣም አመሰግንሻለሁ። እምነቴን ለማወቅና ምድር ገነት ስትሆን በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ያለኝን ተስፋ ልትካፈይኝ ብትችይ በጣም ደስ ይለኝ ነበር።’ ይህን ስላደረግሁ ከትምህርት ቤቱ ተባረርኩ። ከስምንት ዓመት በኋላ ይህችን አስተማሪ አገኘኋት። ቄሱ በጣም ቢቃወማትም መጽሐፉን እንዳነበበች ነገረችኝ። ከዚያም ወደ ዋናው ከተማ ተዛወረችና ከአንዲት የይሖዋ ምስክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ቻለች። “ንጹሕ ልሳን” በተባለው የወረዳ ስብሰባ ላይ ከእኔ ጋር ለመጠመቅ ከጎኔ ቆማ ነበር። በትንቢት እንደተነገረው ‘ከሕፃናት አንደበት እንኳን ጥበብ ይወጣል።’—ማቴዎስ 21:16፤ መዝሙር 8:1, 2
13. አንዳንድ ወጣቶች የሰለሞንን ምክር እንዴት ተቀብለውታል? ይህስ በዓለም አቀፉ ሪፖርት የተገለጸው እንዴት ነው?
13 ሰለሞን የሚከተለውን የሚያበረታታ ምክር ሰጥቶአል፦ “አንተ ጐበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፣ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ።” (መክብብ 11:9) በአሁኑ ጊዜ ይህን የሚያክሉ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ይህን ምክር እየተከተሉ ሙሉ ሕይወታቸውን ይሖዋን በሙሉ ጊዜያቸው ለማገልገል በወጣትነት ዕድሜአቸው ሲጠቀሙና ከትምህርት ቤት እንደተመረቁ ይህን ከማንኛውም ሥራ የበለጠ ሥራ ሲጀምሩ ስናይ በጣም ደስ ይለናል። የአቅኚዎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ ሄዷል። ባለፈው ዓመት 821,108 አቅኚዎች ሪፖርት አድርገዋል። በቤቴል ካገለገሉት 11,092 ወንድሞችና እህቶች ጋር ሲደመር ከጠቅላላዎቹ አስፋፊዎች 21 በመቶ የሚሆኑት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነበሩ ማለት ነው።
14. እህቶቻችን ምን ዓይነት ድርሻ በማበርከት ላይ ናቸው? እንዴትስ ያለ ምስጋና ሊሰጣቸው ይገባል?
14 እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ባሉት ብዙ አገሮች 75 በመቶ የሚያክሉት አቅኚዎች እህቶች ናቸው። ይህም “[ይሖዋ (አዓት)] ራሱ ቃሉን ሰጠ፤ ምሥራቹንም የሚናገሩ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት ናቸው” የሚለውን የመዝሙር 68:11 ቃል ያጠነክረዋል። (የ1980 እትም) እህቶቻችን አብዛኛውን የመስክ ሥራ የሚያከናውኑ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የሚያሳዩት ጥሩ የማስተማር ችሎታ ብዙ ሰዎችን ወደ እውነት ለማምጣት ችሎአል። ብዙ የጉባኤ ኃላፊነት ያለባቸው ወንድሞች በታማኝነት የሚደግፉአቸው ያገቡ እህቶችም በጣም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።—ምሳሌ 31:10-12፤ ኤፌሶን 5:21-25, 33
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ተስፋፍቶአል
15. (ሀ) በዓለም አቀፉ ሪፖርት ላይ ከተዘረዘሩት አገሮች አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሥራ ብልጫ ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ምን ያህል ፍሬያማ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳይ ምን ተሞክሮ ልትናገር ትችላለህ?
15 መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ በጣም ተስፋፍቶአል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በየወሩ በአማካይ በ3,624,091 ቦታዎች ተመርተዋል። ከደቡባዊ ክፍለ ዓለም የተገኘው ሪፖርት እንደሚያሳየው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሰዎችን ጠባይ ሊለውጥ ይችላል። በጥር ወር በ1987 አንድ ሰው በአውስትራሊያ አገር በዘረፋና በአታላይነት ወንጀል ተከስሶ የ25 ወር እስራት ከጨረሰ በኋላ ወደ አገሩ ወደ ኒውዚላንድ ተባረረ። የጎጂ ዕጾች ሱሰኛ ከመሆኑም በላይ ለ17 ዓመታት ዕጾችን ሲሸጥ ቆይቶአል። በሚቀጥለው ዓመት ሚስቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረች። እውቀትዋ እየጨመረ በሄደ መጠን ጠባይዋ መሻሻል እንደጀመረ አስተዋለ። ጥሩ ሚስትና እናት ሆነች። በሰኔ ወር 1989 ሚስቱ ገፋፋችውና በክልል ስብሰባ ላይ ተገኘ። ከዚያ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። በቁመናውና በአኗኗሩ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መታየት ጀመረ። ሰባቱም የቤተሰቡ አባሎች በስብሰባዎች መገኘት ጀመሩ። በኤፌሶን 4:17-24 ላይ የሚገኘውን አስደናቂ የጳውሎስ ምክር በመከተሉ በጥር ወር 1990 ተጠመቀ።
16. (ሀ) የ1990 የጌታ እራት ሪፖርቶች የሚያስደስቱን እንዴት ነው? (ለ) ስለ የትኛው አጣዳፊ ሁኔታ መገንዘብ ይኖርብናል? እነርሱንስ ለመርዳት ምን ማድረግ ይገባናል?
16 ከዓመቱ ሪፖርት በግንባር ቀደምትነት የሚታየው ሚያዝያ 10, 1990 ማክሰኞ ዕለት በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ 9,950,058 ሰዎች መገኘታቸው ነው። ከ212 አገሮች ውስጥ ከ70 የሚበልጡት ከከፍተኛ የአስፋፊ ቁጥር በሦስት እጥፍ የሚበልጡ ሰዎች በጌታ ራት እንደተገኙ ሪፖርት አድርገዋል። ለምሳሌ በሰባት የአፍሪካ አገሮች የመንግሥት ዕገዳ ቢኖርም 62,712 አስፋፊዎች 204,356 ሰዎች በጌታ ራት እንደተገኙ ሪፖርት አድርገዋል። በጦርነት በፈራረሰችው በላይቤሪያ የሚኖሩ 1,914 አስፋፊዎች 7,811 የጌታ ራት ተሰብሳቢዎች ሪፖርት አድርገዋል። 6,427 ከፍተኛ የአስፋፊ ቁጥር ያላት ሐይቲ 36,551 ተሰብሳቢዎች ሪፖርት አድርጋለች። በተበታተኑት የማይክሮኔዥያ ደሴቶች የሚኖሩት 886 አስፋፊዎች 3,958 የጌታ ራት ተሰብሳቢዎች ነበሩአቸው። የስሪላንካ 1,298 አስፋፊዎች 4,521 ተሰብሳቢዎች ሪፖርት አድርገዋል። 73,729 አስፋፊዎች ባሉባት በዛምቢያ 326,991 ሰዎች በጌታ ራት ተገኝተዋል። ከዛምቢያ ሕዝቦች ከ25 ሰው አንዱ በጌታ ራት ላይ ተገኝቶ ነበር ማለት ነው። ዓለም አቀፉ ሪፖርት እንደሚያሳየው ገና ወደ በጎቹ በረት መግባት የሚኖርባቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ቅንነት ብቻ አይበቃም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሥራችንን መጠንና ጥራት ልንጨምርና በጌታ ራት ከተገኙት ሰዎች ብዙዎቹ እምነታቸውን እንዲያጠነክሩ ለመርዳት እንችላለንን? ይሖዋን የሚያወድሱ ባልንጀሮቻችን እንዲሆኑ እንፈልጋለን። ይህም ሕይወት ያስገኝላቸዋል።—መዝሙር 148:12, 13፤ ዮሐንስ 17:3፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
የደስታ ሙላት
17. ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሣኔ የሚያጠነክርልን የትኛው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሳሌ ነውን?
17 ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ደስታችንን ይዘን ለመቆየት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የእስጢፋኖስን የመሰለ ከባድ ፈተና አይደርስብን ይሆናል። ቢሆንም የእርሱ ምሳሌ ሊያጽናናን ይችላል። በተከሰሰበት ጊዜ እንኳን በፊቱ ላይ ይታይበት የነበረው ደስታ አልጠፋበትም። ጠላቶቹ “እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን” አይተውት ነበር። በመከራው ጊዜ ሁሉ አምላክ ከጎኑ ቆሞ ነበር። በሰማዕትነት እስከሞተበት ሰዓት ድረስ ‘በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ’ በድፍረት መስክሮአል። ጳውሎስና በርናባስም ወደ አሕዛብ ዞር ብለው መስበክ በጀመሩ ጊዜ ‘አሕዛብም ሰምተው ደስ ብሎአቸውና የእግዚአብሔርን ቃል አክብረው’ ነበር። ግን አሁንም ስደት ተነሳ። ይሁን እንጂ ያመኑትን ሰዎች አልበገራቸውም። “በደቀመዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።” (ሥራ 6:15፤ 7:55፤ 13:48-52) ጠላቶቻችን ምንም ነገር ቢያደርጉብን፣ በየዕለቱ ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን የመንፈስ ቅዱስ ደስታችን በምንም ዓይነት እንዲቀንስ መፍቀድ አይገባንም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይመክረናል፦ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ።”—ሮሜ 12:12
18. (ሀ) “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም “ምንድን ነች? የአምላክስ ሕዝቦች ከእርስዋ ጋር መደሰት የሚኖርባቸው ለምንድንነው? (ለ) ‘አዲሱ ሰማይና አዲሲቱ ምድር’ የሰው ልጆችን የሚባርኩት እንዴት ነው?
18 ይህ ተስፋ ምን ያህል አስደናቂ ተስፋ ነው! ይሖዋ ለሕዝቦቹ በሙሉ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፣ የቀደሙትም አይታሰቡም። ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ፣ ለዘላለም ሐሴት አድርጉ።” ጌታ ክርስቶስ ‘ከአዲሲቱ ኢየሩሳሌምና’ (አሁን የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት ዋና ከተማ የሆነችው “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም“) በምድር ላይ ከሚኖረው የአዲሲቱ ዓለም ማህበር ጋር በመሆን ለሰው ልጆች ዳርቻ የሌለው ደስታ ያመጣል። (ገላትያ 4:26) የሙታን ትንሣኤ፣ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምናና የዘላለም ሕይወት ከፍ መደረጋቸው፣ ገነት በምትሆነው ምድር የተሟላና ጠቃሚ የዘላለም ሕይወት ማግኘታቸው በጣም ታላቅና የሚያስደስት ተስፋ ነው። ይሖዋ በኢየሩሳሌም እንደሚደሰትና በሕዝቦቹም ሐሴት እንደሚያደርግ ሁሉ የአምላክ ሕዝቦችም “ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሴትን አድርጉ፣ ስለ እርስዋም ደስ ይበላችሁ።” (ኢሳይያስ 65:17-19፤ 66:10፤ ራእይ 14:1፤ 20:12, 13፤ 21:2-4) “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፣ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር እየተከተልን በደስታና በመንፈስ ቅዱስ እንሞላ።—ፊልጵስዩስ 4:4
ደስታችንን አጠቃልለን ለመግለጽ
◻ ኢየሱስ ምን በደስታ የመጽናት ምሳሌ ትቶልናል?
◻ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሁለት ቡድኖች ደስ የሚሰኙባቸው ምን ምክንያቶች አሉአቸው?
◻ ዛሬ ወጣቶችም ሆኑ ሽማግሌዎች በእውነት ሐሴት የሚያደርጉት እንዴት ነው?
◻ የ1990ን ሪፖርት ስንመረምር “አቤቱ ይሖዋ የተሳካ ውጤት ስጠን” ብለን ለምናቀርበው ጸሎት ምን ምላሽ በመስጠት ላይ መሆኑን እንገነዘባለን?
◻ የደስታ ሙላት የሚገኘው መቼና እንዴት ነው?
[ከገጽ 18-21 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]
የይሖዋ ምሥክሮች የ1990 የአገልግሎት ዓመት የጠቅላላው ዓለም ሪፖርት
(መጽሔቱን ተመልከት)
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ መልአክ የጌታ የክርስቶስን መወለድ ‘ታላቅ ደስታ የሆነ የምሥራች’ እንደሆነ አውጆ ነበር