አምላክ በእርግጥ ያውቅሃልን?
“ አቤቱ [ይሖዋ አዓት] ፣ . . . መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ። ” — መዝሙር 139:1, 3
1. የሚያጋጥሙንን ጭንቀቶች፣ ችግሮችና ውጥረቶች ሌሎች ‘አይረዱልንም’ የሚለው ስሜት ምን ያህል የተስፋፋ ነው?
የሚያጋጥምህን ጭንቀት፣ ውጥረትና ችግር በእርግጥ የሚረዳልህ ሰው አለን? በዓለም ዙሪያ ስለሚደርስባቸው ነገር የሚያስብላቸው ቤተሰብ ወይም ዘመድ የሌላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችና አረጋውያን አሉ። በቤተሰብ ውስጥ እንኳ ብዙ ሚስቶች እንዲሁም ባሎች የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ የትዳር ጓደኛቸው በእርግጥ የሚረዳላቸው መስሎ አይሰማቸውም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ተስፋ በመቁረጥ “አንተ እኮ ችግሬን አትረዳልኝም!” በማለት በምሬት ይናገራሉ። ሁኔታቸውን የሚረዳላቸው ማንም ሰው እንደሌለ የሚሰማቸው ወጣቶችም ጥቂት አይደሉም። ይሁን እንጂ ሌሎች ችግራቸውን እንዲረዱላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይጠብቁ ከነበሩት ሰዎች መካከል ከጊዜ በኋላ ሕይወታቸው ትልቅ ትርጉም ያለው የሆነላቸው አሉ። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
2. የይሖዋ አምላኪዎች የሚያረካ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ምንድን ነው?
2 ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ችግራቸውን ተረዱላቸውም አልተረዱላቸው እየደረሰባቸው ያለውን ነገር አምላክ እንደሚረዳላቸው ትምክህት ስላላቸው ነው። የእርሱ አገልጋዮች እንደመሆናቸው መጠን ችግሮቻቸውን ሁሉ ብቻቸውን ለመወጣት አይገደዱም። (መዝሙር 46:1) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃልና አስተዋይ የሆኑ ሽማግሌዎች የሚሰጧቸው ሐሳብ ከግል ችግሮቻቸው ባሻገር ለመመልከት ስለሚያስችላቸው ነው። የታማኝነት አገልግሎታቸው በአምላክ ፊት ክቡር እንደሆነና ተስፋቸውን በአምላክና እሱ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ባደረጋቸው ዝግጅቶች ላይ የሚያደረጉ ሰዎች ወደፊት አስተማማኝ ጊዜ እንደሚጠብቃቸው እንዲገነዘቡ ቅዱሳን ጽሑፎች ይረዷቸዋል። — ምሳሌ 27:11፤ 2 ቆሮንቶስ 4:17, 18
3, 4. (ሀ) ‘ይሖዋ አምላክ’ እንደሆነና እሱ ‘እንደሠራን’ መገንዘባችን በእሱ አገልግሎት ደስታ እንድናገኝ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ ሙሉ በሙሉ ትምክህት የሚኖረን ለምንድን ነው?
3 “እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሉት፤ የደስታ መዝሙር እየዘመራችሁ ወደ እርሱ ፊት ቅረቡ” የሚለውን የመዝሙር 100:2ን (የ1980 የአማርኛ ትርጉም ) ሐሳብ ታውቀው ይሆናል። በዚህ መንገድ አምልኳቸውን ለይሖዋ የሚያቀርቡት ስንቶቹ ናቸው? እንዲህ እንድናደርግ የሚያደርጉን ጥሩ ምክንያቶች በቁጥር 3 ላይ ተገልጸዋል። ጥቅሱ እንዲህ በማለት ያሳስበናል:- “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን።” በዕብራይስጡ ጽሑፍ ውስጥ ይህ ጥቅስ ይሖዋ ኤሎሂም ተብሎ ተጠርቷል። በዚህ መንገድ ይሖዋ ያለው ከፍተኛ ግርማ ሞገስ፣ ክብርና ታላቅነት ተገልጿል። እውነተኛው አምላክ እሱ ብቻ ነው። (ዘዳግም 4:39፤ 7:9፤ ዮሐንስ 17:3) አገልጋዮቹ አምላክነቱን ያውቃሉ። ይህንንም ሐቅ የሚያውቁት በትምህርት እንደተገኘ ግንዛቤ አድርገው ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ ጭምር፣ ይኸውም በሚያሳዩት ታዛዥነት፣ በአምላክ ላይ እምነት ጥለው በመመላለስና ለእርሱ ያደሩ ሆነው በመኖር አምላክነቱን እንደሚያውቁ ያሳያሉ። — 1 ዜና መዋዕል 28:9፤ ሮሜ 1:20
4 ይሖዋ ሕያው አምላክ ስለሆነ ልባችንን እንኳ ሊያይ ይችላል፤ ከእሱ ዓይን የተሰወረ ምንም ነገር የለም። በሕይወታችን ውስጥ ምን ነገሮች እየተካሄዱ እንዳሉ ሙሉ በሙሉ ያውቃል። ላጋጠሙን ችግሮች መንስዔዎቹ ምን እንደሆኑና ከእነዚህም ችግሮች የተነሳ የሚደርስብንን የአእምሮና የስሜት መረበሽ ይረዳል። ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን እኛ ራሳችንን ከምናውቀው የበለጠ ያውቀናል። በተጨማሪም ችግሮቻችንን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳንና እንዴት ከችግሮቻችን ዘላቂ እፎይታ እንደሚሰጠን ያውቃል። በሙሉ ልባችን በሱ ከታመንን አንድ እረኛ የበግ ጠቦት በክንዱ ታቅፎ እንደሚንከባከብ እርሱም በፍቅር ይረዳናል። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ኢሳይያስ 40:10, 11) መዝሙር 139ን ማጥናት ይህን ትምክህት ለማጠንከር ብዙ አስተዋጽዖ ሊያደርግ ይችላል።
መንገዳችንን ሁሉ የሚያይ
5. ይሖዋ ‘መረመረን’ ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ ተፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
5 መዝሙራዊው ዳዊት ጥልቅ በሆነ አድናቆት “አቤቱ [ይሖዋ አዓት]፣ መረመርኸኝ፣ አወቅኸኝም” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 139:1) ዳዊት ይሖዋ እሱን የሚያውቀው ላይ ላዩን እንደነገሩ እንዳልሆነ ትምክኽት ነበረው። አምላክ ዳዊትን የሚያየው ሰዎች በአካላዊ ቁመናው ማለትም በንግግር ችሎታው ወይም ባለው በገና የመጫወት ችሎታ እንደሚመለከቱት አይደለም። (1 ሳሙኤል 16:7, 18) ይሖዋ የዳዊትን ውስጣዊ ማንነት ‘መርምሮ’ ነበር። ይህንንም ያደረገው ለመንፈሳዊ ደህንነቱ ባለው ፍቅራዊ አሳቢነት ነው። ራሳቸውን ለይሖዋ ከወሰኑት አገልጋዮች መካከል አንዱ ከሆንክ ይሖዋ ዳዊትን እንዳወቀው አንተንም ያውቅሃል። ይህስ በውስጥህ የምስጋናና ከአድናቆት የመነጨ የፍርሃት ስሜት አይቀሰቅስብህምን?
6. መዝሙር 139:2, 3 ይሖዋ የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር፣ ሐሳባችንን ሁሉ እንኳ እንደሚያውቅ የሚያሳየው እንዴት ነው?
6 የዳዊት እንቅስቃሴዎች በሙሉ በይሖዋ ፊት የተጋለጡ ነበሩ። ዳዊትም ይህንን ያውቅ ነበር። መዝሙራዊው “አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ፤ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 139:2, 3) ይሖዋ ከምድር በጣም ርቆ በሰማይ ውስጥ የሚኖር መሆኑ ዳዊት ምን እያደረገ ወይም ምን እያሰበ እንዳለ ከማወቅ አላገደውም ነበር። ዳዊት በቀንም ሆነ በማታ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ምንነት ለማወቅ ሲል ይሖዋ የዳዊትን እንቅስቃሴዎች ሁሉ በጥንቃቄ ‘መርምሯል።’
7. (ሀ) በዳዊት ሕይወት ላይ ከደረሱት ነገሮች በመነሳት በእኛ ሕይወት ላይ ስለሚደርሱ አምላክ ስለሚያውቃቸው አንዳንድ ነገሮች ሐሳብ ስጥ። (ለ) ይህንን ማወቃችን እንዴት ሊነካን ይገባል?
7 ለአምላክ ያለው ፍቅርና እሱ በሚሰጠው ኃይል ላይ ያለው ትምክኽት ወጣት የነበረው ዳዊት ግዙፉን ፍልስጤማዊ ጎልያድን ለመጋጠም ፈቃደኛ እንዲሆን አድርጎታል። ይሖዋም ይህንን ያውቅ ነበር። (1 ሳሙኤል 17:32–37, 45–47) በኋላም ሰዎች ያሳዩት የመረረ ጠላትነት የዳዊትን ልብ በጣም እንዲያዝን ባደረገውና የሚደርስበት ተጽዕኖ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሌሊት ባለቀሰበት ጊዜ ይሖዋ ያቀረበውን ምልጃ እንደሰማለት በማወቁ ዳዊት ተጽናንቶ ነበር። (መዝሙር 6:6, 9፤ 55:2–5, 22) በተመሳሳይም ዳዊት ልቡ በምስጋና በሚሞላበት ጊዜ እንቅልፉን አጥቶ ሲያሰላስል ያድር ነበር። ይህንንም ይሖዋ በደንብ ያውቅ ነበር። (መዝሙር 63:6፤ ከፊልጵስዩስ 4:8, 9 ጋር አወዳድር።) ዳዊት አንድ ቀን ምሽት የአንድ ጎረቤቱ ሚስት ገላዋን ስትታጠብ ተመለከተ። ይሖዋ ይህንንም ያውቅ ነበር። እንዲሁም ዳዊት የኃጢአት ምኞቶች አምላክን ለአጭር ጊዜም እንኳ ቢሆን ከአእምሮው ውስጥ እንዲያስወጡት በመፍቀዱ ምን እንደተከሰተም ተመልክቷል። (2 ሳሙኤል 11:2–4) በኋላም ዳዊት የሠራው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደነበረ ለማስታወቅ ነቢዩ ናታን በተላከበትም ጊዜ ይሖዋ ከዳዊት አፍ የሚወጡትን ቃላት ከመስማቱም በተጨማሪ ቃላቶቹን የሚያፈልቀውን ንስሐ የገባ ልብም ተመልክቷል። (2 ሳሙኤል 12:1–14፤ መዝሙር 51:1, 17) ታዲያ ይህ ሁሉ ወዴት እንደምንሄድ፣ ምን እንደምናደርግና በልባችን ውስጥ ምን እንዳለ በጥንቃቄ እንድናስብበት ሊያደርገን አይገባምን?
8. (ሀ) ‘የምንናገራቸው ቃላት’ በአምላክ ዘንድ ባለን አቋም ላይ ለውጥ የሚያመጡት እንዴት ነው? (ለ) በምላስ አጠቃቀም ረገድ የሚኖረውን ድካም እንዴት ታግሎ ማሸነፍ ይቻላል? (ማቴዎስ 15:18፤ ሉቃስ 6:45)
8 አምላክ የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር ስለሚያውቅ እንደ ምላስ የመሰለውን አነስተኛ የሰውነት ክፍል እንኳ እንዴት እንደምንጠቀምበት ቢያውቅ ሊያስገርመን አይገባም። ንጉሥ ዳዊት ይህን ተገንዝቦ ነበር። እሱም “ገና ከመናገሬ በፊት ምን ለማለት እንደማስብ ታውቃለህ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 139:4 የ1980 ትርጉም) በይሖዋ ድንኳን ውስጥ በእንግድነት እንዲያርፉ የሚፈቀድላቸው ሌሎችን የማያሙና ምላሳቸውን ጓደኛቸውን የሚጎዳ አሉባልታ ለማሰራጨት የማይጠቀሙበት ሰዎች መሆናቸውን ዳዊት በሚገባ ያውቅ ነበር። ይሖዋ የሚወዳቸው ሰዎች በልባቸው እንኳ እውነትን የሚናገሩ ናቸው። (መዝሙር 15:1–3፤ ምሳሌ 6:16–19) ማንኛችንም ብንሆን ምላሳችንን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አንችልም። ይሁን እንጂ ዳዊት የነበረበትን ሁኔታ ለማሻሻል ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል አድርጎ አልደመደመም። ለይሖዋ የምስጋና መዝሙሮችን በመግጠምና በመዘመር ብዙ ጊዜ ያሳልፍ ነበር። በተጨማሪም እርዳታ እንደሚያስፈልገው በግልጽ ተናግሯል፤ ስለ ጉዳዩም ለአምላክ ጸልዮአል። (መዝሙር 19:12–14) የእኛስ የምላስ አጠቃቀም ጸሎት የተሞላበት ትኩረት ሊደረግለት የሚያስፈልገው ነውን?
9. (ሀ) በመዝሙር 139:5 ላይ ያለው መግለጫ አምላክ ሁኔታችንን የሚያውቅ መሆኑን በተመለከተ ምን የሚጠቁመው ነገር አለ? (ለ) ይህስ ምን ትምክህት እንዲኖረን ያደርጋል?
9 ይሖዋ እኛን ወይም ሁኔታችንን የሚመለከተው ከተወሰነ አቅጣጫ ብቻ አይደለም። ከሁሉም አቅጣጫ ሙሉ ግንዛቤ ማግኘት ይችላል። ዳዊት አንድን የተከበበች ከተማ እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም “ከፊትም ከኋላም ከበኸኛል ” ሲል ጽፏል። አምላክ ዳዊትን የከበበው ወራሪ ጠላት በመሆን አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ንቁ ጠባቂው ነበር። ዳዊት በማከል “እጅህንም በላዬ አደረግህ ” ብሎ በመናገር አምላክ ቁጥጥርና ጥበቃ እሱን ለሚወዱት ሰዎች ዘላቂ ጥቅም የሚያመጣላቸው መሆኑን አመልክቷል። ዳዊት “እንዲህ ዓይነቱ ዕውቀት ለእኔ እጅግ ድንቅ ነው። ልደርስበት ከምችለው በላይ ከፍ ያለ ነው ” በማለት አስታውቋል። (መዝሙር 139:5, 6 አዓት) አምላክ ስለ አገልጋዮቹ ያለው ዕውቀት እኛ ልንረዳው ከምንችለው በላይ በጣም የተሟላና የተጣራ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሁኔታችንን በእርግጥ እንደሚረዳልንና እሱ የሚያቀርብልን እርዳታ ከሁሉ የተሻለ እንደሚሆን ትምክህት ለማሳደር ያህል የሚበቃ ዕውቀት አለን። — ኢሳይያስ 48:17, 18
የትም ብንሆን አምላክ ሊረዳን ይችላል
10. በመዝሙር 139:7–12 ላይ የሚገኘው ብሩህ መግለጫ የቀረበው የሚያበረታታ እውነት ምንድን ነው?
10 መዝሙራዊው የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ ከሌላ አቅጣጫ በመመልከት “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ ” በማለት ይቀጥላል። ዳዊት ከይሖዋ ለማምለጥ የመሞከር ምኞት አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ የትም ቦታ ቢሆን ይሖዋ እንደሚያውቅና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሊረዳው እንደሚችል ያውቅ ነበር። ዳዊት እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፣ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፣ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፣ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፣ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፣ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች፤ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፣ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። ” (መዝሙር 139:7–12) ከይሖዋ ፊት የትም ልንሄድ አንችልም። ከይሖዋ ዓይን ሊሰውረን ወይም መንፈሱ እኛን ለመርዳት ሊደርስ ከማይችልበት ቦታ ሊያደርሰን የሚችል ምንም ሁኔታ የለም።
11, 12. (ሀ) ምንም እንኳን ዮናስ ለጊዜው ባይገነዘበውም ይሖዋ እኛን ለማየትና ለመርዳት ያለው ችሎታ በዮናስ ሁኔታ የታየው እንዴት ነው? (ለ) የዮናስ ተሞክሮ ሊጠቅመን የሚገባው እንዴት ነው?
11 በአንድ ወቅት ነቢዩ ዮናስ ይህን ዘንግቶ ነበር። ለነነዌ ሰዎች እንዲሰብክ ይሖዋ ልኮት ነበር። በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሳ ይህን የተሰጠውን የሥራ ምድብ ሊያከናውነው የሚችል አልመሰለውም። ምናልባትም አሦራውያን ከነበራቸው የኃይለኝነት ዝና የተነሳ በነነዌ የማገልገሉ ሐሳብ ዮናስን አስፈርቶት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከይሖዋ ፊት ለመደበቅ ፈለገ። ከዚያም በኢዮጴ ወደብ ወደ ተርሴስ የምትሄድ አንዲት መርከብ አገኘ። (ይህም ቦታ በስፔን ውስጥ እንደሆነ ምሑራን ባጠቃላይ የሚስማሙበት ሲሆን ከነነዌ በስተ ምሥራቅ ከ3,500 ኪሎ ሜትር ርቆ ይገኛል።) ያም ሆነ ይህ መርከቧን ሲሳፈር እንዲሁም መርከቧ ውስጥ ገብቶ ሲተኛ ይሖዋ ይመለከተው ነበር። በኋላም ከመርከቧ ሲወረወር ዮናስ የት እንዳለ አምላክ ያውቅ ነበር። ዮናስ በአንድ ትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሆኖ መሐላውን እንደሚፈጽም ቃል ሲገባ ይሖዋ ይሰማው ነበር። ዮናስ ወደ የብስ በመውጣት ምድብ ሥራውን እንዲያሟላ በድጋሚ አጋጣሚ ተሰጠው። — ዮናስ 1:3, 17፤ 2:1 እስከ 3:4
12 ዮናስ የተሰጠውን ሥራ እንዲያከናውን የይሖዋ መንፈስ እንደሚረዳው መጀመሪያውኑ ቢተማመን ኖሮ እንዴት የተሻለ ነበር! ይሁን እንጂ ዮናስ የደረሰበትን ነገር ከጊዜ በኋላ በትህትና መዝግቧል። ይህም ለዮናስ አስቸጋሪ ሆኖበት የነበረውን በይሖዋ ላይ የመመካት ሁኔታ ብዙዎች እንዲያሳዩ ረድቷቸዋል። — ሮሜ 15:4
13. (ሀ) ኤልያስ ከንግሥት ኤልዛቤል ፊት ከመሸሹ በፊት በታማኝነት ያከናወነው የሥራ ምድብ ምን ነበር? (ለ) ኤልያስ ከእስራኤል ክልል ውጭ ሄዶ ለመደበቅ በፈለገበት ጊዜ እንኳን ይሖዋ የረዳው እንዴት ነበር?
13 ኤልያስ ያጋጠመው ነገር ትንሽ ለየት ይላል። ኤልያስ እስራኤላውያን ስለሠሩት ኃጢአት በድርቅ እንደሚቀጡ ይሖዋ ያወጣውን ድንጋጌ በታማኝነት ተናግሯል። (1 ነገሥት 16:30–33፤ 17:1) በቀርሜሎስ ተራራ በይሖዋና በበኣል መካከል በተካሄደው ፉክክር ኤልያስ እውነተኛውን አምልኮ በድፍረት ደግፏል። ከዚያም ኤልያስ በቂሶን ወንዝ ሸለቆ 450 የበኣል ነቢያትን አስገድሏል። ይሁን እንጂ ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው በዛተች ጊዜ ኤልያስ ከአገሩ ሸሸ። (1 ነገሥት 18:18–40፤ 19:1–4) በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ይሖዋ ደረሰለትን? አዎን፣ ደርሶለታል። ኤልያስ ወደ ሰማይ እንደወጣ ያክል ረጅም ተራራ ቢወጣም ኖሮ፣ ወደ ሲኦል እንደገባ ያክል በምድር ታች በዋሻ ውስጥ ቢደበቅም ኖሮ፣ በአንድ ጊዜ በምድር ሁሉ ላይ በሚፈነጥቀው የንጋት ብርሃን ፍጥነት ሩቅ ወደሆነ ደሴት ቢሸሽም ኖሮ፣ እሱን ለማጠንከርና ለመምራት የይሖዋ ክንድ በአጠገቡ ይሆን ነበር። (ከሮሜ 8:38, 39 ጋር አወዳድር።) ይሖዋም ኤልያስን ያበረታው ለጉዞው የሚሆን ምግብ በመስጠት ብቻ ሳይሆን በአንቀሳቃሽ ኃይሉ አማካኝነት የተለያዩ ተአምራቶችን በማሳየት ጭምር ነው። ኤልያስም በዚህ መንገድ በመጠናከር የሚቀጥለውን የነቢይነት ሥራውን አከናውኗል። — 1 ነገሥት 19:5–18
14. (ሀ) አምላክ በሁሉም ሥፍራ በአካል የሚገኝ ነው ብሎ መደምደም ስህተት የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዘመናችን ይሖዋ አገልጋዮቹን በፍቅር ደግፎ ያቆመው በምን ሁኔታዎች ሥር ነው? (ሐ) ሲኦል ውስጥ እንኳ ብንገባ አምላክ በዚያም የሚገኘው እንዴት ነው?
14 በመዝሙር 139:7–12 ላይ ያሉት ትንቢታዊ ቃላት አምላክ በማንኛውም ጊዜ በማንኛውም ቦታ በአካል ይገኛል ማለት አይደሉም። ቅዱሳን ጽሑፎች ከዚህ የተለየ ሐሳብ ይሰጣሉ። (ዘዳግም 26:15፤ ዕብራውያን 9:24) ይሁን እንጂ አገልጋዮቹ እርሱ በማይደርስበት ቦታ ሊሆኑ አይችሉም። ይህም ቲኦክራሲያዊ የሥራ ምድባቸው ወደ ሩቅ ቦታዎች እንዲሄዱ ላደረጋቸው ወንድሞችና እኅቶችም ይሠራል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ለነበሩት የይሖዋ ምስክሮች ይህ አባባል ይሠራ ነበር። እንዲሁም በ1950ዎች መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ወቅት በቻይና ውስጥ ገለልተኛ በሆኑ እስር ቤቶች ውስጥ ለነበሩ ሚሲዮናውን ይህ አባባል ይሠራ ነበር። በተደጋጋሚ ጊዜ መንደራቸውን እንዲያውም አገራቸውን እንኳ ሳይቀር ጥለው ሸሽተው ለነበሩት በአንድ የመካከለኛው አፍሪካ አገር ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ የተወደዱ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንም ይህ አባባል ይሠራል። ይሖዋ አስፈላጊ ከሆነ ሲኦል ውስጥ ማለትም መቃብር ውስጥ እንኳን ሊደርስና በትንሣኤ አማካኝነት ታማኞቹን መልሶ ለማምጣት ይችላል። — ኢዮብ 14:13–15፤ ሉቃስ 20:37, 38
በእርግጥ ሁኔታችንን ሁሉ የሚረዳልን
15. (ሀ) ይሖዋ የእኛን ባሕርይ እድገት የሚመለከተው ምን ያህል ጊዜ ቀደም ብሎ ነው? (ለ) መዝሙራዊው ኩላሊትን በመጥቀሱ አምላክ እኛን እስከ ምን ድረስ እንደሚያውቀን የተገለጸው እንዴት ነው?
15 አምላክ ከመወለዳችን በፊት እንኳን ስለ እኛ እንደሚያውቅ መዝሙራዊው በመንፈስ ተነሳስቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አቤቱ፣ አንተ ኩላሊቴን ፈጥረሃልና፣ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።” (መዝሙር 139:13, 14) ጽንስ በሚጸነስበት ወቅት ከአባታችንና ከእናታችን የተገኘው ዘር ሲዋሃድ ወደ ፊት የሚኖረንን አካላዊና አእምሮአዊ ችሎታ በጥልቅ የሚነካ ንድፍ ያስገኛል። አምላክ ይህ ንድፍ ምን ሊወጣው እንደሚችል ያውቃል። በዚህም ላይ መዝሙራዊው ቅዱሳን ጽሑፎች ብዙ ጊዜ ውስጣዊ ማንነትን እንደሚወክል አድርገው የሚጠቀሙበትን ኩላሊትን ለይቶ ጠቅሷል።a (መዝሙር 7:9፤ ኤርምያስ 17:10) ይሖዋ እኛ ከመወለዳችን በፊት እነዚህን የመሳሰሉ ዝርዝር ሁኔታዎች ያውቃል። በተጨማሪም የሰው አካል በእናቲቱ ማሕፀን ውስጥ ላለው የዳበረ ሴል የሚሆን ጽንሱን ‘የሚሸፍን’ እና ጽንሱ በሚያድግበት ጊዜ መከላከያ የሚሆንለት ተከላካይ ቤት መሰል ነገር እንዲያበጅ አድርጎ በፍቅራዊ አሳቢነቱ የፈጠረው እርሱ ነው።
16. (ሀ) መዝሙር 139:15, 16 የአምላክ እይታ ውስጥ ድረስ ዘልቆ የመግባት ኃይል እንዳለው ጎላ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) ይህስ ሊያበረታታን የሚገባው ለምንድን ነው?
16 መዝሙራዊው የአምላክ የማየት ችሎታ የቱን ያህል ዘልቆ የመግባት ኃይል እንዳለው በማጉላት እንዲህ ሲል ጨምሮ ጽፏል:- “እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ፣ [ቅኔያዊ አነጋገሩ የእናቱን ማህፀን የሚያመለክት ቢሆንም አዳም ከአፈር መሠራቱንም በተዘዋዋሪ መጠቆሙ እንደሆነ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል።] አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ [የሰውነት ክፍሎች] ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር [እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል] በመጽሐፍህ ተጻፈ።” (መዝሙር 139:15, 16) ሰው ሁኔታችንን ተረዳልንም አልተረዳልንም ይሖዋ እንደሚረዳልን ምንም አያጠራጥርም። ይህ እንዴት ሊነካን ይገባል?
17. የአምላክ ሥራዎች ድንቅ መሆናቸውን ስንመለከት ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?
17 የመዝሙር 139 ጸሐፊ በጽሑፉ የገለጻቸው የአምላክ ሥራዎች ድንቅ መሆናቸውን አምኖ ተቀብሏል። አንተም እንዲህ ይሰማሃልን? አንድ በጣም ድንቅ የሆነ ነገር አንድ ሰው በጥልቅ እንዲያስብ ወይም በተመስጦ ትኩር ብሎ እንዲመለከት ያደርገዋል። አንተም የይሖዋ ሥራዎች የሆኑትን ግዑዛን ፍጥረታት ስትመለከት እንደዚሁ እንደሚሰማህ የተረጋጋጠ ነው። (ከመዝሙር 8:3, 4, 9 ጋር አወዳድር።) አምላክ መሲሐዊቷን መንግሥት በማቋቋም ረገድ ስላደረገው ነገር፣ ምሥራቹ በምድር ሁሉ እንዲሰበክ ስለማድረጉ እንዲሁም ቃሉ የሰዎችን ጠባይ እንዴት እንደሚለውጥ ስታይ ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ ወደ አእምሮህ ይመጣልን? — ከ1 ጴጥሮስ 1:10–12 ጋር አወ ዳድር።
18. የአምላክ ሥራዎች አክብሮታዊ ፍርሃት የሚያሳድሩብን ሆነው ስናገኛቸው ይህ እኛን እንዴት ይነካናል?
18 ስለ አምላክ ሥራዎች ስታሰላስል አክብሮታዊ ፍርሃት ያሳድርብሃልን? በራስ ማንነትና ሕይወትህን በምትጠቀምበት መንገድ ላይ ለውጥ እንድታደርግ በኃይል በመገፋፋት ጤናማ ፍርሃት እንዲኖርህ ያደርጋልን? (ከመዝሙር 66:5 ጋር አወዳድር።) ከሆነ ልብህ ይሖዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለማወደስ፣ ስለ ዓላማዎቹና እሱን ለሚያፈቅሩት ሰዎች ወደፊት ስላስቀመጣቸው ነገሮች ለሌሎች ለመናገር ይገፋፋሃል። — መዝሙር 145:1–3
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 150ን ተመልከት።
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ ‘ይሖዋ አምላክ መሆኑን’ ማወቃችን በደስታ እንድናገለግለው የሚረዳን እንዴት ነው?
◻ አምላክ የምናደርገውን ማንኛውንም ነገር ማወቁ ሕይወታችንን ሊነካው የሚገባው እንዴት ነው?
◻ ከአምላክ የማየት ችሎታ በፍጹም የማንሰወር መሆናችን የሚያበረታታን ለምንድን ነው?
◻ ማንም ሰው ሊረዳልን በማይችልበት መንገድ አምላክ ሁኔታችንን ሊረዳልን የሚችለው ለምንድን ነው?
◻ እንደዚህ የመሰለው ጥናት ይሖዋን ከፍ ከፍ እንድናደርገው የሚያድርገን ለምንድን ነው?