የዘላለም ሕይወት ማግኘት በእርግጥ ይቻላልን?
“መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?”—ማቴዎስ 19:16
1. የዕድሜያችንን ርዝመት በተመለከተ ምን ሊባል ይቻላል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሕሻዊሮስ በሚል ስምም የሚታወቀው የፋርሱ ንጉሥ ቀዳማዊ ዜርሰስ በ480 ከዘአበ ከተደረገው ውጊያ ቀደም ብሎ ጦር ሠራዊቱን ጎብኝቶ ነበር። (አስቴር 1:1, 2 NW) ሄሮዶቱስ የተባለው ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ እንደዘገበው ንጉሡ ወታደሮቹን ተዘዋውሮ ሲመለከት አለቀሰ። ምን አስለቀሰው? ቀዳማዊ ዜርሰስ “የሰው ልጅ ዕድሜ ምን ያህል አጭር እንደሆነ ሳስብ በጣም ያሳዝነኛል። የዛሬ መቶ ዓመት ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳቸውም በሕይወት አይኖሩም” ሲል ተናግሯል። አንተም የሰው ዕድሜ በጣም አጭር እንደሆነና ማንም ሰው ማርጀት፣ መታመምና መሞት እንደማይፈልግ ሳታስተውል አትቀርም። ጤናሞችና ደስተኞች ሆነን ሁልጊዜ በወጣትነት ዕድሜ መኖር ብንችል እንዴት ደስ ይል ነበር!—ኢዮብ 14:1, 2
2. ብዙ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው? ለምንስ?
2 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጋዚን በመስከረም 28, 1997 እትሙ ላይ “መኖር ይፈልጋሉ” የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። ጽሑፉ አንድ ተመራማሪ “ዘላለም ለመኖር የመጀመሪያው ትውልድ እኛ እንደምንሆን አምናለሁ”! ሲሉ የተናገሩትን ቃል ጠቅሷል። እናንተም የዘላለም ሕይወት ሊገኝ የሚችል ነገር እንደሆነ ታምኑ ይሆናል። እንዲህ ያለ እምነት ሊኖራችሁ የቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላለም ስለመኖር ስለሚናገር ይሆናል። (መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4) ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተጠቀሱ ነገር ግን የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይቻላል ብሎ ለማመን የሚያስችሉ ምክንያቶች እንዳሉ የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ ምክንያቶች ሁለቱን መመልከታችን በእርግጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንደሚቻል ለማወቅ ያስችለናል።
ዘላለም እንዲኖር ሆኖ የተሠራ
3, 4. (ሀ) አንዳንዶች ለዘላለም መኖር መቻል አለብን ብለው የሚያስቡት ለምንድን ነው? (ለ) ዳዊት ስለ አፈጣጠሩ ምን ብሎ ተናግሯል?
3 ብዙ ሰዎች የሰው ልጅ ለዘላለም መኖር መቻል አለበት ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸው አንዱ ምክንያት በጣም ድንቅ የሆነ አፈጣጠራችን ነው። ለምሳሌ ያህል በእናታችን ማሕፀን ውስጥ ተጸንሰን ያደግንበት ሁኔታ ተአምራዊ ነው። አንድ ስለ እርጅና ብዙ ምርምር ያደረጉ ሰው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ተፈጥሮ ከጽንሰት እስከ ልደት፣ ከልደት እስከ አካለ መጠን ብሎም ሙሉ ሰው እስከ መሆን የሚያደርሱንን ተአምራት ካከናወነ በኋላ እነዚህን ተአምራት ለዘላለም ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችለውን ቀላል አሠራር ላለመከተል መርጧል።” አዎን፣ ተአምራዊ የሆነውን አሠራራችንን ስንመለከት የምንሞተው ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ይነሣል።
4 በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ዳዊት በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ሳይንቲስቶች በማሕፀን ውስጥ የሚካሄደውን ነገር ለመመልከት ባይችልም ስለ እነዚህ ተአምራት አሰላስሏል። ዳዊት ስለ አካሉ አሠራር ያሰላስል የነበረ ሲሆን ‘በእናቱ ሆድ ውስጥ ተሰውሮ’ እንደነበር ጽፏል። በዚያን ጊዜ ‘ኩላሊቶቹ እንደተፈጠሩ’ ተናግሯል። በተጨማሪም “በስውር በተሠራሁ ጊዜ” ብሎ በመናገር ስለ ‘አጥንቶቹ’ መሠራት ተናግሯል። ዳዊት ቀጥሎ “ያልተሠራ አካሌን [“ሽል እያለሁ፣” NW]” ስላለው ነገር የተናገረ ሲሆን ከዚህ ሽል ጋር በተያያዘ መንገድ በእናቱ ማሕፀን ውስጥ “አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 139:13-16
5. በማሕፀን ውስጥ በምንፈጠርበት ጊዜ የትኞቹ ተአምራት ይከናወናሉ?
5 ዳዊትን በእናቱ ማሕፀን ውስጥ ለመፍጠር ሲባል አስቀድሞ በእጅ የተሠራ ንድፍ እንደማይኖር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ዳዊት ስለ ‘ኩላሊቶቹ፣’ ‘አጥንቶቹና’ ሌሎች የአካል ክፍሎቹ አሠራር ሲያሰላስል የእነዚህ የአካል ክፍሎቹ እድገት ሁሉም ነገር ‘በመጽሐፍ የተጻፈ’ ያህል በእቅድ የተደረገ መስሎት ነበር። በእናቱ ውስጥ የሚገኘው ፅንስ የአንድን ሰብዓዊ ሕፃን አካል ለመሥራት የሚያስፈልገውን ዝርዝር መመሪያ በያዙ መጻሕፍት የተሞላ ትልቅ ክፍል እንዳለውና እነዚህ ውስብስብ መመሪያዎች ደግሞ ለእያንዳንዱ የሚያድግ ሕዋስ የተላለፈለት ያህል ነበር። ይህም በመሆኑ ሳይንስ ዎርልድ የተባለው መጽሔት ‘በማደግ ላይ ባለ አንድ ሽል ውስጥ የሚገኝን እያንዳንዱን ሕዋስ በንድፎች ከተሞላ ካቢኔት’ ጋር አመሳስሎታል።
6. ዳዊት እንደጻፈው ‘ግሩምና ድንቅ ሆነን ለመፈጠራችን’ ምን ማስረጃ አለ?
6 ስለ ሰውነታችን ተአምራዊ አሠራር አስበህ ታውቃለህ? ጃረድ ዳይመንድ የተባሉ አንድ ባዮሎጂስት እንዲህ ብለዋል:- “በአንጀታችን ግድግዳ ላይ ያሉትን ሴሎች በየጥቂት ቀናት ውስጥ፣ በፊኛችን ግድግዳ ላይ የሚገኙትን ሴሎች በየሁለት ወር፣ ቀይ የደም ሕዋሶቻችንን ደግሞ በየአራት ወር ሙሉ በሙሉ በአዳዲስ ሴሎች እንተካለን።” ሲያጠቃልሉም “ተፈጥሮ በየቀኑ ፈታትቶ መልሶ ይገጥመናል” ብለዋል። ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው? የኖርንበት ዕድሜ 8ም ሆነ 80 ወይም 800 በአካላችን ከሚገኙት ሕዋሳት መካከል አብዛኞቹ ምንጊዜም ወጣቶች ናቸው ማለት ነው። አንድ ሳይንቲስት በአንድ ወቅት በሰጡት ግምት መሠረት “በአሁኑ ጊዜ በውስጣችን ከሚገኙት አተሞች መካከል 98 በመቶ የሚሆኑት ከምንተነፍሰው አየር፣ ከምንበላው ምግብና ከምንጠጣው ነገር በሚገኙ አዳዲስ አተሞች ይተካሉ።” በእርግጥም ዳዊት ውዳሴ ሲያቀርብ እንደተናገረው ‘ግሩምና ድንቅ ሆነን ተፈጥረናል።’—መዝሙር 139:14
7. የአካላችንን አሠራር በመመልከት አንዳንዶች ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል?
7 አንድ ስለ እርጅና ያጠኑ እውቅ ሊቅ ይህን የአካላችንን አሠራር በመመልከት “እርጅና የሚመጣበት ምክንያት ፈጽሞ ግልጽ አይደለም” ብለዋል። ዘላለም መኖር መቻል ያለብን መስሎ ይታያል። ሰዎች በራሳቸው ቴክኖሎጂ አማካኝነት እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚጣጣሩት በዚህ ምክንያት ነው። ዶክተር አልቪን ሲልቨርስታይን ኮንክዌስት ኦቭ ዴዝ በተባለው መጽሐፋቸው “የሕይወትን ምሥጢር ማግኘታችን አይቀርም። . . . ሰው የሚያረጀው እንዴት እንደሆነ እንረዳለን” ሲሉ በእርግጠኝነት ጽፈዋል። ታዲያ ይህ ምን ውጤት ያስገኛል? “ሞትን ድል ለመንሳት ያስቻለው እውቀት ዘላለም ወጣት ሆኖ የመኖርን ዘዴ ስለሚያስገኝ ከዚያ በኋላ እርጅና የተጫናቸው ሰዎች አይኖሩም” ሲሉ ተንብየዋል። ዘመናዊው ሳይንስ በሰብዓዊው አካል አሠራር ላይ ያደረገውን ምርምር ስንመለከት ስለ ዘላለም ሕይወት ማሰብ የማይጨበጥ ነገር ነውን? የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይቻላል ብሎ ለማመን የሚያበቃ ከዚህ ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ሌላም ምክንያት አለ።
ለዘላለም የመኖር ፍላጎት
8, 9. በታሪክ ዘመናት በሙሉ ሰዎች ምን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነበራቸው?
8 ለዘላለም መኖር የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ፍላጎት መሆኑን ተገንዝበሃልን? አንድ ዶክተር በአንድ የጀርመንኛ ጋዜጣ ላይ “ለዘላለም የመኖር ሕልም የሰው ልጅ ወደ ሕልውና ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ሳይሆን አይቀርም” ሲሉ ጽፈዋል። ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ አንዳንድ ጥንታዊ አውሮፓውያን “ብቁ ሆነው የተገኙ ሰዎች በወርቅ በተንቆጠቆጠ አዳራሽ ውስጥ ዘላለም ይኖራሉ” የሚል እምነት እንደነበራቸው ይገልጻል። የሰው ልጆች ለዘላለም የመኖር ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ምን ያልሞከሩት ነገር አለ!
9 ከ2,000 ዓመታት በፊት በቻይና “ነገሥታትና [ተራ] ሰዎች በታኦኢስት ቀሳውስት መሪነት ሥራቸውን ሁሉ ወደ ጎን በመተው ዘላለም ለመኖር የሚያስችለውን ቅመም ይፈልጉ” እንደነበረ ዚ ኢንሳይክለፒዲያ አሜሪካና ይገልጻል። ሰዎች ባለፉት የታሪክ ዘመናት በሙሉ የተቀመሙ መድኃኒቶችን በመውሰድ፣ እንዲያውም አንዳንድ የውኃ ዓይነቶችን በመጠጣት ወጣት እንደሆኑ ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምኑ ነበር።
10. ሕይወትን ለማራዘም ምን ዘመናዊ ሙከራዎች ተደርገዋል?
10 በዘመናችንም ቢሆን የሰውን ልጅ ለዘላለም የመኖር ተፈጥሯዊ ፍላጎት እውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት በጣም ከፍተኛ ነው። ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆነን የሰዎችን አስከሬን አቀዝቅዞ የማቆየት ልማድ ነው። ይህ የሚደረገው ለሰውዬው ሞት ምክንያት ለሆነው በሽታ መድኃኒት በሚገኝበት ጊዜ እንደገና በሕይወት እንዲኖር ለማስቻል ሲባል ነው። ክራዮኒክስ ተብሎ የሚጠራው የዚህ ልማድ ደጋፊ የሆኑ አንድ ሰው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ተስፋችን እውን ቢሆንና፣ እርጅና የሚያስከትለውን ጉስቁልና ጨምሮ ማንኛውንም በአካላችን ላይ የሚደርስ ጉዳት ለመጠገን የምንችልበት ዘዴ ቢታወቅ በአሁኑ ጊዜ ‘የሚሞቱት’ ወደፊት ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ሊያገኙ ይችላሉ።”
11. ሰዎች ለዘላለም መኖር የሚፈልጉት ለምንድን ነው?
11 ለዘላለም የመኖር ፍላጎት በአስተሳሰባችን ውስጥ ይህን ያህል ሊሰርጽ የቻለው ለምንድን ነው ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ‘አምላክ ዘላለማዊነትን በሰው ልቦና በማሳደሩ’ ምክንያት ይሆን? (መክብብ 3:11 የ1980 ትርጉም) ይህ ቆም ብለን በጥሞና ልናስብበት የሚገባ ነጥብ ነው! እስቲ አስቡ:- ለዘላለም የመኖር ፍላጎታችን እውን እንዲሆን የፈጣሪ ዓላማ ባይሆን ኖሮ ይህን የመሰለ የተፈጥሮ ፍላጎት ለምን ይኖረን ነበር? ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ፈጥሮ ይህ ፍላጎታችን እውን እንዳይሆን ቢያደርግ ፍቅር የጎደለው ድርጊት መፈጸሙ አይሆንምን?—መዝሙር 145:16
መታመን የሚኖርብን በማን ነው?
12. አንዳንዶች ምን የሚል እምነት አላቸው? ሆኖም ተጨባጭነት አለው ብለህ ታምናለህ?
12 የዘላለም ሕይወት ለማግኘት መታመን የሚኖርብን በምን ወይም በማን ነው? በ20ኛው ወይም በ21ኛው መቶ ዘመን የሰው ልጅ ቴክኖሎጂ ነውን? “ለመኖር ይፈልጋሉ” የተሰኘው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጋዚን ላይ የወጣው ርዕስ ስለ “ቴክኖሎጂ አምልኮ” እና “ቴክኖሎጂ ያለውን አቅም በታላቅ አድናቆት ስለመመልከት” ገልጿል። እንዲያውም አንድ ተመራማሪ “የጀኔቲክ ማሻሻያ ቴክኒክ የእርጅናን ሂደት እንድናቆም፣ ምናልባትም ወደ ወጣትነት እንድንመለስ በማስቻል እንደሚያድነን . . . ብሩሕ ተስፋ አለኝ” በማለት እንደተናገሩ መጽሔቱ ገልጿል። ይሁንና የሰው ልጅ እርጅናን ለማስቆም ወይም ሞትን ድል ለማድረግ ያደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ሆኗል።
13. የአንጎላችን አሠራር ለዘላለም እንድንኖር ሆነን እንደ ተፈጠርን የሚያሳየው እንዴት ነው?
13 ታዲያ እንዲህ ሲባል የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ አይኖርም ማለት ነው? በፍጹም አይደለም! የዘላለም ሕይወት የሚገኝበት መንገድ አለ! አስደናቂ የሆነውና ወሰን የሌለው የአንጎላችን የመማር አቅም ይህን ሊያሳምነን ይገባል። ሞሊኪውላዊ ባዮሎጂስት የሆኑት ጀምስ ዋትሰን አንጎላችን “በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ካገኘናቸው ነገሮች ሁሉ በውስብስብነቱ ወደር የማይገኝለት” ሲሉ ገልጸውታል። ኒውሮሎጂስቱ ሪቻርድ ሬስታክ ደግሞ “እስካሁን በታወቀው ጽንፈ ዓለም ውስጥ በትንሹ እንኳን ከአንጎል ጋር የሚመሳሰል ነገር አልተገኘም” ብለዋል። የተፈጠርነው ለዘላለም እንድንኖር ባይሆን ኖሮ ወሰን የሌለው መረጃ የማከማቸትና የመተንተን አቅም ያለው አንጎልና ዘላለም እንዲኖር ሆኖ የተፈጠረ አካል ለምን ይኖረናል?
14. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሰውን ሕይወት በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል? (ለ) በሰው ሳይሆን በአምላክ መታመን የሚገባን ለምንድን ነው?
14 ታዲያ በዚህ ረገድ ልንደርስበት የምንችለው ብቸኛ ምክንያታዊ መደምደሚያ ምንድን ነው? የአካላችንን ንድፍ ያወጣውና የፈጠረን ሁሉን ማድረግ የሚቻለውና ሁሉን የሚያውቀው ፈጣሪያችን አይደለምን? (ኢዮብ 10:8፤ መዝሙር 36:9፤ ሚልክያስ 2:10፤ ሥራ 17:24, 25) ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” ሲል በመንፈስ አነሣሽነት የሰጠውን መመሪያ ብንከተል ብልህነት አይሆንምን? በሰዎች መታመን የማይኖርብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም መዝሙራዊው እንደጻፈው “ነፍሱ [“መንፈሱ፣” NW] ትወጣለች፣ ወደ መሬቱም ይመለሳል። ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል።” ለዘላለም የመኖር አቅምና ችሎታ ቢኖራቸውም ሁሉም ሰዎች ይሞታሉ፣ በሞት ፊት ሁሉም አቅመ ቢሶች ናቸው። መዝሙራዊው “ተስፋው በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምስጉን ነው” በማለት ያጠቃልላል።—መዝሙር 146:3-5
በእርግጥ የአምላክ ዓላማ ነውን?
15. ለዘላለም እንድንኖር የአምላክ ዓላማ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?
15 ይሁን እንጂ በእርግጥ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የአምላክ ዓላማ ነውን? ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። አዎን፣ ዓላማው ነው! በቃሉ ውስጥ በደርዘን በሚቆጠሩ ጊዜያት የዘላለም ሕይወት እውን እንደሚሆን ተናግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ . . . የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት አስረግጦ ይናገራል። የአምላክ አገልጋይ የሆነው ዮሐንስ “እርሱም [አምላክ] የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው” ሲል ጽፏል። አንድ ወጣት “የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?” ብሎ ኢየሱስን መጠየቁ ምንም አያስደንቅም። (ሮሜ 6:23፤ 1 ዮሐንስ 2:25፤ ማቴዎስ 19:16) እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ተስፋ” ስለሰጠበት ‘የዘላለም ሕይወት’ ጽፏል።—ቲቶ 1:2
16. አምላክ “ከዘላለም ዘመናት በፊት” የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሰጠው በምን መንገድ ነው?
16 አምላክ “ከዘላለም ዘመናት በፊት” የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሰጥቷል ሲል ምን ማለቱ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋን ከመፈጠራቸው በፊት አምላክ የሰው ልጆችን ለዘላለም የማኖር ዓላማ እንደ ነበረው ማመልከቱ ነው ብለው አንዳንዶች ያስባሉ። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እያመለከተ ያለው ሰዎች ከተፈጠሩ በኋላ አምላክ ዓላማውን የገለጸበትን ጊዜ ከሆነ አሁንም ቢሆን አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፈቃድ የዘላለም ሕይወት መስጠትን እንደሚጨምር ግልጽ ነው።
17. አዳምና ሔዋን ከኤደን ገነት እንዲወጡ የተደረገው ለምን ነበር? መግቢያውን ኪሩቤሎች እንዲጠብቁ የተደረገውስ ለምንድን ነው?
17 መጽሐፍ ቅዱስ በኤደን ገነት ውስጥ “እግዚአብሔር አምላክም . . . ከምድር አበቀለ። በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ . . . አበቀለ” ይላል። ኃጢአተኛው አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ከገነት የተባረረው “እጁን እንዳይዘረጋ፣ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር” ነበር! ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከኤደን ገነት ካባረረ በኋላ “ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን” አስቀመጠ።—ዘፍጥረት 2:9፤ 3:22-24
18. (ሀ) አዳምና ሔዋን ከሕይወት ዛፍ ቢበሉ ኖሮ ምን ማለት ይሆን ነበር? (ለ) ከዚያ ዛፍ መብላት ምን ያመለክታል?
18 አዳምና ሔዋን ከዚያች የሕይወት ዛፍ እንዲበሉ ቢፈቀድላቸው ኖሮ ይህ ለእነሱ ምን ማለት ይሆን ነበር? በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር መብት ነዋ! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንደሚከተለው በማለት ግምታዊ ሐሳብ ሰጥተዋል:- “የሕይወት ዛፍ የሰውን ልጅ አካል እርጅና ከሚያመጣው ጉስቁልና ወይም በሞት ከሚደመደመው ድካም የሚከላከል አንድ ዓይነት ባሕርይ የነበረው መሆን አለበት” እንዲያውም “በገነት ውስጥ እርጅና የሚያስከትለውን ጉዳት የመከላከል ኃይል ያለው ፈዋሽ ዕፅ ነበር” እስከ ማለት ደርሰዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ዛፍ በራሱ ይህን የመሰለ ሕይወት የመስጠት ባሕርይ እንዳለው አይናገርም። ከዚህ ይልቅ ከፍሬው እንዲበላ የተፈቀደለት ሰው ከአምላክ የዘላለም ሕይወት ዋስትና ማግኘቱን የሚያመለክት ዛፍ ነው።—ራእይ 2:7
የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም
19. አዳም የሞተው ለምንድን ነው? የእሱ ዘሮች የሆንነው እኛስ የምንሞተው ለምንድን ነው?
19 ይሁን እንጂ አዳም ኃጢአት በሠራ ጊዜ እርሱም ሆነ ገና በአብራኩ ያሉ ልጆቹ በሙሉ ለዘላለም የመኖርን መብት አጡ። (ዘፍጥረት 2:17) አዳም ባለመታዘዝ ምክንያት ኃጢአተኛ በሆነ ጊዜ ፍጽምና የጎደለው ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “የኃጢአት ደመወዝ ሞት” ስለሆነ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአዳም አካል ለሞት የተዳረገ ሆነ። (ሮሜ 6:23) ከዚህም በላይ ፍጽምና ያጡት የአዳም ልጆች ለዘላለም ሕይወት ሳይሆን ለሞት ተዳረጉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ይናገራል።—ሮሜ 5:12
20. ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ሆነው መፈጠራቸውን የሚያመለክተው ምንድን ነው?
20 አዳም ኃጢአት ባይሠራስ ኖሮ? የአምላክን ትእዛዝ ባይጥስና ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ ቢፈቀድለት ኖሮስ? የአምላክን የዘላለም ሕይወት ስጦታ አግኝቶ የሚኖረው የት ይሆን ነበር? ሰማይ? የለም! አዳም ወደ ሰማይ እንደሚወሰድ አምላክ የተናገረው ነገር አልነበረም። በዚህችው ምድር ላይ የሚሠራው ሥራ ተሰጥቶት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፣ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ” ካለ በኋላ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው” በማለት ይገልጻል። (ዘፍጥረት 2:9, 15) ሔዋን የአዳም የትዳር ጓደኛ እንድትሆን ከተፈጠረች በኋላ ደግሞ ለሁለቱም በምድር ላይ የሚያከናውኑት ተጨማሪ ሥራ ተሰጣቸው። አምላክ እንዲህ አላቸው:- “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።”—ዘፍጥረት 1:28
21. የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ምን ዓይነት አስደናቂ ተስፋ ተዘርግቶላቸው ነበር?
21 ይህ አምላክ የሰጣቸው መመሪያ ለአዳምና ለሔዋን ምን ዓይነት አስደናቂ ተስፋ ዘርግቶላቸው እንደነበረ አስቡት! በገነቲቱ ምድር ላይ ፍጹም ጤና ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ልጆች ሊያሳድጉ ይችሉ ነበር። ውድ ልጆቻቸው ሲያድጉ ደግሞ በዚህ ፍሬያማና አስደሳች በሆነ የአትክልተኝነት ሥራ እየረዷቸው ገነትን ያስፋፋሉ። እንስሳት ሁሉ ይገዙላቸዋል፣ የሰው ልጅ በሙሉ በኑሮው ደስተኛ ይሆናል። የኤደን ገነት ድንበሮች እየሰፉ ሄደው ምድር በሙሉ ገነት ስትሆን ምን ዓይነት ደስታ ይሰማቸው እንደነበረ አስቡ! የማርጀት ወይም የመሞት ሥጋት ሳይኖርባችሁ ፍጹም የሆኑ ልጆችን እያሳደጋችሁ እንዲህ ባለችው የተዋበች ምድር ብትኖሩ ደስ አይላችሁም ነበር? መልሱን የየራሳችሁ ልብ ይስጥ።
22. አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ እንዳልለወጠ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
22 ታዲያ አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ በጣሱና ከኤደን አትክልት እንዲወጡ በተደረገ ጊዜ አምላክ፣ የሰው ልጆች በገነቲቱ ምድር ለዘላለም እንዲኖሩ ያወጣውን ዓላማ ለወጠ? በፍጹም አልለወጠም! አምላክ ዓላማውን ቢለውጥ የመጀመሪያ ዓላማውን ለማስፈጸም አለመቻሉን አምኖ ተቀበለ ማለት ይሆን ነበር። አምላክ ራሱ “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል፣ የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” በማለት ስለተናገረ አምላክ የሰጠውን ቃል በትክክል እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳይያስ 55:11
23. (ሀ) የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ የአምላክ ዓላማ መሆኑን የሚያረጋግጠው ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንመረምረው ምንድን ነው?
23 አምላክ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ሲል የሰጠው ተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ሰፍሮ የሚገኝ መሆኑ አምላክ ለምድር የነበረው ዓላማ እንዳልተለወጠ ያሳያል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ሳይቀር በተራራ ስብከቱ ላይ የዋሆች ምድርን እንደሚወርሱ ተናግሯል። (መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 5:5) ታዲያ የዘላለም ሕይወት ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለውን ሕይወት ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይገባናል? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ብዙ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይቻላል ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው?
◻ ለዘላለም እንድንኖር ሆነን የተፈጠርን መሆናችንን ምን ሊያሳምነን ይገባል?
◻ አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ምን ነበር?
◻ አምላክ የመጀመሪያ ዓላማውን እንደሚፈጽም እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?