“አቤቱ፣ መርምረኝ”
“ አቤቱ፣ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ . . . የዘላለምንም መንገድ ምራኝ። ” — መዝሙር 139:23, 24
1. ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚይዘው እንዴት ነው?
ሁላችንም ብንሆን ችግራችንን ከሚረዳልን፣ ሁኔታችንን ከሚያመዛዝን፣ በምንሳሳትበት ጊዜ ከሚረዳን፣ ከአቅማችን በላይ እንድናደርግ ከማይጠይቅብን ሰው ጋር ግንኙነት ማድረግ እንፈልጋለን። ይሖዋ አምላክ አገልጋዮቹን የሚይዘው በዚህ መንገድ ነው። መዝሙር 103:14 “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፣ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ” ይላል። የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም እንደሚከተለው በማለት ሞቅ ያለ ግብዣ ያቀርባል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ [ወይም “ከእኔ ጋር በአንድ ቀንበር ሥር ግቡ” አዓት የግርጌ ማስታወሻ] ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” — ማቴዎስ 11:28–30
2. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስንና (ለ) የክርስቶስን ተከታዮች በተመለከተ የይሖዋን አመለካከት ከሰዎች አመለካከት ጋር አነጻጽር።
2 ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚመለከትበት መንገድ ሰዎች ከሚመለከቱበት መንገድ በጣም የተለየ ነው። ይሖዋ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ይመለከታል። እንዲሁም ሌሎች ምንም የማያውቋቸውን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ያስገባል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ‘በሰዎች ዘንድ የተናቀና የተጠላ’ ነበር። ኢየሱስን እንደ መሲህ አድርገው ያላመኑበት ሰዎች ‘አላከበሩትም’ ነበር። (ኢሳይያስ 53:3፤ ሉቃስ 23:18–21) ይሁን እንጂ አብ “በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎ የተናገረለት በአምላክ ፊት ‘የተወደደ [የአምላክ] ልጅ’ ነበር። (ሉቃስ 3:22፤ 1 ጴጥሮስ 2:4) ከኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮችም መካከል በቁሳዊ ነገሮች ድሀ ስለሆኑና ብዙ መከራዎች ስለሚደርሱባቸው የሚናቁ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በይሖዋና በልጁ ፊት ሀብታም ሊሆኑ ይችላሉ። (ሮሜ 8:35–39፤ ራእይ 2:9) ይህ የአመለካከት ልዩነት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?
3. (ሀ) ይሖዋ ለሰዎች ያለው አመለካከት ብዙ ጊዜ ሰዎች ካላቸው አመለካከት የተለየው ለምንድን ነው? (ለ) ውስጣዊ ማንነታችንን መመርመር ለሕይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ኤርምያስ 11:20 ‘ይሖዋ ኩላሊትንና ልብን የሚፈትን ነው’ በማለት ይመልሳል። ይሖዋ ውስጣዊ ማንነታችንን ይመለከታል። ከሌሎች ሰዎች ዓይን የተሰወሩትን ባሕርዮቻችንን እንኳ ሳይቀር ይመለከታል። ይሖዋ በሚያደርገው ምርመራ ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዞ ለመኖር እጅግ አስፈላጊ ለሆኑት ባሕርያትና ሁኔታዎች ቅድሚያ ትኩረት ይሰጣል። እነዚህም እኛን ለዘለቄታው በጣም የሚጠቅሙን ናቸው። ይህን ማወቃችን መንፈሳችንን የሚያረጋጋ ነው፤ በተጨማሪም የሚያሳስብ ነው። ይሖዋ ለውስጣዊ ማንነታችን ትኩረት ስለሚሰጥ እሱ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው ዓይነት ሰዎች ሆነን ለመገኘት ውስጣችንን መመርመሩ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። የይሖዋ ቃል እንዲህ ዓይነቱን ምርመራ እንድናደርግ ይረዳናል። — ዕብራውያን 4:12, 13
የአምላክ ሐሳቦች እንዴት የተከበሩ ናቸው!
4. (ሀ) መዝሙራዊው የአምላክ ሐሳቦች ለእሱ የተከበሩ እንደሆኑ እንዲናገር የገፋፋው ምንድን ነው? (ለ) ለእኛም የተከበሩ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
4 መዝሙራዊው አምላክ ስለ አገልጋዮቹ ስላለው ዕውቀት ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም አምላክ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ሁሉ ለመስጠት ያለውን ልዩ ችሎታ ካሰላሰለ በኋላ “አቤቱ፣ አሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደ ምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 139:17) የሰው ሐሳቦች ምንም ያህል ጥበብ ያለባቸው ሊመስሉ ቢችሉም በተጻፈው ቃሉ ውስጥ የተገለጹት እነዚህ ሐሳቦች ከሰው ሐሳብ በጣም የላቁ ናቸው። (ኢሳይያስ 55:8, 9) የአምላክ አሳቦች በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ እንድናተኩርና በአገልግሎቱ ቀናተኞች እንድንሆን በማድረግ ይረዱናል። (ፊልጵስዩስ 1:9–11) አምላክ ነገሮችን በሚመለከትበት መንገድ እንዴት መመልከት እንደምንችል ያሳዩናል። ራሳችንን እንዳንዋሽ ይረዱናል። በልባችን ምን ዓይነት ሰዎች መሆናችንን በሐቅ እንድንቀበል ይረዱናል። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነህን?
5. (ሀ) የአምላክ ቃል ‘ከሁሉ አስበልጠን’ ምናችንን እንድንጠብቅ አጥብቆ ያሳስበናል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቃየን የመዘገበው ታሪክ ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው? (ሐ) ምንም እንኳን በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ማወቃችን የሚረዳን እንዴት ነው?
5 ሰዎች ለውጫዊ መልክ ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ” በማለት ይመክሩናል። (ምሳሌ 4:23) መጽሐፍ ቅዱስ ምክርም ሆነ ምሳሌ በመስጠት ይህንን እንድናደርግ ይረዳናል። ቃየን አድርጌአለሁ ለማለት ያህል ለአምላክ መሥዋዕት እንዳቀረበ፣ በውስጡ ግን ለወንድሙ ለአቤል በመጀመሪያ ቅሬታ በኋላም የከረረ ጥላቻ እንደነበረው ይነግረናል። በዚያም ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሱ እንዳንሆን አጥብቆ ያሳስበናል። (ዘፍጥረት 4:3–5፤ 1 ዮሐንስ 3:11, 12) መጽሐፍ ቅዱስ የሙሴ ሕግ የሚጠይቀውን ታዛዥነት መዝግቦ ይዞልናል። ነገር ግን ከዚህ በተጨማሪ ሕጉ የሚጠይቀው ዋናው ነገር ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ በሙሉ ልባቸው፣ አእምሮአቸው፣ ነፍሳቸውና ኃይላቸው እሱን መውደድ እንዳለባቸው ያጎላል። እንዲሁም ከዚያ ቀጥሎ በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር ጎረቤታቸውን እንደራሳቸው ይውደዱ የሚለው ትዕዛዝ መሆኑን ይገልጻል። — ዘዳግም 5:32, 33፤ ማርቆስ 12:28–31
6. ምሳሌ 3:1ን በሥራ ላይ በማዋል ረገድ ራሳችንን ምን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል?
6 የአምላክን ትዕዛዞች እንዲያው መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ታዛዥነታችን በልባችን ውስጥ ላለው ነገር እውነተኛ መግለጫ መሆን እንዳለበት በምሳሌ 3:1 ላይ በጥብቅ ተመክረናል። በግል ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ያስፈልገናል:- ‘ለአምላክ ሕጎች ያለኝ ታዛዥነት ከልብ የመነጨ ነውን?’ ማንኛችንም ብንሆን እንከን የለንም ብለን ለመናገር ባንችልም በአንዳንድ ጉዳዮች የልባችን ግፊት ወይም አስተሳሰባችን ጉድለት እንዳለው ከተገነዘብን ‘ይህን ሁኔታ ለማሻሻል ምን እያደረኩኝ ነው?’ እያልን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል። — ምሳሌ 20:9፤ 1 ዮሐንስ 1:8
7. (ሀ) ኢየሱስ በማቴዎስ 15:3–9 ላይ ፈሪሳውያንን ማውገዙ ልባችንን ለመጠበቅ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አእምሮአችንንና ልባችንን መገሠጽን አስፈላጊ የሚያደርጉ ምን ሁኔታዎች ሊኖሩን ይችላሉ?
7 የአይሁድ ፈሪሳውያን በተንኮል ለራሳቸው ጥቅም የሚበጁ ነገሮች እንዲደረጉ እያስተማሩ አምላክን የሚያከብሩ ለመምሰል በሞከሩ ጊዜ ኢየሱስ በግብዝነታቸው አወገዛቸው። እንዲሁም አምልኳቸው ከንቱ መሆኑን ነገራቸው። (ማቴዎስ 15:3–9) በተጨማሪም ኢየሱስ ልብን የሚያየውን አምላክ ለማስደሰት ከፈለግን ፍትወትን በተመለከተ ዘወትር ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ሐሳቦችን እያውጠነጠንን ላይ ላዩን ብቻ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት መምራት በቂ እንደማይሆን አስጠንቅቋል። አእምሮአችንንና ልባችንን ለመገሠጽ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገን ይሆናል። (ምሳሌ 23:12፤ ማቴዎስ 5:27–29) ሰብአዊ ሥራችን፣ በትምህርት ረገድ ያሉን ግቦች ወይም የመዝናኛ ምርጫችን ዓለም በራሱ መልክ እንዲቀርጸን በመፍቀድ ዓለምን እንድንመስል የሚያደርጉን ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ተግሣጽ ያስፈልገናል። የአምላክ ወገን ነን እያሉ የዓለም ወዳጆች ለመሆን የሚፈልጉትን ሰዎች ሐዋርያው ያዕቆብ “አመንዝሮች” ብሎ እንደጠራቸው በፍጹም መርሳት የለብንም። ለምን? ምክንያቱም ‘ዓለም በሞላው በክፉው ስለተያዘ ነው።’ — ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 2:15–17፤ 5:19
8. ከተከበሩት የአምላክ ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
8 በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ከአምላክ ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ጥቅም ለማግኘት እነሱን ለማንበብ ወይም ለመስማት ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። ከዚህም በላይ የአምላክን ሐሳቦች ማጥናት፣ መናገርና በእነሱ ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። ብዙ የመጠበቂያ ግንብ አንባቢዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት በሚደረግባቸው በይሖዋ ምስክሮች የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር ይገኛሉ። ይህንንም ለማድረግ ከሚሠሯቸው ሌሎች ነገሮች ላይ ጊዜ ይገዛሉ። (ኤፌሶን 5:15–17) ከዚህም በአጸፋው የሚያገኙት ነገር ከቁሳዊ ሀብት እጅግ የላቀ ነው። አንተስ እንደዚህ አይሰማህምን?
9. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ አንዳንዶች ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ፈጥነው እድገት የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
9 ይሁን እንጂ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ አንዳንዶች ከሌሎቹ የበለጠ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት ያደርጋሉ። እውነትን በሕይወታቸው ውስጥ ይበልጥ አሟልተው በሥራ ላይ ያውላሉ። ለዚህ የሚረዳቸው ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ ለዚህ የሚረዳቸው ትልቁ ነገር በግል ጥናት መትጋታቸው ነው። በእንጀራ ብቻ እንደማንኖር ይገነዘባሉ። ሰብአዊ ምግብ ዘወትር መመገብ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ መንፈሳዊ ምግብ ዘወትር መመገብም ያንኑ ያህል አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 4:4፤ ዕብራውያን 5:14) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ ጽሑፎችን በማንበብ በየቀኑ የተወሰነ ጊዜ ለማሳለፍ ይጥራሉ። ቀደም ብለው ትምህርቱን በማጥናትና ጥቅሶቹን አውጥተው በማንበብ ለጉባኤ ስብሰባዎች ይዘጋጃሉ። ጽሑፉን በማንበባቸው ብቻ አይረኩም፤ በትምህርቱ ላይ ያሰላስሉበታል። የአጠናን ልማዳቸው የተማሩት ነገር የራሳቸውን ሕይወት እንዴት እንደሚነካው በጥንቃቄ ማሰብንም ይጨምራል። መንፈሳዊነታቸው እያደገ ሲሄድ “አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! . . . ምስክሮችህ [ማሳሰቢያዎችህ አዓት] ድንቆች ናቸው” ሲል እንደጻፈው እንደ መዝሙራዊው ይሰማቸዋል። — መዝሙር 1:1–3፤ 119:97,129
10. (ሀ) የአምላክን ቃል ለምን ያህል ጊዜ በማጥናት ብንቀጥል እንጠቀማለን? (ለ) ቅዱሳን ጽሑፎችስ ይህን የሚያሳዩት እንዴት ነው?
10 የአምላክን ቃል ለአንድ ዓመት፣ ለ5 ዓመት ወይም ለ50 ዓመት ብናጠናውም በፍጹም ከንቱ ድግግሞሽ አይሆንም። የአምላክን ሐሳቦች የተከበሩ አድርገን የምንመለከታቸው ከሆነ ከንቱ መደጋገም አይሆንብንም። ማንኛችንም ብንሆን ከቅዱሳን ጽሑፎች የቱንም ያህል ብንማር ገና የማናውቀው ብዙ ነገር ይኖራል። ዳዊት “አቤቱ፣ . . . ቁጥራቸውም እንደ ምን በዛ! ብቆጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ” ብሏል። የአምላክ ሐሳቦች እኛ ልንቆጥረው ከምንችለው በላይ ናቸው። የአምላክን ሐሳቦች ቀኑን ሙሉ ብንቆጥርና እስክንተኛ ድረስ እንዲሁ ብናደርግ ጠዋት ስንነቃ ገና የምናሰላስለው ብዙ ሐሳብ ይኖራል። ስለዚህ ዳዊት “ተነሳሁም፣ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 139:17, 18) ስለ ይሖዋና ስለ መንገዶቹ ለዘላለም ብዙ የምንማረው አለ። ሁሉንም ወደማወቅ በፍጹም አንደርስም። — ሮሜ 11:33
ይሖዋ የሚጠላውን መጥላት
11. የአምላክን ሐሳቦች ማወቅ ብቻ ሳይሆን አምላክ ለነገሮች ያለው ስሜት በእኛም ውስጥ መኖሩ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 የአምላክን ቃል የምናጠናው አእምሮአችንን በልዩ ልዩ ሐሳቦች ለመሙላት ብቻ አይደለም። የአምላክ ቃል ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ በፈቀድንለት መጠን ስለ ነገሮች አምላክ እንደሚሰማው ሊሰማን ይጀምራል። ይህም እንዴት በጣም አስፈላጊ ነው! እንዲህ ዓይነት ስሜቶችን ካላዳበርን ምን ውጤት ሊያስከትልብን ይችላል? ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን በቃላችን ለመናገር ብንችልም የተከለከለውን ነገር ልንመኝ እንችላለን። ወይም የታዘዝነው ነገር ሸክም ሆኖ ሊሰማን ይችላል። እውነት ነው፣ መጥፎ የሆነውን ብንጠላም እንኳ ከሰብአዊ አለፍጽምና የተነሳ ትግል ይኖርብን ይሆናል። (ሮሜ 7:15) ይሁን እንጂ ውስጣዊ ማንነታችንን ትክክል ከሆነው ነገር ጋር ለማስማማት ልባዊ ጥረት ካላደረግን ‘ልብን የሚፈትነውን’ ይሖዋን እናስደስተዋለን ብለን ልንጠብቅ እንችላለንን? — ምሳሌ 17:3
12. አምላካዊ ፍቅርና አምላካዊ ጥላቻ ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው?
12 አምላካዊ ፍቅር ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግን አስደሳች እንደሚያደርግልን ሁሉ አምላካዊ የሆነ ጥላቻ ደግሞ መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም የሚጠብቅ ኃይለኛ መከላከያ ነው። (1 ዮሐንስ 5:3) ቅዱሳን ጽሑፎች አምላካዊ ፍቅርንም ሆነ ጥላቻን እንድንኮተኩት በተደጋጋሚ አጥብቀው ያሳስቡናል። “እግዚአብሔርን የምትወድዱ፣ ክፋትን ጥሉ።” (መዝሙር 97:10) “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ።” (ሮሜ 12:9) ይህን እያደረግን ነውን?
13. (ሀ) የክፉዎችን መጥፋት በተመለከተ ከየትኛው የዳዊት ጸሎት ጋር ሙሉ በሙሉ በሐሳብ እንስማማለን? (ለ) በዳዊት ጸሎት እንደታየው አምላክ እንዲያጠፋቸው የጸለየላቸው ክፉዎች የትኞቹ ነበሩ?
13 ይሖዋ ክፉዎችን ከምድር ላይ ጠራርጎ ለማጥፋትና ጽድቅ የሚኖርባት አዲስ ምድር ለማምጣት ዓላማ እንዳለው በግልጽ ተናግሯል። (መዝሙር 37:10, 11፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎች የዚህን ጊዜ መምጣት በናፍቆት ይጠባበቃሉ። እንደሚከተለው ሲል ከጸለየው ከመዝሙራዊው ዳዊት ጋር በሐሳብ ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ:- “አቤቱ፣ አንተ ኃጢአተኞችን የምትገድል ከሆንህስ፣ የደም ሰዎች ሆይ፣ ከእኔ ፈቀቅ በሉ። በክፋት ይናገሩብሃልና፤ ጠላቶችህም በከንቱ ያምፁብሃል። ” (መዝሙር 139:19, 20) ዳዊት እንደዚህ ዓይነቶቹን ክፉዎች ራሱ ለመግደል አልጓጓም። በቀል ከይሖዋ እጅ እንዲመጣ ጸልዮአል። (ዘዳግም 32:35፤ ዕብራውያን 10:30) እነዚህ ሰዎች በአንዳንድ ነገሮች ዳዊትን ብቻ ያስቀየሙት አይደሉም። የአምላክን ስም ከንቱ በሆነ መንገድ በመያዝ አምላክን በተሳሳተ መንገድ የወከሉት ሰዎች ናቸው። (ዘጸአት 20:7) በሐሰት አምላክን እናገለግላለን እያሉ የአምላክን ስም የራሳቸውን ዓላማ ለማስፋፋት ሲጠቀሙበት ነበር። ዳዊት የአምላክ ጠላቶች መሆን ለመረጡት ሰዎች ፍቅር አልነበረውም።
14. እርዳታ ሊደረግላቸው የሚችሉ ክፉዎች አሉን? ካሉ እንዴት?
14 ይሖዋን የማያውቁ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ብዙዎቹ ካለማወቅ የተነሳ የአምላክ ቃል ክፉ ናቸው የሚላቸውን ነገሮች ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ መሄዳቸውን ከቀጠሉ በታላቁ መከራ ወቅት ከሚጠፉት ሰዎች መካከል ይሆናሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ በክፉዎች መሞት አይደሰትም። እኛም ብንሆን መደሰት አይኖርብንም። (ሕዝቅኤል 33:11) ጊዜ እስከፈቀደልን ድረስ እነዚህ ሰዎች የይሖዋን መንገዶች እንዲያውቁና በሥራ ላይ እንዲያውሉ ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ለይሖዋ ኃይለኛ ጥላቻ ቢያሳዩስ?
15. (ሀ) መዝሙራዊው ‘የወጣላቸው ጠላቶች’ አድርጎ የተመለከታቸው እነማን ናቸው? (ለ) እኛ ዛሬ በይሖዋ ላይ የሚያምፁትን ‘እንደምንጠላ’ እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
15 እነሱን በተመለከተ መዝሙራዊው እንደሚከተለው ብሏል:- “አቤቱ፣ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም አልተሰቀቅሁምን? ፍጹም ጥል ጠላኋቸው፣ [የወጣላቸው ] ጠላቶችም ሆኑኝ። ” (መዝሙር 139:21, 22) ዳዊት በጥላቻ የተመለከታቸው ለይሖዋ ኃይለኛ ጥላቻ ስለነበራቸው ነው። ሃይማኖታዊ ከሃዲዎች በይሖዋ ላይ በማመፅ ለእሱ ያላቸውን ጥላቻ ከሚገልጹት ሰዎች መካከል ናቸው። ክህደት በይሖዋ ላይ ማመፅ ማለት ነው። አንዳንድ ከሃዲዎች አምላክን እንደሚያውቁና እንደሚያገለግሉ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በቃሉ ውስጥ ያሉትን ትምህርቶች ወይም ትእዛዛት አንቀበልም ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋን ድርጅት አይቀበሉም፤ እንዲያውም ሥራውን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ትክክለኛ የሆነውን ነገር ካወቁ በኋላ ሆነ ብለው እንዲህ ዓይነቱን ክፋት ሲመርጡና ክፋት በውስጣቸው ሥር ሰድዶ ከተዋሃዳቸው አንድ ክርስቲያን እነዚህን ራሳቸውን ከክፋት ጋር ያጣበቁትን ሰዎች መጥላት (በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉሙ) አለበት። እውነተኛ ክርስቲያኖች ለእነዚህ ከሃዲዎች የይሖዋ ዓይነት ስሜት አላቸው። ስለ ክህደት ሐሳቦቻቸው የማወቅ ጉጉት አያድርባቸውም። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን የአምላክ ጠላቶች ላደረጉት ሰዎች “የጥላቻ ስሜት” ይኖራቸዋል። ይሁን እንጂ በቀሉን ለይሖዋ ይተዉታል። — ኢዮብ 13:16፤ ሮሜ 12:19፤ 2 ዮሐንስ 9, 10
አምላክ በሚመረምረን ጊዜ
16. (ሀ) ዳዊት ይሖዋ እንዲመረምረው የፈለገው ለምን ነበር? (ለ) የራሳችንን ልብ በተመለከተ አምላክ እንድናስተውለው እንዲረዳን መጠየቅ የሚኖርብን ምን ነገር አለ?
16 ዳዊት በምንም መንገድ ክፉዎችን ለመምሰል አልፈለገም። ብዙ ሰዎች የውስጥ ማንነታቸውን ለመደበቅ ይጥራሉ። ዳዊት ግን እንደሚከተለው ሲል በትሕትና ጸልዮአል:- “አቤቱ፣ መርምረኝ ልቤንም እወቅ፤ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ፤ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ፤ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ። ” (መዝሙር 139:23, 24) ዳዊት ልቤን ሲል ሥጋዊ የሰውነቱን ክፍል ማለቱ አይደለም። ይህ ሐረግ ካለው ምሳሌያዊ ትርጉም ጋር በመስማማት ውስጣዊ ማንነቱን መጥቀሱ ነበር። እኛም አምላክ ልባችንን እንዲመረምረውና የተሳሳቱ ምኞቶች፣ የፍቅር ወይም ሌሎች ስሜቶች፣ ዓላማዎች፣ ሐሳቦች ወይም ግፊቶች እንዳሉን እንዲያይ መፈለግ አለብን። (መዝሙር 26:2) ይሖዋ “ልጄ ሆይ፣ ልብህን ስጠኝ፣ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ” በማለት ግብዣ ያቀርብልናል። — ምሳሌ 23:26
17. (ሀ) ዕረፍት የሚነሱንን ሐሳቦች አምቀን ከመያዝ ይልቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) በልባችን ውስጥ የተሳሳቱ ዝንባሌዎች ቢገኙ ሊያስደንቀን ይገባልን? እነሱንስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
17 በተሳሳተ ምኞት ወይም የልብ ግፊት ወይም ባለን አንዳንድ የተሳሳተ ጠባይ የተነሳ የሚያሰቃዩና ዕረፍት የሚነሱ በውስጣችን የተደበቁ ሐሳቦች ካሉ ነገሩን ለማስተካከል ይሖዋ እንዲረዳን እንደምንፈልግ የተረጋገጠ ነው። የእንግሊዝኛው የሞፋት ትርጉም “በደል” ወይም አዲሲቱ ዓለም ትርጉም እንደሚለው “ማንኛውም ስቃይ የሚያስከትል መንገድ” ከማለት ይልቅ “የተሳሳተ አካሄድ” በሚለው ሐረግ ይጠቀማል። ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ደግሞ “ማንኛውም አምላክን የሚያሳዝን ጎዳና” ይላል። እኛ ራሳችን ዕረፍት የሚነሱን ሐሳቦች ምን እንደሆኑ በትክክል ላንረዳቸው እንችል ይሆናል። ስለሆነም እንዴት ብለን ችግራችንን ለአምላክ እንደምንገልጽለት አናውቅም። ይሁን እንጂ እሱ ሁኔታችንን ይረዳል። (ሮሜ 8:26, 27) በልባችን ውስጥ መጥፎ ዝንባሌዎች ቢኖሩ ሊያስደንቀን አይገባም። ቢሆንም ሰበብ እየፈጠርን ልንይዛቸው አይገባም። (ዘፍጥረት 8:21) ከውስጣችን ነቅለን ለማውጣት የአምላክን እርዳታ ለማግኘት መፈለግ ይኖርብናል። ይሖዋንና መንገዶቹን በእርግጥ የምንወድ ከሆነ “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል” የሚል ትምክኽት ይዘን እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ ለማግኘት ወደ እርሱ ለመቅረብ እንችላለን። — 1 ዮሐንስ 3:19–21
18. (ሀ) ይሖዋ የዘላለምን መንገድ የሚመራን እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋን መመሪያ መከተላችንን ከቀጠልን ምን የሞቀ የምስጋና ቃል ከእርሱ እንደምናገኝ ልንጠብቅ እንችላለን?
18 መዝሙራዊው ይሖዋ የዘላለምን መንገድ እንዲመራው ካቀረበው ጸሎት ጋር በመስማማት ይሖዋ ትሁትና ታዛዥ የሆኑ አገልጋዮቹን ይመራል። ክፋት ሠርተው ያለ ዕድሜያቸው ሳይቀጩ በመቅረታችው ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ይመራቸዋል። የኢየሱስ መሥዋዕት ያለው ኃጢአትን የማስተሰረይ ዋጋ እንደሚያስፈልገን በውስጣችን ይቀርጽብናል። የእሱን ፈቃድ ለማድረግ እንድንችል በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ለሕይወት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችን ያቀርብልናል። ውስጣዊ ማንነታችንና ውጫዊ ማንነታችን እንዲጣጣሙ ይሖዋ ለሚሰጠን እርዳታ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያጎላልናል። (መዝሙር 86:11) ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ እርሱ ብቻ እውነተኛ የሆነውን አንድ አምላክ ለማገልገል የምንጠቀምበት ዘላለማዊ ሕይወት ከፍጹም ጤንነት ጋር እንደምናገኝ ተስፋ በመስጠት ያበረታታናል። ለመመሪያዎቹ የታማኝነት ምላሽ መስጠታችንን ከቀጠልን ልክ ለልጁ “በአንተ ደስ ይለኛል” እንዳለው ይለናል። — ሉቃስ 3:22፤ ዮሐንስ 6:27፤ ያዕቆብ 1:12
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚመለከትበት መንገድ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከሚመለከቱበት መንገድ የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ አምላክ ልባችንን በሚመረምርበት ጊዜ ምን እንዳየብን ለማወቅ ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?
◻ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን ለማወቅና ልባችንን ለመጠበቅ የሚረዳን ምን ዓይነት ጥናት ነው?
◻ አምላክ የሚናገረውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን እርሱ ለነገሮች ያለው ስሜት በውስጣችን መኖሩ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ እኛ በግላችን “አቤቱ፣ መርምረኝ ልቤንም እወቅ” ብለን መጸለይ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በምታጠናበት ጊዜ የአምላክን ሐሳቦችና ስሜቶች የራስህ ለማድረግ ጣር
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ሐሳቦች “ ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ”
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.