ክብር ባለው መንገድ በመመላለስ ይሖዋን ማክበር
“[የይሖዋ ሥራ] ባለ ክብርና ባለ ግርማ ነው።”—መዝ. 111:3
1, 2. (ሀ) “ክብር” የሚለውን ቃል እንዴት ትገልጸዋለህ? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
የአሥር ዓመት ልጅ የሆነችው ማዲሰን “ክብር ያለው” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ስትጠየቅ “ጥሩ አለባበስ ያለው” በማለት መልሳለች። ይህች ልጅ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምላክ ‘ክብርን እንደለበሰ’ ተደርጎ መገለጹን አታውቅ ይሆናል። (መዝ. 104:1) ክብር ባለው መንገድ መመላለስ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ጥሩ በሆነ መንገድ መልበስን ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያን ሴቶች “በጨዋነትና ራስን በመግዛት ተገቢ የሆነ ልብስ ይልበሱ እንጂ በሹሩባ ወይም በዕንቊ ወይም ዋጋቸው ውድ በሆኑ ልብሶች አይሽቀርቀሩ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። (1 ጢሞ. 2:9) ይሁን እንጂ የይሖዋን ‘ክብርና ግርማ’ ከፍ ከፍ የሚያደርግ ክብር ያለው አኗኗር ከዚህ ያለፈ ነገር ይጨምራል።—መዝ. 111:3
2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ክብር” የሚለውን ቃል የሚያመለክተው የዕብራይስጥ ቃል “ግርማ፣” “ሞገስ” እንዲሁም “ታላቅነት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው “ክብር” የሚለው ቃል “ከሁሉ በላይ መሆንን፣ ላቅ ያለ መሆንን እንዲሁም ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆንን” ያመለክታል። ከይሖዋ በላይ የላቀ ክብር ሊሰጠው ወይም ከፍ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ማንም የለም። ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን እሱን የሚያስከብር መሆን አለበት። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ክብር ባለው መንገድ መመላለስ ይችላሉ የምንለው ለምንድን ነው? የይሖዋ ክብርና ግርማ ግልጽ ሆኖ የታየው እንዴት ነው? የአምላክ ክብር ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? የአምላክን ክብር በማንጸባረቅ ረገድ ከኢየሱስ ክርስቶስ ምን ትምህርት እናገኛለን? የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ክብር ባለው መንገድ መመላለስ የቻልነው ለምንድን ነው?
3, 4. (ሀ) አምላክ የሰጠን ክብር ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል? (ለ) በመዝሙር 8:5-9 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለ ማን የተነገረ ትንቢት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ሐ) ባለፉት ዘመናት ይሖዋ እነማንን አክብሯል?
3 የሰው ልጆች በሙሉ በአምላክ አምሳል ስለተፈጠሩ ክብር ባለው መንገድ መመላለስ ይችላሉ። ይሖዋ፣ የመጀመሪያውን ሰው ምድርን እንዲንከባከባት ኃላፊነት በመስጠት አክብሮታል። (ዘፍ. 1:26, 27) የሰው ዘር በኃጢአት ከወደቀ በኋላም እንኳ ይሖዋ፣ የሰው ልጅ ከምድር ጋር በተያያዘ ያለውን ኃላፊነት እንደገና በመናገር የክብርን ‘ዘውድ አቀዳጅቶታል።’ (መዝሙር 8:5-9ን አንብብ።)a ይሖዋ የሰጠን ክብር እኛም እንድናከብረው ማለትም የእሱን ታላቅ ስም በአክብሮት እንድናወድሰው ያደርገናል።
4 ይሖዋ፣ ቅዱስ አገልግሎት ለሚያቀርቡለት ሰዎች የተለየ ክብር ሰጥቷቸዋል። አምላክ የቃየንን መሥዋዕት ሳይቀበል የወንድሙን የአቤልን መሥዋዕት በመቀበሉ አቤልን አክብሮታል። (ዘፍ. 4:4, 5) ሙሴ ከእሱ በኋላ እስራኤልን በሚመራው በኢያሱ ላይ ‘ከክብሩ እንዲያኖርበት’ መመሪያ ተሰጥቶት ነበር። (ዘኍ. 27:20 የ1954 ትርጉም) የዳዊት ልጅ የሆነውን ሰሎሞንን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ሁሉ እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከእርሱ በፊት ለነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ያላጐናጸፋቸውን ንጉሣዊ ክብር ሁሉ ሰጠው።” (1 ዜና 29:25) አምላክ ‘የመንግሥቱን ግርማ ክብር’ በታማኝነት ላስታወቁት ትንሣኤ ያገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተለየ ክብር ይሰጣቸዋል። (መዝ. 145:11-13) ይሖዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን የኢየሱስ ‘ሌሎች በጎችም’ እሱን በዚህ መንገድ በማወደስ ረገድ ድርሻ እንዲኖራቸው በማድረግ ባርኳቸዋል እንዲሁም አክብሯቸዋል።—ዮሐ. 10:16
የይሖዋ ክብርና ግርማ በግልጽ ታይቷል
5. የይሖዋ ክብር ምን ያህል ታላቅ ነው?
5 መዝሙራዊው ዳዊት፣ የአምላክን ታላቅነት የሰው ልጆች ኢምንት ከመሆናቸው ጋር በማነጻጸር በጻፈው መዝሙር ላይ እንዲህ ብሏል:- “[ይሖዋ፣ NW] አምላካችን ሆይ፤ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው! ክብርህ ከሰማያት በላይ፣ ከፍ ከፍ ብሎአል።” (መዝ. 8:1) ይሖዋ አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ ክብርና ግርማ የተላበሰ አካል ነው፤ ይህም ሲባል ‘ሰማያትና ምድር’ ከመፈጠራቸው በፊትም ሆነ አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግና የሰው ልጆችን ቤተሰብ ወደ ፍጽምና ለማድረስ ያለው ዓላማ ታላቅ ፍጻሜውን ካገኘ በኋላም ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ ክብርና ግርማ የተላበሰ ነው ማለት ነው።—ዘፍ. 1:1፤ 1 ቆሮ. 15:24-28፤ ራእይ 21:1-5
6. መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ክብርን እንደለበሰ የተናገረው ለምንድን ነው?
6 ፈሪሃ አምላክ የነበረው መዝሙራዊ፣ እንደ ዕንቁ በሚያንጸባርቁ ከዋክብት ያሸበረቀውንና ግርማ ሞገስ የተላበሰውን ሰማይ ሲመለከት ተደምሞ መሆን አለበት። መዝሙራዊው፣ ድንቅ የሆነውን የአምላክ የፍጥረት ችሎታ ይኸውም ‘ሰማያትን እንደ ድንኳን መጋረጃ የዘረጋበትን’ መንገድ ሲመለከት በአድናቆት ስለተሞላ ይሖዋን ክብር እንደለበሰ አድርጎ ገልጾታል። (መዝሙር 104:1, 2ን አንብብ።) የማይታይ አምላክ የሆነው ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ያለው ክብርና ግርማ በሚታዩት ሥራዎቹ ላይ በግልጽ ታይቷል።
7, 8. ሰማያት፣ ይሖዋ ክብርና ግርማ እንደተላበሰ ማስረጃ የሚሆኑት እንዴት ነው?
7 ፍኖተ ሐሊብ የተባለውን ጋላክሲ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በዚህ ሰፊ የከዋክብት፣ የፕላኔቶችና የሥርዓተ ፀሐዮች ውቅያኖስ ውስጥ ምድራችን በተንጣለለ የባሕር ዳርቻ ላይ እንደሚገኝ የአሸዋ ቅንጣት ኢምንት ሆና ትታያለች። ይህ ጋላክሲ ብቻ እንኳ 100 ቢሊዮን ከዋክብትን ይዟል! በየቀኑ ለ24 ሰዓታት በእያንዳንዱ ሴኮንድ አንድ ኮከብ ብንቆጥር ከ100 ቢሊዮን በላይ ከዋክብትን ቆጥረን ለመጨረስ ከ3,000 ዓመታት በላይ ይፈጅብናል።
8 ፍኖተ ሐሊብ የተባለው ጋላክሲ ብቻ 100 ቢሊዮን ከዋክብትን ከያዘ በአጠቃላይ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ምን ያህል ከዋክብት እንደሚገኙ መገመት ትችላለህ? የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች፣ ፍኖተ ሐሊብ የሚባለው ጋላክሲ ከ50 እስከ 125 ቢሊዮን እንደሚደርሱ ከሚገመቱት ጋላክሲዎች አንዱ እንደሆነ ይገልጻሉ። ታዲያ በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ምን ያህል ከዋክብት አሉ? መልሱ አእምሯችን ሊረዳው ከሚችለው በላይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ይሖዋ “የከዋክብትን ብዛት ያውቃል፤ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል።” (መዝ. 147:4) ይሖዋ ክብርና ግርማ እንደተላበሰ ማወቅህ ታላቅ ስሙን እንድታወድስ አይገፋፋህም?
9, 10. ዳቦ፣ የፈጣሪያችንን ጥበብ ጎላ አድርጎ የሚያሳየው እንዴት ነው?
9 እስቲ አሁን ደግሞ አስደናቂ የሆነውን ሰማይ ትተን ሁላችንም ስለምናውቀው ስለ ዳቦ እንመልከት። ይሖዋ ‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’ ከመሆኑም በላይ “ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ” አምላክ ነው። (መዝ. 146:6, 7) የአምላክ ‘ክብርና ግርማ’ ከተንጸባረቀባቸው ታላላቅ ሥራዎቹ መካከል ዕፅዋት የሚገኙበት ሲሆን ከእነሱም ምግብ ይዘጋጃል። (መዝሙር 111:1-5ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ “የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:11 NW) በጥንት ጊዜ እስራኤላውያንን ጨምሮ ብዙ ሕዝቦች ዋነኛ ምግባቸው ዳቦ ነበር። ዳቦ በቀላሉ እንደሚዘጋጅ ምግብ ተደርጎ የሚታይ ቢሆንም መሠረታዊ የሆኑ ጥቂት ንጥረ ነገሮች ጣፋጭ ወደሆነ ዳቦ የሚለወጡበት ኬሚካላዊ ሂደት ውስብስብ ነው።
10 መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን እስራኤላውያን ዳቦ የሚያዘጋጁት የስንዴ ወይም የገብስ ዱቄትን በውኃ በመለወስ ነበር። ዳቦ በሚያዘጋጁበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ እርሾ ይጨምሩበት ነበር። እነዚህ ውስብስብ ያልሆኑ ንጥረ ነገሮች አንድ ላይ ሲቀላቀሉ፣ እርስ በርሳቸው ግንኙነት ያላቸው በርካታ ኬሚካላዊ ውሕዶችን ይፈጥራሉ። እነዚህ ውሕዶች በአንድ ላይ ሆነው እንዴት እንደሚሠሩ በትክክል አይታወቅም። ከዚህም በላይ ዳቦ በሰውነታችን ውስጥ የሚፈጭበት ውስብስብ ሂደትም አስገራሚ ነው። መዝሙራዊው “[ይሖዋ፣ NW] ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ” በማለት መዘመሩ ምንም አያስገርምም! (መዝ. 104:24) አንተም እንደ መዝሙራዊው ይሖዋን ለማወደስ ትገፋፋለህ?
የአምላክ ክብር ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
11, 12. በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል?
11 በምሽት በሚታዩት ከዋክብት ለመደመም የሥነ ፈለክ ተመራማሪ፣ ዳቦን ለማጣጣም ደግሞ የኬሚስትሪ ባለሙያ መሆን አያስፈልገንም። ሆኖም የፈጣሪያችንን ግርማ ማድነቅ እንድንችል በእጁ ሥራዎች ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። ማሰላሰላችን ምን ጥቅም አለው? እንዲህ ማድረጋችን በሌሎች የይሖዋ ሥራዎች ላይ በማሰላሰል የምናገኘውን ጥቅም ያስገኝልናል።
12 ይሖዋ ለሕዝቦቹ ሲል ያከናወናቸውን ታላላቅ ሥራዎች አስመልክቶ ዳዊት “ግርማ ስለተላበሰው ክብርህና ድንቅ ስለሆኑት ሥራዎችህ በጥልቅ አስባለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 145:5) መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠና እንዲሁም ባነበብነው ነገር ላይ ለማሰላሰል ጊዜ የምንመድብ ከሆነ ስለ እነዚህ ሥራዎች እንደምናስብ እናሳያለን። እንዲህ ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ለአምላክ ክብርና ግርማ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። ይህን ካደረግን ልክ እንደ ዳዊት እኛም ይሖዋን በማክበር “እኔም ስለ ታላቅነትህ ዐውጃለሁ” ለማለት እንደምንነሳሳ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 145:6) በአምላክ ድንቅ ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናክራል፤ እንዲሁም ስለ እሱ በግለትና በድፍረት ለሰዎች እንድንናገር ያነሳሳናል። አንተስ ምሥራቹን በቅንዓት እየሰበክህ እንዲሁም ሰዎች የይሖዋ አምላክን ክብር፣ ግርማና ታላቅነት እንዲያውቁ እየረዳህ ነው?
ኢየሱስ የአምላክን ክብር ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል
13. (ሀ) በዳንኤል 7:13, 14 መሠረት ይሖዋ ለልጁ ምን ሰጥቶታል? (ለ) ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ተገዢዎቹን የሚይዛቸው እንዴት ነው?
13 የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥራቹን በቅንዓት በመስበክ ክብርና ግርማ የተላበሰውን በሰማይ የሚኖረውን አባቱን አክብሯል። ይሖዋ ለአንድያ ልጁ ‘ግዛትና መንግሥት’ በመስጠት ልዩ ክብር ሰጥቶታል። (ዳንኤል 7:13, 14 የ1954 ትርጉምን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ሥልጣን ማግኘቱ ትዕቢተኛ ወይም የማይቀረብ እንዲሆን አላደረገውም። ከዚህ በተቃራኒ የተገዢዎቹን የአቅም ገደብ የሚያውቅና በአክብሮት የሚይዛቸው ርኅሩኅ ገዢ ነው። ምድር ላይ እያለ እጩ ንጉሥ የነበረው ኢየሱስ ሰዎችን በተለይም በሌሎች ዘንድ የሚገለሉና የማይወደዱ ግለሰቦችን እንዴት እንደያዛቸው የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
14. በጥንቷ እስራኤል ውስጥ በሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎች እንዴት ይታዩ ነበር?
14 በጥንት ጊዜ በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዙ ሰዎች በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ማቅቀው ይሞቱ ነበር። በዚህ ደዌ የተያዘው ግለሰብ የሰውነት ክፍሎች ቀስ በቀስ በበሽታው ይጠቃሉ። በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዘን ሰው ማዳን የሞተን ሰው የማስነሳት ያህል ከባድ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። (ዘኍ. 12:12፤ 2 ነገ. 5:7, 14)b የሥጋ ደዌ በሽታ የያዛቸው ሰዎች ርኩስ እንደሆኑ ተደርገው ስለሚታዩ በማኅበረሰቡ ይጠሉና ይገለሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች፣ ሌሎች ሲቀርቧቸው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ርኩስ ነኝ! ርኩስ ነኝ!” በማለት ሰዎቹ እንዳይጠጓቸው ማስጠንቀቅ ነበረባቸው። (ዘሌ. 13:43-46) በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዘ ሰው ከሞተ ሰው ተለይቶ አይታይም ነበር። በረቢዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዘ ሰው ወደ ሌላ ሰው መቅረብ የሚችለው እስከ 1.7 ሜትር ገደማ ድረስ ብቻ ነበር። አንድ የሃይማኖት መሪ በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዘ ሰው ሲመለከት እንዳይቀርበው ለማድረግ ገና ከሩቁ ድንጋይ ይወረውርበት እንደነበር የሚገልጹ ዘገባዎች እናገኛለን።
15. ኢየሱስ በሥጋ ደዌ ለተጠቃ አንድ ሰው ምን አሳይቶታል?
15 ያም ሆኖ በሥጋ ደዌ የተጠቃ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ እንዲፈውሰው በለመነው ጊዜ ኢየሱስ ያደረገው ነገር ትኩረት የሚስብ ነው። (ማርቆስ 1:40-42ን አንብብ።) ኢየሱስ፣ በሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቃውን ሰው ከማባረር ይልቅ ሌሎች ለሚያገልሉት ለዚህ ሰው ርኅራኄና አክብሮት አሳይቶታል። የኢየሱስ ትኩረት ያረፈው፣ ግለሰቡ ከሥቃዩ እረፍት ማግኘት የሚያሻው አሳዛኝ ሰው በመሆኑ ላይ ነበር። ኢየሱስ በሁኔታው ልቡ ስለተነካ በርኅራኄ ተነሳስቶ ወዲያው እርምጃ ወሰደ። እጁንም ዘርግቶ በሥጋ ደዌ የተያዘውን ሰው በመዳሰስ ፈወሰው።
16. ኢየሱስ ሌሎችን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
16 የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ የአባቱን ክብር ያንጸባረቀበትን መንገድ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ሁሉም ሰው ተገቢው አክብሮት ሊሰጠው እንደሚገባ በመገንዘብ ነው። ሰዎች ያላቸው ቦታና የጤናቸው ሁኔታ አሊያም ዕድሜያቸው አክብሮት እንዳናሳያቸው ሊገድበን አይገባም። (1 ጴጥ. 2:17) በተለይ ደግሞ ባሎች፣ ወላጆች፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሌሎች ግለሰቦች በእነሱ ሥር ላሉት ሰዎች አሳቢነትና አክብሮት በማሳየት እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት እንዳያጡ ሊረዷቸው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህ ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያሟሉት የሚገባ ነገር መሆኑን ሲያጎላ እንዲህ ብሏል:- “እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ።”—ሮሜ 12:10
ለአምላክ ክብር የሚያመጣ አምልኮ ማቅረብ
17. ለይሖዋ አምልኮ ስናቀርብ ለእሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ መመላለስን በተመለከተ ከቅዱሳን መጻሕፍት ምን ትምህርት እናገኛለን?
17 ለይሖዋ አምልኮ ስናቀርብ ለእሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ መመላለሳችን ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። መክብብ 5:1 “ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ” ይላል። ሙሴም ሆነ ኢያሱ በተቀደሰ ቦታ ላይ በቆሙ ጊዜ ጫማቸውን እንዲያወልቁ ታዘው ነበር። (ዘፀ. 3:5፤ ኢያሱ 5:15) ይህንን ማድረጋቸው አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳይ ነበር። እስራኤላውያን ካህናት “ሰውነትን የሚሸፍን” የበፍታ ሱሪ መልበስ ነበረባቸው። (ዘፀ. 28:42, 43) እንዲህ ማድረጋቸው በመሠዊያው አጠገብ በሚያገለግሉበት ጊዜ ሰውነታቸው እንዳይጋለጥ ለማድረግ ይረዳል። የካህኑ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ክብር ባለው መንገድ በመመላለስ ረገድ አምላክ ያወጣውን መሥፈርት ማሟላት ነበረባቸው።
18. የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን ክብር ባለው መንገድ መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?
18 የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ክብር ባለው መንገድ መመላለስ ይኖርብናል። ክብር የሚገባን ሰዎች ሆነን ለመገኘት በሚያስከብር መንገድ መኖር አለብን። ይህም ለይስሙላ ወይም ለታይታ የሚደረግ ሳይሆን ከልብ የመነጨ ሊሆን ይገባል። (1 ሳሙ. 16:7፤ ምሳሌ 21:2) ለይሖዋ አክብሮት በሚያመጣ መንገድ መመላለስ የሕይወታችን ክፍል ሊሆን ይኸውም በባሕርያችን፣ በአመለካከታችን፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት አልፎ ተርፎም ስለ ራሳችን ባለን አመለካከትና ስሜት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል። በእርግጥም፣ ለይሖዋ አክብሮት ማሳየት በምንናገረውም ሆነ በምናደርገው በማንኛውም ነገር ሁልጊዜ ሊንጸባረቅ ይገባል። በባሕርያችን፣ በጠባያችን፣ በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ሐሳብ በቁም ነገር እንመለከተዋለን:- “አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ፣ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም። ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን።” (2 ቆሮ. 6:3, 4) ‘በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የአምላክ ትምህርት እንዲወደድ እናደርጋለን።’—ቲቶ 2:10
የአምላክን ክብር በሚያንጸባርቅ መንገድ መመላለሳችሁን ቀጥሉ
19, 20. (ሀ) ሌሎችን ማክበር የምንችልበት ግሩም መንገድ የትኛው ነው? (ለ) አክብሮት ከማሳየት ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
19 “የክርስቶስ እንደራሴዎች” የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ክብር ባለው መንገድ ይመላለሳሉ። (2 ቆሮ. 5:20) እነሱን በታማኝነት የሚደግፏቸው “ሌሎች በጎች” የመሲሐዊው መንግሥት የተከበሩ ልዑካን ናቸው። አንድ እንደራሴ ወይም ልዑክ የአገሩን መንግሥት ወክሎ በድፍረትና በአክብሮት ይናገራል። እኛም ስለ አምላክ መንግሥት የምንናገረው በአክብሮትና በድፍረት መሆን ይኖርበታል። (ኤፌ. 6:19, 20) ደግሞስ ለሰዎች ‘መልካም ዜና ስናበስራቸው’ አክብሮት እያሳየናቸው አይደለም?—ኢሳ. 52:7
20 ከአምላክ ክብር ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለስ አምላክን ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 2:12) ምንጊዜም ቢሆን ለይሖዋ፣ ለአምልኮው እንዲሁም ለእምነት ባልንጀሮቻችን ጥልቅ አክብሮት እናሳይ። ክብር በሚንጸባረቅበት መንገድ የምናቀርበው አምልኮ ክብርና ግርማ የተላበሰውን ይሖዋን የሚያስደስት ይሁን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “ለምጽ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል የሥጋ ደዌን የሚያመለክት ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የይሖዋን ክብርና ግርማ ማድነቃችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
• ኢየሱስ በሥጋ ደዌ የተጠቃን አንድ ሰው ከያዘበት መንገድ ለሰዎች ክብር ስለማሳየት ምን ትምህርት እናገኛለን?
• በተለያዩ የሕይወታችን ዘርፎች ክብር ባለው መንገድ በመመላለስ ይሖዋን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ፣ አቤልን ያከበረው እንዴት ነበር?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀላል የሚመስለው ዳቦ እንኳ ለይሖዋ ታላላቅ ሥራዎች ማስረጃ ነው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በሥጋ ደዌ የተጠቃውን ሰው ከያዘበት መንገድ ለሰዎች ክብር ስለማሳየት ምን ትምህርት አግኝተሃል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ አምልኮታችንን ማከናወን አለብን