የይሖዋ ታላቅነት የማይመረመር ነው
“እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም።”—መዝሙር 145:3
1, 2. ዳዊት ምን ዓይነት ዝና ነበረው? ለራሱስ ምን አመለካከት ነበረው?
መዝሙር 145ን ያቀናበረው በታሪክ ውስጥ በጣም ታዋቂ የሆነ ሰው ነው። በልጅነቱ መሣሪያ ከታጠቀ አንድ ግዙፍ ሰው ጋር ተዋግቶ ገድሎታል። ንጉሥ ከሆነ በኋላም በጦረኝነቱ ይታወቅ የነበረ ሲሆን በርካታ ጠላቶቹን ድል አድርጓል። ዳዊት ተብሎ የሚጠራው ይህ ሰው የጥንቷ እስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ ነበር። ዳዊት ከሞተም በኋላ ዝናው አልጠፋም፤ ዛሬም እንኳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያውቁታል።
2 ዳዊት በእጅጉ የተሳካለት ሰው ቢሆንም ትሑት ነበር። ስለ ይሖዋ እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፣ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” (መዝሙር 8:3, 4) ዳዊት ራሱን ታላቅ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ከጠላቶቹ ሁሉ የታደገው ይሖዋ መሆኑን ለመግለጽ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የማዳንህንም ጋሻ ትሰጠኛለህ፤ ትሕትናህም ታላቅ አድርጎኛል።” (2 ሳሙኤል 22:1, 2, 36 NW) ይሖዋ ለኃጢአተኞች ምሕረት በማሳየት ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ወይም የትሕትና ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ዳዊትም ይገባኛል ለማይለው ለዚህ የአምላክ ደግነት አድናቆቱን ገልጿል።
‘አምላኬንና ንጉሤን ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ’
3. (ሀ) ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ የሚመለከተው ማንን ነበር? (ለ) ዳዊት ይሖዋን ለማወደስ ምን ያህል ፍላጎት ነበረው?
3 ዳዊት በአምላክ የተሾመ ንጉሥ ቢሆንም የእስራኤል ዋነኛ ንጉሥ አድርጎ የሚመለከተው ይሖዋን ነበር። እንዲህ ብሏል:- “መንግሥት የአንተ ነው፣ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ።” (1 ዜና መዋዕል 29:11) እንዲሁም ዳዊት ለአምላክ አገዛዝ አድናቆት ነበረው። “አምላኬ ንጉሤ ሆይ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም እባርካለሁ። በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 145:1, 2) ዳዊት ይሖዋ አምላክን ቀኑን ሙሉ ለዘላለም የማወደስ ፍላጎት ነበረው።
4. መዝሙር 145 የትኞቹ ክሶች ሐሰት መሆናቸውን ያጋልጣል?
4 መዝሙር 145 አምላክ ፍጥረታቱን ነጻነት የሚነፍግ ጨቋኝ ገዥ ነው በማለት ሰይጣን ላቀረበው ክስ አሳማኝ መልስ ይሰጣል። (ዘፍጥረት 3:1-5) እንዲሁም ሰዎች አምላክን የሚታዘዙት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ እንጂ ስለሚወዱት አይደለም የሚለውን የሰይጣንን ክስ ውሸተኝነት ያጋልጣል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ልክ እንደ ዳዊት ለዲያብሎስ የሐሰት ክሶች መልስ ይሰጣሉ። ይሖዋን ለዘላለም የማወደስ ፍላጎት ስላላቸው በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የሚያገኙትን የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንደ ውድ ሀብት ይመለከቱታል። እስከ አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን፣ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው በመጠመቅ እንዲሁም በፍቅርና በታዛዥነት ተነሳስተው እርሱን በማገልገል እያወደሱት ነው።—ሮሜ 5:8፤ 1 ዮሐንስ 5:3
5, 6. ይሖዋን ለማወደስና ለማመስገን የሚያስችሉ የትኞቹ አጋጣሚዎች አሉ?
5 የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን እርሱን ለመባረክና ለማወደስ ምን ያህል በርካታ አጋጣሚዎች እንዳሉን አስብ። በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያነበብነው ነገር ልባችንን በጥልቅ ሲነካው በጸሎት ልናወድሰው እንችላለን። ይሖዋ ሕዝቦቹን የያዘበትን መንገድ ስንመለከት ወይም ዕጹብ ድንቅ የፍጥረት ሥራዎቹን ተመልክተን በአድናቆት ስንዋጥ ከልብ የመነጨ ውዳሴና ምስጋና ልናቀርብለት እንችላለን። እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወይም በግል ጭውውቶች ወቅት ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ስለ ዓላማዎቹ ስንወያይ አምላካችንን ይሖዋን እናወድሰዋለን። እንዲያውም ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ የምናደርጋቸው ‘መልካም ሥራዎች’ በሙሉ ይሖዋ እንዲወደስ ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 5:16
6 እንዲህ ካሉት መልካም ሥራዎች መካከል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የይሖዋ ሕዝቦች ድህነት ባጠቃቸው አገሮች የአምልኮ ቦታዎችን በመገንባት የሚያከናውኑት ሥራ ይገኝበታል። ከእነዚህ የግንባታ ሥራዎች ውስጥ አብዛኞቹ ሊከናወኑ የቻሉት በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን አንዳንዶች ወደነዚህ ቦታዎች በፈቃደኝነት ሄደው በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራ ላይ በቀጥታ ተካፍለዋል። ከሁሉም የላቀው መልካም ሥራ ግን የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ይሖዋን ማወደስ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በመዝሙር 145 ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ቁጥሮች እንደሚጠቁሙት ዳዊት ለአምላክ አገዛዝ አድናቆት የነበረው ከመሆኑም በላይ መንግሥቱን በማወደስ ተናግሯል። (መዝሙር 145:11, 12) አንተስ ለአምላክ ፍቅራዊ አገዛዝ የዳዊትን ዓይነት የአድናቆት ስሜት አለህ? ስለመንግሥቱ ለሌሎች አዘውትረህ ትናገራለህ?
የአምላክን ታላቅነት የሚያሳዩ ምሳሌዎች
7. ይሖዋን የምናወድስበትን አንዱን ዋነኛ ምክንያት ተናገር።
7 መዝሙር 145:3 ይሖዋን የምናወድስበትን አንዱን ዋነኛ ምክንያት ይነግረናል። ዳዊት “እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም” በማለት ዘምሯል። ይሖዋ ለታላቅነቱ ገደብ የለውም። የሰው ልጆች መርምረው ሊደርሱበት፣ ሊረዱት ወይም ይህን ያህል ነው ሊሉት አይችሉም። ቢሆንም ታላቅነቱን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን በመመርመር ጥቅም ልናገኝ እንደምንችል አያጠራጥርም።
8. አጽናፈ ዓለም የይሖዋን ታላቅነትና ኃይል በሚመለከት ምን ይናገራል?
8 ደማቅ ብርሃን ከሚንጸባረቅበት ከተማ ወጣ ብለህ ጥርት ያለውን የምሽት ሰማይ የተመለከትክበትን ጊዜ ለማስታወስ ሞክር። በጠቆረው ሰማይ ላይ በሚታዩት ለቁጥር የሚያታክቱ ከዋክብት ብዛት አልተደመምክም? እነዚህን የጠፈር አካላት በመፍጠር ታላቅነቱን ያሳየውን ይሖዋን ለማወደስ አልተገፋፋህም? ይሁን እንጂ የተመለከትከው ምድራችን በምትገኝበት ጋላክሲ ውስጥ ካሉት ከዋክብት መካከል በጣም ጥቂቶቹን ብቻ ነው። በተጨማሪም ከመቶ ቢሊዮን የሚበልጡ ጋላክሲዎች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ያለ ቴሌስኮፕ መመልከት የሚቻለው ሦስቱን ብቻ ነው። በእርግጥም በጣም ሰፊ በሆነው አጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኙት ኅልቆ መሳፍርት የሌላቸው ጋላክሲዎችና ከዋክብት ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበትን ኃይልና የማይመረመር ታላቅነቱን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።—ኢሳይያስ 40:26
9, 10. (ሀ) ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ታላቅነት የታየው እንዴት ነው? (ለ) የኢየሱስ ትንሣኤ እምነታችንን የሚያጠነክረው እንዴት ነው?
9 ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተያያዘም የይሖዋ ታላቅነት የታየባቸውን አጋጣሚዎች እንመልከት። ይሖዋ ልጁን ሲፈጥረውና ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ‘ዋና ሠራተኛው’ አድርጎ ሲጠቀምበት ታላቅነቱ ታይቷል። (ምሳሌ 8:22-31) አንድያ ልጁን ለመላው የሰው ዘር ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱም የፍቅሩን ታላቅነት የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) የሰው ልጆች ሙሉ በሙሉ ሊረዱት የማይችሉት ሌላው የይሖዋ ታላቅ ሥራ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ የተሰጠው ክብር የተላበሰ የማይሞት መንፈሳዊ አካል ነው።—1 ጴጥሮስ 3:18
10 የኢየሱስ ትንሣኤ ሊመረመር የማይችለውን የይሖዋን ታላቅነት የተለያዩ ገጽታዎች ያሳያል። ይሖዋ የማይታዩትንም ሆነ የሚታዩትን ፍጥረታት ወደ ህልውና ከማምጣት ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ያከናወነውን ሥራ በሙሉ እንዲያስታውስ እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። (ቆላስይስ 1:15, 16) ይህም ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታትን፣ አጽናፈ ዓለሙን፣ ምድራችንንና በላይዋ ላይ የሚገኘውን ሕይወት በሙሉ ይጨምራል። ይሖዋ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይም ሆነ በምድር ስለተፈጸሙት ነገሮች የነበረውን እውቀት ብቻ ሳይሆን ፍጹም ሰብዓዊ ፍጡር ሆኖ ያሳለፈውን ሕይወትም እንዲያስታውስ አድርጎታል። አዎን፣ የኢየሱስ ትንሣኤ የይሖዋን የማይመረመር ታላቅነት በግልጽ ያሳያል። ከዚህም በላይ ይህ ታላቅ ሥራ ትንሣኤ እንደሚኖር ዋስትና የሚሰጠን ሲሆን በአምላክ መታሰቢያ ውስጥ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙታን እንደሚነሱ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 17:31
ታላላቅና ድንቅ ሥራዎች
11. ይሖዋ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጀመረው ታላቅ ሥራ ምን ነበር?
11 ይሖዋ ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ በርካታ ታላላቅና ድንቅ ሥራዎችን አከናውኗል። (መዝሙር 40:5) በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በጰንጠቆስጤ ዕለት ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብሎ የሚጠራውን በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን ያቀፈ አዲስ ብሔር ፈጥሯል። (ገላትያ 6:16) ይህ አዲስ መንፈሳዊ ብሔር በወቅቱ በነበረው ዓለም ያደረገው መስፋፋት በጣም አስደናቂ ነበር። የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ በተስፋፋው ክህደት ሕዝበ ክርስትና ወደ ሕልውና ብትመጣም ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም ታላላቅ ሥራዎችን ማከናወኑን ቀጥሎ ነበር።
12. መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ በሚነገሩ በብዙ ቋንቋዎች መተርጎሙ የምን ማረጋገጫ ነው?
12 ለምሳሌ ያህል፣ መላው መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ጊዜያችን ተጠብቆ የቆየ ሲሆን ቀስ በቀስ በምድር ላይ በሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ የሚከናወነው ከሰይጣን ወኪሎች የሚሠነዘረው የሞት ማስፈራሪያና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉም ነበር። ታላቅነቱ ወደር የሌለው ይሖዋ ፈቃዱ ባይሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ ከ2,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች መተርጎም ባልቻለ ነበር ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን!
13. ከ1914 አንስቶ ከመንግሥቱ ዓላማዎች ጋር በተያያዘ የይሖዋ ታላቅነት የታየው እንዴት ነው?
13 የይሖዋ ታላቅነት ከመንግሥቱ ዓላማዎች ጋር በተያያዘም ታይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1914 ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በሰማይ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በሰይጣንና በአጋንንቱ ላይ እርምጃ በመውሰድ ከሰማይ ያባረራቸው ሲሆን ወደ ጥልቁ እስከሚጣሉ ድረስ በምድር አካባቢ ተወስነው ይቆያሉ። (ራእይ 12:9-12፤ 20:1-3) ከዚያን ጊዜ አንስቶ በመንፈስ በተቀቡት የኢየሱስ ተከታዮች ላይ የሚደርሰው ስደት ጨምሯል። ይሁን እንጂ ክርስቶስ በዓይን በማይታይ ሁኔታ መግዛት ከጀመረበት ከዚህ ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ድጋፍ አልተለያቸውም።—ማቴዎስ 24:3፤ ራእይ 12:17
14. ይሖዋ በ1919 ምን ድንቅ ሥራ አከናውኗል? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
14 ይሖዋ ታላቅነቱን ያሳየበትን ሌላ ድንቅ ሥራ ያከናወነው ደግሞ በ1919 ነው። በወቅቱ መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ተገትቶ የነበረውን በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ተከታዮች ዳግመኛ እንዲያንሰራሩ አድርጓቸዋል። (ራእይ 11:3-11) ከዚያ ወዲህ ቅቡዓኑ በሰማይ ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ምሥራች በቅንዓት መስበካቸውን አላቋረጡም። የ144,000ዎቹን ቁጥር ለማሟላት ሌሎች ቅቡዓንን የማሰባሰቡ ሥራም ተከናውኗል። (ራእይ 14:1-3) እንዲሁም ይሖዋ በመንፈስ በተቀቡት የክርስቶስ ተከታዮች አማካኝነት ‘ለአዲስ ምድር’ ማለትም ጽድቅ ወዳድ ለሆነ አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ መሠረት ጥሏል። (ራእይ 21:1) ሆኖም ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ የዚህ “አዲስ ምድር” ዕጣ ምን ይሆናል?
15. ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትኛውን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ያከናውናሉ? ምንስ ውጤት አግኝተዋል?
15 በ1935 የነሐሴ 1 እና የነሐሴ 15 መጠበቂያ ግንብ እትሞች በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ ስለተጠቀሱት “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሚያብራሩ ርዕሶች ይዘው ወጥተው ነበር። ቅቡዓን ክርስቲያኖች እነዚህን የይሖዋ አምላኪዎች ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገንና ከቋንቋ ሁሉ እየፈለጉ ከእነርሱ ጋር እንዲተባበሩ ማድረግ ጀመሩ። እነዚህ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከመጪው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት ተርፈው ‘የአዲሲቱ ምድር’ አባላት በመሆን በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። (ራእይ 7:9-14) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በግንባር ቀደምትነት በሚመሩት የመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ አማካኝነት በአሁኑ ወቅት ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ። ከሰይጣንና ምግባረ ብልሹ ከሆነው የእርሱ ዓለም የማያቋርጥ ተቃውሞ እያለም ለተገኘው ይህን የመሰለ እድገት መመስገን የሚገባው ማን ነው? (1 ዮሐንስ 5:19) በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይህን ሁሉ ሊያከናውን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 60:22፤ ዘካርያስ 4:6
የይሖዋ ግርማ እና ክብር
16. ሰዎች ‘የይሖዋን ግርማና ክብር’ ማየት የማይችሉት ለምንድን ነው?
16 የይሖዋ ድንቅና ታላላቅ ሥራዎች ዓይነታቸው ምንም ይሁን ምን መቼም የሚረሱ አይደሉም። ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፣ ኃይልህንም ያወራሉ። የቅድስናህን ግርማ ክብር ይናገራሉ፣ ተኣምራትህንም ይነጋገራሉ። የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፣ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፣ ብርታትህንም ይነጋገራሉ።” (መዝሙር 145:4-6) ሆኖም “እግዚአብሔር መንፈስ” ስለሆነና ማንም ሊያየው ስለማይችል ዳዊት ስለ ይሖዋ ግርማና ክብር ምን ያህል ማወቅ ይችላል?—ዮሐንስ 1:18፤ 4:24
17, 18. ዳዊት ስለ ‘ይሖዋ ግርማና ክብር’ ያለውን አድናቆት ማሳደግ የቻለው እንዴት ነበር?
17 ዳዊት አምላክን ማየት ባይችልም ስለ ይሖዋ ግርማ ያለውን አድናቆት ማሳደግ የሚችልባቸው የተለያዩ መንገዶች ነበሩት። ለምሳሌ ያህል፣ ክፉውን ዓለም በውኃ መጥለቅለቅ እንዳጠፋ የሚናገረውን ታሪክ የመሳሰሉ የአምላክን ታላላቅ ሥራዎች የሚያሳዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባዎችን ማንበብ ይችል ነበር። እንዲሁም አምላክ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነጻ በማውጣት የግብፅን የሐሰት አማልክት እንዴት እንዳዋረደ ሳያውቅ አይቀርም። እንዲህ ያሉት ድርጊቶች የይሖዋ ክብርና ታላቅነት መግለጫዎች ናቸው።
18 ዳዊት ለይሖዋ ግርማ ያለውን አድናቆት ያሳደገው ቅዱሳን ጽሑፎችን በማንበብ ብቻ ሳይሆን ባነበበው ነገር ላይ በማሰላሰል ጭምር እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ሕጉን ለእስራኤላውያን በሰጠበት ወቅት ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር አሰላስሎ ሊሆን ይችላል። በወቅቱ ነጎድጓድ፣ መብረቅ፣ ከባድ ደመናና ከፍተኛ የመለከት ድምፅ ታይቶና ተሰምቶ ነበር። የሲና ተራራ ይናወጥና ይጨስ ነበር። በተራራው ግርጌ ተሰብስበው የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋ በመላእክቱ አማካኝነት በእሳትና በደመና መሃል ‘አሥርቱን ቃላት’ ሲነግራቸው አዳምጠዋል። (ዘዳግም 4:32-36፤ 5:22-24፤ 10:4፤ ዘጸአት 19:16-20፤ የሐዋርያት ሥራ 7:38, 53) የይሖዋን ታላቅነት የሚያሳይ እንዴት ያለ ክስተት ነበር! በእነዚህ ታሪኮች ላይ የሚያሰላስሉ የአምላክ ቃል አፍቃሪዎች ‘በይሖዋ ግርማና ክብር’ መደመማቸው አይቀርም። ደግሞም በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ታላቅነት የሚያሳዩ የተለያዩ ክብራማ ራእዮችን የያዘ የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስ አለን።—ሕዝቅኤል 1:26-28፤ ዳንኤል 7:9, 10፤ ራእይ ምዕራፍ 4
19. ለይሖዋ ግርማ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ምን ሊረዳን ይችላል?
19 ዳዊት ስለ ይሖዋ ክብር ያለውን አድናቆት ማሳደግ የሚችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕግ በማጥናት ነው። (ዘዳግም 17:18-20፤ መዝሙር 19:7-11) እስራኤላውያን የይሖዋን ሕግ መታዘዛቸው ቅዱስና ከአሕዛብ የተለዩ ያደርጋቸው ነበር። (ዘዳግም 4:6-8) እኛም እንደ ዳዊት ቅዱሳን ጽሑፎችን አዘውትረን የምናነብ፣ የምናሰላስልባቸውና በትጋት የምናጠናቸው ከሆነ ለይሖዋ ክብርና ግርማ ያለን አድናቆት ይጨምራል።
የይሖዋ ባሕርያት ታላቅነቱን ያጎላሉ
20, 21. (ሀ) መዝሙር 145:7-9 የይሖዋን ታላቅነት የሚያጎላው ከየትኞቹ ባሕርያቱ አንጻር ነው? (ለ) እነዚህ የአምላክ ባሕርያት እርሱን ለሚወዱት ሁሉ ምን ጥቅም ያስገኙላቸዋል?
20 እስከ አሁን እንደተመለከትነው የመዝሙር 145 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ቁጥሮች ወደር የለሽ በሆነው ታላቅነቱ ላከናወናቸው ነገሮች ይሖዋን የምናወድስበትን አሳማኝ ምክንያት ይዘዋል። ከ7 እስከ 9 ያሉት ቁጥሮች ደግሞ የይሖዋን ባሕርያት በመጥቀስ ታላቅነቱን ያጎላሉ። ዳዊት እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “የቸርነትህን [“የጥሩነትህን፣” NW] ብዛት መታሰብ ያወጣሉ፣ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ። እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፣ ከቁጣ የራቀ፣ ምሕረቱም ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር [“ለሁሉም ጥሩ፣” NW] ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው።”
21 እዚህ ላይ ዳዊት በመጀመሪያ የጠቀሰው ሰይጣን ዲያብሎስ ጥያቄ ያስነሳባቸውን የይሖዋ ባሕርያት ይኸውም ጥሩነቱንና ጽድቁን ነው። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት ያሉት መሆኑ እርሱን ለሚወዱትና ለመንግሥቱ ለሚገዙት ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል? የይሖዋ ጥሩነትና የጽድቅ አገዛዙ ለአምላኪዎቹ ከፍተኛ ደስታ ስለሚያመጣላቸው እርሱን ያለማቋረጥ ያወድሳሉ። ከዚህም በላይ ይሖዋ ጥሩነቱን የሚያሳየው “ለሁሉም” ነው። ይህም ሌሎች በርካታ ሰዎች ጊዜው ከማለፉ በፊት ንስሐ ገብተው እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ተስፋ እናደርጋለን።—የሐዋርያት ሥራ 14:15-17
22. ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚይዘው እንዴት ነው?
22 ዳዊት፣ ይሖዋ በሙሴ ፊት ባለፈ ጊዜ “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” በማለት ለጠቀሳቸው ባሕርያቱም አድናቆት ነበረው። (ዘጸአት 34:6) በመሆኑም “እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፣ ከቁጣ የራቀ፣ ምሕረቱም [“ፍቅራዊ ደግነቱ፣” NW] ብዙ ነው” ለማለት ችሏል። ይሖዋ ታላቅነቱ ይህ ነው የማይባል ቢሆንም ሰብዓዊ አገልጋዮቹን በርኅራኄ በመያዝ ያከብራቸዋል። እንዲሁም መሐሪ ስለሆነ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ ከቁጣ የራቀ ወይም ታጋሽ በመሆኑ አገልጋዮቹን ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ከመግባት ሊያግዷቸው የሚችሉ ድክመቶቻቸውን እንዲያስወግዱ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—2 ጴጥሮስ 3:9, 13, 14
23. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን የይሖዋ ባሕርይ እንመረምራለን?
23 ዳዊት ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ዘላለማዊ ፍቅር ተናግሯል። እንዲያውም የመዝሙር 145 ቀሪ ክፍል ይሖዋ ይህንን ባሕርይ እንዴት እንደሚያንጸባርቅና ታማኝ አገልጋዮቹ ለፍቅራዊ ደግነቱ ምን ምላሽ እንደሚሰጡ የሚያሳይ ነው። እነዚህ ነጥቦች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ይሖዋን ‘ቀኑን ሙሉ’ ለማወደስ የሚያስችሉን አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?
• የይሖዋ ታላቅነት ወደር የለሽ መሆኑን የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
• ለይሖዋ ግርማና ክብር ያለንን አድናቆት ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ የሚገኙት ጋላክሲዎች የይሖዋ ታላቅነት መግለጫዎች ናቸው
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Courtesy of Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ታላቅነት የታየው እንዴት ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን በሲና ተራራ አጠገብ ሕጉን በተቀበሉ ጊዜ የይሖዋን ግርማና ክብር የሚያሳዩ ክስተቶችን አይተዋል