ይሖዋ እረኛችን ነው
“እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም።”—መዝሙር 23:1
1-3. ዳዊት ይሖዋን ከእረኛ ጋር ማነጻጸሩ የማያስደንቀው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ሕዝቡን ስለሚጠብቅበት መንገድ ተናገር ብትባል ምን ትል ነበር? ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያደርገውን ፍቅራዊና ርኅራኄ የተሞላበት እንክብካቤ ከምን ጋር ማነጻጸር ትችላለህ? ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት፣ መዝሙራዊው ንጉሥ ዳዊት በልጅነቱ ከነበረው ሥራ ጋር በማነጻጸር ውብ በሆነ መንገድ ስለ ይሖዋ ገልጿል።
2 ዳዊት በወጣትነቱ እረኛ ስለነበር ለበጎች እንዴት እንክብካቤ እንደሚደረግ ግንዛቤ አለው። እንዲሁም በጎች ጠባቂ ከሌላቸው በቀላሉ ሊጠፉና የዘራፊ ወይም የአውሬ ሲሳይ ሊሆኑ እንደሚችሉ በሚገባ ያውቃል። (1 ሳሙኤል 17:34-36) ያለ አሳቢ እረኛ፣ በጎቹ ጥሩ የግጦሽ መሬት ላያገኙ ይችላሉ። ዳዊት በጎችን በመምራት፣ በመንከባከብና በመመገብ ያሳለፈውን ረጅም ጊዜ በተመለከተ የኋላ ኋላ አስደሳች ትዝታ እንደነበረው ምንም አያጠራጥርም።
3 በመሆኑም ዳዊት ይሖዋ ለሕዝቡ ስለሚያደርገው እንክብካቤ በመንፈስ አነሳሽነት ሲጽፍ የእረኛን ተግባር ማስታወሱ ምንም አያስደንቅም። እርሱ የጻፈው 23ኛው መዝሙር የሚጀምረው “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም” በሚሉት ቃላት ነው። በመጀመሪያ ይህ ንጽጽር ተስማሚ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚያም እረኛ በጎቹን በሚንከባከብበት መንገድ ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚንከባከብ የሚገልጸውን በመዝሙር 23 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንመረምራለን።—1 ጴጥሮስ 2:25
ተስማሚ ንጽጽር
4, 5. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ በጎች ባሕርይ ምን ይገልጻል?
4 ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ መጠሪያዎች ተሰጥተውታል፤ ይሁን እንጂ “እረኛ” የሚለው ስያሜ ፍቅሩንና ርኅራኄውን ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። (መዝሙር 80:1) ይሖዋ እረኛ መባሉ ተስማሚ እንደሆነ በይበልጥ ለመረዳት ሁለት ነገሮችን ማወቃችን ይጠቅመናል፤ እነርሱም:- የበጎችን ባሕርይ ማወቅ እንዲሁም የአንድን ጥሩ እረኛ ግዴታዎችና ባሕርያት መገንዘብ ናቸው።
5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ በጎች ባሕርይ በተዘዋዋሪ መንገድ ብዙ ጊዜ ተገልጿል። በጎች እረኛቸው ለሚያሳያቸው ፍቅር ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጡ (2 ሳሙኤል 12:3)፣ ሰላማዊ እንደሆኑ (ኢሳይያስ 53:7) እና ራሳቸውን መጠበቅ እንደማይችሉ (ሚክያስ 5:8) ተጽፏል። ለበርካታ ዓመታት በግ ሲያረቡ የኖሩ አንድ ጸሐፊ “አንዳንዶች እንደሚገምቱት በጎች ‘ለራሳቸው እንክብካቤ’ አያደርጉም። ከማንኛውም ዓይነት ከብት ይበልጥ የማያቋርጥ ትኩረትና ልዩ እንክብካቤ ይፈልጋሉ” ብለዋል። እነዚህ ደካማ ፍጥረታት በሕይወት እንዲቆዩ አሳቢ እረኛ ያስፈልጋቸዋል።—ሕዝቅኤል 34:5
6. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የጥንት ዘመን እረኛን ውሎ የገለጸው እንዴት ነው?
6 የጥንት ዘመን እረኛ ውሎ ምን ይመስል ነበር? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል:- “በጠዋት በጎቹን ከጉረኖ ያወጣና ፊት ፊታቸው እየሄደ ወደሚመገቡበት የግጦሽ መሬት ያደርሳቸዋል። በዚያም አንድም በግ ከመንጋው እንዳይለይ ጥንቃቄ እያደረገ ቀኑን ሙሉ ሲጠብቃቸው ይውላል፤ በተጨማሪም ለጊዜው እንኳን አንድ በግ ከእይታው ቢሰወርና ከመንጋው ቢነጠል እስከሚያገኘው ድረስ በትጋት ፈልጎ ይመልሰዋል። . . . ሲመሽ መንጋውን ወደ ጉረኖ ያስገባል፤ በሚገቡበት ጊዜ የጠፋ በግ እንዳለ ለማረጋገጥ በር ላይ ሆኖ በዘንጉ እየታገዘ ይቆጥራቸዋል። . . . አውሬ እንዳያጠቃቸው ወይም ሌባ አድብቶ እንዳይሰርቃቸው አብዛኛውን ሌሊት በረታቸውን በመጠበቅ ያሳልፋል።”a
7. አንዳንድ ጊዜ እረኛ ከወትሮው የበለጠ ትዕግሥትና ርኅራኄ ማሳየት የሚገባው ለምንድን ነው?
7 አንዳንድ ጊዜ በጎች፣ በተለይ ደግሞ እርጉዞችና ግልገሎች ሲሆኑ ይበልጥ ትዕግሥትና ርኅራኄ ይሻሉ። (ዘፍጥረት 33:13) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ እንዲህ ይላል:- “ብዙውን ጊዜ በጎች የሚወልዱት ራቅ ብለው በተራራ ግርጌ ነው። እረኛው እናቲቱን በግ ይበልጥ ለጥቃት በምትጋለጥበት በዚህ ወቅት ላይ በንቃት ይጠብቃታል፤ ግልገሉንም አንስቶ በመሸከም ከመንጋው ጋር ይቀላቅለዋል። መራመድ እስከሚጀምር ድረስ በክንዱ ይሸከመዋል ወይም አቅፎ መጎናጸፊያውን ይደርብለታል።” (ኢሳይያስ 40:10, 11) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጥሩ እረኛ ጠንካራ ሆኖም ርኅሩኅ መሆን ይገባዋል።
8. ዳዊት በይሖዋ እንዲተማመን ያደረጉትን የትኞቹን ምክንያቶች ጠቅሷል?
8 “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው” የሚለው አነጋገር በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን ጥሩ አድርጎ አይገልጸውም? መዝሙር 23ን ስንመረምር ይሖዋ ልክ እንደ እረኛ ጥንካሬ እና ርኅራኄ በማሳየት እንዴት እንደሚንከባከበን እንማራለን። በቁጥር 1 ላይ ዳዊት፣ አምላክ በጎቹ ‘አንዳች እንዳይጐድልባቸው’ ሲል አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ እንደሚያደርግ እምነት እንዳለው ገልጿል። ከቁጥር 1 በኋላ ባሉት ጥቅሶች ላይ ደግሞ ዳዊት እንዲህ ያለ እምነት እንዲኖረው ያደረጉትን ሦስት ምክንያቶች ማለትም ይሖዋ እንደሚመራ፣ እንደሚጠብቅና እንደሚመግብ ተናግሯል። እስቲ እነዚህን ነጥቦች አንድ በአንድ እንመርምር።
“ይመራኛል”
9. ዳዊት ስለ ምን ዓይነት ሰላማዊ ስፍራ ተናግሯል? በጎች እንዲህ ያለውን ቦታ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?
9 በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ሕዝቡን ይመራል። ዳዊት “በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 23:2, 3) እዚህ ላይ ዳዊት፣ ሁሉ ነገር በተትረፈረፈበት ስፍራ በሰላም ስላረፈ መንጋ በመናገር አርኪና አስደሳች ስለሆነ እንዲሁም ደኅንነት ስለሰፈነበት ቦታ ገልጿል። “መስክ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “አስደሳች ቦታ” ማለትም ሊሆን ይችላል። በጎች በሰላም ሊያርፉ የሚችሉበትን የሚያድስ ቦታ ራሳቸው ፈልገው ማግኘት አይችሉም። እረኛቸው እንዲህ ወዳለው “አስደሳች ቦታ” መርቶ ሊወስዳቸው ይገባል።
10. አምላክ በእኛ ላይ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው?
10 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሚመራን እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ምሳሌ በመሆን ነው። ቃሉ “እግዚአብሔርን ምሰሉ” በማለት ያሳስበናል። (ኤፌሶን 5:1) በእነዚህ ቃላት ዙሪያ ባሉት ጥቅሶች ላይ ይቅር ባይነት፣ ርኅራኄና ፍቅር ተገልጸዋል። (ኤፌሶን 4:32፤ 5:2) ይሖዋ እነዚህን ውድ ባሕርያት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ እንደሚሆነን ምንም አያጠራጥርም። እርሱን እንድንመስል መጠየቁ የማይመስል ነገር ይሆን? በፍጹም። እንዲያውም ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተሰጠን ምክር ይሖዋ በእኛ ላይ ምን ያህል እምነት እንዳለው የሚያሳይ ግሩም መግለጫ ነው። በምን መንገድ? የተፈጠርነው በአምላክ አምሳል ማለትም ጥሩ ሥነ ምግባር የማሳየትና መንፈሳዊ ሰው የመሆን ችሎታ እንዲኖረን ተደርጎ ነው። (ዘፍጥረት 1:26) ስለዚህ ይሖዋ፣ ፍጹማን ባንሆንም እንኳን እርሱ ያሳያቸውን ባሕርያት ለማዳበር የሚረዳን ውስጣዊ ችሎታ እንዳለን ያውቃል። እስቲ አስበው፣ አፍቃሪው አምላካችን ልክ እንደ እርሱ መሆን እንደምንችል እምነት አለው። የእርሱን ፈለግ ከተከተልን በምሳሌያዊ አነጋገር አስደሳች ወደሆነ ‘የዕረፍት’ ቦታ ይመራናል። የአምላክ ሞገስ እንዳለን ማወቃችን የሚያስገኘውን ሰላም በማጣጣም በዚህ ዓመጸኛ ዓለም ውስጥ ‘ያለ ሥጋት እናድራለን።’—መዝሙር 4:8፤ 29:11
11. ይሖዋ በጎቹን ሲመራ ግምት ውስጥ የሚያስገባው ነገር ምንድን ነው? ይህስ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ላይ የሚንጸባረቀው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ ምንጊዜም እኛን የሚመራው በርኅራኄና በትዕግሥት ነው። እረኛ የበጎቹን የአቅም ገደብ ከግምት ውስጥ በማስገባት ‘በጒዞ ዐቅማቸው ልክ’ ይመራቸዋል። (ዘፍጥረት 33:14) ይሖዋም በተመሳሳይ በጎቹን ‘በጒዞ ዐቅማቸው ልክ’ ይመራል። አቅማችንንና ሁኔታችንን ከግምት ውስጥ ያስገባል። ስለዚህ እርምጃውን ያስተካክላል እንጂ በፍጹም ከምንችለው በላይ አይጠብቅብንም። እርሱ የሚፈልገው የምናደርገውን ነገር በሙሉ ልባችን እንድናከናውን ነው። (ቈላስይስ 3:23) ነገር ግን ዕድሜህ በመግፋቱ ምክንያት የቀድሞውን ያህል ማከናወን ባትችልስ? ወይም ደግሞ አቅምህን የሚገድብ ከባድ ሕመም ቢኖርብህስ? ይሖዋ የሚፈልገው የሙሉ ነፍስ አገልግሎት እንድናቀርብ መሆኑን ማወቃችን በተለይ እንዲህ ባሉት ወቅቶች ያጽናናናል። ሁለት ነፍሶች ፍጹም አንድ ዓይነት ሊሆኑ አይችሉም። በሙሉ ነፍስ ማገልገል ማለት የአንተ አቅም የፈቀደውን ያህል ማገልገል ወይም ኃይልህንና ጉልበትህን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ አገልግሎት ማዋል ማለት ነው። የጉዞ አቅማችንን ሊያዳክሙ የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም ይሖዋ በሙሉ ልባችን የምናቀርበውን አምልኮ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ማርቆስ 12:29, 30
12. ይሖዋ በጎቹን ‘በጒዞ ዐቅማቸው ልክ’ እንደሚመራ ምሳሌ የሚሆነን የትኛው የሙሴ ሕግ ነው?
12 ይሖዋ በጎቹን ‘በጒዞ ዐቅማቸው ልክ’ እንደሚመራ በምሳሌ ለማየት በሙሴ ሕግ ውስጥ ስለ አንዳንድ የበደል መሥዋዕቶች የተጠቀሰውን ሐሳብ እንመልከት። ይሖዋ የሚፈልገው በምስጋና ከተሞላ ልብ በመነሳሳት የሚቀርቡ መልካም መሥዋዕቶችን ነበር። በተጨማሪም መሥዋዕቶቹ እንደ አቅራቢው አቅም የተለያዩ ናቸው። ሕጉ “ሰውየው . . . በግ ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች . . . ያቅርብ” ይላል። ሁለት ዋኖሶች እንኳን ማቅረብ ካቃተውስ? ጥቂት “የላመ ዱቄት” መስጠት ይችላል። (ዘሌዋውያን 5:7, 11) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አምላክ መሥዋዕት ከሚያቀርበው ሰው አቅም በላይ የሆነ ነገር አይፈልግም ነበር። ዛሬም አምላክ አልተለወጠም፤ በመሆኑም መስጠት ከምንችለው በላይ ፈጽሞ እንደማይጠብቅብን ማወቃችን ያጽናናናል። ከዚህ ይልቅ ማድረግ የምንችለውን ነገር በመቀበል ይደሰታል። (ሚልክያስ 3:6) እንዲህ ባለ አሳቢ እረኛ መመራት እንዴት ደስ ይላል!
“አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም”
13. ዳዊት ከይሖዋ ጋር በጣም እንደሚቀራረብ የሚያሳይ በመዝሙር 23:4 ላይ የተጠቀመበት አባባል ምንድን ነው? ይህስ የሚያስገርም ያልሆነው ለምንድን ነው?
13 ዳዊት እንዲተማመን ያደረገው ሁለተኛው ምክንያት ይሖዋ በጎቹን የሚጠብቅ መሆኑ ነው። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋር ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል።” (መዝሙር 23:4) እዚህ ላይ ዳዊት ይሖዋን “አንተ” በሚለው ተውላጠ ስም በመጥራት በጣም እንደሚቀርበው አሳይቷል። ይህ ምንም አያስገርምም፤ ምክንያቱም ዳዊት በመከራ እንዲጸና አምላክ እንዴት እንደረዳው እየተናገረ ነው። ዳዊት ብዙ ጊዜ በጨለማ ሸለቆዎች ውስጥ አልፏል፤ ወይም በሌላ አነጋገር ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀባቸው በርካታ ጊዜያት ነበሩ። ይሁንና አስፈላጊ በሆነ ወቅት እርምጃ የሚወስድባቸውን “በትር” እና “ምርኵዝ” የያዘው አምላክ፣ ከእርሱ ጋር እንደሆነ ይሰማው ስለነበር ፍርሃት እንዲያሸንፈው አልፈቀደም። ዳዊት ጥበቃ እንደሚያገኝ ማወቁ እንዳጽናናውና ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ እንዳደረገው ምንም ጥርጥር የለውም።b
14. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ጥበቃ በተመለከተ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል? ይሁን እንጂ ይህ ምን ማለት አይደለም?
14 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በጎቹን የሚጠብቀው እንዴት ነው? ጋኔንም ይሁን ሰው ማንኛውም ተቃዋሚ የይሖዋን በጎች ከምድር ላይ ለማጥፋት በጭራሽ እንደማይሳካለት መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። ይሖዋ ይህ እንዲሆን ፈጽሞ አይፈቅድም። (ኢሳይያስ 54:17፤ 2 ጴጥሮስ 2:9) እንዲህ ሲባል ግን እረኛችን ከየትኛውም ዓይነት አደጋ ይጠብቀናል ማለት አይደለም። እንደማንኛውም ሰው ችግር ያጋጥመናል፤ እንዲሁም ሁሉም ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸው ተቃውሞ ይደርስብናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ ያዕቆብ 1:2) በምሳሌያዊ አነጋገር ‘በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ የሄድንባቸው’ ጊዜያት ይኖሩ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በስደት ወይም በአንዳንድ የጤና እክሎች ምክንያት ሞት አፋፍ ላይ የደረስንበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። ወይም ደግሞ በጣም የምንወደው ሰው በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ አሊያም በሞት አንቀላፍቶ ሊሆን ይችላል። ሁሉ ነገር ጨለማ በሚመስለን ጊዜ እረኛችን ከእኛ ጋር ይሆናል፤ እንዲሁም ይጠብቀናል። እንዴት?
15, 16. (ሀ) ይሖዋ የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች እንድንወጣ የሚረዳን በምን መንገዶች ነው? (ለ) ይሖዋ በችግር ጊዜ እንዴት እንደሚረዳን የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።
15 ይሖዋ በተአምር ጣልቃ እንደሚገባ ተስፋ አልሰጠም።c ቢሆንም ይሖዋ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ዓይነት እንቅፋት እንድናሸንፍ እንደሚረዳን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። አምላክ የሚያጋጥመንን “ልዩ ልዩ መከራ” ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:2-5) እረኛ በትሩን ወይም ምርኩዙን የሚጠቀምበት አውሬ ለማባረር ብቻ ሳይሆን በጎቹን ጠቆም እያደረገ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዙ ለማድረግ ነው። ይሖዋም በሁኔታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር በሥራ ላይ እንድናውል በወንድሞቻችን በኩል ሊጠቁመን ይችላል። እንዲሁም ለመጽናት የሚረዳንን ብርታት ይሰጠን ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 4:13) በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ከወትሮው የበለጠ “ታላቅ ኀይል” በመስጠት ያስታጥቀናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) የአምላክ መንፈስ ሰይጣን ሊያመጣብን የሚችለውን ማንኛውንም ፈተና እንድንቋቋም ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ይሖዋ ምንጊዜም ሊረዳን ዝግጁ መሆኑን ማወቁ አያጽናናም?
16 አዎን፣ በአደገኛ ሸለቆ ውስጥ ብንገባም የምንጓዘው ብቻችንን አይደለም። በመጀመሪያ ላይ ሙሉ በሙሉ ባንገነዘበውም እንኳን እረኛችን ከእኛ ጋር በመሆን አስፈላጊውን እርዳታ ይሰጠናል። አደገኛ የአንጎል ውስጥ እጢ እንዳለበት የታወቀለትን የአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ተሞክሮ እንመልከት። “እውነቱን ለመናገር መጀመሪያ ላይ ይሖዋ ቢያዝንብኝ ወይም ባይወደኝ ነው ስል አስቤ ነበር። ቢሆንም ከይሖዋ ላለመራቅ ቆርጬ ነበር። ከዚህ ይልቅ ጭንቀቴን አውጥቼ ወደ እርሱ ጮህኩ። ይሖዋም ረዳኝ፤ ብዙውን ጊዜ በወንድሞቼና በእህቶቼ አማካኝነት ያጽናናኝ ነበር። ብዙዎቹ ያለባቸውን ከባድ ሕመም እንዴት እንደተቋቋሙ በመግለጽ ማስተዋል እንዳገኝ ረድተውኛል። ይሰጡኝ የነበረው ሚዛናዊ አስተያየት በእኔ ላይ የተለየ ነገር እንዳልደረሰ እንዳስታውስ ረድቶኛል። ያደርጉልኝ የነበረው ጠቃሚ ድጋፍና ልብን በሚነካ መንገድ አንዳንድ እርዳታዎችን ለመስጠት ራሳቸውን ማቅረባቸው ይሖዋ እንዳላዘነብኝ አረጋግጦልኛል። በእርግጥ ከበሽታዬ ጋር የማደርገውን ትግል መቀጠል አለብኝ፤ መጨረሻው ምን እንደሚሆን አላውቅም። ይሁንና ይሖዋ ከእኔ ጋር እንደሆነና ላለብኝ ችግር አስፈላጊውን እርዳታ መስጠቱን እንደሚቀጥል አምኛለሁ።”
“በፊቴ ማዕድ አዘጋጀህልኝ”
17. ዳዊት በመዝሙር 23:5 ላይ ይሖዋን እንዴት አድርጎ ገልጾታል? ይህስ ስለ እረኛ ከተነገረው ምሳሌ ጋር ምን ግንኙነት አለው?
17 ዳዊት ይሖዋ በጎቹ እስኪጠግቡ ድረስ እንደሚመግባቸው በመናገር በእረኛው ላይ እንዲተማመን ያደረገውን ሦስተኛ ምክንያት ጠቅሷል። “ጠላቶቼ እያዩ፣ በፊቴ ማዕድ አዘጋጀህልኝ፤ ራሴን በዘይት ቀባህ፤ ጽዋዬም ሞልቶ ይፈስሳል” ብሏል። (መዝሙር 23:5) ዳዊት በዚህ ቁጥር ላይ እረኛውን ምግብና መጠጥ አትረፍርፎ እንደሚያቀርብ ለጋስ ጋባዥ አድርጎ ጠቅሶታል። አሳቢ እረኛና ለጋስ ጋባዥ የሚሉት ሁለት ምሳሌያዊ አነጋገሮች ምን ግንኙነት አላቸው? ጥሩ እረኛ መንጋው ‘አንዳች እንዳይጐድልበት’ ለማድረግ ሲል ለም የግጦሽ መሬትና በቂ የመጠጥ ውኃ የት እንደሚገኝ ማወቅ ይገባዋል።—መዝሙር 23:1, 2
18. ይሖዋ ለጋስ ጋባዥ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
18 እረኛችን ለጋስ ጋባዥ ነው? እንዴታ! እስቲ አሁን እያገኘን ስላለነው መንፈሳዊ ምግብ ጥራት፣ ብዛትና ዓይነት አስብ። ይሖዋ በታማኝና ልባም ባሪያ በኩል ጠቃሚ ጽሑፎችን እንዲሁም በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ትምህርት ሰጪ ፕሮግራሞችን ያቀርብልናል፤ እነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ያረኩልናል። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) በጭራሽ የመንፈሳዊ ምግብ እጥረት የለም። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን አዘጋጅቷል፤ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ጽሑፎች በ413 ቋንቋዎች ይገኛሉ። ይሖዋ ‘ከወተት’ ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች አንስቶ እስከ “ጠንካራ ምግብ” ይኸውም ጥልቀት እስካላቸው ትምህርቶች ድረስ መንፈሳዊ ምግቦችን በየዓይነቱ ያቀርብልናል። (ዕብራውያን 5:11-14) በመሆኑም ችግር ወይም ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ጉዳይ ሲያጋጥመን በአብዛኛው ልክ ስንፈልገው የነበረውን ነገር እናገኛለን። እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ምግብ ባይኖር ኖሮ ምን እንሆን ነበር? በእውነትም እረኛችን ለጋስ ሰጪ ነው!—ኢሳይያስ 25:6፤ 65:13
‘በይሖዋ ቤት እኖራለሁ’
19, 20. (ሀ) ዳዊት በመዝሙር 23:6 ላይ ምን እምነት እንዳለው ገልጿል? እኛስ እንዲህ ያለው እምነት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
19 ዳዊት በእረኛውና የሚያስፈልገውን ሁሉ በሚሰጠው በይሖዋ መንገዶች ላይ ካሰላሰለ በኋላ እንዲህ በማለት ደምድሟል:- “በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በጎነትና ምሕረት በእርግጥ ይከተሉኛል፤ እኔም በእግዚአብሔር ቤት፣ ለዘላለም እኖራለሁ።” (መዝሙር 23:6) ዳዊት ይህን የተናገረው፣ ያለፈውን ጊዜ በማስታወስ ከሚሰማው የአመስጋኝነት ስሜትና ስለወደፊቱ ጊዜ በነበረው እምነት ከተሞላ ልብ ተነሳስቶ ነው። ቀደም ሲል እረኛ የነበረው ዳዊት፣ በሰማይ በሚኖረው እረኛው ቤት እስከኖረ ማለትም ከእርሱ ጋር ያለውን ወዳጅነት አጥብቆ እስከያዘ ድረስ ምንጊዜም ከፍቅራዊ ደግነቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል በማወቁ ደኅንነት ተሰምቶት ነበር።
20 በ23ኛው መዝሙር ላይ ተመዝግበው ለሚገኙት ውብ ቃላት ምንኛ አመስጋኞች ነን! ዳዊት፣ ይሖዋ በጎቹን እንዴት እንደሚመራ፣ እንደሚንከባከብና እንደሚመግብ የሚገልጽ በጣም ተስማሚ ምሳሌ ጠቅሷል። እኛም ይሖዋን እንደ እረኛችን አድርገን ለመመልከት የሚያስችል እምነት እንዲኖረን ዳዊት የተናገረው አስደሳች ሐሳብ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጽፎ ቆይቶልናል። አዎን፣ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጠብቀን እስከቆየን ድረስ እንደ አፍቃሪ እረኛ ለረጅም ዘመን አልፎ ተርፎም ለዘላለም እንክብካቤ ያደርግልናል። ይሁንና እኛም በጎቹ እንደመሆናችን መጠን ከታላቁ እረኛችን ከይሖዋ ጋር የመሄድ ኃላፊነት አለብን። ይህ ምንን እንደሚጨምር በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b ዳዊት፣ ይሖዋ ከአደጋ ስለጠበቀው ለማመስገን በርካታ መዝሙሮች አቀናብሯል። ለምሳሌ ያህል በመዝሙር ምዕራፍ 18፣ 34፣ 56፣ 57፣ 59ና 63 አናት ላይ የሚገኙትን መግቢያዎች ተመልከት።
c በጥቅምት 1, 2003 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት—ምን መጠበቅ እንችላለን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• ዳዊት ይሖዋን ከእረኛ ጋር ማነጻጸሩ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
• ይሖዋ በአሳቢነት የሚመራን እንዴት ነው?
• ይሖዋ ችግሮችን መቋቋም እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?
• ይሖዋ ለጋስ ጋባዥ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ እንደ አንድ እስራኤላዊ እረኛ በጎቹን ይመራል