የይሖዋን ስም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ
‘ኑና ከእኔ ጋር ይሖዋን አክብሩት፤ ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ።’ —መዝሙር 34:3
1. ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ምሽት ላይ ኢየሱስና ሐዋርያቱ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ደርብ ላይ ተሰብስበው ይሖዋን በመዝሙር እያወደሱት ነበር። (ማቴዎስ 26:30) ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር እንዲህ ለማድረግ አጋጣሚ አይኖረውም። ከሐዋርያቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የሚያሳልፈውን ይህን ወቅት ይሖዋን በመዝሙር በማወደስ መደምደሙ ተገቢ ነው። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ጀምሮ እስኪጨርስ ድረስ አባቱን ያወደሰ ሲሆን ስሙንም በቅንዓት አሳውቋል። (ማቴዎስ 4:10፤ 6:9፤ 22:37, 38፤ ዮሐንስ 12:28፤ 17:6) መዝሙራዊው ‘ኑና ከእኔ ጋር ይሖዋን አክብሩት፤ ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ’ በማለት ያቀረበውን ሞቅ ያለ ግብዣ ኢየሱስም አስተጋብቷል ማለት ይቻላል። (መዝሙር 34:3) ልንከተለው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
2, 3. (ሀ) መዝሙር 34 ትንቢታዊ መልእክት እንደያዘ እንዴት እናውቃለን? (ለ) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 ሐዋርያው ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር ይሖዋን በመዝሙር ካወደሰ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አንድ ለየት ያለ ክንውን ተመለከተ። ጌታው ከሁለት ወንጀለኞች ጋር በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት እንዲሁም የሮም ወታደሮች ሁለቱ ወንጀለኞች ቶሎ እንዲሞቱ ለማድረግ ጭናቸውን ሲሰብሩ አየ። ይሁን እንጂ ወታደሮቹ የኢየሱስን ጭኖች እንዳልሰበሩ ዮሐንስ ዘግቧል። ወታደሮቹ ወደ ኢየሱስ ሲቀርቡ ሞቶ ነበር። ይህም በመዝሙር 34 ላይ የሚገኘው “ከዐጥንቶቹም አንድ አይሰበርም” የሚለው ትንቢት ፍፃሜ እንደሆነ ዮሐንስ በወንጌል ዘገባው ላይ ገልጿል።—ዮሐንስ 19:32-36፤ መዝሙር 34:20 ሰብዓ ሊቃናት
3 መዝሙር 34 የክርስቲያኖችን ትኩረት የሚስቡ ሌሎች በርካታ ነጥቦችም ይዟል። በመሆኑም በዚህና በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ዳዊት መዝሙሩን ሲጽፍ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ እንዲሁም መዝሙሩ የያዛቸውን የሚያበረታቱ ትምህርቶች እንመለከታለን።
ዳዊት ከሳኦል ሸሸ
4. (ሀ) ዳዊት ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው ለምን ነበር? (ለ) ሳኦል ዳዊትን ‘እጅግ የወደደው’ ለምንድን ነው?
4 ዳዊት ወጣት እያለ ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ ነበር። ይሁን እንጂ ሳኦል ታዛዥ ሳይሆን በመቅረቱ የይሖዋን ሞገስ አጣ። በዚህም የተነሳ ነቢዩ ሳሙኤል ሳኦልን “እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጥቶታል” አለው። (1 ሳሙኤል 15:28) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ ከእሴይ ወንዶች ልጆች ታናሽ የሆነውን ዳዊትን ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው ለሳሙኤል ነገረው። በዚህ መሃል የአምላክ መንፈስ የራቀው ንጉሥ ሳኦል መንፈሱ ይረበሽ ነበር። በዚህም ምክንያት የተዋጣለት የሙዚቃ ባለሞያ የሆነው ዳዊት ንጉሡን እንዲያገለግል ወደ ጊብዓ ተወሰደ፤ ይህ ወጣት የሚጫወተው ሙዚቃ ለሳኦል እረፍት ይሰጠው ስለነበር ንጉሡ ዳዊትን “እጅግ ወደደው።”—1 ሳሙኤል 16:11, 13, 21, 23
5. ሳኦል ለዳዊት የነበረውን አመለካከት የለወጠው ለምንድን ነው? ዳዊትስ ምን ለማድረግ ተገደደ?
5 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ይሖዋ ከዳዊት ጋር መሆኑ ይታይ ጀመር። ይህ ወጣት፣ ጎልያድ የተባለውን ግዙፍ ፍልስጥኤማዊ ድል እንዲያደርግ እንዲሁም በውትድርና ችሎታው በእስራኤል ውስጥ የተከበረ እንዲሆን ይሖዋ ረድቶታል። ይሁን እንጂ ይህ ወጣት የይሖዋን በረከት ማግኘቱ ሳኦል እንዲቀናና ዳዊትን እንዲጠላው አደረገው። ዳዊት በሳኦል ፊት ሆኖ በገና እየደረደረ ሳለ ንጉሡ ሁለት ጊዜ ጦሩን ወረወረበት። በሁለቱም ጊዜያት ዳዊት ከሳኦል ፊት ዘወር በማለቱ የተወረወረበት ጦር ጉዳት አላደረሰበትም። ሳኦል፣ ከእርሱ ቀጥሎ የእስራኤል ንጉሥ የሚሆነውን ዳዊትን ለመግደል ለሦስተኛ ጊዜ ሙከራ ሲያደርግ ግን ይህ ወጣት ሕይወቱን ለማዳን መሸሽ እንዳለበት ተገነዘበ። ሳኦል፣ ዳዊትን ለመያዝና ለመግደል የሚያደርገውን ጥረት ስለቀጠለበት ከጊዜ በኋላ ዳዊት ከእስራኤል ክልል ውጪ ለመሸሸግ ወሰነ።—1 ሳሙኤል 18:11፤ 19:9, 10
6. ሳኦል የኖብ ከተማ ነዋሪዎች እንዲገደሉ ያዘዘው ለምን ነበር?
6 ዳዊት ወደ እስራኤል ድንበር ሲቃረብ የይሖዋ የማደሪያ ድንኳን በሚገኝበት በኖብ ከተማ ለአጭር ጊዜ ቆም አለ። ዳዊት በሚሸሽበት ወቅት የተከተሉት ወጣት ወንዶች የነበሩ ይመስላል፤ በመሆኑም ወደዚች ከተማ የሄደው ለራሱም ሆነ ለእነርሱ የሚሆን ምግብ ፈልጎ ነበር። ሊቀ ካህኑ ለዳዊትና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ምግብ እንዲሁም ዳዊት ከጎልያድ የወሰደውን ሰይፍ ሰጣቸው። ሳኦልም ይህን ሲያውቅ በሁኔታው በመናደድ 85 ካህናትን ጨምሮ የከተማውን ሕዝብ በሙሉ አጠፋ።—1 ሳሙኤል 21:1, 2፤ 22:12, 13, 18, 19፤ ማቴዎስ 12:3, 4
እንደገና ከሞት ማምለጥ
7. ጌት ለዳዊት አስተማማኝ መሸሸጊያ ያልነበረችው ለምንድን ነው?
7 ዳዊት ከኖብ በስተ ምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ የፍልስጥኤማውያን ክልል ሸሸ፤ በዚያም የጎልያድ የትውልድ ከተማ በሆነችው በጌት በንጉሥ አንኩስ ዘንድ ተሸሸገ። ዳዊት ወደዚች ከተማ የሄደው ሳኦል በጌት እንደማይፈልገው ተሰምቶት ይሆናል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የጌት ንጉሥ አገልጋዮች ዳዊትን አወቁት። ዳዊት እንደታወቀ በሰማ ጊዜ ‘የጌትን ንጉሥ አንኩስን እጅግ ፈራው።’—1 ሳሙኤል 21:10-12
8. (ሀ) መዝሙር 56 ዳዊት በጌት ስላጋጠመው ሁኔታ ምን ይነግረናል? (ለ) ዳዊት ከሞት መንጋጋ ለጥቂት ያመለጠው እንዴት ነበር?
8 ብዙም ሳይቆይ ፍልስጥኤማውያን ዳዊትን ያዙት። ይህ የይሖዋ አገልጋይ “እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም” በማለት ይሖዋን የለመነበትን ከልብ የመነጨ መዝሙር ያቀናበረው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። (መዝሙር 56:8 እና በመዝሙሩ አናት ላይ የሚገኘው መግለጫ) በዚህ መንገድ መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ሐዘኑን እንደማይረሳ ከዚህ ይልቅ በፍቅር እንደሚንከባከበውና እንደሚጠብቀው ያለውን እምነት ገልጿል። ዳዊት የፍልስጥኤማውያንን ንጉሥ ለማታለል የሚያስችለው ዘዴም ቀይሷል። በንጉሡ ፊት ሲያቀርቡት እንደ እብድ ሰው ሆነ። ንጉሥ አንኩስ ይህንን ሲመለከት ‘ያበደ ሰው’ ወደ እርሱ በማምጣታቸው አገልጋዮቹን ወቀሳቸው። ይሖዋ፣ ዳዊት የተጠቀመበትን ዘዴ እንደባረከለት በግልጽ መመልከት ይቻላል። ዳዊት ከከተማው የተባረረ ሲሆን በዚህም ጊዜ ቢሆን ከሞት ያመለጠው ለጥቂት ነበር።—1 ሳሙኤል 21:13-15
9, 10. ዳዊት መዝሙር 34ን የጻፈበት ምክንያት ምንድን ነው? ይህንን መዝሙር ሲያቀናብር እነማንን አስቦ ሊሆን ይችላል?
9 ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎች ከእርሱ ጋር ወደ ጌት ይሂዱ ወይም በአቅራቢያው ባሉ የእስራኤል መንደሮች ሆነው ጉዳት እንዳይደርስበት እርሱን ይጠብቁ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚናገረው ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ ዳዊት፣ ይሖዋ በድጋሚ እንዴት እንዳዳነው እንደገና ከተገናኙ በኋላ ሲተርክላቸው ተደስተው መሆን አለበት። በመዝሙር 34 አናት ላይ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ለዚህ መዝሙር መጻፍ ምክንያት የሆነው ይህ ሁኔታ ነው። በዚህ መዝሙር የመጀመሪያ ሰባት ቁጥሮች ላይ ዳዊት ከመከራው ያዳነውን አምላክ ያወድሳል፤ እንዲሁም ለሕዝቦቹ ታላቅ አዳኝ የሆነውን ይሖዋን ከእርሱ ጋር ሆነው ከፍ ከፍ እንዲያደርጉት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ይጋብዛል።—መዝሙር 34:3, 4, 7
10 ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከጌት በስተ ምሥራቅ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለው በተራራማው የእስራኤል አገር በዓዶላም ዋሻ ውስጥ ተሸሸጉ። እዚያ እያሉም፣ በንጉሥ ሳኦል አገዛዝ ሥር ባሉት ሁኔታዎች ያልተደሰቱ እስራኤላውያን ወደ እነርሱ በመምጣት አብረዋቸው መኖር ጀመሩ። (1 ሳሙኤል 22:1, 2) ዳዊት፣ መዝሙር 34:8-22 ላይ ያለውን ሐሳብ ያቀናበረው እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች አስቦ ሳይሆን አይቀርም። በእነዚህ ቁጥሮች ላይ የሚገኙት ሐሳቦች በዛሬው ጊዜ ለምንገኘው ለእኛም አስፈላጊ ናቸው፤ ይህንን ውብ መዝሙር በዝርዝር መመልከታችን እንደሚጠቅመን ምንም ጥርጥር የለውም።
በሕይወትህ ውስጥ በዋነኝነት የሚያሳስብህ ጉዳይ ከዳዊት ጋር ይመሳሰላል?
11, 12. ይሖዋን አዘውትረን እንድናወድስ የሚገፋፉን ምን ምክንያቶች አሉን?
11 “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፤ ምስጋናውም ዘወትር ከአፌ አይለይም።” (መዝሙር 34:1) ዳዊት ከማኅበረሰቡ ርቆ ይኖር ስለነበር በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ብዙ የሚያሳስቡት ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሆኖም በዚህ ጥቅስ ላይ ካለው ሐሳብ መመልከት እንደምንችለው ዕለታዊ ፍላጎቶቹ ይሖዋን ለማወደስ እንቅፋት እንዲሆኑበት አልፈቀደም። እኛም ችግሮች ሲያጋጥሙን ልንኮርጀው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! በትምህርት ቤትም ይሁን በሥራ ቦታ እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር እያለን ወይም በአገልግሎት ስንካፈል በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ይሖዋን ማወደስ መሆን አለበት። እንዲህ እንድናደርግ የሚያነሳሱንን በርካታ ምክንያቶች አስብ! ለአብነት ያህል፣ የይሖዋን ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች በማወቅ የምናገኘው ደስታ መጨረሻ የለውም። እንዲሁም በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል አማካኝነት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች አስብ! ይሖዋ በዘመናችን ፍጹማን ያልሆኑ ታማኝ ሰዎችን ከፍተኛ ሥራ ለማከናወን ተጠቅሞባቸዋል። እነዚህ የአምላክ ሥራዎች ዓለም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች ከሚያከናውኗቸው ተግባሮች ጋር ሲወዳደሩ ምን ይመስላሉ? “ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤ ከአንተም ሥራ ጋር የሚወዳደር ሥራ የለም” በማለት ከጻፈው ከዳዊት ጋር አትስማማም?—መዝሙር 86:8
12 እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም ተወዳዳሪ ለሌላቸው ሥራዎቹ ይሖዋን ሁልጊዜ ለማወደስ እንገፋፋለን። ከዚህም በላይ በአሁኑ ጊዜ የአምላክን መንግሥት የሚያስተዳድረው የዳዊት ዘላለማዊ ወራሽ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ማወቃችን በጣም ያስደስተናል። (ራእይ 11:15) ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት የሚያስተዳድር መሆኑ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ እንደቀረበ ያሳየናል። ከስድስት ቢሊዮን የሚበልጡ የሰው ዘሮች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን አጋጣሚ ሊያጡ ይችላሉ። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ወቅት፣ ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት በቅርቡ ለሰው ዘሮች ምን እንደሚያመጣ ለሌሎች መናገር እንዲሁም እነርሱም ከእኛ ጋር ሆነው ይሖዋን እንዲያወድሱ መርዳት ይኖርብናል። በእርግጥም ጊዜው ከማለፉ በፊት ሰዎች ‘ወንጌሉን’ እንዲቀበሉ ለማበረታታት በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ መጠቀም በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ መሆን ይኖርበታል።—ማቴዎስ 24:14
13. (ሀ) ዳዊት የተመካው በማን ነበር? ወደ አምላክ የሚቀርቡትስ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ትሑት ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እየተሳቡ ያሉት እንዴት ነው?
13 “ነፍሴ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ተመካች፤ ትሑታንም ይህን ሰምተው ሐሤት ያደርጋሉ።” (መዝሙር 34:2) እዚህ ላይ እንደምናየው ዳዊት ባገኘው ስኬት አልተመካም። ለምሳሌ፣ የጌትን ንጉሥ እንዴት እንዳታለለው በጉራ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ በጌት በነበረበት ወቅት ይሖዋ ጥበቃ እንዳደረገለትና ከሞት የተረፈውም በእርሱ እርዳታ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ምሳሌ 21:1) በመሆኑም ዳዊት በራሱ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ተመክቷል። ዳዊት አምላክን ማወደሱ ትሑት የሆኑ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል። ኢየሱስም በተመሳሳይ የአምላክን ስም ሁልጊዜ ያወድስ የነበረ ሲሆን ይህም ትሑትና ለመማር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲመጡ አድርጓል። በዛሬው ጊዜ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ትሑት ሰዎች በቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደተገነባው ዓለም አቀፍ ጉባኤ እየጎረፉ ሲሆን የዚህ ጉባኤ ራስ ደግሞ ኢየሱስ ነው። (ቈላስይስ 1:18) ከብሔራት የተውጣጡት እነዚህ ሰዎች፣ ትሑት የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ስሙን ሲያወድሱ ሲሰሙ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሲረዱ ልባቸው ይነካል።—ዮሐንስ 6:44፤ የሐዋርያት ሥራ 16:14
ስብሰባዎች እምነታችንን ያጠናክሩልናል
14. (ሀ) ዳዊት፣ ይሖዋን በግሉ በማወደሱ ብቻ ረክቶ ነበር? (ለ) ኢየሱስ ለአምልኮ በሚደረጉ ስብሰባዎች ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?
14 “ኑና ከእኔ ጋር እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] አክብሩት፤ ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ።” (መዝሙር 34:3) ዳዊት፣ ይሖዋን በግሉ በማወደሱ ብቻ አልረካም። ወዳጆቹም የአምላክን ስም አብረውት ከፍ ከፍ እንዲያደርጉ ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቦላቸዋል። በተመሳሳይም ታላቁ ዳዊት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ይሖዋን በሕዝብ ፊት በማወደስ ይደሰት ነበር፤ ኢየሱስ በአካባቢው በሚገኘው ምኩራብ፣ በኢየሩሳሌም ባለው የአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ በሚከበሩ በዓላት ላይ እንዲሁም ከተከታዮቹ ጋር ሆኖ ይሖዋን አወድሶታል። (ሉቃስ 2:49፤ 4:16-19፤ 10:21፤ ዮሐንስ 18:20) ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን በማወደስ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ምንኛ አስደሳች መብት ነው! በተለይ በዛሬው ጊዜ ‘ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን በማየት’ ይህንን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው።—ዕብራውያን 10:24, 25
15. (ሀ) የዳዊት ተሞክሮ አብረውት በነበሩት ሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? (ለ) በስብሰባዎቻችን ላይ በመገኘታችን የምንጠቀመው እንዴት ነው?
15 “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ፈለግሁት፤ እርሱም መለሰልኝ፤ ከፍርሀቴም ሁሉ አዳነኝ።” (መዝሙር 34:4) ዳዊት፣ ይሖዋ ያደረገለትን ነገር ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር። በዚህም ምክንያት “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም [“ይሖዋም፣” NW] ሰማው፤ ከመከራውም ሁሉ አዳነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 34:6) እኛም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በምንሰበሰብበት ወቅት ይሖዋ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንድንወጣ እንዴት እንደረዳን የሚያወሱ አበረታች ተሞክሮዎችን ለማውራት ሰፊ አጋጣሚ እናገኛለን። ዳዊት የተናገራቸው ነገሮች አብረውት የነበሩትን ሰዎች እምነት እንዳጠናከሩላቸው ሁሉ እኛም እንዲህ ማድረጋችን የክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን እምነት ይገነባል። ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎች ‘ወደ ይሖዋ በመመልከት አብርተዋል፤ ፊታቸውም ከቶ አላፈረም።’ (መዝሙር 34:5) እነዚህ ሰዎች ከንጉሥ ሳኦል ይሸሹ የነበረ ቢሆንም አላፈሩም። አምላክ፣ ከዳዊት ጋር እንደሆነ እርግጠኞች ስለነበሩ ፊታቸው ያበራ ነበር። በተመሳሳይም ፍላጎት ያላቸው አዲስ ሰዎችም ሆኑ ለረጅም ጊዜ ጸንተው የቆዩ እውነተኛ ክርስቲያኖች እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ይላሉ። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ስለረዳቸው በታማኝነት ለመጽናት ያደረጉት ቁርጥ ውሳኔ በሚያበራው ፊታቸው ላይ ይንጸባረቃል።
ከመላእክት ለሚገኘው እርዳታ አመስጋኞች ሁኑ
16. ይሖዋ እኛን ለማዳን በመላእክቱ የተጠቀመው እንዴት ነው?
16 ‘ይሖዋን በሚፈሩት ዙሪያ የይሖዋ መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም።’ (መዝሙር 34:7) ዳዊት፣ ይሖዋ የማዳን እጁን የሚዘረጋው ለእርሱ ብቻ እንደሆነ አላሰበም። ዳዊት በአምላክ የተቀባ የእስራኤል የወደፊት ንጉሥ እንደነበረ አይካድም፤ ያም ቢሆን ይሖዋ ትልቅ ቦታ የነበራቸውንም ሆነ ተራ የሆኑ ታማኝ አገልጋዮቹን በሙሉ ለመጠበቅ መላእክቱን እንደሚልክ ያውቅ ነበር። በዘመናችንም ይሖዋ ለእውነተኛ አምላኪዎቹ ጥበቃ አድርጎላቸዋል። በናዚ ጀርመንም ሆነ በማላዊ፣ በሞዛምቢክ፣ በአንጎላና በሌሎች በርካታ አገሮች ባለ ሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን ከምድር ገጽ የማጥፋት ዘመቻ አድርገው ነበር። ሆኖም ጥረታቸው ሁሉ ከንቱ ሆኗል። እንዲያውም በእነዚህ አገሮች የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በአንድነት ሆነው የአምላክን ስም ከፍ ከፍ እያደረጉ ሲሆን ቁጥራቸውም እየጨመረ ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅና ለመምራት በቅዱሳን መላእክቱ ስለሚጠቀም ነው።—ዕብራውያን 1:14
17. የአምላክ መላእክት የሚረዱን በየትኞቹ መንገዶች ነው?
17 ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ መላእክት፣ ሌሎችን የሚያሰናክሉ ሰዎች ከአምላክ ሕዝቦች መካከል እንዲወጡ ነገሮችን ማስተካከል ይችላሉ። (ማቴዎስ 13:41፤ 18:6, 10) አንዳንድ ጊዜ እኛ ባናስተውለውም እንኳ መላእክት አምላክን እንዳናገለግል እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ መሰናክሎችን ያስወግዱልናል፤ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች ይጠብቁናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ መላእክት ‘የዘላለሙን ወንጌል’ ለመላው የሰው ዘር በማወጁ ሥራ ስንካፈል ይመሩናል፤ የስብከቱ ሥራ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሚከናወንባቸው ቦታዎችም ጭምር ምሥራቹን ስንሰብክ ይረዱናል። (ራእይ 14:6) መላእክት እንደሚረዱን የሚያሳዩ ተሞክሮዎች የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጇቸው ጽሑፎች ላይ ብዙ ጊዜ ይወጣሉ።a እንደነዚህ ያሉት ተሞክሮዎች በጣም ብዙ በመሆናቸው በአጋጣሚ የተከሰቱ ናቸው ለማለት ያስቸግራል።
18. (ሀ) ከመላእክት እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
18 የመላእክትን መመሪያና ጥበቃ ለማግኘት የይሖዋን ስም በስደት ጊዜም ጭምር ከፍ ከፍ ማድረግ ይኖርብናል። የአምላክ መልአክ የሚሰፍረው ‘ይሖዋን በሚፈሩት ዙሪያ’ ብቻ እንደሆነ አስታውስ። ይህ ምን ያመለክታል? አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? ይህንንስ ባሕርይ እንዴት ልናዳብረው እንችላለን? አፍቃሪ የሆነ አምላክ እንድንፈራው የሚፈልገው ለምንድን ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ)፣ ገጽ 550፣ የ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ፣ ገጽ 53-4 (እንግሊዝኛ)፣ መጠበቂያ ግንብ መጋቢት 1, 2000 ገጽ 5-6፣ ጥር 1, 1991 ገጽ 27 እንዲሁም የካቲት 15, 1991 ገጽ 26 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ዳዊት በወጣትነቱ ምን መከራዎችን አሳልፏል?
• እንደ ዳዊት እኛም በዋነኝነት የሚያሳስበን ምንድን ነው?
• ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን የምንመለከታቸው እንዴት ነው?
• ይሖዋ እኛን ለመርዳት በመላእክቱ የሚጠቀመው እንዴት ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ራማ
ጌት
ጺቅላግ
ጊብዓ
ኢየሩሳሌም
ዓዶላም
ቅዒላ
ኬብሮን
ዚፍ
ሖሬሽ
ማዖን
ኖብ
ቤተ ልሔም
ዓይንጋዲ
ቀርሜሎስ
የጨው ባሕር
[ምንጭ]
ካርታ:- Based on maps copyrighted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት በስደት ላይ እያለም እንኳ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ አድርጓል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚያንጹ ተሞክሮዎችን ስንሰማ እምነታችን ይጠናከራል