አምላክን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ስለ አምላክ በመማርና እሱን ለማስደሰት ጥረት በማድረግ አምላክን ማወቅ ትችላለህ። እንደዚያ ካደረግክ “እሱም ወደ [አንተ] ይቀርባል።” (ያዕቆብ 4:8) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” እንዳልሆነ ማረጋገጫ ይሰጠናል።—የሐዋርያት ሥራ 17:27
አምላክን ማወቅ የሚቻልበት መንገድ
መጽሐፍ ቅዱስን አንብብ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ትርጉሙ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት አምላክ ነው። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ሐሳቡን በመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አእምሮ ውስጥ በማስገባት ነው። አምላክ በዚህ ልዩ መጽሐፍ አማካኝነት ለእኛ ያለውን ፈቃድ ገልጾልናል። በተጨማሪም ፍቅሩን፣ ፍትሑንና ምሕረቱን ጨምሮ የተለያዩ ባሕርያቱን ገልጾልናል።—ዘፀአት 34:6፤ ዘዳግም 32:4
ምን ማድረግ ትችላለህ? በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን አንብብ። (ኢያሱ 1:8) ከዚያም ‘ይህ ሐሳብ ስለ አምላክ ማንነት ምን ያስተምረኛል?’ እያልክ ራስህን በመጠየቅ ባነበብከው ነገር ላይ አሰላስል።—መዝሙር 77:12
ለምሳሌ ያህል ኤርምያስ 29:11ን አንብብ፤ ከዚያም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘አምላክ ለእኔ የሚመኝልኝ ምንድን ነው? ሰላምን ነው ወይስ ጥፋትን? አምላክ ቂመኛ ነው? ወይስ አስደሳች ሕይወት እንዲኖረኝ ይፈልጋል?’
ተፈጥሮን ተመልከት
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “[የአምላክ] የማይታዩት ባሕርያቱ . . . ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።”—ሮም 1:20
ትርጉሙ፦ አንድ ሥዕል ስለ ሠዓሊው ባሕርይ ብዙ ነገር ይገልጻል፤ ወይም ውስብስብ የሆነ የፈጠራ ሥራ ስለ ንድፍ አውጪው ብዙ ነገር ይነግረናል፤ በተመሳሳይም አምላክ የፈጠራቸው ነገሮች የተለያዩ ባሕርያቱን ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል የሰው አንጎል ያለው አቅምና ውስብስብነት የአምላክን ጥበብ ያሳያል፤ በፀሐይና በከዋክብት ውስጥ የታመቀው አስደናቂ ኃይል ደግሞ ፈጣሪያችን ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ያስገነዝበናል።—መዝሙር 104:24፤ ኢሳይያስ 40:26
ምን ማድረግ ትችላለህ? ጊዜ ወስደህ ተፈጥሮን ለመመልከትና ስለ ተፈጥሮ ለመማር ሞክር። ይህን ስታደርግ ‘በተፈጥሮ ላይ የሚታየው አስደናቂ ንድፍ ስለ አምላክ ምን ያስተምረኛል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።a እርግጥ ተፈጥሮ ስለ ፈጣሪያችን ሊነግረን የማይችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን ለዚህ ነው።
በአምላክ ስም ተጠቀም
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ስሜን ስለሚያውቅ እጠብቀዋለሁ። ይጠራኛል፤ እኔም እመልስለታለሁ።”—መዝሙር 91:14, 15
ትርጉሙ፦ የአምላክ ስም ይሖዋ ነው፤ ይሖዋ ስሙን ለሚያውቁና ስሙን በአክብሮት ለሚጠቀሙ ሰዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣል።b (መዝሙር 83:18፤ ሚልክያስ 3:16) አምላክ ስሙን ለእኛ በመንገር ራሱን አስተዋውቆናል። “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው” ብሏል።—ኢሳይያስ 42:8
ምን ማድረግ ትችላለህ? ስለ ይሖዋ ስትናገር በስሙ ተጠቀም።
ይሖዋን በጸሎት አነጋግረው
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው።”—መዝሙር 145:18
ትርጉሙ፦ ይሖዋ በእምነት ወደ እሱ ወደሚጸልዩ ሰዎች ይቀርባል። ጸሎት የአምልኮ ክፍል ነው፤ እንዲሁም ለአምላክ ያለንን ጥልቅ አክብሮት ያሳያል።
ምን ማድረግ ትችላለህ? አዘውትረህ ወደ አምላክ ጸልይ። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ጭንቀትህንና ስሜትህን አውጥተህ ንገረው።—መዝሙር 62:8c
በአምላክ ላይ እምነት ገንባ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ያለእምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም።”—ዕብራውያን 11:6
ትርጉሙ፦ ወደ አምላክ ለመቅረብ በእሱ ላይ እምነት ሊኖረን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በአምላክ ማመን ሲባል አምላክ መኖሩን ማመን ማለት ብቻ አይደለም። የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም እንዲሁም ያወጣቸው መሥፈርቶች ሁሉ ጠቃሚ እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ መተማመንን ይጨምራል። የትኛውም ወዳጅነት ዘላቂ እንዲሆን በመተማመን ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት።
ምን ማድረግ ትችላለህ? እውነተኛ እምነት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ነው። (ሮም 10:17) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን አጥና፤ እንዲሁም አምላክ እምነት የሚጣልበት መሆኑንና ምክሮቹ ጠቃሚ መሆናቸውን ለራስህ አረጋግጥ። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስጠኑህ ፈቃደኞች ናቸው።d
አምላክን የሚያስደስት ምግባር ይኑርህ
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው።”—1 ዮሐንስ 5:3
ትርጉሙ፦ ይሖዋ ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ጥረት በማድረግ ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ወደሚያሳዩ ሰዎች ይቀርባል።
ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና አምላክ ምን እንደሚወድና ምን እንደሚጠላ ለማስተዋል ሞክር። ከዚያም ‘ፈጣሪዬን ለማስደሰት የትኞቹን ማስተካከያዎች ማድረግ ይኖርብኛል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።—1 ተሰሎንቄ 4:1
የአምላክን መመሪያዎች በማክበር እንክብካቤውን አጣጥም
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም።”—መዝሙር 34:8
ትርጉሙ፦ አምላክ ጥሩነቱን በገዛ ሕይወትህ እንድታጣጥም ጋብዞሃል። የአምላክን ፍቅርና ድጋፍ በሕይወትህ ስትመለከት ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ትነሳሳለህ።
ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ አምላክ የሚሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ፤ ይህም የአምላክን መመሪያ መታዘዝ የሚያስገኘውን ጥቅም ለማጣጣም ያስችልሃል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) በተጨማሪም በአምላክ እርዳታ ታግዘው ያጋጠማቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ የተወጡ፣ የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን ሕይወት ያሻሻሉ እንዲሁም እውነተኛ ደስታ ያገኙ ሰዎችን ምሳሌ አስተውል።e
አምላክን ማወቅን በተመለከተ የሚነገሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች
የተሳሳተ አመለካከት፦ አምላክ ከፍተኛ ኃይልና ሥልጣን ስላለው ከእኛ ጋር መቀራረብ አይፈልግም።
እውነታው፦ አምላክ ከማንም የሚበልጥ ኃይልና ሥልጣን ቢኖረውም ወደ እሱ እንድንቀርብ ጋብዞናል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ የቅርብ ወዳጅ የሆኑ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን ታሪክ ይዟል።—የሐዋርያት ሥራ 13:22፤ ያዕቆብ 2:23
የተሳሳተ አመለካከት፦ አምላክ ሚስጥራዊ ስለሆነ እሱን ልናውቀው አንችልም።
እውነታው፦ ከአምላክ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ነገሮች ለመረዳት ከባድ እንደሆኑ አይካድም፤ ለምሳሌ አምላክ የማይታይ መንፈስ መሆኑን መረዳት ሊከብደን ይችላል። ያም ቢሆን አምላክን ማወቅ እንችላለን። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት አምላክን ማወቅ እንዳለብን ይናገራል። (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪያችን፣ ስለ ባሕርያቱ፣ ለሰው ልጆችና ለምድር ስላለው ዓላማ እንዲሁም ስለ መሥፈርቶቹ ሊገባን በሚችል መንገድ ይነግረናል። (ኢሳይያስ 45:18, 19፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:4) በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ስም ነግሮናል። (መዝሙር 83:18) በመሆኑም አምላክን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ወደ እሱ መቅረብም እንችላለን።—ያዕቆብ 4:8
a የአምላክ ጥበብ በተፈጥሮ ላይ የተንጸባረቀው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ለመመልከት “ንድፍ አውጪ አለው?” የሚለውን ዓምድ ተመልከት።
b ብዙዎች ይሖዋ የሚለው ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው ያምናሉ። አምላክ ስሙን ሲነግረን ‘ፈቃዴንና ዓላማዬን እፈጽማለሁ። ምንጊዜም ቃሌን እጠብቃለሁ’ ያለን ያህል ነው።
c “መጸለይ ለምን አስፈለገ? አምላክ ጸሎቴን ይመልስልኛል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d ለተጨማሪ መረጃ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው እንዴት ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
e “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” የሚለውን ዓምድ ተመልከት።