ጥናት 18
መልሶችህን ማሻሻል
1, 2. ሁላችንም ጥሩ መልስ ለመስጠት ጥረት ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
1 ክርስቲያኖች በሙሉ ጥሩ መልስ የመስጠት ችሎታቸውን ማዳበር ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን” ሲል ጽፏል። (ቆላ. 4:6) መልሶቻችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረጋችንም የተገባ ነገር ነው። ጥሩ መልስ ስንሰጥ ልባዊ ደስታ ይሰማናል። “ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፣ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው!” — ምሳሌ 15:23
2 በግልህ መልሶችህን ማሻሻል እንደሚያስፈልግህ ይሰማሃልን? በጉባኤ ስብሰባዎች ስላለህ ተሳትፎ ሙሉ እርካታ አለህ ወይስ ብታሻሽል በጣም ደስ የምትሰኝበት መስክ አለ? በመስክ አገልግሎትህ ባጋጠመህ ሁኔታ ከዚህ የተሻለ ማድረግ ይገባኝ ነበር ያልክበት ጊዜ ይኖራልን? ሁላችንም እንዲህ የሚሰማን ጊዜ ስለሚኖር መልሶቻችንን እንዴት ለማሻሻል እንደምንችል አብረን ብንመረምር ጥሩ ይሆናል።
3, 4. በስብሰባ ላይ ለአንድ ጥያቄ የተለያዩ ሐሳቦች ሊሰጡ የሚችሉት እንዴት ነው?
3 የጉባኤ ስብሰባዎች። በአብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች አንዳንድ ግለሰቦች በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወይም በመጽሐፍ ጥናት ወይም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክለሳ ለሚጠየቁ ጥያቄዎች ምን ጊዜም መልስ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑ ይስተዋላል። ይህ በአጋጣሚ ያገኙት ችሎታ አይደለም። ለበርካታ ዓመታት ካደረጓቸው ጥናቶችና ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ባደረጓቸው ስብሰባዎች አማካኝነት ካካበቱት እውቀት የሚያገኙት መልስ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የወቅቱን ጽሑፍ መዘጋጀታቸውም መልስ ለመስጠት ያበቃቸዋል። አዳዲሶች እንኳን የሚጠናውን ጽሑፍ ቀደም ብለው ካጠኑ ጥሩ መልስ ሊሰጡ ይችላሉ። — ሥራ 15:28
4 በአንድ ጥያቄ ላይ መልስ ለመስጠት የመጀመሪያው ሰው ከሆንክ ወዲያና ወዲህ ሳትል ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ ብትሰጥ ጥሩ ይሆናል። ለጥያቄው መልስ ተሰጥቶበት ከነበረ ግን ውይይቱ በዚሁ ማብቃት ይኖርበታል ብለህ ማሰብ አይገባህም። በአንዱ ጥያቄ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ ለመስጠት ከሚቀጥሉት አንዱን ለማድረግ ትችላለህ። መልሱን ሰፋ አድርጎ ማብራራት፣ በአንቀጹ ውስጥ የተጠቀሱ ጥቅሶች ለመልሱ እንዴት ድጋፍ እንደሚሰጡ መግለጽ ወይም ውይይት የሚደረግበት ነጥብ ሕይወታችንን እንዴት እንደሚነካ ማብራራት ይቻላል። ትምህርቱ ስለ ዓለም ሁኔታ ወይም ስለ ሐሰት ሃይማኖት ልማዶች የሚገልጽ ከሆነ በግል ስላጋጠመህ ተሞክሮ ወይም አንቀጹ የሚናገረው ነገር ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ የአካባቢ ሁኔታ መናገር ትችላለህ። ይህም ውይይቱን ያዳብረዋል።
5. በአጭሩና በራስ አነጋገር መልስ መስጠት ጥሩ የሚሆነው ለምንድን ነው?
5 መልሶች አብዛኛውን ጊዜ አጭርና ነጥቡን የሚያስጨብጡ ሲሆኑ የበለጠ ክብደት ይኖራቸዋል፤ በሚያዳምጡት ሰዎች አእምሮ ውስጥም በይበልጥ ይቀረጻሉ። አብዛኛውን ጊዜ እንደነዚህ ያሉ መልሶች ቢሰጡ ጥሩ ነው። አንድ ግለሰብ የአንቀጹን ሐሳቦች በሙሉ ከላይ እስከ ታች የሚያነበንብ ከሆነ ፍሬ ሐሳቡ ጉልህ ሆኖ ስለማይታይ አድማጮች የጥያቄው መልስ ምን እንደሆነ መገንዘብ ያቅታቸዋል። በተጨማሪም መልስ ሰጪው በራሱ አነጋገር የሚሰጣቸው መልሶች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል። በራስ አነጋገርና ቃላት መልስ መስጠት መልስ ሰጪው ትምህርቱን የራሱ እንዲያደርገው ያስችለዋል። አድማጮችም ያልተገነዘቡትን ሐሳብ እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል። ይህን ችሎታ በማዳበር ረገድ በአገልግሎት ትምህርት ቤት የምትሰጣቸው ንግግሮች ሊረዱህ ይችላሉ።
6. ጥያቄ በሚጠየቅበት ጊዜ መልስ ለመስጠት ዝግጁ በመሆን ረገድ ልንሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?
6 መልስ ለመስጠት ዝግጁ በመሆን ረገድስ ልታሻሽል ትችላለህን? ለዚህም የቅድሚያ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ አንቀጹ በሚነበብበት ጊዜ ወይም ሌሎች ሐሳብ በሚሰጡበት ጊዜ መዘጋጀት ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም ከስብሰባው ማግኘት የሚገባህን ጥቅም ያሳጣሃል። በመልሶችህ ላይ ቀደም ብለህ ምልክት የማድረግ ልማድ ይኑርህ። ረዥም ሐረግ ወይም አረፍተ ነገር ሳይሆን ቁልፍ የሆኑ ጥቂት ቃላትን ብታሰምር እነዚህን ቁልፍ ቃላት መመልከት ብቻውን ሙሉውን ሐሳብ ለማስታወስ ስለሚያስችልህ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ለመሆን ትችላለህ። የአንድ አንቀጽ ጥያቄ በ“ሀ” እና በ“ለ” የተከፈለ ከሆነ የትኛው ክፍል የ“ሀ” መልስ እንደሆነና የትኛው ክፍል የ“ለ” መልስ እንደሆነ በጽሑፉ ሕዳግ ላይ ብታመለክት ከጥናቱ መሪ ቀድመህ ሐሳብ እንዳትሰጥ ሊረዳህ ይችላል። ጽሑፉ የተዘጋጀ ጥያቄ ባይኖረውም እንኳን የአድማጮች ውይይት የሚደረግበት ከሆነ ቁልፍ ነጥብ ነው ብለህ የምታስበውን ብታሰምር ጠቃሚ ይሆናል። ይህን ማድረግህ ቅጽበታዊ መልስ ለመስጠትና ሕያው የሆነ ውይይት ለማድረግ ያስችልሃል። በአንድ ስብሰባ ላይ አንድ ጊዜ መልስ ከሰጠህ በኋላ ሌሎቹን መልሶች ለሌሎች መተው እንደሚገባህ ተሰምቶህ ዝም ማለት አይገባህም። በነፃነት ሐሳብ ለመስጠት ፈቃደኛ ሁን።
7. በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለብን ሊሰማን የሚገባው ለምንድን ነው?
7 አንዳንዶች ከእኔ የተሻለ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ አሉ በማለትና በዓይነ አፋርነት መልስ ከመስጠት ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሐሳባችንን ለሌሎች የማካፈል ኃላፊነት ያለብን መሆኑን እንድንገነዘብ ይመክረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው። እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ።” (ዕብ. 10:23–25) መልስ ስንሰጥ ሌሎችን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እናነቃቃለን፣ እናበረታታቸዋለን፣ ልባቸውም በደስታ ሞቅ እንዲል እናደርጋለን። እኛም ብንሆን እንጠቀማለን። መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ለመቅመስ ስለምንችል በግላችን ማበረታቻ እናገኛለን።
8–12. በመስክ አገልግሎት የሚያጋጥሙንን የተቃውሞ አስተያየቶች እንዴት መመለስ እንደምንችል አንዳንድ ሐሳቦች ስጥ።
8 በመስክ አገልግሎት ለሚያጋጥሙት የተቃውሞ አስተያየቶች መልስ መስጠት። አዘውትረህ የግል ጥናት የምታደርግና ዘወትር በስብሰባዎች የምትገኝ ከሆነ ከቤት ወደ ቤት በምታደርገው አገልግሎት ለሚያጋጥሙህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንደማያዳግትህ ትገነዘባለህ። ይሁን እንጂ የተጠየቅከውን ጥያቄ መልስ የማታውቅ ከሆነ አለማወቅህን ለጠያቂው ለመናገር ማመንታት አይገባህም። ማብራሪያ ይዘህ እንደምትመለስ ንገረው። ሰውዬው ቅን ከሆነ እንደዚያ ብታደርግ ቅር አይለውም።
9 እንደነዚህ ካሉት ጥያቄዎች ሌላ የተቃውሞ አስተያየት ሊያጋጥምህ ይችላል። እንዴት ልትመልስ ትችላለህ? ለተቃውሞ አስተያየቱ መልስ ከመስጠትህ በፊት ስለ ሰውዬው አስተሳሰብ የምታውቀው ነገር ቢኖር ይጠቅምሃል። እንዲህ ብሎ እንዲናገር ያስቻለው ነገር ምን እንደሆነ ልትጠይቀው ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው በክርስቶስ እንደማታምኑ ሰምቼአለሁ ሊል ይችላል። ይሁን እንጂ ሰውዬውን ግራ ያጋባው በሥላሴ መሠረተ ትምህርት ላይ ያለው እምነት ነው። ብዙ የተቃውሞ አስተያየቶች የሚሰነዘሩት እንደዚህ ባለው ግራ መጋባት ምክንያት ነው። ውይይት ከመጀመር በፊት ቁልፍ ስለሆኑ ቃላት መግባባት ላይ መድረስ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ብቻውን ለተቃውሞ አስተያየቱ መልስ ይሆንና በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል።
10 የተቃውሞ አስተያየት በሚሰጥበት ጊዜ የሚቻል ከሆነ የተነሳውን ጥያቄ ሁለታችሁን እንደሚያጋጭ ነገር ሳይሆን ሁለታችሁንም ሊያቀራርብ እንደሚገባ ጉዳይ አድርጎ መያዝ ጥሩ ነው። ስለዚህ አንድን የተቃውሞ አስተያየት እንደማያስደስት ወይም እንደሚያስከፋ ነገር ከመቁጠር ይልቅ ጠያቂውን ከልብ የሚያሳስበው ጉዳይ እንደሆነ አድርገህ ቁጠር። ይህን በአእምሮህ በመያዝ ጉዳዩን በማንሳቱ ደስ የተሰኘህ መሆንህን ልትገልጽለት ትችላለህ። ጥያቄው ለውይይታችሁ ቀጣይነት ቁልፍ እንደሆነና ሰውዬው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች እንዲቀበል አእምሮውን ሊከፍትለት እንደሚችል አድርገህ ቁጠር። በአገልግሎት ትምህርት ቤት በምትሰጠው ንግግር ለተቃውሞ አስተያየቶች መልስ እንድትሰጥ የሚፈልግብህን ሁኔታዎች በመጨመር ለምን በዚህ ጉዳይ ላይ ልምምድ አታደርግም?
11 አንድን ፍላጎት ያሳየ ሰው በምታነጋግርበት ጊዜ ውይይታችሁን ለማቋረጥ ሲል ብቻ ጣልቃ ገብቶ የተቃውሞ አስተያየት የሚሰጥ ሌላ ሰው ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ጠያቂው ራሱ ለተናገረው ነገር ማስረጃ እንዲያቀርብ ልትጠይቀው ትችላለህ። ኢየሱስ ክርስቶስ ስብከቱን ለማስቆም አስበው የተነሱ ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት ጥያቄያቸውን በጥያቄ ይመልስ ነበር። (ማቴ. 22:41–46) ስለዚህ ሰውዬው ለተናገረው ነገር ማስረጃ እንዲያቀርብ መጠየቅ ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል ሰውዬው “እናንተ በሥላሴ አታምኑም” ቢልና አነጋገሩ ክርስቲያኖች በሙሉ በሥላሴ ማመን እንደሚፈለግባቸው የሚያመለክት ከሆነ “መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ሁሉ አምናለሁ። በሥላሴ ማመን እንደሚገባኝ የሚያሳይ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያሳዩኛል?” ለማለት ትችላለህ። በዚህ ጊዜ እውነት ነው ብሎ ለሚያምንበት ነገር ማስረጃ የማቅረቡ ግዴታ በጠያቂው ላይ ይወድቃል።
12 ቅዱሳን ጽሑፎችን አምናለሁ ለሚል ሰው በቀጥታ ከአምላክ ቃል ከተጠቀሰ ቃል የበለጠ አሳማኝ ማስረጃ ሊገኝ አይችልም። የአምላክ ቃል እኛ ከምንናገረው ማንኛውም ነገር ይበልጥ የማሳመን ኃይል አለው። እርግጥ መልስ በምትሰጥበት ጊዜ ሁሉ የጠያቂህ ዝንባሌ ምንም ዓይነት ቢሆን አለመቆጣትና የደግነት መንፈስ ማሳየት አስፈላጊ ነው። የአምላክ አገልጋይ እነዚህን ባሕርያት ማሳየት ይኖርበታል።
13, 14. የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚደረግበት ጊዜ ተማሪው ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች እንዴት መልስ ለመስጠት ይቻላል?
13 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚደረግባቸው ጊዜያት። አብዛኛውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በሚደረግባቸው ቦታዎች እየተወያዩ የነገሮችን ምክንያት ለማስረዳት አመቺ የሆነ የተዝናና መንፈስ ይኖራል። ስለዚህ ተማሪህ ላቀረበው ጥያቄ መልስ ከሰጠህ በኋላ መልሱ አርክቶት እንደሆነ መጠየቅ ጥሩ ልማድ ነው። አሁንም ገና ግልጽ ያልሆኑለት ነጥቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለ መልሱ እርግጠኛ ካልሆንክ ፈልገህ እንደምትነግረው ግለጽለት። ተጨማሪ እርዳታ የሚያስፈልግህ ከሆነ የበለጠ ተሞክሮ ያለውን አስፋፊ መጠየቅ ትችላለህ። አንድን ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በጥልቀት እንዲገባው ስትረዳ ግለሰቡ በሕይወት መንገድ መጓዝ እንዲጀምር መርዳትህ እንደሆነ ትዝ ይበልህ። ወንጌላዊው ፊልጶስ የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ጥያቄ በመመለስ እንደረዳው ሁሉ አንተም እንደዚያው በማድረግ ላይ ነህ ማለት ነው። — ሥራ 8:26–39
14 እየቆየህ ስትሄድ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ የሚነሡትን ጥያቄዎች በሙሉ አንድ ጊዜ አለመመለስ የተሻለ ይሆናል። ወደፊት በምታደርጉት ጥናት የሚሸፈን ትምህርት ከሆነ እስከዚያ ድረስ ብታቆየው ጥሩ ይሆናል። በተጨማሪም ለተማሪው ዕድገት በማሰብ እንዴት ራሱ በልዩ ልዩ ጽሑፎች ላይ ምርምር አድርጎ ለጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘት እንደሚችል ብታሳየው ጥሩ ነው። የማኅበሩን ጽሑፎች ኢንዴክስ ወይም ከጥያቄው ጋር አግባብነት ያለውን ምዕራፍ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ ከተባለው መጽሐፍ ወይም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መጽሐፍ ልታሳየው ትችላለህ። ከዚያ በኋላም ምን እውቀት እንዳገኘና ጉዳዩን በሚገባ ተረድቶት እንደሆነ ልትጠይቀው ትችላለህ። አጥብቀህ ልታስብ የሚገባህ ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ስለመቻልህ ሳይሆን ስለ መንፈሳዊ እድገቱ መሆን ይኖርበታል።
15–18. ለባለ ሥልጣኖች መልስ እንድንሰጥ በምንጠየቅበት ጊዜ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል?
15 በባለ ሥልጣኖች ፊት በምትቀርብበት ጊዜ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ስደት በሚገልጽበት ጊዜ እንዲህ ብሏል:- “ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” (1 ጴጥ. 3:14, 15) በሕጋዊ ፍርድ ቤቶች ቀርበን ስለ እምነታችን መከላከያ እንድናቀርብ የምንጠየቅበት ወይም ምን እንደምናምንና ለምን እንዲህ እንደምናምን የመጠየቅ ሥልጣን ባላቸው የሕግ ተወካዮች ፊት የምንቀርብበት ጊዜ ይኖራል። ሐዋርያው “ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት” ሲል መክሮናል። በልብህ ውስጥ ከፍተኛውን ከበሬታ የምትሰጠው ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነና ሊረክስ የማይገባው የቅድስና ደረጃ እንዳለው እንደምታምን መዘንጋት አይገባህም። ይህን ካደረግህ የምትጨነቅበት ወይም የምትረበሽበት ምንም ምክንያት አይኖርም። አምላክ የመላው ምድር ንጉሥ እንዲሆን የቀባውን ጌታ ካስደሰትን በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች ስለሚወስዱት እርምጃ አንጨነቅም።
16 ይሁን እንጂ በሮሜ 13:1–7 ላይ በተሰጠው ምክር መሠረት በሥልጣን ላይ ለሚገኙት ሰዎች አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። የሚጠይቅህ ባለ ሥልጣን መጥፎ ጥርጣሬ እንዳለው ቢሰማህ ወይም ለይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ጥላቻ እንዳለው የሚያመለክት ቃል በሚናገርበት ጊዜ ሸካራ መልስ በመስጠት አጸፋውን ለመመለስ መፈለግ አይኖርብህም። (ሮሜ 12:17, 21፤ 1 ጴጥ. 2:21–23) እዚያ ቦታ የቀረብከው ምሥክርነት ለመስጠት እንደሆነ አትዘንጋ። ከባለ ሥልጣኖቹ አንዱ እውነትን ሊቀበል ይችል ይሆናል። ይህም ቢቀር ለስብከቱ ሥራ የተሻለ ቀና አመለካከት ይኖረው ይሆናል። ጠባይህና አነጋገርህ የእውነትን መንገድ በጥሩ ሁኔታ የሚወክል ይሁን። — ማቴ. 10:18–20
17 ከዚህም በላይ ብዙ አለመናገር ጥበብ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለፍርድ በቀረበ ጊዜ እንዳደረገው ተቃዋሚዎችህ ለክሳቸው ማስረጃ እንዲያቀርቡ ልትጠይቅ ትችላለህ። (ሥራ 24:10–13) አለበለዚያም ዝም ለማለት ልትወስን ትችላለህ። ክፉ ሰዎች አንተን ለማሳት ወይም ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ልባዊ ፍላጎት ሳይኖራቸው በአንተ ለመጫወት የሚፈልጉ ከሆነ ዝም ማለት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። (ሉቃስ 23:8, 9) ወይም በአንተ አማካኝነት በሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚፈልጉ ከሆነ ዝም ማለት ጥበብ እንደሚሆን ልትወስን ትችላለህ። መዝሙራዊው “ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ” ብሏል። (መዝ. 39:1, 2) በተለይ በእውነተኛ ክርስትና ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ በሚደርስባቸው አገሮች “ዝም ለማለት” እና “ለመናገር” ጊዜው መቼ እንደሆነ ለመለየት መቻል በጣም አስፈላጊ ነው። — መክ. 3:7
18 አንድ የብሪታንያ ጋዜጣ የይሖዋ አገልጋዮች ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ስላላቸው ችሎታ ሲያትት እንዲህ ብሏል:- “ማንኛውም ምሥክር ለሚያደርገው ነገር ሁሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አለው። እንዲያውም ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋቸው መሠረታዊ አቋም መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ፣ ቃል በቃልና በፍጹም እውነት መሆኑን ማመናቸውና መቀበላቸው ነው። ሁለተኛው ጠንካራ ጎናቸው ከዚህ የመነጨ ይመስላል። ለማንኛውም ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይችላሉ።” ሰዎችን ግራ ለሚያጋቡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያስቻለን የአምላክ ቃልና በአምላክ ቃል ላይ የተመረኮዘ ሐሳብ ለመስጠት መቻላችን ነው። በዚህ ሁሉ ሊከበርና ሊወደስ የሚገባው አምላክ ነው። ቢሆንም የምንሰጣቸውን መልሶች ለማሻሻል በመጣር ለይሖዋ የበለጠ ክብር ለማምጣት፣ የራሳችንን ደስታ ለማብዛትና ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላምን ወደሚያገኙበት መንገድ ልንመራቸው እንችላለን።