የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የመዝሙር ሁለተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ችግሮችና ፈተናዎች ሊገጥሙን እንደሚችሉ እንጠብቃለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ችግሮችንና ፈተናዎችን ተቋቁመን ለአምላክ ታማኝ መሆናችንን እንድናሳይ የሚረዳን ምንድን ነው?
ይህን እርዳታ ከአምስቱ የመዝሙር መጻሕፍት በሁለተኛው ውስጥ እናገኘዋለን። ከመዝሙር 42 እስከ 72 ያሉት መዝሙሮች እንደሚያሳዩት በፈተና ለመጽናት ከፈለግን በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመንና የእርሱን ማዳን መጠባበቅ ይኖርብናል። ይህ እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ነው! የመዝሙር ሁለተኛ መጽሐፍ መልእክት እንደ ሌላው የአምላክ ቃል ሁሉ በእርግጥም “ሕያውና የሚሠራ ነው።”—ዕብራውያን 4:12
ይሖዋ “መጠጊያችንና ኀይላችን” ነው
አንድ ሌዋዊ በግዞት ተወስዷል። አምልኮውን ለማከናወን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ መሄድ ባለመቻሉ በሐዘን ቢዋጥም እንዲህ በማለት ራሱን አጽናንቷል:- “ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ።” (መዝሙር 42:5, 11፤ 43:5) ይህ አባባል በመዝሙር 42 እና 43 ላይ ሦስት ጊዜ መደጋገሙ ሁለቱ መዝሙሮች አንድ ግጥም እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በ44ኛው መዝሙር ላይ የሚገኘው ስለ ይሁዳ የቀረበ ልመና፣ አሦራውያን በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን ይሁዳን እንደሚወርሩ ሲዝቱ ብሔሩ የነበረበትን ጭንቀት የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።
በመዝሙር 45 ላይ የሚገኘው የንጉሣዊ ሠርግ መዝሙር ስለ መሲሐዊው ንጉሥ የሚናገር ትንቢት ነው። ቀጣዮቹ ሦስት መዝሙሮች ይሖዋ “መጠጊያችንና ኀይላችን፣” “በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ” እንዲሁም “ብርቱ ምሽግ” እንደሆነ ገልጸዋል። (መዝሙር 46:1፤ 47:2፤ 48:3) መዝሙር 49 “የሌላውን ሕይወት መቤዠት የሚችል ሰው” እንደሌለ ግሩም በሆነ መንገድ ገልጾታል! (መዝሙር 49:7) በሁለተኛው መጽሐፍ ውስጥ ያሉት የመጀመሪያዎቹ ስምንት መዝሙሮች በቆሬ ልጆች የተቀናበሩ ናቸው። ዘጠነኛውን መዝሙር ማለትም መዝሙር 50ን ያቀናበረው ደግሞ አሳፍ ነው።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
44:19—‘ተኵላዎች የሚውሉበት ቦታ’ የተባለው ምንድን ነው? ምናልባት መዝሙራዊው የጦር ሜዳን ለማመልከት ፈልጎ ይሆናል። በዚያ የሞቱ ሰዎች ሬሳ በተኩላዎች ሊበላ ይችላል።
45:13, 14ሀ—“ወደ ንጉሥ ትወሰዳለች” የተባለችው “የንጉሥ ልጅ” ማን ነች? “የዘመናት ንጉሥ” የሆነው የይሖዋ አምላክ ልጅ ናት። (ራእይ 15:3) እርሷም ክብር የተጎናጸፈውን የ144,000 ክርስቲያኖች ጉባኤ የምትወክል ሲሆን ይሖዋ እነዚህን ክርስቲያኖች በቅዱስ መንፈሱ በመቀባት እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። (ሮሜ 8:16) ‘ለባሏ እንደተዋበች ሙሽራ የተዘጋጀችው’ ይህች የይሖዋ “ልጅ” መሲሐዊ ንጉሥ ወደሆነው ሙሽራ ትወሰዳለች።—ራእይ 21:2
45:14ለ, 15—“ደናግል” የተባሉት እነማንን ይወክላሉ? እነዚህ ደናግል የቅቡዓን ቀሪዎች ተባባሪና ደጋፊ የሆኑት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የተባሉት እውነተኛ አምላኪዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት ስለሚያልፉ የመሲሑ ሠርግ ሥነ ሥርዓት በሰማይ በሚጠናቀቅበት ጊዜ ምድር ሆነው ‘የደስታው’ ተካፋዮች ይሆናሉ።—ራእይ 7:9, 13, 14
45:16—የንጉሡ ወንዶች ልጆች በአባቶቹ እግር የሚተኩት በምን መንገድ ነው? ኢየሱስ በምድር ላይ ሰው ሆኖ በተወለደ ጊዜ ሥጋዊ ቅድመ አያቶች ነበሩት። በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ከሙታን ሲያስነሳቸው ደግሞ የእርሱ ልጆች ይሆናሉ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ‘ገዢዎች ተደርገው በምድር ሁሉ’ ይሾማሉ።
50:2—ኢየሩሳሌም “ፍጹም ውብ” የተባለችው ለምንድን ነው? ይህ አባባል የከተማዋን ውበት የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የቤተ መቅደሱ መቀመጫና እርሱ የሾማቸው ንጉሦች ዋና ከተማ ሆና እንድታገለግል በማድረግ ዓላማውን ለማስፈጸም ስለተጠቀመባት ውበት እንድትላበስ አድርጓታል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
42:1-3:- ጠፍ በሆነ ምድር ውኃ እንደምትናፍቅ ዋላ፣ ሌዋዊውም ይሖዋን ናፍቋል። ይህ ሰው በአምላክ ቤተ መቅደስ ይሖዋን ማገልገል ባለመቻሉ የተሰማው ሐዘን እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የምግብ ፍላጎቱ ተዘግቶ፣ ‘እንባው ቀንና ሌሊት ምግብ ሆኖት’ ነበር። ታዲያ እኛ ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን ማገልገል በመቻላችን ልባዊ አድናቆት ልናሳይ አይገባም?
42:4, 5, 11፤ 43:3-5:- ከአቅማችን በላይ በሆነ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ከክርስቲያን ጉባኤ ተለይተን ከሆነ፣ ከዚህ ቀደም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባሳለፍናቸው አስደሳች ትዝታዎች ላይ ማሰላሰላችን እንድንጽናና ሊረዳን ይችላል። እንዲህ ማድረጋችን መጀመሪያ ላይ የብቸኝነት ስሜታችንን ሊያባብሰው ቢችልም እንኳ አምላክ መጠጊያችን እንደሆነና እፎይታ ለማግኘት እርሱን መጠበቅ እንደሚያስፈልገን ያስታውሰናል።
46:1-3:- የትኛውም ዓይነት ክፉ ገጠመኝ ቢደርስብን ‘እግዚአብሔር መጠጊያችንና ኃይላችን’ እንደሚሆን ሙሉ በሙሉ መተማመን ይኖርብናል።
50:16-19:- አታላይ ምላስ ያለው ብሎም ክፋትን የሚያደርግ አምላክን የመወከል መብት አይኖረውም።
50:20:- የሌሎችን ስህተት በአደባባይ ከማውራት ይልቅ ይቅር ልንላቸው ይገባል።—ቈላስይስ 3:13
“ነፍሴ ሆይ፤ ዐርፈሽ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ”
መዝሙር 51 ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ያቀረበው ልባዊ ጸሎት ነው። ከመዝሙር 52 እስከ 57 ያሉት መዝሙሮች ደግሞ ይሖዋ ሸክማቸውን በእርሱ ላይ የጣሉትንም ሆነ ማዳኑን የሚጠባበቁትን ሰዎች እንደሚያድናቸው ያሳያሉ። ከመዝሙር 58 እስከ 64 ያሉት መዝሙሮች ዳዊት የሚያስጨንቁ ነገሮች ባጋጠሙት ጊዜ ሁሉ ይሖዋን መጠጊያው እንዳደረገ የሚገልጹ ናቸው። ዳዊት “ነፍሴ ሆይ፤ ዐርፈሽ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ፤ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ነውና” ሲል ዘምሯል።—መዝሙር 62:5
ከአዳኛችን ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረታችን ‘ለስሙ ክብር እንድንዘምር’ ሊያነሳሳን ይገባል። (መዝሙር 66:2) ይሖዋ በልግስና የሚሰጥ በመሆኑ በ65ኛው መዝሙር ላይ ተወድሷል። በተጨማሪም በመዝሙር 67 እና 68 ላይ ያሉት የውዳሴ መዝሙሮች አዳኝ አምላክ እንደሆነ የሚገልጹ ሲሆን መዝሙር 70 እና 71 ደግሞ ታዳጊ አምላክ በማለት አወድሰውታል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
51:12—ዳዊት “በእሽታ መንፈስ” እንዲደገፍ ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነበር? እዚህ ላይ የተገለጸው የእሽታ ወይም የፈቃደኝነት መንፈስ አምላክ ዳዊትን ለመርዳት ያለውን ፍላጎትም ሆነ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ የሚያመለክት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የራሱን የዳዊትን መንፈስ ማለትም የአእምሮውን ዝንባሌ የሚያሳይ ነው። ዳዊት አምላክን የጠየቀው ትክክል የሆነውን የማድረግ ፍላጎት ማዳበር እንዲችል እንዲረዳው ነበር።
53:1—አምላክ የለም የሚል ሰው “ቂል” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቂልነት የእውቀት ማነስን አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ቂል የተባለው በመዝሙር 53:1-4 በተገለጸው መሠረት ምግባሩ ብልሹ በመሆኑ ነው።
58:3-5—ክፉዎች እንደ እባብ ተደርገው የተገለጹት ለምንድን ነው? ክፉዎች ስለ ሌሎች ሰዎች የሚናገሩት ውሸት ልክ እንደ እባብ መርዝ አደገኛ ነው። የሰዎችን መልካም ስም ይመርዛሉ ወይም ያጠፋሉ። ደግሞም “ጆሮዋን እንደ ደፈነች እፉኝት” የሚሰጣቸውን መመሪያም ሆነ እርማት መስማት አይፈልጉም።
58:7—ክፉዎች ‘ፈጥኖ እንደሚያልፍ ወራጅ ውሃ የሚጠፉት’ እንዴት ነው? ዳዊት በመልካሚቷ ምድር በሚገኙ አንዳንድ ሸለቆዎች ውስጥ ስለሚገኝ ወራጅ ውኃ አስቦ ሊሆን ይችላል። ከባድ ዝናብ ሲጥል የሚመጣው ደራሽ ጎርፍ በእነዚህ ሸለቆዎች ውስጥ የሚገኘውን የውኃ መጠን ከፍ ቢያደርገውም ጎርፉ ቶሎ ያልፋል። ዳዊት ጸሎት ያቀረበው ክፉዎችም እንዲሁ ቶሎ እንዲጠፉ ነው።
68:13—“ከብር እንደ ተሠሩ የርግብ ክንፎች፣ በቅጠልያ ወርቅ እንደ ተለበጡ ላባዎች” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? ግራጫ ቀለም ያላቸው አንዳንድ ርግቦች ላባዎቻቸውን ሲያንቀሳቅሱ የተለያዩ ቀለማት ይታያሉ። በላባቸው ላይ የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍበትም ያብረቀርቃል። ምናልባትም ዳዊት ድል ነስተው ከጦር ግንባር እየመጡ ያሉትን የእስራኤል ተዋጊዎች ጠንካራ ክንፍ ካለው የሚያምር ወፍ ጋር እያመሳሰላቸው ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚሉት ይህ መግለጫ እስራኤላውያን ተዋጊዎች በምርኮ ያመጡትን ቅርጻ ቅርጽም ሊያመለክት ይችላል። ያም ሆነ ይህ ዳዊት፣ ይሖዋ በጠላቶቻቸው ላይ ድል እንዲቀዳጁ ሕዝቦቹን መርዳቱን በተዘዋዋሪ መንገድ እየገለጸ ነበር።
68:18 NW—‘ስጦታ ሆነው የተሰጡት ወንዶች’ እነማን ነበሩ? እነዚህ ወንዶች እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር በወረሩበት ወቅት ከማረኳቸው ሰዎች መካከል ነበሩ። በኋላ ላይም እነዚህ ሰዎች ሌዋውያንን በሥራ እንዲያግዙ ተመድበዋል።—ዕዝራ 8:20
68:30—ዳዊት “በሸምበቆ መካከል ያሉትን አራዊት፣ . . . ገሥጽ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ዳዊት እዚህ ላይ አራዊት ሲል የይሖዋን ሕዝብ ጠላቶች ለማመልከት ምሳሌያዊ አነጋገር መጠቀሙ ነው። ስለዚህ ዳዊት፣ አምላክ እንዲገሥጻቸው ወይም ሕዝቡን ለመጉዳት የሚጠቀሙበትን ኃይል እንዲቆጣጠርለት እየጠየቀ ነው።
69:23 የ1980 ትርጉም—“ወገባቸው ሁልጊዜ ይንቀጥቀጥ” የሚለው አባባል ትርጉም ምንድን ነው? በወገብ አካባቢ ያሉት ጡንቻዎች ከባባድ ዕቃዎችን እንደ ማንሳትና መሸከም ያሉ አድካሚ ሥራዎችን ለማከናወን በጣም አስፈላጊ ናቸው። ስለዚህ የወገብ መንቀጥቀጥ ኃይል ማጣትን ያመለክታል። በመሆኑም ዳዊት ባላንጣዎቹ ኃይል እንዲያጡ ጸሎት ማቅረቡ ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
51:1-4, 17:- ኃጢአት ስንሠራ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለን ዝምድና አበቃለት ማለት አይደለም። ንስሐ ከገባን ምሕረቱን እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
51:5, 7-10:- ኃጢአት ከሠራን፣ ይሖዋ የወረስነውን ኃጢአት ግምት ውስጥ በማስገባት በደላችንን ይቅር እንዲለን ልንለምነው እንችላለን። በተጨማሪም ይሖዋ እንዲያነጻን፣ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት እንዲያድስልን፣ የኃጢአት ዝንባሌዎችን ከልባችን እንዲያጠራልንና ቀና መንፈስ እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል።
51:18:- ዳዊት የሠራቸው ኃጢአቶች የመላውን ብሔር ደኅንነት አደጋ ላይ ጥለውት ነበር። ስለዚህ ለጽዮን በጎ ፈቃዱን እንዲያሳያት ወደ አምላክ ጸልዮአል። አብዛኛውን ጊዜ ከባድ ኃጢአት ስንሠራ የይሖዋን ስምም ሆነ ጉባኤውን እናስነቅፋለን። አምላክ ኃጢአታችን ያስከተለውን ጉዳት እንዲያስተካክለው በጸሎት ልንጠይቀው ይገባል።
52:8:- ይሖዋን በመታዘዝና ተግሣጹን በፈቃደኝነት በመቀበል “በእግዚአብሔር ቤት፣ እንደ ለመለመ የወይራ ዛፍ” መሆን እንችላለን። ይህም ማለት ከይሖዋ ጋር እንቀራረባለን እንዲሁም በአገልግሎቱ ፍሬያማ እንሆናለን።—ዕብራውያን 12:5, 6
55:4, 5, 12-14, 16-18:- ዳዊት የገዛ ልጁ አቤሴሎም የጠነሰሰበት ሴራና የቅርብ አማካሪው አኪጦፌል የፈጸመበት ክህደት ከፍተኛ የስሜት ቀውስ አስከትሎበታል። ይሁንና እነዚህ ችግሮች በይሖዋ ላይ ያለውን የመተማመን ስሜት አልቀነሱበትም። ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ቢደርስብን በይሖዋ ላይ ያለንን የመተማመን መንፈስ እንዲያዳክምብን መፍቀድ አይኖርብንም።
55:22:- ሸክማችንን በይሖዋ ላይ የምንጥለው እንዴት ነው? (1) ስላሳሰበን ነገር ለይሖዋ በጸሎት በመንገር፣ (2) ቃሉና ድርጅቱ የሚሰጡንን መመሪያና ድጋፍ በመቀበል እንዲሁም (3) ችግሩን ለማቅለል የተቻለንን ያህል በመጣር ሸክማችንን በይሖዋ ላይ መጣል እንችላለን።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 11:14፤ 15:22፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
56:8:- ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ችግሩ በእኛ ላይ የሚያስከትለውን ስሜታዊ ቀውስ ጭምር ይገነዘባል።
62:11:- አምላክ የየትኛውም ኃይል እገዛ አያስፈልገውም። የብርታት ሁሉ ምንጭ እርሱ ነው። ‘ኃይል የእርሱ ነው።’
63:3:- የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ‘ምሕረት ከሕይወት ይበልጣል።’ ምክንያቱም ፍቅራዊ ደግነቱን ካላገኘን ሕይወታችን ትርጉም ያጣና ዓላማ ቢስ ይሆናል። ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የጥበብ መንገድ ነው።
63:6:- የሌሊቱ ጊዜ ጸጥታ የሚሰፍንበት ከመሆኑም በላይ ሐሳብን የሚከፋፍሉ ነገሮች ስለማይኖሩ ለማሰላሰል በጣም አመቺ ሊሆን ይችላል።
64:2-4:- ጎጂ ሐሜት የንጹሕ ሰውን መልካም ስም ሊያጎድፍ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱን ሐሜት መስማትም ይሁን ለሌሎች መንዛት አይኖርብንም።
69:4:- አንዳንድ ጊዜ ጥፋት እንዳጠፋን ባይሰማንም እንኳ ሰላም ለመፍጠር ስንል ‘መልሰን’ መስጠታችን ማለትም ይቅርታ መጠየቃችን የጥበብ መንገድ ሊሆን ይችላል።
70:1-5:- ይሖዋ ፈጥኖ እንዲደርስልን የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማል። (1 ተሰሎንቄ 5:17፤ ያዕቆብ 1:13፤ 2 ጴጥሮስ 2:9) አምላክ የሚደርስብን መከራ እንዲቀጥል ይፈቅድ ይሆናል፤ ያም ሆኖ ግን ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችለንን ጥበብና ጸንተን እንድንቆም የሚረዳንን ጥንካሬ ይሰጠናል። መቋቋም ከምንችለው በላይ እንድንፈተን አይፈቅድም።—1 ቆሮንቶስ 10:13፤ ዕብራውያን 10:36፤ ያዕቆብ 1:5-8
71:5, 17:- ዳዊት በወጣትነት ዕድሜው፣ ሌላው ቀርቶ ከግዙፉ ፍልስጥኤማዊ ከጎልያድ ጋር ከመጋጠሙ በፊት እንኳ በይሖዋ በመታመኑ ድፍረትና ብርታት ሊኖረው ችሏል። (1 ሳሙኤል 17:34-37) ወጣቶችም እንዲሁ ማንኛውንም ነገር ሲያደርጉ በይሖዋ መታመን ይኖርባቸዋል።
“ምድርም ሁሉ በክብሩ ይሞላ”
በመዝሙር ሁለተኛ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የመጨረሻው መዝሙር ማለትም መዝሙር 72 ስለ ሰሎሞን ግዛት የሚናገር ነው። ይህም በመሲሐዊው ግዛት ወቅት ለሚከናወነው ሁኔታ ጥላ ነው። ሰላም እንደሚሰፍን፣ ጭቆናና ዓመጽ እንደሚቀር እንዲሁም በምድር ሁሉ የተትረፈረፈ እህል እንደሚኖር የተገለጸ በመሆኑ አስደሳች በረከት እናገኛለን! መሲሐዊው መንግሥት ከሚያስገኛቸው ከእነዚህና ከሌሎች በረከቶች ተካፋይ ከሚሆኑት መካከል እኛም እንገኝ ይሆን? ይህን ማግኘት የምንችለው እንደ መዝሙራዊው ይሖዋን መጠጊያችንና ኃይላችን አድርገን እርሱን ተስፋ የምናደርግ ከሆነ ነው።
‘የዳዊት ጸሎት የተፈጸመው’ እንዲህ በሚሉት ቃላት ነው:- “ብቻውን ድንቅ ነገር የሚያደርግ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። ክቡር ስሙ ለዘላለም ይባረክ፤ ምድርም ሁሉ በክብሩ ይሞላ። አሜን፤ አሜን።” (መዝሙር 72:18-20) እኛም እንደ ዳዊት ይሖዋን ከልባችን እንባርከው፤ ክቡር ስሙንም እናወድስ።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የንጉሥ ልጅ” የተባለችው ማንን እንደምታመለክት ታውቃለህ?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሩሳሌም “ፍጹም ውብ” የተባለችው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?