የይሖዋ ምሕረት ተስፋ ከመቁረጥ ያድነናል
“አቤቱ፣ እንደ ቸርነትህ [ፍቅራዊ ደግነትህ አዓት] መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።” — መዝሙር 51:1
1, 2. አንድ የይሖዋ አገልጋይ በከባድ ኃጢአት ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
የይሖዋን ሕግ ተላልፎ ከቅጣት ወይም ከጉዳት ሊያመልጥ የሚችል ሰው የለም። በአምላክ ላይ አንድ ከባድ ኃጢአት ብንሠራ ይህን በግልጽ ለመረዳት እንችላለን። ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ስናገለግል የቆየን ብንሆንም እንኳን ሕጉን መተላለፋችን ትልቅ ጭንቀት ወይም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ያሳድርብናል። ይሖዋ ጨርሶ እንደተወንና እርሱን ለማገልገል የማንበቃ ሰዎች እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ኃጢአታችን ጥቅጥቅ እንዳለ ጉም የአምላክን ሞገስ ብርሃን እንደከለለብን ሆኖ ይሰማናል።
2 የጥንትዋ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሊወድቅ የቻለው እንዴት ነበር?
የተሳሳቱ እርምጃዎች ከባድ ኃጢአት ወደ መሥራት ሊያመሩ ይችላሉ
3, 4. ዳዊት ብልጽግና አግኝቶ በነበረበት አንድ ወቅት ላይ ምን አጋጠመው?
3 ዳዊት አምላክን የሚወድ ሰው ነበር፤ ይሁን እንጂ የተሳሳቱ እርምጃዎች መውሰዱ ከባድ ኃጢአት ወደመፈጸም አድርሶታል። (ከገላትያ 6:1 ጋር አወዳድር።) ይህ በዳዊት ላይ የደረሰው ሁኔታ በማንም ፍጹም ያልሆነ ሰው ላይ፣ በተለይም በሌሎች ላይ ሥልጣን ባለው ሰው ላይ በቀላሉ ሊደርስ የሚችል ነው። ዳዊት ባለጠጋ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ዝናና ሥልጣን ነበረው። ቃሉን ለመጣስ የሚደፍር ሰው አልነበረም። ከፍተኛ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ሰዎች የእርሱን ቃል ለመፈጸምና እርሱን ለማገልገል በተጠንቀቅ ይጠባበቁ ነበር። ቢሆንም ዳዊት ሚስቶችን በማብዛትና ሕዝቡን በመቁጠር በደል ሠርቶአል። — ዘዳግም 17:14–20፤ 1 ዜና መዋዕል 21:1
4 ዳዊት ቁሳዊ ብልጽግና ባገኘበት በዚህ ወቅት በአምላክና በሰው ላይ ከባድ ኃጢአት ሠራ። ተከታትለው የተፈጸሙ ድርጊቶች ሠይጣን በሸረበው የወጥመድ መረብ ውስጥ እንዲወድቅ አደረጉት። ሕዝቦቹ የሆኑት እስራኤላውያን ከአሞናውያን ጋር በሚዋጉበት ጊዜ እርሱ ግን በቤቱ ሰገነት ላይ ሆኖ ቆንጆይቱ የኦርዮን ሚስት ስትታጠብ ይመለከት ነበር። ኦርዮን በውጊያ ላይ ስለነበረ ንጉሡ ሴቲቱን ወደ ቤተ መንግሥት አስመጥቶ ከእርሷ ጋር ምንዝር ፈጸመ። እንዳረገዘች በሰማ ጊዜ ምን ያህል እንደደነገጠ ልትገምቱ ትችላላችሁ። ዳዊት ኦርዮን መጥቶ ሌሊቱን ከሚስቱ ከቤርሳቤህ ጋር አድሮ ሕጻኑ የኦርዮ ልጅ እንዲባል በማሰብ ኦርዮንን ከጦር ሜዳ አስጠራው። ዳዊት ቢያሰክረውም እንኳን ኦርዮ ከሚስቱ ጋር ለመተኛት እምቢተኛ ሆነ። በዚህ ጊዜ በጭንቀት የተዋጠው ዳዊት ለጦር አዛዡ ለኢዮአብ ኦርዮንን ሊገደል በሚችልበት በውጊያ የመጀመሪያ ረድፍ እንዲያሰልፈው አዘዘው። ኦርዮን በውጊያው ላይ ሞተ። ሚስቱም የተለመደውን የሐዘን ጊዜ ከጨረሰች በኋላ ማርገዝዋ በሰዎች ዘንድ ከመታወቁ በፊት ዳዊት አገባት። — 2 ሳሙኤል 11:1–27
5. ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ከሠራ በኋላ ምን ሆነ? ኃጢአቱስ በራሱ ላይ ምን ውጤት አስከተለበት?
5 አምላክ በነቢዩ ናታን አማካኝነት የዳዊትን ኃጢአት ካጋለጠ በኋላ “ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሳብሃለሁ” አለው። በዚሁ መሠረት ቤርሳቤህ የወለደችው ሕፃን ሞተ። (2 ሳሙኤል 12:1–23) የዳዊት የበኩር ልጅ የሆነው አምኖን የአባቱ ልጅ የሆነችውን ትዕማርን ካስነወራት በኋላ በወንድሟ ተገደለ። (2 ሳሙኤል 13:1–33) አቤሴሎም የተባለው የንጉሡ ልጅ የአባቱን ዙፋን ለመቀማት ሙከራ ካደረገ በኋላ ከዳዊት ቁባቶች ጋር በመተኛት አባቱን አዋረደ። (2 ሳሙኤል 15:1 እስከ 16:22) የእርስ በርሱ ጦርነት በአቤሴሎም ሞት ቢያቆምም ለዳዊት ተጨማሪ ሐዘን አስከተለበት። (2 ሳሙኤል 18:1–33) ይሁን እንጂ ዳዊት የሠራው ኃጢአት ትሁት እንዲሆንና ርህሩህ ከሆነው አምላኩ ጋር ተቀራርቦ መኖር በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘብ አድርጎታል። እኛም ብንሳሳትና ብንበድል በትህትና ንሥሐ ገብተን ወደ ይሖዋ እንቅረብ። — ከያዕቆብ 4:8 ጋር አወዳድር።
6. የንጉሥ ዳዊት በደል ልዩ የነበረው በምን ምክንያት ነው?
6 በተለይ የዳዊት በደል ልዩ ነበር፤ ምክንያቱም እሥራኤላዊ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋን ሕግ በሚገባ የሚያውቅ ሰው ነበር። (ዘዳግም 17:18–20) የይሖዋን ሕግ የማያውቅ የግብጻውያን ፈርኦን ወይም የባቢሎናውያን ንጉሥ ስላልነበረ አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች በተለምዶ የሚያደርግ ሰው አልነበረም። (ከኤፌሶን 2:12፤ 4:18 ጋር አወዳድር) ዳዊት ለይሖዋ ከተወሰነው ብሔር አባል ስለነበረ ምንዝርና ሰውን መግደል ከባድ ኃጢአቶች እንደሆኑ ያውቅ ነበር። (ዘጸአት 20:13, 14) ክርስቲያኖችም እንደዚሁ የአምላክን ሕግ ያውቃሉ። ቢሆንም አንዳንዶቹ ልክ እንደ ዳዊት የኃጢአተኛነት ባሕርይና ሰብዓዊ ድካም ስለሚኖራቸው እንዲሁም ወደ ክፉ ድርጊት የሚገፋፋ ፈተና ሲያጋጥማቸው ካልተቃወሙት የአምላክን ሕግ ይጥሳሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ በማናችንም ላይ ቢደርስ መንፈሳዊ ብርሃናችንን በሚያጨልምና በተስፋ መቁረጥ ግርዶሽ ውስጥ በሚጥለን ሁኔታ ውስጥ መኖር አይገባንም።
መናዘዝ የመንፈስ እረፍት ያስገኛል
7, 8. (ሀ) ዳዊት ኃጢአቱን ለመሰወር በሞከረ ጊዜ ምን ሆነ? (ለ) የተሠራውን ኃጢአት መናዘዝና መተው ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?
7 የአምላክን ሕግ በከባድ ሁኔታ ተላልፈን ከነበረ ኃጢአታችንን ለይሖዋ እንኳን መናዘዝ አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። እንደነዚህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ስንወድቅ ምን ሊደርስብን ይችላል? ዳዊት በመዝሙር 32 ላይ የሚከተለውን የእምነት ቃል ሰጥቶአል:- “ሁልጊዜ ከመጮሄ የተነሳ [መናዘዝ ስችል] ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤ በቀንና በሌሊት እጅህ [የይሖዋ እጅ] ከብዳብኛለችና፣ እርጥበቴም ለበጋ ትኩሳት ተለወጠ።” (ቁጥር 3, 4) ከአምላክ መንገድ ወጥቶ የነበረው ዳዊት ኃጢአቱን ለመሰወርና የሕሊናውን ወቀሳ ለማፈን ያደረገው ጥረት በጣም አድክሞት ነበር። ያደረበት የጭንቀት ስሜት ጉልበቱን በሙሉ ስላሟጠጠበት እርጥበት እንደሌለው በድርቅ የተመታ ዛፍ ሆኖ ነበር። እንዲያውም የአእምሮውና የአካሉ ጤንነት ሳይታወክበት አልቀረም። ያም ሆነ ይህ ደስታ አጥቶ ነበር። ማናችንም እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ብንወድቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
8 ኃጢአታችንን ለአምላክ መናዘዝ ይቅርታና የመንፈስ እረፍት ሊያስገኝልን ይችላል። ዳዊት “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ” ሲል ዘምሮአል። (መዝሙር 32:5) የተሰወረ ኃጢአት በመሥራትህ ምክንያት ተጨንቀሃልን? የአምላክን ምሕረት እንድትቀበል ኃጢአትህን ብትናዘዝና ብትተወው የተሻለ አይሆንምን? ለምን የጉባዔውን ሽማግሌዎች ጠርተህ መንፈሳዊ ፈውስ ለማግኘት አትጥርም? (ምሳሌ 28:13፤ ያዕቆብ 5:13–20) ያሳየኸው የንሥሐ መንፈስ ግምት ውስጥ ይገባል። ደስታህም ከጊዜ በኋላ ሊመለስልህ ይችላል። “መተላለፉ የቀረችለት፣ ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው። እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በደልን የማይቆጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው” ሲል ዳዊት ተናግሯል። — መዝሙር 32:1, 2
9. መዝሙር 51 የተጠናቀረው መቼ ነበር? ለምንስ?
9 ዳዊትና ቤርሳቤህ ስለሠሩት በደል በአምላክ ከመጠየቅ ሊያመልጡ አልቻሉም። ኃጢአታቸው ሊያስገድላቸው የሚችል ቢሆንም አምላክ ምሕረት አድርጎላቸዋል። በተለይ ለዳዊት ምሕረት ያደረገለት ይሖዋ ገብቶለት በነበረው የመንግሥት ቃል ኪዳን ምክንያት ነው። (2 ሳሙኤል 7:11–16) ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር በሠራው ኃጢአት ምን ያህል ተጸጽቶ እንደነበረ ከመዝሙር 51 መረዳት ይቻላል። ልቡ በጸጸት ተመትቶ የነበረው ንጉሥ ይህን ልብ የሚነካ መዝሙር ያጠናቀረው ነቢዩ ናታን በመለኮታዊው ሕግ ላይ የሠራው በደል ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ሕሊናውን አንቅቶ ካስገነዘበው በኋላ ነበር። ነቢዩ ናታን የዳዊትን ኃጢአት ገልጦ ለመናገር ድፍረት አስፈልጎት ነበር። ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሌሎችን በደል ሲያስታውቁ ደፋሮች መሆን ያስፈልጋቸዋል። ንጉሡ ኃጢአቱን ከመካድና ናታን እንዲገደል ከማዘዝ ይልቅ ራሱን ዝቅ አድርጎ ኃጢአቱን ተናዘዘ። (2 ሳሙኤል 12:1–14) መዝሙር 51 ዳዊት እንዲህ ባለው ወራዳ ሁኔታ ወድቆ በነበረበት ጊዜ ለአምላክ በጸሎት የተናገረው ቃል ነው። እኛም በተለይ በደል ፈጽመን የይሖዋን ምሕረት ለማግኘት የምንናፍቅ ከሆንን ይህንን መዝሙር በጸሎታችን ብናሰላስለው ጥሩ ይሆናል።
በአምላክ ዘንድ ተጠያቂዎች ነን
10. ዳዊት ቀድሞ ወደነበረው መንፈሳዊ ሁኔታ ሊመለስ ይችል የነበረው እንዴት ብቻ ነው?
10 ዳዊት ኃጢአቱን ለምን እንደሠራ ሰበብ ለመፍጠር አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ “አቤቱ እንደ ቸርነትህ [ፍቅራዊ ደግነትህ አዓት] መጠን ማረኝ። እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ” ሲል ጸለየ። (መዝሙር 51:1) ዳዊት በመተላለፉ የአምላክን ሕግ ድንበር ዘልሎአል። ይሁን እንጂ አምላክ በፍቅራዊ ደግነቱ ወይም በታማኝ ፍቅሩ ተገፋፍቶ ሞገስ ቢያሳየው ወደ ቀድሞው መንፈሳዊ ሁኔታ ሊመለስ ይችላል። አምላክ ከዚህ በፊት የፈጸማቸው ብዙ የምሕረት ድርጊቶች ንሥሐ የገባው ንጉሥ ፈጣሪው መተላለፉን እንደሚሽርለት የጸና እምነት አሳድሮበታል።
11. በሥርየት ቀን ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች ምን ያመለክታሉ? ዛሬስ ለመዳን ምን ያስፈልጋል?
11 ይሖዋ በሥርየት ቀን ይቀርቡ የነበሩትን መሥዋዕቶች እንደ ጥላ አድርጎ በመጠቀም ንሥሐ የሚገቡ ሰዎችን ኃጢአት ከበደላቸው የሚያነጻበት መንገድ እንዳለው ፍንጭ ሰጥቶአል። አምላክ ምሕረቱንና ይቅርታውን የሚዘረጋልን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነት መሠረት እንደሆነ አሁን እናውቃለን። ዳዊት በይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና ምሕረት ሊታመን የቻለው ለዚህ መሥዋዕት ጥላና አምሳያ የሆኑትን መሥዋዕቶች በማሰብ ብቻ ከነበረ ዛሬ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች አምላክ ለመዳናቸው በሰጣቸው ቤዛ ምን ያህል የበለጠ እምነት ማሳየት ይገባቸዋል! — ሮሜ 5:8፤ ዕብራውያን 10:1
12. ኃጢአት መሥራት ማለት ምን ማለት ነው? ዳዊት ስለሠራው መጥፎ ድርጊት እንዴት ተሰምቶታል?
12 ዳዊት እንደሚከተለው በማለት አምላክን ተማጽኖአል:- “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፣ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።” (መዝሙር 51:2, 3) ኃጢአት መሥራት ማለት የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ዒላማ መሳት ማለት ነው። ይህ ሁኔታ በዳዊት ላይ ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ስለሠራው በደል ግድ የሌለው፣ ቅጣት ስለደረሰበት ብቻ ወይም በሽታ ይይዘኝ ይሆናል ብሎ ያዘነ ነፍሰ ገዳይ ወይም አመንዝራ አልነበረም። ዳዊት ይሖዋን የሚወድ ሰው ስለነበረ ክፉ የሆነውን ነገር ይጠላ ነበር። (መዝሙር 97:10) በሠራው ኃጢአት ይሰቀቅ ስለነበረ አምላክ ሙሉ በሙሉ አጥቦ እንዲያጠፋለት ጸልዮአል። ዳዊት መተላለፉን በሚገባ ይገነዘብ ስለነበረ የኃጢአት ፍላጎቱ እንዲያሸንፈው በመፍቀዱ በጣም አዝኖአል። ኃጢአቱም ሁልጊዜ በፊቱ ይታየው ነበር። ምክንያቱም አንድ አምላክን የሚፈራ ሰው ንሥሐ ገብቶና ተናዝዞ የይሖዋን ይቅርታ እስካላገኘ ድረስ ሕሊናው እረፍት አይሰጠውም።
13. ዳዊት በአምላክ ላይ ብቻ ኃጢአት እንደሠራ ሊናገር የቻለው ለምን ነበር?
13 ዳዊት በአምላክ ዘንድ ተጠያቂነት እንዳለበት ማመኑን እንደሚከተለው በማለት አመልክቶአል:- “አንተን ብቻ በደልሁ፣ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፣ በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።” (መዝሙር 51:4) ዳዊት የአምላክን ሕግ ተላልፎአል። የንግሥና ሥልጣኑንም አቃልሎአል። ከዚህም በላይ “ታላቅ የስድብ ምክንያት” በማድረግ ይሖዋን አሰድቦአል። (2 ሳሙኤል 12:14፤ ዘጸአት 20:13, 14, 17) በተጨማሪም ዳዊት ያደረጋቸው የኃጢአት ሥራዎች በእስራኤላውያን ኅብረተሰብና በራሱ ቤተሰብ ላይ የተሠሩ በደሎች ነበሩ። ልክ በአሁኑ ጊዜ አንድ የተጠመቀ በደለኛ በክርስቲያን ጉባዔና በሚወዱት ሰዎች ላይ ሐዘንና ብስጭት እንደሚያመጣው ማለት ነው። ንሥሐ የገባው ይህ ንጉሥ እንደ ኦርዮን ባሉት ሰዎች ላይ ኃጢአት እንደሠራ ቢገነዘብም በይበልጥ በኃላፊነት የሚጠየቀው በይሖዋ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ከዘፍጥረት 39:7–9 ጋር አወዳድር) የይሖዋ ፍርድ ጻድቅ እንደሚሆን ዳዊት ተናግሮአል። (ሮሜ 3:4) ኃጢአት የሠሩ ክርስቲያኖችም ይህን የመሰለ አመለካከት ሊኖራቸው ያስፈልጋል።
ኃጢአት ለመሥራት በከፊል ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች
14. ዳዊት ኃጢአት ለመሥራት በከፊል ምክንያት የሚሆኑ ምን ነገሮችን ጠቀሰ?
14 ዳዊት ያደረገው ነገር ትክክል እንደነበረ ለማሳመን ባይሞክርም “እነሆ፣ በዓመጻ ተፀነስሁ፣ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ” ብሎአል። (መዝሙር 51:5) ዳዊት የተወለደው ከኃጢአት ጋር ነበር። እናቱም በወረሰችው ኃጢአት ምክንያት በምጥ ተሰቃይታለች። (ዘፍጥረት 3:16፤ ሮሜ 5:12) የጋብቻንና ልጅ የመውለድን ሥጦታ የሰጠው አምላክ ራሱ ስለሆነ ትክክለኛ የሆነ የጋብቻ ግንኙነት፣ መጸነስና መውለድ ኃጢአት ነው ማለቱ አልነበረም። በተጨማሪም ዳዊት እናቱ ስለሠራችው የተለየ ኃጢአት መናገሩ አልነበረም። በኃጢአት የተጸነሰው ወላጆቹ እንደ ማንኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው ኃጢአተኞች ስለነበሩ ነው። — ኢዮብ 14:4
15. አምላክ ወደ ኃጢአት መውደቅን ቀላል የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ የሚያስገባ ቢሆንም ምን ማድረግ አይገባንም?
15 ኃጢአት ሠርተን እንደሆነ ለድርጊቱ ምክንያት የሆነ ወይም አስተዋጽኦ ያደረገ ማንኛውም ዓይነት ነገር ለአምላክ በጸሎት ልንገልጽ እንችላለን። ይሁን እንጂ ይገባናል የማንለውን የአምላክን ደግነት ለሴሰኝነት ማሳበቢያ ማድረግ ወይም የወረስነውን ኃጢአት ለሠራነው ኃጢአት በኃላፊነት እንዳንጠየቅ የምንሸሸግበት መጋረጃ ማድረግ አይገባንም። (ይሁዳ 3, 4) ዳዊት ንፁሕ ያልሆኑ ሐሳቦችን ማስተናገዱና ለፈተና መሸነፉ ላስከተለበት ጥፋት በኃላፊነት መጠየቅ እንደሚገባው አምኖአል። እኛም ብንሆን ለፈተና ተጋልጠን እንዳንጣል እየጸለይን ከዚህ ጸሎታችን ጋር የሚስማማ ድርጊት እንፈጽም። — ማቴዎስ 6:13
ንጹሕ ለመሆን ጸሎት ማቅረብ
16. አምላክ የሚደሰተው በየትኛው ባሕርይ ነው? ይህስ ጠባያችንና አኗኗራችንን እንዴት ሊነካው ይገባል?
16 ሰዎች ለአምላክ ያደሩና ጨዋ ሰዎች መስለው ይታዩ ይሆናል። ይሖዋ ግን የሚያየው ላይ ላዩን ሳይሆን ውስጣቸውን ነው። ዳዊት “እነሆ፣ አንተ [ይሖዋ] በውስጠኛ ክፍሎች እውነት ትደሰታለህ፣ በምሥጢራዊው ሰውነቴ ጥበብን እንዳውቅ አድርገኝ” ብሎአል። (መዝሙር 51:6 አዓት) ዳዊት ኦርዮንን ለማስገደልና የቤርሳቤህን እርግዝና ደብቆ ለማስቀረት ባደረገው ጥረት ብዙ ሐሰትና ሽንገላ ፈጽሞአል። ቢሆንም አምላክ በእውነትና በቅድስና እንደሚደሰት ያውቅ ነበር። ይህም በምግባራችን ላይ በጎ ተጽእኖ ሊያስከትል ይገባል። ምክንያቱም ሸንጋዮችና አታላዮች ብንሆን ይሖዋ ያወግዘናል። (ምሳሌ 3:32) በተጨማሪም ዳዊት አምላክ ንሥሐ በመግባቱ ምክንያት ‘ጥበብን እንዲያውቅ’ ቢያደርገው በቀረው የሕይወት ዘመኑ በሙሉ ከመለኮታዊ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር።
17. በሂሶጵ አንጻኝ ብሎ መጸለይ ትርጉሙ ምንድን ነው?
17 መዝሙራዊው የኃጠአት ዝንባሌዎቹን ለማሸነፍ የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ስለተገነዘበ “በሂሶጵ እርጨኝ፣ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ፣ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 51:7) የሂሶጵ ተክል ከሌሎች ነገሮች ጋር ሆኖ በለምጽ [በቁምጥና አዓት] ተይዘው የነበሩ ሰዎችን ለማንጻት በሚደረገው ሥርዓት ያገለግል ነበር። (ዘሌዋውያን 14:2–7) ስለዚህ ዳዊት በሂሶጵ ከኃጢአቱ እንዲነጻ መጸለዩ ተገቢ ነበር። በተጨማሪም ሙሉ በሙሉ ንጹሕ እንዲሆን፣ ምንም ዓይነት ቆሻሻ ካልነካው በረዶ የበለጠ ነጭ እንዲሆን ይሖዋ እንዲያጥበው መለመኑ ንጹሕ የመሆን ፍላጎት እንደነበረው ያመለክታል። (ኢሳይያስ 1:18) ማናችንም ብንሆን አንድ ዓይነት በደል በመሥራታችን ምክንያት ሕሊናችን የሚወቅሰን ከሆነ ንሥሐ ገብተን አምላክ ይቅርታ እንዲያደርግልን ብንጸልይ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ሊያነጻንና ሊያጠራን እንደሚችል እምነት ይኑረን።
ወደ ቀድሞው ጥሩ ሁኔታ ለመመለስ የቀረበ ልመና
18. ዳዊት ንሥሐ ከመግባቱና ከመናዘዙ በፊት እንዴት ባለ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር? ይህን ማወቅስ በአሁኑ ጊዜ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው?
18 የሕሊና ወቀሳ ደርሶበት የነበረ ማንኛውም ክርስቲያን “ሐሴትንና ደስታን አሰማኝ፣ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል” ሲል ዳዊት የተናገራቸውን ቃላት መረዳት አያስቸግረውም። (መዝሙር 51:8) ዳዊት ንሥሐ ከመግባቱና ኃጢአቱን ከመናዘዙ በፊት ሕሊናው ይረብሸው ስለነበረ በጣም ያዝንና ይተክዝ ነበር። ጥሩ መዘምራንና ሙዚቀኞች የሚያሰሙአቸው የደስታና የሐሴት ዝማሬዎች እንኳ አያስደስቱትም ነበር። ኃጢአተኛው ዳዊት የአምላክን ሞገስ በማጣቱ ምክንያት በጣም ይጨነቅ ስለነበረ አጥንቶቹ እንደተቀጠቀጡበት ሰው ብርቱ ሕመም ይሰማው ነበር። ይቅርታ ለማግኘት፣ መንፈሱ እንዲታደስለትና ቀድሞ የነበረው ደስታ እንዲመለስለት በብርቱ ናፍቆአል። ዛሬም ቢሆን አንድ ንሥሐ የገባ በደለኛ ከአምላክ ጋር የነበረውን ዝምድና ከማበላሸቱ በፊት የነበረውን ደስታ ለማግኘት ከፈለገ የይሖዋን ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገዋል። አንድ ንሥሐ የገባ ሰው የነበረውን “የመንፈስ ቅዱስ ደስታ” መልሶ ካገኘ ይሖዋ ይቅር ብሎታል፣ ይወደዋል ማለት ነው። (1 ተሰሎንቄ 1:6) ይህም እንዴት ያለ መጽናናትን ያስገኛል!
19. አምላክ ኃጢአቱን ሁሉ ቢደመስስለት ዳዊት እንዴት ይሰማው ነበር?
19 በተጨማሪም ዳዊት “ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፣ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 51:9) ይሖዋ ኃጢአትን በሞገስ ዓይኑ ይመለከታል ብሎ ማሰብ አይቻልም። በዚህም ምክንያት የዳዊትን ኃጢአት እንዳይመለከት ፊቱን እንዲመልስ ተጠይቆአል። በተጨማሪም ንጉሡ አምላክ በደሉንና አመጸኝነቱን በሙሉ እንዲደመስስለት ጸልዮአል። የዳዊት መንፈስ ሊነሳሳ የሚችለው፣ ከተጫነው የሕሊና ወቀሳ ሊገላገል የሚችለውና ንሥሐ የገባው ንጉሥ የሚወደው አምላኩ ይቅርታ እንዳደረገለት ሊያውቅ የሚችለው ይሖዋ ይህን ካደረገለት ብቻ ነው።
አንተም ኃጢአት ሠርተህ ከሆነስ?
20. ከባድ ኃጢአት የሠራ ክርስቲያን ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው እንላለን?
20 ማንኛውም ከባድ ኃጢአት የሠራ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን አገልጋይ ንሥሐ ከገባ አምላክ ሞገስ እንዲያደርግለትና ከኃጢአቱ እንዲያነጻው በእርግጠኝነት ሊጠይቅ እንደሚችል መዝሙር 51 ያመለክታል። አንተም በዚህ መንገድ ከባድ በደል የሠራህ ክርስቲያን ከሆንክ ለምን የሰማዩ አባታችን ይቅርታ እንዲያደርግልህ በጸሎት አትጠይቅም? በፊቱ ሞገስ አግኝተህ ለመቆም ከፈለግህ የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልግህ ግለጽለት። ቀድሞ የነበረህን ደስታ እንዲመልስልህ ጠይቀው። ንሥሐ የገቡ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን የመሰለ ልመናቸውን ለይሖዋ በጸሎት ሊያቀርቡ ይችላሉ። እርሱም “በብዙ ይምራል።” (ኢሳይያስ 55:7፤ መዝሙር 103:10–14) እርግጥ አስፈላጊውን መንፈሳዊ እርዳታ እንዲሰጡ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ቀርቦ ማነጋገር ይገባል። — ያዕቆብ 5:13–15
21. ቀጥለን ምን እንመረምራለን?
21 የይሖዋ ምሕረት ሕዝቦቹን ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ያድናቸዋል። ይሁን እንጂ ንስሐ የገባው ዳዊት በመዝሙር 51 ላይ የሚገኙትን ከልብ የመነጩ ተጨማሪ ልመናዎች እንመርምር። ስለዚሁ ጉዳይ የምናደርገው ጥናት ይሖዋ የተሰበረውን ልብ እንደማይንቅ ያስገነዝበናል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ከባድ ኃጢአት በአንድ የይሖዋ አገልጋይ ላይ ምን ዓይነት ውጤት ሊያስከትል ይችላል?
◻ ዳዊት ኃጢአቱን ለመሰወር በሞከረበት ጊዜ ምን ደርሶበት ነበር?
◻ ዳዊት በአምላክ ላይ ብቻ ኃጢአት ሠራሁ ያለው ለምን ነበር?
◻ ወደ ኃጢአት መግባትን ቀላል የሚያደርጉ ሁኔታዎችን አምላክ ግምት ውስጥ የሚያስገባ ቢሆንም ምን ማድረግ አይገባንም?
◻ አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ሠርቶ ከነበረ ምን ማድረግ ይኖርበታል?