ይሖዋ የተሰበረውን ልብ አይንቅም
“የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፣ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም። — መዝሙር 51:17
1. ይሖዋ ከባድ ኃጢአት ሠርተው ንሥሐ የሚገቡትን አምላኪዎች እንዴት ይመለከታል?
ይሖዋ ‘ጸሎት እንዳያልፍ ወደ ራሱ የሚያደርሰውን መንገድ በደመና መዝጋት’ ይችላል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:44) ይሁን እንጂ ሕዝቦቹ በጸሎት መቅረብ እንዲችሉ ይፈልጋል። ከአምላኪዎቹ አንዱ ከባድ ኃጢአት ቢሠራ እንኳን ኃጢአተኛው ንሥሐ ከገባ ይህ ሰው ቀደም ሲል ያደረጋቸውን መልካም ነገሮች የሰማዩ አባታችን ያስታውሳል። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስትያን ባልንጀሮቹ “እግዚአብሔር . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ አመጸኛ አይደለም” ሊል ችሎአል። — ዕብራውያን 6:10
2, 3. ክርስቲያን ሽማግሌዎች የስህተት ድርጊት የፈጸሙ የእምነት ባልደረቦቻቸውን ጉዳይ በሚመለከቱበት ጊዜ ምን ነገር ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል?
2 በተጨማሪም ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእምነት ባልደረቦቻቸው ለአምላክ የታማኝነት አገልግሎት ሲፈጽሙ የቆዩባቸውን በርካታ ጊዜያት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። ይህም የተሳሳተ እርምጃ የወሰደን ወይም ከባድ ኃጢአት የፈጸመና ንስሐ የገባ ክርስቲያን የሚያቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት ይጨምራል። ክርስቲያን እረኞች ስለአምላክ መንጋ አባላት መንፈሳዊ ደህንነት አጥብቀው ያስባሉ። — ገላትያ 6:1, 2
3 መጥፎ ድርጊት ፈጽሞ ንሥሐ የገባ ግለሰብ የይሖዋ ምሕረት ያስፈልገዋል። ይሁን እንጂ ይህ ብቻውን በቂ አይሆንም። ይህም በመዝሙር 51:10–19 ላይ ባሉት የዳዊት ቃላት ተገልጾአል።
ንጹሕ ልብ ያስፈልጋል
4. ዳዊት ንጹሕ ልብና አዲስ መንፈስ እንዲሰጠው የጸለየው ለምን ነበር?
4 ራሱን የወሰነ አንድ ክርስቲያን በሠራው ኃጢአት ምክንያት በመጥፎ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ከይሖዋ ምህረትና ይቅርታ በተጨማሪ ምን ነገር ሊያስፈልገው ይችላል? ዳዊት “አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” በማለት ተማጽኖአል። (መዝሙር 51:10) ዳዊት ይህን ልመና ያቀረበው ከባድ ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌው ገና ከልቡ እንዳልጠፋ ስለተገነዘበ እንደሆነ ግልጽ ነው። ዳዊት ከቤርሳቤህና ከኦርዮን ጋር በተያያዘ የሠራውን የመሰለ ከባድ ኃጢአት አልሠራን ይሆናል። ቢሆንም ወደ መጥፎ ድርጊት በሚመሩ ፈተናዎች ከመሸነፍ ለመዳንና በማንኛውም ከባድ ኃጢአት ከመካፈል ለመራቅ የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። እንዲያውም ከሥርቆትና ከነፍስ ግድያ ጋር የሚተካከል ክብደት ካላቸው እንደ መጎምጀትና እንደ ጥላቻ የመሰሉትን ባሕርያት ከልባችን ለማውጣት መለኮታዊ እርዳታ ሊያስፈልገን ይችላል። — ቆላስይስ 3:5, 6፤ 1 ዮሐንስ 3:15
5. (ሀ) ንጹሕ ልብ ማግኘት ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) ዳዊት አዲስ መንፈስ እንዲሰጠው በጠየቀ ጊዜ የፈለገው ነገር ምን ነበር?
5 ይሖዋ አገልጋዮቹ በሙሉ “ንጹሕ ልብ” ማለትም የሐሳብና የዓላማ ንጽሕና እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ዳዊትም እንዲህ ዓይነቱን ንጽሕና እንዳላሳየ ስለተገነዘበ ልቡን እንዲያጠራለትና ከመለኮታዊ የአቋም ደረጃዎች ጋር እንዲስማማ እንዲያደርግለት ጸልዮአል። በተጨማሪም መዝሙራዊው አዲስና ቅን መንፈስ ወይም የአእምሮ ዝንባሌ እንዲኖረው ፈልጎአል። ወደ ኃጢአት የሚገፋፉ ፈተናዎችን ለመቋቋምና የይሖዋን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲጠብቅ የሚያስችለው መንፈስ አስፈልጎታል።
መንፈስ ቅዱስ በጣም አስፈላጊ ነው
6. ዳዊት ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዳይወስድበት የጸለየው ለምን ነበር?
6 በስህተታችንና በሠራነው መጥፎ ድርጊት ምክንያት ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ አምላክ ሊጥለንና ቅዱስ መንፈሱን ወይም አንቀሳቃሽ ኃይሉን ከእኛ ሊወስድ እንደተቃረበ ሊሰማን ይችላል። ዳዊት እንደዚህ ተሰምቶት ነበር። “ከፊትህ አትጣለኝ፣ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ” የሚል ልመና ያቀረበው በዚህ ምክንያት ነበር። (መዝሙር 51:11) እጅግ አዝኖና ተጸጽቶ የነበረው ዳዊት በኃጢአቱ ምክንያት ይሖዋን ለማገልገል የማይበቃ ሰው እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ከአምላክ ፊት መጣል ማለት የእርሱን በረከት፣ ሞገስና ማጽናኛ ማጣት ማለት ነው። ዳዊት ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ ሁኔታው እንዲመለስ ከተፈለገ የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ማግኘት ይኖርበታል። የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ በንጉሡ ላይ ካረፈ ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስችለውን መለኮታዊ መመሪያ እንዲያገኝ በጸሎት ሊጠይቅ፣ ከኃጢአት ሊርቅና በጥበብ ሊያስተዳድር ይችላል። ዳዊት የመንፈስ ቅዱስ ሰጪ በሆነው አምላክ ላይ ኃጢአት መሥራቱን ተገንዝቦ ይሖዋ መንፈሱን እንዳይወሰድበት መማጸኑ ተገቢ ነው።
7. መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን መጸለይና መንፈሱንም እንዳናሳዝን መጠንቀቅ የሚገባን ለምንድን ነው?
7 እኛስ? መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን መጸለይና የመንፈስ ቅዱስን መመሪያ ባለመከተል እርሱን ከማሳዘን መጠበቅ ይገባናል። (ሉቃስ 11:13፤ ኤፌሶን 4:30) ይህን ሳናደርግ ብንቀር መንፈሱን ልናጣና የዚህ መንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ ጥሩነትን፣ እምነትን፣ የዋህነትንና ራስን መግዛትን ማሳየት ሊያቅተን ይችላል። በተለይ ንሥሐ ባለመግባት ኃጢአት መሥራታችንን ብንቀጥል ይሖዋ አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ይወስድብናል።
የማዳን ደስታ
8. ኃጢአት ሠርተን ከነበረ የመዳን ደስታ ለማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
8 መንፈሣዊ ተሐድሶ ያገኘ ንሥሐ የገባ ክርስቲያን ዳግመኛ በይሖዋ የመዳን ዝግጅት ሊደሰት ይችላል። ዳዊትም ይህንን በመናፈቅ “የማዳንህን ደስታ ስጠኝ፣ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ” ሲል ተማጽኖአል። (መዝሙር 51:12) ይሖዋ አምላክ በሚሰጠው የተረጋገጠ የመዳን ተስፋ ሐሴት ማድረግ ምንኛ ግሩም ነገር ነው! (መዝሙር 3:8) ዳዊት በአምላክ ላይ ኃጢአት ከሠራ በኋላ የመዳን ደስታ እንዲመለስለት በጸሎት ጠይቆአል። ይሖዋ በኋለኞቹ ዘመናት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በኩል የመዳን ዝግጅት አድርጓል። እኛም ራሳችንን የወሰንን የአምላክ አገልጋዮች ሆነን እያለ ከባድ ኃጢአት ከሠራን በኋላ የመዳን ደስታ እንዲመለስልን የምንፈልግ ከሆንን ንሥሐ የመግባት ዝንባሌ እንዲኖረንና በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት እስከመሥራት የሚያደርስ ከባድ ኃጢአት እንዳንሠራ መጠንቀቅ ይኖርብናል። — ማቴዎስ 12:31, 32፤ ዕብራውያን 6:4–6
9. ዳዊት ይሖዋ “በእሽታ መንፈስ” እንዲደግፈው ሲጠይቅ ምን መለመኑ ነበር?
9 ዳዊት ይሖዋ “በእሽታ መንፈስ” እንዲደግፈው ጠይቋል። ይህ የእሽታ ወይም የፈቃደኝነት መንፈስ የሚያመለክተው አምላክ ለመርዳት ፈቃደኛ መሆኑን ወይም ቅዱስ መንፈሱን ሳይሆን ዳዊትን የሚገፋፋውን የአእምሮ ዝንባሌ ነው። ዳዊት አምላክ ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርግና ዳግመኛ ወደ ኃጢአት እንዳይገባ የሚያስችለውን የፈቃደኝነት መንፈስ በመስጠት እንዲደግፈው ጸልዮአል። ይሖዋ አምላክ አገልጋዮቹን ዘወትር ይደግፋል። በተለያዩ ፈተናዎች የጎበጡትን አገልጋዮቹን ቀና ያደርጋል። (መዝሙር 145:14) ይህን መገንዘባችን፣ በተለይ በደል ሠርተን የተጸጸትንና ከእንግዲህ ወዲህ አምላክን በታማኝነት ለማገልገል የወሰንን ከሆንን በጣም ያጽናናናል።
ሕግ ተላላፊዎች የሚማሩት ምንድን ነው?
10, 11. (ሀ) ዳዊት ሕግ ተላላፊ እስራኤላውያንን ምን ነገር ሊያስተምራቸው ይችላል? (ለ) ዳዊት ኃጢአተኞችን ሊያስተምር ይችል የነበረው ራሱ ምን ካደረገ በኋላ ብቻ ነው?
10 አምላክ ከፈቀደለት ዳዊት ለይሖዋ ምህረት ያለውን አድናቆት የሚያሳይና ሌሎች ሰዎችን የሚጠቅም ከራስ ወዳድነት የራቀ ሥራ ለመሥራት ፈልጎአል። ንሥሐ የገባው ንጉሥ ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ቀጥሎ “ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፣ ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ” ብሎአል። (መዝሙር 51:13) ኃጢአተኛው ዳዊት የአምላክን ሕግ ተላላፊዎች ሊያስተምር የሚችለው እንዴት ነው? ምን ነገር ሊነግራቸው ይችላል? ይህስ ምን ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?
11 ዳዊት እሥራኤላውያን ሕግ ተላላፊዎችን ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ በማሰብ የይሖዋን መንገድ በሚያሳያቸው ጊዜ ኃጢአት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ፣ ንሥሐ ምን እንደሆነና የአምላክን ምህረት እንዴት ለማግኘት እንደሚቻል ሊነግራቸው ይችላል። ዳዊት የይሖዋን ሞገስ ማጣትና የሕሊና ጸጸት ምን ያህል እንደሚያሰቃይ ስለቀመሰ ንሥሐ ለገቡና ልባቸው ለተሰበረ ኃጢአተኞች ርህሩህ አስተማሪ ሊሆን ይችላል። እርግጥ፣ የራሱን ምሳሌ በመጥቀስ ሌሎችን ለማስተማር የሚችለው እርሱ ራሱ የይሖዋን የአቋም ደረጃዎች ከተቀበለና የይሖዋን ይቅርታ ካገኘ በኋላ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም በመለኮታዊ ሕግጋት ለመገዛት የማይፈልጉ ሰዎች የአምላክን ሕግጋት ለሌሎች ለማስተማር አይችሉም። — መዝሙር 50:16, 17
12. ዳዊት አምላክ ከደም ወንጀል እንዳዳነው ከማወቁ ጥቅም ያገኘው እንዴት ነው?
12 ዳዊት ፍላጎቱን በሌላ አነጋገር ሲገልጽ “የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ከደም አድነኝ፣ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች” ብሎአል። (መዝሙር 51:14) የደም ወንጀል የሞት ቅጣት ያስከትላል። (ዘፍጥረት 9:5, 6) ስለዚህ ዳዊት የመድኃኒቱ አምላክ በኦርዮን ላይ ከፈጸመው የደም ወንጀል እንዳዳነው ማወቁ የልብና የአእምሮ ሰላም ይሰጠዋል። ከዚያ በኋላ አንደበቱ ስለራሱ ሳይሆን ስለአምላክ ጽድቅ በደስታ ሊዘምር ይችላል። (መክብብ 7:20፤ ሮሜ 3:10) ማንኛውም በዘመናችን የሚኖር ሰው በዝሙት ያረከሰውን ሰው ንጽሕና ሊመልስ ወይም የገደለውን ሰው ከሞት ሊያስነሳ እንደማይችል ሁሉ ዳዊትም የሠራውን የምንዝር ኃጢአት ሊፍቅ ወይም ኦርዮንን ከመቃብር ሊያወጣ አይችልም። ኃጢአት ለመሥራት በምንፈተንበት ጊዜ ይህን ማሰብ አይገባንምን? ይሖዋ በጽድቅ ላሳየን ምህረት ምን ያህል አድናቂዎች መሆን ይገባናል! እንዲያውም ለይሖዋ ምህረት ያለን አድናቆት ሌሎች ሰዎችን ወደዚህ የጽድቅና የይቅርታ ምንጭ እንድንመራ ሊገፋፋን ይገባል።
13. አንድ ኃጢአተኛ በተገቢ ሁኔታ ከንፈሮቹን ከፍቶ ይሖዋን ሊያወድስ የሚችለው በምን ሁኔታዎች ውስጥ ሲሆን ነው?
13 አምላክ በምህረት ከንፈሮቹን ካልከፈተለት በስተቀር ማንኛውም ኃጢአተኛ ስለ ይሖዋ እውነቶች በመናገር ይሖዋን ለማወደስ ከንፈሮቹን በትክክለኛው መንገድ ለመክፈት አይችልም። በዚህም ምክንያት ዳዊት “አቤቱ፣ ከንፈሮቼን ክፈት፣ አፌም ምስጋናህን ያወራል” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 51:15) ዳዊት አምላክ ይቅርታ ስላደረገለት የሕሊና እረፍት ካገኘ በኋላ ሕግ ተላላፊዎችን ስለ ይሖዋ መንገዶች ሊያስተምርና ይሖዋን ከፍ ከፍ ሊያደርግ ይችላል። ልክ እንደ ዳዊት ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸው ሁሉ ይሖዋ ያሳያቸውን ይገባናል የማይሉትን ደግነት ማድነቅና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የአምላክን እውነት ማወጅና ምስጋናውን መናገር ይኖርባቸዋል። — መዝሙር 43:3
አምላክ የሚቀበላቸው መሥዋዕቶች
14. (ሀ) የሕጉ ቃልኪዳን ምን ዓይነት መሥዋዕቶች እንዲቀርቡ ያዝ ነበር? (ለ) መጥፎ ድርጊት መፈጸማችንን እየቀጠልን አንድ ዓይነት በጎ ተግባር በመፈጸም ልናካክስ እንችላለን ብሎ ማሰብ ስህተት የሚሆነው ለምንድን ነው?
14 ዳዊት ጥልቅ የሆነ ማስተዋል አግኝቶ ስለነበረ “መሥዋዕትን ብትወድስ በሰጠሁህ ነበር፣ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም” ለማለት ችሎአል። (መዝሙር 51:16) የሕጉ ቃል ኪዳን ለአምላክ የእንስሳት መሥዋዕት እንዲቀርብ ያዝ ነበር። ዳዊት የሠራው የምንዝርና ነፍስ የመግደል ወንጀል ግን በሞት የሚያስቀጣው ስለነበረ በእንስሳት መሥዋዕት የሚሠረይ አልነበረም። ሊሠረይ የሚችል ቢሆን ኖር የፈለገውን ያህል ዋጋ ከፍሎ መሥዋዕት ቢያቀርብ ቅር አይለውም ነበር። ልባዊ የሆነ ንሥሐ ከሌለ መሥዋዕት ምንም ዓይነት ዋጋ የለውም። ስለዚህ መጥፎ ድርጊት መፈጸሙን እየቀጠለ አንድ ዓይነት ጥሩ ነገር በመሥራት ላካክስ እችላለሁ ብሎ ማሰብ ስህተት ነው።
15. የተሰበረ መንፈስ ያለው ራሱን የወሰነ ሰው ምን ዓይነት ዝንባሌ ይኖረዋል?
15 ዳዊት በመቀጠል “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፣ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” ብሎአል። (መዝሙር 51:17) አንድ ንሥሐ የገባ ሰው ሊያቀርብ የሚችለው ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት “የተሰበረ መንፈስ” ነው። እንዲህ ያለው ሰው የእልከኝነት መንፈስ አይኖረውም። የተሰበረ መንፈስ ያለው ራሱን ለአምላክ የወሰነ ሰው በሠራው ኃጢአት ምክንያት ልቡ በጣም ያዝናል። አምላክ ሞገሱን እንደነሳው ስለሚታወቀው ራሱን ዝቅ ያደርጋል። መለኮታዊ ሞገስ እንደገና ለማግኘት ሲል ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ነው። ከኃጢአታችን ንሥሐ ከመግባታችንና ሙሉ ልባችንን ሰጥተን ለአምላክ ከማደራችን በፊት ምንም ዓይነት ዋጋ ያለው ነገር ለአምላክ ልናቀርብ አንችልም። — ናሆም 1:2
16. በኃጢአቱ ምክንያት ልቡ የተሰበረውን ሰው ይሖዋ እንዴት ይመለከታል?
16 አምላክ እንደ ተሰበረና እንደ ተቀጠቀጠ ልብ ያለውን መሥዋዕት አልቀበልም አይልም። ስለዚህ ሕዝቦቹ ሆነን ስንኖር ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥመን ተስፋ መቁረጥ አይገባንም። በሕይወት መንገድ ላይ በምንጓዝበት ጊዜ ልባችን መለኮታዊ ምሕረት ለማግኘት እንዲጮህ የሚያደርገው እንቅፋት ቢያጋጥመን ተስፋችን ተሟጥጦ አልቋል ማለት አይደለም። ከባድ ኃጢአት ብንሠራ እንኳን ንሥሐ ከገባን ይሖዋ የተሰበረውን ልባችንን አሽቀንጥሮ አይጥልም። የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ይቅርታ ያደርግልናል፣ ወደ ሞገሱም ይመልሰናል። (ኢሳይያስ 57:15፤ ዕብራውያን 4:16፤ 1 ዮሐንስ 2:1) ይሁን እንጂ ጸሎታችን ልክ እንደ ዳዊት መለኮታዊ ሞገስ እንደገና እንዲሰጠን መሆን ይኖርበታል እንጂ የሚያስፈልገን ተግሣጽና እርማት እንዲቀርልን መሆን አይገባውም። አምላክ ዳዊትን ይቅር ብሎታል፤ ሆኖም ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶታል። — 2 ሳሙኤል 12:11–14
ለንጹሕ አምልኮ ማሰብ
17. ኃጢአተኞች አምላክ ምህረት እንዲያደርግላቸው ከመማጸን በተጨማሪ ምን ማድረግ ይገባቸዋል?
17 አንድ ዓይነት ከባድ ኃጢአት ሠርተን እንደሆነ አእምሮአችን በጣም እንደሚረበሽና በነገሩ በጣም የተጸጸተው ልባችን የአምላክን ይቅርታ እንደሚማጸን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ለሌሎች ሰዎችም መጸለይ ይገባናል። ዳዊት ለአምላክ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለማቅረብ ቢጓጓም በጻፈው መዝሙሩ ላይ ራስ ወዳድ በመሆን ሌሎች ሰዎችን አልረሳም። በመዝሙሩ ውስጥ የሚከተለው ጸሎት ይገኛል:- “አቤቱ፣ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ።” — መዝሙር 51:18
18. ንሥሐ የገባው ዳዊት ስለ ጽዮን የጸለየው ለምን ነበር?
18 አዎ፣ ዳዊት ወደ መለኮታዊ ሞገስ የሚመለስበትን ጊዜ ናፍቆአል። ቢሆንም ዳዊት የይሖዋን ቤተ መቅደስ ሊሠራ ተስፋ ያደርግ ለነበረባት ለእስራኤል ዋና ከተማ ለሆነችው ለኢየሩሳሌም ወይም ለጽዮን አምላክ በበጎ ፈቃዱ መልካም እንዲያደርግላት በተጨማሪ ጸልዮአል። በንጉሡ በደል ምክንያት መላው ሕዝብ ችግር ላይ ሊወድቅ ይችል ስለነበረ የዳዊት ኃጢአት መላውን ብሔር አደጋ ላይ ጥሎት ነበር። (ከ2 ሳሙኤል ምዕራፍ 24 ጋር አወዳድር) በዚህ ምክንያት የዳዊት ኃጢአት ‘የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች’ ከሥር እንዲሸረሸሩ ያደረገ ያህል ስለነበረ እንደገና መገንባት አስፈልጓቸዋል።
19. ኃጢአት ከሠራን በኋላ ይቅርታ አግኝተን ከሆነ ስለምን ነገር መጸለይ ተገቢ ይሆናል?
19 ከባድ ኃጢአት ሠርተን ከነበረና አሁን ግን የአምላክን ይቅርታ ካገኘን ተግባራችን ያስከተለውን ጉዳት እንዲጠግንልን መጸለይ ይገባናል። በቅዱስ ስሙ ላይ ነቀፌታ አምጥተን፣ ጉባኤውን በመሸርሸር ጎድተን፣ በቤተሰባችንም ላይ ሐዘን አስከትለን ይሆናል። አፍቃሪው የሰማዩ አባታችን በስሙ ላይ የደረሰውን ማንኛውም ዓይነት ነቀፌታ ሊያስወግድ፣ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ጉባዔውን ሊያንጽ፣ እርሱን የሚወዱትንና የሚያገለግሉትን ወዳጆቻችን ልብ ሊያጽናና ይችላል። እርግጥ ኃጢአት ሠራንም አልሠራን የይሖዋ ስም መቀደስና የሕዝቦቹ ደህንነት ዘወትር ሊያሳስበን ይገባል። — ማቴዎስ 6:9
20. ይሖዋ በእስራኤላውያን መሥዋዕትና መባ የሚደሰተው በምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲቀርቡ ነበር?
20 ይሖዋ የጽዮንን ቅጥሮች እንደገና ቢሠራ ምን ሌላ ነገር ሊፈጸም ይችላል? ዳዊት እንደሚከተለው በማለት ጸልዮአል:- “መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድህ ጊዜ ያን ጊዜ በመሠዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሠዋሉ።” (መዝሙር 51:19) ዳዊት እርሱና ሕዝቡ የይሖዋን ሞገስ አግኝተው ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዲያመልኩት አጥብቆ ፈልጎ ነበር። ይህ ከሆነ በሚያቀርቡት የሚቃጠል መሥዋዕትና መባ አምላክ ይደሰታል። ይህም የሚሆነው የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ጻድቃን በሆኑ፣ ራሳቸውን በወሰኑ፣ ቅን በሆኑና ንሥሐ ገብተው የአምላክን ሞገስ ባገኙ ሰዎች የቀረቡ ስለሚሆኑ ነው። ለይሖዋ ምህረት ባላቸው አመስጋኝነት ተገፋፍተው በመሠዊያው ላይ ከሁሉ የተሻለውንና ውድ የሆነውን የኮርማ መሥዋዕት ያቀርባሉ። ዛሬም ካለን ነገር ሁሉ ምርጥ የሆነውን ለይሖዋ በማቅረብ አምላካችንን እናከብራለን። የምናቀርበው መባ “በወይፈን ፋንታ” የሚቀርበውን የከንፈራችንን ፍሬ ማለትም ለመሐሪው አምላካችን ለይሖዋ የምናቀርበውን ውዳሴ ይጨምራል። — ሆሴዕ 14:2፤ ዕብራውያን 13:15
ይሖዋ ጩኸታችንን ይሰማል
21, 22. መዝሙር 51 እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ይገኝበታል?
21 በመዝሙር 51 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ከልብ የቀረበው የዳዊት ጸሎት ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ እውነተኛ ንሥሐ መግባት እንደሚኖርብን ያመለክታል። በተጨማሪም ይህ መዝሙር እኛን የሚጠቅሙ ኃይለኛ ትምህርቶችን ይዞአል። ለምሳሌ ያህል ኃጢአት ብንሠራ እንኳን ንሥሐ ከገባን በአምላክ ምህረት ልንታመን እንችላለን። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ደረጃ ማሰብ የሚኖርብን በይሖዋ ስም ላይ ስለምናደርሰው ነቀፌታ መሆን ይኖርበታል። (ቁጥር 1–4) ሰማያዊ አባታችን የወረስነውን ኃጢአት ተመልክቶ ምህረት እንዲያደርግልን እንደ ዳዊት ልንማጸን እንችላለን። (ቁጥር 5) እውነተኞች መሆን ይገባናል። አምላክም ጥበብ እንዲሰጠን መለመን ይኖርብናል። (ቁጥር 6) ኃጢአት ሠርተን ከነበረ ይሖዋ እንዲያጠራን፣ ልባችንን እንዲያነጻና ጠንካራ መንፈስ እንዲሰጠን መማጸን ይገባናል። — ቁጥር 7–10
22 በተጨማሪም ከመዝሙር 51 በኃጢአት መንገድ መደንደን እንደማይገባን እንመለከታለን። አለዚያ ግን ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ወይም ተንቀሳቃሽ ኃይሉን ይነሳናል። የአምላክ መንፈስ በላያችን ላይ ከኖረ ግን የአምላክን መንገዶች ለሌሎች ሰዎች ለማስተማር እንችላለን፤ ይሳካልናልም። (ቁጥር 11–13) ብንበድል እንኳን ንስሐ ከገባን ይሖዋ የተሰበረውንና የተቀጠቀጠውን ልብ ስለማይንቅ እርሱን በማወደስ እንድንቀጥል ይፈቅድልናል። (ቁጥር 14–17) በተጨማሪም ይህ መዝሙር ጸሎታችን ስለራሳችን ብቻ መሆን እንደማይገባው ያመለክታል። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉ በረከትና መንፈሳዊ ደህንነት እንዲያገኙ መጸለይ ይኖርብናል። — ቁጥር 18, 19
23. መዝሙር 51 ድፍረት እንዲኖረንና ጥሩ ጎን እንዲታየን የሚያነሳሳን ለምንድን ነው?
23 ይህ ልብን የሚነካ የዳዊት መዝሙር ደፋሮችና ብሩህ የሆነው ጎን የሚታየን እንድንሆን ሊያነሳሳን ይገባል። ተደናቅፈን ኃጢአት ብንሠራ እንኳን እንዳለቀልን አድርገን በማሰብ ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልገን ያስገነዝበናል። ለምን? ምክንያቱም ንሥሐ ከገባንንና ከተጸጸትን የይሖዋ ምሕረት ከተስፋ መቁረጥ ሊያድነን ይችላል። ከልባችን ከተጸጸትንና ለሰማዩ አፍቃሪ አባታችን ሙሉ በሙሉ ያደርን ከሆንን ምህረት እንዲሰጠን የምናደርገውን ጩኸት ይሰማል። ይሖዋ የተሰበረውን ልብ እንደማይንቅ ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው!
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ክርስቲያኖች ንጹሕ ልብና የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
◻ አንድ ንሥሐ የገባ ሰው የይሖዋን ሕግ ለተላለፉ ሰዎች ምን ነገር ሊያስተምር ይችላል?
◻ ይሖዋ አንድን የተሰበረና የተቀጠቀጠ ልብ እንዴት ይመለከታል?
◻ ከመዝሙር 51 እንዴት ያሉ ትምህርቶችን እናገኛለን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥህ ትጸልያለህን? እርሱንስ ከማሳዘን ትጠበቃለህን?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋን እውነት በማወጅ ይገባናል ለማንለው ለይሖዋ ደግነት ያለህን አድናቆት አሳይ