የበለጠ ለማገልገል ትጓጓለህን?
ላውራ እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “በይሖዋ አዝኜበት ነበር። በአቅኚነቴ መቀጠል እችል ዘንድ ያለብንን የገንዘብ ችግር ለማስተካከል እንዲረዳን ሌት ተቀን እጸልይ ነበር፤ ነገር ግን ልመናዬ ሁሉ መና ቀረ። በመጨረሻ አቅኚነቴን ለማቆም ተገደድሁ። በአቅኚነታቸው መቀጠል በቻሉት ላይ ቅናት አድሮብኝ እንደነበር አልክድም።”
በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ የሆነውን የማይክልንም ሁኔታ ተመልከት። የበላይ ተመልካች ለመሆን ሲጣጣር ቆይቷል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1) የጓጓለትን ነገር ለበርካታ ዓመታት ሳያገኝ በመቅረቱ ከእንግዲህ ይህን መብት ከነጭራሹ አልፈልግም ብሎ እስከመመረር ደርሶ ነበር። “የጠበቅሁትን ነገር ሳላገኝ ቀርቼ እንደገና መበሳጨት አልፈለግሁም ነበር” ሲል ተናግሯል።
አንተስ ተመሳሳይ ነገር ገጥሞህ ያውቃልን? የምትወደውን ቲኦክራሲያዊ መብት እንድትተው የሚያስገድድ ነገር ገጥሞህ ያውቃል? ለምሳሌ ያህል አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሆነህ ማገልገልህን ለማቆም ተገደሃልን? ወይም ሌሎች ያገኟቸውን አንዳንድ የጉባኤ ኃላፊነቶች ለማግኘት ትጓጓለህን? ምናልባት ቤቴል ውስጥ ገብተህ ወይም ደግሞ ሚስዮናዊ ሆነህ ለማገልገል ከልብህ እየፈለግህ ሁኔታዎችህ አልፈቀዱልህ ይሆናል።
የምሳሌ መጽሐፍ “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 13:12) በተለይ ደግሞ አንተ የምትጓጓለትን መብት ሌሎች ሲያገኙ ስታይ ይህ አባባል እውነት ይሆናል። የአምላክ ቃል የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም በመቅረቱ ምክንያት ያዘኑትን ሰዎች ለመርዳት የሚሰጠው ጥልቅ ማስተዋል፣ ማጽናኛና ተስፋ ይኖራልን? አዎን፣ አለ። እንዲያውም 84ኛው መዝሙር ከይሖዋ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሳይፈጸሙ የቀሩ ተመሳሳይ ምኞቶች የነበሩት አንድ የይሖዋ አገልጋይ የተሰማውን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው።
የአንድ ሌዋዊ አድናቆት
መዝሙር 84ን የጻፉት በይሖዋ ቤተ መቅደስ ያገለግሉ የነበሩትና ይህን የአገልግሎት መብታቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ሌዋውያኑ የቆሬ ልጆች ናቸው። ከእነርሱ መካከል አንዱ “የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው! ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትወድዳለች ትናፍቅማለች። ልቤም ሥጋዬም በሕያው አምላክ ደስ ተሰኘ” ሲል ጽፏል።— መዝሙር 84:1, 2
ይህ ሌዋዊ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለማገልገል ካለው ከፍተኛ ጉጉት የተነሣ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚያመራው መንገድ ላይ የሚታየው የተለመደ ነገር እንኳ ማራኪ ሆኖ ይታየው ነበር። “ባካ በተባለው ሸለቆ በሚያልፉበት ጊዜ፣ የምንጭ ስፍራ ይሆናል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 84:6 የ1980 ትርጉም) አዎን፣ አካባቢው ደረቅ ቢሆንም ለእርሱ ግን ውኃ እንደጠገበ መሬት ሆኖ ታይቶት ነበር።
መዝሙራዊው በክህንነት የማገልገል መብት የሌለው ሌዋዊ ስለነበር በቤተ መቅደስ ውስጥ ማገልገል የሚችለው በየስድስት ወሩ ለአንድ ሳምንት ብቻ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 24:1-19፤ 2 ዜና መዋዕል 23:8፤ ሉቃስ 1:5, 8, 9) የቀረውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ከሌዋውያን ከተሞች በአንዱ ውስጥ በሚገኘው ቤቱ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች፣ ዋኖስም ጫጩቶቿን የምታኖርበት ቤት አገኘች፤ የሠራዊት አምላክ ንጉሤም አምላኬም ሆይ፣ እርሱ መሠዊያህ ነው።” (መዝሙር 84:3) ሌዋዊው በቤተ መቅደስ ቋሚ መኖሪያዋን እንደሠራችው ወፍ ቢሆን ምንኛ ደስ ባለው!
ሌዋዊው በቤተ መቅደስ ውስጥ የበለጠ ማገልገል ባለመቻሉ በቀላሉ ሊመረር ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ያንን ያክልም ማገልገል በመቻሉ ተደስቶ ነበር፤ በተጨማሪም ዋናው ጥረት ሊደረግለት የሚገባው ነገር በሙሉ ልብ ለይሖዋ ያደሩ የመሆኑ ጉዳይ እንደሆነ እንደተገነዘበ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ የታመነ ሌዋዊ ባገኘው የአገልግሎት መብት ረክቶ እንዲኖር የረዳው ነገር ምንድን ነው?
ባገኘነው ነገር መርካትን መማር
ሌዋዊው “ከአእላፋት ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኀጥአን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ” ብሏል። (መዝሙር 84:10) በይሖዋ ቤት ውስጥ አንድ ቀን እንኳ ማሳለፍ ትልቅ መብት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ሌዋዊው ደግሞ በቤተ መቅደስ ውስጥ ከአንድ ቀን በላይ የማገልገል መብት ነበረው። ባገኘው መብት መርካቱ በደስታ እንዲያዜም አነሳስቶታል።
እኛስ? ስላገኘናቸው በረከቶች እናስባለን ወይስ በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ያሉንን መብቶች መዘንጋት ይቀናናል? ይሖዋ ሕዝቦቹ ለእርሱ ያደሩ በመሆናቸው ምክንያት በርካታ መብቶችንና ሥራዎችን በአደራ ሰጥቷቸዋል። ይህም ከበድ ያሉትን የበላይ ተመልካችነት፣ የእረኝነት፣ የማስተማር ኃላፊነቶችና ሌሎች የተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎችን ይጨምራል። ይሁን እንጂ እነዚህ መብቶችና ሥራዎች ከይሖዋ አምልኮ ጋር የተያያዙ ሌሎች ውድ ነገሮችንም ያካትታሉ።
ለአብነት ያህል ክርስቲያናዊ አገልግሎትን እንውሰድ። ሐዋርያው ጳውሎስ የምሥራቹን የመስበክ ሥራችንን ‘በሸክላ ዕቃ ውስጥ ካለ ውድ ሀብት’ ጋር አመሳስሎታል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) እንዲህ ያለውን አገልግሎት በዋጋ ሊተመን እንደማይችል ውድ ሃብት አድርገህ ትመለከተዋለህን? የመንግሥቱን የስብከት ሥራ በግንባር ቀደምትነት የመራው ኢየሱስ ክርስቶስ ለአገልግሎቱ ተመሳሳይ አመለካከት በመያዝ ምሳሌ ሆኖናል። (ማቴዎስ 4:17) ጳውሎስ “ይህ አገልገሎት ስላለን አንታክትም” ብሏል።— 2 ቆሮንቶስ 4:1
ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም አቅልለን ልናያቸው የማይገቡ ቅዱስ ዝግጅቶች ናቸው። ስብሰባዎቻችን ላይ በጣም አስፈላጊ ትምህርቶችን ከማግኘታችንም በላይ በወንድማማች ኅብረት እንደሰታለን። በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ሐሳብ በመስጠትም ሆነ በሌሎች መንገዶች በፕሮግራሙ ተካፋይ በመሆን በሕዝብ ፊት እምነታችንንና ተስፋችንን መግለጽ እንችላለን። (ዕብራውያን 10:23-25) በእርግጥም ስብሰባዎቻችን ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው የሚገቡ ዝግጅቶች ናቸው!
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ማይክል ለእነዚህ በረከቶች ከፍተኛ ግምትና ልባዊ አድናቆት ነበረው። ይሁን እንጂ ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ባለመቻሉ ያደረበት ብስጭት ለጊዜውም ቢሆን ለእነዚህ ነገሮች ያለውን አድናቆት አዳፍኖበት ነበር። እንደገና በእነዚህ በረከቶች ላይ በማተኮር ሚዛኑን መጠበቅና ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ ችሏል።
አንዳንድ መብቶችን ሳናገኝ በመቅረታችን ቅር ከመሰኘት ይልቅ እንደ መዝሙራዊው ይሖዋ በምን መንገዶች እየባረከን እንዳለ መለስ ብለን መመርመራችን የተገባ ነው።a በምን መንገዶች እየባረከን እንዳለ ማስተዋል ካልቻልን ያሉንን መብቶች፣ እንዴት እየባረከን እንዳለና ለእርሱ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ እየተጠቀመብን እንዳለ ማስተዋል እንችል ዘንድ ዓይናችንን እንዲከፍትልን ወደ ይሖዋ በመጸለይ እንደገና መለስ ብለን ሁኔታዎቻችንን ለመመልከት መጣር ይኖርብናል።— ምሳሌ 10:22
በተጨማሪም የበላይ ተመልካችነትን የመሳሰሉት ልዩ መብቶች አንዳንድ ብቃቶችን ማሟላት የሚጠይቁ መሆናቸውን መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9) በመሆኑም ራሳችንን መመርመርና ልናሻሽለው የሚገባ ነገር ካለ ለማሻሻል ልባዊ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።— 1 ጢሞቴዎስ 4:12-15
ተስፋ አትቁረጥ
አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ሳናገኝ ብንቀር ይሖዋ ይህን መብት ያገኙትን ሰዎች ይበልጥ ይወዳቸዋል ብለን ማሰብ ወይም አንድ ነገር እንዳስቀረብን አድርገን መደምደም አይኖርብንም። እነዚህ ሰዎች በአድሎአዊነት የማይገባቸውን መብት እንዳገኙ እንጂ ቲኦክራሲያዊ ሹመት እንዳልተቀበሉ አድርገን በቅንዓት ማሰብ እንደማይገባን ግልጽ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ መብከንከን ወደ ቅንዓት፣ ቅሬታ አልፎ ተርፎም ጨርሶ ተስፋ ወደ መቁረጥ ሊያደርስ ይችላል።— 1 ቆሮንቶስ 3:3፤ ያዕቆብ 3:14-16
በመግቢያችን ላይ ያነሳናት ላውራ ተስፋ አልቆረጠችም። በመጨረሻ ያደረባትን የቁጣና የቅንዓት ስሜት መቆጣጠር ችላለች። ላውራ አቅኚ ለመሆን ባለመቻሏ ምክንያት ያደረባትን አፍራሽ ዝንባሌ ለማሸነፍ እንዲረዳት ብዙ ጊዜ ወደ አምላክ ጸልያለች። በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ ካሉ ብቃት ያላቸው ወንዶች እርዳታ ለማግኘት መጣሯ አምላክ እንደሚወዳት እንዲሰማት ረድቷታል። እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ይሖዋ የአእምሮ ሰላም ሰጠኝ። ዛሬ እኔና ባለቤቴ አቅኚ መሆን ባንችልም አቅኚ የነበርንባቸውን ጊዜያት በአድናቆት እያሰብን ባሳለፍነው ተሞክሮ ኃይላችንን እናድሳለን። ለአካለ መጠን የደረሰውንም ልጃችንን በአቅኚነቱ እንዲተጋ እንረዳዋለን።” ላውራ አሁን ባላት ነገር በመርካቷ በአቅኚነት አገልገሎታቸው ‘ደስ ከሚላቸው ጋር አብራ ትደሰታለች።’— ሮሜ 12:15
ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች አውጣ
አሁን ባሉን የአገልግሎት መብቶች እንረካለን ማለት ተጨማሪ ቲኦክራሲያዊ ግቦች ማውጣታችንን እናቆማለን ማለት አይደለም። ጳውሎስ ስለ ሰማያዊ ትንሣኤ ሲናገር ‘በፊቱ ያለውን ለመያዝ እንደሚዘረጋ’ ተናግሯል። በተጨማሪም “በደረስንበት በዚያ እንመላለስ” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 3:13-16) ቲኦክራሲያዊ ግቦች እድገት ለማድረግ እንድንጣጣር ይረዱናል። ይሁን እንጂ ፈተናው እነዚህን ግቦች እውን ማድረጉ ላይ ነው።
ተጨባጭ ግቦች ምክንያታዊ ከመሆናቸውም ሌላ ሊደረስባቸው የሚችሉ ናቸው። (ፊልጵስዩስ 4:5 NW) ይህ ማለት ግን ለበርካታ ዓመታት ጠንክሮ መሥራትን የሚጠይቅ ግብ ምክንያታዊነት ይጎድለዋል ማለት አይደለም። እንዲህ ያለው የረጅም ጊዜ ግብ በመካከሉ ተከታታይ ግቦችን ወይም እርከኖችን በማውጣት ቀስ በቀስ ሊደረስበት ይችላል። እነዚህ መንፈሳዊ ዕድገት እያደረግን እንዳለን የሚያሳዩ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እያንዳንዱን እርከን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ ከተስፋ መቁረጥ ይልቅ በጎዳናችን ሁሉ የእርካታ ስሜት እንድናገኝ ያደርገናል።
ግሩም ሚዛናዊነት
ይሁን እንጂ በግል ሁኔታዎቻችንና ባለን የአቅም ውስንነት ምክንያት አንዳንድ መብቶችን ሳናገኝ ልንቀር እንደምንችል መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነው። እነዚህን መብቶች ማግኘት አለብኝ የሚል ግብ ማውጣት ትርፉ ብስጭትና ተስፋ መቁረጥ ነው። እንደዚህ ያሉትን ግቦች ቢያንስ ለጊዜው ልናስተላልፋቸው ይገባል። አምላካዊ እርካታ እንድናገኝ ከጸለይንና የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን በሕይወታችን ውስጥ አንደኛ ቦታ ከሰጠነው ይህን ማድረግ አስቸጋሪ አይሆንብንም። አንዳንድ መብቶችን ለማግኘት የምንጣጣረው ይሖዋን ለማስከበር እንጂ ባደረግነው ነገር ለመወደስ መሆን የለበትም። (መዝሙር 16:5, 6፤ ማቴዎስ 6:33) መጽሐፍ ቅዱስ “ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፣ አሳብህም ትጸናለች” ሲል መናገሩ ተገቢ ነው።— ምሳሌ 16:3
መዝሙር 84ን ስንመረምር መዝሙራዊው የአገልግሎት መብቶችን በሚመለከት ተመሳሳይ ዝንባሌ እንዳሳየና ይሖዋም አብዝቶ እንደባረከው ማስተዋል እንችላለን። ከዚህም በላይ ይህ መዝሙር እስካሁን ድረስ ያሉትን የይሖዋ ሕዝቦች ሲጠቅም ቆይቷል።
በጸሎት በይሖዋ ላይ የምትደገፍ ከሆነ ተጨማሪ መብቶች ለማግኘት ያለህን ጉጉት አሁን ባሉህ መብቶች ከምታገኘው እርካታ ጋር በሚዛናዊነት ለማራመድ ትችላለህ። ተጨማሪ ነገር ለማከናወን ያለህ ምኞት ዛሬ ላገኘሃቸው ነገሮች ያለህን አድናቆትና ይሖዋን ለዘላለም የማገልገል ደስታህን እንዲያሳጣህ አትፍቀድ። “የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW] ነው” የሚሉት የሌዋዊው ቃላት እንደሚያሳዩት በይሖዋ መታመን ደስታ ያስገኝልሃል።— መዝሙር 84:12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እባክህ በመጠበቂያ ግንብ 12-109 ላይ የወጣውን “ቅዱስ ነገሮችን ታደንቃለህን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ልናወጣቸው የምንችላቸው ግቦች
መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ።— ኢያሱ 1:8፤ ማቴዎስ 4:4
ከቅዱሳን ጽሑፎች በሚገኘው ሥልጠና የማስተዋል ችሎታችንን ማሳደግ።— ዕብራውያን 5:14
ከአምላክ ጋር ይበልጥ የጠበቀ ዝምድና መመሥረት።— መዝሙር 73:28
እያንዳንዱን የመንፈስ ፍሬ ማፍራት።— ገላትያ 5:22, 23
የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል።— ፊልጵስዩስ 4:6, 7
በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ መሆን።— 1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16
እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትም ማንበብና በዚያ ላይ ማሰላሰል።— መዝሙር 49:3
[በገጽ 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የግል ግቦችን ስታወጣ የአምላክን ፈቃድ አስቀድም