ይሖዋ መሸሸጊያችን ነው
“እግዚአብሔርን መሸሸጊያ . . . አድርገኸዋልና ክፉ ነገር አያገኝህም።”—መዝሙር 91:9, 10 አ.መ.ት
1. ይሖዋ መሸሸጊያችን ነው ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
ይሖዋ ለሕዝቡ እውነተኛ መሸሸጊያ ነው። ለእርሱ ሙሉ በሙሉ ያደርን ከሆንን “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቈርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም።” ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ‘ከወትሮው የበለጠ ኃይል’ [NW ] ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7-9) አዎን፣ ሰማያዊው አባታችን አምላካዊ አኗኗር እንድንከተል ይረዳናል። በዚህም የተነሳ “እግዚአብሔርን መሸሸጊያ፣ ልዑልንም መጠጊያህ አድርገኸዋልና። ክፉ ነገር አያገኝህም” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት ልብ ልንላቸው እንችላለን።—መዝሙር 91:9, 10 አ.መ.ት
2. ስለ መዝሙር 91 ምን ለማለት ይቻላል? ምን ማረጋገጫስ ይሰጣል?
2 በመዝሙር 91 ላይ የሚገኙትን ቃላት የጻፈው ሙሴ ሳይሆን አይቀርም። በ90ኛው ምዕራፍ መግቢያ ላይ የሰፈረው ሐሳብ መዝሙሩን ያቀናበረው ሙሴ እንደሆነ ይገልጻል። ከዚህ መዝሙር ቀጥሎ በሰፈረው በመዝሙር 91 አናት ላይ የሌላ ጸሐፊ ስም አይገኝም። መዝሙር 91 ምናልባት በቅብብሎሽ መልክ የተዘመረ ሊሆን ይችላል። ይህም ማለት አንድ ሰው የመጀመሪያውን (91:1, 2) ሲዘምር ሌሎች በሕብረት ይቀበሉታል (91:3-8)። ምናልባት ቀጥሎ ያለውን አንድ ሰው ሲዘምር (91:9ሀ) ሌሎች በቡድን ሆነው ይመልሳሉ (91:9ለ-13)። ከዚያም አንድ ዘማሪ የመጨረሻዎቹን ቃላት ይዘምራል (91:14-16)። መዝሙሩ በምንም መልኩ ይዘመር 91ኛው መዝሙር ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ጓደኞቻቸው በቡድን መልክ መንፈሳዊ ጥበቃ እንደሚያገኙ ማረጋገጫ ይሰጣል።a እስቲ ይህን መዝሙር ከእነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች አንፃር እንመርምረው።
‘በአምላክ ምሥጢራዊ ቦታ’ መኖር
3. (ሀ) “የልዑል ምሥጢራዊ ቦታ” ምንድን ነው? (ለ) ‘ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ሥር በማደር’ ምን እናገኛለን?
3 መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “በልዑል መጠጊያ [“ምሥጢራዊ ቦታ፣” NW ] የሚኖር፣ ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ሥር ያድራል። እግዚአብሔርን፣ ‘መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ’ እለዋለሁ።” (መዝሙር 91:1, 2 አ.መ.ት) “የልዑል ምሥጢራዊ ቦታ” እኛና በተለይ ደግሞ የዲያብሎስ ጥቃት ልዩ ዒላማ የሆኑት ቅቡዓን ጥበቃ የምናገኝበት ምሳሌያዊ ቦታ ነው። (ራእይ 12:15-17) መንፈሳዊ እንግዶች ሆነን በአምላክ ድንኳን በማደር ጥበቃ ባናገኝ ኖሮ ሰይጣን ሁላችንንም ባጠፋን ነበር። ‘ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ሥር በማደራችን’ የአምላክን ጥበቃ አግኝተናል። (መዝሙር 15:1, 2፤ 121:5) ከሉዓላዊው ጌታ ከይሖዋ የተሻለ አስተማማኝ መሸሸጊያ ወይም የማይደፈር ምሽግ የለም።—ምሳሌ 18:10
4. ‘አዳኙ’ ሰይጣን የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ምንድን ናቸው? እንዴትስ እናመልጣለን?
4 መዝሙራዊው ጨምሮ እንዲህ ብሏል:- “እርሱ [ይሖዋ] ከአዳኝ ወጥመድ፣ ከአሰቃቂ ቸነፈር ያድንሃልና።” (መዝሙር 91:3 አ.መ.ት) በጥንቷ እስራኤል አንድ ወፍ አዳኝ ብዙውን ጊዜ ወፎችን የሚይዘው ወጥመድ በመጠቀም ነበር። ‘አዳኙ’ ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ወጥመዶች መካከል ክፉ ድርጅቶቹና ‘መሸንገያዎቹ’ ይገኙበታል። (ኤፌሶን 6:11) እኛን ወደ ክፋት የሚመሩና ለመንፈሳዊ ውድቀት የሚዳርጉ ወጥመዶች በመንገዳችን ላይ በስውር ተቀምጠዋል። (መዝሙር 142:3) ሆኖም የኃጢአተኝነትን ጎዳና አንከተልም በማለታችን ‘ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አምልጣለች።’ (መዝሙር 124:7, 8) ይሖዋ ከክፉው ‘አዳኝ’ ስለሚያድነን ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ማቴዎስ 6:13
5, 6. ‘መከራ’ የሚያስከትለው “ቸነፈር” ምንድን ነው? ይሁን እንጂ የይሖዋ ሕዝቦች በዚህ መከራ የማይሸነፉት ለምንድን ነው?
5 መዝሙራዊው ‘አሰቃቂ ቸነፈር’ ጠቅሷል። እንደ ተላላፊ በሽታ በሰው ልጅ ቤተሰብና የይሖዋን ሉዓላዊነት በሚደግፉ ላይ ‘ሥቃይ’ የሚያስከትል አንድ ነገር አለ። ይህን በማስመልከት አርኖልድ ቶይንቢ የተባሉ አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካከተመ በኋላ ብሔራዊ ስሜት ሉዓላዊነታቸውን ያስከበሩ ነፃ መንግሥታት ቁጥር በእጥፍ እንዲጨምር አድርጓል። . . . በአሁኑ ጊዜ ያለው የሰው ዘር ዝንባሌ መከፋፈል ነው።”
6 ባለፉት ዘመናት የተነሱ አንዳንድ መሪዎች የሚከፋፍሉ ዓለም አቀፍ ግጭቶችን ሲያራግቡ ቆይተዋል። በተጨማሪም አምልኮታዊ ክብር በቀጥታ ለእነርሱ ወይም ለተለያዩ ምስሎች ወይም ዓርማዎች እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ አገልጋዮቹ ለእንዲህ ዓይነቱ “ቸነፈር” እንዲንበረከኩ ፈጽሞ አይፈቅድም። (ዳንኤል 3:1, 2, 20-27፤ 6:7-10, 16-22) እንደ አንድ ፍቅርን በተላበሰ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ስንታይ ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እናቀርባለን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ገለልተኝነታችንን እንጠብቃለን እንዲሁም “በአሕዛብ ሁሉ እርሱን [አምላክን] የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ” ያለ አንዳች አድልዎ አምነን እንቀበላለን። (ሥራ 10:34, 35፤ ዘጸአት 20:4-6፤ ዮሐንስ 13:34, 35፤ 17:16፤ 1 ጴጥሮስ 5:8, 9) ምንም እንኳ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን በስደት ምክንያት ‘መከራ’ ቢደርስብንም “በልዑል መጠጊያ [“ምሥጢራዊ ቦታ፣” NW ]” ውስጥ ደስተኞች ሆነንና መንፈሳዊ ደህንነት አግኝተን እንኖራለን።
7. ይሖዋ ‘በላባዎቹ’ የሚጠብቀን እንዴት ነው?
7 ይሖዋ መሸሸጊያችን ስለሆነ ከሚከተሉት ቃላት ማጽናኛ እናገኛለን:- “በላባዎቹ ይጋርድሃል፤ በክንፎቹ ሥር መሸሸጊያ ታገኛለህ፤ ታማኝነቱ [“እውነተኝነቱ፣” NW ] ጋሻና መከታ ይሆንሃል።” (መዝሙር 91:4 አ.መ.ት) አምላክ ጫጩቶቿን ለመጠበቅ በላያቸው ላይ እንደምታንዣብብ ወፍ ይጠብቀናል። (ኢሳይያስ 31:5) ‘በላባዎቹ ይጋርደናል።’ ብዙውን ጊዜ ‘ላባ’ የሚለው ቃል የወፎችን ክንፍ ያመለክታል። አንዲት ወፍ ጫጩቶቿን ከአዳኝ አውሬ ለመጠበቅ በክንፎቿ ትከልላቸዋለች። እኛም እውነተኛውን የክርስትና ድርጅት እንደ መሸሸጊያ አድርገን በመጠጋት እንደ አንዲት የወፍ ጫጩት ምሳሌያዊ በሆነው በይሖዋ ላባ ሥር ተከልለን እንኖራለን።—ሩት 2:12፤ መዝሙር 5:1, 11
8. የይሖዋ ‘እውነተኝነት’ እንደ ትልቅ ጋሻና መከታ የሆነው እንዴት ነው?
8 ‘በእውነተኝነት’ ወይም ‘በታማኝነት’ እንታመናለን። ይህ በጥንት ጊዜ ከነበረው ብዙውን ጊዜም አራት ማእዘን ቅርጽ ካለውና የአንድን ሰው መላ አካል መሸፈን ከሚችለው ትልቅ ጋሻ ጋር ይመሳሰላል። (መዝሙር 5:12) እንዲህ ባለው መከላከያ መታመናችን ከፍርሃት ነፃ ያደርገናል። (ዘፍጥረት 15:1፤ መዝሙር 84:11 አ.መ.ት) እንደ እምነታችን ሁሉ የአምላክ እውነተኝነትም የሚንበለበሉትን የሰይጣንን ፍላጻዎች የሚመክትና ከጠላት መቅሰፍት የሚጠብቅ ትልቅ የመከላከያ ጋሻ ነው። (ኤፌሶን 6:16) ከዚህም በተጨማሪ ተማምነን የምንሸሸግበት ጠንካራ ምሽግ ነው።
‘አንፈራም’
9. ሌሊት የሚያስፈራ ወቅት ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? የማንፈራውስ ለምንድን ነው?
9 መዝሙራዊው ከአምላክ የሚገኘውን ጥበቃ በማስመልከት እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የሌሊትን አስደንጋጭነት፣ በቀን የሚወረወረውንም ፍላጻ አትፈራም፤ በጨለማ የሚያደባ ቸነፈር፣ በቀትር ረፍራፊውም አያሠጋህም።” (መዝሙር 91:5, 6 አ.መ.ት) በርካታ መጥፎ ድርጊቶች የሚፈጸሙት ጨለማን ተገን በማድረግ ስለሆነ ሌሊት የሚያስፈራ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ዛሬ ምድርን በሸፈናት መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ጠላቶቻችን መንፈሳዊነታችንን ለማጥፋትና የስብከት ሥራችንን ለማስቆም ብዙውን ጊዜ በድብቅ ይሠራሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ስለሚጠብቀን ‘የሌሊቱን አስደንጋጭነት አንፈራም።’—መዝሙር 64:1, 2፤ 121:4፤ ኢሳይያስ 60:2
10. (ሀ) ‘በቀን የሚወረወረው ፍላጻ’ ምንን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም? እንዴትስ መመከት እንችላለን? (ለ) ‘በጨለማ የሚያደባው ቸነፈር’ ምንድን ነው? የማንፈራውስ ለምንድን ነው?
10 ‘በቀን የሚወረወር ፍላጻ’ ስድብን የሚያመለክት ይመስላል። (መዝሙር 64:3-5፤ 94:20) እውነተኛውን መልእክት መናገራችንን በመቀጠላችን በቅዱስ አገልግሎታችን ላይ የሚሰነዘረው ግልጽ ተቃውሞ ከንቱ መሆኑ ይረጋገጣል። ከዚህም በላይ ‘በጨለማ የሚያደባ ቸነፈርን’ አንፈራም። ይህ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር በሚገኘውና ሥነ ምግባራዊና ሃይማኖታዊ ደዌ በመታው ጨለማ የዋጠው ዓለም ውስጥ የተንሰራፋውን ምሳሌያዊ ቸነፈር የሚያመለክት ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ይህም አእምሮንና ልብን በድን በማድረግ ሰዎች ለይሖዋ፣ ለዓላማዎቹና ለፍቅራዊ ዝግጅቶቹ ምንም ዓይነት እውቀት እንዳይኖራቸው ያደርጋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:4) መንፈሳዊ ብርሃን ቦግ ብሎ የበራልን በመሆናችን በዚህ ጨለማ ውስጥ ፈጽሞ አንፈራም።—መዝሙር 43:3
11. ‘በቀትር የሚረፈረፉት’ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል?
11 ‘የቀትር ረፍራፊውም’ ቢሆን አያስፈራንም። ‘ቀትር’ የሚለው በዓለም የሚገኘውን የእውቀት ብርሃን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በፍቅረ ነዋይ ወጥመዱ ውስጥ የወደቁ ሁሉ መንፈሳዊ ጥፋት ይገጥማቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) የመንግሥቱን መልእክት በድፍረት ስናውጅ ጠባቂያችን ይሖዋ እንደሆነ ስለምናውቅ ጠላቶቻችንን አንፈራም።—መዝሙር 64:1፤ ምሳሌ 3:25, 26
12. በሺዎች የሚቆጠሩ ‘የሚወድቁት’ በእነማን አጠገብ ነው? በምንስ መንገድ?
12 መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በአጠገብህ ሺህ፣ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃል፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። በዐይንህ ብቻ ትመለከታለህ፤ የክፉዎችንም መቀጣት ታያለህ።” (መዝሙር 91:7, 8 አ.መ.ት) ይሖዋን መሸሸጊያቸው ለማድረግ ፈቃደኞች ሳይሆኑ በመቅረታቸው ብዙዎች በመንፈሳዊ ሞተው ‘አጠገባችን’ ‘ወድቀዋል።’ በዚህም የተነሳ በዛሬዎቹ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ‘ቀኝ’ “አሥር ሺህ” ወድቀዋል። (ገላትያ 6:16) ይሁን እንጂ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆን ራሳችንን ለአምላክ የወሰን ጓደኞቻቸው በአምላክ “ምሥጢራዊ ቦታ” ያለ ስጋት እንኖራለን። በንግዱ፣ በሃይማኖትና በሌሎች መንገዶች መከራ እያጨዱ ያሉት ‘ክፉዎች ሲቀጡ እንመለከታለን።’—ገላትያ 6:7
‘ክፉ ነገር አያገኘንም’
13. የትኞቹ ክፉ ነገሮች አያገኙንም? ለምንስ?
13 ይህ ዓለም የሚታመንበት ነገር ሁሉ ከንቱ እየሆነ ቢመጣም እንኳ አምላክን በአንደኛ ደረጃ እናስቀምጣለን እንዲሁም ከመዝሙራዊው ቃላት ድፍረት እናገኛለን:- “እግዚአብሔርን መሸሸጊያ፣ ልዑልንም መጠጊያህ አድርገኸዋልና። ክፉ ነገር አያገኝህም፤ መቅሠፍትም ወደ ድንኳንህ አይገባም።” (መዝሙር 91:9, 10 አ.መ.ት) አዎን፣ ይሖዋ መሸሸጊያችን ነው። ይሁን እንጂ ልዑሉን አምላክ ደህንነት የምናገኝበት ‘መጠጊያችንም’ እናደርገዋለን። ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ እንደ መሆኑ መጠን እናወድሰዋለን፣ ደህንነት የምናገኝበት ምንጭ ስለሆነ ‘መጠጊያችን’ እናደርገዋለን እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች እናውጃለን። (ማቴዎስ 24:14) ስለዚህ ቀደም ሲል በዚህ መዝሙር ውስጥ የተገለጹትን ጨምሮ ምንም ዓይነት ‘ክፉ ነገር አያገኘንም።’ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ፣ አውሎ ነፋስ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ረሃብና ጦርነት ያሉ ክስተቶች በእኛም ላይ አደጋ ሊያስከትሉ ቢችሉም እንኳ እምነታችንንም ሆነ መንፈሳዊ ደህንነታችንን አያጠፉብንም።
14. የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ገዳይ በሆኑ መቅሰፍቶች ያልተበከልነው ለምንድን ነው?
14 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከዚህ የነገሮች ሥርዓት ርቀው በድንኳን እንደሚኖሩ መጻተኞች ናቸው። (1 ጴጥሮስ 2:11) አንድም ‘መቅሰፍት ወደ ድንኳናቸው’ አይቀርብም። ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ የዓለም ክፍል አይደለንም። እንዲሁም እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ ፍቅረ ነዋይ፣ የሐሰት ሃይማኖት፣ ‘አውሬውንና’ ‘ምስሉን’ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ማምለክን በመሰሉ በመንፈሳዊ ገዳይ በሆኑ መቅሰፍቶች አልተበከልንም።—ራእይ 9:20, 21፤ 13:1-18፤ ዮሐንስ 17:16
15. መላእክታዊ እርዳታ የምናገኘው በምን በምን አቅጣጫዎች ነው?
15 ያገኘነውን ጥበቃ በማስመልከት መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ጨምሮ ተናግሯል:- “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ [ይሖዋ ] መላእክቱን ስለ አንተ ያዛቸዋልና። እግርህ ከድንጋይ ጋር እንዳይጋጭ፣ በእጆቻቸው ወደ ላይ ያነሡሃል።” (መዝሙር 91:11, 12 አ.መ.ት) መላእክት እኛን ለመጠበቅ የሚያስችል ኃይል ተሰጥቷቸዋል። (2 ነገሥት 6:17፤ መዝሙር 34:7-9፤ 104:4፤ ማቴዎስ 26:53፤ ሉቃስ 1:19) ‘በመንገዳችን ሁሉ’ ይጠብቁናል። (ማቴዎስ 18:10) የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነን በምናከናውነው ሥራ የሚያግዘንንና በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳንሰናከል የሚደግፈንን መላእክታዊ አመራርና ጥበቃ እናገኛለን። (ራእይ 14:6, 7) ‘ድንጋዮች’ ማለትም በሥራችን ላይ እንደሚጣሉ እገዳዎች ያሉ ሁኔታዎች እንኳ ሊያሰናክሉንና መለኮታዊ ሞገስ ሊያሳጡን አይችሉም።
16. “አንበሳና” ‘እፉኝት’ የሚሰነዝሩት ጥቃት የሚለያየው እንዴት ነው? ምላሽ የምንሰጠውስ እንዴት ነው?
16 መዝሙራዊው እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በአንበሳና በእፉኝት ላይ ትጫማለህ፤ ደቦሉን አንበሳና ዘንዶውን ትረግጣለህ።” (መዝሙር 91:13 አ.መ.ት) አንበሳ በግልጽ ማለትም ፊት ለፊት እንደሚያጠቃ ሁሉ ከጠላቶቻችን መካከል አንዳንዶችም የስብከት ሥራችንን የሚያስቆሙ ሕጎችን በማውጣት ተቃውሟቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ተደብቆ በድንገት ጥቃት እንደሚሰነዝር እፉኝትም ድንገተኛ ጥቃት ይደርስብናል። ቀሳውስት ከመድረክ በስተጀርባ ሆነው በሕግ አውጪዎች፣ በዳኞችና በሌሎች መንገዶች በመጠቀም አንዳንድ ጥቃት ይሰነዝሩብናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በሚሰጠን ድጋፍ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በችሎት ፊት በመሟገት እፎይታ ለማግኘት አልፎ ተርፎም ‘ለምሥራቹ መከላከያ ለማቅረብና ምሥራቹን በሕግ ለማስከበር እንጥራለን።’—ፊልጵስዩስ 1:7፤ መዝሙር 94:14, 20-22
17. “ደቦሉን አንበሳ” የምንረግጠው በምን መንገድ ነው?
17 መዝሙራዊው “ደቦሉን አንበሳና ዘንዶውን” ስለመርገጥ ተናግሯል። ደቦል አንበሳ በጣም አስፈሪ ሲሆን ዘንዶ ደግሞ መጠኑ ትልቅ የሆነ በደረቱ የሚሳብ እንስሳ ነው። (ኢሳይያስ 31:4) ደቦል አንበሳ ቀጥተኛ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ የቱንም ያህል አስፈሪ ቢሆን አንበሳ መሰል ከሆኑ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ይልቅ አምላክን በመታዘዝ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ እንረግጠዋለን። (ሥራ 5:29) ስለዚህ አስፈሪ “አንበሳ” መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትልብን አይችልም።
18. ‘ዘንዶ’ የሚለው ቃል ማንን ያስታውሰናል? ጥቃት በሚሰነዝርብን ጊዜስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
18 ‘ዘንዶ’ የሚለው ቃል ‘ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለውን ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመውን እባብን’ ያስታውሰናል። (ራእይ 12:7-9፤ ዘፍጥረት 3:15) ዘንዶ አድኖ የያዘውን እንስሳ ሰባብሮ መዋጥ የሚችል አስፈሪ ፍጥረት ነው። (ኤርምያስ 51:34) ሰይጣን ላያችን ላይ ተጠምጥሞ በዚህ ዓለም ተጽእኖዎች በማድቀቅ ሊውጠን ሙከራ በሚያደርግበት ጊዜ ራሳችንን በማላቀቅ ይህን ‘ዘንዶ’ መሬት ጥለን እንርገጠው። (1 ጴጥሮስ 5:8) ቅቡዓን ቀሪዎች በሮሜ 16:20 ፍጻሜ የሚካፈሉ በመሆናቸው እንዲህ ማድረግ ይገባቸዋል።
ይሖዋ—የመዳኛችን ምንጭ
19. ይሖዋን መሸሸጊያችን የምናደርገው ለምንድን ነው?
19 እውነተኛ አምላኪዎችን በሚመለከት መዝሙራዊው አምላክን በመወከል እንዲህ አለ:- “‘ወዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን አውቆአልና እከልለዋለሁ።’” (መዝሙር 91:14 አ.መ.ት) “እከልለዋለሁ” ማለት ቃል በቃል ማንም ሊደርስበት በማይችል “ከፍተኛ ቦታ ላይ አስቀምጠዋለሁ” ማለት ነው። አምላኪዎቹ እንደመሆናችን መጠን ‘ስለምንወድደው’ ይሖዋን መሸሸጊያችን እናደርገዋለን። (ማርቆስ 12:29, 30፤ 1 ዮሐንስ 4:19) በምላሹም ደግሞ አምላክ ከጠላቶቻችን ‘ይታደገናል።’ ከምድር ላይ ማንም ሊያጠፋን አይችልም። ከዚያ ይልቅ መለኮታዊውን ስም ስለምናውቅና በእምነት ስለምንጠራው እንድናለን። (ሮሜ 10:11-13) እንዲሁም ‘በይሖዋ ስም ለዘላለም ለመጓዝ’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።—ሚክያስ 4:5 NW፤ ኢሳይያስ 43:10-12
20. በመዝሙር 91 መደምደሚያ ላይ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ምን ቃል ገብቶላቸዋል?
20 መዝሙር 91 ይሖዋ ስለ ታማኝ አገልጋዮቹ በሚናገረው ቃል ይደመድማል:- “‘ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ። ረጅም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።’” (መዝሙር 91:15, 16 አ.መ.ት) እንደ ፈቃዱ አምላክን በጸሎት ስንጠራው መልስ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 5:13-15) ሰይጣን በሚያነሳሳው ጥላቻ ምክንያት ብዙ መከራ አሳልፈናል። ይሁን እንጂ “በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ” የሚሉት ቃላት ወደፊት ለሚያጋጥሙን መከራዎች የሚያዘጋጁንና ይህ ክፉ ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ አምላክ እንደሚደግፈን ማረጋገጫ የሚሰጡን ናቸው።
21. ቅቡዓኑ ክብር የተጎናጸፉት በምን መንገድ ነው?
21 ሰይጣን ከባድ ተቃውሞ የሚሰነዝርባቸው ቢሆንም እንኳ የቅቡዓኑን ቁጥር የሚያሟሉት በመካከላችን የሚገኙት ቅቡዓን በምድር ላይ ‘ረዥም ዕድሜ’ ከኖሩ በኋላ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በሰማይ ይከብራሉ። ሆኖም የአምላክ ድንቅ የማዳን ሥራ ለቅቡዓኑ አሁንም እንኳ መንፈሳዊ ክብር አስገኝቶላቸዋል። በዚህ የመጨረሻ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ሥራውን በግንባር ቀደምትነት የመምራት ከፍተኛ ክብር አግኝተዋል! (ኢሳይያስ 43:10-12) ይሖዋ በታላቁ የአርማጌዶን የጦርነት ቀን ሉዓላዊነቱን በሚያረጋግጥበትና ቅዱስ ስሙን በሚያስቀድስበት ጊዜ ሕዝቡን በማዳን ታላቅ ሥራ ያከናውናል።—መዝሙር 83:18፤ ሕዝቅኤል 38:23፤ ራእይ 16:14, 16
22. ‘ይሖዋ የሚያመጣውን ማዳን የሚያዩት’ እነማን ናቸው?
22 ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆን ራሳችንን የወሰንን ጓደኞቻቸው መዳንን ለማግኘት የምንጠባበቀው ከአምላክ ነው። ‘በታላቁና በሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን’ አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ ሁሉ ይድናሉ። (ኢዩኤል 2:30-32) በሕይወት ተርፈው ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ከሚገቡት ‘እጅግ ብዙ ሰዎች’ መካከል የምንገኝና በመጨረሻው ፈተና ወቅት ታማኝ ሆነን ከተገኘን የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ በማድረግ ‘ረጅም ዕድሜ ያጠግበናል።’ ብዙ ሰዎችንም ከሞት ያስነሳል። (ራእይ 7:9፤ 20:7-15) በእርግጥም ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ‘መዳንን እንድናይ’ በማድረግ ይደሰታል። (መዝሙር 3:8) እንዲህ ያለውን ታላቅ የወደፊት ተስፋ ከአእምሯችን ሳናጠፋ ለእርሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ ዕድሜያችንን መቁጠር እንችል ዘንድ እንዲያስተምረን አምላክን መጠየቃችንን አናቋርጥ። ይሖዋን መሸሸጊያችን አድርገን እንደምንመለከተው በቃላችንም ሆነ በድርጊታችን እናሳይ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች መዝሙር 91ን ከመሲሐዊ ትንቢት አንጻር ጠቅሰው አልተናገሩም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ለኢየሱስ ክርስቶስ መሸሸጊያና ጠንካራ ምሽግ እንደሆነለት ሁሉ ለኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮችና ራሳቸውን ለአምላክ ለወሰኑት ጓደኞቻቸው በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ በቡድን ደረጃ መሸሸጊያና ጠንካራ ምሽግ ይሆንላቸዋል።—ዳንኤል 12:4
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
• ‘የልዑል ምሥጢራዊ ቦታ’ ምንድን ነው?
• የማንፈራው ለምንድን ነው?
• ‘ክፉ ነገር የማያገኘን’ እንዴት ነው?
• ይሖዋ የመዳኛችን ምንጭ ነው ብለን መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ እውነተኝነት ትልቅ ጋሻ የሚሆነን እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ አገልጋዮቹ ያልተጠበቀ ጥቃትና ቀጥተኛ ተቃውሞ ቢሰነዘርባቸውም እንኳ አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ ይረዳቸዋል
[ምንጭ]
ኮብራ:- A. N. Jagannatha Rao, Trustee, Madras Snake Park Trust