ከአምላክ ጋር ትሄዳለህ?
“ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?”—ሚክያስ 6:8 የ1954 ትርጉም
1, 2. ይሖዋ ለእኛ ያለው ስሜት፣ ልጁን መራመድ ከሚያስተምር ወላጅ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው?
ገና በእግሩ መሄድ ያልጀመረ ሕፃን የተዘረጉትን የአባቱን እጆች ለመያዝ እየተውተረተረ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቂት እርምጃዎችን ይራመዳል። ይህ ለሌላ ሰው ቀላል ነገር ይመስል ይሆናል፤ እናትና አባቱ ግን ትልቅ ተስፋ የሚጥሉበት እድገት ነው። ወላጆቹ በመጪዎቹ ወራትና ዓመታት ከልጃቸው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ይታያቸዋል። በተለያዩ መንገዶች ለልጃቸው የሚያስፈልገውን መመሪያና ድጋፍ ለመስጠት ይናፍቃሉ።
2 ይሖዋ አምላክ ምድራዊ ልጆቹን በተመለከተ ተመሳሳይ ስሜት አለው። በአንድ ወቅት ሕዝቡን እስራኤልን ወይም ኤፍሬምን በተመለከተ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ኤፍሬምን እጁን ይዤ፣ እንዲራመድ ያስተማርሁት እኔ ነበርሁ፤ . . . በሰው የርኅራኄ ገመድ፣ በፍቅርም ሰንሰለት ሳብኋቸው።” (ሆሴዕ 11:3, 4) እዚህ ላይ ይሖዋ፣ ልጁን በትዕግሥት መራመድ ከሚያስተምርና ከወደቀም አንስቶ ከሚያቅፍ አፍቃሪ ወላጅ ጋር ራሱን አመሳስሏል። ወደር የሌለው አባታችን ይሖዋ እንዴት እንደምንራመድ ለማስተማር ዝግጁ ነው። እንዲሁም ለመሻሻል የምናደርገውን ጥረት ለመደገፍ ከጎናችን መሆን ያስደስተዋል። የጭብጡ ጥቅስ እንደሚያሳየው ከአምላክ ጋር መሄድ እንችላለን! (ሚክያስ 6:8 የ1954 ትርጉም) ይሁንና ከአምላክ ጋር መሄድ ሲባል ምን ማለት ነው? እንዲህ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? እንዴት ከአምላክ ጋር መሄድ ይቻላል? ከአምላክ ጋር መሄድ ምን በረከት ያስገኛል? እነዚህን አራት ጥያቄዎች አንድ በአንድ እንመልከት።
ከአምላክ ጋር መሄድ ሲባል ምን ማለት ነው?
3, 4. (ሀ) ከአምላክ ጋር መሄድ የሚለው ምሳሌያዊ መግለጫ አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ከአምላክ ጋር መሄድ ሲባል ምን ማለት ነው?
3 ሥጋ ለባሹ የሰው ልጅ መንፈሳዊ አካል ካለው ከይሖዋ ጋር ቃል በቃል አብሮ መሄድ እንደማይችል እሙን ነው። (ዘፀአት 33:20፤ ዮሐንስ 4:24) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከአምላክ ጋር ስለ መሄዳቸው ሲናገር ምሳሌያዊ አገላለጽ መጠቀሙ ነው። ይህ አነጋገር በየትኛውም ዘመን ለሚኖር፣ የየትኛውም ብሔር አባል ለሆነ ወይም በየትኛውም ባሕል ውስጥ ላደገ ሰው ግልጽ የሆነ መልእክት ያስተላልፋል። ጥንትም ሆነ ዛሬ ከአንድ ሰው ጋር አብሮ ስለመሄድ የማያውቅ ማን ይኖራል? ይህ መግለጫ ፍቅርንና የጠበቀ ቅርርብን አያሳይም? እንዲህ ያሉት ስሜቶች ከአምላክ ጋር መሄድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ጥቂት ማስተዋል እንድናገኝ ይረዱናል። ይሁን እንጂ ነገሩን እስቲ ጠለቅ ብለን እንመርምር።
4 ታማኞቹን ሄኖክንና ኖኅን አስታውስ። ከአምላክ ጋር እንደሄዱ ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው? (ዘፍጥረት 5:24፤ 6:9) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መሄድ” ተብሎ የተጠቀሰው ቃል በአብዛኛው አንድን ዓይነት አካሄድ መከተልን ያመለክታል። ሄኖክና ኖኅ ከይሖዋ አምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ የሕይወት አቅጣጫ ይዘው ለመጓዝ መርጠው ነበር። በዙሪያቸው ባለው ዓለም ውስጥ ከነበሩት ሰዎች በተለየ የይሖዋን መመሪያ ይጠይቁና ይታዘዙ ነበር። በእርሱም ታምነዋል። እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ ውሳኔ ያደርግላቸው ነበር ማለት ነው? አይደለም። ይሖዋ ለሰው ልጆች የፈለጉትን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል፤ ይህን መብታችንንም በራሳችን “አእምሮ” እየተመራን እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። (ሮሜ 12:1) ቢሆንም ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ እጅግ ላቅ ባለው የይሖዋ አስተሳሰብ ለመመራት በትሕትና ፈቃደኞች እንሆናለን። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ኢሳይያስ 55:8, 9) እንዲህ ከሆነ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ወዳጆች ሆነን የሕይወትን ጉዞ መጓዝ እንችላለን።
5. ኢየሱስ በዕድሜ ላይ አንድ ክንድ ስለመጨመር የተናገረው ለምንድን ነው?
5 መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ሕይወትን ከጉዞ ወይም ከመሄድ ጋር ያመሳስለዋል። ንጽጽሩ አንዳንድ ጊዜ በቀጥታ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ተገልጿል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ “ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት [“ክንድ፣” NW] መጨመር የሚችል አለን?” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 6:27) እዚህ ላይ የተጠቀሱት አንዳንድ ቃላት በአእምሮህ ውስጥ ጥያቄ ይፈጥሩብህ ይሆናል። ኢየሱስ በዕድሜ ላይ ስለመጨመር ሲናገር የጊዜ ሳይሆን የርዝመት መለኪያ የሆነውን ‘አንድ ክንድ’ የተጠቀመው ለምንድን ነው?a ኢየሱስ ሕይወትን ከጉዞ ጋር እንዳዛመደው በግልጽ ማየት ይቻላል። መጨነቅ በሕይወት ጉዞህ ላይ ጥቂት እርምጃ እንኳን እንድትጨምር ሊያደርግህ እንደማይችል ትምህርት እየሰጠ ነበር። ይሁን እንጂ ከአምላክ ጋር በምናደርገው ጉዞ በርቀቱ ላይ የምናመጣው ለውጥ እንደሌለ ሊሰማን ይገባናል? በጭራሽ! ይህ ‘ከአምላክ ጋር መሄድ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?’ ወደሚለው ሁለተኛ ጥያቄያችን ይወስደናል።
ከአምላክ ጋር መሄድ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
6, 7. ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የግድ የሚያስፈልጋቸው ነገር ምንድን ነው? ይህንን ፍላጎታችንን ለማሟላት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት ያለብን ለምንድን ነው?
6 ከአምላክ ጋር መሄዳችን አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት በኤርምያስ 10:23 ላይ እንደሚከተለው ተገልጿል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።” ስለዚህ እኛ የሰው ልጆች የሕይወት አቅጣጫችንን የመምራት ችሎታም ሆነ መብት የለንም። የግድ መመሪያ ማግኘት ያስፈልገናል። ከአምላክ ተነጥለው በራሳቸው መንገድ ለመሄድ የቆረጡ ሁሉ አዳምና ሔዋን የፈጸሙትን ዓይነት ስህተት እየሠሩ ነው። የመጀመሪያዎቹ ጥንዶች ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር ራሳቸው የመወሰን መብት እንዳላቸው ተሰምቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-6) በአጭሩ ይህ የእኛ መብት ‘አይደለም።’
7 በሕይወት ጉዞ ላይ መመሪያ እንደሚያስፈልግ አይሰማህም? በየዕለቱ ከባድና ቀላል ውሳኔዎችን ማድረግ የሚጠይቁ ጉዳዮች ያጋጥሙናል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ አስቸጋሪና የእኛንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች የወደፊት ሁኔታ የሚነኩ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በዕድሜና በጥበብ ከእኛ በጣም የሚበልጥ አንድ አካል እነዚህን ውሳኔዎች ስናደርግ የሚረዳንን ፍቅራዊ መመሪያ ሊሰጠን ፈቃደኛ ነው! የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በገዛ አስተሳሰባቸው በመታመን የራሳቸውን እርምጃ ለመውሰድ መርጠዋል። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በምሳሌ 28:26 ላይ የተገለጸውን “በራሱ የሚታመን ተላላ ነው፤ በጥበብ የሚመላለስ ግን ክፉ አያገኘውም” የሚለውን ሐቅ ዘንግተዋል። ይሖዋ በተንኮለኛው ልባችን በመታመናችን ምክንያት ከሚመጡብን አደጋዎች እንድንጠበቅ ይፈልጋል። (ኤርምያስ 17:9) በማስተዋል እንድንጓዝ እንዲሁም እርሱን እንደ ጠቢብ መሪና አስተማሪ አድርገን እንድንታመንበት ይሻል። እንዲህ ካደረግን የሕይወት ጉዟችን አስተማማኝ፣ አስደሳችና አርኪ ይሆናል።
8. ኃጢአትና አለፍጽምና የሰው ልጆችን የት ይወስዷቸዋል? ቢሆንም ይሖዋ ምን እንድናገኝ ይፈልጋል?
8 ከአምላክ ጋር መሄዳችን ተገቢ የሆነበት ሌላው ምክንያት መጓዝ ከምንፈልገው ርቀት ጋር የተያያዘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ አሳዛኝ እውነታ ይገልጻል። ፍጹማን ያልሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ ተጉዘው የሚደርሱት ወደ አንድ ቦታ ነው ለማለት ይቻላል። እርጅና የሚያስከትላቸውን ችግሮች መክብብ 12:5 እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ሰው ወደ ዘላለማዊ ቤቱ ይሄዳል፤ አልቃሾችም በአደባባዮች ይዞራሉ።” እዚህ ላይ ‘ዘላለማዊ ቤት’ የተባለው ምንድን ነው? ኃጢአትና አለፍጽምና ይዘውን የሚሄዱበት መቃብር ነው። (ሮሜ 6:23) ሆኖም ይሖዋ ከመወለድ እስከ መሞት ካለው አጭርና በመከራ የተሞላ ጉዞ የሚበልጥ ነገር እንድናገኝ ይፈልጋል። (ኢዮብ 14:1) አምላክ የፈቀደልንን ረጅም ጉዞ ማለትም ዘላለማዊ ጉዞ የማድረግ አጋጣሚ የምናገኘው ከእርሱ ጋር ከሄድን ብቻ ነው። አንተስ የምትፈልገው ይህንን አይደለም? ከአባትህ ከይሖዋ ጋር መሄድህ አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ከአምላክ ጋር መሄድ የምንችለው እንዴት ነው?
9. ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ከሕዝቡ የሚሰወረው ለምን ነበር? ይሁን እንጂ በኢሳይያስ 30:20 ላይ ምን ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል?
9 ከዚህ በኋላ የምንመለከተውን ሦስተኛ ጥያቄ ከፍተኛ ትኩረት ልናደርግበት ይገባል። እርሱም ‘ከአምላክ ጋር መሄድ የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚል ነው። መልሱን በኢሳይያስ 30:20, 21 ላይ እናገኛለን። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “አስተማሪህ ከእንግዲህ አይሰወርብህም፤ ዐይኖችህም አስተማሪህን ያያሉ። ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ ‘መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ’ የሚል ድምፅ ይሰማል።” በቁጥር 20 ላይ የሰፈሩት የሚያበረታቱ ቃላት እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ በማመጻቸው ምክንያት ከእነርሱ ተሰውሮ የነበረበትን ጊዜ አስታውሰዋቸው ሊሆን ይችላል። (ኢሳይያስ 1:15፤ 59:2) እዚህ ላይ ግን ይሖዋ ለታማኝ ሕዝቦቹ እንደማይሰወርባቸውና ፊታቸው እንደሚቆም ተገልጿል። ይህ አባባል ተማሪዎቹ ሊያውቁ ይገባቸዋል ብሎ የሚያስበውን ለማስተማር ከፊት ለፊታቸው የቆመ አስተማሪ ወደ አእምሯችን እንዲመጣ ሊያደርግ ይችላል።
10. የአስተማሪህን ‘ድምፅ ከኋላህ የምትሰማው’ እንዴት ነው?
10 በቁጥር 21 ላይ ለየት ያለ ምሳሌያዊ መግለጫ ተጠቅሷል። ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚጓዙበትን ትክክለኛ አቅጣጫ ለማሳየት ከኋላቸው እንደሚሄድ ተደርጎ ተገልጿል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ይህ መግለጫ፣ አንዳንድ ጊዜ እረኛ በጎቹን ለመምራትና በተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሄዱ ለመጠበቅ ድምጽ በማሰማት መንጋውን በሚነዳበት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ይሰጣሉ። ይህ ምሳሌያዊ መግለጫ በእኛ ላይ የሚሠራው እንዴት ነው? መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክ ቃል ዘወር ስንል በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፉትን ቃላት እናነባለን። እነዚህ ቃላት የተጻፉት ከረጅም ጊዜ በፊት ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ከኋላችን የምንሰማቸው ያህል ነው። ቢሆንም እንደተጻፉበት ዘመን ሁሉ በጊዜያችንም የሚሠሩ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በየዕለቱ ለሚያጋጥሙን ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች መመሪያ ይሆነናል፤ እንዲሁም ለወደፊቱ የሕይወት ጉዟችን እቅድ ለማውጣት ሊረዳን ይችላል። (መዝሙር 119:105) እንዲህ ያለውን ምክር በጥብቅ ስንፈልግና በሥራ ላይ ስናውል ይሖዋ መሪያችን ይሆናል፤ ከእርሱም ጋር እንሄዳለን።
11. ይሖዋ በኤርምያስ 6:16 ላይ የሕዝቡን ልብ የሚነካ ምን ምሳሌያዊ አነጋገር ተጠቅሟል? ይሁንና ምላሻቸው ምን ነበር?
11 የአምላክ ቃል ያን ያህል በቅርብ ሆኖ እንዲመራን በእርግጥ ፈቅደናል? አንዳንድ ጊዜ ቆም ብለን በታማኝነት ራሳችንን መመርመሩ ጠቃሚ ነው። እንዲህ እንድናደርግ የሚረዳንን አንድ ጥቅስ ተመልከት:- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘መንታ መንገድ ላይ ቁሙ፣ ተመልከቱም፤ መልካሟን፣ የጥንቷን መንገድ ጠይቁ፤ በእርሷም ላይ ሂዱ። ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ።’” (ኤርምያስ 6:16) እነዚህ ቃላት በመስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሞ አቅጣጫ እየጠየቀ ያለን ተጓዥ አስታውሰውን ይሆናል። በእስራኤል የሚኖሩ በይሖዋ ላይ ያመጹ ሰዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ ከተጓዡ ጋር የሚመሳሰል ነገር ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር። ተመልሰው “የጥንቷን መንገድ” መፈለግ ነበረባቸው። ‘መልካሟ መንገድ’ የተባለችው ታማኝ ቅድመ አያቶቻቸው ሲጓዙባት የነበረችውና ብሔሩ በሞኝነት የተዋት መንገድ ነች። የሚያሳዝነው እስራኤላውያን ይሖዋ የሰጠውን ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ለመቀበል አሻፈረን አሉ። በዚያው ቁጥር ላይ “እናንተ ግን፣ ‘በእርሷ አንሄድም’ አላችሁ” የሚል ሐሳብ ይገኛል። ይሁን እንጂ በዘመናችን ያሉ የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ላለው ምክር ከዚህ የተለየ ምላሽ ሰጥተዋል።
12, 13. (ሀ) የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች በኤርምያስ 6:16 ላይ ለተሰጠው ምክር ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ እየሄድንበት ስላለው መንገድ ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?
12 ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች በኤርምያስ 6:16 ላይ የሚገኘው ምክር ለእነርሱ እንደሚሠራ ተሰምቷቸው ነበር። እነዚህ ቅቡዓን በቡድን ደረጃ በሙሉ ልባቸው ወደ ‘ጥንቷ መንገድ’ ተመልሰዋል። ከከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና በተቃራኒ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረተውንና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ታማኝ ተከታዮቹ የደገፉትን “የጤናማ ትምህርት ምሳሌ” የሙጥኝ ብለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 1:13) እስከ አሁን ድረስ ቅቡዓኑ እርስ በርሳቸውና አጋሮቻቸው ከሆኑት “ሌሎች በጎች” ጋር እየተደጋገፉ ሕዝበ ክርስትና የተወችውን ጤናማና አስደሳች የሕይወት ጎዳና ይከተላሉ።—ዮሐንስ 10:16
13 የታማኙ ባሪያ ክፍል መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ በማቅረብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “የጥንቷን መንገድ” እንዲያገኙና ከአምላክ ጋር እንዲጓዙ እየረዳ ነው። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) አንተስ ከእነዚህ መካከል ትገኛለህ? ከሆነ ትክክለኛውን አቅጣጫ ስተህ የራስህን መንገድ እንዳትከተል ምን ማድረግ ትችላለህ? በየጊዜው ቆም እያልክ የሕይወት አቅጣጫህን መመርመርህ መልካም ነው። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አዘውትረህ ካነበብክ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ቅቡዓን በሚያዘጋጅዋቸው መመሪያ የሚሰጥባቸው ፕሮግራሞች ላይ ከተካፈልህ ከአምላክ ጋር ለመሄድ የሚያስችልህን ሥልጠና እያገኘህ ነው። በተጨማሪም የተሰጠህን ምክር በትሕትና ሥራ ላይ የምታውል ከሆነ “የጥንቷን መንገድ” ተከትለህ ከአምላክ ጋር እየሄድክ ነው።
‘የማይታየውን እንደሚታይ አድርጎ’ መሄድ
14. ይሖዋ እውን እንደሆነልን በግል ውሳኔዎቻችን የሚንጸባረቀው እንዴት ነው?
14 ከይሖዋ ጋር ለመጓዝ እርሱ እውን ሊሆንልን ይገባል። ይሖዋ በጥንት እስራኤል ለነበሩት ታማኝ ሰዎች እንደማይሰወርባቸው የነገራቸውን አስታውስ። ዛሬም ቢሆን ለሕዝቡ ራሱን እንደ ታላቅ አስተማሪ አድርጎ ይገልጣል። ይሖዋ አንተን ለማስተማር ከፊትህ የቆመ ያህል ሕያው ሆኖ ይታይሃል? ከአምላክ ጋር መሄድ የምንፈልግ ከሆነ እንዲህ ዓይነት እምነት ያስፈልገናል። ሙሴ እንዲህ ያለ እምነት ስለነበረው “የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቊጠር በሐሳቡ ጸና።” (ዕብራውያን 11:27) ይሖዋ እውን ከሆነልን ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ የእርሱን ስሜት ከግምት ውስጥ እናስገባለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጥፎ ድርጊት የመፈጸምና ኃጢአታችንን ከጉባኤ ሽማግሌዎች ወይም ከቤተሰባችን አባላት የመደበቅ ሐሳብ ፈጽሞ አይኖረንም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች ሊያዩን በማይችሉበት ጊዜም እንኳን ከአምላክ ጋር ለመሄድ እንጣጣራለን። በጥንት ዘመን እንደኖረው ንጉሥ ዳዊት “በቤቴ ውስጥ፣ በንጹሕ ልብ እመላለሳለሁ” የሚል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—መዝሙር 101:2
15. ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር መቀራረባችን ይሖዋ ሕያው ሆኖ እንዲታየን የሚረዳን እንዴት ነው?
15 ይሖዋ ኃጢአተኞችና ሥጋ ለባሽ መሆናችንን እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በማናየው ነገር ለማመን ልንቸገር እንደምንችል ያውቃል። (መዝሙር 103:14) እንዲህ ያሉትን ድክመቶች ማሸነፍ እንድንችል ለመርዳት ብዙ ነገሮችን አዘጋጅቶልናል። ለምሳሌ ያህል በምድር ላይ ከሚገኙት ብሔራት ሁሉ የተውጣጣ “ለእርሱ የሚሆነውን ሕዝብ” ሰብስቧል። (የሐዋርያት ሥራ 15:14) አብረን ስናገለግል እርስ በርሳችን እንበረታታለን። መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የነበሩባቸውን አንዳንድ ድክመቶች ወይም አስቸጋሪ ፈተናዎች እንዲወጡ ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው ስንሰማ አምላካችን ይበልጥ ሕያው ይሆንልናል።—1 ጴጥሮስ 5:9
16. ስለ ኢየሱስ መማራችን ከአምላክ ጋር ለመሄድ የሚረዳን እንዴት ነው?
16 ከሁሉም በላይ ይሖዋ ልጁን ምሳሌ አድርጎ ሰጥቶናል። ኢየሱስ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:6) ይሖዋ ይበልጥ ሕያው ሆኖ እንዲታየን የሚያደርገው ከሁሉ የተሻለው መንገድ ኢየሱስ ምድር ላይ የተጓዘበትን የሕይወት ጎዳና መመርመር ነው። ኢየሱስ የተናገረውም ሆነ ያደረገው ነገር በሙሉ የሰማያዊ አባቱ ባሕርይና አሠራር ፍጹም ነጸብራቅ ነው። (ዮሐንስ 14:9) ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ኢየሱስ ነገሮችን ስለሚይዝበት መንገድ በጥንቃቄ ማሰብ ይገባናል። እንዲህ በጥንቃቄና በጸሎት አስበንበት ውሳኔ የምናደርግ ከሆነ የክርስቶስን ፈለግ እየተከተልን ነው። (1 ጴጥሮስ 2:21) ይህ ከሆነ ከአምላክ ጋር እየሄድን ነው።
ምን በረከት እናገኛለን?
17. በይሖዋ መንገድ ከሄድን ለነፍሳችን ምን ዓይነት “ዕረፍት” እናገኛለን?
17 ከይሖዋ አምላክ ጋር መሄድ በረከት የሞላበት ሕይወት ያስገኛል። ይሖዋ ሕዝቡ ‘መልካሟን መንገድ’ ቢከተል የሚያገኘው ነገር እንዳለ ቃል እንደገባ አስታውስ። “በእርሷም ላይ ሂዱ። ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ኤርምያስ 6:16) እዚህ ላይ “ዕረፍት” የተባለው ምንድን ነው? ደስታና ቅንጦት የሞላበት ኑሮ ማለት ነው? አይደለም። ይሖዋ ከዚህ እጅግ የሚበልጥና የዓለም ሀብታሞች እምብዛም የማያገኙት ነገር ይሰጣል። ለነፍስህ እረፍት የምታገኘው ውስጣዊ ሰላም፣ ደስታና እርካታ ሲኖርህ እንዲሁም መንፈሳዊ ፍላጎትህ ሲሟላ ነው። እንዲህ ዓይነት እረፍት አለህ ማለት በሕይወት ጎዳና ላይ ጥሩውን መንገድ እንደመረጥክ ትተማመናለህ ማለት ነው። በዚህ አስቸጋሪ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለውን የአእምሮ ሰላም ማግኘት ደግሞ ትልቅ በረከት ነው!
18. ይሖዋ ምን በረከት ሊያፈስልህ ይፈልጋል? የአንተስ ቁርጥ ውሳኔ ምንድን ነው?
18 በእርግጥ ሕይወት ራሱ ትልቅ በረከት ነው። ጥቂት ዘመን መኖር ብቻ እንኳን ጨርሶ ካለመኖር ይሻላል። ይሁንና ይሖዋ ከወጣትነት ብርታት፣ ችግር እስከሞላበት የዕድሜ መግፋት ድረስ ያለውን አጭር ጊዜ ብቻ እንድትጓዝ ዓላማው አይደለም። አዎን፣ ይሖዋ ከበረከቶች ሁሉ የላቀውን በረከት እንድታገኝ ይፈልጋል። ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንድትሄድ ይሻል! ይህ ሁኔታ በሚክያስ 4:5 ላይ ጥሩ ተደርጎ ተገልጿል:- “አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።” ይህንን በረከት ማግኘት ትፈልጋለህ? ይሖዋ ‘እውነተኛ ሕይወት’ ብሎ የጠራውን የሚያጓጓ ሕይወት ለማግኘት ትሻለህ? (1 ጢሞቴዎስ 6:19) ዛሬም፣ ነገም እንዲሁም ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት ሁሉ ለዘላለም ከይሖዋ ጋር ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በዚህ ጥቅስ ላይ ያለውን “ክንድ” የሚለውን ቃል “ጥቂት ጊዜ” (ዚ ኢምፋቲክ ዲያግሎት) ወይም “አንድ ደቂቃ” (ኤ ትራንስሌሽን ኢን ዘ ላንግዊጅ ኦቭ ዘ ፒፕል፣ በቻርልስ ቢ ዊልያምስ) እንደሚሉት ባሉ የጊዜ መለኪያዎች ተክተውታል። ሆኖም መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ የገባው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ ክንድ የሚል ሲሆን ርዝመቱም ወደ 45 ሴንቲ ሜትር ገደማ ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ከአምላክ ጋር መሄድ ሲባል ምን ማለት ነው?
• ከአምላክ ጋር መሄድ እንዳለብህ የሚሰማህ ለምንድን ነው?
• ከአምላክ ጋር እንድትሄድ የሚረዳህ ምንድን ነው?
• ከአምላክ ጋር የሚሄዱ ምን በረከቶች ያገኛሉ?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ከኋላችን ሆኖ “መንገዱ ይህ ነው” የሚለንን የይሖዋን ድምጽ እንሰማለን
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስብሰባዎች ላይ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ እናገኛለን