“ነፍሴ ሆይ፣ ይሖዋን ባርኪ”
ናንሲ “ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገልግሎት የማደርገው ተሳትፎ አሰልቺና ምንም ደስታ የማይሰጥ እየሆነብኝ መጥቷል” ስትል ተናግራለች።a ለአሥር ዓመታት ያህል የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ ሆና በአቅኚነት ስታገለግል ቆይታለች። ሆኖም በማከል እንዲህ ትላለች:- “ይህ ግን የጤና አልመሰለኝም። የመንግሥቱን መልእክት እንዲያው ለይስሙላና ከአንገት በላይ እንደማቀርብ ሆኖ ይሰማኛል። ምን ባደርግ ይሻለኛል?”
በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለውን የኪትን ሁኔታም ተመልከት። ባለቤቱ “ሐሳብህ የተበታተነ ይመስለኛል። አሁን የምግብ ሰዓት አይደለም፤ በጸሎትህ ላይ ግን ስለ ምግብ አመስግነሃል” ስትለው በጣም ደነገጠ! ኪት “ጸሎት የማቀርበው እንዲያው በደመ ነፍስ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል።
ለይሖዋ አምላክ የምታቀርበው ውዳሴ ስሜት አልባና ልማዳዊ እንዲሆን እንደማትፈልግ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ የምታቀርበው ውዳሴ በአመስጋኝነት ስሜት ከልብ የመነጨ እንዲሆን ትፈልጋለህ። ይሁን እንጂ የአመስጋኝነት ስሜት እንዲያው እንደ ልብስ ከላይ የሚለበስ ወይም የሚወለቅ ነገር አይደለም። ከውስጥ ፈንቅሎ መውጣት አለበት። አንድ ሰው ከልብ አመስጋኝ መሆን የሚችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ 103ኛው መዝሙር ሰፋ ያለ ግንዛቤ ይሰጠናል።
አንድ መቶ ሦስተኛውን መዝሙር ያቀነባበረው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ዳዊት ነው። መዝሙሩን የጀመረው “ነፍሴ ሆይ፣ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ባርኪ፣ አጥንቶቼም ሁሉ፣ የተቀደሰ ስሙን” በሚሉት ቃላት ነው። (መዝሙር 103:1) አንድ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “መባረክ የሚለው ቃል ከአምላክ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ሲሠራበት ማወደስ ማለት ነው። ይህም ምንጊዜም ለእርሱ ጠንካራ ፍቅር እንዲሁም የአመስጋኝነት መንፈስ መያዝን ያመለክታል።” ዳዊት ይሖዋን በፍቅርና በአድናቆት በተሞላ ልብ ለማወደስ ካለው ፍላጎት በመነሳት የራሱን ነፍስ (ራሱን) “ይሖዋን ባርኪ” በማለት አሳስቧል። ሆኖም ዳዊት ለሚያመልከው አምላክ በልቡ እንዲህ ዓይነት ሞቅ ያለ ስሜት እንዲኖረው ያስቻለው ምንድን ነው?
ዳዊት “ምስጋናውንም [“ሥራዎቹንም፣” NW] ሁሉ አትርሺ” በማለት ይቀጥላል። (መዝሙር 103:2) ለይሖዋ የአመስጋኝነት ስሜት መያዝ ‘በሥራዎቹ’ ላይ በአድናቆት ከማሰላሰል ጋር ግንኙነት እንዳለው ግልጽ ነው። ዳዊት በአእምሮው ይዞት የነበረው የይሖዋ ሥራ ምንድን ነው? የይሖዋ አምላክን የፍጥረት ሥራ፣ ለምሳሌ ያህል ጥርት ባለ ሌሊት በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ መመልከት ልብ ለፈጣሪ በአመስጋኝነት እንዲሞላ ያደርጋል። በከዋክብት የተሞላው ሰማይ ዳዊትን በጥልቅ ነክቶታል። (መዝሙር 8:3, 4፤ 19:1) ሆኖም ዳዊት በ103ኛው መዝሙር ላይ ሌላውን የይሖዋ የሥራ ዘርፍ አስታውሷል።
ይሖዋ ‘ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር ይላል’
በዚህ መዝሙር ላይ ዳዊት የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት የሚያንጸባርቁ ድርጊቶችን ያወሳል። ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያውንና ዋነኛውን በመጥቀስ እንዲህ ሲል ዘምሯል:- ‘ይሖዋ ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር ይላል።’ (መዝሙር 103:3) ዳዊት የራሱን የኃጢአተኝነት ሁኔታ ተገንዝቦ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ነቢዩ ናታን ዳዊትን ከቤርሳቤህ ጋር ስለፈጸመው ምንዝር ከወቀሰው በኋላ ዳዊት “[ይሖዋ] አንተን ብቻ በደልሁ፣ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ” በማለት ጥፋቱን አምኗል። (መዝሙር 51:4) ዳዊት በተሰበረ ልብ እንዲህ ሲል ተማጽኗል:- “አቤቱ፣ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ።” (መዝሙር 51:1, 2) ዳዊት ምሕረት ማግኘቱ የአመስጋኝነት ስሜት እንዳሳደረበት ጥርጥር የለውም! ዳዊት አለፍጽምና የወረሰ ሰው እንደመሆኑ መጠን በሕይወቱ ውስጥ ሌሎች ኃጢአቶችንም ፈጽሟል፤ ሆኖም ንስሐ ለመግባት፣ ተግሳጽ ለመቀበልና አካሄዱን ለማስተካከል አንገራግሮ አያውቅም። ዳዊት አምላክ ባሳየው አስደናቂ ደግነት ላይ ማሰላሰሉ ይሖዋን እንዲባርክ አነሳስቶታል።
እኛስ ብንሆን ኃጢአተኞች አይደለንም? (ሮሜ 5:12) ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳ እንዲህ ሲል በምሬት ተናግሯል:- “በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” (ሮሜ 7:22-24) ይሖዋ ኃጢአቶቻችንን መዝግቦ የማይዝ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኝ መሆን ይገባናል! ይሖዋ ንስሐ ገብተን ምሕረት ስንጠይቅ የፈጸምናቸውን ኃጢአቶች በደስታ ይደመስስልናል።
ዳዊት ‘ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ ይሖዋ ነው’ በማለት ራሱን አስገንዝቧል። (መዝሙር 103:3) ፈውስ ወደ ቀድሞ ሁኔታ የመመለስ ድርጊት ስለሆነ ኃጢአትን ይቅር ከማለት የበለጠ ነገር ያጠቃልላል። የፈጸምነው ስህተት ያስከተለብንን መጥፎ መዘዝ ማለትም ‘ደዌን’ ማስወገድ ያካትታል። ይሖዋ በሚያዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ እንደ በሽታና ሞት ያሉትን አካላዊ የኃጢአት ውጤቶች እንደሚያስወግድ የተረጋገጠ ነው። (ኢሳይያስ 25:8፤ ራእይ 21:1-4) ዛሬም እንኳ ሳይቀር አምላክ ከመንፈሳዊ ደዌዎች እየፈወሰን ነው። ይህ ፈውስ ለአንዳንዶች ከመጥፎ ሕሊናና ከአምላክ ጋር ካላቸው የሻከረ ግንኙነት መላቀቅ ማለት ነው። በዚህ ረገድ ይሖዋ እስካሁን ድረስ በግል ለእያንዳንዳችን ያደረገልንን ‘አትርሱ።’
‘ሕይወትሽን የሚያድናት’ እርሱ ነው
ዳዊት ‘ሕይወትሽን ከጥፋት [“ከጥልቅ ጉድጓድ፣” NW] የሚያድናት ይሖዋ ነው’ በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 103:4) ‘ጥልቅ ጉድጓድ’ የሰው ልጆች የጋራ መቃብር የሆነው ሲኦል ወይም ሔድስ ነው። ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ ከመሆኑ በፊት እንኳ የሞት አደጋ ተደቅኖበት ነበር። ለምሳሌ ያህል የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን ለመግደል በውስጡ ጥላቻ ከማሳደሩም በላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሊገድለው ሞክሯል። (1 ሳሙኤል 18:9-29፤ 19:10፤ 23:6-29) ፍልስጥኤማውያንም ዳዊትን መግደል ይፈልጉ ነበር። (1 ሳሙኤል 21:10-15) ሆኖም በእያንዳንዱ አጋጣሚ ይሖዋ ዳዊትን “ከጥልቅ ጉድጓድ” አድኖታል። ዳዊት እነዚህን የይሖዋ ሥራዎች ሲያስታውስ ምንኛ በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላ ይሆን!
ያንተስ ስሜት እንዴት ነው? ጭንቀት ወይም ሐዘን በተሰማህ ወቅት ይሖዋ ደግፎህ ያውቃል? ወይም በጊዜያችን ይሖዋ የታማኝ ምሥክሮቹን ሕይወት ከሞት አፋፍ ያዳነባቸውን አጋጣሚዎች ታውቃለህ? ምናልባትም በዚህ መጽሔት እትሞች ላይ የወጡ የይሖዋን የማዳን ተግባሮች የሚያሳዩ ታሪኮች በማንበብ ልብህ ተነክቶ ይሆናል። እውነተኛው አምላክ ባከናወናቸው በእነዚህ ሥራዎች ላይ ለምን ጊዜ ወስደህ በአድናቆት አታሰላስልም? እንዲሁም ይሖዋ ለሰጠን የትንሣኤ ተስፋ ሁላችንም አመስጋኝ የምንሆንበት ምክንያት እንዳለ የታወቀ ነው።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15
ይሖዋ ሕይወትን ብቻ ሳይሆን ሕይወትን አስደሳችና ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያስችሉ ነገሮች ይሰጠናል። መዝሙራዊው አምላክ ‘በምሕረቱና በቸርነቱ እንደሚከልለው’ ተናግሯል። (መዝሙር 103:4) ይሖዋ መከራ ሲገጥመን አይተወንም፤ እንዲያውም በሚታየው ድርጅቱና በጉባኤ በሚገኙ የተሾሙ ሽማግሌዎች ወይም እረኞች አማካኝነት እኛን ለመርዳት ከጎናችን ይቆማል። ይህ ዓይነቱ እርዳታ ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ለራሳችን ያለንን አክብሮትና ግምት ሳናጣ ችግሩን እንድንወጣ ያስችለናል። ክርስቲያን እረኞች ለበጎች ከፍተኛ አሳቢነት ያሳያሉ። የታመሙትንና ያዘኑትን ያበረታታሉ እንዲሁም መንፈሳዊ ውድቀት የደረሰባቸውን ለማቅናት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3፤ ይሁዳ 22, 23) እነዚህ እረኞች ለመንጋው ርኅራሄና ፍቅር እንዲያሳዩ የይሖዋ መንፈስ ይገፋፋቸዋል። በእርግጥም ‘ምሕረቱና ቸርነቱ’ ልክ እንደ ዘውድ ግርማ ሞገስ እንዲሁም ክብር ያላብሰናል! ሥራዎቹን ፈጽሞ ባለመርሳት ይሖዋንና ቅዱስ ስሙን እንባርክ።
መዝሙራዊው ዳዊት ራሱን በራሱ መምከሩን በመቀጠል “[ይሖዋ] ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፣ ጎልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 103:5) ይሖዋ የሚሰጠን ሕይወት እርካታና ደስታ ያስገኛል። ሌላው ቀርቶ እውነትን ማወቃችን ራሱ አቻ የማይገኝለት ሃብትና ከፍተኛ ደስታ ያስገኛል! እንዲሁም ይሖዋ የሰጠን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ምን ያህል አርኪ እንደሆነ አስቡ። ስለ እውነተኛው አምላክ የመማር ፍላጎት ያለው ሰው ማግኘትና ይሖዋን ወደ ማወቅና መባረክ ደረጃ እንዲደርስ መርዳት ምንኛ አስደሳች ነው! ሆኖም በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች መልእክቱን ተቀበሉም አልተቀበሉ የይሖዋን ስም ከማስቀደስና ሉዓላዊነቱ እንዲረጋገጥ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ሥራ ድርሻ ማበርከታችን ታላቅ መብት ነው።
የአምላክን መንግሥት በማወጁ ሥራ በጽናት ስንቀጥል ድካም ወይም መዛል የማይሰማው ማን አለ? ሆኖም ይሖዋ ጠንካራ ክንፍ እንዳለውና በሰማይ ላይ በከፍተኛ ርቀት እንደሚመጥቅ “ንስር” ለአገልጋዮቹ ብርታት ይሰጣል። ከቀን ወደ ቀን አገልግሎታችንን በታማኝነት መወጣት እንድንችል አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን እንዲህ ዓይነት ‘ብርታት’ የሚሰጠን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኝ መሆን እንችላለን!—ኢሳይያስ 40:29-31
የሙሉ ጊዜ ዓለማዊ ሥራ ያላት ከመሆኑም በላይ በየወሩ በመስክ አገልግሎት ወደ 50 ሰዓት ገደማ የምታሳልፈው የክላራ ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። እንዲህ ትላለች:- “አንዳንድ ጊዜ ከመድከሜ የተነሳ ወደ መስክ አገልግሎት የምወጣው ራሴን አስገድጄ ሲሆን እንዲህ የማደርገውም አብረን እንድናገለግል የቀጠርኩት ሰው ስለሚኖር ብቻ ነው። ሆኖም እንደምንም ብዬ አገልግሎት ከወጣሁ በኋላ ሁልጊዜ ብርታት እንዳገኘሁ ይሰማኛል።” አንተም ብትሆን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስትሠማራ በመለኮታዊ ድጋፍ አማካኝነት ኃይል እንዳገኘህ ይሰማህ ይሆናል። በዚህ መዝሙር መክፈቻ ላይ ዳዊት “ነፍሴ ሆይ፣ እግዚአብሔርን ባርኪ፣ አጥንቶቼም ሁሉ፣ የተቀደሰ ስሙን” እንዳለው ሁሉ አንተም እንዲህ ለማለት እንድትነሳሳ እንመኛለን።
ይሖዋ ሕዝቦቹን ያድናል
መዝሙራዊው እንዲህ በማለትም ዘምሯል:- “እግዚአብሔር ይቅርታ አድራጊ ነው፤ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል። ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፣ ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን።” (መዝሙር 103:6, 7) ዳዊት እስራኤላውያን በሙሴ ዘመን በግብጻውያን ጭቆና ስር በነበሩበት ጊዜ ስለደረሰባቸው ‘በደል’ ሳያስብ አልቀረም። ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት ነፃ እንደሚያወጣ ለሙሴ ባሳወቀው ነገር ላይ ዳዊት ማሰላሰሉ በልቡ ውስጥ የአመስጋኝነት ስሜት እንዲቀሰቀስ አድርጎ መሆን አለበት።
እኛም አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት ማሰላሰላችን ተመሳሳይ የሆነ አመስጋኝነት እንድናሳይ ሊያነሳሳን ይችላል። ሆኖም የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ በምዕራፍ 29 እና 30 ላይ ተጠቅሰው እንዳሉት የዘመናችን የይሖዋ አገልጋዮች ተሞክሮዎች ላይ ከማሰላሰል ወደኋላ ማለት የለብንም። በዚህ መጽሐፍና በሌሎች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ የሰፈሩት ታሪኮች በዘመናችን ይሖዋ ሕዝቦቹ እስራትን፣ ዓመፅን፣ እገዳዎችን፣ ማጎሪያ ካምፖችን እንዲሁም የጉልበት ሥራ የሚሰጥባቸውን ካምፖች በጽናት እንዲወጡ የረዳበትን መንገድ እንድናስተውል ያስችለናል። እንደ ቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በመሳሰሉ ጦርነት በተካሄደባቸው አገሮች ፈታኝ ሁኔታዎች ተከስተዋል። ይሖዋ ስደት በተነሳ ቁጥር ምንጊዜም ታማኝ አገልጋዮቹን ደግፏቸዋል። ታላቁ አምላካችን ይሖዋ ባከናወናቸው በእነዚህ ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን ዳዊት እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ ስለወጡበት ታሪክ ማሰላሰሉ እንደጠቀመው ሁሉ እኛንም ይጠቅመናል።
በተጨማሪም ይሖዋ ርኅራሄ በተሞላበት መንገድ ከኃጢአት ኩነኔ እንዴት ነፃ እንደሚያወጣን ተመልከት። ‘ሕሊናችንን ከሞተ ሥራ ለማንጻት’ ‘የክርስቶስን ደም’ ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 9:14 የ1980 ትርጉም) በሠራናቸው ኃጢአቶች ተጸጽተን በፈሰሰው የክርስቶስ ደም አማካኝነት ምሕረት ስንጠይቅ “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ” አምላክ ኃጢአታችንን ከእኛ በማራቅ መልሶ ሞገስ ያሳየናል። በተጨማሪም ይሖዋ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ ገንቢ በሆነ ወዳጅነት፣ በጉባኤ እረኞች እና በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት በሚደርሱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አማካኝነት ስለሚሰጠን ነገሮች አስብ። (ማቴዎስ 24:45) እነዚህ የይሖዋ ሥራዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና እንድናጠናክር አይረዱንም? መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። . . . እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።” (መዝሙር 103:8-14) በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ ላይ ማሰላሰላችን በእርግጥ እርሱን እንድናወድስና ቅዱስ ስሙን ከፍ ከፍ እንድናደርግ ያነሳሳናል።
‘ፍጥረቶቹ ሁሉ ይሖዋን ባርኩ’
‘ሟች የሆነ ሰው’ ያለመሞት ባሕርይ ከተላበሰው ‘ከዘላለማዊው አምላክ’ ከይሖዋ ጋር ሲነጻጸር በእርግጥ “ዘመኑ እንደ ሣር” አጭር ነው። ሆኖም ዳዊት በአድናቆት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የእግዚአብሔር ምሕረት ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ፣ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ ነው፤ ቃል ኪዳኑን በሚጠብቁ፣ ትእዛዙንም ያደርጉአት ዘንድ በሚያስቡ ላይ ነው።” (ዘፍጥረት 21:33፤ መዝሙር 103:15-18) ይሖዋ የሚፈሩትን ሰዎች አይረሳም። በተገቢው ጊዜ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል።—ዮሐንስ 3:16፤ 17:3
ዳዊት ለይሖዋ ንግሥና ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ፣ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።” (መዝሙር 103:19) ምንም እንኳ ለተወሰነ ጊዜ የይሖዋ ንግሥና በእስራኤል መንግሥት አማካኝነት በእውን የተገለጸ ቢሆንም በእርግጥ የእርሱ ዙፋን የሚገኘው በሰማይ ነው። ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ከመሆኑም በላይ በዓላማው መሠረት በሰማይም ሆነ በምድር መለኮታዊ ፈቃዱን ያስፈጽማል።
ዳዊት በሰማይ የሚኖሩ መላእክታዊ ፍጥረታት ጭምር ይሖዋን እንዲባርኩ አሳስቧል። እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ቃሉን የምትፈጽሙ፣ ብርቱዎችና ኃያላን፣ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፣ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፣ እግዚአብሔርን ባርኪ።” (መዝሙር 103:20-22) ይሖዋ ለእኛ ፍቅራዊ ደግነቱን ባንፀባረቀባቸው ድርጊቶች ላይ ማሰላሰላችን እኛም እርሱን እንድንባርክ ሊያነሳሳን አይገባም? በእርግጥ ይገባል! በግል ለይሖዋ የምናሰማው የውዳሴ ድምፅ ቅዱሳን መላእክትን በሚያካትተው ከፍተኛ የአወዳሾች ጓድ በሚያሰማው ድምፅ ውስጥ ተውጦ እንደማይቀር እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ምንጊዜም ስለ ሰማያዊ አባታችን በጎ ነገር በመናገር እርሱን በሙሉ ልባችን የምናወድስ ያድርገን። በእርግጥም “ነፍሴ ሆይ፣ ይሖዋን ባርኪ” የሚሉትን የዳዊት ቃላት ፈጽሞ አንርሳ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነቱ በፈጸማቸው ድርጊቶች ላይ ዳዊት አሰላስሏል። አንተስ?