ምዕራፍ 14
አምላክ የሚቀበለው አምልኮ
ከዚህ በፊት ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው አምላክን የሚያስደስቱት ሁሉም ሃይማኖቶች አይደሉም። ሆኖም ፈጣሪያችንን እሱ በሚፈልገው መንገድ ማምለክ እንችላለን። እሱን የሚያስደስተው “አምልኮ [ወይም፣ ሃይማኖት]” የትኛው ነው? (ያዕቆብ 1:27 የግርጌ ማስታወሻ) መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ተመልከት።
1. አምልኳችን በምን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል?
አምልኳችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል። ኢየሱስ ወደ አምላክ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:17) አንዳንድ ሃይማኖቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት ችላ ይላሉ። ይህን እውነት በሰዎች ትምህርትና ወግ ተክተውታል። ይሖዋ ግን ‘ትእዛዙን ገሸሽ በሚያደርጉ’ ሰዎች ደስ አይሰኝም። (ማርቆስ 7:9ን አንብብ።) በሌላ በኩል ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ስንመራና በውስጡ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ስናደርግ ልቡን ደስ እናሰኛለን።
2. ይሖዋን ልናመልክ የሚገባው እንዴት ነው?
ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ሊመለክ የሚገባው እሱ ብቻ ነው። (ራእይ 4:11) እሱን ብቻ መውደድ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ቅርጻ ቅርጽ ወይም ምስል ሳንጠቀም ልናመልከው ይገባል።—ኢሳይያስ 42:8ን አንብብ።
አምልኳችን “ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው” መሆን ይኖርበታል። (ሮም 12:1) ይህም ሲባል እሱ ባወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት አለብን ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች እሱ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ያወጣውን መመሪያ ሊቀበሉና ሊታዘዙ ይገባል። በተጨማሪም ሲጋራ እንደማጨስ፣ ጫት እንደመቃም እንዲሁም ዕፆችን ወይም አልኮልን አላግባብ እንደመጠቀም ካሉ ጎጂ ልማዶች ይርቃሉ።a
3. ከሌሎች ጋር አብረን ይሖዋን ማምለክ ያለብን ለምንድን ነው?
በየሳምንቱ የምናደርጋቸው ስብሰባዎች “በጉባኤ ይሖዋን [የምናወድስበት]” አጋጣሚ ይሰጡናል። (መዝሙር 111:1, 2) አምላክን የምናወድስበት አንዱ መንገድ የውዳሴ መዝሙር መዘመር ነው። (መዝሙር 104:33ን አንብብ።) ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ያዘዘን ስለሚወደንና እንዲህ ማድረጋችን ለዘላለም በደስታ የምንኖርበት አጋጣሚ እንደሚከፍትልን ስለሚያውቅ ነው። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ እርስ በርስ መበረታታት እንችላለን።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ይሖዋ ምስሎችን ተጠቅመን የምናቀርበውን አምልኮ የማይቀበለው ለምን እንደሆነ እንመረምራለን። በተጨማሪም ይሖዋን ማወደስ የምንችልባቸውን ዋና ዋና መንገዶች እንመለከታለን።
4. ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም የለብንም
ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀማችን አምላክን እንደሚያሳዝነው እንዴት እናውቃለን? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በጥንት ዘመን ከአምላክ ሕዝቦች መካከል አንዳንዶቹ ጣዖት ተጠቅመው አምላክን ለማምለክ መሞከራቸው ምን ውጤት አስከትሏል?
አንዳንድ ሰዎች በአምልኳቸው ላይ ምስሎችን መጠቀማቸው ይበልጥ ወደ አምላክ እንዲቀርቡ እንደሚረዳቸው ይሰማቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ እንዲህ ማድረጋቸው ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል ወይስ ከአምላክ ያርቃቸዋል? ዘፀአት 20:4-6ን እና መዝሙር 106:35, 36ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ሰዎች የትኞቹን ነገሮች ወይም ምስሎች ለአምልኮ ሲጠቀሙ ተመልክተሃል?
ይሖዋ ምስሎችን ለአምልኮ ስለ መጠቀም ምን ይሰማዋል?
አንተስ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ተገቢ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
5. ይሖዋን ብቻ ማምለካችን ከሐሰት ትምህርቶች ነፃ ያወጣናል
ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ ማምለክ ከሐሰት ትምህርቶች ነፃ የሚያወጣን እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ።
መዝሙር 91:14ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ እሱን ብቻ በማምለክ እንደምንወደው የምናሳይ ከሆነ ምን እንደሚያደርግልን ቃል ገብቷል?
6. በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የአምልኳችን ክፍል ነው
በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መልስ ስንመልስና መዝሙር ስንዘምር ይሖዋን እናወድሳለን እንዲሁም እርስ በርስ እንበረታታለን። መዝሙር 22:22ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡትን ሐሳቦች መስማት ያስደስትሃል?
አንተስ መልስ ለመመለስ እንዴት መዘጋጀት እንደሚቻል ማየት ትፈልጋለህ?
7. የተማርነውን ነገር ለሌሎች ስንናገር ይሖዋ ይደሰታል
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች መናገር የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። መዝሙር 9:1ን እና 34:1ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተማርካቸው ነገሮች መካከል ለሌሎች መናገር የምትፈልገው የትኛውን ነው?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “አምላክ ልባችንን ስለሚያይ በየትኛውም መንገድ ብናመልከው ይቀበለናል።”
አንተ ምን ይመስልሃል?
ማጠቃለያ
ፈጣሪያችንን ማስደሰት ከፈለግን እሱን ብቻ ልናመልከው፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ልናወድሰውና የተማርነውን ነገር ለሌሎች ልንናገር ይገባል።
ክለሳ
አምላክን በትክክለኛው መንገድ ማምለክ የምንችለው እንዴት እንደሆነ የምንማረው ከየት ነው?
ይሖዋን ብቻ ማምለክ ያለብን ለምንድን ነው?
ከሌሎች ጋር አብረን ይሖዋን ማምለክ ያለብን ለምንድን ነው?
ምርምር አድርግ
‘የጣዖታት ባሪያ ከመሆን ተገላግያለሁ’ የሚል ርዕስ ባለው የሕይወት ታሪክ ላይ አንዲት ሴት ከጣዖት አምልኮ የተላቀቁት እንዴት እንደሆነ ተመልከት።
በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት የሚረዳህ ምንድን ነው?
አንድ ወጣት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይከብደው ነበር፤ ሆኖም እንዲህ በማድረጉ ምን ጥቅም አግኝቷል?
ብዙ ሰዎች መስቀል የክርስትና ምልክት እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ሆኖም መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም ተገቢ ነው?
“የይሖዋ ምሥክሮች መስቀልን ለአምልኮ የማይጠቀሙበት ለምንድን ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)
a እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች በሌሎች ምዕራፎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል።