“አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ”
ይሖዋ ነቢዩ ሳሙኤልን እንዲህ ብሎት ነበር:- “ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት ሰው ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።” (1 ሳሙኤል 16:7) መዝሙራዊው ዳዊትም በምሳሌያዊ ልብ ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጎበኘኸኝ፤ ፈተንኸኝ፣ ምንም አላገኘህብኝም።”—መዝሙር 17:3
አዎን፣ ይሖዋ ትክክለኛውን ማንነታችንን ለማወቅ ልባችንን ይመለከታል። (ምሳሌ 17:3) የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” የሚል ምክር የሰጠው አለምክንያት አይደለም። (ምሳሌ 4:23) ምሳሌያዊ ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? የምሳሌ መጽሐፍ አራተኛ ምዕራፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።
የአባትን ተግሣጽ ስማ
የምሳሌ መጽሐፍ አራተኛ ምዕራፍ የመክፈቻ ቃላት እንዲህ ይላሉ:- “እናንት ልጆች፣ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፣ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ፤ መልካም ትምህርትን እሰጣችኋለሁና፤ ሕጌን አትተዉ።”—ምሳሌ 4:1, 2
ወጣቶች አምላካዊ የሆኑ ወላጆቻቸው በተለይ ደግሞ አባት የሚሰጠውን ጠቃሚ ምክር እንዲያዳምጡ ተመክረዋል። አባት የቤተሰቡን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች እንዲያሟላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት ተጥሎበታል። (ዘዳግም 6:6, 7፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) አንድ ወጣት እንደዚህ ያለ መመሪያ ካላገኘ ወደ ጉልምስና ማደግ ምንኛ አዳጋች ይሆንበታል! በመሆኑም አንድ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ በአክብሮት መቀበል አይገባውም?
ይሁን እንጂ ምክር የሚሰጠው አባት ስለሌለው ልጅስ ምን ማለት ይቻላል? ለምሳሌ ያህል የአሥራ አንድ ዓመቱ ጄሰን ያለ አባት የቀረው ገና የአራት ዓመት ልጅ ሳለ ነው።a በሕይወቱ ውስጥ በጣም የሚረብሸው ምን እንደሆነ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ሲጠይቀው ጄሰን ወዲያው እንዲህ ሲል መልሷል:- “አባት ማጣቴ በጣም ይሰማኛል። ይህ ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ከመጠን በላይ እንዳዝንና እንድተክዝ ያደርገኛል።” ቢሆንም የወላጅ አመራር ያጡ ወጣቶች አጽናኝ ምክር የሚያገኙበት ሁኔታ ተዘጋጅቶላቸዋል። ጄሰንና እርሱን የመሰሉ ሌሎች ወጣቶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ወደሚገኙ ሽማግሌዎችና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጠጋ ብለው አባታዊ ምክር ማግኘት ይችላሉ።—ያዕቆብ 1:27
ሰሎሞን የራሱን ትምህርት በማስታወስ ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “እኔም አባቴን የምሰማ [“ጥሩ፣” NW ] ልጅ ነበርሁና፣ በእናቴም ዘንድ እወደድ ነበር።” (ምሳሌ 4:3) ንጉሡ አስተዳደጉን በተመለከተ ጥሩ ትዝታ እንደነበረው ግልጽ ነው። ወጣቱ ሰሎሞን አባታዊውን ምክር ከልብ የሚቀበል “ጥሩ ልጅ” ስለነበር ከአባቱ ከዳዊት ጋር ሞቅ ያለና የቀረበ ወዳጅነት መሥርቶ መሆን አለበት። ከዚህም በላይ ሰሎሞን በጣም ‘ተወዳጅ’ ልጅ ነበር። አንድ ልጅ እርስ በርስ በጣም በሚቀራረብና ከወላጆች ጋር ያለው የግንኙነት መስመር ክፍት በሆነበት ቤት ውስጥ ማደጉ ምንኛ ጠቃሚ ነው!
ጥበብንና ማስተዋልን አግኝ
ሰሎሞን የአባቱን ፍቅራዊ ምክር አስታውሶ ሲናገር እንዲህ አለ:- “ያስተምረኝም ነበር እንዲህም ይለኝ ነበር:- ልብህ ቃሌን ይቀበል፤ ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ። ጥበብን አግኝ፤ ማስተዋልን አግኝ፤ አትርሳም፣ ከአፌም ቃል ፈቀቅ አትበል። አትተዋት፣ ትደግፍህማለች፤ ውደዳት፣ ትጠብቅህማለች። ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ።”—ምሳሌ 4:4-7
ጥበብ “ዓይነተኛ ነገር” የሆነችው ለምንድን ነው? ጥበብ ማለት ጥሩ ውጤት በሚያመጣ መንገድ እውቀትንና ማስተዋልን በሥራ ላይ ማዋል ማለት ነው። እውቀት ማለት አንድን ነገር በመመርመርና በተሞክሮ ወይም በማንበብና በማጥናት ከእውነታዎች ጋር መተዋወቅ ወይም መላመድ ማለት ሲሆን ይህ ዓይነቱ እውቀት የጥበብ መሠረት ነው። ይሁን እንጂ እውቀታችንን በጥሩ መንገድ በሥራ የመተርጎም ችሎታው ከሌለን ዋጋ አይኖረውም። መጽሐፍ ቅዱስንና “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች ዘወትር ማንበብ ብቻ ሳይሆን የተማርናቸውን ነገሮች ተግባራዊ ለማድረግ መጣጣር አለብን።—ማቴዎስ 24:45
በተጨማሪም ማስተዋልን ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው። ማስተዋል ከሌለን እውነታዎቹ እርስ በርስ ያላቸውን ዝምድና በትክክል መገንዘብና የጉዳዩን ሁለንተናዊ ገጽታ ማግኘት እንዴት እንችላለን? ማስተዋል ከጎደለን ከነገሮች በስተጀርባ ያለውን ምክንያት በመረዳት እንዴት ጥልቅ ግንዛቤ ማግኘት እንችላለን? አዎን፣ እንዲህ እና እንዲያ ነው ብለን ትክክለኛ ወደሆነው መደምደሚያ ለመድረስ ማስተዋል ያስፈልገናል።—ዳንኤል 9:22, 23
ሰሎሞን አባቱ የነገረውን እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ [ጥበብን] ከፍ ከፍ አድርጋት፣ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ ብታቅፋትም ታከብርሃለች። ለራስህ የሞገስ አክሊልን ትሰጥሃለች፣ የተዋበ ዘውድንም ታበረክት[ል]ሃለች።” (ምሳሌ 4:8, 9) አምላካዊ ጥበብ የሚያቅፋትን ሰው ትጠብቀዋለች። ከዚህም በላይ ክብርን ታጎናጽፈዋለች እንዲሁም ውበትን ታላብሰዋለች። እንግዲያው ጥበብን ለማግኘት እንጣጣር።
“ተግሣጽን ያዝ”
የእስራኤል ንጉሥ አባቱ የሰጠውን መመሪያ መልሶ ሲያስተጋባ ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “ልጄ ሆይ፣ ስማ፣ ንግግሬንም ተቀበል፤ የሕይወትህም ዘመን ትበዛልሃለች። የጥበብን መንገድ አስተማርሁህ፤ በቀናች ጎዳና መራሁህ። በሄድህ ጊዜ እርምጃህ አይጠብብም፤ በሮጥህም ጊዜ አትሰናከልም። ተግሣጽን ያዝ፣ አትተውም፤ ጠብቀው፣ እርሱ ሕይወትህ ነውና።”—ምሳሌ 4:10-13
ለአባቱ ጥሩ ልጅ የነበረው ሰሎሞን ትምህርት እንዲያገኝና እንዲስተካከል የሚረዳውን ፍቅራዊ ተግሣጽ መቀበል ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ተገንዝቦ መሆን አለበት። ሚዛናዊ የሆነ ተግሣጽ ካላገኘን ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ለማደግ ወይም የአኗኗር ዘይቤያችንን ለማሻሻል እንዴት እንችላለን? ከስሕተታችን የማንማር ወይም የተሳሳተ አመለካከታችንን የማናርም ከሆነ እምብዛም መንፈሳዊ እድገት እንደማናደርግ የታወቀ ነው። ምክንያታዊ ተግሣጽ አምላካዊ ባሕሪያትን እንድናፈራና ‘በቀና ጎዳና እንድንጓዝ’ ይረዳናል።
ሌላው ዓይነት ተግሣጽ ደግሞ ‘ረጅም ዘመን እንድንኖር’ ያስችለናል። እንዴት? ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፣ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው።” (ሉቃስ 16:10) በትናንሽ ነገሮች ራሳችንን ከገሠጽን በሕይወታችን ላይ ለውጥ የሚያስከትሉ ከባድ ነገሮች ሲያጋጥሙን ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል አይሆንልንም? ለምሳሌ ያህል ‘ሴትን በፍትወት ስሜት ትኩር ብሎ ላለማየት’ ራስን መገሠጽን ከተማርን ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር እንዳንፈጽም ይጠብቀናል። (ማቴዎስ 5:28) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለሁለቱም ጾታዎች እንደሚሠራ የታወቀ ነው። መረን እንዳይለቅ ‘አእምሯችንን በቁጥጥር ሥር የምናደርግ ከሆነ’ በቃልም ሆነ በድርጊት ከባድ ኃጢአት ከመሥራት አደጋ ራሳችንን እንከላከላለን።—2 ቆሮንቶስ 10:5
እርግጥ ነው፣ ተግሣጽን መቀበል ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ሲሆን ነፃነታችንን የሚነፍግ ሊመስለንም ይችላል። (ዕብራውያን 12:11) ሆኖም ተግሣጽን ከተቀበልን እድገት ለማድረግ መንገዳችን የቀና እንደሚሆን ጠቢቡ ንጉሥ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ተገቢውን ስልጠና ያገኘ አንድ ሯጭ ሳይደናቀፍ ወይም ጉዳት ሳያገኘው ፍጥነቱን ጠብቆ ወደፊት መግፋት እንደሚችል ሁሉ ተግሣጽ መቀበላችን ሳናወላውልና ሳንሰነካከል የጀመርነውን የሕይወት ሩጫ እንድንቀጥል ያስችለናል። እርግጥ ነው መንገዳችንን ስንመርጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል።
‘ከክፉዎች መንገድ’ ራቅ
ሰሎሞን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧል:- “በኀጥኣን መንገድ አትግባ፣ በክፉ ሰዎችም ጎዳና አትሂድ። ከእርስዋ ራቅ፣ አትሂድባትም፤ ፈቀቅ በል ተዋትም። ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፣ ካላሰናከሉም እንቅልፋቸው ይወገዳልና። የኃጢአትን እንጀራ ይበላሉና፣ የግፍንም ወይን ጠጅ ይጠጣሉና።”—ምሳሌ 4:14-17
ሰሎሞን ከመንገዳቸው እንድንርቅ ያሳሰበን ክፉ ሰዎች ወራዳ ተግባርን መተዳደሪያቸው አድርገውታል። ለእነርሱ ክፉ ነገር መሥራት እንደ ምግብና መጠጥ ነው። የዓመፅ ድርጊት ካልፈጸሙ በስተቀር እንቅልፍ በዓይናቸው አይዞርም። ባሕርያቸው የተበላሸ ነው! በእርግጥ ከእነርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ሳናቋርጥ ልባችንን መጠበቅ እንችላለን? ይህ ዓለም በሚያቀርባቸው በአብዛኛዎቹ መዝናኛዎች ላይ ለሚታዩት የዓመፅ ድርጊቶች ራሳችንን በማጋለጥ ‘በክፉ ሰዎች ጎዳና መጓዝ’ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! በአንድ በኩል ከአንጀት የመራራትን ባሕርይ ለማፍራት ጥረት ማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ የርኅራኄን ስሜት የሚያደነዝዙ በቴሌቪዥን ወይም በፊልም የሚተላለፉ የክፋት ድርጊቶችን አእምሮን መመገብ የሚጣጣም ነገር አይደለም።
በብርሃን መመላለስህን ቀጥል
አሁንም ከመንገድ ጋር ማመሳሰሉን በመቀጠል ሰሎሞን እንዲህ ሲል ያሳስባል:- “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።” (ምሳሌ 4:18) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ያጠኑትን ተግባራዊ ለማድረግ መጣር ሌሊት ገና ጨለማ እያለ ጉዞ ከመጀመር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የሌሊቱ ጨለማ ለዓይን ለቀቅ እንዳደረገ ወዲያው ሁሉንም ነገር ማየት አይቻልም። ሆኖም ቀስ በቀስ ጎህ እየቀደደ ሲመጣ በአካባቢያችን ያሉትን ነገሮች ይበልጥ መለየት እንጀምራለን። በመጨረሻም ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ስትወጣ እያንዳንዱ ነገር ወለል ብሎ ይታየናል። አዎን፣ ቅዱሳን ጽሑፎችን በትዕግሥትና በትጋት ማጥናታችንን ስንቀጥል እውነት ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነልን ይሄዳል። ልባችንን ከተሳሳቱ ሐሳቦች መጠበቅ የምንፈልግ ከሆነ በመንፈሳዊ ልንመግበው ይገባል።
እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያላቸው ትርጉም ደረጃ በደረጃ ግልጽ እየሆነ ይመጣል። ትንቢቶች ግልጽ የሚሆኑልን የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ብርሃን ሲፈነጥቅባቸውና በዓለም ውስጥ በሚከናወኑት ነገሮች ወይም በአምላክ ሕዝቦች ላይ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ነው። ትዕግሥት አጥተን ስለ አፈጻጸማቸው የራሳችንን ግምታዊ ሐሳብ ከመሰንዘር ይልቅ ‘ብርሃኑ ደማቅ ሆኖ’ እስኪበራ ድረስ መጠበቅ ያስፈልገናል።
በብርሃን ለመመላለስ አሻፈረኝ በማለት የአምላክን አመራር አንቀበልም ስለሚሉ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ሰሎሞን “የኀጥአን መንገድ እንደ ጨለማ ነው፣ እንዴት እንደሚሰናከሉም አያውቁም” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 4:19) ክፉ ሰዎች ምን እንዳደናቀፈው ሳያውቅ በጨለማ የሚደናበርን ሰው ይመስላሉ። ከአምላክ የራቁ ሰዎች በክፉ ሥራቸው እየበለጸጉ ያሉ ቢመስሉ እንኳ የሚያገኙት ስኬት ጊዜያዊ ብቻ ነው። መዝሙራዊው እንደዚህ የመሰሉትን ሰዎች አስመልክቶ እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፣ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው።”—መዝሙር 73:18
በትጋት መቀጠል
የእስራኤል ንጉሥ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ልጄ ሆይ፣ ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሌም ጆሮህን አዘንብል። ከዓይንህ አታርቃት፣ በልብህም ውስጥ ጠብቃት። ለሚያገኙአት ሕይወት፣ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና። አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።”—ምሳሌ 4:20-23
ልብን ስለመጠበቅ የተሰጠው ምክር ጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት የራሱን የሰሎሞንን ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። በወጣትነቱ ለአባቱ ‘ጥሩ ልጅ’ እንደነበረ ሁሉ እስከ ጉልምስና ዕድሜው ድረስ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ቆይቷል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ሰሎሞንም ሲሸመግል ሚስቶቹ ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት፣ የአባቱ የዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም እንደነበረ የሰሎሞን ልብ እንዲሁ አልነበረም” ሲል ይናገራል። (1 ነገሥት 11:4) የአምላክ ቃል የያዛቸውን ማሳሰቢያዎች ‘በልባችን ውስጥ ጠብቀን’ ለማቆየት የማያቋርጥ ንቃት ካላሳየን ደህና ነው የተባለው ልብ እንኳን ሊታለል ይችላል። (ኤርምያስ 17:9) የአምላክ ቃል የያዛቸውን ማሳሰቢያዎች ከልባችን አለማራቅ ማለትም ‘በልባችን ውስጥ’ ማስቀመጥ አለብን። እነዚህ ማሳሰቢያዎች በምሳሌ መጽሐፍ 4ኛው ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙትን ይጨምራሉ።
የልብህን ሁኔታ መርምር
ምሳሌያዊ ልባችንን በመጠበቅ ረገድ ተሳክቶልናልን? ውስጣዊ ማንነታችንን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ኢየሱስ ክርስቶስ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 12:34) አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና።” (ማቴዎስ 15:19, 20) አዎን፣ በአንደበታችን የምንናገረውና በድርጊት የምንገልጸው ስለ ውስጣዊው ልባችን በጣም ብዙ ይናገራል።
ሰሎሞን “የአፍህን ጠማማነት ከአንተ አውጣ፣ ሐሰተኞቹን ከንፈሮችም ከአንተ አርቅ። ዓይኖችህ አቅንተው ይዩ፣ ሽፋሽፍቶችህም በቀጥታ ይመልከቱ። የእግርህን መንገድ አቅና፣ አካሄድህም ሁሉ ይጽና። ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤ እግርህንም ከክፉ መልስ” ሲል አጥብቆ መምከሩ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 4:24-27
ሰሎሞን የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ግምት ውስጥ በማስገባት አነጋገራችንንና ድርጊታችንን መመርመር አለብን። ልባችንን በመጠበቅ አምላክን ለማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ ጠማማ አነጋገርን ማስወገድና የተንኮል ድርጊት ከመፈጸም መቆጠብ አለብን። (ምሳሌ 3:32) በመሆኑም አነጋገራችንና ድርጊታችን ስለ እኛ ምን እንደሚገልጽ ለማወቅ ሁኔታውን በጸሎት ልናስብበት ይገባል። ከዚያም ያገኘነውን ማንኛውንም ድክመት ለማስተካከል እንዲረዳን ይሖዋን በጸሎት እንጠይቅ።—መዝሙር 139:23, 24
ከሁሉም በላይ ‘ዓይኖቻችን ፊት ለፊት ይመልከቱ።’ ለሰማያዊው አባታችን የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ለማቅረብ ባወጣነው ግብ ላይ ይተከሉ። (ቆላስይስ 3:23) በቀና ጎዳና ለመጓዝ የበኩልህን ጥረት በምታደርግበት ጊዜ ይሖዋ ‘በመንገድህ ሁሉ’ ስኬትን እንዲሰጥህ እንዲሁም ‘አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ’ የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመታዘዝ በምታደርገው ጥረት አብዝቶ እንዲባርክህ እንመኛለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እውነተኛ ስሙ አይደለም።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የዓመፅ ድርጊት ከሚንጸባረቅባቸው የመዝናኛ ዓይነቶች ትርቃለህ?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች የሚሰጡትን ምክር ስማ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተግሣጽ ፍጥነትህን አይቀንሰውም
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የማያቋርጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ይኑርህ