በእርግጥ ስርቆት ነውን?
አቢዮደን በናይጄርያ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ የምግብ ቤቱ ተቆጣጣሪ ሆኖ ይሠራ ነበር። አንድ ቀን ማታ የምግብ አዳራሹን ሲቆላልፍ ከ1,827 የአሜሪካ ዶላር (ከ9,135 ብር) ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ የያዘ ቦርሳ ያገኛል። ያለ ምንም መዘግየት ገንዘቡን ለሚመለከተው ክፍል አስረከበ፤ በኋላም የገንዘቡ ባለቤት በሆቴሉ አርፈው የነበሩ አንዲት ሴት መሆናቸው ታወቀ። የሆቴሉ አስተዳደር ለአቢዮደን ከፍተኛ የደረጃ እድገት በመስጠት ሾመው። እንዲሁም “የዓመቱ ኮከብ ሠራተኛ” ተብሎ ተሸለመ። የገንዘቡ ባለቤትም ወሮታውን ከፈሉት።
ኳሊቲ የተባለው የአገሪቱ የዜና መጽሔት አቢዮደንን “ደጉ ሣምራዊ” ብሎ በመጥራት ታሪኩን በመጽሔቱ ላይ አወጣ። አቢዮደን ገንዘቡ አጓጉቶት እንደሆነ በኳሊቲ መጽሔት ሪፖርተር ተጠይቆ ሲመልስ እንዲህ አለ፦ ‘እኔ የይሖዋ ምስክር ነኝ። ስለዚህ የኔ ያልሆነ ነገር ካገኘሁ ለባለቤቱ እመልስለታለሁ።’
በዚያ አገር የነበሩ ብዙ ሰዎች በአቢዮዲን ታማኝነት ተገረሙ። የይሖዋ ምስክሮች የሆኑት የአቢዮደን ጓደኞች ግን ባደረገው ነገር ተደሰቱ እንጂ አልተገረሙም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ባሏቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎች የታወቁ ናቸው። ከሥነ ምግባር ደረጃዎቻቸው ውስጥ አንዱ ሐቀኝነት ነው፤ እንዲያውም የእውነተኛ ክርስትና ደንብ ወይም በጣም አስፈላጊ ክፍል ነው።
አንዳንድ ሁኔታዎች ግን ታማኝነትን ማጉደል በሆነውና ባልሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት አንዳናስተውል ይከልሉብናል። እስቲ ይህን ሁኔታ ተመልከቱት። በምዕራብ አፍሪካ አንድ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤ ውስጥ ገንዘብ ያዥና ሒሳብ ተቆጣጣሪ የሆነ ፌስተስ የሚባል ሰው ገንዘብ በጣም አስፈለገው።a ባለቤቱ ከባድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋታል። የመረመሯት ሐኪሞች ቀዶ ሕክምናው በቶሎ መደረግ አለበት አሉ። ሆስፒታሉ ደግሞ ለሕክምናው ከሚያስፈልገው ዋጋ ግማሹ በቅድሚያ እንዲከፍለው ጠየቀ።
ፌስተስ ገንዘብ የለውም። ገንዘብ እንዲያበድሩት ብዙ ሰዎችን ቢጠይቅም የሚያበድረው አጣ። ከዚያ በእጁ ያለው የጉባኤ ገንዘብ ትዝ አለውና ‘ባለቤቴን ላድናት ስችል እንድትሞት ብተዋት ትክክል ይሆናል? ለምን ከጉባኤው ገንዘብ “አልበደርም?” ያበደርኳቸው ሰዎች ገንዘቤን ሲሰጡኝ እመልሰዋለሁ’ ብሎ አሰበ።
ፌስተስ የራሱ ያልሆነውን ገንዘብ ወስዶ ለሆስፒታሉ ከፈለ። ያቀረበው ምክንያት ትክክል ነበርን? ካጋጠመው አጣዳፊ ሁኔታ አንፃር ያደረገው ነገር ተገቢ ነውን?
ገንዘቡ የማን ነው?
እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ፌስተስ የወሰደው ገንዘብ ከየት እንደመጣና ለምን ዓላማ እንደሚውል እስቲ አጠር አድርገን አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት። ገንዘቡ የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ ለማራመድ የሚፈልጉ የጉባኤው አባላት በፈቃደኝነት ያደረጉት መዋጮ ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ገንዘቡ ደመወዝ ሆኖ የሚከፈል አይደለም። ምክንያቱም ማንም ሰው በጉባኤው ውስጥ ለሠራው ሥራ ገንዘብ አይከፈለውም። ከዚህ ይልቅ ገንዘቡ የመሰብሰቢያ ቦታ ወይም የመንግሥት አዳራሽ ለማግኘትና አዳራሹን በጥሩ ሁኔታ ለመያዝ የሚውል ነው። ይህም ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ሀብታም ድኻ ሳይባል ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ለመቅሰም የሚችሉበት ጥሩና ምቹ የመሰብሰቢያ ቦታ እንዲኖር ያስችላል።
ገንዘቡ የማን ነው? የጉባኤው የጋራ ገንዘብ ነው። ገንዘብ ምን ላይ መዋል እንዳለበት ማንኛውም የጉባኤው አባል በግለሰብ ደረጃ መወሰን አይችልም። ምንም እንኳን የሽማግሌዎች አካል የጉባኤውን የተለመዱ ወጪዎች ለመሸፈን ገንዘብ ሊከፍል ቢችልም ለአንድ የተለየ ነገር ገንዘብ መክፈል በሚያስፈልግበት ጊዜ ግን ሽማግሌዎች ጉዳዩን ለጉባኤው አቅርበው የጉባኤውን ድጋፍ ይጠይቃሉ።
ብድር ነው ወይስ ስርቆት?
ፌስተስ ገንዘቡን በቶሎ ለመመለስ ስላቀደ ያደረገውን ነገር እንደ ብድር ቆጥሮት ነበር። ይሁን እንጂ ዌብስተርስ ኒው ዲክሽነሪ ኦቭ ሲኖነምስ “አብዛኛውን ጊዜ በስውር ወይም ባለ ንብረቱ ሳያውቅ ወይም ሳይፈቅድ የሌላን ሰው ንብረት መውሰድ ወይም ማስወገድ” የሚለውን ሐሳብ ለመግለጽ በሌሎች ቃላት ይጠቀማል። መዝገበ ቃላቱ የተጠቀመባቸው ቃላት “ስርቆት” እና “ሌባ” ናቸው። ፌስተስ ማንም ሳይፈቅድለት ወይም ሥልጣን ሳይሰጠው የጉባኤውን ገንዘብ ወሰደ። አዎን፣ ሰረቀ፤ ስለዚህም ሌባ ሆነ።
በርግጥ ለስርቆት የሚያነሳሱ ነገሮች የአስከፊነታቸው መጠን የተለያየ ነው። ይህንን ከአስቆሮቱ ይሁዳ ምሳሌ መመልከት እንችላለን። እርሱ የኢየሱስንና የሌሎቹን ታማኝ ሐዋርያት ገንዘብ እንዲይዝ ተሰጥቶት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[ይሁዳ] ሌባ . . . ነበረ . . . ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ነበር።” (ዮሐንስ 12:6) ይሁዳ መጥፎ ልብ ስለነበረውና በጣም ስግብግብ ስለነበረ እየባሰበት ሄደ። ውሎ አድሮ የአምላክን ልጅ በ30 ብር እስከመሸጥ ደረሰ።—ማቴዎስ 26:14–16
ፌስተስ ግን ይህን ድርጊት የፈጸመው ለታመመችው ሚስቱ ስለተጨነቀ ነበር። ታዲያ ይህ ማለት ጥፋት የለበትም ማለት ነው እንዴ? በጭራሽ! በሌላ አጣዳፊ ሁኔታ ወቅት የሚፈጸምን ስርቆት አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተመልከት፦ “ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም፤ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፣ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል።” (ምሳሌ 6:30, 31) በሌላ አነጋገር ሌባው ከተያዘ ሕጉ የሚበይነውን ቅጣት በሙሉ ይቀበላል። በሙሴ ሕግ መሠረት አንድ ሌባ የሰረቀውን ነገር መክፈል ነበረበት። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስርቆትን በማበረታታት ወይም ለሌባው ይቅርታ በማድረግ ፈንታ አጣዳፊ ሁኔታ ቢያጋጥምም እንኳን ስርቆት ክስረትን፣ መዋረድንና ከዚህ ይበልጥ ደግሞ የአምላክን ሞገስ ማጣትን እንደሚያስከትል በመግለጽ ያስጠነቅቃል።
የይሖዋ ምስክሮች እንደመሆናቸው መጠን እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ በተለይም በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ክርስቲያኖች ‘ነቀፋ የሌለባቸውና’ ለምሳሌነት የሚበቁ መሆን አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:10) ፌስተስ አገኛለሁ ያለውን ገንዘብ ሳያገኝ ስለቀረ የወሰደውን ገንዘብ መመለስ አልቻለም። ያደረገው ነገር ታወቀ። ምን ደረሰበት? ንስሐ የማይገባ ሌባ ቢሆን ኖሮ ከንጹሑ የክርስቲያን ጉባኤ ይወገድ ነበር። (1 ጴጥሮስ 4:15) እሱ ግን ከልቡ ተጸጽቶ ንስሐ ገባ። በዚህ ምክንያት በጉባኤ ውስጥ ሊቆይ ቻለ፤ የነበሩትን የአገልግሎት መብቶች ግን አጣ።
በአምላክ መታመን
ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋን አገለግላለሁ እያለ የሚሰርቅ ሰው በአምላክ ስምና በስሙ በሚጠሩት ሕዝቦቹ ላይ ነቀፋ ሊያመጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና።”—ሮሜ 2:21, 24
በጥንት ጊዜ ይኖር የነበረው አጉር የተባለ ጠቢብ ሰው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ተናግሮ ነበር። በጸሎቱ ውስጥ ‘ድሀ እንዳይሆን . . . በአምላኩም ስም በሐሰት እንዳይምል’ ጠይቋል። (ምሳሌ 30:9) ጠቢቡ ድኽነት ጻድቅ የነበረ ሰው እንኳን እንዲሰርቅ የሚፈትኑ ሁኔታዎች ሊያመጣበት እንደሚችል መግለጹን ልብ በል። አዎን፣ አንድ ክርስቲያን ከባድ ችግር በሚያጥመው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ባለው ችሎታ ላይ ያለውን እምነት ሊፈትንበት ይችላል።
ሆኖም ታማኝ የይሖዋ ምስክሮች ድሀ የሆኑትም ጭምር አምላክ ‘ከልባቸው ለሚፈልጉት ዋጋ እንደሚሰጥ’ ያምናሉ። (ዕብራውያን 11:6) ይሖዋ ታማኝ የሚሆኑለትን ሰዎች የሚያስፈልጋቸው እንዲሟላላቸው በማድረግ እንደሚሸልማቸው ያውቃሉ። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ይህንን ግልጽ አድርጎታል። እንዲህ አለ፦ “ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ . . . ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:31–33
አምላክ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላሉት ችግረኞች የሚያስፈልጋቸውን የሚሰጣቸው እንዴት ነው? በብዙ መንገዶች ይሰጣቸዋል። አንዱ መንገድ በመሰል አማኞች በኩል ነው። የአምላክ ሕዝቦች እርስ በርሳቸው በእውነተኛ ፍቅር ይዋደዳሉ። “ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፣ ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? ልጆቼ ሆይ፣ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አክብደው ይመለከቱታል።—1 ዮሐንስ 3:17, 18
በዓለም ዙሪያ ከ73,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ከአራት ሚልዮን ተኩል በላይ የሆኑ የይሖዋ ምስክሮች በአምላክ የጽድቅ ደረጃዎች መሠረት እርሱን ለማገልገል በትጋት ይጥራሉ። አምላክ ለእርሱ ታማኝ ሆነው በጎኑ የሚቆሙለትን በፍጹም እንደማይተዋቸው ያውቃሉ። ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ ሁሉ ከንጉሥ ዳዊት ጋር በመስማማት ጮክ ብለው “ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” ይላሉ።—መዝሙር 37:25
ለመስረቅ ከመፈተንና ምናልባትም የአምላክን ሞገስ ለዘላለም ከማጣት ይልቅ እነዚህን ቃላት በመንፈስ አነሳሽነት ባስጻፈው አምላክ ላይ እምነት ማድረግ ምን ያህል የተሻለ ነው!—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሙ ተለውጧል።