“ጥበብን የሚያገኝ ሰው ደስተኛ ነው”
ገጣሚ፣ አርኪቴክትና ንጉሥ ነበር። ከ200 ሚልዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ገቢ ስለነበረው በምድር ላይ ከነገሠ ከማንኛውም ንጉሥ ይበልጥ ባለጠጋ ነበር። በጥበቡም የታወቀ ሰው ነበር። ልትጠይቀው የመጣች አንዲት ንግሥት በጣም ከመደነቋ የተነሳ “እነሆም፣ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል” በማለት ተናግራለች። (1 ነገሥት 10:4-9) እንዲህ የተባለለት የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ነበር።
ሰሎሞን ሀብትም ጥበብም ነበረው። በመሆኑም ከሁለቱ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትኛው እንደሆነ እንዲያውቅ አስችሎታል። “ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW ] ነው፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ከቀይ ዕንቁም ትከብራለች፣ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም” በማለት ጽፏል።—ምሳሌ 3:13-15
ይሁን እንጂ ጥበብ ከየት ሊገኝ ይችላል? ከሀብት ይበልጥ ዋጋ አላት የሚባለው ለምንድን ነው? ምን ማራኪ ገጽታዎችስ አሏት? ሰሎሞን የጻፈውና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ 8ኛ ምዕራፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች ግሩም መልስ ይሰጣል። በዚህ ምሳሌ ውስጥ ጥበብ መናገርና ማድረግ እንደምትችል ሆና ተገልጻለች። ጥበብ ማራኪ ገጽታዎችዋን እንዲሁም የምትሰጠውን ጥቅም ራስዋ ትናገራለች።
“ትጮሃለች”
ምሳሌ ምዕራፍ 8 “በውኑ ጥበብ አትጮኽምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን አትሰጥምን?” የሚሉ መልስ የማያሻቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ይጀምራል።a አዎን፣ ጥበብና ማስተዋል ያለማቋረጥ ይጮኻሉ፤ ሆኖም የሚያሰሙት ድምፅ ጨለምለም ባሉ ቦታዎች ላይ አድብታ ብቻውን ሲንቀዋለል ለምታገኘው ተሞክሮ የሌለው ወጣት ሸንጋይ ቃላቶችን ሹክ ከምትል ሥነ ምግባር የጎደላት ሴት የተለየ ነው። (ምሳሌ 7:12) “በኮረብታ ላይ በመንገድ አጠገብ በጎዳና መካከል ትቆማለች። በበሩ አጠገብ በከተማይቱም መግቢያ፣ በደጁ መግቢያ ትጮኻለች።” (ምሳሌ 8:1-3) ጥበብ የምታሰማው ድምፅ በየአደባባዩ ማለትም በበሩ አጠገብ፣ በጎዳና መካከል እንዲሁም በከተማው መግቢያ ጎልቶና ጥርት ብሎ ይሰማል። ሰዎች ያለ አንዳች ችግር ሰምተው ምላሽ መስጠት ይችላሉ።
በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈውና የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን አምላካዊ ጥበብ የፈለገ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊያገኘው እንደሚችል ማን ሊክድ ይችላል? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ “በታሪክ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙዎች ዘንድ የሚነበብ መጽሐፍ የለም” ብሏል። አክሎም “የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በሰፊው የተሠራጨ መጽሐፍ አይገኝም። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ብዙ ጊዜና በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመ መጽሐፍ የለም” ብሏል። ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከ2, 100 በሚበልጡ ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች የተተረጎመ ሲሆን ከዓለም ሕዝቦች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቢያንስ የአምላክን ቃል የተወሰነ ክፍል በገዛ ቋንቋቸው ለማንበብ ይችላሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን መልእክት በየሥፍራው ለሕዝብ በማወጅ ላይ ናቸው። የአምላክን መንግሥት ምሥራች 235 በሚያክሉ አገሮች ውስጥ በትጋት ይሰብካሉ እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለሰዎች ያስተምራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱት ሁለቱ መጽሔቶቻቸው ማለትም በ140 ቋንቋዎች የሚታተመው መጠበቂያ ግንብ እና በ83 ቋንቋዎች የሚታተመው ንቁ! መጽሔት እያንዳንዳቸው ከ20 ሚልዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ይሰራጫሉ። በእርግጥም፣ ጥበብ በየአደባባዩ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ትጮሃለች!
“ድምፄም ወደ ሰዎች ልጆች ነው”
በሰው የተመሰለችው ጥበብ እንዲህ በማለት ንግግሯን ትጀምራለች:- “እናንተ ሰዎች፣ እናንተን እጠራለሁ፣ ድምፄም ወደ ሰዎች ልጆች ነው። እናንተ አላዋቂዎች፣ ብልሃትን አስተውሉ፤ እናንተም ሰነፎች፣ ጥበብን በልባችሁ ያዙ።”—ምሳሌ 8:4, 5
ጥበብ የምታሰማው ጥሪ ዓለም አቀፍ ነው። ለመላው የሰው ዘር ግብዣ ታቀርባለች። አላዋቂዎች እንኳ ብልሃት ወይም ጥንቃቄ እንዲማሩ፣ ሞኞችም ማስተዋልን እንዲያገኙ ተጋብዘዋል። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ እንደሆነ ስለሚያምኑ የያዘውን የጥበብ ቃል መርምሮ እንዲያገኝ የሚያገኙትን ሰው ሁሉ ያበረታታሉ።
“አፌ እውነትን ይናገራል”
ጥበብ እንዲህ ስትል ጥሪዋን ማቅረቧን ትቀጥላለች:- “የከበረች ነገርን እናገራለሁና ስሙ፤ ከንፈሮቼም ቅን ነገርን ለመናገር ይከፈታሉ። አፌ እውነትን ይናገራልና፣ ከንፈሮቼም ክፋትን ይጸየፋሉ። የአፌ ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤ ጠማማ ዘወርዋራም አይደሉም።” አዎን፣ ከጥበብ የሚገኙት ትምህርቶች በጣም ግሩም፣ ትክክል፣ እውነተኛና ጽድቅ ናቸው። ጠማማ ወይም ዘወርዋራ ነገር የለባቸውም። “እነርሱ በሚያስተውሉ ዘንድ የቀኑ ናቸው፣ እውቀትንም ካገኙአት ሰዎች ጋር የተስማሙ ናቸው።”—ምሳሌ 8:6-9
ጥበብ “ተግሣጼን እንጂ ብርን አትቀበሉ፣ ከምዝምዝ ወርቅም ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ” በማለት መማጸኗ የተገባ ነው። ‘ጥበብ ከቀይ ዕንቁ ስለምትበልጥና የከበረ ነገር ሁሉ ስለማይተካከላት’ እንዲህ ያለ ምልጃ ማቅረቧ ምክንያታዊ ነው። (ምሳሌ 8:10, 11) ግን ለምን? ጥበብን ከሀብት ይልቅ ውድ ያደረጋት ምንድን ነው?
“ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል”
ጥበብ ለሚያደምጧት የምትሰጣቸው ስጦታዎች ከወርቅ፣ ከብር ወይም ከከበረ ዕንቁ ይልቅ የከበሩ ናቸው። ጥበብ እነዚህ ስጦታዎች ምን እንደሆኑ ስትገልጽ “እኔ ጥበብ በብልሃት ተቀምጫለሁ፣ እውቀትንም ጥንቃቄንም [“የማሰብ ችሎታንም፣” NW ] አግኝቻለሁ። እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን ይጠላል፤ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ” ብላለች።—ምሳሌ 8:12, 13
ጥበብ እሷን ላገኘ ሰው ብልሃትንና የማሰብ ችሎታን ትሰጣለች። “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት” ስለሆነ አምላካዊ ጥበብ ያለው ሰው አምላክን የሚፈራና በጥልቅ የሚያከብር ይሆናል። (ምሳሌ 9:10) ስለሆነም ይሖዋ የሚጠላውን ይጠላል። ትዕቢት፣ እብሪት፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ባሕርይ አይታይበትም እንዲሁም ብልሹ አነጋገር አይሰማበትም። ክፉ ለሆነው ነገር ያለው ጥላቻ ሥልጣኑን ያለ አግባብ ከመጠቀም ይጠብቀዋል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ወንድሞች እንዲሁም የቤተሰብ ራሶች ጥበብን ለማግኘት መጣራቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ጥበብ እንደሚከተለው በማለት ትቀጥላለች:- “ምክርና መልካም [“ተግባራዊ፣” NW ] ጥበብ የእኔ ነው፤ ማስተዋል እኔ ነኝ፣ ብርታትም አለኝ። ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፣ ሹማምቶችም የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ። አለቆች በእኔ ያዝዛሉ፣ ክቡራንም የምድር ፈራጆችም ሁሉ።” (ምሳሌ 8:14-16) ጥበብ የምታፈራው ፍሬ ማስተዋልንና ብርታትን የሚጨምር ሲሆን እነዚህ ባሕርያት ደግሞ ለገዥዎች፣ ለታላላቅ ባለ ሥልጣናትና ለሹማምንት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ጥበብ በሥልጣን ላይ ለተቀመጡና ለሌሎች ምክር ለሚሰጡ ሰዎች የግድ ታስፈልጋለች።
እውነተኛ ጥበብ ለሁሉም ሰው የቀረበች ብትሆንም ሁሉም ሰው ያገኛታል ማለት ግን አይደለም። አንዳንዶች ጥበብ ደጃፋቸው ድረስ መጥታላቸው እንኳ አይቀበሏትም። ጥበብ “እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፣ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል” በማለት ትናገራለች። (ምሳሌ 8:17) ጥበብን የሚያገኟት ከልብ የሚሹአት ብቻ ናቸው።
የጥበብ መንገድ ቀናና ጽድቅ ነው። ፈልጎ የሚያገኛትን ሰው ትክሳለች። ጥበብ “ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፣ ብዙ ሀብትና ጽድቅም። ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፣ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር። እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፣ በፍርድም ጎዳና መካከል፣ ለሚወድዱኝ ርስት አወርሳቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም እሞላ ዘንድ” ትላለች።—ምሳሌ 8:18-21
ጥበብ እንደ ጥንቃቄ፣ የማሰብ ችሎታ፣ ትህትና፣ ማስተዋል፣ ተግባራዊ ጥበብ ከመሳሰሉት ግሩም ባሕርያት በተጨማሪ ሀብትንና ክብርንም ትሰጣለች። ጠቢብ ሰው በትክክለኛ መንገድ ሀብት ማግኘት የሚችል ሲሆን በመንፈሳዊም ይበለጽጋል። (3 ዮሐንስ 2) በተጨማሪም ጥበብ ክብር ታጎናጽፈዋለች። ከዚህም በላይ ባገኛቸው ነገሮች ምክንያት እርካታን የሚያገኝ ሲሆን በአምላክም ዘንድ የአእምሮ ሰላምና ንጹሕ ህሊና ይኖረዋል። አዎን፣ ጥበብን የሚያገኝ ሰው ደስተኛ ነው። በእርግጥም፣ ጥበብ የምታፈራው ፍሬ ከወርቅ እና ከተመረጠ ብር የተሻለ ነው።
የተከፈለው መሥዋዕትነት ተከፍሎ ሀብታም መሆን የሚል አመለካከት በሰፈነበት ፍቅረ ንዋይ የተጠናወተው ዓለም ውስጥ ለምንኖረው ለእኛ ይህ ምክር ምንኛ ወቅታዊ ነው! ጥበብ ምን ያህል ዋጋዋ የላቀ መሆኑን መዘንጋት ወይም ሀብት ለማግኘት ብለን ትክክለኛ ያልሆነ መንገድ መከተል የለብንም። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችንንና የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች የመሳሰሉ ጥበብ የሚገኝባቸውን ዝግጅቶች ሃብት ለማግኘት ብለን ችላ አንበላቸው።—ማቴዎስ 24:45-47
“ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ”
በምሳሌ መጽሐፍ 8ኛ ምዕራፍ ውስጥ ጥበብ የተመሰለችው አንድን የማይጨበጥ የማይዳሰስ ባሕርይ ለማስረዳት ብቻ አይደለም። ትልቅ ቦታ ያለው የይሖዋ ፍጥረትም በጥበብ ተመስሏል። ጥበብ እንዲህ በማለት ትቀጥላለች:- “እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፣ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ። ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ። ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፣ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ። ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፣ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፣ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጠር የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር።”—ምሳሌ 8:22-26
እዚህ ላይ በጥበብ ስለተመሰለው ነገር የተሰጠው መግለጫ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ “ቃል” ከተነገረው ጋር ምንኛ የሚስማማ ነው! ሐዋርያው ዮሐንስ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ሲል ጽፏል። (ዮሐንስ 1:1) በጥበብ የተመሰለው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት ያሳለፈውን ሕይወት ያመለክታል።b
ኢየሱስ ክርስቶስ “የሚታዩትና የማይታዩትም . . . በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው።” (ቆላስይስ 1:15, 16) በሰው የተመሰለችው ጥበብ እንደሚከተለው በማለት ትቀጥላለች:- “ [ይሖዋ] ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፣ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፣ ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፣ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፣ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፣ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፣ የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፤ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፤ ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ።” (ምሳሌ 8:27-31) የይሖዋ የበኩር ልጅ አቻ ከሌለው የሰማይና የምድር ፈጣሪ ጋር በትጋት እየሠራ ከአባቱ ጎን ይገኛል። ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው ሲፈጥር ልጁ ዋና ሠራተኛ ሆኖ በሥራው ተካፍሏል። (ዘፍጥረት 1:26) የአምላክ ልጅ በሰው ልጆች በጣም መደሰቱና እነሱን ማፍቀሩ ምንም አያስደንቅም!
“የሚሰማኝ ሰው ደስተኛ ነው”
በጥበብ የተመሰለው የአምላክ ልጅም እንዲህ ይላል:- “አሁንም ልጆቼ ሆይ፣ ስሙኝ፤ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው። ትምህርቴን ስሙ፣ ጠቢባንም ሁኑ፣ ቸል አትበሉትም። የሚሰማኝ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW ] ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፣ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ። እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና፣ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና። እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጎዳል፤ የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።”—ምሳሌ 8:32-36
ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ጥበብ ዋነኛ መግለጫ ነው። “የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነው።” (ቆላስይስ 2:3) እንግዲያው በጥሞና እናዳምጠው እንዲሁም ፈለጉን በቅርብ እንከተል። (1 ጴጥሮስ 2:21) “መዳንም በሌላ በማንም” ስለሌለ እሱን አልቀበልም ማለት በገዛ ሕይወታችን ላይ ጥፋትን መጋበዝና ሞትን መውደድ ማለት ይሆንብናል። (ሥራ 4:12) እውነት ነው፣ ኢየሱስን አምላክ እኛን ለማዳን ያደረገው ዝግጅት እንደሆነ አድርገን እንቀበለው። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ‘ሕይወትንና የይሖዋን ሞገስ ማግኘት’ የሚያመጣውን ደስታ እንቀምሳለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ጥበብን” ለመግለጽ የገባው የዕብራይስጥ ቃል አንስታይ ጾታን የሚያመለክት ስለሆነ አንዳንድ ትርጉሞች ጥበብን በሚጠቅሱበት ጊዜ የአንስታይ ጾታ ተውላጠ ስም ይጠቀማሉ።
b “ጥበብን” ለመግለጽ የገባው የዕብራይስጥ ቃል ሁልጊዜ አንስታይ ጾታን የሚያመለክት መሆኑ ጥበብን የአምላክን ልጅ ለማመልከት ከመጠቀም ጋር የሚጋጭ አይደለም። “አምላክ ፍቅር ነው” በሚለው ጥቅስ ውስጥ “ፍቅር” ለማለት የገባው የግሪክኛ ቃልም እንዲሁ በአንስታይ ጾታ ተገልጿል። (1 ዮሐንስ 4:8) ቢሆንም አምላክን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥበብ በኃላፊነት ቦታ ላይ ላሉ ሰዎች የግድ ታስፈልጋለች
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥበብ የሚገኝባቸውን ዝግጅቶች ችላ አትበል