ደስተኞችና የተደራጃችሁ ሁኑ
የተደራጁ መሆን ነገሮችን በሚገባ ለመሥራት ያስችላል። ውጤታማ መሆን ጊዜንና ሀብትን በተሻለ ሁኔታ እንድንጠቀምበት ያስችለናል። (ገላትያ 6:16፤ ፊልጵስዩስ 3:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2) ሆኖም ሕይወት ማለት መደራጀትና ውጤታማነት ብቻ አይደለም። በመንፈስ አነሳሽነት የተናገረው መዝሙራዊ “ይሖዋ አምላኩ የሆነ ሕዝብ ደስተኛ ነው!” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 144:15 አዓት) የሚፈትነው ሁኔታ በምንሠራው ሁሉ ደስተኛና የተደራጀን ለመሆን የመቻላችን ጉዳይ ነው።
የተደራጀና ደስተኛ
በጥሩ ሁኔታ በመደራጀት ረገድ ታላቁ ምሳሌያችን ይሖዋ አምላክ ነው። ከእያንዳንዷ ሴል አንስቶ ውስብስብ አሠራር እስካላቸው ሕያዋን ፍጥረታት፣ በጣም ትንሽ ከሆኑት አቶሞች አንስቶ እስከ ግዙፎቹ ጋላክሲዎች ድረስ ያሉት ፍጥረታቱ በሙሉ ሥርዓትንና ከፍተኛ የሆነ ትክክለኛነትን ያሳያሉ። ጽንፈ ዓለማዊ ሕጎቹ በልበ ሙሉነት ለሕይወታችን ዕቅድ ለማውጣት ያስችሉናል። ጠዋት ጠዋት ፀሐይ እንደምትወጣና ከክረምት ቀጥሎ በጋ እንደሚመጣ እናውቃለን። — ዘፍጥረት 8:22፤ ኢሳይያስ 40:26
ነገር ግን ይሖዋ የሥርዓት አምላክ ብቻ አይደለም። “ደስተኛ አምላክም” ጭምር ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት፤ 1 ቆሮንቶስ 14:33) ደስተኛነቱ በፍጥረቶቹ ላይ ይታያል። የሚቦርቁ ሙጭሊቶች፣ ጀንበር ስትጠልቅ የሚታየው ግርማ፣ የመብላት ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ምግቦች፣ መንፈስን የሚቀሰቅስ ሙዚቃ፣ የሚያነቃቃ ሥራ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ነገሮች ይሖዋ በሕይወት እንድንደሰት አድርጎ እንደፈጠረን ያሳያሉ። ሕጎቹ የሚያሰለቹ እገዳዎች ሳይሆኑ ደስታችንን ለመጠበቅ የሚረዱ ናቸው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱን ምሳሌ ይቀዳል። እርሱ “ብፁዕና [ደስተኛና አዓት] ብቻውን የሆነ ገዥ” ነው። ልክ አባቱ እንደሚያደርገው ያደርጋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:15፤ ዮሐንስ 5:19) በአባቱ የፍጥረት ሥራ ወቅት አብሮት ሲሠራ ውጤታማ የሆነ “ዋና ሠራተኛ” ብቻ አልነበረም፤ በሚሠራውም ሥራ ይደሰት ነበር። ‘[በይሖዋም] ፊት ሁልጊዜ ደስ ይለው ነበር፣ ደስታውም በምድሩ ተድላውም በሰው ልጆች ነበር።’ — ምሳሌ 8:30, 31
በምናደርገው ሁሉ ይህንኑ የሚመስል ደግነት፣ ደስታና ተድላ ለሰው ልጆች ለማሳየት እንፈልጋለን። አንዳንድ ጊዜ ግን ውጤታማ ለመሆን ጥረት ስናደርግ “[በአምላክ] መንፈስ . . . በሥርዓት መመላለስ” የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ማፍራትን እንደሚጨምር እንረሳለን። (ገላትያ 5:22–25) ስለዚህ የራሳችን ሥራ በምንሠራበት ጊዜና የሌሎችን ሥራ ስንመራ የተደራጀን እንዲሁም ደስተኞች ለመሆን የምንችለው እንዴት ነው? ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው።
በራሳችሁ ላይ አትጨክኑ
በምሳሌ 11:17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ጥሩ ምክር ልብ በሉ። በመንፈስ የተመሰጠው ጸሐፊ በመጀመሪያ “ቸር [ፍቅራዊ ደግነት ያለው አዓት] ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል” ሲል ይነግረናል። በመቀጠልም በተቃራኒው “ጨካኝ ግን ሥጋውን ይጎዳል” አለ። ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን “ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፣ ጨካኝ ግን በራሱ ላይ ጉዳት ያመጣል” በሚል መንገድ ያስቀምጠዋል።
ሳይታወቀን በራሳችን ላይ ጨካኞች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በቅን ልቦና ተነሣሥተን የምንሠራ ግን ጨርሶ ያልተደራጀን በመሆን ነው። ይህስ ምን ውጤት ያስከትላል? አንድ ባለሞያ እንዲህ አሉ:- “ነገሮችን መርሳት፣ በስህተት ፋይል የተደረጉ ሰነዶች፣ በደንብ ያልተረዳናቸው ትዕዛዞች፣ በትክክል ያልተመዘገበ የስልክ ጥሪ — እነዚህ ብል ጨርቅን እንደሚበላ ሁሉ ውጤታማነትን ገዝግዘው ይመጣል ብለን ያሰብነውን ጥሩ ውጤት በማበላሸት ለውድቀት የሚዳርጉ ትንንሽ ነገሮች ናቸው።” — Teach Yourself Personal Efficiency.
ይህም “በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው” ካለው በመንፈስ ተመስጦ ከጻፈው ጸሐፊ ጋር ይስማማል። (ምሳሌ 18:9) አዎን፤ በሚገባ ያልተደራጁና ውጤታማ ሥራ የማይሠሩ ሰዎች በራሳቸውና በሌሎች ላይ መከራና ጥፋትን ያመጣሉ። በዚህ ምክንያት ብዙውን ጊዜ ሌሎች ሰዎች እነርሱን ይርቋቸዋል። ታካች በመሆናቸው በራሳቸው ላይ መከራ ያመጣሉ።
በሕይወት ያለ ውሻ ወይስ የሞተ አንበሳ?
በጣም ከፍተኛ የሆኑ የአቋም ደረጃዎችን በማውጣትም በራሳችን ላይ ልንጨክን እንችላለን። ከላይ ውጤታማነትን በተመለከተ የጻፉት ጸሐፊ “ሙሉ በሙሉ ሊደረስበት የማይቻል ፍጹም የሆነ የአቋም ደረጃ” ላይ ለመድረስ ዓላማ ልናደርግ እንችላለን ብለዋል። በውጤቱም “የኋላ ኋላ ያሰብነው ነገር ሳይሳካልን በመቅረቱ በከፍተኛ ሐዘን ላይ እንወድቃለን” ብለዋል። እንከን የማይወጣለት ለመሆን የሚፈልግ ሰው በሚገባ የተደራጀና ውጤታማ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በፍጹም እውነተኛ ደስታ አያገኝም። ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የሚያገኘው ነገር ብስጭት ብቻ ነው።
እንከን የማይወጣልን ለመሆን ወደመፈለግ አዘንብለን ከሆነ “ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ብናስታውስ መልካም ነው። (መክብብ 9:4) እንከን የማይወጣልን ካልሆንን ብለን እውን ሊሆን የማይችል ጥረት በማድረግ ቃል በቃል ራሳችንን አንገድል ይሆናል፤ ነገር ግን ብዙ በመሥራት በከፍተኛ ሁኔታ ራሳችንን ልንጎዳ እንችላለን። አንድ የታመነ ምንጭ እንደሚለው ይህ “በአካላዊ፣ በስሜታዊ፣ በመንፈሳዊ፣ በአእምሯዊ ሁኔታችን ላይ የኃይል መሟጠጥን እንዲሁም ከሰው ጋር ባለን ግንኙነት የትዕግሥት ማለቅን” ያስከትልብናል። (Job Stress and Burnout) ሊደረስባቸው የማይችሉ ግቦች ላይ ለመድረስ በመጣጣር ራሳችንን ማድከም በእርግጥም በራሳችን ላይ መጨከን ነው፤ ደስታችንንም ማሳጣቱ የማይቀር ነው።
ለራሳችሁ መልካም አድርጉ
‘ፍቅራዊ ደግነት ያለው ሰው ለራሱ መልካም እንደሚያደርግ’ አስታውሱ። (ምሳሌ 11:17) ደስተኛው አምላክ ይሖዋ አቅማችን ውስን መሆኑን እንደሚያውቅ በአእምሮአችን ይዘን እውን ሊሆኑ የሚችሉና ምክንያታዊ ግቦችን የምናወጣ ከሆነ ለራሳችን መልካም እናደርጋለን። (መዝሙር 103:8–14) እኛም ራሳችን አቅማችን ውስን መሆኑን ብናስታውስና ግዴታዎቻችንን በሚገባ ለመወጣት እንደ ችሎታችን መጠን “በትጋት” ብንጥር ደስተኞች ልንሆን እንችላለን። — ዕብራውያን 4:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:15፤ 2 ጴጥሮስ 1:10
እርግጥ ምንጊዜም ቢሆን ወደ ሌላው ጎን ማለትም ለራሳችን በጣም ደግ ወደ መሆን የማዘንበል አደጋም አለ። እንዲያውም ቆራጥ እርምጃ በሚያስፈልግበት ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ለራስህ ራራ” [አዓት ] ሲል ለሰጠው አስተያየት ኢየሱስ የመለሰውን መልስ አትርሱ። የጴጥሮስ አስተሳሰብ በጣም አደገኛ ስለነበረ ኢየሱስ እንዲህ አለው:- “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል።” (ማቴዎስ 16:22, 23) ለራሳችን መልካም ማድረግ አለብን ሲባል የግድ የለሽነትና ለራሳችን ፍላጎት የመገዛት ዝንባሌ ያለን መሆን አለብን ማለት አይደለም። ይህም ደስታችንን ሁሉ ሊያጠፋብን ይችላል። ምክንያታውያን እንጂ ግትር አቋም ያለን ለመሆን አንፈልግም። — ፊልጵስዩስ 4:5
ከሌሎች ጋር የሚያስደስት ግንኙነት ይኑረን
በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ጻፎችና ፈሪሳውያን ከሁሉም ይበልጥ ውጤታማና የተደራጁ የሆኑ መስሏቸው ይሆናል። የአምልኮ መንገዳቸውን በተመለከተ ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዝ ትንንሽና አላስፈላጊ በሆኑ ደንቦች የተተበተበ ነበር። እንደ ሁኔታው ለውጥ ለማድረግ አይቻልም፤ እያንዳንዱ አይሁዳዊ ጥቃቅኖቹን ጉዳዮች ጨምሮ ሕጉን ሙሉ በሙሉ መታዘዝ ይፈለግበት ነበር። . . . ሃይማኖት ንግድ ወደ መሆን እስከሚደርስና ሕይወትም ሊታገሱት የማይቻል ሸክም እስከሚሆን ድረስ ሕግ ነክ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች እየበዙ ሄዱ። ሰዎች በደመ ነፍስ በመመራት ሥነ ምግባርን የሚከተሉ ሮቦቶች እስከመሆን ድረስ ዝቅ ተደረጉ። የሕሊና ድምፅ ታፍኖ መለኮታዊው ቃል ዋጋውን እንዲያጣና ኅልቆ መሣፍርት ከሌላቸው ሕጎች ክምር በታች ተዳፍኖ እንዲቀር ተደረገ።”
በዚህ ምክንያት ኢየሱስ እነርሱን ማውገዙ አያስደንቅም። “ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፣ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም” አለ። (ማቴዎስ 23:4) አፍቃሪ እረኞች ትንንሽና አላስፈላጊ የሆነ የሕጎችና የደንቦች ክምር በመንጋው ላይ ከመጫን ይቆጠባሉ። የኢየሱስ ክርስቶስን የደግነትና አእምሮን የሚያድስ ምሳሌ በመከተል የአምላክን መንጋ በመልካም ሁኔታ ይይዛሉ። — ማቴዎስ 11:28–30፤ ፊልጵስዩስ 2:1–5
ድርጅታዊ ኃላፊነቶች እየበዙባቸው ቢሄዱም ለሌሎች አሳቢ የሆኑ ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸው ሰብዓዊ ፍጡሮች ያውም አምላክ የሚወዳቸው ሰዎች መሆናቸውን ፈጽሞ አይዘነጉም። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3, 7፤ 1 ዮሐንስ 4:8–10) የመንጋው እረኞች፣ ጠባቂዎችና ተከላካዮች በመሆን የሚጫወቱትን ተቀዳሚ ሚና እስኪረሱ ድረስ በድርጅታዊ ጉዳዮች ወይም ሂደቶች አይያዙም። — ምሳሌ 3:3፤ 19:22፤ 21:21፤ ኢሳይያስ 32:1, 2፤ ኤርምያስ 23:3, 4
ለምሳሌ ያህል ከሚገባው በላይ በፕሮግራሞችና አኀዝ ነክ በሆኑ ጉዳዮች መጠመድ ለሰዎች አሳቢ እንዳትሆን ሊያግድህ ይችላል። የመጣው ቢመጣ መነሻና መድረሻውን የሚያመለክተውን ፕሮግራም በጥብቅ መከተል ተቀዳሚ ተግባሩ እንደሆነ አድርጎ የሚያስብ አንድን የአውቶቡስ ሹፌር እንውሰድ። ከመነሻው እስከ መድረሻው ልክ በተመደበው ሰዓት ለመድረስ ባለው ፍላጎት ስሜቱ ተውጧል። ተሳፋሪዎችን የሚመለከታቸው ወደ ኋላ እንደሚጉትቱት ዕንቅፋቶች አድርጎ ነው። ቀርፋፎችና ሥርዓት የሌላቸው እንደሆኑ እንዲሁም ሁልጊዜ አውቶቡስ ማቆሚያው ላይ የሚደርሱት ልክ አውቶቡሱ ሊነሳ ሲል እንደሆነ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ዋነኛው የሥራው ዓላማ የተሳፋፊዎቹን ፍላጎት ማርካት መሆኑን ዘንግቶ ለሥራ ቅልጥፍናው እንቅፋት እንደሚፈጥሩበት አድርጎ በመመልከት ሳያሳፍራቸው ይሄዳል።
ለእያንዳንዱ ግለሰብ የምታስቡ ሁኑ
ርኅራኄ የጎደለው የሥራ ቅልጥፍና በአብዛኛው የግለሰቦችን ፍላጎት ችላ ይላል። ደካሞችና የሥራ ቅልጥፍና የሌላቸው ሰዎች እንደ ሸክም ተደርገው ይቆጠራሉ። ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ መጥፎ ውጤት ሊከተል ይችላል። ለምሳሌ በጥንቷ የግሪክ ከተማ በስፓርታ የሚወለዱ ደካማና ታማሚ ልጆች እንዲሞቱ ተብሎ ይጣላሉ። ጠንካራና የሥራ ቅልጥፍና ያላትን አገራቸውን ለመከላከል የሚችሉ ጠንካራና ቀልጣፋ ወታደሮች ለመሆን አይችሉም። ፈላስፋው በርትራንድ ራስል እንዲህ አሉ:- “አንድ ልጅ በሚወለድበት ጊዜ አባትየው ልጁን ይመረምሩት ዘንድ ወደ ቤተሰቡ ሽማግሌዎች ይወስደዋል። ልጁ ጤነኛ ከሆነ እንዲያሳድገው ለአባትየው ይመለስለታል፤ ካልሆነ ግን ጥልቅ ወደሆነ የውኃ ጉድጓድ ይወረወራል።” — History of Western Philosophy.
ይህ ጨካኝ መንግሥት ተለይቶ የሚታወቀው ከደስታ ጋር ሳይሆን ከግትርነትና ከረገጣ ጋር ተያይዞ ነው። (ከመክብብ 8:9 ጋር አወዳድር።) ስፓርታውያን ባለ ሥልጣኖች በቅልጥፍና አስፈላጊነት ለማመን ጥሩ ምክንያት ነበራቸው፤ ሆኖም አድራጎታቸው ምንም ዓይነት ርኅራኄ ወይም ደግነት የሌለበት ነበር። የነሱ መንገድ የአምላክ መንገድ አልነበረም። (መዝሙር 41:1፤ ምሳሌ 14:21) በአንጻሩ ግን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ የበላይ ተመልካቾች ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች በአምላክ ዓይን ውድ እንደሆኑ ስለሚያስታውሱ ከእያንዳንዳቸው ጋር የሚያስደስት ግንኙነት አላቸው። ጤነኛ የሆኑትን 99ኙን ብቻ ሳይሆን ደካማ የሆነውን ወይም የመንፈስ ጭንቀት ያለበትን አንዱን በግ ያስባሉ። — ማቴዎስ 18:12–14፤ ሥራ 20:28፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14, 15፤ 1 ጴጥሮስ 5:7
ከመንጋው አትራቁ
ሽማግሌዎች በእነርሱ ሥር ካለው መንጋ አይርቁም። የንግድ ዘዴዎችን የሚያጠኑ ዘመናዊ ተመራማሪዎች ግን ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት አንድ ሥራ አስኪያጅ ወይም ተቆጣጣሪ ከሚቆጣጠራቸው ሰዎች ራቅ ማለት ይኖርበታል የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ። አንድ የአየር ኃይል መኰንን በእሳቸው ሥር የሚሠሩትን ሰዎች በጣም ሲቀርቧቸው እንዲሁም በጣም ሲርቋቸው ያጋጠማቸውን የተለያየ ውጤት አንድ ተመራማሪ እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ:- “ከመኮንኖቹ ጋር በጣም የቀረበ ግንኙነት ሲኖራቸው መኮንኖቹ የተዝናኑ በመሆን ስለ ሥራ ቅልጥፍናቸው እምብዛም የሚጨነቁ አይመስሉም። ከእነርሱ ጋር ብዙም የማይቀራረቡና የስልጣን ቦታቸውን የሚጠብቁ ሲሆን ግን የበታች መኮንኖቹ አንድ ነገር ተፈጥሮ ይሆናል ብለው ተጨነቁ። . . . ስለዚህ ይህንን ጭንቀታቸውን ለሥራቸው የበለጥ ትኩረት ወደ መስጠት አዞሩት። በውጤቱም በወታደራዊ ተቋሙ ውስጥ በግልጽ ሊታይ የሚችል የሥራ ቅልጥፍና ተገኘ።” — Understanding Organizations.
ይሁን እንጂ የክርስቲያን ጉባኤ ወታደራዊ ተቋም አይደለም። የሌሎችን ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠሩ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል ይጥራሉ። እርሱ ዘወትር ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይቀራረብ ነበር። (ማቴዎስ 12:49, 50፤ ዮሐንስ 13:34, 35) ይበልጥ ቀልጣፎች እንዲሆኑ ሲል አስጨንቋቸው አያውቅም። በእርሱና በተከታዮቹ መካከል በሁለቱም ወገን የልበ ሙሉነትና የመተማመን ጠንካራ ማሠሪያ እንዲኖር አድርጓል። ደቀ መዛሙርቱ ከልብ የመነጨ ፍቅራዊ ትስስር ይታይባቸው ነበር። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8) እንዲህ ዓይነት መቀራረብ ካለ ሙሉ በሙሉ በአምላክ ፍቅር የሚንቀሳቀስ ደስተኛ የሆነ መንጋ ይኖራል። መንጋው የሚደርሱትን መመሪያዎች ያለማንጎራጎር እየፈጸመ ለአምላክ በሚያቀርበው የፈቃደኝነት አገልግሎት ይተጋል። — ከዘጸአት 35:21 ጋር አወዳድር።
ብዙ ጥቅሶች እንደ ደስታና ወንድሞችን ማፍቀር የመሰሉ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ያጎላሉ። (ማቴዎስ 5:3–12፤ 1 ቆሮንቶስ 13:1–13) ከዚህ ጋር ሲወዳደር የቅልጥፍናን አስፈላጊነት የሚያጎሉ ጥቅሶች አነስተኛ ናቸው። በጥሩ ሁኔታ መደራጀት አስፈላጊ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ሁልጊዜ የተደራጁ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የመዝሙር ጸሐፊዎች የአምላክ አገልጋዮች ደስተኞች እንደሆኑ አድርገው ምን ያህል በተደጋጋሚ እንደገለጿቸው አስቡ። ስለ ይሖዋ ሕግጋት፣ ማሳሰቢያዎችና ደንቦች ብዙ የሚናገረው መዝሙር 119 እንዲህ ሲል ይጀምራል:- “በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ፣ በእግዚአብሔርም [በይሖዋም አዓት] ሕግ የሚሄዱ ምስጉኖች [ደስተኞች አዓት] ናቸው። ምስክሩን የሚፈልጉ፣ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች [ደስተኞች አዓት] ናቸው።” (መዝሙር 119:1, 2) የተደራጀህና ደስተኛ መሆን ፈታኝ ነው። ይህንን ፈተና ታልፈው ይሆን?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታላላቆቹን የሰማይ ክበቦች የሚወክለው አርሚላሪ ስፌር የተባለ የድሮ መሣሪያ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አፍቃሪ እረኛ የሆነው ይሖዋ የሥርዓት አምላክ ብቻ ሳይሆን የደስታም አምላክ ነው
[ምንጭ]
Garo Nalbandian