“አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል”
የአምላክ ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው መመሪያ “ከወርቅ ይልቅ የከበረ፣ እጅግ ከጠራ ወርቅም የተሻለ ነው።” (መዝሙር 19:7-10) ለምን? ምክንያቱም “የጠቢብ [የይሖዋ] ትምህርት የሕይወት ምንጭ ናት፤ ሰውን በሞት ወጥመድ እንዳይያዝ ታደርገዋለች።” (ምሳሌ 13:14) ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን ምክር በተግባር ማዋላችን የተሻለ ሕይወት እንድንኖር የሚያስችለን ከመሆኑም ሌላ አደጋ ላይ ከሚጥሉ ወጥመዶች እንድንርቅ ይረዳናል። ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙትን እውቀት ለማግኘት መጣራችንና ከተማርነው ነገር ጋር ተስማምተን መኖራችን በጣም አስፈላጊ ነው!
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ምሳሌ 13:15-25 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው የተሻለ ሕይወትና ረጅም ዕድሜ ማግኘት እንድንችል በእውቀት እንድንመላለስ የሚረዳ ምክር ሰጥቷል።a እጥር ምጥን ያሉ ምሳሌዎች በመናገር በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ እንድንሆን፣ አገልግሎታችንን በታማኝነት እንድናከናውን፣ ለተግሣጽ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረንና ባልንጀሮቻችንን በጥበብ እንድንመርጥ የአምላክ ቃል እንዴት ሊረዳን እንደሚችል ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ለልጆቻችን ውርስ መተውም ሆነ ፍቅራዊ ተግሣጽ መስጠት አርቆ አሳቢነት መሆኑን ተናግሯል።
መልካም ማስተዋል ሞገስ ያስገኛል
ሰሎሞን “መልካም ማስተዋል ሞገስን ታስገኛለች፤ የከዳተኞች መንገድ ግን አስቸጋሪ ነው” ብሏል። (ምሳሌ 13:15) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “መልካም ማስተዋል” ወይም ጥሩ የመረዳት ችሎታ ተብሎ የተተረጎመውን ሐረግ ለማመልከት የተሠራበት የመጀመሪያው ቃል “አርቆ አሳቢነት፣ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታና ብስለት የተሞላበት አስተሳሰብ ማንጸባረቅን ያሳያል” ሲል ተናግሯል። እንዲህ ዓይነት ባሕርያት ያሉት ሰው በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ መሆን አያስቸግረውም።
ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን የሆነውንና ከጌታው ጠፍቶ የሄደውን አናሲሞስን ወደ ጌታው መልሶ ሲልከው የእምነት ባልንጀራው የሆነው ፊልሞናን እንዴት በማስተዋል እንደያዘው ተመልከት። ጳውሎስ ወደ ፊልሞና ቤት ቢሄድ ኖሮ ይቀበለው በነበረው መንገድ አናሲሞስን በደግነት እንዲቀበለው አሳስቦታል። እንዲያውም አናሲሞስ በፊልሞና ላይ ዕዳ ካለበት ጳውሎስ እዳውን ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል። እርግጥ ጳውሎስ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርግ ፊልሞናን ማዘዝ ይችል ነበር። ሐዋርያው ግን ጉዳዩን በዘዴና በፍቅር ለመያዝ መርጧል። ጳውሎስ በዚህ መንገድ ከፊልሞና በጎ ምላሽ እንደሚያገኝ ብቻ ሳይሆን ከጠየቀው በላይ ለማድረግ እንደሚነሳሳም እምነት ነበረው። እኛም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አይኖርብንም?—ፊልሞና 8-21
በሌላ በኩል ደግሞ የከዳተኛ መንገድ አስቸጋሪ ወይም “ሸካራ” ነው። (የ1954 ትርጉም) እንዴት? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንዳሉት እዚህ ላይ የገባው ቃል ትርጉም “ደንዳና ወይም ግትር ማለት ሲሆን ክፉ ሰዎች ያላቸውን ርኅራኄ የጎደለው ባሕርይ ያመለክታል። . . . ሌሎች የሚሰጡትን ጥበብ የተሞላበት ምክር የማይሰማና ቸልተኛ በመሆን በክፋት መንገዱ ለመሄድ የቆረጠ ሰው የጥፋት ጎዳናን መርጧል።”
በመቀጠልም ሰሎሞን “አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል፤ ተላላ ግን ሞኝነቱን ይገልጣል” ብሏል። (ምሳሌ 13:16) ማስተዋል ከእውቀት ጋር የተያያዘ ባሕርይ ሲሆን አንድ ነገር ከማድረጉ በፊት ነገሮችን በጥንቃቄ የሚያመዛዝን ልባም ሰው የሚያንጸባርቀው ባሕርይ ነው። አስተዋይ ሰው ተገቢ ያልሆነ ነቀፋ ብሎም ስድብ ሲሰነዘርበት ከንፈሩን ይገታል። የመንፈስ ፍሬዎችን በማንጸባረቅ ቁጣውን መቆጣጠር እንዲችል አምላክ እንዲረዳው ይጸልያል። (ገላትያ 5:22, 23) ይህ አስተዋይ ሰው ያናደደው ግለሰብ ወይም ሁኔታ ስሜቱን እንዲቆጣጠረው አይፈቅድም። እንዲያውም ራሱን የሚቆጣጠር ከመሆኑም ሌላ ነቀፋ ሲሰነዘርበት ወዲያውኑ ቱግ ብሎ ጥል ውስጥ እንደሚገባ ሰው ላለመሆን ይጠነቀቃል።
ከዚህ በተጨማሪ አስተዋይ ሰው ውሳኔ የሚያደርገው በእውቀት ላይ ተመሥርቶ ነው። በጥበብ የሚወሰድ እርምጃ በግምት ወይም በስሜት የሚደረግ አሊያም ብዙዎች ያደረጉትን በማድረግ የሚገኝ አለመሆኑን ያውቃል። በመሆኑም ያጋጠመውን ሁኔታ ጊዜ ወስዶ ይመረምራል። ከጉዳዩ ጋር ዝምድና ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ያሰባስባል እንዲሁም ያሉትን አማራጮች ለማወቅ ይጥራል። ከዚያም ቅዱሳን ጽሑፎችን በመመርመር ከጉዳዩ ጋር ዝምድና ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች ወይም መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማወቅ ይጥራል። እንዲህ ዓይነት ሰው ቀና በሆነ ጎዳና ላይ መጓዙን ይቀጥላል።—ምሳሌ 3:5, 6
‘ታማኝ መልእክተኛ ፈውስ ያመጣል’
የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ከአምላክ የተቀበልነውን መልእክት የማወጅ አደራ ተሰጥቶናል። ቀጥሎ የተጠቀሰው ምሳሌ የተሰጠንን ተልእኮ በታማኝነት እንድንወጣ ይረዳናል። “ክፉ መልእክተኛ መከራ ውስጥ ይገባል፤ ታማኝ መልእክተኛ ግን ፈውስን ያመጣል” ይላል።—ምሳሌ 13:17
ጥቅሱ ትኩረት የሚያደርገው በመልእክተኛው ባሕርያት ላይ ነው። መልእክት አድራሹ በክፋት መልእክቱን ቢያዛባ ወይም ቢቀይርስ? እንዲህ በማድረጉ አይቀጣም? የነቢዩ ኤልሳዕ አገልጋይ የነበረው ግያዝ በስግብግብነት ለሶርያ ጦር አዛዥ ለንዕማን የውሸት መልእክት ባደረሰ ጊዜ የተፈጸመውን ሁኔታ ተመልከት። ንዕማንን የለቀቀው የሥጋ ደዌ በሽታ ወደ ግያዝ ተላልፏል። (2 ነገሥት 5:20-27) መልእክተኛው ታማኝነቱን ቢያጓድልና ከነጭራሹ መልእክቱን ማወጁን ቢያቆምስ? መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱን ከመንገዱ እንዲመለስ ባታደርገው፣ ያ ክፉ ሰው በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ስለ ደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ” ይላል።—ሕዝቅኤል 33:8
በሌላ በኩል ታማኝ መልእክተኛ ለራሱም ሆነ መልእክቱን ለሚያዳምጡት ሰዎች ፈውስ ነው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ሲል አሳስቦታል፦ “ለሕይወትህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፤ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንና የሚሰሙህንም ታድናለህና።” (1 ጢሞቴዎስ 4:16) የመንግሥቱን ምስራች በታማኝነት ማወጅ የሚያስገኘውን ፈውስ አስብ። ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ውስጣዊ ስሜት የሚነካ ከመሆኑም በተጨማሪ ነፃ ወደሚያወጣው እውነት ይመራቸዋል። (ዮሐንስ 8:32) ሰዎች ለመልእክቱ ጆሯቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም እንኳ አንድ ታማኝ መልእክተኛ ‘ራሱን ያድናል።’ (ሕዝቅኤል 33:9) እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልእኮ ለመፈጸም ቸልተኞች አንሁን። (1 ቆሮንቶስ 9:16) እንዲሁም ‘ቃሉን ለመስበክ’ ምንጊዜም ጠንቃቆች እንሁን፤ ሰዎች እንዲቀበሉን ብለን መልእክቱን አለሳልሰን ወይም ቀባብተን ማቅረብ የለብንም።—2 ጢሞቴዎስ 4:2
“ዕርምትን የሚቀበል . . . ይከበራል”
አንድ አስተዋይ ሰው ጠቃሚ ምክር ሲሰጠው አልቀበልም ማለት ይኖርበታል? ምሳሌ 13:18 እንዲህ ይላል፦ “ተግሣጽን የሚንቅ ወደ ድኽነትና ኀፍረት ይሄዳል፤ ዕርምትን የሚቀበል ሁሉ ግን ይከበራል።” ምክር የተሰጠን ሳንጠይቅ ቢሆን እንኳ በአመስጋኝነት መቀበላችን ጥበብ ነው። ምክር እንደሚያስፈልገን ባልተገነዘብንበት ወቅት የሚሰጠን ተገቢ የሆነ ምክር በጣም ሊጠቅመን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱን ምክር መከተላችን ከሐዘንና አስከፊ ከሆኑ ሁኔታዎች ይጠብቀናል። ምክሩን ችላ የምንል ከሆነ ለኅፍረት እንዳረጋለን።
ጥሩ ነገር ሠርተን ስንመሰገን እንነቃቃለን እንዲሁም እንበረታታለን። ይሁን እንጂ ዕርምት ሊሰጠን እንደሚችል መጠበቅና ሲሰጠንም መቀበል ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፋቸውን ሁለት ደብዳቤዎች ተመልከት። ለታማኝነቱ ያመሰገነው ቢሆንም እንኳ ደብዳቤዎቹ ለጢሞቴዎስ ብዙ ምክር ይዘዋል። ጳውሎስ ይህን ወጣት የበላይ ተመልካች እምነትንና ጥሩ ህሊናን አጥብቆ ስለመያዝ፣ በጉባኤ ውስጥ ካሉ ከሌሎች ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት፣ ለአምላክ የማደርንና ኑሮዬ ይበቃኛል የማለትን ባሕርያት ስለማዳበር፣ ሌሎችን ስለማስተማር፣ ክህደትን ስለመዋጋትና አገልግሎቱን ስለማከናወን በነፃነት መክሮታል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣት ክርስቲያኖች ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ምክር መጠየቅና የሚሰጣቸውንም ምክር በደስታ መቀበል ይኖርባቸዋል።
‘ከጠቢባን ጋር መሄድ’
ጠቢቡ ንጉሥ “ምኞት ስትፈጸም ነፍስን ደስ ታሰኛለች፤ ተላሎች ግን ከክፋት መራቅን ይጸየፋሉ” ብሏል። (ምሳሌ 13:19) የዚህን ምሳሌ ትርጉም በተመለከተ አንድ ማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ውጥኑ ሲሳካለት ወይም ምኞቱ ሲደርስለት ከፍተኛ የእርካታ ስሜት ይሰማዋል . . . አንድ ሰው ያሰበውን ነገር ማድረጉ ከፍተኛ ደስታ ስለሚያስገኝለት ሞኞች ከክፋት መራቅን በጣም ይጸየፋሉ። ምኞታቸው ሊሳካ የሚችለው በክፉ መንገዶች ብቻ ነው። ክፋትን ከተዉ ደግሞ ፍላጎታቸውን በማሳካት የሚያገኙት ደስታ ሊቀርባቸው ነው።” ተገቢ የሆኑ ምኞቶች ማዳበራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ባልንጀሮቻችን በአስተሳሰባችን ላይ እንዲሁም በምንወዳቸውና በምንጠላቸው ነገሮች ረገድ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራሉ! ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጊዜ የማይሽረው ሐቅ ተናግሯል፦ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጉዳት ያገኘዋል።” (ምሳሌ 13:20) አዎን፣ በመዝናኛም ሆነ በኢንተርኔት እንዲሁም በምናነባቸው ጽሑፎች አማካኝነት የምንወዳጃቸው ሰዎች አሁንም ሆነ ወደፊት በማንነታችን ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ። ባልንጀሮቻችንን በጥበብ መምረጣችን በጣም አስፈላጊ ነው!
‘ውርስ መተው’
የእስራኤል ንጉሥ “መጥፎ ዕድል ኀጢአተኛን ይከታተላል፤ ብልጽግና ግን የጻድቃን ዋጋ ነው” በማለት ገልጿል። (ምሳሌ 13:21) ይሖዋ ለጻድቃን ስለሚያስብ ጽድቅን መከታተል ወሮታ ያስገኛል። (መዝሙር 37:25) ይሁን እንጂ “ጊዜና አጋጣሚ” ሁላችንንም እንደሚገናኘን መዘንጋት የለብንም። (መክብብ 9:11 NW) ለድንገተኛ ሁኔታዎች አስቀድመን ለመዘጋጀት ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖራል?
ሰሎሞን “ደግ ሰው ለልጅ ልጆቹ ውርስ ትቶ ያልፋል” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 13:22ሀ) ወላጆች ልጆቻቸው ስለ ይሖዋ እንዲማሩና ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርቱ በመርዳት እጅግ ጠቃሚ የሆነ ውርስ ይተዉላቸዋል! ከዚህ በተጨማሪ አንድ ወላጅ በድንገት ልሞት እችላለሁ ብሎ በማሰብ አቅሙ የሚፈቅድለት ከሆነ ቤተሰቡ የገንዘብ ችግር እንዳይገጥመው ዝግጅት ማድረጉ አስተዋይነት አይሆንም? በብዙ አገሮች ውስጥ የቤተሰብ ራሶች ኢንሹራንስ ሊገቡ፣ የኑዛዜ ሠነድ ሊያዘጋጁ እንዲሁም ገንዘብ ሊያጠራቅሙ ይችላሉ።
ክፉ ሰው ስለሚተወው ውርስ ምን ማለት ይቻላል? ሰሎሞን በመቀጠል “የኀጢአተኞች ሀብት ግን ለጻድቃን ይከማቻል” ብሏል። (ምሳሌ 13:22ለ) በአሁኑ ጊዜ ሊገኝ ከሚችል ጥቅም በተጨማሪ ይሖዋ “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ለመፍጠር የገባውን ቃል ሲፈጽም ይህ እውነት መሆኑ ይረጋገጣል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በዚያን ጊዜ ክፉዎች ከምድር ገጽ ተጠራርገው ሲጠፉ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ።”—መዝሙር 37:11
አንድ አስተዋይ ሰው ያለው ሀብት ጥቂት ቢሆንም እንኳ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በጥንቃቄ ነው። ምሳሌ 13:23 “የድኾች ዕርሻ የተትረፈረፈ ምርት ያስገኛል፤ የፍትሕ መጓደል ግን ጠራርጎ ይወስደዋል” ይላል። ጥቂት የነበረው ነገር ተግቶ በመሥራትና በአምላክ በረከት ብዙ ይሆናል። ይሁን እንጂ የፍትሕ መጓደል የሀብት ጸር ሊሆን ይችላል።
‘በጥንቃቄ ቅጣ’
ፍጽምና የሚጎድላቸው ሰዎች ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ ከልጅነት አንስቶ መሰጠት አለበት። የእስራኤል ንጉሥ “በአርጩሜ ከመቅጣት የሚሳሳለት ልጁን ይጠላል፤ የሚወደው ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል” ብሏል።—ምሳሌ 13:24
አርጩሜ ወይም በትር ሥልጣንን ይወክላል። ምሳሌ 13:24 ላይ ወላጆች ያላቸውን ሥልጣን ለማመልከት ተሠርቶበታል። በዚህ አገባቡ የተግሣጽ በትር መጠቀም ሲባል የግድ ልጅን መምታት ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም የቅጣት ዓይነት ያመለክታል። አንዳንድ ጊዜ አንድን ልጅ በደግነት መውቀስ መጥፎ አመሉን እንዲያርም በቂ ሊሆን ይችላል። ሌላ ልጅ ደግሞ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ያስፈልገው ይሆናል። ምሳሌ 17:10 “መቶ ግርፋት ተላላን ከሚሰማው ይልቅ፣ ተግሣጽ ለአስተዋይ ጠልቆ ይሰማል” ይላል።
ወላጆች ምንጊዜም ቢሆን ተግሣጽ መስጠት ያለባቸው ልጁን ለመጥቀም ሲሉ በፍቅርና በጥበብ መሆን አለበት። አፍቃሪ የሆነ ወላጅ ልጁ የሚሠራቸውን ጥፋቶች አይቶ እንዳላየ አያልፍም። ከዚህ ይልቅ የልጁ ጠባይ ይባስ ከመበላሸቱ በፊት መጥፎ አመሎቹን ለማስወገድ ሆን ብሎ ይከታተለዋል። እርግጥ አንድ አፍቃሪ ወላጅ “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” የሚለውን የጳውሎስን ምክር ይከተላል።—ኤፌሶን 6:4
አንድ ወላጅ ልጁን መረን የሚለቅና አስፈላጊውን እርማት የማይሰጥ ቢሆንስ? እንዳሻው እንዲሆን ስለተወው ልጁ ካደገ በኋላ ወላጁን ያመሰግነዋል? በፍጹም! (ምሳሌ 29:21) መጽሐፍ ቅዱስ “መረን የተለቀቀ ልጅ . . . እናቱን ያሳፍራል” ይላል። (ምሳሌ 29:15) አንድ ወላጅ ልጁን ቀጥቶ የማያሳድግ ከሆነ ግድ የለሽ እንደሆነ ወይም ልጁን እንደማይወድ ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወላጅ ኃላፊነቱን በደግነትና በጥብቅ መወጣቱ ለልጁ እንደሚያስብ ያሳያል።
በትክክለኛ እውቀት ላይ ተመሥርቶ ሕይወቱን የሚመራ አስተዋይና ጻድቅ ሰው ይባረካል። ሰሎሞን “ጻድቅ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤ የክፉዎች ሆድ ግን እንደ ተራበ ይኖራል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ምሳሌ 13:25) በቤተሰብ ሕይወታችን፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት፣ በአገልግሎት ወይም ተግሣጽ ሲሰጠን በሌላ አባባል በማንኛውም የሕይወት ዘርፍ ይሖዋ የሚበጀንን ያውቃል። እንዲሁም በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ካደረግን በጣም አርኪ ሕይወት እንደምናገኝ የተረጋገጠ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በምሳሌ 13:1-14 ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ለማግኘት የመስከረም 15, 2003 መጠበቂያ ግንብ እትም ገጽ 21-5ን ተመልከት።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስተዋይ የሆነ ሰው አግባብ ያልሆነ ነቀፋ ሲሰነዘርበት ምላሱን ይገታል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታማኝ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ብዙ መልካም ነገሮች ያከናውናል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መመስገን የሚያበረታታ ቢሆንም እርማት ሲሰጠን በደስታ መቀበል አለብን
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ አፍቃሪ ወላጅ ልጁ ሲያጠፋ እያየ ዝም አይልም