ጽድቅ አንድን ሕዝብ ከፍ ከፍ ያደርጋል
ለበርካታ ቀናት ዝናብ ሲዘንብ ሰንብቶ አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፍ ስትነሣ በጠራ ሰማይ ላይ ፀሐይ ፍንትው ብላ ብትመለከት ምን ያህል እንደምትደሰት እስቲ ገምተው! አሁን መሬቱ በቂ ዝናብ ስላገኘ ሣር ቅጠሉ ሁሉ ይለመልማል። በአንድ ወቅት ይሖዋ አምላክ የጽድቅ አገዛዝ የሚያስገኛቸውን በረከቶች ለመግለጽ እንዲህ ዓይነት መግለጫ ተጠቅሞ ነበር። ለንጉሥ ዳዊት እንዲህ ብሎት ነበር፦ “በሰው ላይ በጽድቅ የሚሠለጥን፣ በእግዚአብሔርም ፍርሃት የሚነግሥ፣ እርሱ እንደ ማለዳ ብርሃን ፀሐይ አወጣጥ፣ በጠዋትም ያለ ደመና እንደሚደምቅ፣ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል።”—2 ሳሙኤል 23:3, 4
የዳዊት ልጅ በሆነው በንጉሥ ሰሎሞን የጽድቅ አገዛዝ ዘመን አምላክ የተናገራቸው ቃላት እውነት ሆነው ተገኝተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር” ሲል ይዘግባል።—1 ነገሥት 4:25
የጥንት እስራኤላውያን አምላክ የመረጣቸው ሕዝቦች ነበሩ። አምላክ ሕጎቹን ከሰጣቸው በኋላ ትእዛዛቱን ካከበሩ “በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ” እንደሚያደርጋቸው ገለጸላቸው። (ዘዳግም 28:1) እስራኤላውያንን ከፍ ከፍ ያደረጋቸው የራሳቸው ጽድቅ ሳይሆን የይሖዋ ጽድቅ ነበር። አምላክ ለእነሱ የሰጣቸው ትእዛዛት በዙሪያቸው ከነበሩት አሕዛብ ሕግጋት በጣም የላቁ ነበሩ። እስራኤላውያን እንደነዚህ አሕዛብ ሰዎች ስለሆኑ ፍጽምና አልነበራቸውም። ስለዚህ ከአሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ብለው የነበሩት የላቀ ደረጃ ባለው በይሖዋ ሕግና ይህን ሕግ በጥብቅ በመከተላቸው ምክንያት ነው። የይሖዋን ሕግ ይታዘዙ በነበረበት ወቅት የእሱን ሞገስና በረከት አግኝተዋል። ንጉሥ ሰሎሞን በግዛት ዘመኑ ይህን ሁኔታ ተመልክቷል። “ጽድቅ ሕዝብን ከፍ ከፍ ታደርጋለች” ሊል ችሏል። በተጨማሪም “ኃጢአት ግን ሕዝብን ታስነውራለች” በማለት አስጠንቅቋል።—ምሳሌ 14:34
እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት ሳይታዘዙ በመቅረታቸው የነበራቸው ከፍ ያለ አቋም ዝቅ ማለቱ ያሳዝናል። በብሔር ደረጃ ውርደት ደርሶባቸዋል። ይህም አምላክ ከጊዜ በኋላ ለአንድ አዲስ መንፈሳዊ ብሔር ሞገስ እንዲያሳይና እነሱን ለዘለቄታው እንዲተዋቸው አድርጎታል።—ማቴዎስ 21:43
መንፈሳዊ እስራኤል
በትውልዱ አይሁዳዊ የነበረው ያዕቆብ የክርስቲያኑ አስተዳደር አካል በኢየሩሳሌም ባደረገው ስብሰባ ላይ አምላክ “ለስሙ የሚሆን ሕዝብ ከእነሱ መካከል ለመምረጥ ወደ አሕዛብ ትኩረት እንዳደረገ” በመንፈስ አነሣሽነት ተናግሮ ነበር። (ሥራ 15:14 አዓት) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አዲስ ክርስቲያን ብሔር “የአምላክ እስራኤል” ሲል ጠርቶታል። (ገላትያ 6:16) ጴጥሮስ እነዚህ ሰዎች የተጠሩበትን ዓላማ አስመልክቶ ሲናገር “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 2:9) የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች እንደ መሆናቸው መጠን በዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪዎች መሆን ነበረባቸው። የይሖዋ ጽድቅ ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።—ፊልጵስዩስ 2:15
የእነዚህ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ምርጫ አልማዝ ከማውጣት ጋር ሊነጻጸር ይችላል። ብዙ የአልማዝ ክምችት ያለበት አፈር ሲጣራ ከ3 ቶን አፈር ውስጥ 1 ካራት (200 ሚሊ ግራም) አልማዝ ብቻ ሊገኝ ይችላል። በአንድ ወቅት አልማዝን ለመለየት ይሠራበት የነበረው ዘዴ አልማዝ ያለበትን አፈር ከውኃ ጋር ከቀላቀሉ በኋላ ቅልቅሉን ግራሶ በተቀባ ጠረጴዛ ላይ ማፍሰስን የሚጨምር ነበር። አልማዝ ከውኃ ጋር ስለማይዋሃድና በግራሶው ላይ ተጣብቆ ስለሚቀር የማያስፈልገው ነገር በውኃው ታጥቦ ይወሰዳል። በዚህ ደረጃ ላይ አልማዝ የማይማርክ ነው። ይሁን እንጂ ቅርጽ ሲወጣለትና ሲወለወል በሁሉም አቅጣጫዎች ብርሃን ያንጸባርቃል።
ከውኃ ጋር የማይዋሃደው አልማዝ በዙሪያው ያለው ነገር ክፍል እንዳልሆነ ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦችም ከዓለም የተለዩ ናቸው። (ዮሐንስ 17:16) ለመጀመሪያ ጊዜ ለብርሃን ሲጋለጡ እምብዛም ብርሃን ላያንጸባርቁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ቃልና መንፈስ አዲስ ስብዕና ከፈጠረላቸው በኋላ በዚህ ዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪዎች ይሆናሉ። ከአሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያሉትና በሁሉም አቅጣጫዎች የመንግሥቱን እውነት ክብራማ ብርሃን የሚያንጸባርቁት በራሳቸው ጽድቅ ሳይሆን በይሖዋ ጽድቅ ነው።
ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ገደማ ክህደት ወደ ጉባኤዎች ውስጥ ሰርጎ ገባና በብዙዎች ላይ ተጽዕኖ አሳደረባቸው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ከዓለም ብሔራት ጋር ስለ ተቀላቀሉ በዙሪያቸው ካለው ዓለም ተለይተው ሊታወቁ አልቻሉም።
በአሁኑ ጊዜ የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ታማኝ ቀሪዎች የይሖዋን ሞገስ መልሰው አግኝተዋል። ራሳቸውን ከዓለም ከመለየታቸውም በተጨማሪ ‘ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ’ ራሳቸውን አንጽተዋል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) በይሖዋ ፊት ንጹሖችና ቅኖች ስለሆኑ የይሖዋን ጽድቅ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። ይህም ከዓለም ብሔራት ሁሉ የላቀ ከፍተኛ ሞገስ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት በመስበካቸው ምክንያት ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ ተስበው የሕዝቦቹ ክፍል ሆነዋል።—ራእይ 7:9, 10
ዓለም ልዩነቱን ሊመለከት ይችላል
አንዳንድ ጊዜ ዓለማዊ ባለ ሥልጣናት የአምላክ አገልጋዮችን ጠባይ ያደንቃሉ። ከጥቂት ጊዜ በፊት የደቡብ አፍሪካ ርዕሰ ከተማ በሆነችው በፕሪቶሪያ የሚገኙ የትርኢት ማሳያ ስፍራዎች የጥበቃ ዋና ኃላፊ ለዓመታዊ ስብሰባዎቻቸው በእነዚህ ስፍራዎች ስለተጠቀሙት ከተለያዩ ዘሮች ስለተውጣጡት የይሖዋ ምሥክሮች አስተያየት ሰንዝረው ነበር። የጥበቃው ዋና ኃላፊው ከጻፏቸው ነገሮች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፦ “እያንዳንዱ ሰው ትሕትና ያሳያል፤ እርስ በርሳቸው በደንብ ይግባባሉ። በተጨማሪም ሁሉም እንደ አንድ ደስተኛ ቤተሰብ ሆነው ይኖራሉ። ባለፉት ጥቂት ቀናት የታየው ጠባይ ሁሉ የማኅበራችሁ አባላት ያላቸውን ግሩም የሆነ ሥነ ምግባር የሚያስመሠክር ነው።”
የይሖዋ ሕዝቦች እንደነዚህ ባሉ ትላልቅ ስብሰባዎች ብቻ ሳይሆን በግል ሕይወታቸውም ጭምር ለአምላክ ሕዝብ ጽድቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በጆሃንስበርግ ከምትኖር አንዲት ሴት የሚከተለውን ሐሳብ የያዘ ደብዳቤ ደርሶት ነበር፦ “ባለፈው ሳምንት ቦርሳዬን በመኪናዬ አናት ላይ እንዳስቀመጥኩት ረስቼው መንዳት ጀመርኩ። ቦርሳው በያን ስመትስ ጎዳና ላይ ወደቀና በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች እንደያዘ ሚስተር አር— የተባለ አንድ የጉባኤያችሁ አባል አገኘው። ከዚያም ስልክ ደውሎ ጠራኝና ሰጠኝ። . . . በአሁኑ ጊዜ በጣም ብርቅ እየሆነ ለመጣው ለዚህ የሐቀኝነት ባሕርይ ከፍተኛ አድናቆት አለኝ። በተጨማሪም አባላቶቻችሁ በጥብቅ የሚከተሏቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ስላወጣ ጉባኤያችሁን አመሰግናለሁ።”
አዎን፣ ሕዝቦቹ የይሖዋን የጽድቅ ትእዛዛት አጥብቀው በመከተላቸው ከዓለም ተለይተው በግልጽ ይታያሉ። ይህ የይሖዋን ጽድቅ ስለሚያሳይ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ይሳባሉ። ሰዎች በተፈጥሯቸው ንጹሕና ያልተበከለ ነገር ይማርካቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት አንድ ሰው በስዊዘርላንድ ዙሪክ ወደሚደረግ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ከመጣ በኋላ የጉባኤው አባል ለመሆን እንደሚፈልግ ተናገረ። እህቱ በመጥፎ ሥነ ምግባር ምክንያት እንደ ተወገደች ከጠቀሰ በኋላ “መጥፎ ጠባይን በቸልታ የማይመለከት” ድርጅት አባል ለመሆን እንደሚፈልግ ገለጸ። ሌላው ቀርቶ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንኳ “የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ውስጥ ከሚገኙ በጣም ጥሩ ሥነ ምግባር ካላቸው ቡድኖች መካከል እንደሆኑ” አምኗል።
ጽድቅ ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ኃጢአት በተለይ ደግሞ አንድ ከባድ ኃጢአት በኅብረተሰቡ ዘንድ ከታወቀ የአንድን ሰው መልካም ስም ሊያጎድፍ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ግለሰቦች ከባድ ኃጢአት ሲሠሩ የክርስቲያን ጉባኤ ነቀፋ ይደርስበታል። የጉባኤው ታማኝ አባላት ኃጢአት የሠራው ግለሰብ ከቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ በምሕረት ተግሣጽ እየተቀበለ መሆኑን በመጠቆም የጉባኤውን መልካም ስም ለመከላከል በቂ ምክንያት አላቸው። አንድ ሰው ኃጢአት መሥራቱን ከቀጠለና ንስሐ ካልገባ ጉባኤው ያገለዋል ማለትም ይወገዳል።—1 ቆሮንቶስ 5:9–13
አንዳንዶች የሚወገዱበት ምክንያት
ምንም እንኳ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ከክርስቲያን ጉባኤ ቢወገዱም እነዚህ ሰዎች በመላው ዓለም ከሚገኙት ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ውስጥ በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሚገኝ ግለሰብ ላይ እንዲህ ዓይነቱ ጥብቅ እርምጃ የሚወሰደው ለምንድን ነው? የኃጢአቱ ሁኔታ ወሳኝነት አለው። ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ ግምት ውስጥ የሚገባው ነገር ኃጢአተኛው ከሠራው ከባድ ኃጢአት ከልቡ ንስሐ የገባ መሆኑ ወይም አለመሆኑ ነው። ከልቡ ከተጸጸተ፣ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ለሠራው ኃጢአት ይቅርታ ከለመነና በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ያላቸውን ሰዎች እርዳታ ከጠየቀ የአምላክን ሞገስ እንደገና ለማግኘትና የጉባኤው አባል ሆኖ ለመቀጠል የሚያስፈልገውን እርዳታ ሊያገኝ ይችላል።—ምሳሌ 28:13፤ ያዕቆብ 5:14, 15
ከአባቱ ጋር ጥሩና ጤናማ የሆነ ቅርርብ የነበረው ልጅ አባቱን የሚያሳዝን አንድ ነገር ሲያደርግ ወዲያውኑ ያንን ውድ ቅርርብ ለመመለስ ሁለቱም ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይም ሕይወታችንን ለይሖዋ ስንወስን ከእሱ ጋር ከሁሉ የበለጠ ውድ ዝምድና መሥርተናል። ስለሆነም አንድ እሱን የሚያሳዝን ነገር ስንሠራ ከሰማያዊ አባታችን ጋር የነበረንን ቅርርብ መልሰን ለማግኘት ወዲያውኑ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
ተወግደው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የአባካኙን ልጅ ምሳሌ ልብ ማለታቸው ያስደስታል። እዚህ ምሳሌ ላይ ይሖዋ አንድ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ከድርጊቱ ከተመለሰና አምላክ ይቅርታ እንዲያደርግለት ከጠየቀ እጁን ዘርግቶ ለመቀበል ዝግጁ በሆነ አፍቃሪ አባት ተመስሏል። (ሉቃስ 15:11–24) እውነተኛና ልባዊ የሆነ ንስሐ መግባት እንዲሁም ከመጥፎ ድርጊት መመለስ የይሖዋን ሞገስ መልሶ ለማግኘትና ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ለመመለስ የሚያስችል መንገድ ሆኖ ተገኝቷል። የጥፋተኛነት ስሜት ሸክም የሆነባቸው አንዳንድ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች ኃጢአታቸውን ለመናዘዝና ፍቅር ወደ ሰፈነበት ጉባኤ ለመመለስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተገፋፍተዋል። በዚህ መንገድ ይሖዋ በኢሳይያስ 57:15 ላይ የተናገራቸውን ቃላት ተገንዝበዋል።
ሰይጣን ግለሰቦች የይሖዋን ፍቅራዊ እንክብካቤ መልሰው እንዳያገኙ ስለሚፈልግ ሰዎች ለፈጸሟቸው ኃጢአቶች ምንም ይቅርታ እንደማያገኙ ለማሳመን ይፈልጋል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የማንኛውንም ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ሌላው ቀርቶ ‘የዓለምን ሁሉ’ የተወረሰ ኃጢአት ለመሸፈን በቂ ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ቤዛው የማይሸፍነው ኃጢአት ቢኖር በአምላክ መንፈስ አሠራር ላይ ሆን ብሎ እንደ ማመፅ የሚቆጠረው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ላይ የሚሠራ ኃጢአት ነው፤ የአስቆሮቱ ይሁዳና አያሌ ጻፎችና ፈሪሳውያን እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ኃጢአት ሠርተዋል።—ማቴዎስ 12:24, 31, 32፤ 23:13, 33፤ ዮሐንስ 17:12
የይሖዋን ጽድቅ ማስከበር
የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎች በ1919 የይሖዋን ሞገስ መልሰው ስላገኙ ከቀን ወደ ቀን በዙሪያቸው ካለው ዓለም በአቋማቸው ከፍ ከፍ እያሉ ሄደዋል። ይህ የሆነው በእነሱ ጥሩነት ምክንያት ሳይሆን ለይሖዋ ሕግጋትና የአቋም ደረጃዎች ራሳቸውን ለማስገዛት ፈቃደኛ በመሆናቸው ነው። በዚህም ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ታማኝ ጓደኞች በመሆን ከእነሱ ጋር ተባብረዋል። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ሰዎች ከአምላክ የጽድቅ ደረጃዎች በጣም በራቀው ዓለም ውስጥ ለይሖዋ ክብርና ምስጋና ያስገኛሉ። ይህ በአንድ ወቅት ፐርሰናሊቲ የተባለ አንድ የደቡብ አፍሪካ መጽሔት “የይሖዋ ምሥክሮች በመልካም ባሕርያት የተሞሉና በአብዛኛው ሲታይ ከመጥፎ ባሕርያት ነፃ የሆኑ ይመስላሉ” እንዳለው ነው።
ለአምላክ አክብሮት በጎደለው ዓለም ውስጥ ይህን ከፍ ያለ የአቋም ደረጃ ይዞ ለመቆየት እያንዳንዱ የክርስቲያን ጉባኤ አባል በይሖዋ ፊት ንጹሕና እንከን የሌለበት አኗኗር እንዲኖረው ያስፈልጋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት በንጹሕ ነገሮች ተመስላለች። ይህች ድርጅት ፀሐይን የተጎናጸፈችና ጨረቃ ከእግሮቿ በታች ያላት አንዲት ውብ ሴት ሆና ታይታለች። (ራእይ 12:1) አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ቅድስት እንደ ሆነችና ማራኪ ውበት እንዳላት ተገልጿል። (ራእይ 21:2) የክርስቶስ ሙሽራ ታማኝ አባላት “የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ቀጭን ልብስ” ተሰጥቷቸዋል። (ራእይ 19:8 የ1980 ትርጉም) እጅግ ብዙ ሰዎች ‘ነጭ ልብስ ለብሰው’ ታይተዋል። (ራእይ 7:9) የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ንጹሕ ድርጅት ይስባቸዋል። ከዚህ በተቃራኒ የሰይጣን ድርጅት ርኩስ ነው። እሱ ያቋቋመው ሃይማኖታዊ ሥርዓት በአንዲት ጋለሞታ የተመሰለ ሲሆን ከቅድስቲቱ ከተማ ውጪ ያሉት እንደቆሸሹና እንደረከሱ ተገልጿል፣—ራእይ 17:1፤ 22:15
ጻድቃን የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል። የይሖዋን ጽድቅ ከፍ ከፍ ያደረጉት በጉባኤ የታቀፉት ሰዎች ከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት የመትረፍ ተስፋ አላቸው። አምላክ በምሳሌ 1:33 ላይ “የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፣ ከመከራም ስጋት ያርፋል” የሚል ተስፋ ሰጥቷል።
ታላቁ ሰሎሞን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲሱ ዓለም ላይ በጽድቅና ይሖዋን በመፍራት የሚገዛበት ወቅት ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ ጊዜ ደመና እንደሌለበት የጠዋት ፀሐይ ጮራ ይሆናል። መላው የምድር ነዋሪ በሰላምና በጸጥታ ይኖራል። እያንዳንዱ ሰው ከምሳሌያዊ የወይንና የበለስ ዛፍ ሥር ይቀመጣል። ጻድቅ የሆነ ሰብዓዊ ማኅበረሰብ ምድርን ያስውባታል። ከዚያ በኋላ ምድር በጽንፈ ዓለም ውስጥ ትክክለኛ ቦታዋን በመያዝ ለአምላካችን ለይሖዋ ዘላለማዊ ውዳሴ የምታመጣ ትሆናለች።—ሚክያስ 4:3, 4፤ በተጨማሪም ኢሳይያስ 65:17–19, 25ን ተመልከት።
[ምንጭ]
Garo Nalbandian