‘እርማትን የሚቀበል አስተዋይነቱን ያሳያል’
“ልብህን ለምክር፣ [“ለተግሣጽ፣” የ1954 ትርጉም] ጆሮህንም ለዕውቀት ቃል ስጥ” በማለት ምሳሌ 23:12 ይናገራል። “ተግሣጽ” ወይም ሥነ ምግባራዊ ሥልጠና በዚህ አገባቡ ራስን በራስ መገሠጽንና ሌሎች የሚሰጡንን ተግሣጽ መቀበልን ያመለክታል። ምን ዓይነት ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልግና እንዴት መሰጠት እንዳለበት ለመወሰን፣ ተግሣጽ በእውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት እሙን ነው። በዚህም ምክንያት ተግሣጽ ለመስጠት ታማኝ ከሆነ ምንጭ ለሚገኝ ‘የዕውቀት ቃል’ ጆሮን መስጠት አስፈላጊ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ ጥበብ ያዘሉ ግሩም ምክሮችን ይዟል። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት ምሳሌዎች “ጥበብንና ተግሣጽን ለመቀበል፤ . . . ጽድቅን፣ ፍትሕንና ሚዛናዊ ብያኔን በማድረግ፣ የተገራ ጠቢብ ልቦናን ለማግኘት” ይረዳሉ። (ምሳሌ 1:1-3) እኛም ጆሯችንን ወደ እነዚህ ምሳሌዎች በማዘንበል ጠቢብ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። ምሳሌ ምዕራፍ 15 ቁጣን መቆጣጠር ስለሚቻልበት መንገድ እንዲሁም በአንደበት አጠቃቀምና እውቀትን በማስተላለፍ ረገድ ተጨባጭ መመሪያ ይሰጣል። እስቲ ከዚህ ምዕራፍ ላይ የተወሰኑ ቁጥሮችን እንመልከት።
‘ቍጣን ለማብረድ’ የሚረዳው ምንድን ነው?
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን የምንናገራቸው ቃላት ቁጣን ሊያስነሱ እንደሚችሉ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል።” (ምሳሌ 15:1) “ቍጣ” የሚለው ቃል በአንድ ነገር አለመደሰትን በስሜትም ሆነ በድርጊት ማሳየትን ለመግለጽ የሚያገለግል ነው። ታዲያ አንድ ሰው ተቆጥቶ ሲናገረንም ሆነ እኛ ራሳችን ስንቆጣ ነገሮችን እንዴት መያዝ እንዳለብን ከላይ ያሉት ቃላት የሚጠቁሙን እንዴት ነው?
በዚህ ወቅት ስሜትን የሚጎዱና ሸካራ የሆኑ ቃላት መጠቀም ሁኔታውን ይበልጥ ያባብሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የለዘበ መልስ መስጠት አብዛኛውን ጊዜ ነገሮችን ያረጋጋል። እርግጥ ነው፣ ለተቆጣ ሰው የለዘበ መልስ መስጠት ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ያስቆጣውን ነገር ማስተዋል ከቻልን እንዲህ ያለ መልስ ለመስጠት አያዳግተንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ [“አስተዋይነት፣” የ1980 ትርጉም] ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤ በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 19:11) ምናልባት ግለሰቡ የተቆጣው በራሱ ስለማይተማመን ወይም የሌሎችን ትኩረት ለማግኘት ፈልጎ ይሆን? እንዲቆጣ ያደረገው ትክክለኛ ምክንያት እኛ ያደረግነው ወይም የተናገርነው ነገር ላይሆን ይችላል። በክርስቲያናዊው አገልግሎት ላይ ስንሆን የምናነጋግረው ግለሰብ አብዛኛውን ጊዜ የሚቆጣው ስለ እምነታችን የተሳሳተ ወሬ በመስማቱ ወይም ጭፍን ጥላቻ ስላለው አይደለም? ታዲያ በእኛ ላይ የግል ጥላቻ እንዳለው አድርገን በማሰብ ሸካራ መልስ መስጠት ይኖርብናል? አንድን ሰው እንዲቆጣ ያደረገው ነገር በቀላሉ የማይታወቅ ቢሆንም እንኳ ሰውን ሊጎዱ የሚችሉ ቃላትን ተጠቅመን መልስ መስጠታችን ራሳችንን መገሠጽ አለመቻላችንን ያሳያል። እንዲህ ያለ ምላሽ ላለመስጠት መጠንቀቅ ይኖርብናል።
የለዘበ መልስ ስለ መስጠት የተሰጠው ምክር ቁጣችንን እንድንቆጣጠር በመርዳት ረገድም ጠቃሚ ነው። የተሰማንን ስሜት አድማጭን በማያስከፋ መንገድ መግለጽን በመማር ይህንን ምክር ልንሠራበት እንችላለን። ከቤተሰባችን አባላት ጋር ባለን ግንኙነትም እነሱን ከማመናጨቅ ወይም ከማንቋሸሽ ይልቅ ስሜታችንን ረጋ ባለ መንፈስ ለመግለጽ መጣር ይኖርብናል። ኃይለ ቃል መናገር በአብዛኛው አጸፋ ወደ መመለስ ሊያመራ ይችላል። ስሜትን በተረጋጋ መንፈስ መግለጽ እርስ በርስ መካሰስን ከማስቀረቱም በላይ ግለሰቡን ይቅርታ እንዲጠይቅ ሊያነሳሳው ይችላል።
‘የጠቢብ አንደበት ታወድሳለች’
ራስን መገሠጽ በምንናገርበት መንገድ ብቻ ሳይሆን በምንናገረው ነገር ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል። ሰሎሞን “የጠቢብ አንደበት ዕውቀትን ታወድሳለች፤ የተላሎች አንደበት ግን ቂልነትን ያፈልቃል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 15:2) ሌሎችን የመርዳት ፍላጎት ስናዳብር እንዲሁም ስለ አምላክ ዓላማና እርሱ ስላደረገው ልዩ ዝግጅት ስንናገር ‘ዕውቀትን ማወደሳችን’ አይደለም? ተላላ የሆነ ሰው ግን እውቀት ስለሌለው ይህን ማድረግ አይችልም።
ሰሎሞን በአንደበት አጠቃቀም ረገድ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠቱ በፊት “የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ” በማለት ትኩረት የሚስብ ሐሳብ አስፍሯል። (ምሳሌ 15:3) “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” የሚል ቃል ስለተገባልን በዚህ አባባል መደሰት እንችላለን። (2 ዜና መዋዕል 16:9) አምላክ ሥራችን መልካም ይሁን አይሁን ለይቶ ያውቃል። መጥፎ እየሠሩ ያሉትንም ስለሚመለከታቸው ከተጠያቂነት አያመልጡም።
ሰሎሞን በመቀጠል ገራም አንደበት ያለውን ጥቅም ሲገልጽ “ፈውስ የምታመጣ ምላስ [“ጤናማ አነጋገር፣” የ1980 ትርጉም] የሕይወት ዛፍ ናት፤ አታላይ ምላስ ግን መንፈስን ትሰብራለች” ብሏል። (ምሳሌ 15:4) “የሕይወት ዛፍ” የሚለው አገላለጽ አንደበት የመፈወስ ወይም የማበርታት ባሕርይ እንዳለው ይጠቁማል። (ራእይ 22:2) የጠቢባን ጤናማ ንግግር የአድማጮቻቸው መልካም ባሕርያት ጎልተው እንዲታዩ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ መንፈሳቸውንም ያድሳል። በተቃራኒው አታላይ ወይም መጥፎ ምላስ ግን የአድማጩን መንፈስ ይሰብራል።
ተግሣጽን መቀበልና ‘እውቀትን መዝራት’
ንጉሥ ሰሎሞን “ተላላ የአባቱን ምክር ይንቃል” በማለት ከተናገረ በኋላ አክሎ “መታረምን የሚቀበል ግን አስተዋይነቱን ያሳያል” ብሏል። (ምሳሌ 15:5) አንድ ሰው ምክር ሳይሰጠው እንዴት ‘መታረምን ሊቀበል’ ይችላል? ይህ ጥቅስ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተግሣጽ መሰጠቱ ተገቢ እንደሆነ አያሳይም? በቤተሰብ ውስጥ ተግሣጽ መስጠት የወላጆች በተለይም የአባት ኃላፊነት ሲሆን ልጆች ደግሞ የመቀበል ግዴታ አለባቸው። (ኤፌሶን 6:1-3) ይሁን እንጂ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በሆነ መንገድ ተግሣጽ ይቀበላሉ። ዕብራውያን 12:6 እንዲህ ይላል:- “ጌታ የሚወደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል።” ተግሣጽ ሲሰጠን የምናሳየው ምላሽ ጠቢብ ወይም ተላላ እንደሆንን ያሳያል።
ሰሎሞን ንጽጽሩን በመቀጠል “የጠቢባን ከንፈር ዕውቀትን ታስፋፋለች [“ትዘራለች፣”የ1954 ትርጉም]፤ የተላሎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም” ብሏል። (ምሳሌ 15:7) እውቀትን ለሌሎች ማዳረስ ዘርን ከመዝራት ጋር ይመሳሰላል። አንድ ገበሬ በሚዘራበት ወቅት አንድ ቦታ ላይ ብቻ ዘሩን ደፍቶት ከመሄድ ይልቅ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ዘሩን በመበተን መላውን ማሳ እንደሚያዳርስ ሁሉ እውቀትም ለሌሎች በዚሁ መንገድ መተላለፍ አለበት። ለምሳሌ፣ በአገልግሎት ላይ አንድ ሰው ስናገኝ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምናውቀውን ሁሉ በአንድ ጊዜ መንገር የጥበብ እርምጃ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ጠቢብ የሆነ ሰው ንግግሩን ይቆጣጠራል። ይህ ግለሰብ እውቀትን ‘በሚዘራበት’ ወቅት በአንድ ጊዜ ለመወያየት የሚያነሳው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብቻ ሲሆን ያንን እያጠናከረ ይሄዳል። በዚህ መንገድ አድማጩ የሚሰጠውን ምላሽ እየተመለከተ ቀስ በቀስ እውቀትን ይዘራል። ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ሲነጋገር ያደረገው ይህንኑ ነበር።—ዮሐንስ 4:7-26
እውቀትን ለሌሎች ማካፈል ትምህርት የሚሰጡና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን መናገርን ያካትታል። እውቀት የሚጨምር ሐሳብ ለማካፈልና ለማበረታታት ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከዚህም የተነሳ “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል።” (ምሳሌ 15:28) እንግዲያው ንግግራችን መሬቱን በደንብ አጥግቦ ፍሬ እንዲሰጥ እንደሚያደርግ ለስለስ ያለ ዝናብ እንጂ ያገኘውን ሁሉ ጠራርጎ እንደሚወስድ ጎርፍ መሆን የለበትም!
‘በኑሮአችን ሁሉ ቅዱሳን መሆን’
ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው እውቀትን በመዝራት ‘የከንፈራችንን ፍሬ የምስጋና መሥዋዕት’ አድርገን ስናቀርብ የጥበብ እርምጃ መውሰዳችን ነው። (ዕብራውያን 13:15) ይሁን እንጂ ይህ መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ‘በኑሮአችን ሁሉ ቅዱሳን መሆን’ ይጠበቅብናል። (1 ጴጥሮስ 1:14-16) ሰሎሞን ሁለት ተነጻጻሪ ምሳሌዎችን በመጠቀም የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ያጎላልናል። እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እግዚአብሔር የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል፤ የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል። እግዚአብሔር የክፉዎችን መንገድ ይጸየፋል፤ ጽድቅን የሚከታተሉትን ግን ይወዳቸዋል።”—ምሳሌ 15:8, 9
የሕይወትን መንገድ ትተው የሚሄዱ ሰዎች ለተግሣጽ ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? መጨረሻቸውስ ምን ይሆናል? (ማቴዎስ 7:13, 14) “ከመንገድ የሚወጣ ሰው ጥብቅ ቅጣት ይጠብቀዋል፤ ዕርምትን የሚጠላ ይሞታል።” (ምሳሌ 15:10) አንዳንድ ክፉ አድራጊዎች፣ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ግለሰቦች የሚሰጧቸውን ምክር ከመቀበልና ከልባቸው ንስሐ ከመግባት ይልቅ የጽድቅን ጎዳና መተውን ይመርጣሉ። ይህ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!
አንድ ሰው ተግሣጽን በልቡ እየጠላ ነገር ግን እንደተቀበለው ቢያስመስልስ? ይህም ቢሆን ሞኝነት ነው። የእስራኤል ንጉሥ “ሲኦልና የሙታን ዓለም በእግዚአብሔር ፊት የተገለጡ ናቸው፤ የሰዎች ልብማ የቱን ያህል የታወቀ ነው!” ብሏል። (ምሳሌ 15:11) በምሳሌያዊ አባባል፣ ሙታን ከሚገኙበት ሥፍራ ማለትም ከሲኦል የባሰ ሕያው ከሆነው አምላክ የራቀ ቦታ የለም። ይሁን እንጂ ይህም ቦታ ቢሆን በፊቱ የተገለጠ ነው። አምላክ በሲኦል ያሉትን ሙታን ማንነትና ሁለንተናዊ ባሕርያቸውን በሙሉ ጠንቅቆ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ በትንሣኤ ሊያስነሳቸው ይችላል። (መዝሙር 139:8፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ታዲያ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን ማወቅ ለይሖዋ ምን ያህል ቀላል ይሆን! “ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፏል። (ዕብራውያን 4:13) ያልሆኑትን ሆኖ በመታየት ሰዎችን እንጂ አምላክን ማሞኘት አይቻልም።
ተግሣጽን ለመቀበል ፈቃደኛ የማይሆን ሰው ተግሣጹን ብቻ ሳይሆን ሰጪውንም ጭምር ይጠላዋል። “ፌዘኛ ሰው የሚዘልፈውን አይወድድም” በማለት ሰሎሞን ተናግሯል። ይህንን ሐሳብ ይበልጥ ለማጠናከር “ወደ ጠቢባንም አይሄድም” ብሏል። (ምሳሌ 15:12 የ1954 ትርጉም) እንዲህ ያለው ሰው መንገዱን ለማስተካከል ብዙም ተስፋ የለውም!
አዎንታዊ አመለካከት
ከዚህ ቀጥሎ ባሉት በሦስቱም ምሳሌዎች ላይ ሰሎሞን “ልብ” የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። ጠቢቡ ንጉሥ ውስጣዊ ስሜታችን በፊታችን ላይ እንዴት እንደሚነበብ ሲናገር “ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፤ የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል” ብሏል።—ምሳሌ 15:13
ለልብ ሐዘን ምክንያት የሚሆነው ምንድን ነው? “ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 12:25) አሉታዊ የሆኑ የሕይወት ገጽታዎች መንፈሳችንን እንዳይሰብሩት ምን ማድርግ ይኖርብናል? ልንለውጣቸው የማንችላቸውን ሁኔታዎች በማሰብ ከመብሰልሰል ይልቅ ይሖዋ አሁን በሰጠን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከትና ወደፊት በምናገኘው ነገር ላይ ማተኮር ይገባናል። ይህም ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ይረዳናል። እውነት ነው፣ ‘ደስተኛ ወደ ሆነው አምላክ’ መቅረብ በሐዘን ለተሰበረው ልባችን ደስታ ይሰጠዋል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW
ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው መልእክት ከፍተኛ የመጽናኛና የደስታ ምንጭ ነው። መዝሙራዊው ደስተኛ ስለሆነ ሰው ሲናገር “ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 1:1, 2) ምንም እንኳ ልባችን ቢያዝንም መጽሐፍ ቅዱስን ካነበብንና ባነበብነው ነገር ላይ ካሰላሰልን እንበረታታለን። በተጨማሪም አምላክ የሰጠን አገልግሎት አለን። “በእንባ የሚዘሩ፣ በእልልታ ያጭዳሉ” የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።—መዝሙር 126:5
ሰሎሞን በመቀጠል “አስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይሻል፤ የተላላ አፍ ግን ቂልነትን ያመነዥካል” ብሏል። (ምሳሌ 15:14) ይህ ምሳሌ ጠቢብና ተላላ ሰው በሚሰጡት ምክር መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። አስተዋይ ልብ ያለው ሰው ምክር ከመስጠቱ በፊት እውቀትን ይሻል። በደንብ ካዳመጠ በኋላም ስለ ጉዳዩ በቂ መረጃ ለማግኘት ይጥራል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሕግጋትንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማወቅ ቅዱሳን ጽሑፎችን ይመረምራል። ምክሩም ቢሆን ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው በአምላክ ቃል ላይ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ግን ተላላ ሰው ትክክለኛውን ገጽታ ለማግኘት ከመጣር ይልቅ አፉ ላይ የመጣለትን ዝም ብሎ ይናገራል። ስለዚህ ምክር ስንፈልግ አዋቂና በሳል ወደሆኑ ወንድሞች እንጂ እኛ መስማት የፈለግነውን ነገር ወደሚነግሩን ሰዎች መሄድ አይኖርብንም። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምክር ከመስጠታቸው በፊት ‘ዕውቀትን የሚሹ’ ‘ስጦታ የሆኑ’ ወንዶች በመኖራቸው እንዴት ታድለናል!—ኤፌሶን 4:8
ቀጥሎ ያለው ምሳሌ ደግሞ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ያለውን ጠቀሜታ የሚያጎላ ነው። የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ይላል:- “የተጨቈኑ ሰዎች ዘመናቸው ሁሉ የከፋ ነው፤ በደስታ የተሞላ ልብ ግን የማይቋረጥ ፈንጠዝያ አለው።” (ምሳሌ 15:15) ሕይወት ደስታና ሐዘን፣ ሳቅና ለቅሶ የሞላባት ናት። አሉታዊ የሆኑ ጎኖችን ብቻ እያሰብን የምንኖር ከሆነ ሐዘን አስተሳሰባችንን የሚቆጣጠረው ከመሆኑም በላይ ሕይወታችንን ጨለማ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ አሁን ባገኘናቸው በረከቶችና አምላክ በሰጠን ተስፋ ላይ የምናሰላስል ከሆነ አስጨናቂ የሆኑት የሕይወት ገጽታዎች ጎልተው አይታዩንም፤ ውስጣዊ ደስታም ይኖረናል። አዎንታዊ አመለካከት ልባችን “የማይቋረጥ ፈንጠዝያ” እንዲኖረው ያደርጋል።
እንግዲያው ተግሣጽን ከፍ አድርገን እንመልከተው። በስሜታችን ወይም በንግግራችን አሊያም በድርጊታችን ብቻ ሳይሆን በአመለካከታችን ላይም ተጽዕኖ እንዲያሳድር እንፍቀድ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል”
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተግሣጽ መስጠት የወላጆች ኃላፊነት ነው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የጠቢባን ከንፈር ዕውቀትን ትዘራለች”